ተመስገን ደሳለኝ

ከወር በፊት ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩን አማካሪዎች በጨረፍታ›› በሚል ርዕስ በጀመርነው የ‹‹ጨረፍታ ዳሰሳ›› ሁለት አማካሪዎችን ‹‹ጨርፈን›› አይተን ነበር፡፡ ጓድ (ዶ/ር) ፋሲል ናሆምን እና ባይሎጂስቱን ሬድዋን ሁሴንን። በእርግጥ ስለሁለቱ አማካሪዎች ዛሬም ጥቂት እናይና ወደ ዋናው አጀንዳችን ወደፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ እናመራለን። ከዛ በፊት ግን ስለእነጓድ ፋሲል ጥቂት ተጨማሪ መረጃዎችን ደግሞ ማየቱ ያስፈለገበትን ምክንያት ላስረዳ፤

 

የፍትህ አንባቢያን እንደምታስታውሱት በሁለት ክፍል ሁለት አማካሪዎችን ተመልክተን ነበር፡፡ ሆኖም በዶ/ር ፋሲል ናሆም ላይ የቀረቡት ‹‹የአቋም-ተቃርኖ›› ማሳያ ማስረጃዎች በቂ አይደሉም የሚል አስተያየት ወደ ዝግጅት ክፍሉ ቀረበ። በእርግጥ በወቅቱ ያቀረብኩት ማስረጃ በቂ ነው በሚል ነው እንጂ የማስረጃ እጥረት እንኳ አልነበረም፤ ማስረጃ በገፍ ነው፡፡ ስለዚህም ወደ ፕሮፌሰሩ ከማለፋችን በፊት ጥቂት ስለፋሲል ናሆም ለመጨመር ተገደድኩ፡፡

 

ጓድ ፋሲል ናሆም! በእርግጥ ‹‹ጓድ›› ከማለት ‹‹ዶክተር›› ማለቱ ቀላልም ተገቢም ነበር፡፡ ሆኖም ‹‹ጓድ››ን የመረጥኩበት ምክንያት ለዛሬ በማስረጃነት ያቀረብኩት የደርጉ ልሳን የሆነው የካቲት መፅሔት ቃለ-መጠይቅ ባደረገላቸው ጊዜ የኢሰፓ አባላት መለያ ዩኒፎርም የነበረውን ‹‹ካኪ›› ለብሰው በመፅሄቱ ላይ ፎቶግራፋቸው የሚታየውን ዶ/ ር ፋሲልን ‹‹ጓድ…›› እያለ ስለሚጠራቸው ነው፡፡ እኔም አንባቢያን እንዳይደናገሩ ስል በቀጥታ መፅሄቱ የተጠቀመበትን የማዕረግ ስም እጠቀማለሁ። ጓድ…

 

ጓድ ፋሲል ናሆም በ1978ዓ.ም ወርሃ ‹‹የካቲት-መጋቢት›› እና ወርሃ ‹‹ግንቦት-ሰኔ›› ከታተመው ‹‹የካቲት መጽሔት›› ጋር ነው ሰፋ ያለ ቃለ መጠይቅ አድርገው የነበርው፡፡ ይህ መጽሔት የሚታተመው ‹‹በማስታወቂያና መርሐ ብሔር ሚኒስቴር›› ስር ነው፡፡ የግንቦት-ሰኔው እትም ‹‹ከአፄዎቹ ትውፊት ወደ ህዝባዊ መንግስት›› በሚል ርዕስ ነው የጓዱን ቃለ-መጠይቅ ያተመው፡፡ መፅሄቱ ለጓድ ፋሲል ቃለ-መጠይቅ ሲያደርግላቸው ለሁለተኛ ጊዜው ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል መጽሔቱ በመግቢያው ላይ እንዲህ ያለው፡-

 

‹‹በኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት አንስቲትዩት የሕገ መንግስትና የሕግ ጥናት ዘርፍ አስተባባሪ፣ ጓድ ፋሲል ናሆምን ለ2ኛ ጊዜ በማነጋገር (በ9ኛ ዓመት ቁጥር 6-7/1978 ስለሕገ መንግስት ቅርጽና ይዘት ጓዱን አነጋግረን የሰጡንን መልስ ማቅረባችን ይታወቀሳል) አቅርበናል፡፡››

 

የሆነ ሆኖ ዶ/ር ፋሲልን ‹‹ጓድ›› እያለ ‹‹የሚያንቆለጳጵሳቸው›› መንግስት ወድቆ፣ በአዲሱ መንግስት የጠ/ሚኒስትር መለስ አማካሪ ከሆኑ በኋላ፣ መለስ እና ፓርቲያቸው ለሰማዩም ለምድሩም አጀንዳ በማስፈራሪያነትም ሆነ በመከራከሪያነት ስለሚያቀርቡት ህገ መንግስት ‹‹ማህቶት›› ለተባለ የብአዴን ጋዜጣ ሲያብራሩ እንዲህ አሉ፡-

 

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፌደራሊዝም፣ ብሔረሰባዊ ፌደራሊዝም ነው፡፡ ይህ አገር የሚገነጣጥል ህዝብን የሚለያይ አፍራሽ ተልዕኮ ያለው ነው ብለው የተቹ ግለሰቦችና ቡድኖች አልጠፉም፡፡ እውነቱን ያየን እንደሆነ ግን በኢትዮጵያ በመንፀባረቅ ላይ ያለው ሐቅ ከዚህ በጣም የራቀ ነው፡፡ አገር የሚገነጣጠልበት፣ ሕዝብ የሚለያይበት ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጥንካሬ የሚያራምዱበት ሁኔታ ነው ጎልቶ የሚታየው፡፡›› (ማህቶት ጋዜጣ ግንቦት 11/1991)

 

