ኢህአዴግ የማይሰማቸው የኢህአዴግ ድምፆች
ተመስገን ደሳለኝ
‹‹...ኑሮ ተወደደ፣ ድህነት በረከተ፣ ህግ ተፋለሰ፣ አድሎአዊ አስተዳደር ሰፈነ፣ የብሔር ከፍፍሉ አስከፊ ደረጃ ደረሰ፣ ስራ አጥ ተንሰራፋ፣ ሀገር ጥሎ የሚሰደደው በዛ፣ ረሀብተኛው ስፍር ቁጥር አጣ፣ በሀገር ላይ የመኖር ዋስትና ጠፋ፣ ሰላም ደፈረሰ፣ ተስፋ መነመነ፣ ሀብት ንብረት ማፍራት ከበደ፣ አምባገነንነት ገነገነ፣ ፓርላማው በአንድ ጉልበተኛ ፓርቲ መዳፍ ወደቀ፣ በልማት ስም ያለጥናት ማፈናቀሉ ለስቃይ ዳረገ፣ ግብር የነጠቃን ያህል አደገ...ወዘተርፈ››ምንም እንኳ እነዚህ ድምፆች ከ‹‹ብሔራዊ መዝሙር›› በበለጠ በየቀኑ የሚሰሙ ቢሆንም ዋናው ባለጉዳይ ኢህአዴግ ግን ሊሰማቸው አይፈልግም። አለመፈለግ ብቻም አይደለም፤ እንዲህ አይነት ድምፆች የሚያሰሙትን በመወንጀል፣ በመፈረጅ፣ በማስፈራራት፣ በማሰር፣ በማሳደድ... ስራ ላይ ተጠምዷል። በአጠቃላይ በሀገሪቱ ላይ ሮሮአቸውን የሚያቀርቡ በሙሉ ‹‹ፀረ-መንግስት››፣ ‹‹ፀረ-ሰላም››፣ ‹‹ፀረ-ልማት›› ተብለው እየተወገዙ ነው።
እንግዲህ በኢህአዴግ ችግሩ እንዲፈታለትም ሆነ እንዲሻሻልለት የሚጠይቅ በሙሉ ‹‹የስርዓቱ ተቃዋሚ›› ተደርጎ ከተወሰደ መቼስ ምን ይደረጋል። ‹‹አውቆ የተኛ...›› ከማለት በቀር፡፡ ሆኖም የዚህ ፅሁፍ አላማ ከኢህአዴግ ውጭ ሆነው የሚጮኹ ‹‹ነባር ድምፆች››ን ማስተጋባት ሳይሆን በዛው በኢህአዴግ ውስጥ ሆነው የሚጮኹ ድምፆች ለምን ሊሰሙ እንዳልቻሉ መጠየቅ በመሆኑ ወደዛው እንለፍ።
እንደ መግቢያ
…የሀገራችን ታሪክ እንደሚነግረን የቀድሞ ነገስታቶች በአስተዳደራቸው ላይ ህዝቡ ስላለው አመለካከት መረጃ የሚያገኙት እንደዋዛ በየሜዳው ከሚውሉ እረኞች ጨዋታ ነው፡፡ እናም እነዚህ ነገስታቶች ‹‹ህዝባዊ አሮሮዎችን›› ለመስማት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ እንኳን ተነግሮአቸው ባይነገራቸውም ‹‹እረኛ ምን አለ?›› ሲሉ ይጠይቁ ነበር። መቼም ‹‹እረኛ…›› ሲሉ ህዝቡን እንጂ በመስክ ላይ ከብት ሲያገድ የሚውል ብላቴናን እንዳልሆነ ለማንም አይጠፋውም። ምክንያቱ ደግሞ የወቅቱ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ብሶቶች የሚነገሩት እንዲህ እንደዛሬው በነፃ ሚዲያ ሳይሆን በእረኛ አንደበት በመሆኑ ነው።
ወደኢህአዴግ ስትመጣ ግን የምታገኘው የዚህን ግልባጭ ነው። በያዘው ስልጣን አማካኝነት የሚቆጣጠራቸው ‹‹መንግስታዊ›› እና ‹‹ድርጅታዊ›› ሚዲያዎች ብቻ የሚነግሩትን ‹‹ካድሬ ሰራሽ ፕሮፓጋንዳ›› እንደቁም ነገር ወስዶ መግለጫ ያወጣል፤ መግለጫ ማውት ብቻም አይደለም፤ ይህንኑ ፕሮፕጋንዳ ‹‹ለነቃፊዎቹ›› እንደመከራከሪያ፣ ለአለም አቀፍ ተቋማት ደግሞ እንደ ‹‹ምላሽ›› አድርጎ ያቀርበዋል። ነገር ግን እነዚህ ሚዲያዎች ሁልጊዜም የሚያወሩት ሀገሪቱ በልማት ጎዳና ምን ያህል እየገሰገሰች እንደሆነ ብቻ ስለመሆኑ ማጣራት እንኳ አይፈልግም። በእርግጥ ይህ የኢህአዴግ ባህሪ ብቻ አይደለም፣ የሁሉም አምባገነን ገዥ ፓርቲዎችም እንጂ። የዚህ አይነት ጠቅላይ ፓርቲዎች አምባገነንት የሚያሳየን የመሪዎቻቸውን ማንአለብኝነትን ነው፡፡ ይህን ፍለጋ ብዙ መድከም ሳያስፈልግ አቶ መለስ በወጣትነታቸው በጥልቅ አፍቅሮት ወደሚያነሷቸው ማኦ ዜ ዱንግ መመልከት ይበቃል፡፡ አዎን! ማኦ ዜ ዶንግ የተባሉት ቻይናዊ አምባገነን በስልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን በሀገሪቱ ሬዲዮ የሚነበበው ግጥም እንዲህ የሚል ነበር፡-
“All rivers flow into the sea and every Red heart turns towards the sun. O chairman Mao, Chairman Mao, the mountains are tall, but not as tall as the blue sky. Rivers are deep, but not as deep as the ocean. Lamps are bright but not as bright as the sun and moon. Your kindness is taller then the sky, deeper than the ocean, and brighter than the sun and moon. It is possible to count the stars in the highest heavens, but it is impossible to count your contributions to mankind” (Peking Radio 1967 ዓ.ም. ያቀረበው ሲሆን እኔ ያገኘሁት ደግሞ “MAO NINIAN SMART” ከሚል መፅሐፍ ላይ ነው።) እናም ይህንን ‹‹መወድስ›› በቀላሉ ወደአማርኛ ስንመልሰው እንዲህ የሚል ሆኖ እናገኛዋለን፡-
‹‹ወንዞቹ ወደ ባህር ይፍሰሱ
ቀያይ ልቦች ወደ ፀሀይ ይመልከቱ
ኦ ሊቀመንበር ማኦ፣ ኦ ሊቀመንበር ማኦ
ተራሮቹ ረጃጅም ናቸው፣ ነገር ግን እንደ ሰማያዊው ሰማይ አይረዝሙም
ወንዞቹ ጥልቅ ናቸው፣ ከውቂያኖስ ግን አይጠልቁም
የአምፖሎቹም ብራሃን እንደ ፀሀይና ጨረቃ አይፈካም
ትህትናህ ከሰማይ ይሰፋል፣ ከውቅያኖስ ይጠልቃል፣
ከፀሀይና ጨረቃም በላይ ያበራል፡፡
በከፍታው ሰማይ ላይ ያሉ ከዋክብትን መቁጠር ይቻላል
አንተ ለሰው ልጆች ያደረከውን ውለታ ግን መቁጠር ያዳግታል፡፡››
ይህ በቻይንኛ የቀረበው ‹‹ውዳሴ ወማኦ›› ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ደግሞ እንዲህ የሚል ‹‹ውዳሴ ወመለስ›› ሆኖ እናገኘዋለን ‹‹ሊቀመንበር መለስ እናምንሀለን፣ አባይን የደፈረ መሪ፣ የአፍሪካ መሪ፣ ድህነትን ታግሎ ያሸነፈ፣ ታታሪ፣ ታጋይ፣ ቆራጥ፣ ብልሁ መሪ፣ የአፍሪካ ተደራዳሪ፣ የምስራቅ አፍሪካ አለቃ ከሚሉት ጀምሮ ሰለሞን ተካልኝ ‹(ለአቶ መለስ) ከቅንድብህ ውበት የሚፈልቅ› ሲል ከዘፈነው ዘፈን እስከ ትግርኛው ‹ልጅ ውለጅና ስሙን መለስ በይው› ድረስ ውዳሴ ወመለስን›› እናገኛለን። እመነኝ ይህ የየትኛውም አምባገነን መሪ ‹‹ወካይ›› ባህሪ ነው። ለሳዳም ሁሴንም ሆነ ለመሀመድ ጋዳፊ እንዲሁ ይዘፍን ነበርና። እንዳልኩህ ዛሬም ቢሆን በቋፍ ላሉት ለኢሳያስ አፈወርቂ፣ ለሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ፣ ለዑመር አልበሽር፣ ለመለስ ዜናዊ... የሚቀርበው ቅኔ መወድስ በነበረበት አለ።
