ቤታቸውን እየከፈቱ ሰው ሌባ ይላሉ
የስዊድን ጋዜጠኞችና…
ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም
የስዊድን ጋዜጠኞች በቃሊቲ መታሰራቸው ያሳዝናል፤ የሚያሳዝነው ራሳችንን በማጋለጣችን እንጂ ስዊድኖቹ ይጎዳሉ በማለት ብቻ አይደለም፤ በአጠቃላይ በሁለት ‹‹ጥፋቶች›› እርግጠኛ መሆን የሚቻል ይመስለኛል፤ አንደኛ፣ ያለፈቃድ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ተገኝተዋል፤ የትም አገር ቢሆን ወንጀል ነው፤ ፋርስ ወይም ኢራን በተደጋጋሚ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞታል፤ ሁለተኛው በእኔ ግምት ጥፋታቸው የሚሆነው የምዕራባውያን አጠቃላይ ‹‹የነፃነት ትግል›› የተባለውን ሁሉ በተቻላቸው መጠን ለመርዳት ያላቸው እምነት ነው፤ ለዚህ እምነታቸው ብዙ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፤ እንዲያው በደፈናው ትግልን ከመደገፍ ጀምሮ እስከ ሃይማኖት ድረስ የነፃነት ታጋዮች ነን- ባዮችን የሚረዱበት ምክንያት ያገኛሉ።
እነዚህን ሁለት ጥፋቶች ምዕራባውያን ጋዜጠኞችና የትምህርት ተመራማሪዎች፣ ሰላዮችም በየትም የሶስተኛ ዓለም አገር ለዘመናት ሲጠቀሙባቸው ቆይተዋል፤ በኢትዮጵያም ቢሆን ሻቢያንና ወያኔን በተለያዩ መንገዶች ይረዷቸው እንደነበረ የታወቀ ነው፤ የኢትዮጵያን ድንበር እየዘለቁም ከዓማጽያኑ ጋር ይገናኙና ይረዱም ነበረ፤ ዛሬ ስዊድኖቹ የተያዙት በሰሜን እንደለመዱት በደቡብም የሶማሌ ነፃ አውጪ ድርጅትንና ሌሎችንም ለመርዳት ሲሞክሩ ይመስለኛል፤ የስዊድን ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ውስጥ በስልጣን ላይ ያሉት ከነፃ አውጪነት ወደገዢነት መዛወራቸው አልገባቸውም፤ እነዚህ ስዊድኖች ሽብርተኞች አይመስሉኝም፤ አገራቸውም ጦርነትን ከተወ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ ይመስለኛል፤ ስለዚህም ጦርነትን ቢያንስ ለራሳቸው የሚወዱ ሰዎች አይደሉም።
አፈናና ጭቆና በአለበት አንዳንዴም እየተጋበዙ፣ አንዳንዴም ሳይጋበዙ በውስጥ ጉዳይ ይገባሉ፤ እርዳታ ለመስጠት ብቁ ናችሁ የተባሉ ሰዎች ምክር ለመስጠት ሲሆን ብቁ የማይሆኑበት ምክንያት አይታያቸውም፤ ለደሀነታችን ምጽዋት ሲሰጡን ለደሀነታችን መሰረት የሆነው የነጻነት ማጣት እንደሆነ ያውቃሉ፤ በዚህ በኩል ለመርዳት ሲፈልጉ የማይፈቀድላቸው ሲሆን ለአገራችን ከአላቸው ክብር ለነፃነት ያላቸው ክብር ይበልጥባቸውና አጥር ጥሰው በጓዳችን ይመጡብናል፤ ስዊድኖች ብቻ ሳይሆኑ ምዕራባውያን አገሮች ሁሉ በዚህ ዘዴአቸው ሲጠቀሙ ዘመናት ተቆጥረዋል፤ ስለዚህም አሁን የስዊድን ጋዜጠኞች ያደረጉት አዲስ አይደለም፤ በዚህ የአውሮፓውያን ዘዴ አሁን በስልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ቡድን ያለፈውን አገዛዝ ለመጣል