ዶክተሩ ይህን ያሉት በዘመነ ኢህአዴግ እሳቸው ራሳቸው ተሳትፈውብት ስለተዘጋጀው ሕገ-መንግስት ነው፡፡ በዘመነ ደርግ ስለነበረው ሕገ-መንግስት ደግሞ እንዲህ ብለው ነበር፡-


‹‹የኢህደሪ ሕገ-መንግስት የኢትዮጵያን እውነታዎች ከአለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ከማርክሲም -ሌኒንዝም ርዕዮተ ዓለም አኳያ በማገናዘብ የተረቀቀ ነው፡፡… ለዚህ አይነት መንግስት የሚያስፈልገው ሕገ መንግስት ደግሞ ለሶሻሊስታዊ ህብረተሰብ ግንባታ መሰረት የሚጥል የሽግግር ሕገ-መንግስት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስትም አብዮታዊ መሪያችን ጓድ መንግስቱ ኃ/ማርያም ባጭሩ እንደገለፁት ‹ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮትን እያጠናቀቀ ለሶሻሊዝም ግንባታ መሰረት የሚጥል ሕገ መንግስት› ነው፡፡›› (የካቲት መፅሄት ግንቦት-ሰኔ 1978ዓ.ም እትም)


…ፋሲል ናሆም በ1960ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ በ1964ዓ.ም የማስተርስ፣ በ1967ዓ.ም ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት በአለማችን በህግ ት/ቤትነት ተስተካካይ የለውም ከሚባለው ‹‹ዬል›› ዩኒቨርስቲ መሆኑን ስናውቅ ነው ቃለ መጠይቃቸው በእጅጉ የሚደንቀን፡፡ እግዜር ያሳያችሁና! እኒህ የዬል ዩኒቨርስቲ የህግ ምሁር ህገ-መንግስቱ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ መሆኑን ለማስረዳት የህግ ሊቅ አድርገው ያቀረቡልን ‹‹አብዮታዊ መሪያችን ጓድ መንግስቱ ኃ/ማርያም ባጭሩ እንደገለፁት…›› እያሉ ነው፡፡ መቼስ ከዚህ በላይ አስደናቂ ነገር የትም የለ፤ የትም፡፡
የሆነ ሆኖ ጓድ ፋሲል አሁን በስራ ላይ ስላለው ህገ-መንግስት ተናግረው አይወጣላቸውም፡፡ ለምሳሌ ጥር 15/2004ዓ.ም በወጠው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ፡-


‹‹ሕገ-መንግስታችን ያለፈውን የተዛባ የህዝቦች አመለካከትን በመለወጥ ኢትዮጵያን በሕዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተች አገር አድርጓታል፡፡ የህዝቦች እኩልነት በውስጡ የዜጐች፣ የፆታ፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋና የባህል እኩልነትን ያካተተ ጥልቅ አስተሳሰብ ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት አድርጓቸዋል›› ብለዋል፡፡ ስለደርግ ሕገ-መንግስት ደግሞ እንዲህ ሲሉ ‹‹ዝማሬ መላዕክ›› አሰምተው ነበር፡-

 

‹‹ከዚህ ቀደም በአገራችን ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ከፍተኛ ተሳትፎ ውይይት የተካሄደበት የህገ-መንግስት ረቂቅ ሰፊ ማህበራዊ መሰረት ላለው የኢትዮጵያ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ዋስትና እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ሕገ-መንግስቱን የሪፐብሊኩ ዋስትና ከሚያሰኙት ምክንያቶች ዋነኛው በተወካዮቹ አማካይነት አርቅቆ፣ በረቂቁ ላይ ተወያይቶበት፣ የመጨረሻውን ረቂቅ በውሳኔው የሚያጸድቀው ራሱ ሰርቶ አደሩ ህዝብ መሆኑ ነው፡፡ …በየካቲት 1966 በግብታዊ እንቅስቃሴ የጀመረው አብዮታችን በተለያዩ የሶሲዮ-ኢኮኖሚ መስኮች ያስከተለው የሞት ሽረት ትንቅንቅ እንዲያውም በላቀ መንገድ በሕገ መንግስቱ መስክም ተንፀባርቋል፡፡ …በአጠቃላይ አዲሱ ሕገ-መንግስት የተረቀቀው የዛሬይቱን ኢትዮጵያና የዛሬይቱን ዓለም ተጨባጭ ሁኔታ፤ ዛሬ ደግሞ ከትናንትናና ከነገ ተለይቶ አይታይምና የትናንቷን ኢትዮጵያ ሁኔታ በማጥናትና ነገ ኢትዮጵያ ወዴት ነው የምታመራው? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ነው፡፡›› (የካቲት መፅሄት ግንቦት-ሰኔ 1978ዓ.ም እትም)


እኒህ ናቸው የእኛ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር›› አማካሪ፡፡ ‹‹የነገይቷ ኢትዮጵያ…›› ጭምር ሲሉ ያዘጋጁትን ህገ-መንግስት መልስው ሲያነቋሽሹ፣ ሲዘልፉ፣ ሲረግሙ ድንቅፍ የማያደርጋቸው፡፡ ሆኖም ይህን እየፃፍኩ ሳለ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ እናም ከትዝታዬ ጥቂቱን ልተርክላችህ ተነሳሳሁ፡- (ቀኑንና የሚንስትሩን ስም መጥቀሱ ለጊዜው ይቆይልኝ) ደህና! ከዚህ ቀደም በሚንስትር ማዕረግ ያሉ አንድ ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣን ቢሮአቸው ድረስ እንድመጣ በፃሃፊያቸው በኩል ያስጠሩኛል፡፡ መቼም ነገሩ ቴዲ አፍሮ እንዳለው ‹‹እቴጌ ሲጣሩ…›› ነውና በተጠራሁበት ሰዓት ከቢሮአቸው ተገኘው፡፡

 

