ከቧንቧና ከምንጭ የሚገኘው ውሃ ወደ ቦቴ መኪና እደላ ተሸጋገረ

ዋካ ከስዊድን

መግቢያ 

ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ የዳውሮ ዋካ ህዝብ የተለያዩ የልማት ጥያቄዎችን ለመንግሥት ማቅረቡ ይታወቃል። ጥያቄውን ተከትሎ ገዢው የህወሃት መንግስት ፍትሃዊ ምላሽ ለህዝቡ ለመስጠት ባለመፈለጉና ባለመቻሉ የተነሳ በአካባቢው ከፍተኛ አለመረጋጋት ተከስቶ እንደነበርና መንግሥትም ዴሞክራሲያዊ የነበረውን የህዝብ ጥያቄ ተቀብሎ ኃላፊነት ባለው መልኩ አጥንቶና መርምሮ ውሳኔ መስጠት ሲጠበቅበት በርካታ ህዝብ በማሰርና በማንገላታት ብሎም በማስፈራራት ህዝባዊ እንቅስቃሴውን በጉልበት ለመግታት ሞክሯል።

 

የህዝቡ ጥያቄ የነበረው የተለያዩ የልማት አውታሮች እንዲዘረጉለት፤ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲገነባለት፤ ያለምንም የህዝብ ተሳትፎ በጥቂት ባለስልጣኖች ፍላጎትና ውሳኔ የተነጠቀው የወረዳ ማዕከሉ ቀደም ሲል ወደነበረበት ዋካ ከተማ እንዲመለስለት፤ ሙስናና አድሏዊ አሰራር እንዲቆም፤ ሙሰኞች ብቃት ያለው የማጣራት ሥራ ተሰርቶ ለህግ እንዲቀርቡ... ወዘተ የሚል ነበር።

 

በወቅቱ የዳውሮ ዋካ ህዝብ አንስቶት ከነበረው የልማት ጥያቄ መካከል አንዱ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ነበር። የዳውሮ ዞን ማዕከል በሆነችው የተርጫ ከተማ የመጠጥ ውሃ ጠፍቶ ህዝቡ በውሃ ጥም እየተሰቃየ ይገኛል። በሌሎችም የዳውሮ ወረዳ ማዕከሎች የውሃ ችግሩ ተስፋፍቷል። በተፈጥሮ በምንጭና በጉድጓድ ውሃ ሃብታም የነበረችው ዳውሮ ዛሬ እንደ ምግብ ራሺን ከሳልኒ የግልገል ግቤ ቁጥር 3 ፕሮጀክት በተገኘ የውሰት ቦቴ መኪና ውሃ ለህዝቧ እየታደለ ይገኛል። ችግሩ እየከፋበት መጥቷል።

 

በተርጫ ከተማ ለዚህ የውሃ ችግር መፍትሄ ለማግኘት ያስችል የነበረው አዲስ የጉድጓግ ውሃ ቁፋሮ፤ የቧንቧ መስመር መዘርጊያና የማስፋፊያ ሥራ ሲጠናቀቅ ውጤቱ ዜሮ ሆነ የሚል እሮሮ ተነስቷል።በሌሎችም የዳውሮ ወረዳ ማዕከሎችና አንዳንድ ቀበሌዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ከምንጭ የማጎልበቻ ግንባታ ሥራው ሲጠናቀቅ ውሃ የለውም። ቧንቧው ውሃ አያፈስም። ወድያ ቢጠመዘዝ ወዲህ ጠብታ የለም። ነገሩ እንዲህ ነው።

 

ለዞኑ የውሃ ግንባታ ከክልል የተላከው ገንዘብ በጥቅሉ ወደ 20 ሚልዮን ብር ገደማ ነው። የተላከው ገንዘብ ሥራ ተሰርቶበታል! ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለህዝቡ መንግሥት አቀረበለት! ተብሎ በካድሬዎቹ ከበሮ ተደልቆና  የግንባታው ገንዘብ ሂሳብ ተወራርዶ ጨዋታው አልቋል። ውሃ ግን የለም። ህዝቡ እያለቀሰ ነው። አንዳንድ ሚዲያዎችም ዘግበዉት ነበር።

 

ህዝቡ ግራ ተጋብቷል። ይህ የውሃ ቧንቧ እመሬት ውስጥ የተቀበረው ውሃ እንደ ደቡብ ሱዳኑ የነዳጅ ምርት ሥር ለሥር ወደ ጎረቤት አገር ነው ውሃ እየመጠጠ የሚወስደው ወይስ ሚስጥሩ ምንድነው? እያለ ግራ ገብቶት ሰንብቷል። የውሃ ጥማቱም እያሰቃየው ይገኛል። የንጽህናውን ጉዳይ አትርሱት።