…በሀገራችን ታሪክ የነበረው የቅሬታ ወይም የምስጋና አቀራረብ ‹‹እረኛ ምን አለ?›› በሚል እንደነበረ ነግሬሃለሁ። አዎን! እረኛ እንደ ፍቅር እስከመቃብሩ ‹‹ጉዱ ካሳ›› ህዝቡ በሹክሹክታ የሚያወራውን በይፋ እንዲናገር በማህበረሰቡ ባልተፃፈ ህግ የተፈቀደለት ነው። ማህበረሰቡም ይህንን ስለሚያውቅ ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ብሶቱን በእረኛ በኩል ያስተላልፋል፡፡ እናም ነገሰታቶቹ አና ደጃዝማቾቹ መኳንቶቻቸውን ሰብስበው ‹‹እረኛው በሜዳ ምን ይላል?›› ሲሉ የጠይቃሉ፡፡ ምን አልባትም፡-
‹‹አህያ መጣች ተጭና ቁልቋል
ደጃዝማች… አመድ ላይ ወድቋል›› የሚል መልስ የሰማ ደጃዝማች
አስተዳደሩን በብርቱ ይገመግማል፡፡ አሊያም አመድ ላይ መውደቅን በፀጋ ይቀበላል ማለት ነው፡፡ ሌላ እንጨምር፤ በንጉስ የስቅላት ቅጣት በተማረረ ማህበረሰብ ውስጥ ያለ እረኛ ከጋራ-ጋራ በሚገማሸር ድምፁ እንዲህ ሲል ልትሰማው ትችላለህ፡-
‹‹ወይ አልተቀደሰ የባረኩት ሰው
ንጉስ መስቀልዎን ቢተዉት ምነው››
ይህ ግን ገደብ አለው፡፡ ምክንያቱም የቻለውን ያህል በገደምዳሜ ብሶቱን ተናግሮ ለውጥ ያላገኘ እና በንጉሱ ጭካኔ ትዕግስቱ ያለቀ ህዝብ፡-
‹‹ወገራ አሳላፊ ደምቢያ እንጀራ ጣይ
ተበላህ ጎንደሬ አትነሳሞይ?›› ይልና ‹‹መሬት አንቀጥቅጥ›› የሚሉት አይነት አብዮት አሊያም ከግብፅያውያን አስር እጅ የበረታ አመፅ ሊቀሰቅስ ይችላል፡፡ እረኞችም ይቀባበሉታል፡፡ ከፈፋ-ፈፋ፣ ከገደላ-ገደል፣ ከተራራ-ተራራ በሚያስተጋባ ነጎድጓዳ ድምፅ ‹‹ተበላህ ጎንደሬ አትነሳሞይ?›› ሲሉ ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ ማለት ነው፡፡
በአስተዳዳሩ ያኮረፈ ደግሞ ሀገር ጥሎ በውድቅት ሌሊት ሲሸሽ እንዲህ ብሎ በእረኛ ያስነግራል ወይም እራሱ ይናገራል፡-
‹‹እኔ እዘጋዋለሁ ቤቴን እንዳመሉ
የት ሄደ ቢሏችሁ ከፍቶት ኼደ በሉ››፤ ይህ እንግዲህ በአዲስ መስመር ለማናሳው ሃሳብ እንደ ምሳሌ የቀረበ ነው፡፡ እናም ምሳሌውን እዚሁ ገተን፡፡ ወደ ዋናው ጉዳይ እንመለስ፡፡
እንደምታውቀው አፄ ኃይለስላሴ እና ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ከተቃዋሚዎቻቸውም ሆነ ከደጋፊዎቻቸው ምንም አይነት ተቃውሞን መስማት አይፈልጉም። ወይም እንዲሰማ አይፈቅዱም። በእርግጥ የመለስ ዜናዊ ከዚህ ይለያል። ለምን ብለህ ከጠየክ እየመረራቸውም ቢሆን በአዋጅ የ‹‹ነፃ ፕሬስ››ን ህልውና ደንግገዋልና የሚል መልስ ልታገኝ ትችላለህ። እናም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጉድለታቸውን፣ ስህተታቸውን፣ ኢ-ፍትሃዊ አካሄዳቸውን... የሚሰሙበት መንገድ አላቸው፡፡ እዚህ ጋ ግን ስተህ እንዳታስት፣ መስማትና መቀበል ለየቅል ናቸው። እኔም ብሆን ‹‹ይሰማሉ›› አልኩህ እንጂ ይቀበላሉ አላልኩም፡፡
