መለስ አርገው ጋሜ፤ በምኒልክ ነፍስ (ሊያነቡት የሚገባ)
ፕሮ/ር ጌታቸው ኃይሌ
ፖለቲካዊ ጭምተኝነት አላዋጣም። ለአንድነት ሲባል ሲሰደቡ ዝም ማለት ጋሜን ከሚጓዝበት የጥፋት መንገድ አልመለሰውም። ራሱን እንዲታዘብ አልቀሰቀሰውም። እንዲያውም የኢትዮጵያን ጀግኖች እንደልቡ እንዲያንቋሽሽ አበረታትቶታል።
መች ይኸ ብቻ፤ ስድቡ የጣፈጠን ይመስል፥ ሚስቱ ለሌላ ስትዳርበት ሎጋው ሽቦ እንደሚዘፍን ሞኝ፥ ግኖቻችን ሲሰደቡ፥ ለኢትዮጵያ አንድነትና ክብር ደማቸውን ያፈሰሱ አባቶቻችንና እናቶቻችን ሲቀለድባቸውና ታሪክ የሌለን ሕዝብ ስንደረግ እናጨበጭባለን። "ስለፍቅር ሁሉም ይቅር" ማለት "ወንጀልህ ይደበቅልህ፤ አንተ በሠራኸው ወንጀል እኔ ልወንጀልልህ፤ ስላንተ እኔን ዐፈር ይብላኝ" ማለት አይደለም። "እስካሁን የሠራሁት ስሕተት ነበር" ብሎ የሚጸጸት ከማህላችን ካለ፥ ጓደኞቹ የነበሩ አገር ወዳድ ልጆች እንደሚያደርጉት፥ የሠራውን ረግሞ፥ ሐዘን ተሰምቶት ሲመለስ፥ "ከሰው ጥፋት፥ ከዕንጨት ንቅዘት አይጠፋም" ብለን በታላቅ አክብሮት እንቀበለዋለን። ግን፥ ታሪካችንን ለማውደም፥ "ወደጥፋት የገፋፋኝ የእገሌ በደል ነው" ማለት ከጸጸት ጋር አብሮ አይሄድምና አንቀበለውም። ታሪክ እንደሚነግረን ከሆነ፥ እገሌ ኢትዮጵያውያንን አስሰልፎ ኢትዮጵያን አገለገለ እንጂ፥ እነእገሌን አልበደለም። መለስ በአማራው ላይ ሲዘምት አማራ ነን የሚሉትም ሌሎችም የመሰላቸው በአማራው ላይ የዘመተ ነው። አይደለም፤ የዘመተው ያለፉት የሩቅና የቅርብ ጊዜ አፄዎቻችን ጠጋግነው በሰጡን ኢትዮጵያ ላይ ነው። አንድ ሰው መንገድ ለማውጣት ደን ቢመነጥር፥ ከደኑ ጋር ጠላትነት ያወጀው አላስኬድህ፥ አላሳልፍህ ስላለው ነው።
እነ መለስ አማርኛ ተናጋሪውንና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዩን የሚመነጥሩት ኢትዮጵያን ለማጥፋት በሚሞክሩበት ጊዜ አላስኬድ ስላሏቸው ነው። እነዚህ ኢትዮጵያውያን ሲመነጠሩ የምንቆጣው ኢትዮጵያን የማፈራረሱ ዓላማው ሲፈጸም ወለል ብሎ ስለታየን እንጂ፥ እንደነሱ አማሮች ስለሆንን ለአማሮች አድልተን አይደለም። ኦርቶዶክሶቹን ሁሉ መመንጠር ስለያዙ፥ የእነሱና የሌሎች ኢትዮጵያውያን ሁሉ መገፋት እኩል ያስቆጣናል። ታላቁ ቁጣችን ግን መለስና ደጋፊዎቹ ኦርቶዶክስ ያልሆነውን ሁሉ በኦርቶዶክሱና በሀገሪቱ የጥንት ቅርስ ላይ በርብርቦሽ እንዲነሡ ማወጁ ነው። ኤርትራን ከኢትዮጵያ የገነጠለ የየትኛው ሃይማኖት ተከታይ ነው? ዛሬ ኢትዮጵያን የሚገዛት ማነው? የጥንት ገዳማትን ለማጥፋት ቈርጦ የተነሣ ማነው? ለምንስ ነው? የዛሬ አራት መቶ ሰባ ዓመት ያቆመውን የሃይማኖት ጦርነት የሚቀሰቅሰው "ኢትዮጵያ ሆይ" እያሉ የሚጮኹትን የኦርቶዶክስ ምእመናንን ኃይል ለማዳከምና አገሪቱን እንደፈለገው ለመበዝበዝና ለማስበዝበዝ እንዲመቸው አይደለምን? የኦርቶዶክስ ምእመናን ብትንትናቸው ቢወጣ ስንቶችና እነማን እንደሚደሰቱ ያውቃል፤ እኛም ልብ እንበለው።