ባለስልጣናቱ የወረዳ ማዕከልነት ከነፈጓትና ህዝቡን ካሰቃዩባት እንዲሁም የንጹህ ምንጭ ውሃ ባለሃብት ከሆነችው የዋካ ከተማ በመንግስት መኪና ውሃ ያስግዛሉ ይጠጣሉ። ሌላው ነዋሪ እንዳያየው ተብሎ በተለይ ማታ ማታ ውሃ ይጋዛል። ከዋካ ወደ ተርጫ መሆኑ ነው። ተራው የመንግሥት ሰራተኛ፤ ደሃ የከተማው ነዋሪና አርሶአደር በውሃ ጥም እየተሰቃየ ይገኛል። የንጽህናውን አጠባበቅ ጉዳይ ሳንዘነጋው ይሁን።

 

ከዚህ በታች የማቀርበው ዝርዝር መረጃ ከውሃ ሥራ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው የወረዳ የዞንና የክልሉ የውሃ ቢሮ መ/ቤቶች እንዲሁም በየደረጃው ከሥራው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው ባለሙያዎችና ከአካባቢው ነዋሪዎች ያገኘሁትና እውነተኛ ነው። የመረጃዬን ምንጮች መጥቀሱና ማንሳቱ  ለደህንነታቸው ጎጂ ሊሆን እንዳይችል አላነሳሁትም። የህዝብን በደል ለማጋለጥና ወንጀልን ላለመተባበር ላደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋናዬ ይድረሳቸው። በትዕግስት አንብቡት።

 

ዝርዝር ጉዳይ 

የጉድጓድ ውሃ ግንባታ ለማከናወን ከፍተኛ ጥንቃቄና ዝግጅት የሚያስፈልገው ነገር መሆኑ ይታወቃል። ገንዘብ ብቻውን የግንባታውን ሥራ እውን ሊያደርገው አይችልም። ብቃት ያለውና ለህዝቡ ታማኝ የሆነ ባለሙያ ያስፈልጋል። ከከርሰ ምድር ጥናት ጀምሮ አጠቃላይ የግንባታውን ሥራ ከወረቀት ላይ ንድፈ ሃሳብነት ወደ ተግባር ለውጦ እመሬት ላይ እውን ማድረግ ብቃት ያለውን ባለሙያ ይጠይቃል፡።

 

የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ፤ የውሃ መስመር መዘርጋት፤ ምንጭ የማጎልበት ሥራ የእውቀት የሙያና በቂ የሥራ ልምድ የሚያስፈልገው የተለያዩ ባለሙያዎች የጋራ ሥራ ነው። ለፖለቲካው ታማኝ የሆነ ካድሬ እየተመለመለ በአፉ የሚሰራው ሥራ አልነበረም።  

 

የውሃ ልማት ግንባታ ሥራ ጋዜጣ ከማደልና ህዝብን ሰብስቦ ውሸት ከማውራት ጋር አይዛመድም። እንዲሁም አንድ ከበላይ አካል የተነገረውን ፍሬ የሌለው ነገር እንደ ዘፈን አዝማች አንድም ነገር ሳይጨምር ወይም ሳይቀንስበት ያችውኑ የተነገረችውን ነገር ከመደጋገም ይለያያል።  

 

ወደ ፍሬ ነገሩ ልውሰዳችሁ። በዳውሮ ዞን በተርጫ ከተማ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ግንባታ እንዲከናወን ይወሰናል። የውሃ ጉድጓዱን ለመቆፈር ተመርጦ የነበረው ቦታ መልካዓ ምድሩ በቂ ጥናት ተደርጎበት በቂ ውሃ በከርሰ ምድሩ ውስጥ እንደሚገኝ በከርሰ ምድር ባለሙያዎች ጥናቱ አበቃና የሥራ ዝርዝሩ ወጥቶ ጨረታ ተካሄደ። በዚሁ መሠረት የዳውሮ ዞን ውሃ መምሪያ ጨረታውን ላሸነፈው የሥራ ተቋራጭ የከርሰ ምድር ጥናቱ የታካሄደበትን ትክክለኛ ሥፍራ በማሳየትና በማስረከብ የግንባታውን ሥራ እንዲያስጀምር ኃላፊነት ተሰጠው።

 

ከዚህም በተጨማሪ የዳውሮ ዞን የውሃ ልማት መምሪያ የሥራ ድርሻ የነበረው ከፍተኛ ባለሙያዎቹን በመመደብ የግንባታ ሥራውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፤ የባለሙያ እጥረት ካለ ከክልል ውሃ ቢሮ ተጨማሪ ከፍተኛ ባለሙያዎችን በመጠየቅ በአግባቡ መቆጣጠር፤ በባለሙያዎች እየተረጋገጠ ሲቀርብ በተገባው ውል መሠረት የየዙሩን የሥራ ክፍያ ማድረግ፤ ሥራው ሲጠናቀቅ ከባለሙያ ሪፖርት በኋላ አስፈላጊውን ርክብክብ በመፈጸም ህብረተሰቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ነበር።

