ታረቀኝ ሙጬ

በራስ ላይ ችግር በመፍጠር እንደህወሓት ያለ ጅላንፎ የትም የለም - ለነርሱ እርግጥ ነው የብልጣብልጥነት መለያቸው መሆኑ ነው። ኢሕአዲግ የህወሓት የመሀል አገር ስም መሆኑን መቼም ማንም አያጣውም። ለዚህ ነው በርዕሴም ሆነ በዚህ አንቀጽ መጀመሪያ ይህን የማጭበርበሪያ ካባ ላነሳ ያልወደድኩት።

 

እናም በድጋሚ ልግለጸው ወያኔ ለዘዴው ሲል መጠራት በሚፈልግበት ስያሜ ኢሕአዲግም በሉት ወይም የእውነት መጠሪያው ሊሆን በሚገባው ህወሓትም ይባል እንደዚህ ያለ ችግርን በመፍጠር የሚደሰትና በራሱም ላይ ችግርን በመፍጠር የሚታወቅ ሌላ አካል በዓለም የለም። በቀላሉ ሊያልፋቸው የሚችላቸውንና የሚገባውን መሰናክሎች ሆን ብሎ ያጦዛቸዋል - በማጦዙም እንደሚጠቀም የሚያምን ይመስለኛል። ይህን ለማለት መነሻ የሆነኝ የዛሬው የቪኦኤ ዜና ነው።

 

ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ከመጀመሬ በፊት የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ ቪኦኤ ጋብዞት ስለፍትህ ጋዜጣ ወቅታዊ ሁኔታ ይናገር ነበር። ባለፈው ዓርብ ከታተመች በኋላ ሥርጭቱ እንዳይካሄድ ስለተደረገችው የፍትህ ጋዜጣ ነበር እየተጠየቀ የነበረው። በከፍተኛ የወረቀት ግብኣት ቀረጥና ግብር እንዲሁም የማሳተሚያ ዋጋ መናር ሳቢያ በተጎሳቆለ የጋዜጣ ሽያጭ ገቢ ከመቶ ሺህ ብር በላይ እንደከሰሩ ገልጹዋል። ይህ አይደለም የተነሳሁበት ዋና ጉዳይ። ቢሆንም ግን የምትችሉ ዜጎች ያቅማችሁን ያህል የዚህችን ጋዜጣ ኅትመት ብትደግፉ ታላቅ ታሪካዊ ሥራ እንደሠራችሁ እንድታውቁት ልጠቁም እወዳለሁ። ባልረባ ነገር ከሚጠፋ ብዙ ገንዘብ ቀነስ አድርገን ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ብናውል ትውልድ ሲዘክረን ይኖራል።

 

እነዚህ ልጆች ብዙዎቻችን ተስፋ ቆርጠን እንደፍጥርጥሯ ትሁን ብለን የተውናትን ሀገር ከነጎልያድ ጋር በብዕር እየታገሉ ስላሉ ቢያንስ በገንዘባችን ልንደግፋቸው ይጠበቅብናል፤ ገንዘብ ጠፊ ነው - ምናባቱ። በመሠረቱ እነሱ ቆርጠው የተነሱት ለሞተ እህል ሳይሆን ለኅሊናቸውና ለተፈጠሩባት መሬት የነጻነት ትንሣኤ ነው። እንዴት እየኖሩ ይህችን ጋዜጣ ነፍስ ሊዘሩባት የኛንም የመኖር ተስፋ ሊያለመልሙ እንደቻሉ ልንገምት ይገባል፤ እንደኛ እንደጥቂቶቻችን ሀገር ውስጥ ወይም ውጪ ሀገር በስደት የተሻለ ሥራ ሠርተው ሊኖሩ ሲችሉ ዛሬ እታሠር ነገ በሚል ሥጋት ነፍስና ሥጋቸው እየተሟገተ በአሳዳጆቻቸው ሳዖሎች መሀል በነበልባላዊ እሳት እየተጫወቱ ያሉት ለሀገር ብለው ነውና ‹ለሠራተኛ ደመወዙን አትከልክሉት› የሚለውን መጽሐፋዊ ቃል ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም፤ ሁሉም ያልፋልና መርሳት ለሌለብን ሀገራዊ ጉዳይ ቅድሚያውን እንስጥ። ስንለግስም እንደግብዞች ለታይታና ለግብር ይውጣ ሳይሆን ከአንጀታችንና በሥውር ይሁን፤ ነገ የኢትዮጵያ አምላክ ወሮታችንን በግልጽ ይከፍለናል። ይህ ጥሪ በውጪም በሀገር ውስጥም ለሀገራቸው ሲሉ ጊዜያቸውንና መላ አቅማቸውን ለሚያውሉ ሁሉ እንዲሆንልኝ በትህትና ላሳስብ እፈልጋለሁ። በድረ ገፆች አካባቢም ለዚሁ የተቀደሰ ሀገራዊ ጉዳይ 24 ሰዓት ኮምፒውተር ላይ ተደቅነው ዐይናቸውን እያሞጨሞጩ አንጎላቸውን እያደከሙ ያሉ ወገኖቻችን የኛን ትኩረትና እገዛ ይሻሉ።