ከ1960ዎቹ ጀምሮ፥ ከለውጥ ፈላጊዎች ማህል ብዙዎቹ የሚያሰሙት ወቀሳ ኢትዮጵያን አደላድለውና ተንከባክበው የሰጡንን መሪዎችና ተመሪዎች አባቶቻችንንና እናቶቻችንን የአንድ ነገድ ሰዎችና ወንጀለኞች የሚያደርግ ነው። ታሪክ እንደሚነግረን፥ የአፄ ምኒልክ ሠራዊት የኢትዮጵያን አንድነት ለመመለስ በዘመተበት ጊዜ አዝማቹን ተከትሎ የዘመተውና እዚያው እዘመተበት ሀገር የቀረው ሠራዊት ከየቦታው የከተተ ሕዝብ እንጂ፥ የአንድ ነገድ ሕዝብ (አማራ ብቻ) አልነበረም። ሠራዊቱ መግባባት ስለነበረበትና ከሠራዊቱ አብዛኛው አማርኛ ስለሚገባው በአማርኛ ይነጋገር ነበር። ይኸ የሆነው ሌላ መግባቢያ ቋንቋ ስለሌለ ነበር እንጂ ሁሉም አማሮች ስለሆኑ አልነበረም። የአፄ ምኒልክን ታላላቅ የጦር መሪዎች (ደጃዝማች መሸሻን፥ ራስ ጎበናን፥ ደጃዝማች ባልቻን፥ ፊታውራሪ ብተ ጊዮርጊስን፥ ራስ መኰንንን፥ ራስ አሉላን) አንድ ያደረጋቸውና በሹመት ያሳደጋቸው ኢትዮጵያዊነት እንጂ፥ ነገዳቸው አልነበረም። አፄ ኃይለ ሥላሴም ማስተዳደሩን ስላላወቁበት ያመኗቸው ከዷቸው እንጂ፥ የኢትዮጵያን ሕዝብ እኩል ለማየት ወደኋላ ብለው አያውቁም ነበር።
ደብተራዎቹ ሲጽፉ "እንዳንተ ያለ እስከዛሬ አልተነሣም፥ ወደፊትም አይነሣም" ለማለት ባልደፍርም፥ ዳግማዊ ምኒልክን ያህል አስተዋይ ንጉሥ እስካሁን በኢትዮጵያ ላይ አልተነሣም። አንዳንዶቹ ጻድቆች ነበሩ፤ አንዳንዶቹ ሞት የማይፈሩ ደፋሮች ነበሩ፤ አፄ ምኒልክ ግን ዘዴኛ ነበሩ። ጻድቆቹ በጸሎት ሲታቀቡ፥ ደፋሮቹ የትም ወድቀው ሲቀሩ፥ አፄ ምኒልክ በኦሮሞቹ ወረራ ምክንያት አጥንቷ የተሰባበረውን ኢትዮጵያን ጠግነው፥ በሁሉም ዘንድ "እምየ" ተብለው፥ አርጅተው አፍጅተው አለፉ። ዜና ኅልፈታቸው ተፈርቶ ሳይሰማ ጥቂት ዓመታት አለፉ። "የንጉሥ መሞት ሲሰማ አልጋ ይፈርሳል" ይባል ስለነበረ፥ "የአፄ ምኒልክ ሞት የተደበቀው ብጥብጥ እንዳይነሣ፥ አልጋ እንዳይፈርስ ነው" የሚሉ አሉ። ተሳስተዋል። የመሞታቸው ዜና ወዲያው እንደሞቱ ያልተነገረው፥ "የእምየ" መርዶ ሕዝቡን እንዳያሰቅቀው ተፈርቶ በጭምጭታ እንዲያውቀው ታቅዶ ነው። እውነትም በጭምጭምታ አወቀው።
