ኢትዮጵያውያን በዚህች ሰዓት (ተሻለ መንግሥቱ)
ተሻለ መንግሥቱ
በውጪ ሀገራት የምትኖሩ ወገኖቻችን እኛ በሀገር ውስጥ ያለነው ወገኖቻችሁ እየኖርን እሚመስላችሁ ከሆነ እያልኖርን መሆናችንን ትረዱ ዘንድ ይህችን አጭር ዘገባ በጥሞና አንብቡና የምንገኝበትን ሰቆቃ ተገንዘቡልን፤ ‹እኛ› ስል ብዙዎቻችንን ማለቴ እንጂ የኀልውናችን መረጋገጥ ለኅልውናቸው ማሸብረቅ መሠረት የሆነውን እነአያ እንደልቡን እንዳልሆነ መቼም ካለተጨማሪ ማብራሪያ ይገባችኋል ብዬ እገምታለሁ።
ምንም ልታደርጉልን ባይቻላችሁ የስቃያችን አበቅቴ እንዲያጥር በጸሎታችሁ ዕርዱን። ዘወትርም አስቡን። በከፍተኛ የግፍ ዱላ ባልተወለደ አንጀት እየተደበደብን ስለሆነ ፈጣሪ ይህን በሀገራችን ቀርቶ በየትም የዓለም ክፍል ታይቶና ተሰምቶ እማይታወቅ የወገን ለወገን ግፍ ተመልክቶ ዕንባችንን እሚያብስ ደገኛና ለሀገርና ለወገን ተቆርቋሪ መንግሥት እንዲሰጠን አምርራችሁ ጸልዩልን፤ ጥቂት ከልቡ እሚጸልይ ዜጋ እንኳን ቢኖር እኮ ፈጣሪ ፊቱን እንደሚመልስልን ግልጽ ነው፤ በዘመነ ሎጥ ውስጥ በሚገኝ ሕዝብ መሃል ልባዊና ሥሙር እሚሆን ጸሎት እንደብርቅ ይቆጠራል። (ርዕሴ ከ‹ጴጥሮስ በዚያች ሰዓት› ጋር እንዲጓነፍ ያደረግሁት ሆን ብዬ ነው - ሁሉም ያው ሥቃይ ስለሆነ።)
በቀደም ዕለት አንድ ቦታ ሄድኩ። በዚያም ቦታ ይህን አሳዛኝ ነገር ሰማሁ።
አዲስ አበባ ከተማ እየታመሰች መሆንዋን መቼም ታውቃላችሁ - በተለያዩ ብዙ ምክንያች። አንደኛው ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸውና ከቀያቸው ቤታቸውን መንግሥት የፈለገውን ግምት ሰጥቶ እዲፈናቀሉና ወደሌሎች ሩቅ ሥፍራዎች እየሄዱ እንዲሠፍሩ የሚደረገው ዓይን ያወጣ ዜጎችን በንብረታቸው እንዳያዙ የሚያደርግ መንግሥታዊ የውንብድና ሥራ ነው፤ ወያኔ በአንድ አፉ የድሆች መንግሥት ነኝ እያለ በሌላው መንታ እጁ ድሆችን እያሳደደ ነው። ወይም የሱ ድሆችና የነእገሌ ድሆች የሚባል አዲስ ክፍፍል ተፈጥሯል ማለት ነው። ለነገሩ ይሄ የኮብል ስቶንና ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ እሚባለው እኮ ያጡ የነጡ ኢሕአዲጋዊ ድሆች የዕለት ጉርስ እሚያገኙበትና በጭንቅ ወቅት በመጠነኛ የውሎ አበል ክፍያ የድጋፍ ሠልፍ እሚወጡ ናቸው ይባላል። (ለመኖር ሲል ለሥልትም የሚጠጋ ሞልቷል)