በዚህ አይነቱ ነገር (ሰምቶ ባለመቀበል) በመለስ ዜናዊ አና በመንግስቱ ኃ/ማርያም መካከል ልዩነት የለም። ለዚህ ጉድለታቸው የሚያቀርቡት ምክንያት ያው በደርግ ዘመን እንሰማው የነበረው ‹‹አናርኪስት፣ ፀረ-አብዮተኛ፣ የኢምፔሪያሊስት ተላላኪ፣ የአረብ ቅጥረኛ፣ አቆርቋዥ፣ በፔትሮ ዶላር የሰከረ፣ ተገንጣይ፣ አስገንጣይ…›› ስማቸው ተቀይረው ‹‹ፀረ-ህገ መንግስት፣ ደርግ-ኢሠፓ፣ ፀረ-ልማት፣ ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ሻዕቢያ አልቃይዳ፣ አልሼባብ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ...›› በሚል የዚህ ዘመንም መወንጀያ ሆኗል።
ይህንን ካሴት ገልብጠን ስንሰማው ደግሞ በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ የኢህአዴጎችን ድምፅ ያሰማናል። በእርግጥ ብዙዎቻችን በኢህአዴግ ውስጥ ከሚገኙ ካድሬዎች ‹‹የእኛ አይነት ድምፅ›› የሚሰማ አይመስለንም። ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ ኢህአዴግ አይስማቸው እንጂ ድምፆቹ ተሰምተዋል፤ ምንም እንኳ የቁራ ጩኸት ሆነው ቢባክኑም። ለማስረጃ ያህልም የኤፌድሪ መከላከያ ሚንስትር አባል የሆነው ኮሎኔል ሞገስ ሀብቱን እንውሰድ። በቅድሚያም ጥቂት ስለኮለኔሉ ማንነት ልጭረፍልህ፡፡
... ኮሎኔል ሞገስ ሀብቱ በ1959 ዓ.ም. ኮረም ላይ ተወለደ። በ1976 ዓ.ም. ኢህዴንን (ብአዴን) ተቀላቀለ፡፡ እናም በታምራት ላይኔ እና በረከት ስሞኦን ይመራ የነበረው ኢህዴን ታጋይ ሆኖ ከቀድሞ መንግስት ጋር በተደረገው ወታደራዊ ግብግብ በጦር አውድ የዋለ ነባር ታጋይ ነው።
ኮሎኔሉ አሁንም የመከላከያ አባል ቢሆንም በተለያየ ጊዜ እራሱ ታግሎ ስላመጣው መንግስት አምባገነንት እና ማምታታት በተወዳጅ ግጥሞቹ ተቃውሞውን ገልፆአል፣ ተችቷልም፤ የሰማው ግን የለም። መቼም የኤፌዴሪ መከላከያውን ኮሎኔል ሞገስ ሀብቱን ሻዕቢያ፣ ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ ኦብነግ... ነው የሚል የለም። (ያው ለሃያ አመት የሰማነውን ‹‹በሬ ወለደ›› መልስ እስከምንሰማ የኮለኔሉን ታቃውሞ ማድመጣችንን ወይም ማሰላሰላችንን እንቀጥል)
ለምሳሌ ያህልም ከእነዛ የሮሮ ግጥሞቹ መሀል ‹‹መንግስት ሲጋብዝ...›› የሚለውን እንደወረደ እንየው፡-
...መቶ ሺህ ብር ይውጣ
ሰው ጠግቦ እንዲጠጣ
ውስኪውም ብዙ-ብዙ
ቢራም ብዙ-ብዙ
ምግብም-ብዙ ግዙ
ሁሉም በገፍ ይምጣ
ሰው ጠግቦ እንዲወጣ፤
እየበላህ-ብላ
እየጠጣህ ጠጣ
ከህዝብ ነው እንጂ
ካንተ ኪስ አይወጣ፤
ስትፈልግ ደፍተህ-ሌላ አዲስ አስሞላ
ምግብም ተትረፍርፏል-ተፍተህ ደግመህ ብላ
ምን ይጨመርልህ-ምን ነገር ጎደለ?
ለሂሳቡ አታስብ-ከፋይ ገበሬ አለ፤
መቼም ይህን ያለው ነባር የኢህአዴግ ታጋይ፣ ያውም የመከላከያ ኮሎኔል ባይሆን ኖሮ ‹‹ቅፅል›› ማዥጎድጎድን እና ተራ ውንጀላን እንደ ምርጥ ፕሮፖጋንዳ የሚቆጥረው ኢህአዴግ ኮለኔሉን በማጠልሸት ዘመቻው አፈር-ድሜ ባበላውም ነበር። ግና ምን ዋጋ አለው… የራስን ሰው…
እንግዲህ የግጥሙን አንጓ ይዘን ከእነ ጉልበቱ መሬት ስናወርደው በ‹‹ማዳበሪያ ዕዳ›› እንዲሁም የተቃዋሚ አባል፣ ደጋፊ እየተባለ ቁምስቅሉን ከሚያየው ገበሬ በሚሰበሰብ ገንዘብ የህወሓት ልደት፣ የብአዴን ውልደት፣ የኦህዴድ ብስራት፣ የደኢህዴን ሰርግ.... በሚል የሚካሄደውን ዘረፋ ይነግረናል፡፡
‹‹እየበላህ ብላ
እየጠጣህ ጠጣ››ም ፍንትው አድርጎ የሚያሳየን ወፋፍራም ድግሶች እንደአሸን የፈሉት በህዝብ ገንዘብ እንደሆነ ነው። እንዳልኩህ ኮለኔሉ ነባር ታጋይ ነው፤ በምርጥ ብዕሩ የነገረንም የወሬ ወሬ ሰምቶ አይደለም፡፡ የአይን እማኝ በመሆኑ የታዘበውን እንጂ፡፡ (ማስታወሻ፡- ኢህአዴግ በትጥቅ ትግሉ ዘመን በደርግ መንግስት ላይ አርሶአደሩን ለማነሳሳት ከተጠቀመበት ‹‹ፀረ-ደርግ ቅስቀሳ›› አንደኛው ደርግ ለ10ኛው አብዮት በአል ድግስ ያወጣውን መጠን የለሽ የህዝብ ገንዘብን ነው፡፡ …ታሪክ ራሱን ይደግማል ይሉሃልም ይህ ነው፤ ሌላ አይደለም)
በግልባጩ የኢህአዴግ የአመራር አባላት ‹‹ኢህአዴግ የቆመው ለገበሬው ነው›› ሲሉ ትሰማለህ፣ ወይም ሰምተሀል። የኢህአዴግ ታጋዩ ደግሞ ‹‹ከገበሬው በሚሰበሰበው ገንዘብ አስረሽ ምችው እየተባለበት ነው›› ይልሃል፡፡ በእንዲህ አይነት መልኩ የሀገር ሀብት የሚባክነው ለድርጅቶቹ ‹‹ልደት›› ብቻ አይደለም። በየስብሰባው፣ ግምገማው፣ ሴሚናሩ፣ ወርክ-ሾፑ፣ ቡና ጠጡ፣ ምልመላውም... ነው፡፡ እንዴት ያሳቅቃል ጃል? ማለቂያ አልባ ብክነት።
የሆነ ሆኖ ኮሎኔሉ የሚሰማው ባያገኝም ኢህአዴግ የሀገሪቱን አመታዊ ባጀት ሳይቀር በብድር እና ዕርዳታ በጅቶ ሉአላዊነቱን ለለጋሽ ሀገራት አሳልፎ መስጥቱንም ‹‹የመንግስታት ብድር›› በሚል ግጥሙ በጩኹት ተቃውሟል፡-
‹‹…ሞኞች ናቸው ልበል-መንግስታት አንዳንዴ
ብድር ባደባባይ-ያስፎክራል እንዴ፤
ይህንን ወሬ ሰምተን- ገርሞን ስናበቃ
ሄዱ እንባላለን-ዕዳ ለማሰረዝ
ሰጪውን ጥየቃ፤
...ትልቁ ሰውዬ ያገሪቱ መሪ
ትንሽ ማፈር የለም መልሰው ሲሄዱ...