አፄ ምኒልክ ሥልጣናቸውን እስኪያረጋግጡ ድረስ እንደ ራስ ዘውዴ፥ እንደ ልጅ አበበ፥ እንደ ወይዘሮ ባፈና ያሉ ተቃዋሚዎች ነበሩባቸው። ወደኋላ ግን ሕዝቡ መሪነታቸውን የሚከበር ሆኖ ስላገኘው ሁሉም አክብሮት፥ አድንቆት፥ ወዶት ነበር። አፄ ምኒልክ የሀገር ውስጥ ጦርነት የሥልጣን ሽሚያ እንጂ፥ የጠላትነት ነገር እንዳይደለ ስለገባቸው፥ ያሸነፉትን እንደ ጠላት እያዩ መበቀልን ያለፈ አሳፋሪ ታሪክ አደረጉት--በመንግሥቱና በፖለቲካ መንትያው በመለስ ዜናዊ ዘመን እስኪመለስ ድረስ ማለቴ ነው። ታሪካቸው እንዲህ ይላል፤ "ጥፋት የተገኘበት ሰው ገንዘቡን ተወርሶ እጁን ታስሮ መሬቱ ይሸጥ ነበር። ነፍስ የገደለ ሰውም ራሱ ቢያመልጥ ዘመዱ እስከ ሦስት ትውልድ መሬቱ ይነቀል ነበር። ንጉሠ ነገሥት ግን …ከዋያት በመለስ አዋሽ ድረስ ያለውን የጋሻ መሬት ሁሉ እንደመንዝ ርስት አድርጌልሃለሁ። ምንም ብታጠፋ በገንዘብህ ተቀጣ እንጂ መሬትህ አይነቀል ብለው አዋጅ ነገሩ።"
አንዳንድ ኦሮምኛና ትግርኛ ተናጋሪዎች ስለአፄ ምኒልክ ጭካኔ ሲናገሩ ይሰማሉ፤ ይጽፋሉም። ግን ሁሉም የሚጽፉት ማስረጃ የሌለው፥ ከአፄ ምኒልክ ፍልስፍና ጋር የማይስማማ ፈጠራ ነው፤ ማስረጃ ካላቀረቡ አንዱንም አናምነውም። አንዳንድ ጊዜ ማስረጃችን "በአፍ ሲወርድ ሲዋረድ ከእኛ የደረሰ ታሪካዊ ድርጊት ነው" ይሉናል። ይኸ እውነትን ለማግኘት ለሚደረግ ጥረት አይጠቅምም። ለመርታት ቈርጦ የተነሣ ተከራካሪ የፈለገውን ያህል እየፈጠረና "ከእገሌ ሰማሁት" እያለ ሊጨምርበት ይችላል። አንዳንዶቹ ደግሞ፥ መሰሎቻቸው ዋሽተው የጻፉትን ለማስረጃ ያቀርባሉ። የዋሾ ማስረጃ እውነትን በሚፈልጉ ዘንድ ቦታ የለውም። ያይጥ ምስክሯ ድምቢጥ ነው። ይልቅስ አፄ ምኒልክ በአዋጅ ለማስቀረት ብዙ የሞከሩት ሰለባና "ሲዳምቲቲን" ሳይገድል ጠጉር አለመላጨት የማን ባህል እንደሆነም እባካችሁ ኦሮሞዎቹን ጠይቁልን።
ከላይ እንዳልኩት፥ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የአሸናፊ ጭካኔ ከምኒልክ ዘመን ሲደርስ ቆሞ ነበር። አንዳንድ የወያኔ ካድሬዎች ከአድዋ ድል በኋላ እግራቸውን የተቈረጡትን አስካሪዎች እያስታወሱ ለምኒልክ ጨካኝነት ማስረጃ ሊያረጓቸው ይፈልጋሉ፤ አያዋጣም። ጭካኔው የማይገባ ቢሆንም፥ እነዚህ ካድሬዎች ስለምክንያቱና ከዚያ ወዲህ በተደረጉት ብዙ ጦርነቶችና ድሎች ጊዜ ስላለመደገሙ አይናገሩም። የአድዋ ጦርነት ዘመን ንጉሡ ፍልስፍናቸውን በሥራ ላይ የሚያውሉበት ዘመን አልነበረም። የባርያ ንግድን የሚያቆሙበት ጊዜ እስኪመጣ ድረስ እንዳላቆሙት፥ እግር ቆረጣውንም ማቆም የሚችሉበት ዘመን ሲመጣ ወዲያው አቁመውታል። ተሸናፊውን ሁሉ "ወንድሜ፥ ልጄ" ብለው ይንከባከቡትና ወደግዛቱ ይመልሱት ነበር እንጂ፥ እንኳን እግሩን ሌባ ጣቱን አልነኩበትም።
