”ተቃወሙት” ስለተባለው አዲስ ቤተክርስቲያን
በስዊድን “አዲስ ቤተክርስቲያን ይከፈታል" መባሉን ምዕመናን ተቃወሙት በሚል ለቀረበ ጽሑፍ የተሰጠ ምላሽ
ቀሲስ ፍሰሐ ተስፋዬ
መግቢያ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! አለመታደል ሆነና ዛሬ አውላላ ሜዳ ላይ ቆሜ የማስነብባችሁ ነገር ከላይ በጠቀስኩት ብሎግ ላይ ስማችንን ለማጉደፍ የፈለጉ አንድ ግለሰብ በእኔ፣ በአቡነ ኤልያስና በአባ ኒቆዲሞስ ላይ የጻፉትን የሐሰት ውንጀላ ለማስተባበልና እውነቱን ለማሳየት ነው። ራሴን አስተዋውቄ ዝርዝር ነገሩን በመጠኑ አስረዳለሁ።
ሰላም ብሎግ ላይ ”በስዊዲን “አዲስ ቤተ ክርስቲያን ይከፈታል" መባሉን ምዕመናን ተቃወሙ” በሚል ርዕስ የወጣውን ጽሑፍ ወደ ደጀ ሰላም ብሎግ ሄደው ለማንበብ እዘህ ይጫኑ! ... (ወይንም በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)
እኔ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ስሜ ፍሰሐ ተስፋዬ ይባላል። የምኖረው በስቶክሆልም ስዊድን ነው። በክህነት ደረጃዬ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ካህን ነኝ። ድቁና በ1976 ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳስ ዘከፋ ጂማ ተቀብያለሁ። ቅስና በ1985 ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአርባምንጭ ተቀብያለሁ። በደብር አስተዳዳሪነት ደግሞ በዳውሮ ዋካ ደብረ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ከ10 ዓመት በላይ አገልግያለሁ። በዘመናዊው ትምህርት ደግሞ የትምህርት ባለሙያ ስሆን፤ በመምህርነት፣ በርዕሰ መምህርነት፣ በትምህርት ባለሙያነትና በኃላፊነት ወደ ሃያ ዓመት ያህል አገልግያለሁ። በመምህራን ኮሌጅና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ትምህርቴን ተከታትያለሁ። በከፍተኛ የትምህርት ባለሙያነት አገልግያለሁ።
በገዥው የወያኔ መንግሥት ዘመን ሀገሬን እጠቅምበታለሁ የምለውን አስተሳሰብና አመለካከት በማራመዴ በተለያዩ ጊዜአት እየታሰርኩ ስጉላላ የቆየሁ ነኝ። የእኔን የሀገር ቤት ማንነት የሚገልጽ በቂ አድራሻና በአካባቢያ ያለው ህብረተሰብ በደንብ የሚያውቀኝ ሰው ነኝ። ስለራሴ በዚሁ ላብቃና ወደዚህ ጽሑፍ ዋና ሃሳብ ልዝለቅ።
ይህንን የዘረዘርኩት ያለምክንያት አይደለም። ወይም ራሴን ማስተዋወቅ ፈልጌም አይደለም። በእኔ ላይ አንድ ግለሰብ ላደረሰብኝ የሐሰት ስም ማጥፋት ጽሑፍ ትክክለኛ ምላሽ ለመስጠት እንዲያመቸኝ ራሴን ማስተዋወቄ ነው። ጸሐፊውን መቼም አንቱ ልበላቸውና ስማቸውን ሳይጠቅሱት ትተውታል። እኔ ግን እንደሳቸው ስሜን በመደበቅ መዋሸት አያስፈልገኝም። ውሸታም ደፋር አይደለም እንጂ ወደፊት ደፍረው ከወጡና እውነተኛ ከሆኑ በፊት ለፊት ስንገጥም ታውቋቸው ይሆናል።
ጸሐፊው በስዊድን “አዲስ ቤተክርስቲያን ይከፈታል” መባሉን ምዕመናን ተቃወሙ በሚል መንደርደሪያ ርዕስ የእኔን ስም ለማጥፋት ሞክረዋል። የእኔስ ግድ የለም በተለይ የብፁዕ አቡነ ኤልያስ ስም ያላግባብ መጠቀሱ ያሳዝነኛል።
እኔ ግን ከወያኔ ጋር ነፃነትን ሽጦና የባርነት ቀንበርን ተሸክሞ ከመኖር ይልቅ ተሰድጄ ካገሬ መውጣትና መኖር ነበረብኝና ነው የተሰደድኩት። ሌሎች እኔነቴን የሚያሳዩትን መረጃዎች ሲያስፈልጉ ወደፊት እመለስበታለሁ።
በስቶክሆልም ስዊድን ውስጥ በአንድ ቤተክርስቲያን ባልሆነ የግል ማህበር ውስጥ የሕዝብ ቤተክርስቲያን መስሎኝ ለተወሰኑ ዓመታት ሳገለግል ቆይቻለሁ። ከዚያም በእኛ በካህናትና በቤተክርስቲያኗ ባለቤቶች መካከል የተፈጠረው ያለመግባባት እያደገ መጣ። የደበቁንን መረጃ አግኝተን እኛንም ሆነ የስቶክሆልምን ምዕመናን ይቅርታ እንዲጠይቁ የመከርናቸውን ምክር ባለመቀበላቸው ምክንያት ትተንላቸው ልንወጣ ችለናል እንጂ፤ ጸሐፊው እንደቀባጠሩት ጸቡ የተፈጠረው በዋናነት በቀኖና ጉዳይ እንጂ በፖለቲካ አመለካከት ብቻ አይደለም።
ወደ ዝርዝር ጉዳዩ ልውሰዳችሁ።
ጸሐፊው ፖለቲከኛ፤ ሰነፍ፤ ምግባረ ብልሹ ወዘት በማለት ወርፈውኛል። በመሠረቱ በዚህ ባለንበት የስደት ዓለም እንኳንና ሳይሰሩ ቀን ከሌሊት ተሰርቶም ራስንና ቤተሰብን መምራት የሚከብድበት ዓለም መሆኑን በውጪው ዓለም ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይገነዘባል። ይህች “የሥነ ምግባር ብልሹነት” የምትባል የወያኔ ታፔላ የሆነች ቃል ከኮከበ ጽባህ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራን ጀርባ ተነስታ ማነህ ባለሳምንት ብላ በደጀ ሰላም አልፋ እውጭ ሀገር ተሰድዳ መጥታ ስታበቃ እኔ ላይ ከየት እንደመጣችና ማን እንደለጠፈብኝ ለማወቅ አልከበደኝም። ለዚህ ማስረጃ አሁን ምን እንደምሰራና የሚከፈለኝን እዚህ ላይ ማውራት አያስፈልገኝም። ተጧሪ ነው ከዘራ ይዞ ይዞራል አለማለታቸው ይመሰገናሉ።
በካህናትና በማርያም “ቤተክርስቲያን” ባለቤቶች መካከል የተፈጠርው ያለመግባባት ምክንያቱ ምንድነው?
