ተመስገን ደሳለኝ (ፍትህ ጋዜጣ - አዲስ አበባ)

ማን ይፈራል ሞት
ማን ይፈራል
ለእናት ሀገር ሲባል

(ይህንን መዝሙር ያደመጥኩት በዘንድሮ አመት የግንቦት ሃያ ዋዜማ ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በ1985 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተደርጎ የነበረ የተቃውሞ ሠልፍ ብሎ እንድንመለከተው ከጋበዘን ፕሮግራም ላይ ነው ። የኢቲቪ ዓላማ ‹‹ኢህአዴግ ያሸነፈው ደርግን ብቻ ሳይሆን ስልጣን ከያዘ በኋላ ይነሱ የነበሩ ተቃውሞዎችንም ነው›› የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ነው)


በእርግጥ ዛሬ የነበረው አፈና እና እስር በዛን ወቅትም ነበረ፡፡ ነገር ግን እንዲህ እንደዛሬው ለተቃውሞ አደባባይ መውጣት ቀርቶ ገዥውን ፓርቲ ድምፅን ከፍ አድርጎ ማማት የሚያስፈራበት ደረጃ ላይ ገና አልተደረሰም። የምዕራባውያኖችም አድናቆት በህወሓት አመራር ቆሌ ላይ ያረፈበት በመሆኑ በበረኽኞቹ ባለስልጣናት ላይ ‹‹ሆደ ሰፊነት›› የሚስተዋልባቸው ጊዜያት ይበዛሉ፡፡ ለዚህም ይመስለኛል በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ የተሸለሙ ግዙፍ ሠልፎች ላይ ሳይቀር ‹‹ማን ይፈራል ሞት ማን ይፈራል?››ን የመሳሰሉ ሀገራዊ እና ቀስቃሽ መዝሙሮችን በድፍረት እንሰማ የነበረው።

 

‹‹We will be back soldiers››


‹‹እንመለሳለን! ወታደሮች›› የምትል ግጥም የት እንዳነበብኩ ትዝ አልልህ አለኝ። የግጥሟ ባለቤት ከቼ ጉቬራ ጋር በቦሊቪያ ጫካ የመጨረሻውን ጦርነት የተካፈለ አንድ ወታደር ነው። በዛ አሳዛኝ ጦርነት እነ ቼ አስራ ሰባት ሆነው ነበር በአሜሪካ ይደገፍ ከነበረው የቦሊቪያ መንግስት ወታደሮች ጋር የተፋለሙት፡፡ በዚህ የጀብደኞች ውጊያ የመጨረሻ ውጤትም ቼ ተማረከ። ይህ ገጣሚ ወታደርም እንደ እድል ሆኖ ከጦርነቱ ተረፈ። ከዚህ በኋላም ነው የተጀመረው ህዝባዊ አብዮት መቀጠሉ እንደማይቀር ሌሎች አጋሮቹን ሲያፅናና ‹‹እንመለሳለን! ወታደሮች›› ያላቸው-በግጥሙ፡፡ …የያ ትውልድ ተጋሪው ነብይ መኮንንም ‹‹ እንመለሳለን! ጓዶች›› የምትል በእንግሊዝኛም በአማርኛም የተፃፈች ግጥም አለችው። ነብይ ይህችን ግጥም የገጠመው ጉራማይሌው ድርጅቱ ኢህአፓ እንዲህ ተበትኖ ይቀራል ብሎ ባለማሰቡ ተስፋ ሰንቆ ይሆን? ወይስ ስሙ ብቻ የቀረው ተወዳጁ ፓርቲ ተመልሶ መጥቶ ይህንን ትውልድ ያነቃቃል በሚል እሳቤ? …እንጃ! መላ ምቱ ግን ሁለቱም ቢሆን እንኳ ያሳዝናል-ተስፋው መክኗልና፡፡


በእርግጥ ያ ትውልድ የጀመረውን ሳይጨርስ፣ መደማመጥና መቻቻል እንደ ሰማይ ርቆት እርስ በእርሱ ተላለቋል። ይሄ የሚካድ አይደለም፡፡ እንዲሁም የተሸነፈው የኢህፓ የከተማ አባልና የአሲምባ ታጋይ ‹‹ጓዶች እንመለሳለን›› አይነት መልእክቱን ትቶ፣ ወጥቶ ከቀረ ከ30 አመት በላይ ሆኖታል፡፡ በዚህ በእኛ ዘመን አንድ እንኳ የተመለሰ አላየንም። ‹‹… We will be back comrades›› ከተሰኘችው የመፅናኛ ግጥም በቀር፡፡