ያለፈውን ለታሪክ እንተወው ብለን ነው እንጂ፥ ትችት ከተጀመረ ሁሉም መተቸት አለበት። ለምሳሌ፥ በ1870 ዓ.ም. ቦሩ ሜዳ ላይ በንጉሠ ነገሥቱ በአፄ ዮሐንስ ዋና ወምበርነት የሃይማኖት ክርክር ተድርጎ ነበር። የተረቱት መላሳቸው እንዲቆረጥ አፄ ዮሐንስ ሲፈርዱባቸው እንዲምሯቸው ሊቃውንቱ በብዙ ለምነዋቸው ነበር። ግርማዊነታቸው ግን አገር የከዱ ይመስል፥ "በፈጣሪዬ ላይ በድፍረት ያልሆነ ቃል ተናግረዋልና አልምራቸውም ብለው እጅ እግራቸውንና ምላሳቸውን አስቆረጧቸው።" አንዱ እዚያው እፊታቸው ሞተ። የሚገርመው፥ ኦሮሞዎች ነን ከሚሉት ማህል ደግሞ፥ አንዳንዶቹ አፄ ምኒልክን ሲወነጅሉ ማስረጃ አለመስጠታቸው ብቻ ሳይሆን፥ ባለውለታ ወዳጃቸው ሊያደርጓቸው የሚገባቸውን ንጉሥ መወን ላቸውና መጥላታቸው ነው።
አፄ ምኒልክ አንድ ሕዝብ እስኪያደርጓቸው ድረስ፥ በጉድሩ፥ በወለጋ፥ በአርሲ፥ በከፋ፥ በኢሉባቦር፥ በጨርጨር፥ በ ረር፥ በሸዋ የሚኖሩ ኦሮሞዎች አይተዋወቁም ነበር። እንኳን ሊተዋወቁ፥ አንዱ መኖሩን ሌላው አያውቅም ነበር። እንደሱማሌዎች የጎሳ ጥርቅሞች እንጂ አንድ ሕዝብ አልነበሩም። አንድ ጎሳ ጎረቤት ጎሳ እንደነበረው የሚያውቀው ከብት ሲዘራረፉ ነው። ዛሬ ኦሮሞዎች፥ "እኛ ኦሮሞዎች" ከማለታቸው በፊት፥ አንድ አድርጎ "እኛ ኦሮሞዎች" ለማለት ያበቃቸውን ምኒልክን ማመስገንና "ነፍሳቸውን አድባራችን ትማር" ማለት ይገባቸዋል። ከወቀሱም ወደኬንያ የተወሰዱትን ኦሮሞዎች ከእንግሊዝ እጅ ሳያስጥሏቸው በመቅረታቸው መሆን አለበት። እውነቱን ለማወቅ የፈለገ፥ ቢያንስ ቢያንስ አዛዥ ተክለ ሥላሴ ጢኖ የጻፉትን "የአፄ ሱስንዮስን ታሪክ"፥ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጂራ የጻፉትን "የጎጃም ታሪክ"፥ አቶ ይልማ ደሬሳ የጻፉትን "የኢትዮጵያ ታሪክ"፥ አባ ባሕርይ የጻፉትን "ዜናሁ ለጋላ"ን፥ እኔ ያሳተምኩትን "የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፥ ኦሮሞችን ከተመለከቱ ሌሎች ሰነዶች ጋራ"ን በጥሞና አንብቦ መረዳት ይችላል።
አንዳንዶቹ፥ "ታሪካችንን ደብተራ አይጽፈውም" ይላሉ። እነዚህ ኦሮሞና አማራ የሚባሉ ደራሲዎች የጻፉት ካልጣማቸው፥ ቃልቻ የጻፈውን እንየው። እውነት ከሆነ እንቀበለዋለን። እነዚህ የጠቀስኳቸው ሰነዶች በአንድ በኩል፥ ስለኢትዮጵያ መንኮታኮትና ስለ ቅርሷ መውደም መርዶዎች ስለሆኑ፥ ያስለቅሳሉ። በሌላ በኩል፥ ስለትንሣኤዋ ብሥራት ስለሆኑ፥ ያስደስታሉ። በመጠኑም ቢሆን ለማብራራት ያህል፥ ገራችን በቅርብ ታሪኳ በጹናሚ (tsunami) ደረጃ የሚገመቱ ሁለት አደጋዎች ደርሰውባታል፤ አንዱ የግራኝ መሐመድ የሃይማኖት ወረራ ሲሆን፥ ሁለተኛው የኦሮሞች የኢኮኖሚ ወረራ ነው። የግራኝ ወረራ ጂሃድ ስለነበረ ያተኰረው ገዳማቱንና አብያተ ክርስቲያናቱን በእሳት ማጋየት፥ ካህናቱን አንገታቸውን በሰይፍ መቅላት ነበር። የክርስቲያኖቹን አገዳደል የግራኝ መሐመድ ታሪክ ጸሐፊ ሲያብራራው፥