በነገራችን ላይ የኢሕአዴግ በተለይ ዝቅተኛ ባለሥልጣናት - ከቀበሌ ጀምሮ - እልም ያሉ ማይሞችና ከፊደልም ከዕውቀትም ጋር የተጣሉ ደናቁርት ሊሆኑ የቻሉበት ምክንያት ሆን ተብሎ ነው ወይንስ ወደ ኢሕአዲግ ውድብ እሚጠጋ በመጠኑም ቢሆን የፊደል ዘር የለዬ ዜጋ ጠፍቶ ነው? ጭራሽ ያልገባኝና የማይገባኝ ነገር ቢኖር ይህ ነገር ነው። የትም ሂዱ እምታገኙት ባለሥልጣን በአካል እንጂ በአስተሳሰብ ሰው አይመስላችሁም። እንዴ? ጉዳይ ልታስፈጽሙ ሄዳችሁ ብታዩዋቸው ካለባበስ ጀምሮ ብዙዎቹ ጭልጥ ያሉ ባላገሮች አይደሉ እንዴ? ውራጅ ሱፍ በአዲዳስ እሚያደርጉ ሁሉ እኮ አሉ! እንዴት እነዚህ ማይማን ሀገርንና ሕዝብን ይመራሉ? ኢትዮጵያ ብላ ብላ በነሲብ የምትነዳ ሀገር ሆና ትረፈው?! ለነገሩ መለስ ለፖለቲካ አመራር ታማኝነት እንጂ መማር ዋጋ እንደሌለው ቀድሞ - አላንዳች ሀፍረትና ማመንታት - አሳውቆናል፤ ዳሩ ማንን ፈርቶ? ምን መለስ ብቻ የፒኮሎ ማኪያቬሊ መጽሐፍም እንዲሁ ነው እሚለው - ለነገሩ መለስስ የሱ ደቀ መዝሙር አይደል? ያቺን ውዳሴ ሥልጣን ሳያነብ ወደሥልጣን ማማ ማንም ዝር አይልም። ቤተ መንግሥት እኮ ቤተ ክርስቲያን አይደለም። እርኩቻና መጠላለፍ እሚበዛባት ብዙ የማር ቀፎም የተሰቀለባት ልዩ ቦታ ናት። የኋላ ኋላ የንቢቱ ንድፊያ አይጣል እንጂ።
አንድ በቤት ፈረሳ ጉዳይ ሲያለቅሱ የታዘብኳቸው ሰውዬ ታሪክ ይህን ይመስላል። የብዙዎችን ሥቃይ ስለሚወክል ባጭሩ ልግለጽላችሁ።
የሰውዬው ቤት ትንሽ ቀደም ሲል ራሳቸው ቢሸጡት ኖሮ በሚሊዮን የሚገመት ዋጋ ያወጣ ነበር፤ ሥፍራው ዐይን ቦታ ስለሆነ ማንም ይፈልገዋልና። በቅርቡ ግን ቦታው ለኢንቬሰተሮች ሊሸጥ ነው ተባለና ብር 127 ሺህ ተሰጥቷቸው እንዲለቁ ሱሪ ባንገት ዓይነት በጣም አጭር የጊዜ ገደብ ይሰጣቸዋል። በዚያ ላይ ለአፍራሻ ግብረ ኃይል ብር 20 ሺህ ከዚያው ገንዘብ ቀንሰው እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ። የግፍ ግፍ ሰውዬው ‹በራሴው አፍርሼ፣ እንድወስድ የተፈቀደልኝንም ንብረት ሳይሰባበርብኝና ሳይበካክንብኝ ይዤ ልሂድ› ቢሉም እንኳን ‹ማፍረሱን ይችላሉ፤ ነገር ግን የማፍረሻውን ሂሳብ ገቢ ማድረግ ግድ ስለሆነ ያስገባሉ› ይባላሉ። እኔንም ሆነ ማንንም በቦታው የነበርነውን ሰዎች ሊገባን ያልቻለው ሌላው ዕንቆቅልሽ ይህ ነበር። ራሳቸው ካፈረሱ ለምን የማፍረሻ ሂሳብ እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ? መንግሥት ካለሥራ አስቀምጦ እሚቀልበው አፍራሽ በድን ማለቴ ቡድን አለ ማለት ነው? የኢሕአዲግ መንግሥት ሆይ! ይህን ታውቃለህን? ግፍ ሲበዛ ለእናንተስ ጥሩ ነው ትላላችሁ? እባካችሁ ይህን ዓይነቱን ጥርሱን ያገጠጠ ብልሹ አሠራር አስተካክሉ። ሕዝብ አምርሮ እያለቀሰባችሁ ነው።
በመሠረቱ ከተሞች ሲያድጉና ሲሻሻሉ ማየት ያስደስታል እንጂ ማንንም አያስከፋም። መንገዶችና ቤቶች ሕንፃዎችም ተሠርተው ማየትን የሚጠላ የለም። ነገር ግን በዜጎች ላይ ግፍና በደል እየተሠራ የሚሠራ ቤትም ሆነ መንገድ ወይም ሕንፃ ጽናት የለውም፤ በዕንባና በልቅሶ ዋይታ የተገነባ ከተማ የኋላ ኋላ ፈራሽ ነው። ደግሞም ሕዝብን ሊያገለግል የሚገባውን የመንግሥት ሥልጣን ሕዝብን ለማስለቀስ ማዋል የበደል በደል ነው። ከአንድ ምሥኪን ዜጋ በጉልበት ቀምቶ ለአንድ ሀብታም ካሬውን በሃያና ሠላሳ ሺህ ብር እየሸጡ ድሃን ማፈናቀል በምድር እሚያስጠይቅ ወንጀል ብቻ ሳይሆን በሰማይም ነፍስን መቀመቅ እሚከት ሥርየት የሌለው ኃጢያት ነው። ለጊዜው ኀሊና በምቾት ሞራ ተሸፍኖ የማስተዋል አቅሙን ቢነጠቅም እየቆዬ ግና ለጸጸት የሚዳርግ ትልቅ ስህተት ነው። ስለዚህ ሀገርና ከተሞች ይደጉም ካልን - ማደግም አለባቸው - ድሃን ሳይበድሉና እሚገባውን እያደረጉ እንጂ እንዳሁኑ እንደወያኔ በማን አለብኝነት የሰውን የዘመናት ጥሪትና የአባት እናት ቅርስ ምሥማርና ቆርቆሮ እንኳን ሊገዛ የማይችል አልባሌ ዋጋ እየቆረጡ ቤትን በላያቸው ላይ ማፍረስ ዛሬ ባይሆን ነገ ያስጠይቃል፤ እኛም ዝም አንልም፤ ዛሬ ባንችል ነገ። ይህን ሁሉ ዕብሪትና ትምክህት ታሪክ በፈርጅ በፈርጁ እየመዘገበ ለትውልድ ፍርድ ያስቀምጠዋል።
የሌሎች ዜጎችን ብሶት ደግሞ እነሆ። አንዱ ሰውዬ የራሱ ቤት አለው። ለጊዜው መፍረስ አያሰጋውም። ነገር ግን ካርታ ፕላን እሚባለውን አንዱን ወያኔያዊ ድሆችን የማስለቀሻ ሥልት ለማውጣት የገፈገፈው ገንዘብ በዱሮው ዘመን ቢሆን ስንትና ስንት ቪላ ቤት ያሠራ ነበር። ሰውዬው በጣም ድሃ ነው። ሥራው በአንድ የመንግሥት ድርጅት ጥበቃ ነው። ባለቤቱ ባላት አነስተኛ ሥራ ባይደጎም ደመወዙ የቤተሰቡን የምግብ ፍጆታም አይሸፍንም። ዘመድ ረድቶት እንደምንም የተጠየቀውን ብዙ ገንዘብ ከፈለ - ለአፈር ግብር - ለካርታ ማውጫ - ለመሃንዲስ - ለዓመታዊ ግብርና ለመሳሰለው። በወያኔ መንግሥት መቼም ገንዘብ የማንገፈግፍበት የገቢ አ/ርዕስ/ት የለም። ይሁንና ለዚያች የራሱ ቤት እንዲከፍል የተበየነበት ብር 1567.15 ዓመታዊ ግብር ከሁሉም ይብስ የመኖር ተስፋውን አጨልሞበታል። የሚያገኘው አነስተኛ ወርኃዊ ገቢ እንኳንስ ይህን ዓመታዊ ግብር እንዲከፍል ሊያስችለው በቅጡ እንዲኖርም አላደረገውም። ይታያችሁ - እጅግ አነስተኛ በሆነ የጡረታ ገንዘብና በልመና እንዲሁም ዘመድ አዝማድ በሚወረውርለት ፍርፋሪ እሚተዳደር ዜጋ እንዴት አድርጎ ነው ይህን ያህልና ከዚህም በላይ የሚተመን ግብር እሚከፍለው? አንድ ዜጋስ በራሱ ቤት ይህን ያህል ውድ ኪራይ እንዲከፍል እሚገደደው ለምንድነው? አንድ ሰው አነስተኛ ቤት ከከተማ ውጪ ቢከራይ በዓመት ከዚህ ገንዘበ የበለጠ አይከፍልም። ዘመኑ የኡኡታ ሆነ። ብሶትን ሰሚ ጠፋ። እግዜሩም እምቢ አለ። ሰይጣኑም ሳይቀር ተጓደደብን፤ ኮራ። እነዚህን መሠሪ ነቀርሣዎች እሚነቅል ወጌሻ ባገር ጠፍቶ ዜጎች በገዛ ቀያቸው ባይተዋርና የበይ ተመልካች ሆኑ። በዘራቸውና በማንነታቸው እንዲያፍሩ እየተደገ፣ ለዓመታት ከኖሩባቸው የሀገራቸው ልዩ ልዩ ሥፍራዎች በልዩ ቀጭን የበላይ ትዕዛዝ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ በለበሷት ልብስ ብቻ እንዲባረሩ እምቢ ቢሉም እንዲገደሉ እየተደረገ … ብዙና ብዙ ግፍ እየተፈጸመ ነው። ቢሆንም ይህም ሁሉ በአግባ እየተመዘገበ ነው …
ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ፤
እስከ ማእዜኑ እግዚኦ ትረስዐኒ ለግሙራ፣
እስከ ማእዜኑ ትመይጥ ገጸከ እምኔየ።
እስከ ማእዜኑ አነብር ኀዘነ ውስተ ነፍስየ፤
ወትጼዕረኒ ልብየ ኩሎ አሚረ፣
እስከ ማእዜኑ ይትዔበዩ ጸላእትየ ላዕሌየ።
ነጽረኒ ወስምዐኒ እግዚኦ አምላኪየ።
መዝሙረ ዳዊት 12
How much longer will you forget me, Yahweh? Forever?
How much longer will you hide your face from me?
How much longer must I endure grief in my soul,
and sorrow in my heart by day and by night?
How much longer must my enemy have the upper hand of me?
Look and answer me, Yahweh my God!