በግልባጩ ደግሞ ከያ ትውልድ ስደትን የወረሱ ኢትዮጵያውያን ብዛታቸው ሺህ ምን ተሺ ደርሷል። ባለፈው ሳምንትም በይደር ያቆየነው ይህንኑ አጀንዳ ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን ኑሮን ስለመረጡና በታህሪር ናፍቆት ስለተቃጠሉ ኢትዮጵያውያን።


…በአስር ክልል የተዋቀረችው እምቦቀቅላዋ ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያውያኖችን አይን በእጀጉ እየሳበች ነው። ከአራት አመት በፊት በመንግስት በተደረገ ቆጠራ የደቡብ ሱዳን ህዝብ 8.26 ሚሊዮን እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የቆዳ ስፋቷ 644,629 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይደርሳል። ከሀገሪቱ ገቢ 98% የሚሆነው ከነዳጅ ዘይት የሚገኝ ነው። የማዕከላዊ ኢኳቴሪያ ስቴት የሀገሪቱ ዋና ከተማ ‹‹ጁባ›› የምትገኝበት ክልል ነው። በጁባ ለዛሬው የደቡብ ሱዳን የነፃነት ጥያቄ መልስ የሰጠው የኤስ.ፒ.ኤል.ኤ (SPLA) ድርጅት መስራች እና ሊቀመንበር የነበረው የጆን ጋራንግ መካነ መቃብር በብቸኛው አደባባይ ይገኛል። ጋራንግ ለነፃነት ትግል ወደ ጫካ ከመግባቱ በፊት በሱዳን ጦር ሠራዊት ውስጥ እስከ ኮለኔል ማዕረግ ድረስ የደረሰ ሲሆን፣ ‹‹ሉዋ ስቴት›› ከተሰኘው የአሜሪካ ዩኒቨርስቲም ፒ.ኤች.ዲውን ያገኘ ወታደር ነበር።


የሆነ ሆኖ እንደሀገር ከቆመች ገና ሁለት አመት ያልሞላት የደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች አይን የምትሞላ እየሆነች ነው። ከ6 ሺህ የማያንሱ ኢትዮጵያውያኖች በቅጥሯ ከሀገራቸው ማግኘት ያልቻሉትን ‹‹ዳቦ ፍለጋ›› እንደተሰባሰቡ ይነገራል። The Citizen, The Juba Post, South Sudan Today, New Times, Daily Monitor የተሰኙ ጋዜጦች በግል አሳታሚዎች የሚንቀሳቀሱባት ጁባ ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ብቻ ሳይሆን ለፕሬስ ነፃነት መከበርም ተስፋ ያላት ትመስላለች። በቴሌኮም ዘርፍ የተሰማሩ አራት ድርጅቶችም ፈጣን አገልግሎት ሰጪዎች ናቸው። ሌላው በደቡብ ሱዳን አስገራሚ ነገር የምናገኘው በመካላከያ ሰራዊቷ ውስጥ ነው። በትግሉ ዘመን ሽምቅ ተዋጊ የነበሩት ታጋዮች ከነፃነት በኋላ የደቡብ ሱዳን ብሄራዊ ሰራዊት ተደርገዋል፡፡ በአለማችንም ከየትኛውም ሀገር የበለጠ የጄኔራል ማዕረግ ያላቸው አዛዦች በዚሁ ሰራዊት ውስጥ ነው የሚገኙት። አስገራሚውም ነገር ይህ ነው፤ ምክንያቱም ጦርነቱ ካበቃ በኋላ አንጋፋ ታጋዮች በሙሉ ጄነራሎች እንዲሆኑ የተደረገበትን ወታደሪዊ ኮሜዲ እንመለከታለንና፡፡ በዚህም ምክንያት የጄኔራሎቹ ቁጥር ከአምስት መቶ በላይ ሊሆን ቻለና በብዛታቸው ከአለማችን ሀገራት ቀዳሚ ሆኑ። በእርግጥ የጄነራል ማዕረግን እንደ ‹‹ሬሽን›› በማደል ደቡብ ሱዳን የመጀመሪያዋ ሀገር አይደለችም፡፡ የኢህአዴግ ኢትዮጵያ ትቀድማታለች፡፡


ከዚህ ባሻገር ደቡብ ሱዳን ዛሬም ቢሆን መረጋጋት የተሳናት ሀገር ናት፤ ይህ ግን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የሚያሰጋ አይደለም። የእነሡ ስጋት በሀገራቸው ከእነቤተሰቦቻቸው በረሃብ ማለቃቸው ብቻ ነው።
በደቡብ ሱዳን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚያስችል መልኩ ኢትዮጵያውያኖች የሚገኙት የ250 ሺህ ሰው መኖሪያ በሆነው ጁባ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የተሰማሩበት የስራ መስክ በአገልግሎት ዘርፍ ወይም በጉልበት ስራ ላይ ነው፡፡ በሆቴል፣ በካፍቴሪያ፣ በፀጉር ቤት እና በሹፍርና ሙያ ላይ ሲሆን፣ ጥቂቱ ደግሞ በሱዳናውያን ‹‹ቦዳ ቦዳ›› እየተባለ በሚጠራው የሞተር ሳይክል የታክሲ አገልግሎት ይሰጣሉ።


በሀገሪቱ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪም ኤርትራዊያን፣ ዩጋንዳውያን እና ኬንያውያን በብዛት ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን የእነዚህ አገር ዜጎች በአብዛኛው የተሰማሩበት የስራ መስከ እንደ ኢትዮጵያውያኖች በዝቅተኛ (በጉልበት) ስራ አይደለም፡፡ ጠንካራ ካፒታል በሚጠይቁ የንግድ ስራዎች ጭምርም ነው፡፡ በተለይ ኤርትራውያኖቹ በዚህ በኩል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የደቡብ ሱዳንን የውሃ ፋብሪካ፣ የሀገር አቋራጭ ትራንስፖርት፣ የኮንስትራክሽን እና የመድሀኒት ማምረቻዎችን ተቆጣጥረውታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ጁባ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ የሚያስኬደውን መንገድ እየሰራ ያለው ተቋራጭ ድርጅት ንብረትነቱ የኤርትራዊያን ነው፡፡

ስለኤርትራውያኖች ጥንካሬ እና መረዳዳት በጁባ ለተገኘው ተባባሪ ዘጋቢያችን አስተያየቱን የገለፀው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ‹‹ኤርትራውያኖቹ እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ መንግስት ነው እርስ በእርስ የሚተባበሩት፡፡ አንድ ኤርትራዊ ወደ ጁባ ሲመጣ ባዶ እጁን ቢሆንም ከሶስት ወር በላይ ግን ተቀጥሮ ሲሰራ አይታይም፡፡ ምክንያቱም የሀገሩ ሰዎች መነሻ ካፒታልን ጨምሮ ለንግድ ስራ የሚያስፈልገውን በሙሉ በብድር ያሟሉለታል፡፡ እኛ ጋር ግን ይህ የለም፡፡ በተጨማሪም ከአዲስ አበባ የሚመጡ ስደተኞች ስራ የመናቅና የስንፍና ባህሪ አለባቸው›› ብሏል፡፡


ከዚህ ሌላ በወሲብ ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሴት ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ሀገራት ሴቶች በብዛታቸው ይልቃሉ፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያኖች ከሀገራቸው ሲነሱ በጉዟቸው ላይ የደላላ ጣልቃ ገብነት ከሌለ ከስድስት ሺህ እስከ ሰባት ሺህ ብር ድረስ ወጪ አድርገው ነው ወደ ሚጓጉሏት ጁባ የሚደርሱት፡፡ ነገር ግን በጉዞአቸው ላይ ደላላ ስለገባበት ብቻ እስከ 56 ሺህ ብር ድርስ አውጥተው የመጡ የደቡብ ኢትዮጵያ ተወላጆች እንዳሉ ለዘጋቢያችን አስተያየት የሰጠው ስደተኛ አረጋግጧል፡፡


