ዮሐንስ በቀለ ከጀርመን

የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ ይከበራል። በሰኔና በህዳር ወር። በዚሁ መሰረት የ2004 ዓ.ም. የሰኔ ሚካኤል በዓል ሰኔ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. በጀርመን ኮሎኝ ከተማ በሚገኘው በደበረሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተከብሯል። ይህ ቤተክርስቲያን በሃገሪቱ የመጀመሪያውና ባሁኑም ጊዜ የራሱን ቤተክርስቲያን ገዝቶየሚገለገል ብቸኛው ቤተክርስቲያን ነው። በርካታ ሌሎች ቤተክርስቲያናትንም አፍርቷል። የተመሰረተበትን ሰላሳኛ ዓመት በሚቀጥለው የፈረንጆቹ 2013 ያከብራል፤ ዝግጅቱ ካሁኑ እየታሰበበት ነው። ሃሳቤ ስለቤተክርስቲያኑ ታሪክ ለማውራት ስላልሆነ፤ ከዚህ በላይ አልቆይበትም።

 

የዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ከላይ ባመላከትኩት ሰኔ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ስለዋለው በዓልና ከበዓሉ ጋር የተፈጠረ የግርግር አጋጣሚ ነው። በዓሉ በጣም በደመቀና ከሃገሪቱ ካራቱም ማዕዘናት በተሰባሰቡ ምዕመናን ተሳታፊነት ተከብሮ ነበር። በነገራችን ላይ፤ ሚካኤል የሚውለው ወር በገባ በ12 ነው፤ እንዴት በ10 ተከበረ የሚል ጥያቄ የምታነሱ ካላችሁ፤ ትኖራላችሁም። ጉዳዩ እንዲህ ነው፤- በስራ ቀን ማንም ምእመን ለዚህ በዓልመገኘት ስለማይችል፤ ለ12 ቀረብ የሚለውን ቅዳሜና ዕሁድን በማስደገፍ በዓሉን ማክበር አስፈላጊ ሆኗል። እንዳጋጣሚ 12 በእሁድና ቅዳሜ ላይ ካልዋለ በስተቀር፤ በዚህ መልክ ማክበሩ የተለመደ አማራጭ ሆኖ ቆይታል። ስለ 10 እና ስለ 12ም በዚሁ ይብቃኝና ወደተነሳሁበት ልሻገር፤

 

አጋጣሚ ያልኳችሁ የግርግር ጉዳይ፤ በቅድሚያ የግርግሩን መነሾ አጣርቼ እስከምደርስበት ድረስ ስለነበረው ሂደት፤- የተሰበሰበው ተሳላሚ ቁጥሩ በጣም የበዛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ አንዱ ከሌላው ጋር ለብዙጊዜ ሳይገናኝ ቆይቶ በመገናኘቱ አንገት ላንገት ተቃቅፎ መሳሳሙ፤ ሰላምታ መለዋወጡ ፋታ ስለማይሰጥ፤ በዚህ ጊዜ ቦምብም ቢፈነዳ እንኳን ፈጥኖ ለመስማት አስቸጋሪ ነበር፤ ሁሌም እንዲሁ ነው።

 

