Ginbot 7ግንቦት-7ያሬድ አይቼህ

የሰሞኑ የዲያስፓራ ፓለቲካዊ ወግ ትኩሳት ወደ ግንቦት-7 አዙሮዋል። ጉዳዩ እንዲህ ነው፦ ግንቦት-7 አባል ነበርን የሚሉ ነገር ግን አሁን ‘ግንቦት-7ዲ’ ሚባል ድርጅት አቋቋምን የሚሉ ሁለት ሰዎች በፓልቷክ የቃሌ ክፍል ዛሬ ቅዳሜ ቃለምልልስ ተደረገላቸው። አስተናጋጁ ኮሮጆ-ኢትዮጵያ ምራቁን የዋጠ መስተንግዶ አድርጓል - ምስጋና ለኮሮጆ-ኢትዮጵያ ይድረሰው። ወደ ጉዳዩ ልመለስ።

 

እናም የ’ግንቦት-7ዲ’ መሪዎች ነን የሚሉት እነዚህ ሁለት ወገኖቻችን ግንቦት-7 ‘ዴሞክራሲያዊ’ አይደለም የሚል ስጋታቸውን ደጋግመው ለድርጅቱ መሪዎች ለሊቀመንበሩ ለዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ለጸሐፊው ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ማቅረባቸውንና፤ ላቀረቡት ስጋት ‘ስድብ’ እንጂ ተደማጭነት እንዳላገኙ በቃለ ምልልሱ ወቅት ደጋግመው አስምረውበታል። እኔ ግን አላመንኳቸውም። ልብ በሉ! ግንቦት-7ን አልደግፍም፤ ይሳካለታል የሚል እምነትም የለኝም። ግን የ’ግንቦት-7ዲ’ ምኑም አልተዋጠልኝም። ሶስት ምክንያቶች ልዘርዝር፦

 

1. ‘ዴሞክራሲ’

እንደሌሎች የባዕድ ጽንሰ ሃሳቦች ‘ዴሞክራሲ’ የሚለውንም ጽንሰ ሀሳብ በአገራችን የፓለቲካ ሂደት ውስጥ ሁሉም እንደፈለገው ነው ሚተረጉመው። አንድ ጊዜ አንድ ዘመዴና እጮኛው የአሜሪካን ኤምባሲ ለምን ቪዛ እምቢ እንዳላቸው የጻፉትን ደብዳቤ ኢሜል አርገውልኝ “ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብታችንን ተጥሷል” የሚል አስፍረውበት አይቼ ተገርሜ ነበር። ቪዛ እና ዴሞክራሲን ምን አገናኛቸው?!

 

አንድ ሰው እኔ ቤት መቶ ዴሞክራሲያዊ መብቴ ይከበር ቢለኝ ፡ 911 ደዉዬ በፓሊስ ማጅራቱን አሲዤ እንደማስወጣው አልጠራጠርም። በቤቴ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የለም፣ ቤተሰባዊ ስርዓት እንጂ። ዴሞክራሲያዊ አሰራር በሁሉም ስፍራ አይሰራም። በተለይም ደግሞ እንደ ግንቦት-7 ያለ የሚስጥር (ህቡዕ) ድርጀት እንዴት አርጎ ነው ዴሞክራሲያዊ ሚሆነው? እንዴ! የአሜሪካኑ የስለላ ድርጅት በዴሞክራሲያዊ አሰራር ይሰራል ብሎ እንደመገመት ነው። ትልቅ ስህተት ነው።

 