 

የተርጫ ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ግንባታ ሥራ ብቻ ሳይሆን በዳውሮ ዞን ውስጥ ባሉት ወረዳዎች  ውስጥም በተደረጉ የመጠጥ ውሃ ግንባታና የምንጭ ማጎልበት ሥራዎች የዞኑ የውሃ ልማት መምሪያ የሥልጣን ደረጃው የሚመለከተውን ሥራ ሁሉ በራሱ ደረጃ ጨረታውን አከነውኖ የሥራ ውል በመግባት በብቃት ግንባታውን በመቆጣጠር አስፈጽሞ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ማስቻል ነው። ይህን የምላችሁ በመመሪያ ላይ የተቀመጠው ነገር ነው።

 

እስቲ የተከናወነውን እንመልከት።ለተርጫ ከተማ ነዋሪዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለማቅረብ በደቡብ ክልል ውሃ ቢሮ ተወሰነና እንቅስቃሴው ይጀመራል። ግልጽ ጨረታ ይወጣና አሸናፊው ተቋራጭ ውል ይፈፀምና ወደ ግንባታው ሥራው ተገባ። ይህ የጨረታ ሥራ የተከናወነው በክልል ውሃ ቢሮ በኩል ነው። ከክልል ውሃ ቢሮ 15 ሚልዮን ብር ለውሃ ግንባታው ሥራ ማስፈጸሚያ ይመደብና ወደ ዳውሮ ዞን የውሃ መምሪያ ገንዘቡ ተላከ።

 

የዞኑ የውሃ መምሪያ የሥራ ድርሻ በውሃው ልማት ግንባታ ላይ ምን መሆን እንዳለበት ገልጫለሁ። ነገር ግን የዞኑ የውሃ ልማት መምሪያ የሥራ ድርሻውን ወደ ጎን በመተው ያከናወነውን ሥራ ደግሞ እንመልከት።

 

በከፍተኛ ባለሙያዎቹ ግንባታው ሊከናወን የሚገባውን ቦታ በመምረጥና በመለየት የከርሰ ምድር ጥናት ሥራ ቀደም ሲል ተከናውኖ አብቅቷል። በተመረጠው ቦታ በጣም በርካታ የውሃ መጠን በከርሰ ምድሩ ውስጥ መኖሩን ባለሙያዎች አረጋግጠዋል። በጥናቱ መሠረት ቦታው ተለይቶ ከታወቀ በኋላ የቁፋሮና የግንባታው ሥራ እንዲከናወን ነበር በጀቱ ወደ ዞኑ የተላለፈው።

 

ነገር ግን የዳውሮ ዞን የውሃ ሃብት ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ግንበቶ በራሱ ፈቃድ ያለአንዳች በቂ ምክንያት ከኮንትራክተሩ ጋር በመወያየት ብቻ ቀደም ሲል ጥናቱ ከተካሄደበት ሥፍራ አንስቶ ግንባታውን እሱና ኮንትራክተሩ ወደተስማሙበት ወዳልተጠና አዲስ ቦታ አዛወረው። እንግዲህ ትልቁ ስህተት እዚህ ላይ ነው። ሌሎች ችግሮችም እንደዚሁ በጀብደኝነት ተከታትለው ተፈፀሙ።  

 

የዳውሮ ዞን የውሃ ልማት ከፍተኛ ኤክስፐርቶች በጉዳዩ ላይ የሰጡት አስተያየት ተቀባይነት አጣ። ባለሙያው የግንባታ ቦታው ለውጥ በፍጹም ተገቢ እንዳይደለ አስረድቷል። ለውጥ እንኳን ቢያስፈልግ የሚዛወርበት የግንባታ ሥፍራ በከርሰ ምድሩ ውስጥ በቂ የውሃ መጠን ስለመኖሩ በባለሙያዎች እንደገና በሚገባ ሊጠና እንደሚገባ ሊያስረዳ ሞከረ። በአጠፌታው አቶ ደሳለኝ ግንበቶ በራሱ ግምገማ ተርጫን ሊያጥለቀልቅ የሚችል ውሃ በከርሰ ምድሩ ውስጥ መኖሩን በተደጋጋሚ በንግግር አረጋገጠ። የከርሰ ምድርን ውሃ እንዴት አጮልቀህ አየኸው? ያለው አንድም አካል የለም። ኧረ እንዳያጥለቀልቀን እባክህ!! ያሉትም አይጠፉም። እንዴት ቀለደ!!  በአገርና በህዝብ ላይ መቀለድ!!