የከተማው ሺሻ እና ጫት ቤት በሙሉ የተያዘው በኢትዮጵያውያን እንስቶች ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያውያኖች በየደረሱበት ሀገር መዋረዳቸውን እና መናቃቸውን የሚያሳየን በእንዲህ አይነት ስራዎች ጭምር መሰማራታቸው ነው፡፡ ለነገሩ ሀገራቸውም ቢሆኑ ይህ ውርደትና ንቀት የሚቀርላቸው አይመስለኝም፡፡ ወደ ስደት ሲሄዱም ይኽው ነው የሚያጋጥማቸው፡፡ ከነተረቱስ ‹‹ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ…›› አይደል የሚባለው፡፡ ሳይጠቀስ የማይታለፈውን እና ሀገራዊ ክብራችንን ውርድት ላይ የሚጥል አንድ አሳዛኝ ነገር ልጨምርላችሁ፡፡ አዲስ አበባ የሚገኘው የደቡብ ሱዳን ኢምባሲ ወደ ሀገራቸው መግባት የሚፈልገውን ኢትዮጵያዊ ልክ እንደ ሰሜን አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት ሁሉ የባንክ ሂሳብ መግለጫ (Bank Statement) የሚጠይቁበት መስፈርት ነው፡፡ ልብ በሉ ነፃነቷን ካገኘች እንኳ ገና ሶስት አመት ያልደፈነች ሀገር ናት ዛሬ ኢትዮጵያዊ ወደሀገሬ ሲጋባ ወጪና ገቢውን የሚያሳይ የባንክ ሰነድ ካላቀረበ አንዴ ሀገሬ ከገባ በኋላ እዚሁ ጠፍቶ ሊቀር ስለሚችል በባንክ በቂ ተቀማጭ ገንዘብ ወይም ንብረት እንዳለው አረጋግጬ ነው ቪዛ የምሰጠው ነው እያለች ያለችው፡፡ መቼም ለአንድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ከዚህ በላይ ውርድት የትም የለ፡፡ እንዲሁም በሱዳናውያን ዘንድ ‹‹ኢትዮጵያውያኖች ችግር የማይችሉ እና ሱሰኞች ተደርገው ይወሰዳሉ›› ተብሎ በራሳቸው በስደተኞቹ የሚነገረው ሌላው አሸማቃቂ ነገር ነው፡፡ እዚህ ጋር የሚነሳው ጥያቄ ‹‹እናስ! መፍትሄው ምንድር ነው?›› የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ምንአልባት በቀላሉ ‹‹የዚህ መፍትሄ ስደት ሳይሆን ለችጋርና ለውርደት የዳረገህን መንግስትህን በታህሪራውያን አይነት ሰላማዊ አብዮት ከስልጣኑ ማባረር›› የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያምም ‹‹ስደትን የኢትዮጵያውያን ባህል ያደረጉት አገዛዞች ናቸው›› ያሉበትንም አውደ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ እናም እህቶቻችን በዚህ መሰል አዋራጅ ህይወት ውስጥ እንዲያዘግሙ ያስገደዳቸውን ስርአት መታገስ እንዴት ትክክል እንደማይሆን ብዙ አይገባኝም፡፡

 

የታህሪር ናፍቆት
የቱኒዚያውያንን ዳና ተከትለው የተጓዙ ግብፃውያን ታህሪር በተሰኘው በታላቁ አደባባያቸው ተሰባስበው ሲያበቁ ለ30 ዓመት ያህል ጨፍልቆ በገዛቸው የሙባረክ መንግስት ላይ ጮኹ፤ በጣም ጮኹ። ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ይከበሩ ዘንድ ጮኹ፡፡ አስከትለውም በይስሙላ ምርጫ መታለል በቃን ሲሉ ከፒራሚዶቻቸው ርዝመት ልቆ በሚሰማ ድምፅ ጮኹ። ነገር ግን ይህ ሁሉ ጩኸት በግብፅ ሰማይ ስር ውሎ ቢያድርም የሙባረክ ቤተ መንግስት ጆሮውን ሊሰጠው አልወደደም። የታህሪር ጎበዛዝትም በጩኸታቸው ቀጠሉ። …እነሆ መጮኹ በጀመሩም በ18ኛው ቀን በዚህ ዘመን የሙባረክ መንግስት በጩኸት የፈረሰ ሁለተኛው አምባገነን መንግስት ሆነና አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተገለጠ። የግብፅ ህዝብም በነፃነት ደስታ ተሳከረ፡፡ የታህሪር ናፍቆት ማለትም ይህ ነው-ሌላ አይደለም።


አሁን ጥያቄው ‹‹ኢትዮጵያውያኖችስ ታህሪርን ይናፍቃሉን?›› የሚል ነው። በግሌ ‹‹በእርግጠኝነት ናፍቀዋል›› ከሚሉት ወገን እሰለፋለሁ። ለዚህም እውነት ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ከኑሮ ውድነት እስከ ሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ድረስ ያለው መንግስታዊ ምክንያቶች የብዙዎችን ቀልብ ወደ አብዮት አደባባይ ለመሳቡ በቂ ማረጋገጫ አይሆኑም የሚል ማን አለ? ከሃያ አንድ አመት በላይ የአንድ ፓርቲ እና የአንድ ሰው አምባገነናዊ አገዛዝም እንዲሁ ለታህሪር ናፍቆት ቀልብ ለመስጠት በቂ ነው።