ሚንስትሩም ምቾት ካለው የቢሮአቸው ሶፋ ወንበር በአንደኛው ላይ እንድቀመጥ ጋበዙኝ፡፡ (በእርግጥ አልጠጣሁም እንጂ ቡናም ጋብዘውኝ ነበር) እናም ለጥቂት ደቂቃ በአርምሞ ሲመለከቱኝ ቆዩና ‹‹ምክርና ማስፈራሪያ›› ቅልቅል የሆነውን ዲስኩራቸውን ማሰማት ጀመሩ፡፡ ብዙ ተናገሩ፤ ከኢህአዴግ ጠንካራ ጎን አንዱ የሰበሰባቸው የአመራር አባላት በሙሉ መናገር የሚችሉ ናቸው፡፡ በእርግጥ መናገራቸውን እንጂ የተናገሩትን አመኑበትም አላመኑበትም ደንታ የሚሰጣቸው አለመሆናቸው ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ከሁለት ሰዓት በላይ ከፈጀው ከሚንስትሩ ዲስኩር ከልቤ የተሰነቀረው ሀገር ክህደትን ጨምሮ በበርካታ ክስ መንግስት ሊከሰኝ እንደሆነ፣ ነገር ግን በሁለት ሳምንት የጊዜ ገደብ ውስጥ በጋዜጣው ላይ የሚወጡ ፁሁፎችን ይዘት መቀየር ወይም ወደ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ራሴን መቀየር እንዳለብኝ የሚያስገድድ አማራጭ መንግስት እንደሰጠኝ የነገሩኝ ነው፡፡ (እንዳሉትም ከሁለት ሳምንት በኋላ ተከሰስኩ፡፡ እናም ማዕከላዊ ፖሊስ ምርመራ ክፍል ቀርቤ ከ35 በላይ ክስና ከ100 በላይ ውንጀላዎች ቀርበውብኝ ለሁሉም ውንጀላዎች ቃል ሰጥቼ በዋስ ተፈታሁ)

 

የሆነ ሆኖ ክቡር ሚኒስትሩ በንግግራቸው መሀል እንዲህ አሉኝ፡- “you are young” (አንተ ወጣት ነህ) እነእስክንድር ነጋ ኢህአዴግን ቢጠሉ የደርግ ወታደሮች ስለሆኑ ነው፡፡ አንተ ግን ምክንያት የለህም፤ ደርግ አይደለህም፤ እናም ራስን አርም፡፡›› አሁንም ግራ ገባኝ፡፡ እስከማውቀው ድርስ እስክንድር ነጋ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ዲግሪው ድረስ አሜሪካን ሀገር የተማረ ሲሆን፤ ወደ ኢትዮጵያ የመጣውም ደርግ ከወደቀ በኋላ አንጋፋ ታጋዮች ‹‹ዴሞክራሲ ሰፈነ›› ያሉትን ቃል አምኖ ነው፡፡

 

ምንም እንኳን ኢህአዴግን ማመን ጉም መዝገን ሆኖ ያመነውን ባያገኝም፡፡ እናም ያን ጊዜ ሚንስትሩን ‹‹እስክንድር ነጋ እኮ ደርግ አይደለም›› ብዬ ባልመልስላቸውም ዛሬ ግን ልመልስላቸው ወደድኩ፤ አዎ! ‹‹ይህን ንግግርዎን የኢሰፓ አባል ጓድ ፋሲል ናሆም እንዳይሰማዎት፡፡››


በሌላ ቀን ደግሞ አንድ ‹‹አፍቃሬ ኢህአዴግ›› ጋዜጣ ‹‹አቶ ተመስገን ደሳለኝ በ1968ዓ.ም የደርግ አባል ነበሩ›› ብሎ ፃፈ፡፡ ያኔ እንዲህ እንደዛሬው ፍትህ ላይ ፎቶዬ አይወጣም ነበር፡፡ እናም ጥቂት የማይባሉ አንባቢዎችን አሳተ፡፡ ሆኖም ለዚህ አይነቱ ውንጀላ መልስ መስጠት አስፈላጊ አይደለም በሚል አለፍኩት፡፡ ዛሬ ግን ለዚያ ጋዜጣ የሚሆን አንድ ጥያቄ በዚሁ አጋጣሚ ማቅረቡ አስፈላጊ ሆኖ አገኘሁት፤ ጥያቄው የሚያተኩረውም እንዲሁ ‹‹በጨረፍታ›› በሌላ ጊዜ በምንመለስባቸው፣ በሌላኛው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ንዋይ ገ/አምላክ ላይ ነው፡፡ ጥያቄውም ይህ ነው ‹‹የጠቅላይ ሚንስትር መለስ የኢኮኖሚ አማካሪ ንዋይ ገ/አምላክ በደርግ ጊዜ ምን ነበሩ?›› (በረሃ ነበሩ እንዳትሉኝ፤ እሳቸው በረሃ አልገቡም፤ ምንአልባት ውቤ በረሃ ገብተው ካልሆነ በቀር)


እሺ! ወደ እንድሪያስ እሸቴ ከማለፋችን በፊት ለመጨረሻ ጊዜ አንድ ነገር ልጨምር-አማካሪ ሬድዋን ሁሴንን የሚመለከት፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- ከ97-2002ዓ.ም በነበረው የፓርላማ ዘመን በኢትዮጵያ የህዝብ ቆጠራ ተካሂዶ ነበር፡፡ እናም ውጤቱ ለፓርላማው ሲቀርብ ተቃውሞ ገጠመው፡፡ የቀረበው ተቃውሞ የአማራ ህዝብን እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በሚመለከት የቀረበው አሀዝ ትክክል አይደለም ‹‹አሳንሳችሁታል›› የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን ሬድዋን ሁሴን የተቃዋሚዎቹን ተቃውሞ ‹‹መሰረተ ቢስ›› ሲሉ አጣጥሉት፡፡ ሆኖም ሬድዋን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በነበሩበት ዘመን ‹‹ዤል›› ለተሰኘው መጽሔት (መጽሔቱ የታተመበት ቀን፣ ወር እና አመተ ምህረት የለውም) እንዲህ ብለው ነበር፡-