ብሎ የጸለየው እንደኛው የመከራ ዶፍ ቢወርድበት ነውና እኛም ተግተን መጸለይና የፈጣሪን አፋጣኝ ምላሽ በብርቱው መሻት ይኖርብናል። አለበለዚያስ በቁማቸን አለቅን፤ሞትን።
የኑሮውን ውድነት ያየን እንደሆነ ሰው ቆሞ መሄዱ በተዓምር እንጂ የእውነት አይመስልም። እፍ ቢሏት እልም በምትል ወጠምሻ አንዴ በሚጎርሳት እንጀራ በጥብስ ስም የሚቀርብላቸሁን በቀላሉ የማይታኘክ አኞ ሥጋ ብትቆጥሩት ከአሥር ፍሬ አይበልጥም፤ ለዚያ የምትከፍሉት ግን እጅግ አነሰ ቢባል 30 ብር ነው - ሊያውም ዝቅተኛ ሆቴል ቤቶች፤ ይቺን ዓይነት ምግብ ሁለት ብትበሉም ቅም ላይላችሁ ይችላል። እነሱም አይፈረድባቸውም። አንድ ኩንታል ጤፍ 1600 እና 1700 ብር ተገዝቶ በእንጀራ ስም ማዕድ ላይ እንጀራ መቅረቡ ራሱም እሚገርም ነገር ነው። የአንድ ብር ከሃያ ሣንቲሟ ባኒ(የፈረንጅ ዳቦ) ሕጻን ልጅ ባንዴ ይጎርሳታል። ሥጋውም ለመድሓኒት እሚሆንም እየጠፋ ነው። ሥጋ መብላት ኃጢያት ነው ተብሎ በቄሰ ገበዝ የተገዘተ ይመስል የኔ ቢጤ ድሃ ሁላ መብላቱ ቀርቶብን በአሁኑ አያያዝ ማየትም ላይፈቀድልን ነው። አንድ ኪሎ ሥጋ አዲስ አበባ ላይ በጥብስ ወይ እንዳንበሣ በጥሬ ልብላ ብትል በአማካይ 150 ብር ደርሷል አሉ - እኔማ በየት አባቴን ዐውቄው። ሽሮውም የብርንዶ ያህል ሆኖብኝ እያንገዳገደኝ መጥቷል ዘመዶቼ። የኑሮ ውድነቱ በገጠሩም ብሷል ነው እሚባለው። ዕድሜ ለዚህ መከረኛ ሞባይል ሁሏም ከየአቅጣጫው ሃሎ ሃሎ እየተባባለች ኑሯችንን ሽቅብ ማጦዙን፣ የመሠረታዊ ዕቃዎችን ዋጋ በየቀኑ በሚገርም ፍጥነት ወደሰማየ ሰማያት ማጓኑን ሥራየ ብላ ተያይዛዋለች። ግን ገንዘቡን አጠራቅማ አጠራቅማ መቼና የት እንደምትበላው እግዜር ይወቅላት። ዘመናችን የገንዘብ ዕውቀታችንን ሰማይ አድርሶ የሌላ ነገር ዕውቀትና ግንዛቤያችንን ወደእንስሳቱ ዝቅተኛ የዕውቀት ደረጃ ሳያወርደው አልቀረም። የሚገርም ሀገራዊ ሥዕል ነው እያየን ያለነው - ፎቶ አያነሱት ነገር።
እነቲማቲምና ሽንኩርትማ አይነሱ። ድንችም ባቅሙ ቀን ወጥቶለታል - እንደበቆሎ ሁሉ። በቆሎ ለከብት መኖነት እንዳልዋለ ዛሬ ከስንዴና ሽምብራ ባልተናነሰ የቀለጤዎች ምግብ ሆኗል። ስኳር? የት ተገኝቶ? ምን አለፋችሁ አንድ ሺህ ብር ይዛችሁ ገበያ ብትወጡ የአሥር ሳንቲም ፌስታል እንኳን አንዳችም የረባ ዕቃ ሳትገዙ ያልቅና ቆሌያችሁን ይገፈዋል። ከዚያ ቁና ቁና እየተነፈስሽ በየጥጋጥጉ ተቀምጠሸ አሥሬ በወረቀት እያሰላሽ ከእህህሽ ጋር ወደጎጆሽ መጓዝ ነው - እየቆዘምሽና በኢትዮጵያ የመፈጠር ዕድልሽን