በእርግጥ እዚህ ጋር ሌላም ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ‹‹ታህሪርን የናፈቀው ለውጥ ፈላጊው ብቻ ነውን?›› የሚል፡፡ ‹‹አይደለም!›› ብሎ መከራከርም ይቻላል፡፡ አቶ መለስና ፓርቲያቸውም ታህሪርን ለመናፈቃቸው ጥቆምታዎችን እያየን ነውና፡፡ ለዚህ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሚቀርቡ ትንተናዎች ጆሮ ብንሰጥ ወደ እውነታው ይገፉናል። በቅርቡ በኢትዮጵያ ተካሂዶ በነበረው የ “World Economic Forum” ስብሰባ ላይ ተገኝቶ የነበረው ጋዜጠኛ ሪቻርድ ዳውደን ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር ቃለ መጠይቅ ማድረጉ ይታወቃል። ይህ ጋዜጠኛም ከቃለ መጠይቁ በኋላ በፃፈው ኮመንተሪ ላይ መለስም ታህሪርን ለመናፈቃቸው የተለያዩ ማሳያዎችን ጠቅሶ አቅርቧል። “The Arab spring was watched closely by Ethiopians and it appears Meles senses it is coming” (ኢትዮጵያውያኖች የአረብ አብዮትን በንቃት ተመልክተውታል እናም ይህ አይነቱ ነገር እንደሚፈጠር መለስም ገብቶአቸዋል) ሲል ለሰአታት ሁለቱ ብቻ የቀዩበትን አጋጣሚ ተጠቅሞ የደረሰበትን መላምታ አስቀምጧል፡፡


ምናአልባት ብዙዎቻችን ‹‹መለስ ስለምን የህዝቡን ማመፅ ይናፍቃሉ?›› ብለን የዳወደንን መላምት ላንቀበል እንችል ይሆናል። ሆኖም መላምቱ ስጋና ደም ሊለብስ የሚችልበት እድል ሰፊ ለመሆኑ ምክንያት መጥቀስ ይቻላል። በቀላሉም ከዚህ ቀደም ዊክሊክስ የተባለው ድህረ ገፅ የአሜሪካንን ገበና በገለጠበት ጊዜ ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ በተለያየ ቦታ ፈንጅ የሚፈነዳው በራሱ በመንግስት ነው›› ሲሉ የአሜሪካው አምባሳደር ወደ ሀገራቸው ማስተላለፋቸውን አስነብቦናል። ይህንን ሴራ ታህሪርን ከመናፈቅም በላይ አድርገን ‹‹መንግስታዊ ሽብርተኝነት›› ልንለው እንችላለን፡፡ ከዚህ ሌላም ዛሬም ድረስ የቀድሞ ቅንጅት መሪዎች በድህረ ምርጫ የተከሰተውን የሰኔ አንድንም ሆነ የጥቅምት 22ቱን ‹‹የጎዳና ላይ ነውጥ›› ሆን ብሎ የፈጠረው ኢህአዴግ ነው ሲሉ የሚከራከሩበትን አንጓ ስንመዘው ‹‹ኢህአዴግ በህዝቡ ላይ የተፈጠረውን መነቃቃት ለመደምሰስና የቅንጅት መሪዎችን እስር ቤት አስገብቶ፣ ተቃዋሚዎችን በመረጠውና ከጎናቸው በቆመው ህዝብ ላይ ፍርሃትን ለማንገስ በራሱ ሰዎች የፈጠረው አመፅ ነው›› የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። በዚህ ከተስማማን የአረብ ሀገራት አብዮትን ተከትሎ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ምልክት እየታየ መሆኑ ላይ መስማማታችን አይቀሬ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱን መላምቶች ካሰናሰልን ደግሞ መለስ እንደ ድህረ ምርጫ 97 አይነት እርምጃ ለመውሰድ ከህዝቡ ቀድመው ቢዘጋጁ የሚደንቅ አይሆንም ማለት ነው፡፡


