የተባበሩ ጩኸቶች- ቦአዚዝ፣ መጅሊስ፣ መምህራን…
ተመስገን ደሳለኝ
ጀርመናዊው ካርል ማርክስ ‹‹አለምን ለሁለት የከፈለ›› የሚል ቅጽል ለማግኘቱ በምክንያትነት የሚነሱት የራሱን ሶስት የዳስ ካፒታል ቅፆች፣ ኮሚኒስት ማኒፌስቶ እና የ1844ቱ ማንስክሪፕትን ጨምሮ ሌሎቹ ስራዎች እስኪመጡ ድረስ የምድሪቱ የማህበረ-ኢኮኖሚ መዋቅር በካፒታሊዝም ላይ ይደመደማል የሚል ትንተና ሰለነበር ነው።
ካርል ማርክስ በተጠቀሱት ስራዎቹ የማህበረሰብን የእድገት ደረጃዎች ጋርዮሻዊ፣ የባሪያ አሳዳሪ፣ ፊውዳሊዝም እና ካፒታሊዝምን በመሰሉ አራት ተከታታይ ስርዓቶች ውስጥ እንደሚያልፍ፣ በመጨረሻም ካፒታሊዝም በሚያጋጥመው ውስጣዊ ተቃርኖ ሶሻሊዝም እንደሚወለድ ተነበዮአል።
እናም ድንገት የተከሰተው ካርል ማርክስ ‹‹Equal wealth of distribution (እኩል የሀብት ክፍፍል ወይም እኩልነት ይስፈን)›› የሚል አስተሳሰብ አመጣና አለምን አስደነገጠ፡፡ በሂደትም እነ ፌዴሪክ ኤንግልስ፣ ቭላድማሪ ኤሊች ኡሊያኖቭ ሌኒን… አዳብረውት ‹‹ሶሻሊዝም›› በሚል የዳቦ ስም ገበያ ላይ ዋለ። ይህንን ተከትሎም አለም ለሁለት ተከፈለ ‹‹በሶሻሊዝም እና በካፒታሊዝም›› (ምስራቅ እና ምዕራብ) በሚል ርዕዮተ-አለም ይሉሃል የፖለቲካ ተንታኞች።
መቼም ካርል ማርክስ ሚስትና ልጆቹን እያስራበ እነዚህን ሁሉ ሲፅፍ ‹‹አለምን ለሁለት ከፍዬ ታሪክ እሰራለሁ›› ብሎ አይደለም። (ህይወቱ ባለፈ ጊዜ እንኳ በቀብር ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት ስምንት ሰዎች ብቻ ናቸው)፤ ሌሎች ባለታሪኮችም ‹‹ታሪክ ልስራ› ብለው ተነስተው አይደለም ታሪክ የሰሩት። ሆኖም ኢ-ፍትሃዊነትን፣ ጭቆናን፣ መገፋትን፣ አድሎን፣ በደልን፣ ደህንነትን፣ ረሃብን… አንቀበልም ሲሉ የፈጠሩት ‹‹እምቢተኝነት›› ነው ሄዶ ሄዶ አዲስ ታሪክ የሰራው። በዚህም ባቡር ተሳፍረው ያለፉ በርካታ ባለታሪኮች አሉ። ከሀገራችንም እንደምሳሌ ማንሳት ካስፈለገ ጥቂቶቹ የህወሓት መስራቾች የሰሩትን ገድል ማየት ትችላለህ። ምንድር ነው የሰሩት? ብለህ ጠይቅ፣ የምታገኘው ግልፅ ነው። አዎ! ‹‹ተበደልን›› ወይም ‹‹የትውልድ አካባቢያችን ተበደለ›› ሲሉ አመፁ። ይህ አመጻቸውም መነሻ ምክንያት ስለነበረው ብዙዎች ተቀላቀሏቸው። ከ17 ዓመት ውጣ ውረድ በኋላም ‹‹እልፍ›› ሆኑ። ‹‹እልፍ ሆነናል›› ሲሉም እየዘመሩ መንግስት መሰረቱ፡፡ ይህ ትልቅ ታሪክ ነው። ለአላማ የመፅናታቸውን ተሞክሮ በሚገባ ከተከተለከውና በልቦናህ ካሰረፀከውም እመነኝ ተጠቃሚ ልትሆን የምትችልባቸው የዕድል ቁጥሮች ጥቂት አይደሉም።
