ደራሲና ገጣሚ በእውቀቱ ስዩም

አለማየሁ ገላጋይ ‹‹የሁለት ስልጡን ህዝቦች ወግ›› የተባለች ኩርማን መጣጥፍ ባለፈው ሳምንት ፍትህ ላይ አውጥቶ አነበብሁ። በመጣጥፏ ውስጥ ኢትዮጵያንና ጃፓንን ባንድ የዘመን ምዕራፍ ላይ ያወዳድራል። ዳግማዊ ቴዎድሮስን ሙትሱሂቶ ከተባለው የጃፓን መሪ ጋር ያነፃፅራል። በመጨረሻ በጃፓን አምሳል ሳንሰለጥን መቅረታችን አስቆጭቶት ሁኔታችን ‹‹..ነባሩን ኢትዮጵያዊ ስልጣን ጥሎ ቻይናዊ እድገትን አንጠልጥሎ ሆኗል›› በማለት ወጉን ይዘጋል።


የኔ ፅሁፍ አላማ የዓለማየሁን ሐተታ መጠራጠር ነው፡፡ ብዙዎቻችን እንደሰማነው ፈር ቀዳጅ ሊቃውንት ተብለው የሚታወቁት እነ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ፣ ገብረ እግዚአብሔር ጊላማርያም፣ ተክለ ሐዋርያት ተክለማርያም፣ በኋላም ከበደ ሚካኤል ኢትዮጵያን በጃፓን መንገድ ለመግፋት ሞክረው ነበር፡፡ የዛሬ ልጅ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ‹‹ሙከራቸው ለምን አልተሳካም?›› የሚል መሆን አለበት፡፡ ምናልባት ጃፓንን እንደ አርአያ (ሞዴል) ማጨት በራሱ ስሕተት ሳይሆን ይቀራል?


በቀደምቶቻችን መፍረድ አይቻልም፡፡ ጃፓን ከትቢያ ተነስታ ያስመዘገበችው እመርታ በጣም አስደናቂ በመሆኑ ሊቃውንቶቻችንን ቢያማልል አይገርምም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላለ- ከመንገድ ላይ ምኝታ አርፍዶ የተነሣ አገር ስልጣኔን ሀ ብሎ ከመጀመር ይልቅ ተጠናቆ የተገኘውን መኮረጅ አዋጭ ነበር።


ኢትዮጵያን በጃፓን አምሳል ለማሰልጠን ያለሙ ሊቃውንት ሁለቱ አገሮች ተመሳሳይ ጠባይ አላቸው ብለው የሚያምኑ ነበሩ፡፡ ይህንን እምነት አለማየሁ ይጋራዋል፡፡ የዛሬ ሳምንት ከፃፈው፣ ልጥቀስ።


‹‹ኢትዮጵያና ጃፓን በስልጣኔ ረገድም መንትያ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ የሁለቱም ነባር ስልጣኔ ካውሮፓ ስልጣኔ የተለየና መንፈሳዊነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ Theocentric ይሉታል፡ ፡ እንደ አውሮፓ ስልጣኔ በቁስ ላይ የተመሰረተ የሰውን ልጅ ማዕከል ያደገረ Anthrocentric አይደለም››


በበኩሌ ከዚህ ሐተታ ጋር መስማማት ያስቸግረኛል፡፡ የጃፓኖች ገናና ሐሳቦች ቡዲዝምና ኮንፊሽየሳዊነት መንፈሳዊነት ባያጡም እግዚአብሔርን ማዕከል ያደረገ Theocentric በሚለው ድንኳን ውስጥ አይቀመጡም፡፡ ጃፓኖች ብዙ እሴቶችን ከኮንፌሽየስ ስለወሰዱ ኮንፊሺየሳዊነትም በምድራዊነት ላይ አጥብቆ ስለሚያተኩር ስልጣኔያቸው በቁስ ላይ አልተመሰረተም የሚለው አያሳምንም።


