አቢቹ ነጋ

በአለማችን በቀደምት ታሪካቸው ከሚታወቁት አምስት ሃገሮች መካከል አንድዋ ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ በራስዋ ታሪክ ወግና ባህል ስትኩራራና ስትመጻደቅ ይኸው ከ3,000 ዘመን በላይ አስቆጠረች።

 

 

ኢትዮጵያኖች በሰፊው ከምንኩርራባቸው ዋና ዋናወቹ የራስ ፊደልና ቋንቋ፥ ታሪካዊ ሃውልቶች፥ የክርስትናና እስልምና እምነቶችን ተቀብለን የባህልችን አካል ያደረግን፥ ቅኝ ግዛትን አፈርድሜ ያገባን፥ በውበታችንና በባህላችን ስብጥርነት የምንኮራ፥ የሃገር አንድነትን ለበዙ ዘመናት የጠበቅን፥ የህግ የበላይነትን ጠንቅቀን የተረዳን ወዘተ ይገኙበታል። እነኝህ ኩራቶች ግን ከታሪክነት አልፈው ዳቦ አልባሳትና መጠለያ ሊሆኑን አልቻሉም።

 

ሊቃውንት እንደሚሉት ከሆነ በጥሩ ታሪክ ላይ የተገነባ ማህበረሰብና ሃገር ለፖለቲካዊ፥ ኢኮኖሚያዊና ሕብረሰባዊ እድገት የተዘጋጀ ሊሆን ይገባዋል ይሉናል። በእኛ ሃገር ሁኔታ ግን ይህ መላምትና አስተሳሰብ በተቃራኒው ያለ ይመስላል።

 

የሀገራችን ስልጣኔና እድገት በአስከፊ ሁኔታ እንደግመል ሽንት ወደ ሗዋላ የሚሂድ፥ ተሻለ ሲባል ደግሞ እንደ ውታደር እርግጫ ባላበት የሚረግጥ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂው ማነው ያልን እንደሆነ መልሱ እኛ ይሆናል። ምክኒያቶችስ ምን ሊሆኑ ይችላሉ ለሚሉት ግን መልሱ እንደዚህ ቀላል አይሆንም። ይህን ከባድ ጥያቄ ለመመለስ ራሱን የቻለ የስነ ማህበር፥ የስነ ፖለቲካ፥ የስነ ኢኮኖሚ ምርምርና ጥናት ያስፈልገዋል። መጠናትም አለበት። ለምን ያልን እንደሆነ በሽታው ካልታወቀ መፍትሔውን ማግኘት ያስቸግራል እና ነው። ምርምሩና ጥናቱ እስኪደረግ ግን ተጨባጩን ሁኔታ በመዳሰስ መሰረታዊ የሆኑትን መተንተን ይቻል ይሆናል። ከሁሉ መቅደም ያለበት ተግባር ግን ራስን መፈተሹ ላይ ማተኮሩ ይጠቅማል። እራሱን ያላወቀ ሌላውን አውቆ መለወጥ ያስቸግረዋልና።

 

ለዛሬው ፍተሻ ሊረዱ የሚችሉ ሁለት ታሳቢወችን እንመልከትና ራስችንን እንታዘበው። መታዘብ ከቻላን ደግሞ ይህን ለመቀየር እኔ ምን ሰራሁ በማለት እራሳችንን እንሞግተው። በዚህ ሙግት ደግሞ መልሱን ከውስጣችን ፈልቅቆ ማውጣት አያዳግተንም። አሸናፊና ተሸናፊውም ራሳችንና ህበረተሰባችን ይሆናል።

 

እድገት በጰሎትና በልመና አይገኝም

የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት በጰሎት ጉንብስ ቀና፥ ተቀምጦ በመመኘት፥ ሌላውን በማወደስና በማድነቅ፥ ወይም በመተቸት የሚገኝ አይደለም። እድገት በአርቆ አስትዋይነት፥ እውቀትን በተግባር በመተርጎም፥ ከሊሎች በማጥናትና ጠቃሚውን ገነዘባችን አርገን በመጠቀም፥ የምርምርን ግኝት በስራ በመተርጎም፥ እርስበርስ ተመካክሮ ለህዝብ በመስራት የሚገኝ የስራ ትሩፋት/ረድኤት ነው።