በአናቱም የስነ ልቦና ባለሙያዎች ‹‹ብዙውን ጊዜ አምባገነኖች አደጋ ይከሰታል ብለው ከጠረጠሩ አደጋው እነርሱ ባላሰቡበት እና ለቁጥጥር አስቸጋሪ በሆነበት ጊዜ ከሚከሰት በፈለጉትና በቀላሉ ሊቆጣጠሩት በሚችሉት ወቅት ሆነ ብለው እንዲከሰት ያደርጋሉ›› የሚለው ትንተናቸውን ስንደምረው ምንአልባት መለስ ሳያስቡት ህዝባቸው አብዮት አደባባይን ከሚያጥለቀልቅ ባሰቡት እና አመቺ ነው ባሉት ጊዜ፣ በቀላሉ ሊቀለበስ የሚችል አብዮት እንዲነሳ አድርገው የሀይል እርምጃ በመውሰድ ለተወሰኑ አመታት ዝም-ጭጭ ማድረግ ይፈልጋሉ የሚል ሆኖ ብናገኘው አሁንም በጨለማ ውስጥ ጥቁሯን ድመት የመፈለግ አይነት ድካም አድርገን መውሰድ የለብንም። ጆን ክላውድ የተባለ ፀሀፊ ‹‹The Psychology of dictatorship: Why Gaddafi Clings to Power›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ፁሁፍ ‹‹Dictators may fight to the end because they don’t understanding that any end is possible›› (አምባገነኖች እስከ መጨረሻው ድረስ የሚዋጉት መጨረሻ የሚባል ነገርን ስለማይረዱት ነው) ማለቱን ጠቅሶም መከራከር ይቻላል፡፡ መቼም ራሳቸው አቶ መለስ ዳውደን ስለጋዳፊ አወዳደቅ በጠየቃቸው ጊዜ “He was a malign influence on the area. His departure was less benign than we had hoped.” (ሰውየው በአካባቢው ላይ የፈጠረው ተፅእኖ ክፉ ቢሆንም ውድቀቱ ያሰብነውን ያህል በጎ አይደለም) ሲሉ በአብዮት የሚመጣ መልካም ለውጥ አለመኖሩን በገደምዳሜ ለማስተላለፍ የፈለጉበት አንጓም ሲፈረካከስ በአረብ አብዮት ስጋት ከሰላማዊ እንቅልፍ መፋታታቸውን ይጠቁማለ፡፡


በእርግጥ በሀገራችን ያለው ስርአት ዘውግ ተኮር በመሆኑ የሚነሳው አብዮት ከግብፃውያን የታህሪር ጀግኖች በተለየ መልኩ የሚታይ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ግብፆች ወደ ታህሪር ሲያቀኑ የሃይማኖትም ሆነ የብሔር ልዩነት አልፈጠሩም። ከዚህ በተጨማሪም ሁልጊዜም ራሳቸውን ‹‹የዴሞክራሲ ጠበቃ›› አድርገው የሚቆጥሩት ምዕራባውያኖች ጣልቃ ገብተው ይረዱናል የሚል ተስፋም ሰንቀው አይደለም። ይህ እንደማይሆን አስቀድመው አውቀዋልና። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን የዚህን ግልባጭ ነው የምናገኘው፡፡ ዛሬም አሜሪካንን ተስፋ ያደረጉ ፖለቲከኞቻችን ብዙ ናቸው። አስማማው ኃይሉ የተባሉ የቀድሞ የኢህአፓ ታጋይ ‹‹ከደንቢያ-ጎንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ›› በሚል ርዕስ ታሪካዊ ልቦለድ ብለው በፃፉት መጽሐፍ ላይ ምዕራባውያንን መተማመን ጉም የመዝገን ያህል መሆኑን ለመግለፅ እንዲህ ሲሉ ፅፈዋል፡-
‹‹በአፍሪካ ቀንድ ኃያል ነው ሲባል የኖረውን የደርግን መንግስት የደመሰሱ የሻዕቢያና የሕወሓት ድርጅቶች ተቀምጠው፣ ግንባር ጠዋት ፈጥረው ማታ ሲያፈርሱ ለሚስተዋሉት ተቃዋሚዎች ትኩረት የሚሰጥበት ምክንያት አልነበረም። ከዚህም ሌላ የምዕራቡ ዓለም በል ካለው ከአስር ሜትር እርቀት መርፌ እንደሚያይ ከጠመመ ደግሞ በጠራራው ፀሐይ ከጎኑ የቆመን ዝሆን ማየት እንደማይፈልግ ያልተረዱት ተቃዋሚዎች ‹ለካፒታል ሂል› መናፍስት በከንቱ ደጅ ሲጠኑ ከረሙ››


ሪቻርድ ዳውደንም ‹‹We only talked about Egypt’s role in the region, never about what was happening in side Egypt. It’s the same with Ethiopia›› (እኛ ከሙባረክ ጋር የተነጋገርነው ግብፅ በአካባቢው ላይ ስለሚኖራት ሚና ነበር። ግብፅ ውስጥ በሚፈጠሩ ነገሮች ላይ በጭራሽ አልተነጋገርንም። ከኢትዮጵያም ጋር ያለው የዚህ ተመሳሳይ ነው) በማለት አሜሪካዊ ዲፕሎማት የነገሩትን ጠቅሶ ይህንኑ ያጠናክራል።