ከሀገር ውጭ ደግሞ አንድ እንጨምር፡። ታሪኩ የቅርብ ነው። ቦታውም ሰሜን አፍሪካ ነው። የታሪኩ ባለቤት መሀመድ ቦአዚዝ የተባለ ቱኒዝያዊ ወጣት ነው። ይህ ወጣት በሀገሩ ቱኒዚያ ለዕለት እንጀራው የሚሆን ስራ አጣና ብዙ ተንከራተተ፡፡ ሌላው ቀርቶ በአነስተኛና ጥቃቅን እንኳን ሳይቀር የሚያደራጀው አጣ። ችግሩም ሲበረታበት አትክልት በጋሪ እያዞረ መሸጥ ጀመረ። ይህም ሆኖ እንቅፋት ገጠመው። በእርግጥ እንቅፋቱ የገበያ እጦት አልነበረም። ለዚህማ ‹‹ኢንሽ አላህ›› ከተማ ለከተማ በጋሪ የሚያዞረውን ፍራፍሬና አትክልት የሚገዛው አላጣም። እንቅፋቱ ከመንግስት ነው። ይኽውም የከተማው ደንብ አስከባሪዎች ጎዳና ላይ አትሸጥም ብለው ንብረቱን ነጠቁት። ይህን ጊዜም ቦአዚዝ ወሰነ። በህይወቱ የመጨረሻውን-አደገኛ የሆነ ውሳኔ። የውሳኔውም መንፈስ ሲጨመቅ እንዲህ የሚል ነው ‹‹ህግጋቱ የስርዓቱ ደጋፊና ወገን ላልሆነ ቱኒዝያዊ ኢ-ፍትሃዊ ነው። እናም ዛሬ እኔ ይህንን አሰራር ብቻዬን መለወጥ ባልችልም ድርጊቱን ለመቃወም ግን ራሴን ማጥፋት እችላለሁ››
ወስኖም ሲያበቃ ነዳጅ ገዛ። የገዛውን ነዳጅ እንደያዘ ወደ ከተማው አስተዳደር ቢሮ አመራ። ከቢሮው ፊት ለፊት ሲደርስ ቆመ። በነዳጅ የተሞላውን ኮዳም ክዳን አነሳ። ነዳጁንም በላዩ ላይ አርከፈከፈ። ገላው በነዳጅ ራሰ። ይህን ጊዜ የልብ ምቱ ጨመረ። የፍርሃት ግን አልነበረም። ኢ-ፍትሃዊነትን በመቃወም ራሱን ቤዛ ከማድረግ በወሰነው ቁርጠኛ ውሳኔ እንጂ። በእርግጥም የመጨረሻው ጊዜ እንደደረሰ ገብቶታል። ሆኖም አንድ ነገር እንደሚቀረው ያውቃል። ‹‹አላሃ-ጀነትን›› ያወርሰው ዘንድ የህሊና ፀሎት ማድረግና ከአምላኩ ጋር መታረቅ። እናም በለሆሳስ ፀሎቱን አደረሰ። ከአምላኩ ጋርም እንደታረቀ ባሰበ ጊዜ በእጁ የያዛትን ማቀጣጠያ ክብሪት ለኮሰ። ሰውነቱም እንደ ጧፍ ይነድ ጀመረ። በድንገትም አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት…እያሉ የተሰባሰቡ የአካባቢው ነዋሪዎች እሳቱን ለማጥፋት የአቅማቸውን ያህል ተረባረቡ። ማጥፋትም ቻሉ። እሳቱ ግን መጀመሪያውኑ ከቦኢዝዝ ገላ ላይ የቻለውን ያህል በልቶ ስለነበረ ሆስፒታል በደረሰ በሶስተኛው ቀን ህይወቱ አለፈ።
ይህንን ተከትሎም በርካታ ቱኒዚያውያን በመንግስታቸው ላይ ‹‹የተቃውሞ ህብረ ድምፅ›› አሰሙ። ጩኸታቸውም በረከተ፣ የቤን አሊም መንግስት በአፍሪካ እና በአረብ ሀገራት በ‹‹ጩኸት የፈረሰ›› የመጀመሪያው መንግስት ሆነ። ቱኒዚያም ከአምባገነን ስርዓት ነፃ ወጣች። የቦአዚዝ መንፈስ ግን መጮኹን አላቋረጠም። ድንበር ተሻግሮም ፈርኦኖቹ ጋ ደረሰ፤ አምባገነኑ ሆስኒ ሙባረክም በ18 ቀናት ጩኸት ተንኮታኮተ። ይህንንም ተከትሎ በአለማችን በየትኛውም ጫፍ ያሉ ‹‹ጉልቤ›› መንግስታቶች በዚህ የነፃነት መንፈስ መብረክረክ ያዙ። ከተብረክራኪዎቹም አንደኛው የሞሮኮው ፈላጭ ቆራጭ ንጉሰ ነገስት አገዛዝ ነው። ይህ አገዛዝም ተደነባብሮ “ህገ-መንግስታዊ ዘውዳዊውን ስራአት (Constitutional Monarchy)” ሊያሻሻል ቃል ገብቶ የ‹‹እፎይታ ጊዜ›› ተሰጠው (በእኛ ሀገር የእፎይታ ጊዜ የሚሰጠው የኮንድምንየም ቤት ለገዛ ብቻ ነው)