 

ካለዘር ልጅ እንደማይወለድ ሁሉ ካለገንዘብም ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም። የሁሉም ነገር ቁልፍ ገንዘብ መሆኑን አንርሳ። ገንዘብ እንኳን በዓለም በገዳምም የደም ሥር ነው። በዘመናችን ደግሞ የዓለም አበጋዝ አቶ ብሩ ስለሆነ በብዙ ገንዘብ ጥቂት ነገር ብቻ እየተገዛበት ክፉኛ ተቸግረናል፤ በዚህም ምክንያት ብዙ ገንዘብ የማግኘት አስፈላጊነት ለብዙ ነገሮች ማቀድና መሥራት የማያልፉት ቅድመ ሁኔታ ሆኗል፤ ‹ከሌለህ የለህም› ነው እኮ ብሂሉም የሚለው። ብዙውን ጊዜ የምንረሳው ነገር ስለሆነ ነው አለወትሮየ ይህን ነገር እንዲህ ያፀናሁት - መቀነቷን ፈትታ ለክርስቶስ ሙዳየ ምፅዋት ያላትን ሁሉ የለገሰችዋን የዚያችን ምሥኪን መበለት ታሪክ በማጣቀስ የመስጠትን ማጽደቅ አብዝቶ እንደሚሰብክ የቤተ ክርስቲያን ቆሞስ ሆንኩባችሁ አይደል? ይቅርታችሁን - ምን ላድርግ ‹ዋ ብሎ ጉርስ› አይቀርም ብዬ ነው። ንፋስ እየተመገቡ ለነፃነት መታገል የለም። ዘመኑ የኅብስተ መና ባለመሆኑ በዚህ ረገድ ሁሉም እንዲያስብበት የግል ጥሪየን በድጋሚና በከፍተኛ አፅንዖት ላስተላልፍ እወዳለሁ።

 

ተመልከቱ። መለስ ዜናዊ ታሟል እየተባለ በስፋት ተወርቷል፤ እየተወራም ነው። ይሄ ዜና ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ናኝቷል። የበቀደሟ ፍትህ ልትል የምትችለውም ከዚህ ያለፈ አይሆንም። የመለስ ነፍስ ገሃነም ገባች መቼም አትልም - አንደኛ የመለስ ነፍስ የት እንደምትገባ ከአንድዬ ዕውቀትና ከኛ ከምሥኪኖች ግምት በስተቀር ማንም በርግጠኝነት አያውቅም - ሁለተኛ ይሙት ይዳን ገና በውል አልተለየም። ከዚያ ባለፈ የተለመደውን ትንተና ትሰጥ እንደሆነ እንጂ ሀገር የሚበታትን አዲስ ወሬና መረጃ ይዛ አትወጣም።

 

ይህን መጻፍ ምን ክፋት አለው? እንዲያው በባዶ ሜዳ አቧራ ለማጤስ ካልተፈለገ በስተቀር ወያኔ በዚህች በሦስትና አራት ወጣቶች በምትዘጋጅ ደቃቃ ጋዜጣ ላይ ፌዴራል ወታደር ማዝመትና የታተመ ጋዜጣን ሥርጭት ማስቆም ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? ይህን ያዘዘው ነፈዝ የወያኔ ካድሬስ ማንኛው ይሆን? ምን አዲስ ነገር ሊወጣ? ነው መለስ ሲድንና ቢድን ‹ይሄውልህ እኛ ያንተ ሎሌዎች አንተ በታመምህ ጊዜ የፍትህን ጋገዜጣ ኅትመት ቀጥ አደረግናት! እስላሞችን እርስ በርስ አናጭተን ስናበቃ በመሃላቸው ገብተን ይህን ያህል ሙትና ቁስለኛ፣ ይህን ያህል ደግሞ እሥረኛ አድርገን ጠበቅንህ፤ እኛ ለአንተ መንበር የማንሆነው ነገር የለም፤ ለአቤቶሁን ዙፋን ቀናኢ መሆናችንንም ለዓለሙ አስመስክረናል!› ሊሉ አስበው ይሆን? እንዲያ ከሆነ ያድርግላቸው፤ በዚህ ሤራ ለተጎዱ ግን ፈጣሪ ይሁናቸው። እንደ እውነቱ ግን ይህ ዓይነቱ እዚያ ማዶ ጠብ አድርሰኝ ዓይነት ጠብ ያለሽ በዳቦ አስተኔ ተግባር እንደ እንግሊዝ ወታደር (በፎክላንድ ደሴት አርጀንቲናን የገጠሙ ወቅት) በጥጋብ ምድርን እየረገጡ ጦር አምጣልን ከማለት ውጭ ምንም የረባ ትርጉም የለውም።