ዋናው ልዩነቱ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ይከበር እንላለን እኛ። አይ እኛ የቤተክርስቲያኗ ባለቤቶች ያልነው ይሆናል ይደረጋል በሚሉት የቤተክርስቲያንዋ ባለቤቶች መካከል በተፈጠረ ልዩነት ነው። የቤተክርስቲያንዋ ባለቤቶች ደግሞ መቀደስ እንጂ ካህን ሌላ ምንም ጥያቄ ለማንሳት አይችልም ባዮች ናቸው። አንኳር አንኳር የሆኑትን የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ግድፈቶች አሉ። ሊስተካከሉ ይገባል። ሊጣሱ አይገባም ብለናል።
የተጣሱትን የቤተህርስቲያን ሥርዓቶችንና ቀኖናዎችን እንመልከት
ቀደም ብለው ከአገር በመውጣታቸውና በመሰደዳቸው ምክንያት አብዛኛው ወገኖቻችን ቤተክርስቲያን መስርተው አባቶች ካህናትን ለአገልግሎት በማምጣት የቤተክርስቲያን ሥርዓት እንዲከበር፤ ምዕመናን እንዲበዙ፤ በስደት የሚወለዱ ህፃናት የአገራቸውን ሐይማኖት፣ ባህልና ቋንቋ እንዲያውቁ ከፍተኛ ጥረት በማድረጋቸው ሊመሰገኑና ሊኮሩ ይገባል።
ሆኖም አንዳንዶች የቤተክርስቲያን ትርጉም ያልገባቸው ከማን አንሼዎች የቤተክርስቲያን ሥርዓትና ቀኖናዋን በመጣስ ለአገልግሎት ያመጡትን ካህናት እንድግል የቤት ሠራተኛ በመቁጠር ተገቢውን ክብር አጉድለው ሊያሰሯቸው ሲሞክሩ ይስተዋላል።
ይህንን ባለመገንዘብ ለካህናት አባቶች መቀደስን፣ መባረክን፣ ክርስትና ማንሳትን፣ ማጥመቅን፣ ብቻ የስራ ድርሻ አድርገው ሲሰጡ የቤተክርስቲያን አመራርና አስተዳደር ካህናት አባቶችን እንደማይመለከት ቆጥረው ከፍትሐ ነገሥት መጽሐፍ ገጽና አንቀጽ ሲጠቅሱ ቃለአዋዲውን ሳያነቡት ዘንግተውት ነው የቤተክርስቲያንን አመራርን ለካህናትና ለሌላው ባለተራ ላለመስጠት የሚዋደቁት ብዬ ራሴን አላታልልም።
1. ሥልጣነ ክህነት የሌለው ሰው ከታቦት ቁልፍና ከታቦተ ህግ ጋር ግንኙነት የለውም። ታቦተ ህጉን ማንም ይይዘው ዘንድ አይገባም። ታቦተ ህግ የሚገኝበት ቤተ መቅደስ ቁልፍ ማለት ታቦተ ህግ ማለት ነው። ታቦተ ህግ ደግሞ ከሌሎች ንዋየ ቅድሳት ጋር መያዝ ያለበት በካህን እጅ ብቻ ሊሆን እንደሚገባ በቃለ ዓዋዲው ገጽ 30 አንቀጽ 25 በቁጥር 1 ላይ ተመልክቷል። ክህነት የሌለው ምዕመን ታቦተ ህጉን መያዝ እንደሚገባው አልተፈቀደም። ስለዚህ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ደንብና መመሪያ መሰረት ታቦተ ህጉ አሁን ከያዘው ምዕመን እጅ ወጥቶ በካህን እጅ እንዲቀመጥ ይደረግ ብለናል።
2. የቤተክርስቲያኗ የመተዳደሪያ ደንብ ገጽ 3 ተራ ቁጥር 2 የመተዳደሪያ ደንብ ለውጥ በሚለው ሥር የሚከተለው ሃሳብ ሰፍሯል። ”ማኅበሩ እንዲፈርስ በሚደረግበት ጊዜ የሚገኘው ንብረት የቤተ ክርስቲያኑን መንፈስ የሚከተል የበጎ አድራጎት ዓላማ ላለው ማኅበር እንዲተላለፍ ይደረግ” ይላል። ማርያም ቤተክርስቲያን ናት ወይስ ማህበር? በሚል ጠይቀናል። ስንፈልግ ቤተክርስቲያን ናት እንላለን ካልሆነም ማህበራችን ናት ደስ ያለን ቀን እናፈርሳታለን ነበር መልሱ። ታዲያ ማህበር ከሆነ የጽዋ ወይም የሰንበቴ ካልሆነም የአክስዮን እንጂ ቤተክርስቲያን አለን እያሉ ማጭበርበር ተገቢ ነው አንባብያን? ከዚህ ጥዬ መውጣቴ እስካሁን ምን ትሰራ ነበር? ለምን ዘገየህ? ልባል እችላለሁ። መልሴ ቤተክርስቲያን መስሎኝ ሳላውቀው ደንባቸውን ሸሽገውኝ ነው። ደንባቸውን ባለፈው ህዳር ወር መግቢያ ላይ ሰው አሳይቶኝ ደንግጬ ባነንኩ ወገኖቼ። እውነቱ ይህ ነው። (የማህበሩን ደንብ እዚህ ላይ ተጭነው ይመልከቱት።) ገጽ 3 ላይ የማህበሩ ደንብ ማሻሻያ ጊዜ በሚለው ስር ተራ ቁጥር 2 ላይ ይመልከቱና ማርያም ማህበር እንጂ ቤተክርስቲያን ያለመሆንዋን አረጋግጡ። በአጭሩ ተጭበርብሬ ነው። እናንተ ከእኔ ተማሩ።