 

ይህንን አሰራር የተከራከሩትን ከፍተኛ ባለሙያዎች በማስፈራራትና በማሸማቀቅ ፀጥ ማሰኘት ቻለ። እናንተ ባለሙያዎች የሆናችሁ ነፍጠኞች ፀረ ዳውሮ ልማቶች ...ወዘተ ናችሁ እረፉ! ዋ! በሚል የስድብ እሩምታ ባለሙያዎችን አፋቸውን ዘጋ። አከታትሎም አ አ አ ብሎ ተወ አልጨረሰውም። አሸባሪዎች ቢላቸው ጉድ ነበር። አሸባሪዎችን አውቃቸዋለሁ እያለ ሰውን ሁሉ ያስፈራራል አሉ።

 

የሚገርመው ነገር  አሁን የሆነው አስቀድሞ ባለሙያዎቹ የተናገሩት ነው። ከግንባታው ሥራ በፊት ሊሰራ የሚገባው የቦታ መረጣ ጥናት ሥራ እጅግ አስፈላጊ ነበር። ሲሆን ሲሆን ጥናት የተደረገበትንና ውሃ እንዳለበት በባለሙያ የተረጋገጠው ሥፍራ ሊለወጥ አይገባም። የግንባታ ሥፍራ ሲለወጥ ሊዛወር የተፈለገው ሥፍራ በቂ ውሃ ያለው መሆኑ ጥናት ተከናውኖ አስቀድሞ ሊረጋገጥ ይገባ ነበር።

 

ግን አልተደረገም። አቶ ደሳለኝ ግንበቶ ሲቆፈር የሚወጣው ውሃ ተርጫ ከተማን ያጥለቀልቃል ብሎ ፎክሮ ያዛወረው የግንባታ ሥራ እንኋኳንና ተርጫን ሊያጥለቀልቅ አንድ ባልዲ የሚሞላ ውሃ ሊያመነጭ አቃተው።

 

የሚገርመው ነገር ባለሙያዎችን በማግለል ያላግባብ እንዲካሄድ የተደረገው የውሃ ግንባታ ሥራ እንዲጠናቀቅ የተመደበው 15 ሚልዮን ብር ነበር። ምንም ውሃ ማመንጨት ያልቻለው ግንባታ የተፈቀደለት ገንዘብ አንሰ ተብሎ ሌላ 2 ሚልዮን ብር ከጨረታው ዋጋ በላይ ለሥራው የወጣ /ቫሪዬሽን ኮስት/ አለ ተብሎ ቀርቦ አቶ ደሳለኝ ለኮንትራክተሩ መፍቀዱና መክፈሉ ነው። ይገርማል!! ውሃ ለሌለው ባዶ ግንባታ አነሰ ተብሎ ሁለት ሚልዮን ብር ተመረቀለት።

 

ማስተዋል ያለብን ነገር አለ። መንግሥት ይህንን ገንዘብ የመደበው ወይም ለህዝቡ የላከው በአግባቡ የውሃ ልማት ግንባታ ተካሂዶ ህብረተሰቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ ለማስቻል ነበር። ህብረተሰቡ ከውሃ ወለድ በሽታዎች እንዲጠበቅ ለማድረግ ነበር። የተላከው ገንዘብ እንዲሁ ሜዳ ላይ ፈሰሰ። ከፊሉም ገንዘብ የግለሰቦች ሲሳይ ሆነ። ኮንትራክተሩ ግንባታውን ማካሄድ እንጂ ውሃ ከጉድጓድ ወጣ አልወጣ ብዙም ላያስጠይቀው ይችል ይሆናል። አላውቅም። ግን ህዝቡስ አያሳዝንም?

 

ሆዳም አመራር ከራሱ ሆድ ውጪ ለሌላው ወገኑ የሚያስብ አእምሮ የለውም። አይኑም አያይም። 

አንዳንድ ጥያቄዎችን ላንሳና ወደ ሌላው የውሃ ግንባታ ሥራ ልውሰዳችሁ። አቶ ደሳለኝ ግንበቶ ውሃ ማመንጨት ላላስቻለው ግንባታ ባለሙያ ሳያየው ለምንድነው ተጨማሪ የቫሪዬሽን ዋጋ ብር 2 ሚልዮን  እንዲከፈል የወሰነው? የግንባታ ቦታውን ወደ ሌላ ወዳልተጠናበት ሥፍራ ለማዛወር በግሉ የወሰነበት ምክንያት ምንድነው? የባለሙያዎችን አስተያየትና ጥያቄ አልቀበልም ያለበት ምክንያት ምንድነው? ሌሎች የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ምነው ዝም አሉ? ወይስ ሁሉም ድርሻ ድርሻቸውን አግኝተው ነው? ክልል ላይ ያለው ዋናው ሿሚው የዳውሮ ተወካይ ነኝ ባይ አመራርስ ምነው ዝም አለ? ይህንን ሙስና አልሰማም ይሆን? አይመስለኝም።

 