 

ካለፉት ተምሮ የወቅቱን ሁኔታ ከመጭው እራይ ጋር አገናዝቦና አልሞ የማይሰራ ህብረተሰብ በቁሙ የሞተ ለምሆኑ ጥርጥር የለውም። ሃይማኖት የሚረዳው የመንፈሳዊ ህይወታችንን ሃያሉ እግዚአብሔር እንዲቀድሰው ለማድረግ እንጅ የህብረተሰብን የእድገት ጎዳና እንዲቀድ/እንዲቀይስ አይደለም። እትዮጵያኖችን እጅግ ከተጠናወተን አጉል ልማድ አንዱ ለችግራችን፥ ለኋላቀርነታችን፥ ለድንቁርናችን፥ ለመጨቆናችን የምንሰጠው መፍትሄ እሱ ወይም እግዚአብሔር ያውቃል ሆኖዋል። እግዚአብሔር የስንፍናችንና የኋላቀርነታችን መሸሸጊያ ደን አይደለም። ሊሆንም አይችልም። እግዚአብሔርማ አውቆ የሚአስብ ዐእምሮ፥ የሚያዩ አይኖች፥ የሚሰሩ እጆችና እግሮች ወዘተ ሰጦናል። ሃያሉማ በራሱ አምሳል ፈጥሮ ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት ብሎናል። የምንባዛውና መሬትን የምንሞላው የቀንና የማታ ስራ ሲሰራ እንጅ ስለተመኘነውና ስለለመነው ብቻ አይመጣም። ሊመጣም አይችልም። ይህን የምንመኝ ከሆነ ደግሞ በሰማይ ላይ ከመትኖርዋ የትንቢት ላም ወተት እንደመጠበቅ ይቆጠራል።

 

የምንበላው ምግብ፥ የምንለብሰው ልብስ፥ የምንኖርበት ቤት የሚገኘው የተፈጥሮ ሃብትን ተጠቅመን ስናመርት ብቻ ነው። ስራ ካልፈለግን እንደሌሎቹ የዱር አራዊት/እንስሣት አውሪ ሆነን ጫካ ውስጥ በመኖር አድነን መብላት ይኖርብናል። አደንም ቢሆን ቁጭ በማለት አይገኝም። ብዙ መጓዝን፥ የአደን መሳሪያ መፍጠርን፥ ታድኖ የተያዘውን አርዶና ጠብሶ የመብላት ስራን ይጠይቃል። እንድናድግና ድህነትን አጥፍተን ከተመጽዋችነት ለመላቀቅ የስራን ክቡርነት በማስቀደም ከዚያም እግዚአብሔር ያውቃልን በማስከተል ቢሆን ይመረጣል።

 

ንቀት

ኢትዮጵያዊያኖችን የተጠናወተን መጥፎ በሽታ አንዱ ንቀት ነው። ነጮችን፥ ፈረንጆችን፥ ቻይናወችን፥ ጥቅሮችን፥እራሳችንን ወዘተ መናቅና ማጣጣል እንደትልቅ ኩራት አድርገን ይዘነዋል። በመሰረቱ ሌላውን የሚንቅ ሁልጊዜ አስተሳስበ ድሃ የሆነ ሰው ውይም ለራሱ ከሚገባው በላይ ከፍተኛ ግምት የሚሰጥ ሰውና ማህበረሰብ ነው። ይህ ደግሞ ለእድገት እንቅፋት ነው። በእጅጉም የሗዋላቀርነት ምልክት እንጅ ሌላ ትርጉም የለውም። ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግስት ስራ እንደጀመርሁ አንድ ወንድሜ እንዲህ ሲል መከሮኝ ነበር። ሁልግዜ መማር፥ ማወቅ፥ መጠየቅና መመራመር እንዳለብኝ አለቃን መፍራት ሳይሆን ማክበር የስራ ባልደረቦቸን መናቅ ሳይሆን ከነሱ መማር እንዳልረሳ አስታውሶኝ ነበር። አለቃን መፍራት ሳይሆን ማክበርን፥ የስራ ባልደረቦችን መናቅ ሳይሆን ከነሱ መማር፥ የራስንም ትንሽ እውቀት ለማካፈል መዘጋጀት አዋቂነት ነው። ከሃያ አመት በሗዋላም ይህ አውነታ አልተለወጠም። የሚለወጥም አይሆንም። ትምህርት ተጨረሰ፥ ዲግሪ ተገኘ ማለት መማር፥ መመራመር፥ መጠየቅ ቆመ ማለት አይደለም። መጠየቅ ምንጊዚም ያደርጋል ሊቅ። ፕሮፊሰር መስፍን መጠየቅና መጠራጠር ወደእውቀት ያመራል ይሉናል።