 

አንዲት ጋዜጣ ተሰራጨች አልተሰራጨች የመለስን መታመምም ሆነ በሞት መሰናበት አታስቀርም። ግን ምን ዓይነት የልብ መደፈን ነው? ችግርን በሩቅ ለማስቀረት ከመሞከር ይልቅ መጥራትና እየመነገጉ ማባባስ የወያኔ ተፈጥሯዊ ባሕርይ እንደሆነ መቅረቱ ምን ዓይነት መረገም ይሆን እባካችሁን? እንዲያው ከመካከላቸው አንድ እንኳን ምራቅ የዋጠ መካሪ ሰው ይጥፋ? እነዚህን የመሰሉ ደናቁርት ከሦስት ሰባት ለሚበልጥ ዘመን ይግዙን? ምን ዓይነት አዙሪት ውስጥ ቢያስገቡን ይሆን እኛም የተጃጃልንላቸው? ምን እስኪያደርጉን ድረስ እንደምንጠብቅ ሳስበው ይገርመኛል።

 

በዚሁ ምሽት የቪኦኤ ዜና ሐተታ ላይ የመድረክ ፓርቲ አንድ ወጣት ባለሥልጣን ሲናገር እንደሰማሁት ወያኔ ካለመለስ ባዶ እንደሆነ በተጨባጭ ማስረጃ አስቀምጦታል፤ ነገሩ አዲስ ሳይሆን ፀሐይ የሞቀውና ብዙዎቻችን አሳምረን የምናውቀው ነው። ወያኔ ያለ መለስ ንብ የሌለው ባዶ ቀፎ ነው - አራት ነጥብ። ወንድማገኝ እንዳለው ለዚህም ነው በአንድ ሰው መታመም ምክንያት የሀገሪቱ መንግሥታዊ እንቅስቃሴ ሁሉ ከመለስተኛ የዕለት ከዕለት መደበኛ ተግባራት ውጪ ቀጥ ብሎ የቆመው። የሚገርም ነገር ነው። ደግነቱ የራሳቸው ፍጡርና ጉዳይ አስፈጻሚያቸው መሆኑ በጄ እንጂ ፈረንጆቹ በሣቅ ሳይሞቱ አይቀሩም - በተከሉት አሻንጉሊታቸው የመሣቅ መብታቸውን እናከብራለን - ሣቃቸው ኢትዮጵያን አይመለከትም። የወያኔ ኢትዮጵያ ግን የምትገርም ሀገር ናት። እኛም በዚህ የታሪክ አጥቅ ላይ የምንገኝ ዜጎች የምንገርም ሕዝብ ነን።

 