አለማየሁ ያውሮፓ ስልጣኔን ከኢትዮጵያ ስልጣኔ ጋር የሰሜንና የደቡብ ያክል የሚያቃርነው ዕጓለ ገብረዮሐንስ ያቀረቡትን ሐሳብ ያለ ሂስ ስልተቀበለው ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ የኢትዮጵያ ነባር ባህል ስለተፈጥሮ ባጠቃላይ ስለሰው ልጅ በነጠላ ባለው አሉታዊ አስተያየት እንዲሁም ለግለሰባዊነት በሚሰጠው የተጋነነ ቦታ ከሩቅ ምስራቅ ይልቅ ወደ አውሮፓ ጠጋ ይላል፡፡ የሚለየን ነገር ቢኖር አብረን ሄደን ሄደን፣ ብርሃነ ሕሊና (ኢንላይትመንት) የተባለው ያመለካከት ፌርማታ ላይ ሳንደርስ መውረዳችን ይመስለኛል፡፡ በጥንታዊት ኢትዮጵያና በጥንታዊት ጃፓን መካከል ከነበሩት ልዩነቶች አንዱ ስለለውጥ የነበራቸው አስተያየት ነው፡፡ ቀዳሚውን ማክበር አዲሱን መጠራጠር የኢትዮጵያውያን ጠባይ ነበር፡፡ ካዲሱ ብልሃት አሮጌውን ግራ መጋባት መምረጥ፣ ከማያውቁት መልአክ፣ የሚያውቁትን ሰይጣን የሙጥኝ ማለት ብሔራዊ መለዮ ነበር፡ ፡ የዚህ ምክንያት ግልፅ ነው፡፡ በአገራችን ታሪክ በሰላምና በሲሳይ የተደመደመ ለውጥ ብዙ አልተመዘገበም፡፡ እንግዳ ሆኖ ገብቶ ባላንጣ ሆኖ የማያድር ባእድ ብዙ አልታየም፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ ለውጥን ከጥፋት እንግዳን ከጠላት ጋር የሚያቆራኝ ብሄራዊ አእምሮ ሳይፈጠር አልቀረም።


ባገራችን የመኪና ወፍጮ ሲገባ እናቶቻችን ጋኔን ይፈጭበታል በማለት በድንጋይ ወፍጮአቸው ላይ ረጉ፡፡ ይህንን የተመለከቱ ተራማጅ ነን ባዮች በእናቶቻችን ‹‹አላዋቂነት›› ሲሳለቁ ተመስጌን ገብሬ የተባለ ፀሐፊ ስላቁን ከንቱ ለማድረግ ተነሳ፡፡ እንደ ተመስጌን እይታ ከሆነ፣ በጊዜው የመኪና ወፍጮ ባለቤት የሆኑት ፈረንጆች የባላገሮችን ዱቄት ከቋት ላይ ይሰርቁ ነበር፡፡ ባላገሮች ይህንን ቢያውቁም ፈረንጆችን ሌባ ብሎ ከማሳቀቅ በጋኔን ላይ ማሳበብ ጥሩ የማህበራዊ ዘዴ ሆኖ አገኙት፡፡ ስለዚህ እናቶቻችንን በማህበራዊ ህይወት ፈሊጣቸው ልናደንቃቸው እንጂ ባልገባን ነገር ልንሳለቅባቸው አይገባም ባይ ነው፡፡ ተመስጌንን ቃል በቃል አልጠቀስኩትም፡፡ ግን ሐሳቡ ከዚህ እንደማይወጣ ርግጠኛ ነኝ።


እንግዲህ አስቡት፡፡ የመኪና ወፍጮ ድካምን ከማቃለል ይልቅ የዱቄትን መጠን በማቅለል ተዋውቋል ማለት ነው። የለውጥ መሳሪያ ከጉድለት ጋር ሲገጣጠም ሰዎች ለውጥን በበጐ ሊያዩት እንዴት ይችላሉ?


ጥንታዊ ጃፓን ግን ለውጥን የሚያስጠላ ክፉ እድል የገጠማት አይመስልም፡ ፡ ባርትራንድ ረስል የተባለ ፈላስፋ እንደጠቀሰው ጃፓኖች ቡዲዝምን ከጐረቤት አገር ተውሰው በብሔራዊ ሀይማኖት ከማድረጋቸው በፊት በጥቂት መሳፍንት ላይ ሞከሩት።


አዳዲሶቹ የቡዲስት ተከታዮች የባላገሮች እምነት ከሆነው ሺንቶይዝም ተከታዮች በብልጥግና ከበለጡ ቡዲዝምን እናስገባዋለን ነበር እቅዳቸው፡፡ የቤተ ሙከራው ውጤት እንደሚያሳየው በተውሶ የመጣው እምነት ካገር ቤቱ እምነት የተሻለ ብልጥግና አፈራ፡፡ ስለዚህ ቡዲዝም፣ ቤት ለእንግዳ ተባለ፡፡ ሼንቶይዝምም በእንግዳው መምጣት ሳይገፋ ቀጠለ።


እንግዲህ ለጃፓኖች

1. አንድ ያስተሳሰብ መስመር የሚለካው በጠቃሚነቱ እንጂ በአገር በቀልነቱ ወይም በማይረጋገጥ እውነቱ አይደለም።
2. አዲሱ የነባሩ ጠላት አይደለም። ‹‹የጐመን ምንቸት ውጣ የገንፎ ምንቸት ግባ›› የሚል የለውጥ መዝሙር አይሰራም።