ለዚህም ነው ግብፃውያን ለመጀመሪያ ጊዜ በታህሪር አደባባይ በተሰባሰቡበት ጊዜ በፖሊሶች ተገርፎ የተገደለ ካህሊል ሰይድ የተባለ ግብፃዊን ሞት ከጥያቄያቸው ጋር አሰናስለው ለተከታታይ ቀን ያዜሙበት፡፡ ‹‹ሁላችንም ካህሊል ሰይድ ነን›› ይላል የመዝሙሩ ርዕስ፡፡ …የዛሬ 42 አመት ወደ ኋላ ስንሄድ ደግሞ የቀድሞው ‹‹ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዩንቨርስቲ›› ተማሪ እና ‹‹የመሬት ላራሹ›› ዋነኛ አቀንቃኝ የነበረውን የጥላሁን ግዛውን በመንግስት ታጣቂዎች መገደል ተከትሎ የዩንቨርስቲው ተማሪዎችን ተከትለው መላው ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ‹‹ጥላሁን ለምን ሞተ? ለምን? ለምን ሞተ?›› ሲሉ ዘምረው አንጋፋውን ንጉሳዊ ስርአት የገረሰሱበትን ወርቃማ ታሪክ እናገኛለን፡፡ ይህ ትውልድ ደግሞ እንዲህ የሚል ይመስለኛል ‹‹የኔሰው ገብሬ ለምን ሞተ? ለምን? ለምን ሞተ?››፣ ‹‹ዳዊት ለምን ሞተ? ለምን? ለምን ሞተ?›› …
ምክንያቱ ደግሞ በርካታ ተደራራቢ እና ከባድ ጭቆናዎችን ተከትሎ የተፈጠረው የለውጥ ጥያቄ ብቸኛው መነሻም ሆነ መድርሻው ሀገር ውስጥ በመሆኑ ነው። ለዚህ ጥሪ ምላሽ የሚሰጡ የሃያ አንድ አመት ችግሮች የወለዷቸው ብዙ ቅሬታዎች አሉና። እዚህ ጋር የትውልድ ተጋሪዎቼን ወኔ ለሚጠራጠሩ የጨረፍታ ምልክታ ልስጥ። ከሃያ አንድ አመት በኋላ የምንመራው በቅዱስ ቁራን እንጂ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አይደለም፤ የሚያገለግሉንም ካድሬዎች ሳይሆኑ መንፈሳውያን መሆን አለባቸው ሲሉ ጠንካራ የፀረ-መጅሊስ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉትን ሙስሊም ወንድምና እህቶቻችንን ሀገራዊ ለውጥ ናፋቂውን ትውልድ አይወክሉም ብሎ የሚከራከር ያለ አይመስለኝም። ከማህበራዊ ድረ ገፆች ጀምሮ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ‹‹ሀገሬን ሀገሬን…›› የሚሉ አፍላ ወጣቶችም እንዲሁ በየአካባቢው የፈነጠቁ ሌላው የለውጡ ተስፋዎች ናቸው። ሃያ አመት በቅጡ ካልሞላቸው ወጣቶች (ሴቶችም ወንዶችም) ውስጥ የፖለቲካ ጋዜጣና መፅሀፍ በቀንደኝነት የሚከታተሉ እየበረከቱ የሄዱበት ዘመን ነው-ይህ ዘመን፡፡ ዛሬ ገጣሚያኖቻችንም ቢሆኑ እንደቀድሞው በቀንዳ አውጣ ስልት አይደለም እያስደመሙን ያሉት፡፡ ድንገት ገንፍለው የፍርሃትን መጋረጃ ቀዳደው ባይጥሉም ቢያንስ እየበሳሱት እንደሆነ የሚታዩ ምልክቶች አሉ፡፡