90 ሚሊዮን አካባቢ የሚገመት ሕዝብ በአንድ ሰው እስትንፋስ ሲመራ፡- ያ ሰው ሲታመም የሚታመም ሀገር፣ ያ ሰው ሲሞት ወይም ቢሞት የሚሞት (political death) ሕዝብ፣ ያ ሰው ሆስፒታል ሲገባ ሆስፒታል የሚገባ የሀገር አስተዳደር፤ ያ ሰው ICU(Intensive Care Unit) ሲገባ ICU የሚገባ ፓርላማና የ‹መንግሥት› አስተዳደር ባለቤቶች መሆናችን በዓለም ድንቃ ድንቅ ታሪኮች መዝገብ (Genius Book of Records) እንድነመዘገብ ሳያደርገን አይቀርም። እንዴት ያሳፍራል? እናንተ አታፍሩም? አደጉ ከሚባሉ አገሮች የአንዱ ሀገር ዜጋ በሆነ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ተነስቶ ‹ኦ! በዕቅዳችን መሠረት በርግጥም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ሞቷን ጨርሳ ሞታለችና የቀብር ሥነ ሥርዓቷን ሳትበለሻሽ በጊዜ እናከናውን!› ቢል ትክክል ይመስለኛል። ይህን ጽሑፍ ስጽፍ እንደማሽላዋ እያረርኩ በመሣቅ ነው። መለስ ከታመመ ወዲህ ሁላችንም ጦጣና ዝንጀሮ ሆነናል። ምክንያቱም በኢትዮጵያ እርሱ ብቻ ነበርና ሰው! ሌሎቻችን በእርሱ ፈቃድ ውለን የምናድር፣ በእርሱ ፈቃድ የምንተነፍስ፣ በእርሱ ፈቃድ የምንሞት ወይ የማንሞት፣ በእርሱ ፈቃድ የምንራባና የምንመክን፣ በእርሱ ፈቃድ የምንታመምና የምንድን፣ በእርሱ ቅዱስ ፈቃድ የምንተኛና የምንነቃ፣ በእርሱ ፈቃድ ደናቁርት ተመርጠው የሚሾሙ ወይ የሚሻሩልን…. እርሱ የፈለገውን ብቻ የምንሆን የእርሱ ፍጡራን… የእርሱ ጥፍጥፎች … የእርሱ ጡቦችና ሸክላዎች ነበርን ፤ ነን። ጉድ ነው። አቤት ያንት ያለህ! እንዴት ያለው ጉድ ውስጥ ነው የምንገኝ።

 

የጦጦች ፓርላማ ባለቤቶች፣ የዝንጀሮዎች የሚኒስትሮች ካቢኔ ባለቤቶች፣ የዓሣማዎች የፖሊት ቢሮ አባላት ባለቤቶች፣ የማይማን የተወካይ ምክር ቤት ተብዬ ባለቤቶች፣ የእስስት ድርጅታዊ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ባለቤቶች፣ የዥቦች የጦር አበጋዝና ፊታውራሪዎች ባለቤቶች… መሆናችንን በገሃድ የተረዳነው ሰሞኑን ነው - መለስ ከታመመ ወዲህ። የሁሉም ቁልፎች ያለው በመለስ እጆች ውስጥ መሆኑን ያወቅነው ሰሞኑን ነው - እርሱ ከታመመ ወዲህ። እኔ የሰማሁት የኒኩሌር መሣሪያ ግምጃ ቤት ቁልፍ በሀገር መሪ እጅ ውስጥ ይቀመጣል ሲባል ነበር። ለካንስ የእያንዳንዱ ዜጋ ነፍስና ሥጋ መቆጣጠሪያ ቁልፍም በአንድ የሀገር መሪ እጅ ሊገባ ይችላል? አቤት ቅሌት! እስከዚህ ተዋርደናል?

 

ሲሞት ምን ይውጠን ይሆን? ያን ነው መፍራት። መለስ ክፉኛ እንደታመመ ተዘግቧል። በታላላቅ ስብሰባዎች አለመገኘቱ ክፉኛ የመታመሙ ምልክት እንደሆነ ልንገምት እንችላለን። በርግጥ ሰው እንደየስሜቱና ፍላጎቱ የመለስን ነፍስ ከሥጋው ከመለየት አንስቶ ለዕረፍት ነው ከሚዲያና ከሥራ ዘወር ያለው እስከሚለው ድረስ በዓለም ዙሪያ እየተናፈሰ ነው። እንደዛሬው ምሽት የቪኦኤ ዜና ዘገባ ከሆነ እኔ የመለስ ማንኛውም ወቅታዊ ሁኔታ አያሳስበኝም። በጣም እያሳሰበኝ ያለው ሁኔታ የአንድ ሰው ዕጣ ፋንታ የአንዲትን ሀገር ዕጣ ፋንታ እስከዚህ የሞት የሽረት አድርጎ የመገኘቱ አጠቃላይ መሪር እውነታ ነው።

 