…ወደዚያ አበዳሪ፤…
ተቀበልከውም አልተቀበልከውም ይህ የኮሎኔል ሀብቱ ግጥም የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ በየትኛው ፎርሙላ እንደሚቀመር የሚጠቁም ነው። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ‹‹አዋጭ›› እንዳልሆነ በተለያዩ ስነ-አመክንዮ የሚሞግቱ ኢኮኖሚስቶችን ሳይቀር ኢህአዴግ የሚያጣጥለው በብድር የሚሰሩ ህንፃዎችን በመቁጠር መሆኑን ለመተቸት ነውና፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ኮሎኔሉም፡-
‹‹ሞኞች ናቸው ልበል - መንግስታት አንዳንዴ
ብድር በአደባባይ ያስፎክራል እንዴ...›› ሲል የተቸው። በአናቱም አበዳሪ ሀገራት ምን ያህል ተበዳሪውን መሪ አሻንጉሊት እንደሚያደርጉ የገለፀበት ስንኝን እዚሁ ታገኘዋለህ፡-
‹‹ትልቁ ሰውዬ ያገሪቱ መሪ
ትንሽ ማፈር የለም መልሰው ሲሄዱ...
. ..ወደዚያ አበዳሪ...
የሚለውን ማለቴ ነው፡፡ እነዚህን የኢህአዴግ ድምፆች ኢህአዴግ ሊሰማ አይፈልግም። ለነገሩ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያምም አይሰሙም ነበር።
እኔና አንተ ግን እንቀጥል። እንደምታውቀው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቃል በታነፀው ጀግናው ኢህአዴግ ውስጥ ‹‹መታዘዝ›› እንጂ ‹‹ለምን?›› ማለት ለሰይፍ ይዳርጋል። ይህ ብቻ አይደለም ድርጅቱ ‹‹አለማም አጠፋምም›› ከአንተ የሚጠበቀው የታዘዝከውን ድርጅታዊ ተልዕኮ ማስፈፀም ነው። በተቀረ ማሰብ፣ መመራመር.. የሚባሉ ተፈጥሮአዊ መብቶችን ለመጠቀም መሞከሩ የማታ ማታ ከገደል እንደሚከት የብዙ መስራች ታጋዮችን አሳዛኝ ፍፃሜ ጠቅሼ ላስረዳህ እችላለሁ። ደግሞም ለዚህም ይመስለኛል ራሱ ኮሎኔል ሞገስ ሀብቱ ‹‹ተጐለት እንደቃ›› ሲል በግጥሙ የታገለለትን ድርጅት አምርሮ የተራገመው፡-
‹‹አታስብ ይለኛል-ላስብ እንጂ አምርሬ
ሌላው ጠግቦ ሲያድር-በራብ እያለቀ…
…ያገሬ ገበሬ፤
…ለምን አላስብም-አሰብ አስምሬ
የደላኝ መስሎታል-ከሱ ጋር መኖሬ፣
አታስብ ይለኛል-አንዳንዱ ከርፋፋ
ጥቁሩ ነጭ ሆኖ-እውነት እየጠፋ፣
አታስብ አትበለኝ- ንዝንዝህ ይብቃ
አንተው ማሰብ አቁም ተጐለት እንደ ዕቃ።››
መቼም የዚህን ያህል ምሬት ያውም ከነባር ታጋይ፣ ያውም ከወደ መከላከያ ተቀጣጠለ ቢባል ማን ያምናል?... በግሌ ድሮም ቢሆን ሰራዊቱ ከህዝብ ጎን እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ብሶትህ-ብሶቱ፣ እሮሮህ-እሮሮው፣ ጥቃትህ-ጥቃቱ፣ ጩኸህት-ጩኸቱ ለመሆኑ ጥርጣሬ አይግባህ። እኔን ካላመንከም እስቲ የመከላከያውን ኮሎኔል ግጥም በደንብ አስተውለው፡-
‹‹አታስብ ይለኛል- አንዳንዱ ከርፋፋ
ጥቁሩ ነጭ ሆኖ-እውነት እየጠፋ›› እናሳ! የአንተና የእኔስ ጥያቄ ምንድር ነው? ስለምን ጥቁሩን ነጭ? ረሃቡን-ጥጋብ፣ ስደቱን-ጉብኝት… ትሉናላችሁ አይደለም እንዴ? ይህ ነው ኢህአዴግ ሊሰማው ያልፈቀደው የኮሎኔሉ ድምፅ። የሰራዊቱ ጩኸት። ከታጠቀው የአፈሙዝ ላንቃ በላይ የሚጮኽ… ለዚህም ነው ደግሜ ደጋግሜ ተስፋ አለን የምልህ።
