አቤ ቶክቻው

ትላንት ከፌስ ቡክ ላይ የተገኘ የአንዲትን ህፃን አበሳ የሚያሳይ ቪዲዮ በማቅረብ “ኡኡታ…” አሰምተን ነበር። ኡኡታውን በርካቶች ተቀባብለውታል። በቪዲዮው ውስጥ እየቀረፀች ስትስቅ የነበረችው በጨረፍታ ስሟ የሚሰማው ሜሮን ብዙዎች ከደብዳቢዋ ሴትዮ እኩል ጠምደዋታል። እኔም ጠምጃታለሁ። ነገር ግን ላመሰግናትም እወዳለሁ። ምክንያቱም፤ ቢያንስ ይህ አይነቱ ጥቃት ይፋ እንዲሆን አድርጋለች።

 

ጥቃቱ ይፋ ከሆነ በኋላ “የአፋላጊ ዶት ኮም” ኩባንያ መስራች የሆኑት አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ልጅቷን እና ጥቃት ሰንዛሬዋን ሴት ለጠቆመ አስር ሺህ ብር እሰጣለሁ ብለው ማስታወቂያ አስነገሩ። በዚህ ግዜም የጠመድናት ሜሮን ድጋሚ እየሳቀች የህፃኗ እናት ወይዘሮ ሃሊማ ያሉበትን ጠቆመች። ሪፖርተር እንደዘገበው ወይዘሮዋን በገኟቸው ወቅት፤

 

በአዲሱ ሚሊኒየም የሕፃናት ደህንነት የሁላችን ኃላፊነት ነው፤ የሚል ቀይ ቲሸርት ለብሰው…

 

ይችትላችሁ እንግዲህ ዋና ስላቅ። (በቅንፍም የወይዘሮ ሃሊማን የቲሸርት መፈክር  ከመንግስት ባህሪ ጋር ማመሳሰል ያሸልማል!)

 

ወይዘሮ ሃሊማ “ልጅቷን የደበደብኩት በወቅቱ በጣም ተናድጄ ስለነበረ ነውና ይቅርታ አድርጉልኝ” ሲሉ ቪዲዮውን የተመለከቱትን ሰዎች በሙሉ ይቅርታ ጠይቀዋል። ይሄም ስላቅ እንደማይሆን ማስረጃ የለንም። ሪፖርተር አያይዞ ሲዘግብም ልጅቷ “ከዛ በኋላ ካላጠፋሁ ተመትቼ አላውቅም” ማለቷን ነግሮናል።

 

አንግዲህ ከዚህ በኋላ ያለው የፖሊስ ስራ ነው። እኛ የተጠየቅነውን ይቅርታ ለወይዘሮ ሃሊማ እንሰጣቸዋለን ህግ ደግሞ ተገቢውን ቅጣት ይሰጣቸዋል። አለበለዛ ከህጉ ጋር እንደተዛዘብን እንቀጥላለን!

በዚሁ ወደ ቡጨቃችን እናምራ:-

 

እኔ የምለው፤ በደርግ ግዜ የሰራዊቱ አባል የነበረው ሰራዊት ፍቅሬ አሁን ደግሞ የኢህአዴግ ሰራዊት አባል ሳይሆን እንደማይቀር ይገመት የለ? ለነገሩ እንዲገጣጠምልኝ ብዬ እንጂ የሰራዊቱ አባል ሳይሆን የኢህአዴግ አባል ማለቴ ነው።

 

“አብዬ ዘርጋው” በሚለው የሬድዮ ድራማ ላይ ሲተውን ድንገት ታዋቂ የሆነው ሰራዊት ፍቅሬ አሁንም የተለያዩ የክልል ቴሌቶን ማስታወቂያዎችን የአነስተኛና ጥቃቅን አክሲዮን ንግድ ማስታወቂያዎችን በሙሉ ጠቅልሎ ይዞ የማስታወቂያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኗል እየተባለ ይታማል።

 