አሜሪካንን ብናይ ፕሬዝደንቱ ቢታመም ወይም ቢሞት ጉዳያቸው አይደለም - ምርጫ እስኪከናወን በቅጽበት ምክትሉ ይተካል። የሀገርን ኅልውና የሚፈታተን ነገር አይገጥምም። ዛሬ ለምሳሌ በቅርባችን በአፍሪካ የጋና መሪ ዐርፏል፤ወዲያው ነው የተነገረው፤ ዛሬ ማክሰኞ ጧት ዐረፈ - ምክትሉ ወዲያውኑ አረዳ። ችግር የለም - ነፍሱን ይማር። ምክትሉ ይተካና ሀገሪቱን እስከምርጫው ጊዜ ድረስ ይመራል፤ የዛሬ ስንት ወር ገደማ በናይጄሪያ የሆነውም እንደዚሁ ነው - እንደኛ መጋጃዎች ሰማይ ምድሩ አልተደፋባቸውም። በብዙ ሀገሮች የአንድ ሰው ሕይወት የሀገርን ሕይወት አይበልጥም፤ አይለውጥምም። የኛ ግን ልዩ እርግማን ነው። በአዲስ አበባ አሁን ዛፎች እንኳን አይንቀሳቀሱም - መለስ የለማ! የመለስ ትዕዛዝ አልደረሳቸውማ! ካለመለስ አመራር ፀሐይ አትወጣም - ንፋስም አይነፍስማ! ውይ - ከዚህች ሀገር በቶሎ ይለየኝ!!! አትፍረዱ - ይፈረድባችኋል። እኔ እዚችው አራት ኪሎ ሥር ስለምኖር አንጎሌ ሊፈነዳ የቀረው ጊዜ በጣም ጥቂት ነውና በተለይ በጥሩ ሥፍራ ያላችሁ ወገኖች በምሬቴ ብዛት ብትፈርዱ ነፍሴ ትፋረዳችኋለች።

 

አንዳንድ መጥፎ አጋጣሚዎች ብዙ ነገርን ይበልጥ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። የሰሞኑ የመለስ ሁኔታ የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖርና ለፖለቲካችን ድፍን ጆሮ የማይሰጥ ዜጋ ብዙ አስቀያሚ ሀገራዊ ክስተቶችን ይመለከታል። እነ በከተ ስምዖንን የመሰሉ የኤርትራ መጋዣዎች የጌታቸውን መታመም ለመሸፈንና በእርሱ የበሰበሰ አስተሳሰብ እንደተነዱ፣ በእርሱ ብስናታምና ቅርሻታም አንደበት እየተመሩ ሀገሪቱን መቀመቅ መክተታቸውን ለመቀጠል የሚያደርጉት የዕውር ድንብር ጉዞና የሌት ከቀን ሩጫ ያሳዝናችኋል። በቀላሉ ሊያልፏቸው የሚችሉና የሚገቡ በራሳቸው ሳይቀር የተፈጠሩ ችግሮችን እያጦዙ የእባካችሁ አትርሱን አባዜያቸውን በቲቪያቸው ሲያናፍሱ ስታዩ የመረገማችን አንደኛ ደረጃነት ይታሰባችሁና ይሰቀጥጣችኋል።

 

የሌሎች ሀገሮች ፖለቲከኞች ሀገርን የሚያለማ ዕቃና የቴክሎጂ ውጤት ኢምፖርት ሲያደርጉ ያዩ የኛዎቹ ጉዶች ከሊባኖስና ከሌላው የዐረቡ ዓለም አህባሽ የተባለ መጤ ሃይማኖት ኢምፖርት አድርገው ሕዝበ ሙስሊምን ሲያተራምሱ ማየት የዘመናችንን የጭልፊትና የተኩላ መንግሥት በአካል ያሳየናል። ይህም ችግር መንግሥት ሠራሽ በመሆኑ ሳይፈጠር ሊቀር የሚችል ችግር ነበር። ምን አለፋችሁ - ከሞላ ጎደል ሁሉም የኢትዮጵያ ችግሮች የተፈጠሩት በወያኔ ነው። ወያኔ በመሠረቱ ተፈጥሮው ካለ ችግር የሚኖር አይደለም። ሰላም የማይመቻቸው አንዳንድ መንግሥታት አሉ - ወያኔ ዋናው ነው። ‹ፀጥ ሲል አልወድም› የሚል ተቀጥላ ያገኘውም ለዚህ ነው። ወያኔ ሀገር አማን ከሆነ ይሸበራል፤ ይደናገጣል፤ አንዳች ነገር እየተሸረበብኝ ነው ብሎም ያምናል። ምክንያቱም አነሳሱም፣ ዕድገቱም፣ ሥልጣን አቀማሙም፣ በሥልጣን ላይ መቆየቱም … ሁለ ነገሩ ሕገ ወጥ ነውና - እንደቀድሞዎቹ ሁሉ።