የሆነ ሆኖ የቦአዚዝ መንፈስ ጉዞውን ቀጠለ፤ ‹‹ሆ ብሎ ተነሳ›› እያለም ሊቢያ ገባ። ሊቢያውያኖችም ዳር እስከዳር ተነቃነቁ። ጋዳፊም በቦአዚዝ መንፈስ ተገፍተው የወጡ ‹‹ቁጡ›› ሊቢያውያኖችን በሀይል ለማፈን ያደረገው ሙከራ ሀገሪቱን በአንድ ጀንበር የጦር ቀጣና አስመስላት። አመፁም በረታ፡፡ የለውጥ ናፋቂዎቹ ጩኸትም ከቤንጋዚ እስከ ትሪፖሊ አስተጋባ። ከታሪክ እንደተማረነው ህዝብ ተሸንፎ አያውቅምና ከብዙ ትንቅንቅ በኋላ ትግሉ በህዝብ አሸናፊነት ሲርጥ ላይ ተደመደመ። ጋዳፊም ከአርባ አመት በላይ የቆየበትን ወንበር ከ‹‹ታላቅ-ውርደት›› ጋር አጣ። ጋዳፊ ከወንበር ማጣትም አልፎ በአሰቃቂ ሁኔታ ተሰቃይቶ ተገሎ-ተቀበረ። አሁንም የቡአዚዝ መንፈስ አላረፈም። ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ የመን፣ ሶሪያ እያለ… ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡ በእርግጥ የየመናዊያን ድምፅ ፍሬ አፍርቷል። የሶሪያውም እነሆ በደጅ ቆሟል።
ከዚህም ባሻገር ይህ የነፃነት መንፈስ ብዙ ሀገራትን እንቅልፍ ነስቷል። አንዳንዶቹ በየቀኑ ፖሊሲ በማውጣት እና ለህዝባቸው በየቀኑ ቀቢፅ-ተስፋ በመስጠት ስራ ላይ ተጠምደዋል። አረ ከዚያም አልፈው አንዳንድ ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች ላይ ወንጀል እየፈበረኩ እስር ቤት ማስገባት ሁሉ የጀመሩ አሉ።
…ለዚህም ነው ቦአዚዝ አለምን ከለወጡ ሰዎች ተርታ ተሰልፏል የምልህ፡፡ ካርል ማርክስ ‹‹የአለም ሰራተኞች ተባበሩ›› ብሎ ባመጣው አዲስ ርዕዮተ-አለም፣ አለምን ለሁለት እንደከፈለው ሁሉ የቦአዚዝ መንፈስም አለምን እየቀየረ ነው። የራሱ የካርል ማርክስንንም ሆነ የምዕራብዊያን የርዕዮተ-አለም መሀንዲሶችን ‹‹ድምዳሜ›› ሳይቀር አፋልሶታል። ለምሳሌ ምዕራቡም፣ ምስራቁም የአረብ ሀገራትን ህዝብ ‹‹ለለውጥ የማይመቹ፣ ለአብዮት የማይነሱ…›› ወዘተ እያሉ ብዙ ጽፈዋል። ይህ ደግሞ የመነጨው እስልምናን በቅጡ ሳይረዱ ‹‹እስልምና ለዲሞክራሲ፣ ለሰብአዊ መብት፣ ለሰው ልጅ እኩልነት፣ ለህግ የበላይነት…አይመችም›› የሚል ጨለምተኛ አስተሳሰባቸውን በሙሁራኖቻቸው በኩል ከ‹‹ባህል ወሳኝነት (Cultural Detriminzim)›› ኀልዮት ጋር እያያዙ እስከመተንተን በመደረሳቸው ነው፡፡ የነፃነቱ መንፈስ ግን እነዚህን ሁሉ የለወጠ ሆነ። ቱኒዚያ፣ ግብፅ፣ ሊቢያ፣ የመን… ብዙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የሚኖሩባቸው ሀገራት ናቸው። ነገር ግን ዛሬ የዴሞክራሲ አብዮት አካሄደው ወደ ሌላ የታሪክ ምዕራፍ እየተሸጋገሩ ነው፡፡ ሶሪያውያንም እያካሄዱ ያለው አብዮት፣ የፖለቲካ እንጂ የሃይማኖት አይደለም።