 

በማህበራዊና በህግ ፍልስፍና መርህ መሰረት እውነት ሁልጊዚ ያድናል፥ መናቅ ያስገምታል ያዋርዳል ይላሉ። ሌላውን መናቅ እስካላቆምን ድረስ እድገታችን ባለበት የሚሄድ ወይም ወደ ኋዋላ የሚአፈገፍግ ይሆናል። ከግለሰቦች፥ ከህብረተሰብ፥ ከድሃ ሃገሮችም ሆነ ከበለጸጉት ብዙ የምንማረው አለ ይኖራልም። እንክርዳዱን ከፍሪው ለይቶ የሚጠቅመውን የራስ ማድረግ ብልህነት ነው። እርግጥ ንቀን የምንተዋቸው ነገሮች የሉም ማልት ግን አይደለም። የማይጠቅመውን ከሚጠቅመው ለይቶና አበጥሮ ለማውጣት መጀመሪያ ማወቅና መመራመርን ይጠይቃል።

 

የሰአት ክቡርነት

በስደት አለም ላይ ባሉ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ እየተለመደ የመጣ ባህሪ እንመልከት። በተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮጵያዊያን ሃገራቸውን ለቀው በመውጣት በአምስቱም አሃጉራት ተበትነው ይገኛሉ። በአብዛኛው ለስደት የዳረጓቸው ምክንያቶች ኢኮኖሚያዊ፥ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ናቸው። በሃገራችን ባህል ዘመድ ከዘመዱ፥ ጓደኛ ከጓደኛው፥ ህብረተሰብ ከህብረተሰብ በችግር፥ በደስትና በሃዘን ተረዳድቶ፥ ተጠያይቆና ተደጋግፎ ይኖራል። በውጭ ሃገር ግን ሁኔታው ከዚህ ይቃረናል። ሰው ካልሰራ ማንም ቀና ብሎ የሚያየው የለም። በካናዳ፥ በአሜሪካ፥ በአውሮፓ፥ በአውስትራሊያ፥ ወዘተ ያየነውና የሰማናው ነው። ካልተሰራ ደግሞ በዌልፊር ተስፈኛ ሆኖ መኖር ሲሆን ይህ ደግሞ እጅግ ያዋርዳል።

 

ከሞላጎደል ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የተሰደዱበትን ሃገር ባህልና ወግ ለምደው ጥሩ የመስራት ባህልን አካብተው ይገኛሉ። ብዙዎቹ በስደት አለም ላይ ሆነው የሚሰሩትን ያህል በሃገራቸው ቢሰሩ ኢትዮጵያ የትበደረሰች ያስብላል (በርግጥ ሃገራችን ዚጎችዋን ለማሰራት የሚአስችል የስራ ህግና ስነስራት ስላልገነባች በዚጎችዋ ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም። ሊላም ሊላም ምክንያት…)። ስለሆነም በብዙ የውጭ ሃገር ከተሞች እንደምናየውና እንደምንሰማው የኢትዮጵያኖች የስራ ችሎታ፥ ብቃትና ዲሲፕሊን ከማንም የማይተናነስ (ሲሆን ባይበልጥ) ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ ይበል ይበርታ ያሰኛል። በአንጻሩ ደግሞ በሰለጠነ አለም ተቀምጠው ወደሗዋላ የሚሔዱበትና የሚአሳፍር ስራ የሚያከናውኑበት ሆኖ ይገኛል።

 