"ካፊሩ (ክርስቲያኑን ነው) አንገቱ በሰይፍ ሲቀላ፥ ነፍሱ እየተቅለበለበች ገሃነም ገባች" እያለ መዝግቦታል። "መቸም ሰው በዚያ ጊዜ ባይገደልም፥ መሞቱ አይቀርም ነበር" ቢባልም፥ ክርስትና ኢትዮጵያ ከገባበት ከአራተኛው መቶ ዓመት ምሮ የተከማቹት ገና ማንነታቸው እንኳን ሳይታወቅ የቀሩ፥ የዓለም ታሪክ ሊኖርባቸው የሚችሉ ብዙ መጻሕፍት ከገዳማቱ ጋር አብረው የእሳት ራት ሆኑ። መጻሕፍቱ ማንነታቸው ሳይታወቅ ተቃጠሉ ከተባለ ኖረው ለመቃጠላቸው ማስረጃችን ምንድነው? አንደኛ፥ ከተረፉት አንዳንድ መጻሕፍት ኅዳግ ላይ የመጻሕፍት ስም ተዘርዝሮ ይገኛል። ከተዘረዘሩት ውስጥ አንዳንዶቹ ዛሬ የሉም። ሁለተኛ፥ በተረፉት መጻሕፍት ውስጥ ከሚጠቀሱት መጻሕፍት ውስጥ አንዳንዶቹ ዛሬ የሉም። የት ሄዱ? ለጥፋታቸው ዋናዎቹ ተጠርጣሪዎች ሁለቱ ጹናሚዎች ናቸው።
ወደ ሁለተኛው ጹናሚ ልሂድ፤ የግራኝ ጦርነት በግራኝ መሞት ሲያቆም፥ ኢኮኖሚያቸውን ከብት ማርባት ላይ የመሠረቱ የኦሮሞች ጎሳዎች የከብት መንጋቸውን በአገሪቱ ላይ ከደቡብ እስከ ሰሜን ለቀቁባት። መንጋው ወደፊት ሲዘምም፥ ከምድር የሚነሣው አቧራ ፀሐይዋን ይሸፍናት ነበር። የገበሬውን ሰብል ከአንበጣ ጋር እየተሻማ ላፍ አደረገው። የግራኝ ሠራዊት ያደከመው ሕዝብ ለረኀብ ተጋለጠ፤ አዲሱን ኃይል መቋቋም አልቻለም። ከአንድ ቦቅሰኛ ጋር ዓሥራ አምስት ዙር የተቧቀሰ ቦቅሰኛ ከትኩስ ቦቅሰኛ ጋር አንድም ዙር ሊቧቀስ አይችልም። ነገሥታቱ እድሜያቸውን ሙሉ በዘመቻ ቦቅስ ቢያሳልፉትም፥ የኦሮሞዎችን አገር ማውደም ሊመክቱ አልቻሉም። ከግራኝ የተረፈው የሥልጣኔ ቅርስ ወደመ። አብያተ ክርስቲያናት የጥጃ ማደሪያ ሆኑ። በሀገሪቷ ላይ የደረሰው የቅርስ መውደም ብቻ ሳይሆን፥ ገዢዎቹ ከቀይ ባሕር እስከ ጥቁር ዓባይ አንድ ሀገር ያደረጓትን ራሷን ኢትዮጵያን በታትነው የጎሳዎች ከብት መዋያ አደረጓት። አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ እንደመዘገቡት፥ ገሪቱ እንደገና አንድ የሆነችውና ሰላም የሰፈነባት በምኒልክ አመራርና በጎበና ዳጨ አዝማችነት ነው።