ሁላችንም እንደምናውቀው እስከ ቦአዚዝ መስዋእትነት ድረስ ‹‹አብዮት›› የሚተነትነውም ሆነ፣ የሚብራራው ከካርል ማርክስ የመደብ ጥያቄ አንፃር ብቻ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም የማርክሲስቶቹ አብዮት በደም የሚመጣ ነው። ዛሬ ግን ይህ ተቀይሮአል። አብዮት እንዲነሳ ጥልቅ የመደብ ቅራኔዎች መኖር እንደማያስፈልገው ሁሉ፣ ደም አልባ አብዮትም ማካሄድ እንደሚቻል የቡአዚዝ መንፈስ ከነስኬቶቹ ጮኾ ይናገራል። እነዚህ ሁኔታዎች ናቸው የቦአዚዝን ተፅዕኖ ከካርል ማርክስ ተፅዕኖ ጋር የሚያመሳስሉት። ደግሞም መስዋዕትነቱ በሚሊዮን ሳይሆን በቢሊዮን በሚቆጠሩ የአለማችን ለተገፉ፣ ለተበደሉ ዜጐች ተስፋ መሆኑን አትዘንጋ። ዘመኑም ካርል ማርክስ የጭቁኖች ነፃ አውጭ ተደርጎ እንደ‹‹መሲህ›› ይታየበት የነበረው አይነት ዘመን ላይ ነው ያለው-ሰላማዊ አብዮቱ… ይህ ታሪክ ከተሰራ ከአንድ አመት ብዙም የዘለለ አይደለም።
…በኢትዮጵያ ከህወሓት በተጨማሪ በርካታ ያልተሳኩ የ‹‹ፀረ-ጭቆና›› ድምፆች ተደምጠዋል፡፡ በትግራይ የቀዳማይ ወያኔ አመፅ፣ በጎጃም፣ በባሌ፣ በሲዳማ.. ተከታታይ የገበሬው የአመፅ ጩኸት በምድሪቱ ናኝቷል፡፡ እነዚህ ምንም እንኳ የከሸፉ ጩኸቶች ቢሆኖም ለሌላ አዲስ ጩኸት ግን መነሻ መሆናቸው አይካድም።
ይህ ማለት ግን በኢትዮጵያ የተሳኩ ጩቶች አልተከሰቱም ማለት አይደለም፤ ተከስተዋልና። ለምሳሌ የያ ትውልድ የ‹‹መሬት ላራሹ›› ጩኸት የአፄውን መንበር እስኪገፈተር ድረስ የተጓዘ ‹‹ውጤታማ ጩኸት›› ነው። የህወሓትም ጩኸት እንዲሁ የአምባገኑን ወታደራዊ መንግስት ግብአተ-መሬት ያስፈፀመ ታላቅ ጩኸት ለመሆን የበቃ ነው።
ዛሬ ደግሞ ከፀረ-መጅሊስ እስከ መምህራን በርካታ ጩኸቶች እየተሰሙ ነው፡፡ መጅሊስ ይውረድ፣ ገዳሙ ስኳር ፋብሪካ አይሆንም፣ ዝቋላ ሲቃጠል አየር ኃይሉ አልተባበረንም፣ የደሞዝ ጭማሪው ሙያችንን ዝቅ ያደረገ እኛንም ያወረደ ነው…. ብቻ እነዚህ ሁሉ ከጣሪያ በላይ የሆኑ ጩኸቶች ሆነዋል፡፡ በተለይም በየጁማው ‹‹አላህ ወክበር›› በሚል የምስጋና ድምፅ ታጅቦ ‹‹መጅሊሱ አይወክለንም›› የሚለው ጩኸት እየበረታ ነው።
‹‹የመምህራን ማህበር›› አይወክለንም የሚለው የመምህሩ ጩኸትም እንዲሁ አጋዥ የሚሻ ብርቱ ጩኸት ነው። እዚህ ጋ አንድ ገጠመኝ ልንገርህ። (የት መጽሐፍ ላይ እንዳነበብኩት አላስታውስም) ሆኖም ታሪኩ እንዲህ ነው። ጊዜው በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ነው። አንድ በእግዚአብሔር የማያምን /ኢ-አማን/ ጀርምናዊ ሂትለር ብዙዎችን ከጨፈጨፈ በኋላ እርሱ ጋር እንዴት እንደደረሰ የተረከው ነው፡፡ የጀርመናዊው ትርክት ይህ ነው፡-
‹‹የናዚ ወታደሮች መጀመሪያ ‹ጂብሲ›ዎችን ወሰዷቸው፡፡ እኔም ጂብሲ ስላልሆንኩኝ ዝም አልኩ፡፡ ቀጥለውም አይሁዶችን ወሰዱ፡፡ አይሁድ ስላልሆንኩኝም ‹አያገባኝም› ብዬ ቁጭ አልኩ፡፡ ከዛም ካቶሊኮች ጋር መጡ፣ አሁንም ካቶሊክ ስላልሆንኩ አያገባኝም አልኩ። ቀጥለውም ናዚን የማይደግፉ ፕሮቴስታኖች ጋር መጡ፡፡ ፕሮቴስታንት ስላልሆንኩ ‹ምን አገባኝ› ብዬ ተቀመጥኩ። ሆኖም በመጨረሻ እኔ ጋር መጡ፡፡ ነገር ግን ማንም የቀረ ስላልነበረ የሚጮኸልኝ አጣሁ›› …ድንቅ ምሳሌ።
ጥቂት ስለመምህራን..