ግብዣ ተጠርቶ በሰአቱ አለመገኘት የስልጣኔና የኩራት መለያ እየሆነ ከመጣ አመታት አስቆጥሯል። በነዚህ ሃገሮች ህይወት የሚሽከረከረው በሶስት አብይት ነገሮች ነው። እነዚሁም ገንዘብ ጊዜና ስራ ናቸው። የስራ ዋጋ ደሞዝ የፓርኪንግ ተመን በአጠቃላይ ኑሮ የሚተመነው በጊዜ ተሰልቶ በሚሰጥ ገቢ ነው። የህዝብ መጓጓዣ ባቡር፥ አየር፥ ኦውቶብስ፥ መርከብ፥ ወዘተ በሰዓት ይነሳሉ በሰዓት ይደርሳሉ። ሰዓት ያላከበረ ሰው ወይም በስአቱ ያልተገኘ ተሳፋሪ ብቻውን ይቀራል። ለዚህ ነው ባቡር ቆሞ ኦይጠብቅም የሚባልው።

 

የጊዜንና ሰዓትን ክቡርነት የማይረዳ ግለሰብም ሆነ ህብረተሰብ ከጊዜው የኢኮኖሚ፥ የፓለቲካና የማህበራዊ ባቡር ጋር አብሮ መጓዝ ያቅተዋል። በነዚህ ሃገሮች በሰዓትና በቀጠሮ የማይገኝ ሰው ወይም አለመገኝት ሶስት ባህሪያትን የሚገልጹ ናቸው። ደንታቢስነት/ግድየለሽነት፥ የዋሾነት/ የምነተቢስነት፥ የድንቁርና ባህሪያት መግለጫዎች ናቸው።

 

ስለዚህ ሗላቀር አስተሳሰብ ትቂት አሳፋሪዎችን በተጨባጭ በካናዳ ዋና ከተማ ኦታዋ የሆኑትን በናሙናነት እንመልከት። በከተማይቱ ከ3-4ሽህ ኢትዮጵያዊያን ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። ከከተማዋ ማነስ የተነሳ ኢትዮጵያኖቹ ከሞላጎደል ይተዋወቃሉ ማለት ይቻላል። ሁሉም የለት ጉርሱን የአመት ልብሱን ለማምረት ሲኳትን ጊዜው ያልፋል። በአንጻሩ ኢትዮጵያዊያኖች የሚገናኙባቸው ብዙ እድሎችም አሉአቸው። ከነዚህም ዋና ዋናወቹ በደስታ፥ በሃዘን፥ በጸሎት ቤት፥ በህረተሰብ ስብሰባወች፥ በግብዣወች ወዘተ ላይ ነው። በተለያዩ የመህበራዊ ጥሪዎችና ግብዣዎች ያለማጋነን አንድም ጊዝ ተጋባዥ ህብረተሰብ ስአቱን አክብሮ የተገኘበትን ለአብነት መጥቀስ ያስቸግራል።

 

ከችግሩ አሳሳቢነት የተነሳ የሃይማኖት አባቶችና አለቆች ውግዘት በተሞላበት ሁኔታ፥ የኮሚኒቲ መሪዎች፥ በድሜአቸውና በተመክሮአቸው አንቱ የተባሉ ግለሰቦች እንዲሁም ምሁራን ስለሰዓት ይከበር ሲአስተምሩና ሲወቅሱ ይደመጣል። ምክሩም ሆነ ትምህርቱ ሁሉም ገደል ገብቷዋል። ህብረተሰቡም ጀሮ ዳባ ልበስ በሎ በዚህ አሳዛኝና ሗላቀር ድርጊቱ ቀጥሎበታል። ይህን አስነዋሪ ባህሪና ልምድ ቢቻል ከነአካቲው ለማስወገድ ባይቻል ለማሻሻል ጥረት ሲአደርግም አይታይም። የጉዳይ አሳሳቢነት እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም ይባስ ብሎ ከመጥፎ ልምድነት አልፎ እንደኩራትና እንደስልጣኔ እየታየ መጥቷል። ያደቆነ ባህሪ ሳያቀስ አይተውም አንደተባለው

 