‹‹የስልጤ ህዝብ ብዛት በትክክል ሰፍሯል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ለምሳሌ በ1987/1994ዓ.ም የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት መሰረት እንኳን ብንነሳ የተሳከሩ ነገሮችን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ….ከስልጤ ህዝብ ወደ ግማሽ የሚሆነው መንደሩን ለቆ የተበተነ በመሆኑ ከላይ በተጠቀሰው መረጃ መሰረት የስልጥኛ ተናጋሪው ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ እንደሆነ ተቀምጧል፡፡ በትክክል ቢቆጠር ከዚህ እንደሚጨምር እንገምታለን፡፡››


በበኩሌ ‹‹በስልጤ ህዝብ የቆጠራ ውጤት ላይ የተሳከሩ ነገሮች አሉ›› የሚለውን የሬድዋንን ቅሬታ አምንበታለሁ፡፡ እዚህ ሀገር የማይሳከር ነገር የለምና፡፡ የሚደብረው ግን ሬድዋን ከስልጤ ህዝብ ጎን በነበሩበት ጊዜ የጮኹለትን ችግር፣ ከኢህአዴግ ጎን በቆሙ ጊዜ ሲረግሙት ነው፡፡ በእርግጥ የሬድዋን ልዩ መገለጫም ይህ ነው፡፡ በተቃዋሚነት ዘመን ኢህአዴግ የሚያቀርባቸውንና የሚናገራቸውን ሁሉ ‹‹የማይታመን፣ የተሳከረ…›› ሲሉ ቆይተው ኢህአዴግ በመሆን ከሚገኘው ‹‹ሙሉ ጥቅም›› ጋር ወደኢህአዴግ ከገቡ በኋላ ተመሳሳይ ተቃውሞን ማጣጣል ስራዬ ብለው ይዘውታል፤ በነገራችን ላይ እነፋሲል፣ ሬድዋን፣ እንድሪያስ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ›› የሚል ማዕረግ መያዛቸውን አይተን ‹‹መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ጨለማ ነው›› ብለን ብናስብ ‹‹ተሳሰታችሁ›› የሚለን የለም፡፡ …እነሆ አሁን የቀረን የአየር ሰአት የአማካሪ እንድሪያስ እሸቴ ነውና ወደዛው እንለፍ፡፡

 

ሁላችንም እንደምናውቀው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹‹አሸንፈው›› ከበረሃ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ነው ፕ/ር እንድሪያስ እሸቴም ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ የገቡት፡፡ በእርግጥ መምጣታቸው ክፋት የለውም የመጡት ወደሀገራቸው ነውና፡፡ እናም ለምን መጡ? የሚል ጥያቄ አላነሳም፤ ሆኖም ስለአመጣጣቸው የተነገሩትን ማየቱ ግን አይከፋም፡፡ ለምሳሌ የእንድሪያስ እሽቴ የቅርብ ወዳጅ የሆኑት አቶ አሰፋ ጨቦ ጓደኛቸው እንድሪያስ ወደ ኢትዮጵያ የመጡበትን ምክንያት እንዲህ ይገልፁታል፡-


‹‹ዳዊት የወያኔ ደንገጡር ሆኖ በ1983ዓ.ም ክረምት አዲስ አበባ ከጎረፉት ውስጥ አንዱ ነበር፡፡ የጎረፉት ከኑሮ ሽሽት ይሁን የአገር ፍቅር አቃጥሏቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ የአንዳንዶቹን የፊትም ሆነ የኋላ ታሪክ ሳየው ከ‹ፍቅሩ› ይልቅ ‹ሽሽቱ› ጎላ ይልብኛል፡፡ ጥቂቶቹ አቶ ክፍሌ ወዳጆ፣ አብዱል አባቦራ፣ እንድሪያስ እሸቴ፣ ዳዊት ዮሐንስ፣ ተኮላ ሀጎስን ከዚህ እመድባቸዋለሁ፡፡›› (ኢትኦጵ መጽሔት ቅጽ 1 ቁጥር 1 ሰኔ 1991)


ይህንን የሚያጠናክር ሌላም አለ፡፡ እንዲህ የሚል ‹‹እንድሪያስ እሸቴ በአሜሪካ በሚገኙት በርክሌ፣ ብራውን እና ፔንሲልቫንያ ዩኒቨርስቲዎች የማርክሲስት ኮርሶችን ይሰጡ ነበር፡፡ ሆኖም የቀዝቃዛውን ጦርነት ካፒታሊስቷ አሜሪካ በአሸናፊነት ተወጣች፡፡ የበርሊን ግንብም ወደቀ፡፡ እናም ስለማርክሲስተ ማስተማሩም ሆነ መማሩ በአሜሪካ ገበያ ገዥ ያጣ ‹አሞሌ› ሆነ፡፡ ነገር ግን ዩኒቨርስቲው የእንድሪያስን ውለታ ከግምት በማስገባት ‹ፌሎሽፕ› በመስጠት መጽሐፍ ይፅፉ ዘንድ ዕድል ሰጣቸው፡፡ የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ይሄም ለፕሮፌሰሩ ‹ዳገት› ሆነባቸው፡፡ ይኽን ጊዜም ለእንድሪያስ የሚሆን አማራጭ ያጣው ዩኒቨርስቲ ከግቢው እንድሪያስን አባረራቸው፡፡ ከዚህ በኋላም ነው ‹ለጌታ ኢህአዴግ ማደር› የሚል አማራጭ የተከሰተላቸውና ወደኢትዮጵያ የመጡት›› የቅርብ ሰዎቻቸው እንደሚሉት፡፡