አንድ እንጨምር-ከዛው ከታጋዮች ሰፈር፡፡ ነባር የኢህአዴግ /ብአዴን/ ታጋይ ነው። ሙሉጌታ ተስፋዬ ይባላል። በአናቱም ጎበዝ ባለቅኔ ነው። በእርግጥ ከጥቂት አመት በፊት በድህነት ተሰቃይቶ ራሱን ሰቅሎ ህይወቱ አልፏል። ይህ ባለቅኔ ለእናት ድርጅቱ በግጥም የተቃውሞ ድምፁን አሰምቶ ነበር ያለፈው፡፡ ነበር ባይሰበር…ሆነ እንጂ፤ ነገር ግን ትቶ ካለፈው ግጥም ጥቂት መዝዤ ላስታውስህ። የግጥሙ ርዕስ ‹‹ተንጋላ የሞተችውን የመንታ እናት ጣር አየሁት›› ይላል።
‹‹…በመድፍ መፍቀድ ምን ይገዳል
ካያያዝ እንጂ ይቀደዳል
ወትሮም ካነጋገር እንጂ ይፈረዳል
መጀን…
ሰው ስንል ሰው ፈጀን አይደል
እንኳን ሰው ሲበደል… ወተት እየሸፈተ
ያሁኑ ይባስ ሞት ካንገት ደረሰ አሉ የታገሱት…››
አየህ! የታጋዩ ምሬት እኔ ከምልህም በላይ አልፏል። ከወደቀው ጋር ያለውን እያነፃፀረ ‹‹ያሁኑ ይባስ ሞት ካንገት ደረሰ አሉ የታገሱት›› ሲል ይጮኻል፤ ሰሚ ባያገኘም። ‹‹እሪ በከንቱ››ም ይሉሀል ይህ ነው ሌላ አይደለም። …ግና ማን ያውቃል ‹‹የመስቀል ወፍና አደይ አበባ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ›› ያለውስ ማን ነበር? ወታደር ወይስ ህዝብ? …ሁለቱም ይሆኑ? ብቻ እንጃ…
አሁን ደግሞ ታጋዩ ባለቅኔ በቀጥታ ‹‹ለመለስ ዜናዊ›› ሲል ‹‹ሹመት›› በሚል ርዕስ ያሰፈረውን ግጥም እንይ፡-
‹‹…ቢፈቅደኝ… አያሞኘኝ…
ቢያቅደኝ… ቢመኘኝ…
… አሜን ብዬ ካደርኩ… ምንአለ እሚሳነኝ
…ዕድሜ እየነገረ-ልብ እየሰረገ…
እጅ እያጋገረ-ቀን እየማገረ
ቢሾሙም… ጥንስስ ነው
ሲመጡም… እንጥስ ነው
ቢሄዱም… ብጥስ ነው
ቢኖሩም… ቅንጥስ ነው
እሁ… ተነፈስኩ
ፈሰስኩ…
እንደ ደም ባልረጋም…
ካልተሾምኩ አልሰጋም››
ይልሃል ታጋዩ ባለቅኔ።
‹‹ቢፈቅደኝ እያሞኘኝ›› ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን አካሄድም በግልፅ ይተቻል፡፡ ያውም ይህ ግጥም መታሰቢያነቱ ለራሳቸው ለጠቅላይ ሚንስትሩ እንደሆነ በ2003ዓ.ም በታተመው ‹‹የባለቅኔው ምህላ›› መፃሀፉ ገልፆ ነው የተቸው። ከዚህም አልፎ ‹‹ቢሾሙም…ጥንስስ ነው›› እያለ ባልበሰለ እና ባልተደራጀ ሁኔታ ታግሎ የመሰረተውን መንግስት ተችቷል። ሆኖም የሰማው የለም። ይህንን እና የመሳሰሉትን ድምፆች ነው ኢህአዴግ የማይሰማቸው የኢህአዴግ ድምፅ እያልኩህ ያለሁት።
ተጋዳላይ ሙሉጌታ ተስፋዬ ‹‹ከሰው መርጦ ለሹመት›› በሚል ርዕስ ካሰፈረው ቅኔ ውስጥ ደግሞ ይችን እንምዘዝ፡-
‹‹…ግራርን ለታቦት የመረጠ
ዛሬ የሱ ተራ ሲደርስ ለራሱ መሆን ተስኖት ካረጠ
ይበለው ነውጂ እሰዬ
የማየው ቀን ናፍቆ ከስዬ›› ትልና ድንገት ሳታስበው ለመለስ ዜናዊ የስልጣን መደልደል አመቻች ተደርገው ወደሚወሰዱት እነ ስዬ አብርሃ ትመራሃለች። ሆኖም ግጥሙ ቅኔ በመሆኑ፣ ቅኔ ደግሞ ስለማይብራራ ‹‹ከስዬ›› የምትለውን ቃል ሳናብራራ እንዘለዋለን።
…ተጋዳላዩ እንደገና ይጮኻል። ጩኸቱንም ባይሰሙት ለዳግም ትግል አዋጅ ይለፈፋል። የአዋጁ ርዕስ ‹‹የማረሻው ሹምሽር›› ይላል።
‹‹…አንገቱን ቁልቁል ቀልሶ…
ድፍት የሚለው የኛ ቤት ቁና?