3. ከቀኖና ቤተክርስቲያን አንጻር ሴት ልጅ ካህናት አባቶችን ለመምራት አትችልም። ትመራም ዘንድ አይፈቀድም። አንዲት ሴት እንደ ኢትዮጵያዊ ካህን መቅደሱን ተቆጣጥራ፤ ሊቀ ካህንና የደብር አስተዳዳሪ ሆና የምትመራው ቤተክርስቲያን በእውነት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ነው? አሁን የቤተመቅደሱ መሪ ሴት አይደለችም? ይህ ጉዳይ እንዲቀየር ካህናት ቢጠይቁ ታዲያ ስህተቱ ምንድነው? ስለዚህ ወ/ሮዋ ከቤተክርስቲያን የበላይ አመራርነታቸው ተገቢ ነው? ሴት ቤተ እግዚአብሄርን ልትመራ ይገባል? በተለይ ከእኛ ቀደም አገልግሎታቸውን ትተው የሄዱት ካህን ይህን ጥያቄ በግልጽ ማቅረባቸው ይታወሳል። መልሱ ይህ ኢትዮጵያ አይደለም ተብለዋል። ታዲያ ክርስቲያን ህዝብ ሆይ! ይህ የቤተክርስቲያናችንን ቀኖና አያፈርስም? ይህ ልክ ነው ጸሐፊው?
4. ህዝበ ክርስቲያኑ በተለያየ የሥራና የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር ላይ እንዲሳተፍ በሩ ክፍት ይሁን። ቤተ ክርስቲያን የህዝብ በምትደረግበት ጊዜ ታድጋለች፤ ትሰፋለች፤ ወደሚቀጥለው ትውልድ ለመሸጋገር አያዳግታትም። ይህ ካልሆነ ግን ከፍተኛ የተሳትፎ ድርሻውን የያዘ ግለሰብ ወይም ቡድን ሲያልፍ አገልግሎትዋና እንደ ቤተክርስቲያን መቀጠልዋ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። ስለዚህ ቤተክርስቲያኗ እስከወዲያኛው ዘመን እንድትቀጥል ለህብረተሰቡ የአመራር ተሳትፎ እንዲኖረው አድርጉ አልኳቸው። በንግግር ሳይሆን በተግባር ”እንቢ ማህበራችን ውስጥ ማንም አይገባም” አሉኝ።
5. የማህበሩ ደንብ የቤተ ክርስቲያኑ የሥራ አስኪያጅ አካል ለአንድ ዓመት የሚመረጡ አምስት አባሎችና ሁለት ተለዋጮች ይኖሩታል ይላል። እነሆ እነርሱ ሰባት ዓመታቸው አልፏል። ሥልጣን ልቀቁ። ለተረኛ አስረክቡ። ወጣቱ ትውልድ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገብቶ ያገልግል። በሩን ልቀቁት ነው ያልኩት።
ይህንና ይህን የመሳሰሉትን በርካታ መስተካከል የሚገባቸውን ቁልፍ ነገሮች በዝርዝር ጽፌ ማሻሻያ እንዲያደርጉበት አቅርቤላቸዋለሁ። ባለፈው አገልግሎቱን አቋርጦ የሄደው ሌላው ካህን እባካችሁ ቤተክርስቲያንን አትዳፈሩ ብለዋቸው መክረዋቸው ነበር። ”አርፈው ይቀድሱ እንቢ ካሉ በረንዳ ይወድቃሉ” የሚል መልስ ተሰጧቸው፤ በመጨረሻም እንዴት እንዳደረጉዋቸውና እንዴት ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ የስቶክሆልም ህዝብ ያውቀዋልና ይቅር።
እኔን እንደቀደሙት ካህን ወደ ሀገር ቤት ችለው የሚያስባርሩኝ ባለመሆኔ የተያዘው መንገድ በስድብ ስሜን ማጥፋት ነው ተብሎ የብዕር ስም እንኳን ባልለጠፈ ጸሐፊ እየተሰደብኩ ነው። ቆሞስ አባ ኒቆዲሞስ ላይ ደግሞ ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ የተደረገው ሙከራ ሁሉ በእግዚአብሄር ኃይል ከሽፎባቸው ተበሳጭተው አሁን ወደ ተራ ስድብ አምርተዋል። እርሳቸው ምናልባት ወደፊት ስለራሳቸው የሚሉት ይኖራቸው ይሆናል።
ለአዲስ ቤተክርስቲያን ምሥረታ መነሻው ምክንያት ምንድነው
የዚህ ቤተ ክርስቲያን መሥራቾች በዋናነት እኔ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ (ቀሲስ ፍሰሐ ተስፋዬ) እና ቆሞስ አባ ኒቆዲሞስ አስፋው ከሌሎች ሦስት ዲያቆናት ጋር ሆነን ነው። ሌሎች የዚህ ቤተክርስቲያን መስራቾችም ቀደም ሲል እኛ ስናገለግል በነበረበት በአንድ የግል ቤተክርስቲያን ውስጥ ተገልጋይ የነበሩ ምዕመናንና ሌሎች የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያምን አባላት ናቸው።
በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ በግል ሀብታቸውና ገንዘባቸው እንዲሁም በፈቃዳቸው ቤተክርስቲያን አሠርተው ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ ያስቻሉ አሁን በሕይወት ያሉም ሆነ ያለፉ በርካታ የእምነታችን አባላት እንዳሉና እንደነበሩ ይታወቃል።
እነርሱም ቤተክርስቲያን አቋቁመው ለሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲገለገልበት አስረክበዋል። ህዝበ ክርስቲያኑም ቤተክርስቲያኑን በብጹዐን አባቶች ወይም በቆሞሳት አስባርኮ፤ ካህናትን ቀጥሮ ቤተክርስቲያኑ የጋራ ንብረታችን ነው ብሎ አምኖ ማስገልገልና ማገልገል ይጀምራል።
ካለፉት አባቶቻችን ታሪክ የምንማረው ግለሰብም ሆነ አንድ ቡድን ቤተክርስቲያን የሚያሳንጸውና አገልግሎቱ እንዲቀጥል የአቅሙን ያህል የሚያደርገው (እናንተም እንደምታደርጉት ማለት ነው)፤ የእግዚአብሔር ክብር መገለጫና አምላካዊ ፀጋና በረከት ማግኛ፤ እንዲሁም የሰማያዊውን ሕይወት በማሰብ እንጂ የገንዘብ ገቢ ማግኛ ወይም የግላዊ ክብር መግለጫ ሥፍራ በመፈለግ አይደለም።
ይሁን እንጂ ቅሉ በማንኛውም መንገድ ቤተክርስቲያን ቢመሠረትና በአበው ህግ በቀኖና ቤተክርስቲያን መሠረት የሚመራ ቢሆን አይጠላም ነበር። በስዊድን በአገልግሎት የቆየንበት፤ እንዲሁም በአንዳንድ በአውሮፓና በአሜሪካ ከተሞች የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አመሠራረት ከላይ በጠቀስነው ተቃራኒ በሆነ መልኩ ከአንድ የግል ካምፓኒ ወይም አክስዮን ማህበር ጋር ተመሳሳይነት ባለው ህግ የተመሠረቱና የሚመሩ ናቸው።
ሥልጣነ ክህነት የሌለው ምዕመን ታቦተ ህጉን እንደግል ንብረት በማሰብ እንደ ቄሰ ገበዝ ራሱን ቆጥሮ ታቦተ ህጉንም ሆነ ሌላውን ንዋየ ቅድሳት ይቆልፍበታል። ከግል ንብረት ምንም ልዩነት በሌለው መልኩ በርካታ ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን ወጣ ያሉ ድርጊቶች ይፈጸማሉ። በካህናት አባቶች እጅ ክብሩ ሳይጓደል ታቦተ ሕጉ የሚቀመጥበትን መንገድ ለማመቻቸት ብዙ ሞክረናል፤ አስተምረናል፤ መክረናል፤ ደክመናል።
የደከምነው ድካም ውጤት ሊያመጣ ባለማቻሉ በጣም ብናዝንም፤ የህዝብ ንብረት ባልሆነና በቀኖና ቤተክርስቲያን መሠረት ባልተመሠረተ የግል ተቋም ላይ ማዘኑ ተገቢ አለመሆኑን አመንን። አቤቱታ ሊቀርብ የሚችልበት መንፈሳዊም ሆነ አስተዳደራዊ መዋቅር የለም። የመተዳደሪያ ደንቡም ይህንኑ የግለሰቦችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ነው።
ማህበረ ምዕመናኑ ኢትዮጵያዊ ነው። እምነታችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ነው። ካህናት፣ ንዋየ ቅድሳት እንዲሁም የአገልግሎቱን ሥርዓት ከኢትዮጵያ አምጥተን ቤተክርስቲያን አቋቁመን ስናበቃ፤ ያቋቋምነውን ቤ/ክርስቲያን በስደት በምንኖርበት አገር ቤተክርስቲያን ደንብ እንመራዋለን ካልን እንቸገራለን።
ሴቶች እናቶቻችን በርካታ ቅድስና ያላቸውን ሥራዎች ማከናወናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት ያከበርነውን የጌታችንን ትንሳኤ ቀድመው በማየት ያበሰሩት ሴቶች ናቸው። የአይሁድን ልቅሶ፣ ሐዘንና ዋይታ ወደ ደስታ የለወጠችው አስቴር እናታችን ሴት ናት። (መጽ፣ አስቴ፥ 4፣ 3)። የሴቶች የቅድስና ስራ ከጥንት ጀምሮ ያለ ታሪክ ነው።