መቼም ስለእንድሪያስ እሸቴ ስንነጋገር ‹‹ጎበዝ›› አስተማሪና ‹‹በሙያቸው የበቁ›› ሙሁር መሆናቸውን ክድን አይደለም፡፡ የሚካድም አይደለም፡፡ ጥያቄው ከእንድሪያስ ‹‹ምሁርነት›› ኢትዮጵያ ምን አተረፈች? የሚለው ነው፡፡ መቼም ለዚህ ጥያቄ ራሳቸው የእንድሪያስ አድናቂዎችም (በምሁርነታቸው) ምላሽ የላቸውም፡፡ እኛም የለንም፤ ምን አልባት ከውብ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታ ጋር ‹‹ፒትልስ›› ለብሶ መንጎማለል የሀገር ገፅታ ይገነባል ካልተባለ በቀር፡፡

 

የእንድሪያስ እሸቴ ¬¬‹‹ኢ-ሞራል›› ስራ ብለን ስናወራ የመጀመሪያ ሆኖ የምናገኘው በግንቦት 20 ማግስት በኢቲቪ የሰጡት ምስክርነት ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፤ ጊዜው ኢህአዴግ እና ሻዕቢያ ‹‹እፍ›› ባለ አፍላ ፍቅር ውስጥ የነበሩበት ነው፡፡ እናም የቀድሞ መንግስት ወታደሮች ‹‹ሀገር አትገነጠልም›› በሚለው የቀድሞ መንግስት መፈክር ስር ተሰባስበው ከሻዕቢያና ኢህአዴግ ጋር ብርቱ ትግል አድርገው ነበር፡፡ የማታ ማታም የትግሉ በለስ ከመንግስት ይልቅ ወደ አማፂያን አድልቶ መንግስት ተሸነፈ፡፡ ኤርትራም ከኢትዮጵያ ተገንጥላ በሻዕቢያ መዳፍ ስር ገባች፡፡ ይህንንም ተከትሎ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችና ሲቪሎች ከእነ ቤተሰቦቻቸው ከኤርትራ ምድር ‹‹ሓድጊ›› ተብለው ተባረሩ፡፡ የሻዕቢያ ታጋዮችና ደጋፊዎችም የእነዚህን ሰዎች ንብረት ከመቀማት አልፎ የወርቅ ጥርሳቸውን ሳይቀር በሀይል እየነቀሉ ወስደው ሲያበቁ አንገላትተው አባረሯቸው (በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሴቶችና ህፃናቶችም ከተባራሪዎቹ ውስጥ አሉበት) ይህንንም ተከትሎ በመሀል ሀገር ብርቱ ተቃውሞ ተነሳ፡፡ ሻዕቢያም በኢትዮጵያ ‹‹ኪሳራ›› በአፍሪካ ቀንድ ‹‹የአፍሪካ ሲንጋፖር››ን የመገንባት ህልም ነበረውና የመሀል ሀገር ሰዎችን ከጠዋቱ በግልፅ ማስቀየሙ እንቅፋት ሊሆንበት እንደሚችል ጠረጠረ፡፡

 

ጠርጥሮም አልቀረ ይህ አይነቱ ድርጊት በኤርትራ አልተደረገም ሲል ‹‹አይኔን ግንባር ያድርገው›› ብሎ ማለ (መማሉን እንኳን እርግጠኛ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከዚህ ቀደም ኢቲቪ ሻዕቢያ አዲስ አበባን እንደባግዳድ አደርጋለሁ ብሎ ምሏል ስላለ ያው መማሉ አይቀርም በሚል ነው) ሆኖም ያመነው የለም፡፡ ስለዚህም በድፍን አዲስ አበባ ምስክር ማፈላለግ ጀመረ፡፡ ፍለጋውም አድክሞ አልተወውም-ቀናው፡፡ በወቅቱ ኤርትራዊት ባለቤት የነበራቸው ፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ በሻዕቢያ አይን ሞሉ፡፡ ምስክር ይሆኑ ዘንድም ወደኤርትራ ሄዱ፡፡ ስለሁኔታው እኔ ከምናገር የቅርብ ወዳጃቸው አሰፋ ጨቦ ይናገሩ፡-

 

‹‹እነ ኢሳያስ ወደ አስመራ ሲመለሱ ይዘዋቸው ከሄዱት ውስጥ እንድሪያስና ጓደኛው ነበሩ፡፡ ከአስመራ በተመለሱ ማግስት እኔና ባለቤቴ ግዮን ሆቴል በምሳ ሰዓት አገኘናቸው፡፡ ‹መሄዴ ነው ቸኩያለሁ… ኢንተርቪው አለብኝ… የቲቪ ሰዎች ይጠብቁኛል፡፡› አለን እጅጉን አጥብቄ ይዤው ‹በእኔ ሞት ስለኤርትራ እውነትም ውሸትም አትናገር ህዝቡ ሀገር ሞቷል ብሎ ለቅሶ ላይ ነው ያለው…› አልኩት፡፡ አልቀረም ሄዶ ተናገረ፡፡ ባለቤቴ ማታ ‹ና..ና የጓደኛህን ጉድ ስማ!› አለችኝ ቲቪ እያየች፡፡ እኔ ደፍሬ አላየሁም፡፡ በነጋታው አገር ሲያወራ ሰማሁ፡፡ ከዚያ አገር ስቀሎ! ስቀሎ! እያለው ጥሎ ወጣ፡፡›› (ዝኒ ከማሁ)

 