ይህን ይህን ስናይ ኢትዮጵያውያን እና ጃፓናውያን ‹‹መንትያ›› የሚያሰኝ ያመለካከት መስመር ወይም የስነ ልቦና ዘይቤ እንዳልነበራቸው እንረዳለን፡፡ የጃፓን ባህላዊ አመለካከቶቻቸው ወደ ምዕራባውያን ስልጣኔ በፍጥነት የሚያደርሱ መንኮራኩሮች ነበሩ፡፡ ስለኢትዮጵያ ተመሳሳይ አስተያየት መስጠት አይቻልም።


ፋናወጊዎቻችን ኢትዮጵያን ዳግማዊት ጃፓን ለማድረግ ያደረጉት ያልተሳካ ጥረት የተደመደመው የጃፓንን ኋላቀር ሕገ-መንግስት በመገልበጥ ነው፡፡ ጃፓኖች የቁሳዊ እድገታቸውን የሚመጣጠን ያስተዳደር ስርዓት አልነበራቸውም፡ ፡ በሌሎች አገሮች ዴሞክራሲ በሰፈነበት ወቅት ኢትዮጵያ ታዛዥነትን የሚያጋንነውን ጥንታዊ የጃፓን ህገ መንግስት መገልበጧ ነፃነቷን አስከፍሏታል።


ስለዳግማዊ ቴዎድሮስ

‹‹አፄ ቴዎድሮስ›› ይላል ዓለማየሁ ‹‹አፄ ቴዎድሮስ አውሮፓዊ ስልጣኔ እንዲገባ ከመፈለጋቸው ጐን ለጐን ነባሩ ስልጣኔያችን እንዳይጠፋ ይጣጣሩ ነበር፡፡ እውነት ትክክለኛነት ፍርድ የነባሩ ስልጣኔ አውዶች እንደሆኑ ተገንዝበው በአርአያነት ያከናውኗቸው ነበር፡፡ እውነትን የሚያጠፋ ትክክለኛነት የሚበርዙና ፍርድን የሚያዛቡ ካጋጠማቸው መቀጣጫ ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም ነበር››


በኔ አስተያየት፣ በዘመነ መሳፍንት የነበሩ አብዛኛዎቹ ገዢዎች ያውሮፓ ስልጣኔን ማስግባት ይፈልጉ ስለነበር ዳግማዊ ቴዎድሮስ በዚህ በኩል ልዩ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ አለማየሁ አብዝቶ የተሳሳተ የመሰለኝ ግን ቴዎድሮስን የሞራል ስልጣኔ ምሳሌ ሊያደርጋቸው ሲሞክር ነው፡፡ የዳግማዊ ቴዎድሮስ ወኔያምነት አልበገር ባይነት አንድ ነገር ነው፡፡ ስነምግባራቸው ደሞ ሌላ ነገር ነው።


ይልቁንም ‹‹ነባር ስልጣኔያችን እንዳይጠፋ ይጣሩ ነበር›› የተባለው በማስረጃ እስካልተደገፈ ድረስ አያሳምንም። ለኔ ተቃራኒው የበለጠ እውነት ነው፡፡ ለምሳሌ ውስንም ቢሆን ሀሳብን የመግለፅ ስልጡን ባህል ካጤ ቴዎድሮስ በፊት ነበር። በቅኔ ቤት አሠረ ንጉስ የሚል መጠሪያ ነበረው፡፡ በዚህ የቅኔ መንገድ ነገስታቱን መውቀስ የእርምት ሐሳብ መጠቆም የተፈቀደ ነበር፡፡ ለምሳሌ በአድያም ሠገድ ኢያሱ ዙፋን ፊት የቀረበ ቅኔ እንዲህ ይላል።