ግንቦት-7 ሲጀምር “የፍትህ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ” ብሎ ነው ያወጀው፤ ንቅናቄ እንጂ የፓለቲካ ፓርቲ አይደለም። ልብ በሉ! የፓለቲካ ፓርቲ አይደለም። የፓለቲካ ፓርቲ ነን ቢል ኖሮ ያኔ የፓርቲውን አሰራር በድምጽ ብልጫ እንዲሆን ማድረጉ ተገቢ ይሆናል፤ ነገርግን ገና ቅቤው ያልወጣለትን ወተት ቅቤውን አምጣ ብሎ መጠየቁ የዴሞክራሲያን ምንነት አለመገንዘብ ነው። ቅቤ እንዲወጣ ነው ግንቦት-7 ሚነቃነቀው። ተነቃንቆ ሳያበቃ ቅቤ መጠበቅ ‘ላም ካልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው’። ስለዚህ ‘ግንቦት-7ዲን’ አላምናቸውም።

 

2. የተጣረሰ አስተሳሰብ

የ’ግንቦት-7ዲ’ መሪዎች ነን ያሉት ወገኖቻችን በሰጡት ቃለምልልስ የአስተሳሰብ መጣረስ በተደጋጋሚ አንጸባርቀዋል። ለምሳሌ አንዱ ግለሰብ ግንቦት-7 አማራዎችን ሊያጠቃ ወይም ሊጨቁን የተነሳ ነው የሚል አይነት ሃሳብ ሰንዝሯል። እዚህ ላይ “ግንቦት-7 ከተመሰረተ 4 ዓመት ሆኖት ሳለ ለምን እስካሁን ቆየህ” የሚል ጥያቄ ነው የፈጠረብኝ። ዶ/ር ብርሃኑን ለማጥቃት የሚፈልጉ ሰዎች ዶ/ር ብረሃኑ ለንድን ላይ አንድጊዜ “የትግሬን አምባገነን በአማራ አምባገነን” መተካት አልፈልግም አይነት ንግግር ተናግሮ ነበር። ያን ያለበት ምክንያት ግን አማራዎችን ለማጥቃብ ብሎ አልነበረም። ያን ያለው የመኢአድን መሪ የአቶ ሀይሉ ሻዉልን የአመራር ዝንባሌ ለመተቸት እንጂ።

 

በተጨማሪም ‘ዶ/ር ብርሃኑ ቅንጅትን አፈረሰ’ የሚል ሃሳብ የ’ግንቦት-7ዲ’ መሪ ነን ካሉት ሰዎች አንዱ አንስቷል። ቅንጅት ከፈረሰ እኮ ወደ 6 አመት ተጠጋው። አንድ ሰው ግንቦት-7 ውስጥ አባል ሲሆን ‘ዶ/ር ብርሃኑ ቅንጅትን አፍርሷል ስለዚህ አባል ልሁን” ብሎ ነው እንዴ አባል ሚሆነው? አይመስለኝም። በቅንጅት መፍረስ የሚደሰት ሰው ካልሆነ በስተቀር በቅንጅት መፍረስ ሚቆጭ ሰው፣ በተለይ ዶ/ር ብርሃኑን ዋነኛ ‘አፍራሽ’ ነው ብሎ ሚያምን ሰው የግንቦት-7 አባል አይሆንም (ለስለላ ካልሆነ በስተቀር)።

 

3. ለምን አሁን?

የ’ግንቦት-7ዲ’ መሪ ናቸው የተባሉት ሁለቱ ወገኖቻችን ለምን የአሁኑን ሰአት መረጡ? በተለይም ኢህአዴግ ነርቩ ከፍተኛ መናወጥ ውስጥ ባለበት ወቅት፣ ኦህዴድ ላይ ዱላ እየበዛበት ባለበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ውጥረት ውስት ባለበት ወቅት … ምን ነው ይሄንን ጊዜ መርጠው የ’ግንቦት-7ዲ መስራቾች’ በፓልቷክ ብቅ አሉ? (በነገራችን ላይ ቃለምልልሱ መደረግ የነበረበት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች መወያያ መድረክ [Current Affairs] ነበር። የክፍሉ መሪዎች ብስለት ጎድሏቸው ነው እንጂ ጉዳዩን ቶሎ ወደ አደባባይ አውጥተው ሊያከስሙት ይችሉ ነበር። ‘ጪስ አይቶ እሳት የለም’ ማለት በጣም ሞኝነት ነው እና እነደዚህ አይነት ሁሌታዎች ላይ የአደጋን መቀነስና መቆጣጠር [damage control] መስራት ያስፈልጋልና የክፍሉ መሪዎች አስቡበት።)