ቡደሃ፣ ዛራቱስትራ፣ ኢየሱስ፣ ነብዩ መሀመድ… የመምህር ‹‹አናት››፣ የዕውቀት የመዐዘን ድንጋዮች እንደማለት ናቸው። ወይም ትጉህ እረኞች። መቼም መምህር ሲባል ቀድሞ ትዝ የሚሉን እነዚህ ናቸው። ደግሞም መምህር የሚመዘነው በእነርሱ የስብና መነፅር ነው። በሀገራችንም ቢሆን ሙያው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የተከበረ ነበር፤ በማህበረሰቡም የሚሰጠው ቦታ ከፍ ያለ ነበር። ለዚህም ይመስልኛል በሰርግ ላይ ሁሉ ሳይቀር የሚዘፈነው ዘፈን እንዲህ የሚል የነበረው፡-
የእኛ ሙሽሪት ኩሪ፣ ኩሪ
አገባች/ ወሰዳት/ አስተማሪ
እነሆም አስተማሪ ማግባት ክብርና ኩራት የሆነበት ያ ደጉ ዘመን እንደዋዛ ተረት ሆኖ አልፏል፡፡ እንዲህ ‹‹…ነበር›› እያልን የምንተርከው ሆኗአል ማለቴ ነው።
እውነትም እኮ የመምህር ደግ ዘመን ታሪክ ሆኖአል። ሌላው ቀርቶ በማህበረሰቡ ዘንድ፣ ለአስታራቂነትም ሆነ ለሽምግልና በግንባር ቀደምትነት የሚፈለገው መምህር ነበር። የዛሬን አያድርገውና፡፡ ተማሪ መምህሩ የሚገባበት ምግብ ቤት እንኳ ደፍሮ አይገባም። (ይህ ምንም እንኳ የተጋነነ ቢሆንም ተማሪ ለመምህሩ የነበረውን የአክብሮት ደረጃ ያሳያል። ወይም የመምህር እና የአስተማሪ ግንኙነት ምን ይመስል እንደነበረ ምስክር ሊሆን ይችላል።)
ዛሬ ያለውን የመምህርና የተማሪ ግንኙነት ብናይ በእጅጉ እናዝናለን። ‹‹ተማሪው መምህሩን ደበደበ›› የሚል ወሬ መስማት ተራ ነገር ሆኗአል። ስርአቱ ደግሞ ለዚህ አይነትቱ ‹‹የሞራል ውድቀት›› መዳለድሉን አመቻችቷል። ለምሳሌ የኢህአዴግ አባል የሆነ አንድ ተማሪ መምህሩ እያስተማረ፣ ተማሪዎችም በተመስጦ እያደመጡ ሳለ ከፈለገ ያለመምህሩ ፍቃድ ትምህርቱን አቋርጦ ይወጣል። ምን አልባት ተማሪው ትንሽ በሰል ያለ ከሆነ ግንለመምህሩ በጨዋነት እንዲህ ብሎት ይወጣል ‹‹ስብሰባ አለብኝ››
በንፋስ ስልክ የቲቪቲ ኮሌጅ በ2002ዓ.ም የትምህርት ዘመን ‹‹ቢዝነስ ኢኮኖሚክስ›› ያስተምር የነበረ አንድ መምህር የገጠመውን እንዲህ ሲል አጫውቶኛል፡-
‹‹የማስተምረው ቢዝነስ ኢኮኖሚክስ ነው። እናም ስለሀገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ ገቢ (GDP) ሳስተምር ‹ሀገሪቱ ደሃ ነች› ማለቴን በክፍል ውስጥ የነበሩ የኢህአዴግ ወጣት ሊግ አባላት ተማሪዎች ለኮሌጁ ዲን ይነግሩታል። ዲኑም ከምክትል አካዳሚክ ዲኗ ጋር በመሆን ቢሮአቸው አስጠሩኝ። ምክትል ዲኗ ቃል በቃልም ‹ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ጋር ለማሰለፍ ኢህአዴግ እቅድ አለው። ስለዚህም ተማሪዎቹን ኢትዮጵያ ደሃ ነች እያልክ መናገር የለብህም› ሲሉ ከገሰፁኝ በኋላ የቃል ማስጠንቀቂያ ሰጡኝ።››