እየተራገምሽ። ልትገዢ ካቀድሽው አሥር ነገር ውስጥ ሲሶውን ከገዛሽ በለስ ቀንቶሻል። ትራንስፖርትም ለጉድ ሆኗል። በደርግ የ5 ብር የክፍለ ሀገር ጉዞ ዛሬ በአባዱላና መሰል ሚኒባሶች ባማካይ ብር 200 ሲሆን በመንግሥት ዋሊያ ይሁን ጅግራ በሚባለው አውቶቡስ ብር 130 ግድም ነው። በከተማ ውስጥ ቀደም ሲል በ5 ብር ደርሰህ እምትመጣበት ዙረት ዛሬ ብር 30 ከበቃህ በእግርህም ተጉዘሃል ማለት ነው - በዚያውም እኮ የሰውነት ማፍታቻ ስፖርት ነው። ለአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ኮንትራት ታክሲ ብር 300 ወይም ከዚያ በላይ ቢጠሩልህ መጮህ የለብህም፤ መተው ወይም ገብተህ መሄድ - ሀገርህ ለብሶትና ሮሮ ቅንጣት ቦታ የላትም። ከፍ ሲል እንደተናገርኩት የሰው ገንዘባዊ ዕውቀት እንደ አሜሪካ የጠፈር መንኮራኩር እጅጉን ወደላይ መጥቋል ልጄ።
ገንዘብ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በዐይናችን ላይ ሂድ ተብሎ ተፈቅዶለታል። በዚህ መሃል ድሃ እየታሸች እየተወቀጠች ናት። ወሩ ዓመት ይሆንብናል። ደመወዝ ከመቀበላችን ያልቃል። ምጣት ነው - ስሑል ነበልባላዊ የሲዖል እሳት በኢትዮጵያ ወርዶ እየፈጀን ነው። የወሩ ቀናት በብርሃን ፍጥነት ሲመጡና ሲሄዱ ብታስተውልም ደመወዙ ግን ዓመትና ሁለት ዓመት ከዚያም በላይ ዘግይቶ ነው እሚደርስልህ፤ የአንጻራዊነትን ሕግ እዚህ ላይ ነው እምትረዳ ወንድማለም። ቀናት ሲከንፉ ደመወዝ ግን እየተንጠባረረብህ ለዓመታት ሲቆይብህ! በዚያ ላይ የመዋጮው ነገር ደግሞ አይነሳ፡- ‹በጠ.ሚኒስትር መለስ የተደፈረው› አባይ አለልህ - ዕድር አለልህ - የሠፈር ኮብል ስቶን ንጣፍ አለል - ት/ቤት አለልህ - ምኑ ቅጡ! እነዚህ ሁሉ ያንተን ድህነት አይረዱልህም። በጠፋ ዛፍ ከዛፍ ሸምጥጠህ የምትሰጣቸው ይመስል ሁሉም ‹አምጣ፤አምጣ›ይሉሃል። ይሉኝታ ብሎ ነገር አልፈጠረባቸውም። ከሁሉ ሆድ ደግሞ እጅግ ሰፊው - ቦርቃቃውና ከላስቲክ የተሠራው የወያኔው መንግሥት ሆድ ነው። በምንም መንገድ አይጠግብም። መጥኔ በኪራይ ቤት ለሚኖሩ እላለሁ። መጥኔ ሕጻናት ልጆች ላሏቸው እላለሁ። መጥኔ እየገዙ ለሚመገቡ እላለሁ። መጥኔ ትዳራቸውን ለሚፈቱ እላለሁ። መጥኔ ብዙ ቤተሰብ ላላቸው እላለሁ። ብቻ የማልለው የለኝም። ቢጨንቀኝ። በርግጥ ይህ ኑሮ - እኛ ከማለፋችን በፊት - ያልፍ ይሆን???
ተሻለ መንግሥቱ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)