ሰራዊት ፍቅሬ ከዚህ በፊት ጋዜጠኞች “ልማታዊ የማስታወቂያ ባለሞያ ነህ ይባላል…ምን አስተያየት አለህ?” ብለው ጠይቀውት ነበር። እርሱም ሲመልስ “ልማታዊ” ማለት ምን ማለት ነው? በአገሬ ልማት ላይ እሳተፋለሁ ከዚህ ውጪ ልማታዊ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አይገባኝም?” አይነት መልስ ሰጥቶ ነበር።

 

ውድ ሰራዊት፤ “ልማታዊ” ማለት እንዴት መሰለህ? ቆይ ላስረዳህማ…

 

በአዲሳባ  ቋንቋ፤ አንድ ሰው ልማታዊ ሆኗል ከተባለ… በአቶ በረከት መፅሀፍ ምረቃ ላይ ተገኝቶ ፈርሙልኝ ይላል ማለት ነው። አንድ ሰው ልማታዊ ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለጥያቄ ቀጥሮ ጥያቄውን እንዳይከብዳቸው ጥረት ያደርጋል ማለት ነው… አንድ ሰው ልማታዊ ነው ከተባለ አባይ ወንዝ ሄዶ ሊያለማ ይምላል ይገዘታል ማለት ነው። (ልብ አድርግ ይምላል ይገዘታል አልኩ እንጂ ያለማል አላልኩም)

 

ስለዚህ እነዚህን ሁሉ አንተም አድርገሃል ወደፊትም ታደርጋለህ ተብሎ ይገመታል። እናም ሰራዊት ሆይ ልማታዊ ነህና አትፍራ!

 

ለነገሩ ለዛሬው ቡጨቃ ያነሳሳኝ መቼለታ ሰራዊት በኢቲቪ ቀርቦ ስለ አባይ ያወራውን ሰምቼ ነበር።

 

“በአባይ ልማት ላይ በተለያየ መልኩ አስተዋፅኦ ልናደርግ ወንዙ ድርስ ሄደን ቃል ገብተን ነበር ነገር ግን ምንም አልሰራንም…” ብሏል ሰራዊት። እሰይ አፌ ቁርጥ ይበልልህ እንዲህ ሀቅ ሀቁን ስንነጋገር እንዴት ጥሩ ነው መሰለህ…?

 

ወዳጄ ከዚህ በፊት አንድ ጨዋታችን ላይ እነ ሰራዊት ፍቅሬ አባይ ላይ ሄደው ስለፈፀሙት መሀላ አውግተን ነበር። ታድያ ያኔ መሀላውን ለመፈፀም፤ ለጉዞ፣ ለውሎ አበል እና ለመሳሰሉት የወጣው ወጪ የትየለሌ ነበር።

 

እናም አርቲስቶቻችን ሄደው “አባይ ብረሳህ ሞት ይርሳኝ” ብለው ምለው ሲያበቁ፣ አሁን ርስት አድርገውት አንድ አመት ሞላቸው።

 

በዚህም ምክንያት ሰራዊት ፍቅሬ ሂሱን ውጧል። አዎ እኛም እንነግረዋለን ሰራዊት ሆይ የማስታወቂያ ገንዘብ ብቻ መዋጥ አግባብ አይደለም ሂስንም መዋጥ ይገባል። ደግመንም እንጠይቀዋለን፤ ህዝቡ “ሆ…” ብሎ ለአባይ መስጠት አለበት ብለኸን ነበር… አሁንስ መስጠት እና ስጡ ማለት እንዴት እንደሚለያዩ  ገባህ ይሆን…?

 

ሰራዊት ሆይ አሁንም “ህዝቡ መረባረብ አለበት” ብለህ አትፍረድ ከየት አምጥተን ነው የምንረባረበው? ችግር እየረበረበን እንደሆነ አታውቅምን? በማለት ከቦጨቅን በኋላ እንኳን እኛ ምስኪኖቹ አንተም መረባረብ አልቻልክም ብለን እናሽሟጥጣለን!

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