አንድን ምንም የገንዘብ አቅምና ሌላ የገቢ ምንጭ ያልነበረውን የመንግሥት ሠራተኛ ህዝብን አስዘርፈውና አብረውት ዘርፈው ባለሃብት አድርገውት ሲያበቁ ከሥልጣን አነሳነው ማለት ማንን ለማሞኘት ነው? ባይናገርም ህዝብ ያውቃል፤ ጊዜውን ጠብቆ አንድ ቀን እውነቱን ፊት ለፊት መናገሩ አይቀርም።

 

ሁለተኛውን የውሃ ልማት ሥራ ግንባታ እንመልከት። በተርጫ ከተማ የእግር ኳስ ስታዲየም አካባቢ የውሃ ግንባታ ሥራ እንዲከናወን ይወሰንና በጀት ይመደባል። የውሃው ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ጥናት ሊደረግ ሆነ። ባለሙያዎች ዝግጅት አጠናቀው የከርሰ ምድር ጥናት ለደረግ እንቅስቃሴ ይጀምራሉ። ወዲያው የመምሪያው ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ግንበቶ ባለሙያዎችን ጠርተው ምንም የከርሰ ምድር ውሃ ጥናት እንዳማያስፈልግና የቁፋሮው ሥራ እንዲጀመር ከኮንትራክተር ጋር ውል የተገባ መሆኑን ለባለሙያዎቹ ይነግራሉ።

 

ባለሙያዎቹ ጥናት ሳይደረግ ግንባታ እንዲካሄድ መወሰኑ ተገቢ አለመሆኑን በመግልጽ የግንባታው ሥራ በቂ ውሃ መኖሩ ሳይረጋገጥ በዘፈቀደ ተገንብቶ ወደፊት ውሃ ላያመነጭ እንደሚችል ያስረዳሉ። ነገር ግን ሰሚ አላገኙም። ባለሙያዎቹ የሰጡት ሙያዊ አስተያየት ተቀባይ አላገኘም። ይባስ ተብሎ ባለሙያዎቹ የልማት ሥራ ታደናቅፋላችሁ ተብለው የዞኑ ከፍተኛ ካድሬዎች ቢሮ ተጠርተው ዝም እንዲሉና አርፈው እንዲቀመጡ ማስጠንቀቂያ ብጤ ተሰጣቸው። ዝም እንዲሉ ተገደዱ።

 

በተለይ የከርሰ ምድር ጥናት ከፍተኛ ባለሙያው አሰራሩ በፍጹም ትክክል ያለመሆኑንና ወደፊት ከግንባታው በኋላ በቂ ውሃ ላይገኝ እንደሚችል እዚያው እተጠሩበት ቢሮ ለካድሬዎቹ ፍርጥም አድርገው ተናገሩ። የባለሙያው አስተያየት ጠቃሚ ነው አላሉም ካድሬዎቹ። የከርሰ ምድሩ ባለሙያ “ነፍጠኛ ተብዬው” እንደተነበዩት ቁፋሮውና ግንባታው ሲጠናቀቅ ውሃ የማያመነጭ ሆነ። እጅግ ያሳዝናል። ታዲያ ከፍተኛ ካድሬዎቹ ዛሬስ ምን ይሉ ይሆን? ባለሙያዎቹ ግን የህሊና ነፃነት አላቸው።

 

እዚያው ተርጫ የአንድ ሌላ ግንባታ ጉዳይ ላንሳና ላብቃ። ይህ የግንባታ ሥራ ደግሞ በጣም የሚገርም ነገር አለው። የግንባታ ሥራው መጠሪያ በተርጫ እንዱስትሪያል ኮሌጅ የውሃ ማስፋፊያ ሥራ ነበር። ሥራው በኮሌጁ ውስጥ በተለያዩ የመማሪያና የሥራ ማከናወኛ ብሎኮች የውሃ መስመሮችን መዘርጋትና የማስፋፊያ ሥራ ለማከናወን የተወጠነ ነበር።

 

አንድ ነገር አስተውሉ። በየዓመቱ ሰኔ ወር የበጀት መዝጊያ ወቅት ነው። ከዚህ ሥራ ጅማሮ በፊት በነበረው ሰኔ ወር ከዘመኑ ተመላሽ በጀት ተገኘ ተብሎ በርካታ የውሃ ቱቦዎችና ሌሎች የግንባታ ማቴሪያሎች ተገዝተው እዚያው እንደስትሪያል ኮሌጅ ውስጥ እንዲቀመጡ ተደርጎ ነበር። የተገዙት ዕቃዎች የተቀመጡት በሚስጢር አይሁን እንጂ ለምን ሥራ እንደሚውሉ ግን በጣም ሚስጢር ነበር።

 