እንዲህም በመሆኑ በዚሁ ዕለት በደጀሰላሙ አዳራሽ መግቢያ ላይ የፖሊሶችን እንቅስቃሴ እየተመለከትን እንዳለን፤ ዛሬ ደግሞ ፖሊስ ምን ሊያደርግ መጣ? ሲል አንዱ ይጠይቃል፤ በቤተክርስቲያኑ አካባቢ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ስለሌለ፤ ለዚያን ዕለት የተለየ ፈቀድ በማስወጣት ብዙ መከናዎች ስለሚደረደሩ ትራፊክ እንዳይታወክ ፖሊሶችም ባካባቢው ስለሚታዩ፤ ምናልባት አንዱ ያላግባብ ፓርክ አድርጎ እሱን እየፈለጉ ይሆናል ሲል፤ ሌላውደግሞ ፖሊሶቹን የኢትዮጵያን ምግም እንዲቀምሱ ጋብዘዋቸው ይሆና በማለት መላ ሲመታ፤ በዚህ መሃልም አንድ ለየት ያለ ”ታሊባን ገብቶ ይሆናል ማን ያውቃል፤ ዘንድሮ እኮ በየኃይማኖቱ መተለብሞያ ሆኗል“ ሲል፤ አንዳንዶች ሲስቁ፤ ብዙዎቻችን ከፋይዳም አልቀጠርነውም። ሁሉም የቆየ ትዝታ እያናወዘው የባጥ የቆጡን ሲለፈልፍ፤ እንደገና በመሃሉ ደግሞ፤ አንዲት ሴት አይ! አይ! ታቦት ቆሞ እንዴት እንዲህ ይደረጋል ደሞስ ፖሊስ ባይጠራ! በማለት እያጉረመረመች በማሃላችን ታልፋለች፤ በዚህ ጊዜ ዛሬ አንድ ነገር አለ፤እስቲ አንዱን ካህን እንጠይቅ፤ እየተባባልን እነዳለን፤ ወደየቤታችን መመለሻ ጊዜ እየደረሰ ስለሆነም፤ ሕዝቡ ከቤተክርስቲያኑ ግቢ መውጣት ጀምሯል፤ እኔም እየወጣሁ እንዳለ፤ ወደመኪናዬ ለመሄድ መንገዱ ለማቋረጥ ቆም ስል፤ ከቤተክርስቲያኑ ማዶ ባለው የመንገድ ጠረዝ ላይ የቆሙ ካህናት ከቤተክርስቲያኑ እየወጣ ያለውን ሕዝብ መንገዱን አቋርጦ እንዳይሸገር፤ የተሻገረውንም እንዲመለስ እዚያው ቆዩ ወዲሕ አትምጡ ምን ታደርጋላችሁ እያሉ ሲማጠኑ ሳይ፤ አጠገቤ የቆሙ አንድ በቅርብ የማውቃቸውን ሴት ምንድነው ይሄ ግርገር? የሚያውቁት ጉዳይ አለ? ስል ጠየኳቸው፤

 

”አንዲት ያበደች ሴት ታቦቱን አጅበው ከሚሄዱት ቄሶች መካከል የቄስ እንትናን ቀሚሳቸውን ጨምድዳ ይዛ ልትደበድባቸው ይሁን ለምን አይታወቅም፤ እሳቸውም ልቀቂኝ እያሉ ሲከላከሉ በመሃሉ በጥፍሯ ቧጥጣ እጃቸውን አደማቻቸው። ይመስለኛል በዚህ ምክንያት ፖሊሶችም ተጠረተው መጥተው ይዘው እየመረመሯት ነው” አሉኝ።

 

የፖሊሱ ስም ሲጠራ ቀደም ሲል እንዳልኳችሁ በደጀሰላሙ በራፍ ላይ ስለነበረው የፖሊስ እንቅስቃሴ ሲደረደሩ የነበሩት መላምቶች ታወሱኝና፤ ታዲያ ፖሊስ ደጀሰላም አዳራሽ ምን ወሰደው ስላቸው፤ ”ያበደች“ የሚል ቅጽል የሰጧት ሴት የቄሱን እጅ በጥፍሯ ከቧጠጠችና የአካል ጉዳት ካደረሰች በሁዋላ፤ በደጀሰላሙ አዳራሽ ውስጥ ተሸሽጋ ስለነበር፤ እሷን ለመያዝ የሚደረግ የፖሊስ እንቅስቃሴ እንደነበር አረጋገጡልኝ።

 

የዚህን ጊዜ፤ ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ፤ አንድ ቆየት ያለ ተመሳሳይ ትዝታዬ እፊቴ ድቅን አለ። ከአራትና አምስት ዓመት በፊት ይሆናል በዚሁ ቤተክርስቲያን የህዳር ሚካኤል በዓል ሲከበር፤ የሆነ ጉዳይ ነው።

 