በአንድ ወቅት ሁለት ተጋቢወች ለሰርጋቸው እራት ግብዣ እንግዶቻቸውን ከምሽቱ ሰባት ሰዓት እንዲገኙላቸው ይጠራሉ። ሙሽሮቹ ከምሽቱ ስምንት ሳት አካባቢ በለሞዚናቸው ወደግብዣው ይመጣሉ። ባለሊሞውን ከምሽቱ/ከለሊቱ አስራሁለት ሳት ላይ ተመልሶ እንዲወስዳቸው ተስማምተው ያሰናብቱታል። ይህ ሊሞዝን በሰዓትና በፕሮግራም የሚሰራ በመሆኑ ወዲያው ወደሌላው ስራው ይፈተለካል። ሙሽሮችም አንግዶቻቸው እንዳልመጡ ይነገራቸዋል። የጝደኛ መኪና አስጠርተው ወደቢታቸው ይመለሳሉ። ካልጋ ወርዶ አመድ ማለት ይህ ነው። እንግዶቻቸው ከምሽቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ እየተንጠባጠቡ ይደርሳሉ። አብዛኛው እንግዳ (80%)የሚሆነው አስር ሰዓት ላይ ይገባል። ከዛም ሙሽሮቹ ተጠርተው ይመጣሉ። ያው የተለመደው ተዝፍኖ ተበልቶ ተጠጥቶ ግብዣው ወደ አስራሁለት ሳአት ገደማ ይጠናቀቃል። ከሁሉ የሚገርመው ነገር ቢኖር ሰዓት አክባሪ ፋረንጆችም አብረው ሲንቃቁ መዋላቸው ነው።

 

ይህ ብዙ ሳይቆይ እንደገና በዚህ ሰሞን በዚሁ ከተማ ሌላ ሰርግ ይደረጋል። የጥሪ ወረቀቱና ፕሮግራሙ የሚለው ከቀኑ አራት ተኩል ሰዓት ላይ ይገኙልን ይላል። ተጋባዥ አዳራሹ የመጣው ግን ከመሽቱ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ነው። ሙሽሮቹ የገቡት ከምሽቱ ስምንት ሳት ላይ ሲሆን የራት ግብዣው የተጀመረው ከዘጠኝ ሰዓት ላይ ነው። ይህማለት ደግሞ ሰዓት አክባሪ ተጋባዥ ካለ አራት ሰዓት ተኩል ሙሉ ተቀምጦ ሲጠብቅና መቀመጫውን ከወንበር ጋር ሲአለፋ ውልዋል ማለት ይቻላል። የሚገርመው አንዳንድ ተጋባዦች ህጻናት ልጆች ስላሏቸው አራት ሳይበሉ ወደቤታቸው የተመለሱ መሆኑን ይህ ጽሃፌ ዋቢ ምስክርነት መስጠት ይችላል።

 

በሌላ ወቅት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የአድዋን 116ኛ መታሰቢያ ክብረ በአል ምክንያት በማድረግ ህብረተሰቡን ከቀኑ ሁለት ሰዓት እንዲገኙለት በአክብሮት ጠርቶ አብዛኛው ተጋባዥ የደረሰው በአራት ሰዓት ለይ ነው። የሚገርመው አንዳንዶቹ ፕሮግራሙ ሊፈጸም ግማሽ ሰዓት ሲቀረው ደርሰዋል። በዚህም ምክንያት ማህበረሰቡ ተጨማሪ ያዳራሽና ሌሎች ክፍያወች አክሎ የፕሮግራሙን ግዜ ለማራዘም ተገዿል። ማህበረሰቡ ለእለቱ ያወጣቸው መርሃግብሮች በጊዜ እጥረት ምክንያት ማስተናገድ ባለመቻሉ አንዳንድ መርሃግብሮች እንዲሰረዙ መደረጉን ካስተናጋጆች ተረዳን።

 

ኧረ ዲያስፖራን ምን ነካው ሲባል አይ ሰው በስአቱ ስለማይመጣ እኔ አስቀድሜ ወይም በሰዓት ደርሸ ለምን ልንቃቃ ሲል ይደመጣል። የሚገርመው ይህ መጥፎ ባህሪና ልምድ ኢትዮጵያኖች ተሰደው በሚገኙባቸው አምስቱም አሃጉራት ተመሳሳይ መሆኑ ከማስገረምም በላይ አሳዛኝ ሆኖ እናገኘዋለን። ድንቄም ስልጣኔ። ሁሉም እንዲህ ካለ ማነው ሰዓት አክባሪ የሚሆነው። ቀጠሮ የማያከብር ዳያስፖራ ለራሱ ያልበጀ አገርም አያኮራ ለማለት እንገደዳለን። በቅርቡ ወደ ኢትይዮጵያ ሄጀ የወገኖቻችንን ሰዓት አክባሪነት ሳይ በጅጉ ደሳለኝ። ተሟጦ አልቆ የነበረው ተስፋዬ እንደገና ለመለመ።