ለውሃ ግንባታ ሥራው ከግማሽ ሚልዮን ብር በላይ ይመደብና ወደ ሥራው እንዲገባ የመምሪያ ኃላፊ ይወስናል። የማስፋፊያው ሥራ ጨረታ በውስን ጨረታ እንዲከናወን አደረገ። ዝግ ጨረታ እንዲሆን ያደረገበት ምክንያት አለው እንመጣበታለን። ጨረታውን የሰጠው ቀደም ሲል የከተማውን የጉድጓድ ውሃ ለገነባው የሥራ ተቋራጭ ድርጅት ይሰጣል። “ተሰጠ አሉ”።

 

ለሥራው በሙሉ አዲስ የሥራ ዝርዝር እንዲወጣ ተደርጎ ምንም የባለሙያ አስተያየት ሳያስፈልግ ውል ይደረግና ወደ ሥራው ይገባል። የሥራ ውል የገባውና ያለጨረታ በግብዣ ወደ መስመር ሥራው ግንባታ የገባው የሥራ ድርጅት ውል የገባው ለፎርማሊቲ እንጂ ውል የሰጠውም ሆነ ውል ተቀባዩ አቶ ደሳለኝ ግንበቶ ሆነና ተገኘ። ሥራውን በውስን ጨረታ አቶ ደሳለኝ የሰጠው ሥራውን ራሱ ሊሰራው ተወያይቶና ከሥራ ድርጅቱ ጋር በሚስጢር አስቀድሞ ጨርሶ ኑሯል።

 

ኮንትራክተሩ ነጋዴ መሆኑን አትርሱ። ትርፍ የሚያገኝበትን ሁኔታ በማንኛውንም መንገድ መሞከሩ አይቀርም። ሊገርመን አይገባም። መንግሥት ህዝብን አገልግል ብሎ ያስቀመጠው ኃላፊ ተቆጣጥሮ ሊያሰራው ያልፈለገውንና ያልቻለውን ነጋዴውን ምን አድርግ ነው የምትሉት?  

 

ከላይ የገለጽኩላችሁ በበጀት መዝጊያ ወቅት በመንግስት በጀት የተገዙት የውሃ ቱቦዎች በሚስጥር ተገዝተው በኮሌጁ ውስጥ  የተቀመጡበት ምክንያትና ጨረታውን ያለውድድር ለሥራ ተቋራጭ የሰጠ ያስመሰለው ራሱ አቶ ደሳለኝ ግንበቶ ሥራውን በጅ አዙር ያለውድድር ወስዶ ሊሰራው በማቀዱ ነበር። በመንግስት በጀት ያስገዛውንም ቱቦ ወስዶ ወደ ራሱ ግንባታ ጥሬ ዕቃነት ለወጠው። ተጠቀመበት። ምን ይህን ያህል ልጁን እንዳስጨከነው ሳስበው ይገርመኛል።

 

በጣም ግሩም የሚባል ድራማ ነው የተከወነው። የድራማው ደራሲና ዋና አዘጋጅ አቶ ደሳለኝ ግንበቶ ሲሆን እንዲከውን የረዳው ደግሞ ኮንትራክተሩ ነው። በመንግሥት በጀት የተገዛውን የመስመር መዘርጊያ ቱቦም ቀደም ሲል ያዘጋጀው ለራሱ ስለነበር እሱንም ወስዶ ውሃ የማያስተላልፍ መስመር ዘረጋሁ ብሎ ስልጣኑን በመጠቀም ምዝበራውን ፈፀመ።

 

ለግንባታው የተመደበውን ራሱ አጫርቶ ራሱ ውስኖ ራሱ አሸንፎ በጠራራ ፀሃይ መንግሥት ባለበት አገር ብር አምስት መቶ ስልሳ ሽህ ብር ወደ ኪሱ ከተተው። ሥራውን እንኳን በተወሰነ ደረጃ ሰርቶ የተወሰነውን ከይቅርታ ጋር ብሎ እንኳን ቢሰርቅ እኔ አላዝንበትም ነበር ግን ምንም ሳይሰራ በጨበጣ የገዛ ወገኑን መዝረፉ ያሳዝናል።

 

 በውስን ጨረታ ስም አዙሮ ጨረታውን ራሱ ውል ሰጥቶ ግንባታውን ራሱ ወስኖ በእጅ አዙር ራሱ የሥራ ተቋራጩ ወኪል ሆኖ መውሰድ ይሏችኋል ይኼ ነው። ቱቦዎቹም የሥራ ዝርዝር ውስጥ ዋጋቸው ሳይካተት የምርጥ ማዳበሪያነትን ሚና ተጫወቱ። በህዝባችን የልማት ሥራ ላይ የተሰራው ደባ ይህን ይመስላል።

 