አንድ ሰው ብዙ ገጽ ያለው ጽሁፍ የዞ ወደ ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ይገባና ላንብብ ይላል፤ ቦታው አይደለም በመባል ይከለከላል፤ ከዚያ ታቦቱ ወጥቶ ቤተክርስቲያኑን በከፊል ዞሮ ከተመለሰ በሁዋላ፤ ከቤተክርስቲያኑ በራፍ ላይ ቆም ይልና አጠቃለይ ቤተክርስቲያኑን በተመለከተ በቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ንግግር ተደርጎ የማሳረጊያ ጸሎት ይፈጸምና ታቦቱ እንዲገባ ማድረግ የተለመደ ሥርዓት ስለሆነ፤ ታቦቱ በተመደበለት ቦታ ይቆማል፤ ካህናቱም አጅበው ቆመዋል። ምዕመናንም የሚደረገውን ንግግር ለማዳመጥና የመሰናበቻ ቡራኬውን ለመቀበል በጸጥታ ቆመዋል። በዚህ ጊዜ ያ ወረቀት ላንብብ ብሎ የተከለከለ ሰው፤ ታቦቱም እንደቆመ፤ ካህናቱም አጅበው እንዳሉ አስተዳዳሪው ላይ አነጣጥሮ አጭቆ የያዘውን የእንቁላል ናዳ ያወርድባቸዋል። ባጠገቡ ያሉ ምዕመናን በመረባረብ ናዳው እንዳይቀጥል ሲያቋርጡት፤ አንዲቷ ምዕመን በሴት አቅሟም ቢሆን፤ ጎሻሽማ ከምዕመናኑ መሃል እንዲፈተለክ ታደርገዋለች። ከዚያም ሰውየው እግሩ እንዳመራው ወደዚያ ቦታ ደግሞ ላይመለስ ወደሁዋላው ጠጠር ወርውሮ ይሰወራል። በሁዋላ እንደሰማሁት ”የፈሲታ ተቆጢታ“ እንዲሉ በተስኪያን ልሳለም ሄጄ ተደብድቤ ኩላሊቴ አደጋ ደርሶበታልና አስተዳዳሪው የተሳላሚዎቹን ሰላምና ጤንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ስላለበትና ይህንን ባለማድረጉ ይጠየቅልኝ ሲል ለፖሊስ አመልክቶ፤ የተጎዳው ኩላሊት ተፈልጎ ባለመገኘቱ፤ ጉዳዩ ፖሊስ ጣቢያን ሳያልፍ ባጭር ይቀጫል።

 

የሁዋላ ሁዋላ ሰውየው ያንን ያደረገበትን ምክንያት ለማወቅ ባደረግሁት ጥረትና እንደተረዳሁት፤ ጉዳዩ ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ እንደሆነና ሊያነብ ያዘጋጀውም ጽሁፍ ይህንኑ የፖለቲካ መልዕክት ለማስተላለፍ እንደነበረና በኢትዮጵያ ውስጥ የሰፈነውን ጸረ-ዴሞክራቲክ አገዛዝ ለማስወገድ የሚደረገው ትግል የኃይማኖት ተቋማትንም ተሳትፎ ጭምር ማካተት አለበት ከሚል አቋሙ የመነጨ እንደሆነ ነው። ይኸ አቋም ከሶስት ዓመት በፊት ግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዴሞክራሲንቅናቄ ”ሁለ ገብ ትግል“ ሲል ጸሎትንም ጭምር እንደሚያጠቃልል ካስቀመጠውና ብዙ ታጋይም እየደገፈው ያለ የትግል ራዕይ ጋር የሚጣጣም ሲሆን፤ እንቁላል ወርዋሪው ተጋዳላይም አፈጻጸም ላይ ስህትት ከመፈጸሙ በስተቀር፤ የሁለገብ ትግልን አስፈላጊነት ቀደም ብሎ የደረሰበት መሆኑ ያስመሰግነዋል። በእኔ እምነት በኃይማኖት ተቋማት የሚደረገው የትግል ተሳትፎ፤ የክርስቲያን ኃይማኖት ተቋማት ወገኖች የሆኑ አባቶች እንደሚሉት ”የአቡነ ዘበሰማያት ጦር ሲወረወር እንጂ ሲወጋ አይታይም“ የሚለውን መመሪያ ጠብቆ መካሄድ ስላለበት ታቦትን አጅበው በቆሙ ካህናት ላይ የእንቁላል ናዳ ማውረድን አይጨምርም። የዚህ ዓይነቱ እርምጃ በተቃራኒው መቅሰፍትን የሚጋብዝም ሊሆን ይችላልና። ምናልባት ሌሎቻችንም ይህንን ጉዳይ ብናጤነው ከጥፋት ያድነናል። ይህንን በዚህ አደብ ላሲዘውና ከሰኔ 10ሩ 2004 ዓ.ም. የኮሎኝ ደብረሰላም ቅዱስ ሚካኤል በዓል ጋር ተያይዞ አንዲትን ሴት ማዕከል አድርጎ ወደተናሳው አጋጣሚ ልመልሳችሁ።

 