ለማንም ዕብቅ ገለባ
ሰለባ ሁነህ ከምታነባ
አልገዛም በል አሁንም… አሻፈረኝ በል እንደገና››
እንግዲህ ይህንን ያለው እኔ ወይም የዘመን አቻዎቼ ሳይሆኑ የመለስን መንግስት ለስልጣን ለማብቃት ወጣትነቱን በትግል ያሳለፈው ታጋይ ሙሉጌታ ነው። ሙሉጌታ የማንም ተላላኪ አይደለም፤ የኢህአዴግ ታጋይ እንጂ። ሆኖም ቢከፋው፣ አምባገነንነት ነግሶ ቢያይ፣ ደጋግሞ ቢጮኽ የሚሰማው ቢያጣ ‹‹አልገዛም በል አሁንም… አሻፈረኝ በል እንደገና›› ሲል ለትግል ይቀሰቅሳል።
የሆነ ሆኖ ታጋዩ ባለቅኔ ብሶቱን ተናግሮ አልጨረሰም። እናም ‹‹እንደሰዶም›› የሚል ርዕስ በሰጠው ግጥሙ እንዲህ ይላል።
‹‹…ብቻ በቃን…
ኢትዮጵያ እጆቿን የዘረጋችው ዛሬ ነው
ሌላም ጊዜ ካምላኳ ጐን አትለይም…
ያሁኑ ግን ቁርጥ ነው
የትውልድ ጥንድ ምጥ ነው…
ሞት አንገት ላይ ደረሰ… ማህተብን ሊፈታተን…››
(በነገራችን ላይ እንዲያ ባልደረቦቼን ሳይቀር በአሸባሪነት ያስከሰሰው የ‹‹በቃን›› ተቃውሞ የመጣው ከታጋዮች መሆኑን ከታጋዩ ግጥም ገና አሁን ማወቄን አልደብቅህም) …ሞት አንገት ላይ ደርሷልና ማህተምህን ሊፈታተን ‹‹በቃ›› በለው… ይልሃል፡፡
ታጋዩ ‹‹የራበው ህዝብ መሪዎቹን ይበላል›› የምትለውን የፖለቲከኞቻችን አገላለፅም በግጥሙ ደግሞታል፡-
‹‹እጅ እንደቻለ እየቆረሰ
አፍ እንደቻለ እየጎረሰ
እንደጎኑ ካላደረ
እንደአቅሙ ካልተንደረደረ
እንደተስፋው ካላደረ
…ከእንግዲህ ቁልቁለቱን ደፍሮ
ሽቅብ ተንደርድሮ
ከነዓን ነው ዘንድሮ››
እንዴት እንዴት ታጋይ ሙሉጌታ? ከነዓን ነው ዘንድሮ? ከነዓን የት ትሆን? አብዮት አደባባይ ወይስ ታህሪር? (መቼም ባለቅኔዎች የነብይነት ፀጋ ይደረብላቸዋል ይባላል)
የሆነ ሆኖ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ በመከላከያው ኮለኔል ሞገስ ሀብቱ ምርጥ ግጥም ብንዘጋው ምን ይለናል? ደህና! የግጥሙ ርዕስ ‹‹እጅ የሰጠ ትውልድ›› ይላል፡-
…መይሳው ካሳ-አባደፋር፣ አባ ኦና
ይልቅስ እውነት ልንገርህ-የአንተን ተረት ተወውና
ቀልቡ ባህር ማዶ ላለ ለዚህ ትውልድ፣ ለዚህ አለም
ፍርሃት እጅ አለመስጠት ነው
እጅ መስጠት ነውር አይደለም››
እውነት ይሆን የትውልድ ተጋሪዎቼ ኮለኔሉ እንዳለው ቀልባችን ባህር ማዶ ኮብልሎ እጅ ሰጠ እንዴ?
ድል ለኢትዮጵያ ሰራዊት!
ፍትህ ጋዜጣ (አዲስ አበባ)