እንድሪያስን ‹‹ስቀሎ! ስቀሎ!›› ያስባለው ‹‹ከኤርትራ ወታደሮችም ሆኑ ሲቪሎች ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ ከእነ ንብረታቸው በሰላም፣ በፍቃደኝነት ነው ወደአገራቸው ኢትዮጵያ የመጡት›› ሲሉ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው መመስከራቸው ነው፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ እነዚህ ተፈናቃዮች ያለአንዳች ንብረት የተባረሩ በመሆናቸው፣ በአዲስ አበባ ሳይቀር በዋና ዋና አደባባዮች የላስቲክ ቤት ሰርተው ጎዳና ወድቀው ነበር፤ ያውም ከእነ ህፃናት ልጆቻው፡፡ መቼም የአንድ ፕሮፌሰር ‹‹ምሁርነት›› መረጋገጫው የዚህ አይነት የጭካኔ ምስክርነት በአደባባይ በመስጠት ነው? የሚል አለ ብዬ አላስብም፡፡

 

እንድሪያስ እሸቴ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ነበር የASPA Scholarship አግኝተው ከሌሎች ስድስት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር ወደ አሜሪካ የሄዱት፡፡ በእርግጥ ይህን ስኮላር ያገኙት በትምህርታቸው ‹‹ጎበዝ›› የሚባሉ ስለነበር እንደሆነ አያጨቃጭቅም፡፡ አጨቃጫቂው ሌላ ነውና፡፡

 

…እንድሪያስ አሜሪካ ከገቡ በኋላ በዊሊያም ኮሌጅ እና ዬል ዩንቨርስቲ ውስጥ እስከ ዶክትሬት ድግሪያቸው ድረስ ተምረዋል፡፡ በነገራችን ላይ እነእንድሪያስ እሸቴ አሜሪካን ሀገር ሳሉ ከጥቂት ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ‹‹እምቢልታ›› የተሰኘ መጽሔት ያዘጋጁ ነበር፡፡ ‹‹የዛች የመጽሔት አድራጊ ፈጣሪም እንድሪያስ ነበር›› ሲሉ ነግረውኛል በአሜሪካ አብረዋቸው ይኖሩ የነበሩ አንድ ጓደኛቸው፡፡

 

የሆነ ሆኖ ከዕለታት በአንዱ ቀን ‹‹እምቢልታ መጽሔት›› ፓናል ዲስከሽን በአሜሪካ ያዘጋጃል፡፡ ዝርዝሩን ከአስፋ ጨቦ እንስማ፡-

 

‹‹1983 በጋ በኢትዮጵያ ጉዳይ ፓናል ዲስከሽን ይደረጋልና ተካፈል ተብዬ በደብዳቤ ተጋበዝኩ፡፡ አዘጋጁ ‹የእምቢልታ› መጽሔት ነው፡፡ የዚህ መጽሔት አዘጋጆች ደግሞ እንድሪያስ እሸቴ፣ ክፍሌ ወዳጆ፣ ሙሉጌታ ከበደ ናቸው፡፡ የውይይቱ ተካፋዮች እኔ፣ ዶ/ር በረከት ኃብተስላሴና እንድሪያስ እሸቴ ነን፡፡ አዳራሹ ግጥም ብሏል፡፡ ወጥመድ ውስጥ መግባቴን ከገባሁ በኋላ አወቅሁ፡፡ በረከትና እንድሪያስ የኤርትራ ወኪሎች ናቸው፡፡ እኔ የኢትዮጵያ ወኪል ሆንኩ፡፡ ውይይት ሳይሆን የአቋም መግለጫ ሆነ፡፡ የፖለቲካ አጀንዳ ማሳመኛ መድረክ ሆነ፡፡ ውይይት ሳይሆን ጦር ሜዳ ሆነ፡፡ አዳራሹን ከሞላው 90% ወያኔና ሻዕቢያ ናቸው፡፡ …ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት እኔ በዝረራ ልሸነፍ ኖሮአል፡፡ የእኔ መዘረር ደግሞ የአገሬ መዘረር ‹ማረጋገጫ› ሊሆን መሰለኝ፡፡ እንዳለ ወረዱብኝ፡፡ አገሬንም ወረዱባት›› (ዝኒ ከማሁ)
እንግዲህ አማካሪ ፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ እንዲህ ናቸው፡፡ ሀገርን ያህል ነገር በዝረራ ለመጣል የሚታገሉ-ጎልያድ፡፡ የኢትዮጵያዊነት ቅጥር ለመናድ የሚባትቱ-ጎልያድ፡፡ ታሪክን በማፈረስ ሀሴት የሚያደርጉ! ለነገሩ ድልድይ በማፍረስ እና ታሪክ በማፍረስ መካከል ልዩነት የለም፡፡

 

ለእንድሪያስ እሸቴ ‹‹ሀገር የተዋቀረበት››ን ታሪክ አፍራሽነት እንደ አስረጅ የሚቀርበው በ1988 ዓ.ም. የካቲት 23 ቀን መቶ አመት የሞላው የአድዋ ድል አከባበርን አስመልክቶ ያቀረቡት የታሪክ ትንተና ነው፡፡ ወቅቱ ኢህአዴግ ‹‹ኢትዮጵያን አፍርሼ ልስራ›› በሚል ያዙኝ ልቀቁኝ ይል የነበረበት ነው፡፡ በአናቱም የአንድነታችን መግለጫ የሆነው ባንዲራ ‹‹ጨርቅ›› እየተባለ የሚዘለፍበት፣ የሀገሪቱ ታሪክ ከ3 ሺህ ወደ መቶ አመት የአሽቆለቆለበት ሲሆን፤ በግልባጩ ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ጎሰኝነት የአሻቀበበት፣ በአጠቃላይ የታሪክ ‹‹ግሽፈት›› የተከሰተበት፣ ‹‹የሀገር ፍቅር›› ፈተና ላይ የወደቀበት ወቅት ነበር-ያ ወቅት፡፡ እናም ኢህአዴግ ታላቁን የአድዋ ድል በሚመለከት አዲስ ታሪክ መተረክ ጀመረ፡፡ ‹‹ድሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ነው›› የሚል፡፡ ይህ ሴራ ኢህአዴግ ሀገርን የመከፋፈል እስትራቴጂውን ይበልጥ ወደ መሬት ለማወርድ የሞከረበት ነው፡፡ ለዚህም አዲስ ታሪክ የሻዕቢያና የኢህአዴግ ‹‹ቋሚ-ተጠሪ›› ፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ መስካሪ ሆነው ብቅ አሉ፡፡ እናም እንዲህ አሉ ‹‹አዎ! የአድዋ ድል በአፄ ምኒሊክ መሪነት የተገኘ የኢትዮጵያ ህዝብ ድል አይደለም፡፡ ምንሊክና ወታደሮቻቸው ከጦርነቱ ግንባር ሽሽት ጀምረው ሳለ የትግራይ ህዝብ ገትሮ መዋጋቱን ቀጥሎ፣ እያሸነፈ ሲሄድ በማየታቸው የጀመሩትን ሽሽት ትተው ወደ አድዋ ተመለሱ፡፡›› የምሁራኖች አሳሳችነት አደገኛ ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ምክንያቱም ሲዋሹ እንኳ ቀለም ያለው ውሸት አይዋሹምና።