 

የዚህን የሚለየው የኅልውናው መሠረት ልዩነትን ማራገብ ነው - የቀድሞዎቹ ግን አንድነትን መስበክ ነበር። በአንድነትና በልዩነት መካከል ደግሞ ልዩነት አለ። ልዩነትን እየነቀሱ ያን በማን አባት ገደል ገባ ዓይነት የልጆች ጨዋታ እያጦዙ መኖር ውጤቱን ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ውስጥ አይተነዋል። አንድነትን እየሰበኩ የሥልጣን ዕድሜን ማቆየትንም ከዚያ በፊት በነበረን ጊዜ አይተነዋል። ልዩነቱ ግልጽ ነው። በ‹እያኖሩ መኖር›ና በ‹እየገደሉ መኖር› መካከል እንደሚገኝ ያለ ልዩነት ነው የሁለቱ ሥርዓቶች ልዩነት - እንደኔ ዕይታ። ክፉ አባትና ጨካኝ/አረመኔ ሽፍታ ለየቅል ናቸው። ‹ያልወለድኩት ልጅ ቢለኝ አባባ፣ አፌን አለው ዳባ›። አዎ፣ በቁሜ የሸጠኝና የለወጠኝ የወንበዴ መንግሥት ከጨካኝ አባቶቼ ጋር የመወዳደር ሞራላዊም ሆነ ማንኛውም ዓይነት ብቃት የለውም። እዚህ ላይ ለየዋህ አንባቢ የምለው ነገር አለ፡- የብሶቴ መሠረት የሰዎቹ ድርጊት እንጂ የዘውጋቸው ማንነት አይደለም። የዘውግ ነገር የሥልት ጉዳይ ነው። የአገዛዝ ሥልት። እንጂ በቀለ መጣ ፈይሣ ለኔ ያው ነው። ቢጠቅም ቢጠቅም አጎቱን አረጋኸኝን ወይም አክስቱን ጫልቱን ነው። በተረፈ ለአንድ የሥልጣን ወንበር 90 ሚሊዮን ሰው ይወዳደራል ወይም ቦታውን ይይዛል ማለት የሞኝነቶች ሁሉ ቁንጮ ነው። እናም ይቺ የዘውግ ነገር ወያኔን ተመርኩዞ ዘመን የፈጠራት የአገዛዝ ዘዴ ናት። ግን እጅግ አስቀያሚና እጅግ ኋላ ቀር ለማንምም የማትመከር አደገኛና መርዘኛ ዘዴ።

 

በበጎም ሆነ በመጥፎ መልኩ ከዚህ ሥርዓት ብዙ የምንማራቸው ነገሮች አሉ። የበጎው ነገር ለጊዜው በይደር ይቀመጥልንና በመጥፎው ረገድ ግን በዋናነት ከአሁን በኋላ በምንፈጥረው የፖለቲካ ሕይወት ሀገራችን በአንድ ሰው እስትንፋስ እንድትራመድ መፍቀድ እንደሌለብን ያገኘነው ግንዛቤ ነው። ይህን ነገር በቤተሰብ ደረጃ፣ በቡድን ደረጃ፣ በአካባቢ ደረጃ፣ በፓርቲ ደረጃ፣…. ከአሁኑ መለማመድ ይኖርብናል። ይህን ለማድረግ ደግሞ እንደጣዖት እንዲመለክ ከሚከጅለው የግልብ አስተሳሰብ ተጠቂ ጀምሮ ከሁሉም ዜጋ ብዙ ይጠበቃል።

 

ለምሳሌ በቤተሰብ ደረጃ ብናይ አባት ምንም እንኳን በባህላችን የቤቱ ምሰሶ ተደርጎ ቢወሰድም እናትም ተገቢው ክብርና ቦታ እንዲሰጣትና የአንዳቸውን ጉድለት ሌላኛቸው ባፋጣኝ እንዲሞሉት ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይገባል። አባት ቢሞት ቤት መፍረስ የለበትም። እርግጥ ነው የኢኮኖሚ ሁኔታ የተወሰነ ተፅዕኖ ማሳደሩና በዚያም ሳቢያ በቤተሰብ ውስጥ ልዩነት መፈጠሩ የታወቀ ነው። ሆኖም ክፍተቱን በቶሎ ለማጥበብ መሞከር ይገባል። አባት ሲሞት ቤተሰቡ መድቀቅ የለበትም። ወዲያው ተፅናንቶ ሕይወት መቀጠል ይገባል። ሁለት የሕይወት መንገዶች አሉ - መሞትና አለመሞት። የሞተው አንዱን ይዟል። በሞተው ዳፋ ግን ያልሞቱት እንዲሞቱ ወይም በሞትና በሕይወት መካከል ሆነው እንዲጠራወዙ ማድረግ አይገባም። በፖለቲካው ረገድም እንደዚሁ ማድረግ ከጥገኝነትና ከተዋራጅነት ያድናል። አለበለዚያ እንደጥንቱ የወላይታ ሥርዎ መንግሥት ንጉሡ ሲሞት አራት አሽከሮች ከነሕይወታቸው እንደሚቀበሩት አስተኔ መሆኑ ነው። ያ ዓይነቱ ሕግ ነው በነመለስ እየተተገበረ ያለው - እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ዓይነት ኦሪታዊ ሕግ።