በሰለጠነው የምዕራባዊያን ዓለም ሴቶች ቤተክርስቲያን ይመራሉ፤ ክህነት ይቀበላሉ፤ ክህነት ይሰጣሉ፤ ሊቀ ካህን ይሆናሉ። ይህንን ህግ ተቀብለን በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ያን ተግባራዊ እናድርግ ብንል እንቸገራለን። ክህነት ለሴቶች እህቶቻችንም ሆነ እናቶቻችን አይሰጥም። ሊቀካህን ሆነው ቤተክርስቲያን ሊመሩ አይችሉም። ይህ ህግ አባቶቻችን ያስቀመጡት ነው። ዛሬ እንለውጥህ ብንለው ከድፍረት ውጭ ሊሆን አይችልምን? የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ያን የምትመራው አባቶቻችን ባኖሩልን የቤተክርስቲያናችን ህግ መሠረት ብቻ መሆኑን ለአፍታም ልንዘነጋው አይገባም።
ለወደፊት ለእኛም አገልግሎት ሆነ ለተገልጋዩ ምዕመናን ቀጣይ የአምልኮ ዘመን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጠበቀ፤ የአባቶችንም ሆነ የአገልጋይ ካህናትንና የተገልጋይ ምዕመናንን መብት ሊጠብቅና ሊያስጠብቅ፤ ሊያከብርና ሊያስከብር የሚችል፤ ንብረትነቱና ባለቤትነቱ በስዊድን ስቶክሆልም የሚኖር የመላው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ህዝበ ክርስቲያን ሀብት የሆነ፤ ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን ያላፈነገጠና በብፁዓን አባቶች የሚመራ፤ ግለሰብ እንዳሻው የማይመራው፤ ለቤተክርስቲያን የሥልጣነ ክህነት የማዕረግ ልዩነት ክብርና ትኩረት የሚሰጥ ቤተክርስቲያን መመሥረትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያናችን ሳይበረዝ ለትውልድ የማስተላለፍ ሃዋሪያዊና ታሪካዊ የሆነ አደራ እንዳለብን በማመን ለተግባራዊነቱ ተነሳን። እነርሱም ለህገ ቤተክርስቲያን አንገዛም አሉን። ምን ማድረግ እንዳለብን ወስነን ተለየናቸው።
ታዲያ ቤተክርስቲያን አስፈቅደን ከፍተን ለህዝብ ከማገልገል ወዲያ ካህንና መነኩሴ በስደት ዓለም ምን እንዲሰሩ ኢንቬስተሮቹ እንደሚፈልጉ አልገባንምና ጠይቁልን። ታዲያ አባቶች መነኮሳት ቤተክርስቲያንን መስርተው በስደት ያለውን ምዕመን ካላገለገሉ ቆብና ቀሚሳቸውን ጥለው ምን እንዲሰሩ እንደሚፈልጉ አልገባኝ።
ይህን እስቲ ማን ይጠየቅ?
አንባብያን በስቶክሆልም ስዊድን የቅ/ሥላሴ ቤ/ክርስቲያን እና የማርያም ማህበር ሲመሰረቱ በቂ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል አገልጋይ ካህን ቀርቶ ለሁለት አንድ እንኳን ካህን አልነበራቸውም። ይህንን እኔም አውቃለሁ። እኔ ስመጣ ሁለቱም ካህን አልነበራቸውም። ተመልከቱ! ካህን ያልተረከበው ታደቦት፤ ካህን የሌለው ማዕጠንት፤ ካህን የሌለው ቤተክርስቲያን ተመሰረተ። ማን ከማን ያንሳል የሚል የእልህ ቤተክርስቲያን መሆናቸው ነው። ከሥላሴ ምሥረታ በኋላ ሌላ ቤተክርስቲያን መመስረት ሳያስፈልግ በጋራ መስራት የማይቻል አልነበረም። ሥላሴ በቶሎ ወደ ሥርዓተ ቤ/ክርስቲያን ሲመለስ ሌላው በማህበርነት ቀጠለ።
ለምን ቤተክርስቲያን መሰረታችሁ? ያላቸው የለም። ብፁዕ አባታችንም የዚያኔ ቡድንተኞቹ ከመድሐኔዓለም ሲለዩ መለየታቸው ተገቢ እንዳይደለ አስተምረው መክረው ደክመው ስላልሰሟቸው ተዉአቸው። አሁን አንዱ በኢትዮጵያ ሲኖዶስ ይተዳደራል። አንዱ ደግሞ የቤተክርስቲያኑ ባለቤት በሆነ ግለሰብ ይተዳደራል።
እነርሱ ጥቂት ምዕመናን ተሰባስበው በግላቸው ያለሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ ቤተክርስቲያን ሲከፍቱ ትክክል ነን ብለው ካመኑ፤ ታዲያ ዛሬ ካህናት በህብረት ሆነው በህግ ሊቃጳጳሱን አስፈቅደው አዲስ ቤተክርስቲያን ሲያቋቁሙ ምነው ተበሳጩ? ምነው በካህናቱ ላይ ተራ የስድብ ናዳ አወረዱ? ብፁዕነታቸው ምን አድርገው ነው ይህ ወቀሳና ማስፈራሪያ የሚሰነዘርባቸው? እውነት አሁን የእምነታቸው ጉዳይ አሳስቧቸው ነው እኚህ ጸሐፊ? አይደለም!