ድምፀ ቃለ ሐሜት ተሰምዓ ኢያሱ በዘመንከ ሠናይ

ከመ ሰማዕነ ባሕቱ እንዘ ይብለከ ነዳይ

ፍትሕከ ይብራህ ከመ ፀሐይ

ሢመት ኩሉ ዘታሕተ ሰማይ

እስመ ኮነ ለዘቦ ንዋይ

ኢያሱ በመልካም ዘመንህ የሐሜት ቃል ተሰማ

ድሃ እንዲህ ሲልህ ሰማን

ፍርድህ እንደ ፀሐይ ይብራልን

ከፀሐይ በታች ያለው ሹመት ሁሉ ገንዘብ ላለው ብቻ ሆኗልና።


ባለቅኔው የንጉሡ አድልኦ በመዘርዘር ወቀሳውን አቅርቧል። ወቀሣውን ካቀረበ በኋላ ወህኒ አልወረደም
ከባለቅኔዎች ያልተናነሰ የነፃ አመለካከት ፋና ወጊዎች አዝማሪዎች ነበሩ፡ ፡ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ግን አዝማሪ ቀጥቅጠው በመግደል የሚካኤል ስዑልን ፈለግ ተከትለው የነፃ ሐሳብን ባሕል ባጭር አስቀሩት፡፡ በጊዜው አዝማሪ መግደል በዛሬ ዘበን የተቃዋሚ ጋዜጠኛ ከመግደል ጋር መሣ ነው፡፡ ከዳግማዊ ቴዎድሮስ ፊት ቅሬታ መግለፅ ምን አይነት ቅጣት እንደሚያስከትል ለማስረዳት የሚከተለውን ገጠመኝ ካለቃ ዘነብ እጠቅሳለሁ።


‹‹..አግታ በደረሱ ጊዜ አንድ ሴት ከሽፍቶች ምሽት ተያዘች፡፡ ንጉሥ ቴዎድሮስም ግፈፏት ባሉ ጊዜ ደንግጣ ደም ፈሠሣት፡፡ ንጉሱም አልብሳት አሉ፡ ፡ ሴቲቱም እንዲህ አለች፡፡ የሞትሁኝ ቀድሞ ባለብስ ምን እዳዎ ባለቺ ጊዜ ንጉሱም በነፍጥ በላት አሉ፡፡ በተመታችም ጊዜ ሞተች፡፡ የባሩድ እሣት በነካት ጊዜ ሁለት ቀን እንደ ጧፍ ነደደች››


ያጤ ቴዎድሮስን ግፍ በሰፊው በመዘገብ የአርብ አንባቢን ድብርት በድብርት የማድረግ አላማ የለኝም፡፡ አለማየሁ ንጉሱን የሞራል ስልጣኔ አርአያ ሊያደርግልን የሞከረውን ለማስተባበያ የጠቀስኩት ይበቃል፡፡ እውነት ለመናገር አጤ ቴዎድሮስ በዘመናቸው ከነበሩ ወደረኞቻቸው ጋር ሲመዛዘኑ በሞራል እጅግ ኋላ ቀር ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ስሙ ያልታወቀ ያጤ ቴዎድሮስ የዜና መዋዕል ፀሐፊ አገው ንጉሤ ስለተባለው የንጉሱ ተቃዋሚ የፃፈውን እንመልከት፡፡
‹‹…(አገው ንጉሤ) ጭራሽ ሩህሩህ ናቸው ይላሉ፡፡ ይቆረጥ በቃ የተፈረደበት እንደሆነ አያ እግርና እጅ በውሃ አይበቅልም ገርፈህ ስደደው ይሉ ነበር ይላሉ፡፡ ይሙት በቃ ቢፈረድበትም ገንዘብ ይከፍሉ ነበር ይላሉ፡፡››


በዚህ ብርቅ አንቀጽ ውስጥ መስፍኑ፣ የሞት ፍርድን በደም ካሣ ለመተካት እጅና እግርን ለመቁረጥ የሚፈፀምን ቅጣት ደግሞ ጨርሶ ለማስቀረት መጣሩን እመለከታለን። እጅና እግርን መቁረጥ ዳግማዊ ቴዎድሮስ እንደ ሽመና የሚራቀቁበት ቅጣት ነበር፡፡ ለነገሩ ይህ አይነቱ ጭካኔ የፍትሐ ነገሥት ድጋፍም አያጣም፡፡ በኔ ግምት ያገው ንጉሤ ትልቅነት ገናናውን ልማድና ፍትሃነገስቱን ቸል ብሎ የገዛ ልቦናውን ለማድመጥ መድፈሩ ነው፡፡ ልቦናው ‹‹…እግርና እጅ በውሃ አይበቅልም›› የምትል፣ ብትቀጥንም ጠጅ የሆነች፡ እንደ ምሥጢረ ሥጋዌ ያልተወሳሰበች ለባላገሩ በቀላሉ የምትገባ የሞራል ፍልስፍና አቀብሎታል፡፡ ይህ እንግዲህ የብርሃነ ሕሊና ውጤት ነው፡፡ ብርሐነ ሕሊና ማለት ያለ ደጋፊ ራስን ችሎ ማወቅ ማለት ነው ብሏል አማኑኤል ካንት።


ያገው ንጉሤ የሞራል ሐሳብ ከዳግማዊ ቴዎድሮስ ዘመን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ከዛሬይቱ ኢራንና ሳኡዲ አረቢያ ጋር ሲነፃፀር እጅግ የቀደመ ነበር ማለት ይቻላል።


ፅሁፌን በዚህ ሰውዬ ብሩሕ ሐሳብ በመደምደሜ ራሴን እንደ እድለኛ ቆጠርሁት።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