 

በፓርቲም ረገድ ሁሉም የፓርቲ አባላት ሊያስቡበት የሚገባ ነገር አለ። አንድ ሰው ምንጊዜም አንድ ነው። ለአፍ ያህል ‹አንድ አይነድ፤ አንድ አይፈርድ›፣ ‹አንድ በሬ ስቦ ፣ አንድ ሰው ከስቦ› እያልን የትብብርን በጎነት እንናገራለን፤ በተግባር ግን እስከዚህም ነን፤ እናም የማለፊያ ብሂሎቻችንን አንድምታ ትተን ‹ሰማይ አይታረስ፤ ንጉሥ አይከሰስ› ወደሚለው የአሸርጋጅነት ባህል እንሳባለን። እርግጥ ነው - ብዙ ዕውቀት ያለው - ልምድ ያለው - በቂ የአመራር ችሎታ ያለው … በሳል ሰው ይኖራል፤ ጥሩ ነው። ነገር ግን ያን ሰው ልክ ምትክ የለሽ አድርገን ዝንታለሙን ንጉሠ ነገሥት ከማድረግ በመቆጠብ ሌሎችም ዕውቀትና ልምድ እንዲያገኙ ማድረግና ከአንድ ሰው የሁልጊዜ አመራር መውጣት ተገቢ ነው፤ በአንድ ሰው መመካት ባሪያ ያደርጋል። በራስ የመተማመንን ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬ ይገድላል። ስለዚህ ሁሉም መሪ ሁሉም ተመሪ ሊሆን የሚችልበትን ዴሞክራሲያዊ(ይህ ቃል እንዴት እንደሚቀፈኝ - ወያኔን እግዜር ይይለት!) ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል፤ ያኔ አንዱ በሁሉም ሁሉም በአንዱ እንዲተማመኑ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፤ የጌታና ሎሌ ግንኙነትም ይወገዳል።

 

‹ባጠፋ እወቀሳለሁ፤ እከሰሳለሁ፤ ከሥልጣንና ከጥቅም እነሳለሁ፤ በውርደትና በቅሌት ስሜ ይጠፋል፤ እታሰራለሁ…› በሚል ሁሉም ይጠነቀቃል። መደማመጥ ይፈጠራል፤ መግባባት ይዳብራል። በሂደት አምባገነንነት በታሪክ መዝገብ ብቻ የሚነበብ ይሆናል። ለዚህ ዓይነቱ አሠራር የጋዳ ሥርዓትን መኮረጅ ክፋት ለውም - ጥሩ ነገር ቢቀዳ አይጎዳም። በዚህ ረገድ በተሸናፊነት ስሜት በአንድ ሰው ላይ ልናሳድር የምንችለውን የትምክህት አስተሳሰብ - ከኔ በላይ ዐዋቂና የአመራር ብቃት ላሣር - እኔ ከሌለሁ እነ እገሌ ባዶ ጭንቅላት ስለሆኑ መምራት አይችሉም… የሚሉትንና የመሳሰሉትን አስተሳሰቦች ማስወገድና ‹እኔ ባልኖርም እነእገሌ አሉ› የሚል የወል አስተሳሰብ እንዲዳብር ማድረግ እንችላለን። አለበለዚያ እንደ እስካሁኑ እንዲያውም ከደረስንበት የዓለም ሥልጣኔ አኳያ ከእስካሁኑም ይበልጥ እንጎዳለን። አንድ ሰው ደግሞ በተፈጥሮው ሰው ነውና ብዙ ሲመኩበት መባለጉ ድብቅ መጥፎ ባሕርያቱንም ማምጣቱ አይቀርም - ልጓም የሌለው የጋማ ከብት ገደል ሊከት እንደሚችል ሁሉ በሕግ ያልተመራ ሰውም ከዚህ በባሰ እንጦርጦስ ሊከት እንደሚችል ከመለስ ዜናዊ በከፍተኛ የደምና የአጥንት ክፍያ ተምረናል።