 

ለሗላቀሩ ዲያስፖራ ግን በጅጉ አዘንሁለት። የሚአሳዝነው ግን በውጪ ሃገር ተወልደው የሚአድጉት ልጆቻችው ከዚህ ሗለቀር ዲያስፖራ ወላጅና ህብረተሰብ ምን ይማሩ ይሆን በማለት ተከዝሁ።

 

እስኪ እንጠያየቅ ዲያስፖራ። ሰዓትን ማክበር ያልቻለ ዲያስፖራ በምን ታምር ነው ስለሃገሩ ፖለቲካዊ፥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የሚዶልተው? ይህነው ለሃገሩ አለኝታነኘ እያለ የሚመጻደቀው። ከሆነ እሰየው። ይህ ታዛቢ ግን ለማመን ይቸገራል። እንደእኔ ግምትና አስተሳሰብ የቀጠሮን ሰዓት የማያከብር ዲያስፖራ ለራሱ ሳይበጅ እንዴት ሃገር ያኩራ። ተው ጎበዝ እራሳችሁን አታስገምቱ። አገራችሁንና ወገናችሁንም አታዋርዱ፥ አታሳፍሩ።

 

ብዙ ነገር ባህያ አይጫንም ይላል ያገራችን ሰው። ደሮ እንኳ በደመነፍስ ስአቷን ሳታዛንፍ ትቀሰቅሰናለች ወይም ንጋትን ታበስራለች። እንስሣት በተወሰነ ሰዓት ባለቤታቸው ምግብ ካስለመዳቸው በዛችው ቦታና ሰዓት ይገኛሉ። መጋቢያቸው ከዘገየ በመጮህ እሮሮ ያሰማሉ። ህጻናት በተወሰነ ሰዓት መተኛት ከለመዱ ሰዓትዋ ስትደርስ ያዛጋሉ ወይም ያለቅሳሉ። ሰልሆነም በለመዱአት ሰዓት ይተኛሉ ይነሳሉ። ይህን የሚአዛቡት ካመማቸው ወይም ከራባቸው ብቻ ይሆናል። ከእንስሳት የተሻለ የማሰብ ዐአምሮ ያለን፥ የጊዜና ሰዓትን ጥቅምና ጉዳቱን ጠንቅቀን እያወቅን ብሎም ገንዘብ በሆነበት ሃገር እየኖርን፥ ይብዛም ይነስም ዘመናዊ ፊደል ዘመናዊ ለመሆን ቆጠርን እያልን የምናወራ እንዼት ይህን መገንዘብና ማሻሻል ያቅተናል። ማሻሻል ይቻላልና እንዝመትበት።

 

ምናልባት በዚች ጽሁፊ አስቀይሚአችሁ ከሆነ ከወዲሁ ይቅርታ እጠይቃልሁ። ለሁላችንም የሚበጅ ስለመሰለኝና በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ሰው ሲብከነከን ወይም ከንፈሩን ሲመጥ ስለማይና ስለምታዘብ ነው ወደ አደባባይ ያወጣሁት እንጅ አዲስ ግኝት ወይም ሮኪት ሳይንስ ሆኖም አይደለም። በመጨረሻም በዚህ ጉዳይ ላይ ማንም ጲላጦስ ሆኖ ያለ የለም። ሑላችንም የችግሩ አካሎች ስለሆን የመፍትሄውም አካል መሆን ይገባናል። ስለሆነም ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ራሱን ፈትሾ ከተስተካከል ለራሱ ክብርን፥ ለሃገሩ ኩራትንና አለኝታነትን ያጎናጽፋል።

ቸር ይግጠመን።


የናንተው አቢቹ ነጋ ነኝ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!