ይህ ሁኔታ መምህሩ በመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚጠቀማቸው እያንዳንዱ ቃላት ምን ያህል እንደሚጨነቅ ያሳያል። ወይም መምህሩ ተማሪውን ምን ያህል እንደሚፈራው ያመላክታል። ይሰልለኛል ብሎ ይጠረጥረዋል። እራሱንም በፍርሃት ውስጥ ይከታል። እናም ቀስ በቀስ መታፈንን እየለመደው ይሄዳል። አፈናን አምኖ የተቀበለ መምህር ደግሞ ምን አይነት ተማሪ ‹‹ሊያወጣ›› እንደሚችል መገመት ይቻላል። ለዚህም ነው መምህራኖች ለተማሪዎች ስለሀገሪቱ ችግር በግልፅ የማይናገሩት። ምንአልባትም የሰሞኑ የመምህራን ጥያቄ በተቀናጀ መልኩ ሊቀርብ ያልቻለው የእነዚህ የእነዚህ ተፅኖዎች ድምር ውጤት ገፍቶት ሊሆን ይችላል።
የመምህር ፖለቲካ
በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ላይ መምህር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። ለምሳሌ ለታላቁ የየካቲት አቢዮት ፍንዳታ የመጨረሻው ‹‹ካምሱር›› የኢትዮጵያ መምህራን የካቲት 11 ቀን 1966 ዓ.ም. ‹‹ሴክተር ሪቪዩ›› በሚል ተዘጋጅቶ የነበረውን አዲስ የትምህርት ስርዓት በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸው ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው መምህራን ማህበር ነፃ፣ በራሱ የሚተማመን፣ ተለጣፊ ያልሆነ ነበረ። ለዚህም አስረጅ የሚሆነው አብዮቱ ተቀጣጥሎ ደርግ ከተመሰረተ በኋላም ‹‹ደርግ በጥቅማ ጥቅም ተታሎ አብዮቱን ትቶ ወደካምፑ ሊመለስ ይችላል›› የሚል ስጋት ተፈጠረ።
ይህን ጊዜም የመምህራን ማህበር ለደርግ እንዲህ የሚል ግልፅና አጭር ማስጠንቀቂያ ፃፈ፡-‹‹…በያዝከው ብትቀጥል አለንልህ፣ ብታፈገፍግ ግን አለንብህ››፤ እንዲሁም ደርግ ስልጣን ከያዘ በኋላ አምባገን አካሄዱን በመቃወም የተለያዩ መግለጫዎችን አውጥተዋል፤ወታደራዊው መንግስትም የመምህራን ማህበር ጽህፈት ቤትን ከቦ የማባዣ ማሽኖችን ለመውሰድ ሞከረ። ሆኖም አልተሳካለትም። ሙሉ ታሪኩንም ከክፍሉ ታደሰ ‹‹ያ ትውልድ›› ቅፅ 1 መፅሀፍ ላውርድልህ፡-
‹‹ወታደራዊ መንግስቱ ምን እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል መምህራኑ ቀድመው ተገንዝበው ኑሮ፣ ውሳኔዎቹን ያዘለው ጽሑፍ ሌላ ቦታ እንዲታተም አድርገው፣ ‹እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል› በማለት ጽሑፍ አወጡ። የጽሑፉ አርእስት ስለአይጧና ድመቷ ከተጻፈው አጭር ታሪክ የተወሰደ ሲሆን፣ አይጧ ከጉድጓዷ እስክትወጣ ድረስ ድመቷ አድፍጣ ትጠብቅ ኑሮ፣ አይጢት ብቅ ስትል ድመት ልትከመርባት ፈጥና ተንቀሳቀሰች። ሌላ መሸሸጊያ አዘጋጅታ ትጠብቅ የነበረችው አይጢት፣ ከሌላኛው ጉድጓድ አፋፍ ላይ ቆማ ‹እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል› በማለት አላገጠች።››
ይህ ነው የአንድ ማህበር የጥንካሬ መገለጫ። የደርግ ውድቀት ማግስት አካባቢም የነበረው የማምህራን ማህበር ጠንካራ ሊባል ይችል የነበረ ነው። መሪዎቹም እንደ ዶ/ር ታዬ ወልደሰማያት ያሉ መንፈሰ ፅኑና አቋም ያላቸው ምሁራኖች እንደነበሩ የትላንት ትዝታ ነው።