እኔ ራሴ አቡነ ኤልያስ ስር ሆነን በውጭው ሲኖዶስ ውስጥ እንታቀፍ ብዬ ጥያቄ አቅርቤ የቤተክርስቲያንዋ ባለቤት አቡነ ኤልያስ ቤተክርስቲያኔ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለመሳለም ሊመጡ ይችሉ ይሆናል እንጂ በሌላ ሁኔታማ አይሆንም ብለውኝ አልነበረም እንዴ ትናንት? ምነው ዛሬ ቤተክርስቲያን አስከፈቱብን የሚል ጫጫታ መጣ? የስዊድን ሀገር አብያተ ክርስቲያናት የተመሠረቱት በሁለት መንገድ ነው። የመጀመሪያውና አንጋፋው የመድሃኔዓለም መንበረ ጵጵስና በአንድ የተከበሩ ታላቅ መንፈሳዊ አባት የበላይነት የሚመራ ሲሆን፤ ንብረትነቱና ሀብትነቱም በስዊድን ሀገር የሚገኝ ስደተኛ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ነው።
ሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ የተመሠረቱት የዛሬ ስድስት አመት ገደማ ከመድሃኔዓለም ቤ/ክርስቲያን ተገንጥለው የወጡ ግለሰቦች የመሰረቷቸው ናቸው። ከሁለቱ አንዱ በሀገር ቤቱ ሲኖዶስ የሚመራ ሲሆን፤ ሌላኛዋ አንዷ ደግሞ የግል ንብረት ብጤ በመሆንዋ የምትመራው ባለቤትዋ በሆነ ግለሰብ ነው።
የገረመኝ ነገር ቤተክርስቲያን መክፈት ትተን ካህናቱ ጣሪያው ላይ ያስቀመጥነውን መስቀል አውርደን ጨረቃ ወይም ኮከብ ማድረግ ነበረብን? እንዲህ ቢሆን ምን ያህላችን እንቆረቆር ነበር? እውነት አሁን ጸሐፊው ለእምነታቸው ተቆርቁረው ነው? ከተቆረቆሩ እስቲ አሉ ከሚሏቸው ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚፈጸመውንና ካህናት ተቃውመውት ለማስተካከል ጉልበት ያጡበትን ተመልክተውና ለዚያ መስተካከል ቢታገሉ ያምርብዎታል እላለሁ።
ሊቀጳጳስ ቤተክርስቲያን እንዲመሰረት ተገቢ ነው ብሎ መፍቀድ ወይም ያለመፍቀድ ከእግዚአብሄር የተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት ነው። ጸሐፊው ካህናቱን መዝለፋቸው አያስገርምም። የገረመኝ ከደረጃቸው በላይ ሊቀጳጳሱን ቤተክርስቲያን ለምን እንዲከፈት ፈቀድክ የሚል ድፍረታቸውና ማስፈራሪያቸው ነው።
ያለመታደል ሆኖ ትግሉ ማንነቱን ከደበቀ፤ የኢትዮጵያዊያን መሰባሰብ የሚያበሳጨው፤ ሁሉን ነገር እኔ ካልተቆጣጠርኩት ከሚለው፤ ሆን ብሎ ዓይኑን ካንሸዋረረ ጋር መሆኑ ያሳዝናል። ኢትዮጵያዊያንን ሊያሰባስብ ይችላል ይህ አዲሱ ቤተክርስቲያንና ብፁዕ አባታችንን አትተባበሯቸው እንበላቸው እናስፈራራቸው ብለውት አረፉት። አቡነ ኤልያስ አይፈሩም።
ለጸሐፊው የምለው እርስዎ እውነተኛ ከሆኑ ራስዎትን ”እገሌ ነኝ” ብለው በግልጽ ይቅረቡና በግንባር ከኢትዮጵያዊው አባት እግር ሥር ወድቀው ንስሓ ይግቡ እልዎታለሁ። ውሾቹ ቢጮሁም ግመሉ በፍጥነት ከማጓዝ አይገታምና በከንቱ አትድከሙ። መስላችሁ ከመኖር ሁኑና ኑሩ። ክርስትና በመሆን የሚኖርበት ህይወት እንጂ በመምሰል የሚኖርበት አይደለም።
ቀጥታ ምላሾች
ጸሐፊው ለብፁዕ አቡነ ኤልያስ በሰጡት ማሳሰቢያ የተለያዩ ሃሳቦችዎን ሰንዝረዋል።
1. በገጽ 2 ቁጥር 3 ላይ አዲስ የተመሰረተው ቤተክርስቲያን ወደፊት ይወርዳል ተብሎ ለሚጠበቀው የቤተክርስቲያን አንድነትና ሰላም በእጅጉ ጎጂ መሆኑን በማስረዳት ራሳቸውን እንዲያገሉ ጠይቀዋል።
በመሠረቱ የዚህ ጽንሰ ሃሳብ የሥጋት መነሻ መንደር የት አካባቢ እንደሆነ በግሌ አውቀዋለሁ። ነገር ግን ብፁዕ አቡነ ኤልያስም ይሁኑ የሌሎች ወንድሞቻቸው የሆኑት ብፁዓን አባቶች አቋም ጸሐፊው እንደቀባጠሩት ሳይሆን፤ ወጥ በሆነ ብሄራዊ እርቀ ሰላም ወርዶ በማንኛውም ሁኔታ ከሀገራቸው ተሰደው የወጡ ኢትዮጵያውያን ፍጹም ሰላምና ምህረት ተደርጎ ወደ ሀገራቸው መግባትና መውጣት ሲችሉ፤ የተጣሰው ቀኖና ቤተክርስቲያን ሲስተካከል እንጂ፤ አንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በቤተክርስቲያን ስም ሲነግድ ደርሰውበት ትክክለኛን ፍትሃዊ የሆነ እርምጃ በመውሰዳቸው ምክንያት እርቀ ሰላሙ ይስተጓጎላል ብለው አይስጉ - የተከበሩ ጸሐፊ።
እዚህ በሚደረገው የቤተክርስቲያን ምስረታ ላይ ሲሆን፣ ይቃወሙ ካልቻሉም ግን እንዳይተባበሩ የጠቁት፤ ጸሐፊ ሆይ! ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በዋልድባው ገዳም የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ላይ እንደ ሰሜን ጎንደሩ ሊቀ ጳጳስ ገዳም ፈርሶ በምትኩ የስኳር ፋብሪካ እንዲመሰረት እንዲተባበሩ ነው የሚፈልጉት? ወይስ በገዳማቱ ቃጠሎና ዘረፋ?