በአናቱም ሁላችንም እንደምናውቀው በ2002ቱ ምርጫ ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ አሸንፌያለሁ ብሎናል። መቼም ይህ ማለት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደጋፊዬና ወዳጄ ነው የማለት ያህል ነው። ይህ ሁኔታ ህዝቡ ከገዥው ፓርቲ ጋር ለተያያዙ ነገሮች በሚሰጠው ትኩረት ይለካ ቢባልስ? ለምሳሌ ‹‹ህዳሴ›› የተሰኘው የኢህአዴግ ጋዜጣ እና ፍትህ ጋዜጣ ቢነፃፀሩ የትኛው በስርጭት ብዛት ይበልጣል? ብለን ልንነሳ እንችላለን፡፡ ያለአንዳች ክርክርም ፍትህ ብለን ከተስማማን ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ መረጡኝ ያላቸውን ኢትዮጵያዊ ፈልገን ልናገኝ አንችልም ማለት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ከዶቼ ቬሌና ቪኦኤ የሬዲዮ ፕሮግራሞች በአድማጭ ቁጥር ማን የተሻለ ነው? የሚል ጥያቄም ማንሳት ይቻላል፡፡ አቶ መለስን አወድሰው የተፃፉ መጽሐፍቶች ከዋጋቸው በታች ሲሸጡ የነጋሶ ጊዳዳ ‹‹ዳንዲ›› መጽሐፍ ከ25ሺ ኮፒ በላይ በአጭር ቀን ውስጥ ተሽጦ ማለቁም ቢሆን የሚያመላክተው ነገር አለ። የአቶ በረከት ስምኦን ‹‹የሁለት ምርጫ ወግ›› መጽሐፍ ገዢ ሲያጣ፣ በቅርቡ ያውም ከጋዜጣ ላይ ተሰባስቦ የታተመ መፅሀፍ በአስር ቀን ውስጥ 40 ሺህ ኮፒ ተሸጦ ማለቁም የሚያስተላልፈው መልዕክት አለ።


እንዲህ አይነት የህዝብ ውሳኔዎችን ዳኛ አድርገን ብንወስድ በትውልዱ ሀገር ወዳድና የመንፈስ ጥንካሬ ላይ ጥያቄ ያላቸው ሰዎች መልስ ያገኛል ብዬ አስባለሁ። የእኔም በሀገሬ ወጣቶች ላይ የመተማመን መነሻ ይህ ነው-ሌላ አይደለም። እነዚህ ወጣቶች ናቸው ታህሪርን ተስፋ ያደረጉት። ይህ ማለት ግን በዱር በገደሉ ከሚሰደዱትም በላይ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አቅም እያላቸው ኢትዮጵያ የተፀነሰውን ፅንስ ሳይቀር አሜሪካ ሄደው በመውለድ መጭው ትውልድንም ከሀገሩ አርቀው ለስደት ያዘጋጁ ኢትዮጵያውያኖች የሉም ማለት አይደለም። ይህ እንዳለ ሆኖ በየጫት ቤቱ የሚሰበሰቡ ስርዓቱ የፈጠራቸው ‹‹ወጣት ስራ ዓጦች›› በዋነኛነት አጀንዳ አድርገው የሚያነሱት ፖለቲካ መሆኑንም ልብ ልንለው የሚገባው፡፡ እኔም እያልኩ ያለሁት ‹‹ፖለቲካ እና ኮረንቲን በሩቁ›› የሚል ፈሊጥ ተከታዮች ያሉትን ያህል ‹‹ፖለቲካ እና ኮረንቲ ብርሃን ይፈጥራሉ›› ብለው የሚያምኑና ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሄ በሀገራችን ነው ያለው የሚሉ የአዲሱ ትውልድ ብላቴናዎች በዝተዋል ነው።


የሆነ ሆኖ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች ‹‹ልጆቼ ‹ፋኖ ተሰማራ› ብለው እንዲዘምሩ አልፈልግም ሲሉ ከዚህ በኋላ የ‹‹ጓዶች እንመለሳለን›› ተስፋ የሞተ ታሪክ ነው የሚል አንድምታ ያለው መልስ ሰጥተው ነበር። ባለፈው አመት የግንቦት ሃያን በዓል አስታኮ በሚሊኒየም አዳራሽ ፓርቲያቸው በጠራው ስብሰባ ላይ ደግሞ የታህሪር ናፍቂዎች ሟርት መክሸፉን ተናግረዋል። ዘንድሮ ግን እንዲህ የሚሉ አይመስለኝም። ከፈርኦን ምድር የተነሳው የታህሪር ሽታ ወይ እየሰነፈጣቸው አሊያም እያወዳቸው ነውና። ትውልዱም ቢሆን የያ ትውልድን ‹‹ጓዶች እንመለሳለን›› መዝሙር የሚመርጠው አይመስለኝም። ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ጀምሮ የሚተወው ነገር የለምና። ምናአልባት የያ ትውልድ ወካይ በአፓርታይድ የጭቆና ዘመናት ነፃነታቸውን ለማግኘት ላይ ታች ሲሉ የዋተቱትን የደቡብ አፍሪካ ልጆችን አንድ የሀገራቸው ባለቅኔ በጠራበት መንፈስ ይናገሩም ይሆናል። እንዲህ እያሉ፡-


‹‹ተራሮችን እየወጡ፣ ወንዞችን እና ሸለቆዎችን
አቋርጠው እየመጡ ያሉት ልጆቼ ናቸው››

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