 

የሆነ ሆኖ የትግራይ ህዝብ ጭምር ይህንን የኢህአዴግን እና የእንድሪያስን አዲስ ታሪክ አጥብቆ ተቃወመ፡፡ መኢአድም በወቅቱ መስቀል አደባባይ በጠራው የተቃውሞ ስብሰባ ላይ በቂ መልስ ሰጠ፡፡ ታዋቂው የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ታማኝ በየነም በአደባባዩ በመገኘት እንዲህ አለ ‹‹የአድዋ ድል እና የአፄ ሚኒሊክ አስተዋጽኦ በሆዳም ምሁራኖች የፈጠራ ታሪክ አይበረዝም›› (ታማኝ በሲዲ ያዘጋጀውን ማየት ይቻላል)

 

ዛሬ ላለው የብሔር ፌደራሊዝም በር ከፋች የሆነው ‹‹የብሔር ጥያቄ›› በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ (ከዋለልኝ በፊት) እንዲነሳ ያደረኩት እኔነኝ ሲሉ እንድሪያስ ይከራከራሉ፡፡ የአደረ ውለታን ታሳቢ በማድረግም ኢህአዴግ ያግዛቸዋል፡፡ በቅርቡም በመቀሌ በተከበረው ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች ቀን›› ላይ እንድሪያስ “Yankees go home (ያንኪዎች ከአገራችን ውጡ)›› በሚል ርዕስ ስለኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ የሚያትት አንድ ፅሁፍ አቅርበው ነበር፡፡ እናም ኢህአዴግ እንድሪያስ በተማሪው እንቅስቃሴ ላይ ‹‹ወካይ-ስብዕና›› እንዲኖራቸው እየጣረ ነው፡፡ በእርግጥ እንድሪያስን የዚያ ታሪክ ‹‹እምብርት›› ላይ ማስቀመጡ፣ ለኢህአዴግ የእንድሪያሳን ተክለሰውነት በመገንባት ብቻ ላይ በማነጣጠር የተቀመረ አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም የተማሪውን የ‹‹መሬት ላራሹን እና የብሄር ጭቆናን›› የሚመለከቱ ጥያቄዎችን ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ እንደመለሰው በየሚዲያው ቀርበው ይመሰክሩለት ዘንድ ነው-‹‹ባለ-ታሪክ›› እያደረጋቸው ያለው፡፡

 

እውነታው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፤ እንድሪያስ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ ላይ ከብዙሃኑ የአልተለየ ተሳትፎ እንደነበራቸው ባይካድም በሀገር ውስጥ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ላይ ግን አንዳችም ተሳትፎ የላቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ በዩንቨርስቲ ተማሪነት ሀገር ውስጥም አልነበሩም፡፡

 

የሆነ ሆኖ ከእንድሪያስ ‹‹ምሁር››ነት ኢትዮጵያ ምን አተረፈች? የሚለው ሊመዘን ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ “Callaloo” በተባለ ጆርናል ላይ እ.እ.አ በ2010ዓ.ም በታተመ ቃለ መጠይቃቸው ስለ “Public intellectual” (ህዝባዊ ምሁርነት) ተጠይቀው እንዲህ ሲሉ መልሰው ነበር፡-

 

“The most important step is to have a change in public conception, and to persuade people of the merit of public conception, and to make the conception, realized psychologically, institutionally, and so on. That is what Public intellectuals are supposed to do and I agree with this and I agree with the Socratic one as well, fighting complacency… It may sound dogmatic, but I believe in the slogan ‘the unexamined life is not worth living.’ And part of the role of the public intellectual is to make sure that your fellow citizens, your community does not stop examining itself, That we are not complacent.”

 

(እጅግ አስፈላጊ ነው ብዬ ከማምንባቸው ነገሮች ውስጥ አንደኛው ህዝባዊ ንቀተ-ህሊናን በተመለከተ ጥቂቶችን መሰረት የሚያደርግ ህዝባዊ መረዳት በስነ-ልቦና ላይም ሆነ ተቋማዊ በሆነ ሁኔታ መረጋገጥ ይኖርበታል የሚል ነው፡፡ ይህን ማድርግ ያለባቸው ህዝባዊ ምሁራን ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ አቋሜ በተጨማሪ ባሉ ነገሮች መርካትን አጥብቀን መቃወም ያስፈልገናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ‹‹መጠይቅ የሌለበት ህይወት ዋጋቢስ ነው›› ከሚለው ሶክራቴካዊ ሀሳብ ጋር ስለምስማማ የአደባባይ ምሁራን ማህበረሰባቸው ህይወቱን እና ኑሮውን ከመፈተሽ እንዳይታቀብ ማድረግ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡)

 