አንዳንድ ኦሮሞች "አፄ ምኒልክ ዘመቱብን" እያሉ ያጒረመርማሉ። የሚደግፏቸው የውጪ ጸሐፊዎች አላጡም። ኦሮሞዎቹ በዓሥራ ስድስተኛው ምእት ዓመት ማህል ኢትዮጵያን መውረራቸው፥ ምኒልክና ሠራዊታቸው በዓሥራ ዘጠነኛው ምእት ዓመት ኦሮሞዎች በወረሩት መሬት ላይ መዝመታቸው የማይካድ ታሪክ ነው። ግን ወረራው ገር ማጥፋቱን፥ ዘመቻው ገር ማቅናቱን መርሳት የለብንም። የአያቶቻቸው/ የአያቶቻችን ወረራ የሰባበራትን ሀገር ለመጠገን የተሻለው መላ ምን መሆን ነበረበት? አፄ ምኒልክ "በሰላም ግቡ" ሲሏቸው አንዳንዶቹ "እሺ" ሲሉ ሌሎቹ "እምቢ" አሉ። ለምን እምቢ አሉ? "ኢትዮጵያ ውስጥ አብረን በሰላም እንኑር" አሏቸው እንጂ፥ "ላደረሳችሁት ጥፋት አፈላማ ከፍላችሁ፥ ከብታችሁን እየነዳችሁ ወደመጣችሁበት ተመለሱ" አላሏቸውም። ሁለተኛም፥ የ ገሪቱን አንድነት ለማስከበር አፄ ምኒልክ ዘዴያቸው ረድቷቸው ቀናቸው እንጂ፥ ከእሳቸው በፊት የነበሩ ሌሎቹ ነገሥታት ያላደረጉትን አላደረጉም። እነዚያ ተሳናቸው፤ ጥበበኛው አፄ ምኒልክ ስላወቁበት ቀናቸው። ውንጀላው ስለቀናቸው ብቻ ነው። ምኒልክ ተነሥቶ ባያነሣ ጋሻ፥ እንግሊዞች ገራችን እየተቈራረጡ የሱዳንና የኬንያ መስፋፊያ ያደርጓት ነበር።
ስለ አጤ ምኒልክ ጥበበኛነት የሚወራው በከንቱ አለመሆኑን ከሚያስረዱ ድርጊቶች ለጊዜው ትዝ ያሉኝን አጠር አጠር እያደረግሁ ላንሣቸው።
አንደኛ፤ የአፄ ቴዎድሮስ እስረኞች መቅደላ ላይ ሲማቅቁ ልጅ ምኒልክና አጃቢዎቻቸው ምንም ሳይነካቸው አመለጡ።
ሁለተኛ፤ መኳንንቶቻቸው "እንዋጋለን እንጂ ለአፄ ዮሐንስ አንገብርም፤ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ከተባሉ በኋላ፥ ንጉሠ ሸዋ መባልዎን አንቀበልም" ሲሉ፥ እንግሊዞች ለአፄ ዮሐንስ የሰጧቸው መሣሪያ ምን ያህልና ምን ዓይነት እንደሆን ስለሚያውቁ፥ ለጊዜው መገበርን መረጡ። አፄ ምኒልክ ሊያሸንፉት የማይችሉትን፥ ለማሸነፍ ጊዜና ዘዴ ይፈልጉለታል እንጂ፥ ጦር አይገጥሙትም።
ሦስተኛ፤ አፄ ዮሐንስ በንዴት ደርቡሾች ላይ ሲዘምቱ፥ አፄ ምኒልክ ከድርቡሾች ጋር በእንግሊዞች ላይ የጋራ ግምባር ፈጠሩ። እንግሊዞች ሪር አድሚራል ሂወትን ልከው አፄ ዮሐንስን እንደቀለዱባቸው፥ ሬነል ሮድን ልከው አፄ ምኒልክን ሊቀልዱባቸው ቢሞክሩ አልተሳካላቸውም። አምባሳደር ሬነል ሮድ አፄ ምኒልክ እንደቀለዱበት ያወቀው ወደመጣበት ከተመለሰ በኋላ ነው። ግን እዚያው ባለበት ጊዜ የውል ውይይት ሳይጀምሩ ከማን ጋር እንደሚዋዋል በምልክት ሲያስጠነቅቁት፥ "ጣሊያን ምጽዋን እንድትይዝ ለምን ጋበዛችኋት?" አሉት። ሲሰማ ክው አለ። ምንም ከማያውቅ የዋህ ሰው ጋር የሚነጋገር መስሎት ነበር።