 

አቶ መለስ ዜናዊ ነፍሳቸውን ይማረውና በመሞታቸው ኢህአዴግ ከፍተኛ መናጋት ውስጥ መግባቱን አምናለሁ። አቶ መለስ የኢህአዴግ መሪ የሆኑት ድርጅቱ ከተመሰረተበት ቀን ጀምሮ ነው። ታዲያ በአቶ መለስ ሞት ምክንያት አንገቱ የተቆረጠውን ኢህአዴግን የሚቃወም ሰው ለምን ግንቦት-7ን ለማዋረድና ለማፍረስ ይነሳል? አሁንም ደግመዋለሁ፣ ‘ግንቦት-7ዲን’ አላምናቸውም። በፍጹም አላምናቸውም።

 

ከዚህ ወዴት?

ግንቦት-7 የኢህአዴግ ችግር እንጂ የኔ ችግር አይደለም። ግንቦት-7 ቢሳካለት የሚጎዳው ኢህአዴግ እንጂ ሌሎች ፓርቲዎች አይደሉም። ምንም እንኳን የግንቦት-7 መመስረትና የመረጣቸው የትግል ጎዳናዎች ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዳበር አወንታዊ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብዬ ባላምንም፣ ግንቦት-7ን በዚህ ጊዜ ማጥቃቱ የኢህአዴግ የፕሮፓጋንዳ ስራ እንጂ የዴሞክራሲ ታጋይነት ምልክት አርጌ አላየውም። ይሄ ጥቃት ግንቦት-7ን ይበልጥ ጠንካራ ያደርገው ይሆናል፤ ነገር ግን አናግቶ ከጨዋታ ዉጭ ያስወጣዋል የሚል ግምት የለኝም፤ እንዲያውም ይበልጥ ‘አምባገነን’ መሆን እንዳለበት ነው ሚገፋፋው። መሆን ሳይኖርበትም አይቀርም።

 

ያም ሆነ ይህ ግን አንድ መሰረታዊ እውነታ አለ፦ ትግሉ አገር ቤት እንጂ ዲያስፓራ አይደለም። አንድ የመድረክ ልኡካን በአሜሪካን አገር በቅርቡ በተደረገ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚከተሉትን ቢያደርጉ የሳካላቸዋል፦

 

1. የሰከነ ስራ፦ ዘለቄታዊነት ያለውና አርቆ ሚያስብ ትግል መታገል

2. ትብብር፦ በትብብር ላይ የተመሰረተ ከመጠላለፍ የራቀ ፓለቲካ

3. አቅም፦ በአቅም ግንባታ ላይ ያተኮረ ትግል

4. ስራ ክፍፍል፦ ዲያስፓራ የገንዘብ ድጋፍ እና የዲፕሎማሲ ትግል ያድርግ፣ መድረክ አገር ውስጥ ይታገላል።

 

እነዚህን አራት ነጥቦች ልብ እንበል። ያለዚያ የዲያስፓራው ድራማ ሌላ 21 አመታት ማስቆጠሩ አይቀርም። እንስከን፣ እንተባበር፣ አቅም እንገንባ፣ የስራ ድርሻችንን እንወቅ።

አንዷለም አራጌ ይፈታ!

እስክንድር ነጋ ይፈታ!

በእስር ቤት ሚማቅቁ የፓለቲካ እና የህሊና እስረኞች ሁሉ ይፈቱ!

ጥገናዊ ለውጥ ለኢትዮጵያ!


ጸሀፊውን ለማግኘት በዚህ ይጻፉ፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