ተጠቅሞበታል፤ ለምዕራባውያን አገሮች የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ የሚያሰማው ጩኸትና ሮሮ በደርግ ዘመን ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ሲሆንባቸው በተመሳሳይ ዘዴ ለመጠቀም መሞከራቸው ያስደንቅም፤ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ኢትዮጵያን ሄራልድ የሚባለው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ በስዊድን መንግሥት ላይ የከረረ ርእሰ አንቀጽ እንደጻፈ ትዝ ይለኛል።
የስዊድን ህዝብ ለኢትዮጵያ ያሳየውን ርኅራኄና ያደረገውን እርዳታ ልናስታውስ ይገባል፤ ለማኝ መሆን አሳፋሪ ውርደት ነው፤ ውለታ-ቢስ ለማኝ መሆን ደሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆነናል፤ ስዊድኖች የኢትዮጵያን የዓየር ኃይል አቋቁመውልናል፤ የሚያኮራ ድርጅት ነበር፤ የኢትዮጵያ ቴሌ ኮሚዩኒኬሽንንም ያቋቋሙት ስዊድኖች ናቸው፤ ይህም የሚያኮራ ድርጅት ነበር፤ በዚያ ላይ ሰፊ የትምህርት ቤት ሕንፃዎችን የመሥራት እቅድ ነበራቸው፤ ከዚህ ጋር አያይዘውም የሕንጻ ኮሌጅን አቋቋሙ፤ በተጨማሪም በአርሲ ያደረጉትን የእርሻ ሥራ ማሻሻል እንደትልቅ ውለታ ናስታውሰው ይገባል፤ እነዚህን ትላልቅ የስዊድን ሕዝብ ውለታዎች የማነሣው የአገር ድንበርን የመጣስ ወን ልን ለማካካሥ አይደለም፤ እውነተኛው ጳውሎስ ‹‹ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው፤›› ያለውን ለማስታወስና በመንፈስ ልዕልና እንድናየው ነው፤ ስዊድኖቹን አስሮ በማቆየት የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ባለሥልጣኖቹ የሚያገኙት ጥቅም የለም፤ ትርፉ ገመናን ማሳየት ነው።
በእኛም በኩል ትክክለኛ ሚዛን ይዘን ስንመለከተው ምዕራባውያኑ አገሮች የሚያደርጉት ነገር ምን ያህል እንደሚንቁን ያሳያል፤ እነሱ ይንቁናል፤ እነሱ አጥራችንን ይነቀንቃሉ፤ እነሱ ያኮረፈውን ሁሉ እየደጎሙ ያቆራቁሱናል፤ እያልን ከመቆጣታችን በፊት ነገሩን ዘወር አድርገን ስንት መቶ ኢትዮጵያውያን የስዊድንን፣ የኖርዌይን፣ የኢጣልያንን፣ ርመንን…አጥር እየጣሱ ገብተዋል ብለን ራሳችንን ብንጠይቅና ምክንያቱንም ብንረዳው፣ የስዊድኖቹ የኢትዮጵያን አጥር መጣስ ኢምንት ያደርገዋል፤ ብዙ በስዊድን ያሉ ኢትዮጵያውያን ኩሩ ባለአገር ሆነዋል።
ሕግን በርኅራኄ ከአራሱት በግልጽ አጥፍተዋል የተባሉትን ስዊድኖች ብቻ ሳይሆን ከኢሜይልና ከስልክ ባላለፈ ከማይተዋወቋቸው ሰዎች ጋር በነበራቸው የቃላት ንኪኪት ብቻ እንደ ርዕዮት በቃሊቲ የሚገኙት ጋዜጠኞች (የነሱ ሽብርተኛነት ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነውና) ባለስልጣኖቹ ከጉልበት ይልቅ የመንፈስ ልዕልና ቢያሳዩ ያስከብራቸው ነበር።
ከፍትህ ጋዜጣ (አዲስ አበባ)