መደምደሚያ

ከላይ ያብራራሁትን ጉዳዮች የሚያስረዳ ዶኩመንት በእጄ አለ። ከዚህ ጽሁፍ ጋር አባሪ አድርጌ ለህዝብ ባቀርብ ደስተኛ ነበርኩ። ይህ መረጃ ከየት ወጣ? ማን አወጣው? እንዴት ወጣ? ይህን መረጃ ያስተላለፍክ አንተ ነህ በሚል ከመረጃው ጋር ግንኙነት ያላቸውም ሆነ የሌላቸው እውነተኛና ንጹሃን ወገኖቼን ለጉዳት ላለማጋለጥ ለጊዜው መረጃውን ለማቆየት ወሰንኩ።

 

የዳውሮ ዞን ባለስልጣኖችን አንድ ነገር ላሳስባችሁ። የማታውቁትንና ያልሰማችሁትን አዲስ ነገር እየነገርኳችሁ እንዳልሆነ አውቃለሁ። አንድ የመንግሥት ሰራተኛ የሚያገኘው የወር ደመወዙ ከወር ወደ ወር አላዳርስ ብሎት በሚሰቃይበት፤ የኑሮ ውድነት ከአገር የኤኮኖሚ የቁጥጥር አቅም በላይ በሄደበት አገር አንድ የመምሪያ ኃላፊ አዋሳ ብርሃን እንሹራንስ ውስጥ 250 000 /ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር/ ከራሱ የባንክ ሂሳብ አንድ ጊዜ በአንድ ባለሃብት ሥም የባንክ ሂሳብ አዟዙሮ የሚያስቀምጥበትን አቅም እንዴት ሊያገኝ ቻለ? ብር ከየት አመጣ? አሁን የተርጫ ህዝብ ተበደልኩ ግፍ ተፈፀመብኝ ቢልና መንግስትን ቢጠይቅ ነፍጠኛ ነው፤ አሸባሪ ነው፤ ግንቦት 7 ነው ልትሉት ነው?

 

አዋሳ አሊቶ ሰፈር መኖሪያ ቤት በአንድ ጊዜ ክፍያ በብር 350 000 /ሶስት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር/ ቦታና ቤት ሲገዛ እውነት አልሰማችሁም? ይህንኑ የገዛውን ቤት ሰሞኑን በአንድ ባለሃብት ሥም አዟዙሮ የማስቀመጡን እውነት አታውቁም? እኔ ግን ይህንን ድርጊት የሚያውቅና የተባበረው ሌባ ጓደኛ እመካከላችሁ እንዳለ አረጋግጥላችኋለሁ። እስቲ ብርሃን ኢንሹራንስን ጠይቁ!

 

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አሸባሪው ማነው? የተበደለው ህዝብ ነው ወይስ ህዝብን የሚረግጠውና የሚመዘብረው ተሿሚና ካድሬ? የተርጫም ሆነ የዋካ ህዝብ አሻባሪ አይደለም። አሸባሪው ካድሬውና ተሿሚው ነው። ህዝቡን የሚግጠውና የሚያስግጠው ሌባው አመራሩ ነው። ህዝብ አሸባሪ ሳይሆን ተሸባሪ ነው። ተሸብሯል ህዝብ። እውነቱ ይህ ነው።

 

መልዕክት

የተከበራችሁ የተርጫ ከተማ ነዋሪዎች!! በንጹህ የመጠጥ ውሃ ግንባታ ዙሪያ የተሰራው ዝርፊያና ደባ ይህን ይመስላል። እናንተ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንድታገኙ የተላከላችሁ የግንባታ በጀት የግለሰቦች መፈንጫ ሆኗል። እንደልባቸው እየተከፋፈሉ ግለሰቦች ቤት ይገነቡበታል። ቤት ይገዙበታል። ይጨፍሩበታል።

እናንተ ግን የመጠጥ ውሃ አጥታችሁ ትሰቃያላችሁ። በታሪክ ሰምተን በማናውቀው ሁኔታ በልመና በተገኘ የቦቴ መኪና ውሃ እየተጋዘ በከባድ ሰልፍና ወረፋ እንዲሁም ድካም አንድ የብርጭቆ ዉሃ ለማግኘት ተስኗችኋል። ቁልቁል ማደግ ይሏችኋል ይህ ነው።

 

የዞን መዲና፤ የማረቃ ወረዳ ማዕከል፤ የተርጫ ዋና አስተዳደር ጽ/ቤትና የተርጫ ማዘጋጃ ቤት ዋና ከተማ “ተርጫ” አራት የመንግሥት መዋቅር ያለባት ከተማ ነዋሪ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አጥቶ ሲሰቃይ ቁጭ ብለው የሚያዩት ካድሬዎች ህሊናቸው ምን ይላቸው ይሆን? ቀድሞስ ህሊና ሲኖራቸው አይደል!! ሆዱን እየሞላ በስልጣን ላይ አንድ ተጨማሪ ቀን የሚቆይበትን እንጂ ለህዝቤ ለወገኔ ምን ልስራ የሚል ወገንተኛና አሳቢ ጠፋ።

 

አመራሩ ብቃት ያለው ችሎታ ያለው ልምድና ትምህርት ያለው ግለሰብ ወደ ሥልጣን ወደ አመራር የማያቀርብ ነው። አንድ አመራር ሲመጣ የተሻለ ነገር ሊመጣ ይችል ይሆናል የሚል ተስፋ ሰንቆ ህዝብ ሲጠብቅ በራሱ አስቦ እውነትና በብዙኋኑ የሚደገፍ ነገርን ማድረግና መስራት ሲገባው በሃሳብ ሲወርድ ታዩታላችሁ። ያሳዝናል!! 