በአሁኑ ወቅት ያለውን የመምህራን ማህበር ማንሳት አልፈልግም። ይህ ማህበር የሚተነፍሰው በ‹‹ፖለቲካ ሳምባ›› ነውና። ለዚህ ማህበርም ትልቁ የስራ ድርሻ ከመምህሩ ላይ ወርሃዊ መዋጮ መሰብሰብ ነው። የመምህሩ እና የማህበሩ ግንኙነትም እዚህ ድረስ ብቻ ነው። ከዚህ በተረፈ የመምህሩ መብት ተናደ፣ተገነደሰ፤ መምህሩ የፓርቲ አባል አልሆንም ስላለ ከስራ ተባረረ ወይም የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊ ተበሎ ታገደ… ሲባል ማህበሩ ትንፍሽ ሲል አይሰማም።
መቼም ከዚህ በኋላ ማህበሩ እና መምህሩ በአንድ መስመር ይሰለፋሉ ማለቱ ከባድ ነው፡፡ የደሞዝ ጭማሪውን አስመልክቶም በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ መምህራኖች የያዙት አቋም የተቀናጃ ባይሆንም በሂደት ለውጥ ማምጣቱ አይቀርም።
የሰባ ሶስት ብር ጭማሪው ከ‹‹ቀልዳዊ አስተዳደር›› የመነጨ መታበይ ነው። በተቀረ ለቀልድ ለቀልዱማ በመምህሩ ገቢ ላይ ብዙ ቀልዶች አሉ። ለምሳሌ ያህልም እንጥቀስ። ቀልዱ የተሰማው ‹‹ትምህርት በሬዲዮ›› የሚባለውን የማስተማር ፕሮግራም ተንተርሶ ነው። እናም በሬዲዮኑ የሚያስተምረው መምህር ስለ‹‹ኢትዮጵያ የብር ኖቶች›› ክፍልፋይ እያስተማረ ነው። ትምህርቱንም በማስረጃ ለማስደገፍ ‹‹እባክዎ መምህር ለተማሪዎቹ የአንድ ብር ኖት ያሳዩአቸው›› አለ፤ መምህሩም እንደተባሉት አደረጉ። ቀጥሎም የሬዲዮኑ መምህር አምስት እና አስር ብሮችን በየተራ እንዲያሳዩአቸው መምህሩን ጠየቀ፤ መምህሩም አሳዩአቸው። በመጨረሻም ‹‹እባክዎ መምህር ለተማሪዎቹ የሀምሳ ብር ኖት እና የመቶ ብር ኖቶችን በየተራ ያሳዩአቸው?›› አላቸው። መምህሩም ከተማሪዎቹ ፊት ለፊት እንደቆመ፣ በተሰበረ ድምፅ ‹‹ተማሪዎች አሁን የተጠሩትን የብር ኖቶች የደሞዝ ዕለት አሳየችኋላሁ›› ሲል መለሰላቸው የሚል መራር ቀልድ አለ። እንግዲህ እያወራን ያለነው በደሞዝ ማግስት ሃምሳ ብር በኪሱ ስለማይኖረው መምህር ነው።
መቼም መንግስት በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ላለ መምህር ሰላሳ አንድ ብር እና ሰባ ሶስት ብር ጨምሬአለሁ ማለቱ ያው የተለመደ ቧልተኝነቱ ማሳያ ነው። ነገሩን አሰፋሪ የሚያደረገው ግን ከመምህሩ ችግር፣ ከመምህሩ ኑሮ፣ ከመምህሩ ትዳር…በተቀነሰ ገንዘብ የሚተዳደረው የመምህራን ማህበር ‹‹መምህሩ በጭማሪው ደስተኛ ነው›› ሲል በኢቲቪ ‹‹እርችት›› መተኮስ ነው።
የሆነ ሆኖ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ መምህራኖች እያቀረቡት ያለው ጥያቄ ህጋዊ ሲሆን፤ ጥያቄያቸው ይፈፀም ዘንድ እየተጓዙበት ያለውም መንገድ እንዲሁ ህጋዊ እና ሰላማዊ ነው። ከወራት በፊት በዳውሮ ዞን ‹‹ፍትህና ልማት›› የለም ሲል ራሱን ያቃጠለው የኔሰው ገብሬ መምህር መሆኑንም መዘንጋት የለብህም። ለእኔ መምህር ማለት የኔሰውና ሰሞኑን ድምፃቸውን በድፍረት እያሰሙን ያሉት መምህራኖች ናቸው።