እውነት ግን ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ ናቸው ‹‹የአደባባይ ምሁራን ማህበረሰቡ ይህወቱን እና ኑሮውን ከመፈተሽ እንዳይተቃብ ማድረግ አለባቸው›› ያሉት? እንዴት ነው ነገሩ እስከአሁን ድረስ ስለሰውየው ‹‹ምሁራዊ ሰውነት›› ተስማምተን ነበር እዚህ የደረስነው፡፡ ሆኖም ፕሮፌሰሩ ራሳቸው ባስቀመጡልን መስፈርት ስንገመግማቸው የራሳቸውን ምሁራዊ ሰውነት ያንኮታኩትብናል፡፡ ምናአልባት ይህን ያሉት ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ወይም ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ቢሆኑ ኖሮ ይገባን ነበር፡፡ የእንድሪያስ ግን… ‹‹ማህበረሰቡ ህይወቱን እና ኑሮው እንዲፈትሽ ማስተማሩ የምሁራን ስራ ነው›› ያሉት አስቂኝ ነው ወይም ሰውየው ደህና ቧልተኛ ናቸው ብልን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ አሊያማ እሳቸው የሚመከሩት መንግስትም አይደል እንዴ እንኳን ኑሮን ልንፈትሽ ግብር በዛ፣ መሬታችንን በሊዝ ስም ተነጠቅና፣ የደሞዝ ጭማሪው አነሰን.. እንዳንል በሀይል ሰንጎ የያዘን፡፡ ሰው እንዴት በዚህ እድሜውና፣ ፕሮፌሰር የሚል ማዕረግ ተሸክሞ የሚናገረውና የሚያደርገው ነጭ እና ጥቁር ይሆናል?

 

ወጣም ወረደ የምሁራኖች ሚና ምንጊዜም የሚለካው ከህዝባዊ ፋይዳው አንፃር ነው፡፡ የሚያምኑበትን እውነት በአደባባይ በመመስከር እና በአደባባይ የመንግስትን ውሸቶች በማጋለጥና በመተቸትም ነው፡፡ የአደባባይ ሙሁርነት ትርጓሜም ቦታውን የሚያገኘው በዚህ መስመር እንጂ እንድሪያስ በቆሙበት ጠርዝ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ‹‹ድህነት፣ ረሃብ፣ በሽታ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የፍትህ መዛባት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ሙስና… ›› ያሉ ችግሮች እንደሆኑ ራሱ ኢህአዴግም ያመናል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ‹‹የመንግስት ሌቦች›› ሲሉ ችግሩ እንዳለ በይፋ ተናግረዋል፡፡ እንድሪያስ እሸቴ ግን ትንፍሽ ያሉት ነገር የለም፡፡ ታዲያ የቱ ጋ ነው ከራሳቸው አልፈው ሌላውም ህይወቱንና ኑሮውን እንዲፈትሽ የሚመክሩት? ለምሳሌ በደርግ ዘመን ይኼ አይነቱ ችግር በስፋት ነበር፡፡ ሆኖም መንግስቱ ኃ/ማርያም ከስልጣን ይወርድ ዘንድ የጠየቁ የአደባባይ ምሁራኖች ነበሩ፡፡

 

እነዚህ ምሁራኖችም ‹‹ሚያዝያ 1 ቀን 1983 ዓ.ም. ለጓድ መንግስቱ ኃ/ማርያም የኢሰፓ ዋና ፀሐፊ የኢህዴሪ ፕሬዚዳንት የአብዮታዊ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፤ ጓድ ፕሬዘዳንት…›› በሚል የሚጀምር ደብዳቤ ለጓድ መንግስቱ ኃ/ማሪያም ፅፈው ነበር፡፡ የደብዳቤው ፍሬ ነገር መንግስቱ እና ፓርቲያቸው ስልጣናቸውን ከህዝብ ለሚመረጥ የአገር ሽማግሌ የሽግግር መንግስት እንዲያስረክቡ የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ደብዳቤ ላይ ዘጠኝ ምሁራኖች ስምና ፊርማቸውን አስፍረውበታል፡፡ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፣ ዶ/ር መኮንን ቢሻው፣ ዶ/ር ታዬ ወልደሰማያትን ጨምሮ ማለት ነው፡፡

 

እዚህ ጋር ነው እንድሪያስ የአደባባይ ምሁር ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለው ንትርክ ጉንጭ አልፋ የሚሆንብን፡፡

 

እንድሪያስን ራሳቸው ከላይ ባስቀመጡት የህዝባዊ ምሁርነት መስፈርት ስናያቸው እንኳንም እዛ ብያኔ ላይ ሊደርሱ የጠቀስናቸውን ምሁራን እንኳን አያስተካክሉም፡፡ እንደ ፕ/ር እንድሪያስ ዓይነቶቹ ከአምባገነናዊ አገዛዞች ጋር ጥቅማዊ ግንኙነት የሚፈፅሙ ምሁራንን የሚያወግዘውና በአለም አቀፍ ደረጃ ከ100 ህዝባዊ ምሁራን ውስጥ የተመደበው ፕ/ር ጆርጅ አይቴ እንዲህ አይነት ሙሁራኖችን በትህና አልባ ቅፅል ይጠራቸዋል፣ “No tears for African intellectuals” በሚለው ፅሁፉ፤ ጋናዊው ኢኮኖሚስት ምሁራዊ ማንነታቸውን እንደ አቶ መለስ ላሉ አምባገነኖች በጥቅማጥቅም የሚለወጡ ምሁራንን “Prostitute intellectuals” (ሴተኛ አዳሪ ሙሁራን) ሲል ይጠራቸዋል፡፡ የእንድሪያስ የዓመታት ታሪክ እርሳቸውን በዚህ ቅፅል እንድንጠራቸው አያደርገንም?


…አማካሪ ፕሮፌሰር እንድሪያስን በተመለከተ ‹‹ጨረፍታ››ችንን አልጨረስንምና ሳምንት እመለስበታለሁ፡፡

ምንጭ፦ ፍትህ ጋዜጣ (አዲስ አበባ)

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