የመጣው ኢትዮጵያ ከሱዳን ደርቡሾች ጋር እንዳትስማማ ቃል እንዲገቡለት ነበር። የማይከበር ቃል ያለው እንግሊዝ አገር ብቻ መስሎታል። "ግዴለህም፥ ደርቡሾች የሃይማኖታችን ጠላቶች ናቸው። እኛ እንደናንተ ክርስቲያኖች ነን" ሲሉትና በሰማው ሲደሰት፥ የደርቡሽ መልእክተኞች ከጓዳ ሆነው ይስቁ ነበር። እንግሊዝና ፈረንሳይ በኮሎኒ ሽሚያ ጊዜ በማህላቸው ግጭት እንዳይነሣ ሁለቱ ገሮች መስማማታቸውን ንጉሡ ስለሚያውቁ፥ የሱዳኖቹ መልእክተኞች ከመመለሳቸው በፊት የሰጧቸው ምክር፥ "በምሥራቅ (ከግብጽ) እንግሊዞች ሲመጡባችሁ፥ የፈረንሳይ ባንዲራ ሰቅላችሁ ጠብቋቸው። በምዕራብ (በፋሹዳ) ፈረንሳዮቹ ሲመጡባችሁ የእንግሊዝ ባንዲራ እያውለበለባችሁ ተቀበሏቸው" የሚል ነበር።
አራተኛ፤ የአድዋ ጦርነት እንደሚነሣ ቀደም ብለው ስላወቁት፥ ከአዲስ አበባ እስከ አድዋ ድረስ በሚሰፍሩበት ቦታ ሁሉ ለሠራዊታቸው የሚሆነውን ስንቅ ቀደም ብለው አከማችተው ነበር።
አምስተኛ፤ ጥንት የክርስቲያን ገሮች በቅድስት ገር በኢየሩሳሌም ቦታ ሲይዙ ኢትዮጵያም ይዛ ነበር። ግን እዚያ የሚኖሩ መነኮሳት ሕይወት ነገሥታቱን ሁል ጊዜ ያስቸግር ነበር። በተለየ መንገዱ በሙስሊሞች ኃይል ስለተያዘ እንኳን ገንዘብ ሊላክላቸው ጳጳስ ከግብጽ የሚመጣው እንኳን በስንት ጭንቅ ነበር። አርቆ አስተዋዩ አፄ ምኒልክ መነኮሳቱን በወለዱ ሊያኖራቸው የሚችል ገንዘብ ከባንክ አስቀመጡላቸው። መኳንንቶቻቸውም እዚያ ቤት እንዲያሠሩ መክረዋቸው፥ የሠሯቸው ቤቶች እስከዛሬ ይከራያሉ።
ስድስተኛ፤ የአጼ ምኒልክ ችሎታ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የጦር ስልት ዐዋቂም ነበሩ። ለምሳሌ፥ አድዋ ላይ የኢጣልያን የጦር ሠራዊት ከምሽጉ ውስጥ እንዳለ ሊገጥሙት አልፈለጉም፤ የመሸገን ጠላት ለማሸነፍ እንደማይቻል በአፄ ዮሐንስ ላይ ከደረሰው ሽንፈት ስለተማሩ፥ እስኪወጣ ጠበቁት። ሲወጣ ልብ-ራሱን አሉት። ሁለተኛም፥ ንጉሡ ጦርነት እንደ ቸዝ ጨዋታ መሆኑን ያውቁ ነበር። በቸዝ ጨዋታ ንጉሡ ከሞተ፥ ሠራዊቱ እንዳለ ቢሆንም፥ ንጉሡ የሞተበት ተጫዋች ተሸናፊ ይሆናል። ኢትዮጵያ ከሱዳን ደርቡሾች ጋር ባደረገችው ጦርነት ያገኘችውን ድል ያጣችው ንጉሡ አፄ ዮሐንስ ጦሩን ስለመሩ ነው። ንጉሡ ተመትተው ሲሞቱ፥ ሠራዊታችን ተበተነ። አፄ ምኒልክ ግን የአድዋን ጦርነት ያዋጉት አደጋ በቀላሉ ከማይደርስባቸው ሰዋራ ቦታ ላይ ሆነው ነበር። ሆኖም፥ ከኢትዮጵያ ብዙ ሰው ሞቷል። ግን ከሞቱት ውስጥ አንዱ ንጉሡ ቢሆኑ ኖሮ፥ የተሸነፈው ጠላት መሸሹን ትቶ ተመልሶ መጥቶ ድላችንን ይነጥቀን ነበር፤ አድዋም ሌላዋ መተማ ትሆን ነበር። ግን በንጉሡ የጦር ስልት ዐዋቂነት ተሸንፎ ሸሸ። የተንኮታኮተችውን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ሌሎቹ ሲሳናቸው አፄ ምኒልክን የቀናቸውም በዚሁ በዘዴኛነታቸው ነው።