ትውልድ የሚቀርፀው መምህር ነው፤ ሀገር የሚቀይረው መምህር ነው። በሀገራችን ከየትኛውም የስራ ዘርፍ ይልቅ በርካታ ዜጎች የተሰማሩበት የስራ ዘርፍም የመምህር ሙያ ነው። እናም መምህራኖቹ ይህንን የ‹‹ሰው ሀይል ካፒታል›› ይዘው ነው ጥያቄአቸውን በሰላማዊ መንገድ እያቀረቡ ያሉት። በእርግጥ ለጊዜው የመምህሩ ድምፅ ጎልቶ እንዳይወጣ ያደረገው ራሱ መምህሩ ለአመታት ‹‹ሎሌ›› ሆኖ የመቆየቱ ልማድ ነው። ዛሬ ግን ‹‹መምህር ሎሌ አይደለም!›› ያሉ ጥቂት መምህራኖች ወደ አደባባይ እየወጡ ነው። በእርግጥ በአደባባዩ ሌላም የለውጥ ድምፅ አለ፤ የፀረ-መጅሊስ ድምፅ። ይህ ብርቱ ድምፅ ነው፡፡ ማን ያውቃል? ነገ ደግሞ የፀረ-ሲኖዶስ ድምፅ ሊሰማ ይችል ይሆናል። ፓትርያርኩ ከሲኖዶሱም ሆነ ከምዕመናኑ የተግባቡበት ሁኔታ የለም። መቼም ካለጠፋ ቦታ ገዳምን ያህል፣ ያውም ዋልድባን ስኳር ፋብሪካ ለማድረግ መንቀሳቀስ…
ዘመኑ የለውጥ ዘመን ነው። ይህ የኮከብ ትንበያ አይደለም። በመሬት ያለ የፀረ ጭቆና፣ የፀረ-ድህነት… ድምፅ ነው።
እናም ከጀርመናዊ ኢ-አማኒ መማሩ አይከፋም። ‹‹…በመጨረሻም እኔ ጋ መጡ ማንም የቀረ ስላልነበረ የሚተባበረኝ አጣሁ!›› ካለው ማለቴ ነው፡፡ ሌላም ማጠናከሪያ ተመሳሳይ ታሪክ አለ፤ የጅቦች እና የበሬዎች። ነገሩ እንዲህ ነው፡-
በአንድ መስክ ላይ ወደተሰማሩ ሶስት በሬዎች ሁለት ጅቦች ይሄዳሉ። ሶስቱ በሬዎች ነጭ፣ ቀይ እና ጥቁር ቀለም ያላቸው ናቸው። ሁለቱ ጅቦችም ከበሬዎቹ ትንሽ እራቅ ብለው ጥቁሩን እና ቀዩን በሬ ይጠሩና ‹‹እኛ ከእናንተ ጋ ፀብ የለንም፣ ፀባችን ከነጩ በሬ ጋ ስለሆነ እናንተን አያገባችሁም›› ይሏቸዋል፡፡ በሬዎቹም ‹‹እኛን ካልነካችሁን አያገባንም›› ሲሉ ይመልሱላቸዋል። ይህን ጊዜ ጅቦቹ ነጩን በሬ ለሁለት ተጋግዘው በማጋደም ዘነጣጥለው በሉት። ጅቦቹ እንደገና ከጥቂት ቀናት በኃላ ወደእዛች መስክ ተመልሰው ይሄዱና ጥቁሩን በሬ ለብቻ ጠርተው ‹‹እኛ ከአንተ ጋ ፀብ የለንም፤ ፀባችን ከቀዩ በሬ ጋር ብቻ ነው ይሉታል››፤ ጠቁሩ በሬም ‹‹እኔን ካልነካችሁኝ እንደፈለጋችሁ›› ይላቸዋል፤ ጅቦቹም ወዲያውኑ ቀዩን በሬ ዘነጣጥለው በሉት፡፡ አሁንም ይህ ከሆነ ከጥቂት ቀናት በኃላ ጅቦቹ ወደእዛች መስክ ለመጨረሻ ጊዜ ይሄዱና ብቻውን ወደቀረው ጠቁሩ በሬ ይንደረደራሉ፤ ይህን ጊዜም በፍርሃት የተዋጠው ጥቁሩ በሬ ‹‹እኔን ላትነኩኝ ውል አለን እኮ›› ሲላቸው፣ ጅቦቹም እየሳቁ ‹‹አሁንማ ምን ውል ያስፈልጋል፣ያንግዜ እኮ የተዋዋልነው እንዳትተባበሩብን ነው›› አሉና ግራና ቀኝ አጣድፈው በሉት፡፡ ትብብር ለዘላለም ይኑር! ለዚህም ነው በቀዳዳ አጮልቀህ አትመልከት።
መመልከት ያለብህ በርህን ከፍተህ ወጥተህ ነው የምልህ።
…በፁሁፉ መጀመሪ ላይ ያነሳነው ካርል ማርክስ ‹‹ወዛደሮች ተባበሩ›› የሚለውን ብሂሉን በዚህ ዘመን አይን ካየከው እመነኝ ‹ተጨቋኞች ተባበሩ›› ወደሚል መፈክር ተቀይሯል። አዎን ኢትዮጵያውያን ጭቁኖች ተባበሩ። በእናንተ ህብረት ፊት መቆም የሚቻለው ማንም የለምና።
ፍትህ ጋዜጣ (አዲስ አበባ)