ይልቅ ባለፈው ሰሞን በተደረገው የአባቶች የእርቅ ድርድር ላይ አዲስ ቤተክርስቲያን እንዲቋቋም ለምን ፈቀዱ ያሉዋቸውና የወቀሱዋቸው ብፁዕ አባታችን አቡነ ኤልያስ ከወያኔ ተልከው ለመጡት አባቶች እነርሱ የሚኖሩትን የተንደላቀቀ ኑሮና የሚጠቀሙበትንና የሚገዛላቸውን የመኪና ዓይነት ጠቅሰው ከምንኩስና ህይወት ጋር አዛምደው ምድራዊ ድሎት ሰማያዊውን ስራቸውን ምን ያህል እንደጎዳው ጭምር አስተምረዋቸው መላካቸውን እኔ ልንገርዎት። እርስዎ ይህ እውነት መሆኑን ከሀገር ቤት አባቶችዎ ጠይቀው ይረዱ።
2. ጸሐፊው ለአንድ ከተማ አንድ ዓይነት ታቦት በቂ ነው ወደሚል ድምዳሜ ደርሰው ተጨማሪ ተመሳሳይ ታቦት አያስፈልግም በሚል ብፁዕነታቸውን ኮንነዋል። ይህ ውሳኔ በመሠረቱ በብፁዕ አቡነ ኤልያስ የተፈጸመ ሳይሆን፤ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ገብተው እውነተኛ የማርያም ቤተክርስቲያን መስሏቸው ሲወናበዱ የነበሩ የካህናትና የማህበረ ምዕመናኑ የጋራ ውሳኔ ነው።
3. ጸሐፊው አያይዘው በአንድ ፌርማታ ርቀት አዲሱ ቤተክርስቲያን እንደተመሰረተ ጽፈዋል። ብፁዕ አቡነ ኤልያስን ለመኮነን ካልሆነና ከስዊድን ውጭ የሚኖርን ሕዝብ ለማታለል ካልሆነ በቀር ከሱንድቢቤሪ እስከ ሶለንቱና ድረስ ያለው ርቀት እውነት አንድ ፌርማታ ነው? በማንኛውም ዓለም ያላችሁ አንባብያን ጎግል ማፕ ውስጥ ገብታችሁ ስቶክሆልም ከተማ ከሱንድቢቤሪ እስከ ሶሌንቱና ከእግር ጉዞ ባሻገር ያለውን የፌርማታ ብዛት ተመልከቱ። ነጭ ዉሸት ነው። እውነቱን ግን እኔ ልዘርዝረው /Sundbyberg, kalbery, Solna, Ulriksdal, Hellenelund, Sollentuna/ የሚባሉ ፌርማታዎች አሉ። ቤተክርስቲያን መፍቀዱ ችግር ይፈጥራል ያሉት ችግር ለመፍጠር ሞካሪው እርስዎና መሰሎችዎ ናችሁ እንጂ ሌላ ችግር የለም።
4. ጸሐፊው ሆይ! የብፁዕነታቸውን የቀኖና አርበኝነት ተርከውልናል። አልተሳሳቱም ልክ ነዎት። ብፁዕነታቸው ሰባት ዓመት ሙሉ የታገሉለት ቀኖና ቤተክርስቲያን ዛሬ ትግላቸው ፍሬ አፍርቶ ጸሎታቸው ሰምሮ የግል ድርጅቱ ፈርሶ በምትኩ እውነተኛይቱ በስቶክሆልም ሶሌንቱና የደብረ ቅዱሳን ምክሓ ስዱዳን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ለመመስረት በቅታለች።
ይህንን ጽሑፍ የምታነቡ ካህናት አባቶች ሆይ!
ጸሐፊ ሆይ! ለካህናት አባቶችም ጭምር ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። እዚህ ላይ በከንቱ ደክመዋል። እንደግል ድርጅት ከሌሎች ሀገሮች አትራፊ ነጋዴዎች ጋር በመተባበር የተቋቋመች ሳትሆን፤ ብቃት ባለው አደረጃጀት በሰፊ የማህበረ ምዕመናን ተሳትፎ አገልግሎት እንድትሰጥ ሆና የተመሰረተች ቤተክርስቲያን መሆኗን ሊያውቁ ይገባል።
ጸሐፊ ሆይ! እንደእርስዎ ቅስቀሳ ካህናት አባቶችን ከእኛ ከወንድሞቻቸው እንዲርቁ ለማድረግም ሞክረዋል። በካህናት ወንድሞቻችን አዕምሮ የሚመላለሰው እውነታ ግን ከዚህ የተለየ መሆኑን ልንገርዎት። በአሁኑ ሰዓት በውጭው ዓለም በስደት የሚገኙ አብዛኛዎቹ አባቶች ቤተክርስቲያን ብጤ የግል ማህበር ውስጥ እውነኛይቱን ቤተክርስቲያንን እያገለገሉ ያሉ መስሏቸው ወይም አማራጭ አጥተው የእለት ኑሯቸውን ለመግፋት ሲሉ የእጅ አዙር ሎሌነት ውስጥ ገብተው መከራ በሚያዩበት የውጪው ዓለም፤ የእኛ ቤተክርስቲያን መመስረት ለአባቶች ካህናት ታላቅ የድል ብስራት ሆኖ የሚያስደስታቸው እንጂ ከእኛ የሚያሸሻቸው ስራ ያልሰራን በመሆኑ ሊኮሩ ይገባል ብለን እናምናለን። እውነታውም ይህ ነው።
በመላው ዓለም ለምትገኙ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን አማኞች በሙሉ
በተለይ ስቶክሆልም!