ስለእንቁላል ወርዋሪው ተጋዳላይ ያቀረብኩትን ተመሳሳይ ጥያቄ በማንሳት ነበር ስለጉዳዩ ማጣራቴን የቀጠልኩት። እንደደረስኩበትም ታዲያ፤ የግጭቱ መነሻ ሴቲቱ የአካል ጉዳት ያደረሰችባቸው ካህን የቅዱሳን ማኅበር (ማኅበረ ቅዱሳን) እየተባለ በሚጠራው ድርጅት መናፍቅ ተብለው የተፈረጁ መሆናቸው እንደሆነ ማወቅ ችያለሁ። የአካል ጉዳት አድራሿም የዚህ ድርጅት አባል በመሆኗና ለኃይማኖቷ ያላት ቀናኢነትም፤ በድርጅቷ መናፍቅ ተብሎ የተፈረጀ ሰው የክህነት ልብስን ለብሶ የሚካኤልን ታቦት አጅቦ ሲሄድ ማየት የሚያስችል ትዕግስት በማጣቷ፤ የካሕኑን ቀሚስ ከሁዋላ ጨምድዳ በመያዝ፤ መናፍቁን ከታቦቱ አጠገብ ለማራቅ ባደረገችው ሙከራ የተፈጠረ ችግር መሆኑን ተረዳሁ። ማጣራቴን እንደቀጠልኩ ነኝ፤ ከዚያ በፊት ግን በመናፍቅነት ስለሚያስፈርጁ ምክንያቶች የሚከተለውን ልበል፤

 

በቅዱሳኑ ድርጅት መርህ መሰረት አንድን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታይ በመናፍቅነት ከሚያስፈርጁ ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ የቤዛይተ ዓለምን (ማርያምን) የመላዕክትንና የቅዱሳንን አማላጅነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባት እንደሆነ ያዙት፤ ወደ ማጣራቴ፦

 

በመናፍቅነት የተፈረጁትን ካህን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የማውቀቸው ሲሆን፤ ባንድ በተወሰነ ዘመን ወንጌልን ሲሰብኩ አዳምጫቸዋለሁ። ጥሩ አስተማሪ እንደሆኑም በአቅሜ ልክ የሆነ አድናቆት አለኝ። ይሁንምና ካህኑ ለተወሰነ ጊዜ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አካባቢ ርቀው፤ ምን አግኝቷቸው ወይም ምን አግኝተው እንደሆን በውል የማውቀው ባይኖርም፤ በተለምዶ ጴንጤ እየተባለ በሚጠራው በአብዛኞቹ ታላላቅ ቤተክርስቲያኖች በተስፈንጣሪነት በሚፈረጀው ቤተክርስቲያን አካባቢ የቆዩ እንደነበሩ ስለማውቅ፤ በእርግጥም እኝህ ካህን እንዴት እንደገና ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተመልሰው የራሳቸውም ሰበካ ኖሯቸው አገልግሎት ለመስጠት ቻሉ የሚለውን ጥያቄዬን ይዤ ወደሚመለከተው አካል በማቅናት የሚከተለውን መልስ እጄ ማድረግ ችያለሁ።

 

ካህኑ እንደማንኛውም በዳይ ሁሉ በደላቸውን ተናዘው፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት መሰረት ንስሃ ገብተው፤ በሊቀጳጳስ ተባርከው አግልግሎታቻውን እንዲቀጥሉ ተደርጎ፤ በዚሁ በጀርመን አገር የቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተክርስቲያን አቋቁመው እያስተዳደሩ እንደሚገኙ ተረዳሁ። ሆኖም ያቺ የኃይማኖቷ ቀናኢነት ትዕግስት የነሳት ሴት ይህንን ሳታውቅ ቀርታ ይሆን፤ ያንን ድርጊት የፈጸመችው? የሚል ተከታይ ጥያቄ አቅርቤላቸው የሰጡኝ መልስ በሚገባ እንደምታውቅ እንደሆነ ብረዳም፤

 

ምናልባት በንስሃ የማይጸዳ ልዩ ሃጢያት ነው የሚባል እንዳለና እኝህ ካህንም የዚህ ዓይነቱን ሃጢያት ፈጽመው ግንዛቤ ሳያገኝ፤ የታለፈ ካለ በማለት ለአባቶቹ አቅርቤ በንስሃ የማይወርድና የማይነጻ ኃጢያት እንደሌለ ተረዳሁ።

 

ይህንን ሁሉ ካጠናከርኩ በሁዋላ እኛ ስለግርግሩ በመጀመሪያ የጠየኳቸው ሴት ”ያበደች ሴት“ ያሉትን አስታወስኩና በእርግጥም ምናልባት የአዕምሮ መታወክ ያጋጠማት ልትሆን ትችላለች የሚለውን ድምዳሜ ከጥርጣሬ ነጻ ነው ባልልም ተቀብዬው ሃሳቤን ቋጨሁ።


ዮሐንስ በቀለ ከጀርመን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