 

ሰሞኑን አንዱ ካድሬ ስብሰባ ብሎ ጠርቷችሁ አይዟችሁ አትቆጡ የተርጫ ከተማን የውሃ እጥረት ችግር ያመጣው አባይ ስላልተገደበ ነው። አባይ ሲገደብ ችግሩ ይቀረፋል ቢላችሁ አትዘኑ። የመጠጥ ውሃው እጥረት በሚቀጥለው አምስት አመት መሪ እቅዳችን ማግስት ይደመሰሳል ቢላችሁ ግራ ሊገባችሁ አይገባም። መፍትሄው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋዜጣን ማንበብ ነው ቢላችሁ እንዴት ብላችሁ አትጠይቁት።

 

አሸባሪዎችና ጋዜጠኞች የመጠጥ ውሃውን ግንባታ አደናቀፉት ቢሏችሁ አይግረማችሁ።ነፃ ህሊናውን እውቀቱንና ሙያውን ተጠቅሞ ለህዝቡ ያቅሙን ያህል ለመስራት የሚችል ባለሙያ የህዝብ ወገንተኛ ሰው በብቃትና በብዛት እያለ ሊሰራ የሚያስችለው ነባራዊ ሁኔታ ግን የለም። እውነቱ ይህ ነው። ከውሃ ዘርፍ ባለሙያዎች ተማሩ። መፍትሄው ምንድነው? ታዲያ ምን ይሻላል? የሚለውን እያንዳንዱ ዜጋ ለራሱ ሊያስብ ይገባዋል።

 

በአጭር ጊዜ የውሃ ግንባታውን በጀት በተለያዩ መንገዶች ጠልፎ ወደ ኪሱ ያስገባውን ግለሰብ በግምገማ በቀላል ሂስ ማለፍ ምን ይባላል። የተርጫ ከተማ ነዋሪ ህዝብ የዞኑ አስተዳዳሪን ቀርቦ ባቀረበው ከባድ ወቀሳ በኋላ መወገዱን ሰማሁ። እውነት አሁን መረጃ አጥተው ነው፤ አይመስለኝም፡

 

ወገኖቼ ተርጫ ከተማ የሚኖረው አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ ነው። ባላሥልጣኖችን መተቸትና መናገር ቀርቶ ቀና ብሎ ለማየት ነፃነት እንደሌለው ጠንቅቄ አውቃለሁ። ነፃ የሆነ የግል ሃሳብ ማቅረብ አስቸጋሪ ነው። ከፍተኛ ማስፈራሪያ ይደርስበታል። ከሥራ ይታገዳል ይባረራል ይዛወራል የደረጃ ዕድገት ይከለከላል ብዙ ችግር ይከተለዋል።

 

ነጋዴውና ሌላውም ነዋሪው ህዝብ የተለያየ የበቀል እርምጃ ሊወሰድበት ይችላል። ለዚሁ በቅርቡ ዋካ ከተማ መወለዳቸው ወይም እዚያ መኖራቸውና መስራታቸው እንደወንጀል ተቆጥሮባቸው ከዋካ ከተማ ተነስተው ወደ ተርጫ የተዛወሩ የመንግስት ሰራተኞችን ማየት በቂ ማስረጃ ነው።

 

ስለዚህ ወንጀለኛ ካድሬን ወደ ህግ ማቅረብ ከባድ መሆኑን አስተውላለሁ። ነገር ግን እውነቱን መስማትና ማወቅ አስፈላጊ ነው። ወንጀለኛና ህዝብን የሚያስለቅስና የሚያስነባ ዘራፊ ካድሬ ሌባና ተባባሪዎቹ እውነት እላችኋለሁ ጊዜው ሊረዝም ይችላል ግን ዋጋቸውን ህዝብና እግዚአብሄር ይሰጣቸዋል። አያመልጡም።

 

ዓላማዬ በዳውሮ ህዝብ ጫንቃ ላይ ሆነው የሚዘርፉትን ሌቦችና ሙሰኞችን ማጋለጥ ነው።

 

በቀጣይ ጽሁፌ በዳውሮ ዞን በወረዳዎች ዉስጥ የተካሄደውን የውሃ ግንባታና የምንጭ ማጎልበት ሥራ እንደዚሁ አቀርብላችኋለሁ። ቸር ያሰንብተን!!    

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