የተጻፈው ነገር ሁሉ ውሸት ነው። ካህናትን እናንት ምንም አትናገሩ። ቀኖና ዶግማ ምናምን አትበሉ። ብቻ ቀድሱልን ነው የተባልነው። እኛ እንመራችኋለን፤ ብቻ ቀድሱ እናንተ። የሚመራው ቤተክርስቲያን ነው። የሚመራው ምዕመን ድቁና እንኳን የሌለው ነው። ተዉ! እኛ እንምራው ቃለዓዋዲው ለእኛ ይፈቅዳል መምራቱን አልን፤ እንቢ አሉን። ታዲያ ይቅር ሞክሩት ብለን ወጣን፤ ሌላ ምን እናድርግ? እግዚአብሔር ያሳያችሁ! የግል ድርጅት ማለት የግል ቤት ነው።
ጸሐፊው እኔን ከሌሎች ወገኖቼ ጋር ሊያጋጭ ይችል ይሆናል ብለው አስበው ይመስለኛል እኛ የአቡነ አረጋዊን ታቦት በተደራቢነት ለራሳችን የግል ዓላማ ማሳኪያ እንዳስገባን አድርገው አቅርበውታል። አሁን ይህን ማንሳት ምን ይጠቅማል? በዚያ ዙሪያ ያለውን እውነታ የማያውቅ ሰው ቢኖር ሆን ብሎ የዘነጋ ሰው ብቻ ነውና በዚህ እንኳን መቀጣጠፍ አይጠቅምም እልዎታለሁ።
ጸሐፊ ሆይ! “ይሉሽን ባልሰማስ ገበያም ባልወጣሽ” እንዲሉ በስቶክሆልም ከተማ ውስጥ በሚቋቋሙ ማህበራዊም ሆነ ሐይማኖታዊ ተቋማት ውስጥ እየገባ ህዝቡን ሲያበጣብጥ የኖረ ማን መሆኑን እርስዎም ያውቃሉ፤ የስቶክሆልም ህዝብ ያውቀዋል። የቤተክርስቲያን ማሊያ ለብሰን አክስዮን የምናጫውት ጥቅም ፈላጊዎች አንሆንም ግድ የሎትም።
እኛ የመሠረትነው ቤተክርስቲያን ለወደፊት ለእኛም አገልግሎት ሆነ ለተገልጋዩ ምዕመናን ቀጣይ የአምልኮ ዘመን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጠበቀ፤ የአባቶችንም ሆነ የአገልጋይ ካህናትንና የተገልጋይ ምዕመናንን መብት ሊጠብቅና ሊያስጠብቅ፤ ሊያከብርና ሊያስከብር የሚችል፤ ንብረትነቱና ባለቤትነቱ በስዊድን ስቶክሆልም የሚኖር የመላው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ህዝበ ክርስቲያን ሀብት የሆነ፤ ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን ያላፈነገጠና በብፁዓን አባቶች የሚመራ፤ ግለሰብ እንዳሻው የማይመራው፤ ለቤተክርስቲያን የሥልጣነ ክህነት የማዕረግ ልዩነት ክብርና ትኩረት የሚሰጥ ቤተክርስቲያን መመሥረትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያናችን ሳይበረዝ ለትውልድ የማስተላለፍ ሃዋሪያዊና ታሪካዊ የሆነ አደራ መወጣታችንን እወቁልን።
መልዕክት
አንዳንድ ካህናት በሚኖሩበት አገር ያሉትን ስደተኞች በማጽናናትና በማስተማር ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ልጆቻቸውን ቃለ እግዚአብሄር ይመግባሉ። ቀኖና ቤተክርስቲያንን ያስተምራሉ ህይወታቸውን ይለውጣሉ። አንዳንዶች ካህናት ደግሞ በተቃራኒው ሲሰሩ ማየት የተለመደ ነው። የሚከተለውን ስናገር ውስጤ ከፍተኛ ሓዘን ይሰማዋል።
አንድ ካህን ምንም አስገዳጅ የሆነ ሁኔታ ሳይኖር፤ ጦርነት በሌለበትና ሰላም ባለበት አገር ምዕመን ከሊቀጳጳስ ጋር በመጣላቱ ብቻ ምዕመኑን ለማስደሰት በሚል ካህን ቀርቶ ዲያቆን በሌለበት ሥፍራ ታቦትን የመሰለ ክቡር ነገር አጓጉዞ አምጥቶ ለምዕመን በእጅ መስጠት ተገቢ ነው ወገኖቼ? ይህንን እያደረገ ያለ ካህን ምን እየሥራ ነው ይባላል? እምነቱን እያስፋፋ ነው ወይስ ሰው እያስደሰተ? ታቦቱን ማምጣቱ ስህተት ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ታቦት ካህን በደብሩ ከሌለ ካህን ወዳለበት ደብር ተወስዶ ይዳበላል እንጂ ምን አድርግ ተብሎ ነው ለምዕመን በእጁ የሚሰጠው? በእጁ ይዞ የለመደ ምዕመን ሥልጣነ ክህነት እንዳለው ካህን ራሱን ቆጥሮ፤ እኔስ ምን ሆኛለሁ ማለት ጀምሮ ሲያበቃ ማላቀቅ ችግር ሆነ። ኧረ! እባካችሁ የአባቶችን ሥርዓት እናስጠብቅ።
ምዕመናንም ሥርዓተ ቤተክርስቲያን እንዲጠበቅ በሥርዓተ ቤተክርስቲያን ላይ በድፍረት በሚያላግጡት ላይ ጫና በማሳረፍ በማውገዝ ወደ ትክክለኛ ህጋዊ አቅጣጫ ለመመለስ በጋራ መትጋት አለብን።
እንግዲህ አበቃሁ። የጸሐፊውን ማንነት ካወቅሁ ወይም እኔ ነኝ ብሎ ራሱን ካስተዋወቀ ከተጨማሪ መረጃ ጋር እመለሳለሁ። በነገራችን ላይ ይህ በክፋትና በምቀኝነት በመነሳሳት በስም ማጥፋት ዘመቻ የዳከረ ጸሐፊ ራሴን በአግባቡ እንድገልጽ፤ ስለቤተክርስቲያኑ አመሰራረትና የነበረውን ቅድመ ሁኔታ እንዳሳውቅ ስለረዳኝ ምስጋና ለማቅረብ ባልፈቅድም፤ ፈጣሪ ሆይ ”ጸላዕትየ እኩየ ይቤሉ ላዕሌየ፣ ማእዜ ይመውት ወይሰዐር ስሙ” ቢሉኝም እኔ ጠላቴን ከፊቴ አጥፋ የማይወዱኝን ሁሉ አርቅ ብዬ አልጸልይበትም። ቸር ያክርመን!