 

እውነትን ለመናገር መንግሥቱ ቆንጆ ባሕርያት ነበሩት - መለስም። ግን በጊዜ ሂደት ወደ አምልኮት ደረጃ ሊለወጡ የቻሉት በሰው ግፊት ነው። ሰው ደግሞ ይሰቅልና በኋላ ማውረድ ይሳነዋል። ሁሉም አምባገነኖች በመጀመሪያ ተለማማጭና ፈሪዎች ናቸው። ያላቸው ብቸኛ ሀብት በአካባቢያቸው ተደማጭ ሊያደርጋቸው የሚችል መጠነኛ ዕውቀትና ብዙ ድፍረት ነው - በአፍ ጅዶ ሰውን ማነሁለልና (በተለይ የዋሆችን) ማሣቅም ልዩ ተፈጥሯቸው ነው። ጥበብና መንፈሳዊ ዕውቀት ግን የላቸውም - በምትኩ ጀብደኝነትና እልኸኝነት ይበዛቸዋል። በዚያም ምክንያት በማንኛውም ነገር የሚበልጣቸውን ሰው እያወደሙ ደናቁርትና ሆዳም አምላኪዎቻቸውን በሥራቸው ይኮለኩላሉ። ይህም የኒኮሎ ማኪያቬሊ መርህ ነው። የወጡበትን መሰላል ሁሉም ስለሚያውቀው ማንም እንዳይወጣበትና ማማውን እንዳይቀማቸው ሰባብረው ይጥሉታል። የወጡበትን መሰላል እንክትክት አድርገው ስለሚሰባብሩት ግን የሚወርዱበት መሰላል ያጡና አወራረዳቸው እጅግ አስቀያሚ ይሆናል። አምባገነን በተፈጥሮው ሁነኛ ዘመድና ወዳጅ የለውም። የሚጠጓቸው ሁሉ ለጥቅምና ለሥልጣን ነው። ጊዜ ዘመም ሲልባቸው ግን የሚቀሩት ከጥቂት ዘመዶቻቸውና በጣት ከሚቆጠሩ እጃቸው በደም የጨቀዬ ታዛዥ አሽከሮቻቸው ጋር ብቻ ነው። ይህን ከልምድ እናውቃለን። ማንም እስኪነግረንም አንጠብቅ።

 

በዚህ በወያኔ ሥርዓት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች እውነተኛ ሰዎች ቢሆኑ አንድ ሁለት ቃላትን በምክር መልክ ብሰጥ ደስ ባለኝ። ነገር ግን አውቆ የተደበቀን መጥራት ወይም አውቆ የተኛን መቀስቀስ ትርፉ ድካም ነውና አልሞክረውም። ለእኞች ግን ያልኩትነን ብያለሁ። ሰሚ ካለ ይስማ። አሊያም መከራው ሲመጣ የግዱን እንዲሰማ ያደርገዋል። ሁሉም የሚቻለው ጌታ አርቆ የማሰብን ጥበብ ያላብሰን። ከሰው እንጂ ከፈጣሪ የሆነ ነገር አያጣላንም። ፈጣሪ ደግሞ ሁሉም ፍጡራኑ እንዲዋደዱለትና እንዲፋቀሩለት እንጂ ጦር እየተማዘዙ እርስ በርስ እንዲተላለቁበት ፈጽሞ አይሻም። አስተዋይ ልቦና የሰጠው ምድራዊ ይህን ሁሉ በቀላሉ ይገነዘባል፤ አንደበቱንና እጁንም ከሚያስቀይም ንግግርና ከመጥፎ ድርጊት ያቅባል። … ትናንትን በዛሬ መስትዋት የኋሊት እያየን እንደምንመለከተው ሆነን እንደምንም አለፍን፤ዛሬ ደግሞ ወደድንም ጠላንም እንዲህ ነን፤ ነገ ‹ትናንት እንዲህ ነበርን› ብለን በትዝታ ራሳችንን በመቃኘት ዛሬን በነግ ወዲያ ማስፈራሪያነት ለመጥቀስ ያብቃን። አሜን።

ለማንኛውም ገምቢ አስተያየት:- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