አንዳንድ የትግራይ ጸሐፊዎች አፄ ምኒልክን ሸዌ፥ አፄ ዮሐንስን ትግሬ በማድረግ (አፄ ዮሐንስም አፄ ምኒልክም የሁላችን ንጉሦች መሆናቸውን ከአእምሯቸው እንዳይገባ መግቢያውን ጥርቅም አርገው ዘግተው)፥ "የናንተ አፄ ምኒልክ የነገሡት የኛን አፄ ዮሐንስን ሸውደው ነው" ይላሉ። ይህ አነጋገር ታሪክ ጸሐፊ ነኝ ከሚል ሰው ብዕር ከወጣ ተንኮል ነው። የማይሸውድ ፖለቲከኛ የት አገር አለ? እንግሊዝ ወይስ ፈረንሳይ አገር? አፄ ዮሐንስስ ቢሆኑ የነገሡት እንዴት ነው? ባላምባራስነት የሾሟቸውን አፄ ቴዎድሮስን ሸውደው አይደለም እንዴ? የእኛ የሆነውን ሁሉ የእኛ ብሎ በመቀበል ከአድላዊነት፥ ከጎጠኝነት፥ ከቅናት በሽታ መፈወስ ይቻላል።
ወጣት ጋሜ ሆይ፤ መለስ አርገው!! ነገሩ ሁሉ በመጠኑ ብቻ ሳይሆን፥ በልኩም በትክክሉም ይሁን። በሀገራችሁ፥ በታሪካችሁ፥ በሃይማኖታችሁ፥ በማንነታችሁ የሚዘመትባችሁ አገር ወዳድ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ደግሞ የተስፋ ብልጭታ ለማይታይበት ነገር ጭብጨባችሁን ገታ አድርጋችሁ፥ ገራችሁን፥ ቅርሳችሁን፥ ታሪካችሁን፥ ማንነታችሁን ለማዳን የተዘመተባችሁን አዲሱን ዘመቻ በአንድነት መክቱ። ከሆነ፥ የሚያዋጣው ያለፈውን ለታሪክ ትተን፥ በሰላምና በብልጽግና አብሮ ለመኖር ሁላችንም (እስላም፥ ኦርቶዶክስ፥ አረሚ ሳንል) በአንድነት በዛሬው የጋራ ጠላት ላይ አብረን መነሣት ነው። አህዮች እንኳን ጅብ ሲመጣባቸው ከመበላት የሚድኑት ኋላ-ቀርነት አስተሳሰባቸውን ትተው፥ በኋላቸው በኩል ተገጣጥመው በጋራ ሲመክቱ ነው። ከሁሉም ጋር መተባበር ካልተቻለ ግን፥ ለሀገሩ፥ ለቅርሱ የሚቆጨው ክፍል የተስፋ ብልጭታ በማይታይበት ጥረት ላይ ጊዜ ማሳለፍን አቁሞ፥ ዘዴውን ከአህያም ቢሆን ተምሮ፥ አስፈላጊውን ማድረግ ነው። ከሌሎቹ ውስጥ ብዙዎቹ ወያኔ ውለታ እንደዋለላቸው ስለሚቆጥሩት፥ ሌሎቹ ደግሞ ፍላጎታቸው ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ስለሆነ፥ ደግሞ ሌሎቹ ሃይማኖታችን ፖለቲካ ውስጥ አያስገባም ስለሚሉ፥ ምንም ብትለማመጧቸው ኮከባቸው ከኮከባችሁ ጋር አይገጥምም። የቤተ ክርስቲያኗ መሪም በወያኔ ካድሬነት ምእመናኑን ስለከዳ፥ የ ገር ማዳን መስቀሉን የምትሸከሙት ብቻችሁን ነው። ሆኖም ብዙኃን ናችሁ። ብዙኃን የሚጠቁት ኅብረት ሲያጡ ነው። "አንድ አርገን" እያላችሁ የምትጸልዩ ሁሉ የአንድነትን ጥሪ ካልሰማችሁ፥ ጸሎታችሁ አይሰማላችሁም። ቃሌን ሰምታችሁ የምትችሉትን ሳትሠሩ አትጨቅጭቁኝ ብሏል።



