አማኑዔል ዘሰላም

ልማት ለአንድ አገር በጣም አስፈላጊ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ ሰለጠኑ ከሚባሉ አገራት ጋር ስትነጻጸር ብዙ የሚቀራት ናት። አገራችንን ከድህነት ነጻ ለማውጣት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደ መካከለኛ አገራ ውስጥ እንድትመደብ ለማድረግ፣ ኢሕአዴግ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው። ይህ ኢሕአዴግ የጀመረውን የልማት እንቅስቃሴ ከመደገፍ ባሻገር፣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ባላቸው አቅምና ጉልበት የድርሻቸውን ሊያበረክቱበት የሚገባ እንቅስቃሴ ነው።

 

 

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ ለፓርላም ካደረጉት ንግግር፣ አንድ ግሩም አባባል አደመጥኩ። «የአይቻልም መንፈስን መስበርና የይቻላል መንፈስን በአገራችን ማምጣት አለበን» ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ኢሕአዴግ ብቻውን የሚያደርገው ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በጋራ ተባብሮ የሚሰራው እንደሆነም ሳይገልጹ አላለፉም።

 

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ፣ የልማት እንቅስቃሴዎችን ይቃወማል ብዬ አላስብም። አገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ፣ ኢትዮጵያ አድጋ፣ ትልቅ ደረጃ እንድትደርስ መፈለግ ብቻ ሳይሆን መክፈል ያለበትን መስዋእትነት ለመክፈል ዝጉጁ ነው።

 

በአገር ቤት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የአንድ ወር ደሞዙን ለአባይ ወንዝ ግንባታ እንደከፈለ የሚታወቅ ነው። አገር ቤት ያሉ ወገኖቻችን በተፈጠረው የዋጋ ግሽፈትና ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ ኑሮን መግፋት ቢያቅታቸውም፣ ቢያማቸውም፣ የሚያምኑበት ጉዳይ ነውና ካላቸው ከትንሹ ገቢያቸው 12% ሲሰጡ አልከፋቸውም።

 

እንደምንሰማው አገር ቤት የሚኖረው ሕዝብ፣ እንደገና ለሁለተኛ አመት የደሞዙን 12% እንዲያዋጣ ተጠይቆ እያዋጣ ነው። የኑሮ ውድነት፣ ትንሽ እንኳን ጋብ ባላለበት ሁኔታ እንደገና፣ መዋጮ በማዋጣት ችግር ውስጥ እንዲገባ መደረጉ ተገቢ አይመስለኝም። ሌላ አማራጭ ባይኖር ኖሮ፣ «እሺ ፣ ምንም ማድረግ አይቻልም» እንል ነበር:። ነገር ግን ሌላ አማራጭ አለ። እርሱም ማዋጣት የሚከብደውን ሕዝብ ማስጨነቅ ሳይሆን ማዋጣት የሚችለውን በተለይም በዳያስፖራ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ በስፋትና ማሳተፍና ማንቀሳቀስ ነው።

 

«ዳይስፖራውን ለማሳተፍ ሞክረናል፤ ከዳያስፖራውም ብዙ ገንዘብ ሰብስበናል» የሚል ምላሽ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት ሊሰጡ ይችላሉ። ትክክል ነው። በተለያዩ የአሜሪካን የአውሮፓ ከተሞች ብዙ ገንዘብ ተሰብስቧል። ቦንድ የገዙ ዜጎች ብዙ ናቸው። ነገር ግን በበቂ ሁኔታ ዳያስፖራውን በማሳመንና በማግባባት ስራ ተሰርቷል ብዬ አላስብም። ስራ ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ ለአባይ ወንዝ ግንባታ የሚያስፈልገው ወጪ በሙሉ ይሸፈን ነበር። አገር ቤት ካለውም ድሃ ወገናችን መዋጮ አይጠየቅምም ነበር።

 

የአባይን ግድብ ለመገንባት ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል። በሰሜን አሜሪካ ብቻ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ወደ አንድ ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። በውጭ ያለነው አንድ ሚሊዮኖቻችን በሰዓት 5 ዶላር ብቻ ነው የሚከፈልን ብለን ብንወስድ፣ የአመት ደሞዛች ወደ 10000 ዶላር ይደርሳል። አገር ቤት መዋጮ እንዲያዋጣ ሕዝቡ ከተጠየቀው 12% በታች፣ 10% ለኢትዮጵያ ልማት ብንመድብ፣ በአመት አንድ ቢሊዮን ዶላር በቀላሉ ማሰባሰብ እንችላለን። በአራት አመት ውስጥ ለአባይ ግድብ ግንባታ የሚያስፈልገውን በሙሉ፣ የአለም ባንክ ወዘተረፈ የመሳሰሉትን ሳንለምን፣ ኑሮ የከበደውንም አገር ቤት ያለውን ሕዝባችንንም ሳናስጨንቅ፣ ማሟላት ተቻለ ማለት ነው። እንግዲህ ሂሳቡን በግልጽ አስቀጬዋለሁ። ፍላጎቱና መግባባቱ ካለ ፣ አቶ ኃይለማርያም እንዳሉት በርግጥ እንችላለን። አዎን ይቻላል።

 

ትልቁ ጥያቄ መግባባቱና መስማማቱ ላይ ነው። በቅርቡ አምባሳደር ግርማ ብሩ ዋሺንገትን ዲሲ ከሚገኝ የሃገር ፍቅር ራዲዮ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ሲቋጩ የተናገሩትን ልጥቀስ።

 

«አንድ አገር ነው ሊኖረን የሚችለው። ሰው በምርጫ አይደለም በአንድ አገር ውስጥ የሚወለደው። ያቺን ያለችንን አገር፣ በክብር ለመጠበቅ እንድንችል፣ ሁሉ ልዩነቶቻችንን አቻችለን፣ የአገራችን መሰረታዊና ብሄራዊ ጥቅም የሚመለከቱ ጉዳዮች ሲኖሩ፣ አንደ አንድ መቆም አለብን» ነበር ያሉት አምባሳደሩ።

 

በውጭ አገር የሚኖረው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከኢሕአዴግ የሚፈልገው ኢሕአዴግ አገር ቤት ያለውን ሕዝብ እንዲያከብርና የሕዝቡን ጥያቄና ፍላጎት እንዲያሟላ ነው። አገር ቤት ባሉ እሥር ቤቶች የሕሊናና የፖለቲካ እሥረኞች ከሌሉ፣ ኢትዮጵያውያን በነጻነትና ያለ ፍርሃት በአገራቸው የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ የማምለክ ነጻነታቸው ከተረጋገጠ፣ በባለስልጣናቱም ሆነ ከባለስልጣናቱ ጋር ዝምድናና ግንኙነት ባላባቸው ግለሰቦች የሚፈጸሙበትን ግፎች አቤት የሚልበት ነጻና ገለልተኛ የፍርድ ስርዓት ከተዘረጋ፣ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ተቃውሞም ሆነ ቅሬታ የሚያሰማበት ምንም ምክንያት አይኖረም።

 

ኢሕአዴግ በውጭ አገር የሚኖረውን ኢትዮጵያ በስፋት ለማቀፍ ይችል ዘንድ፣ ሊያደርጋቸው የሚገባ ተግባራት አሉ። እነርሱ እጅግ በጣም ጥቂትና ቀላል ናቸው። በዋናነት አምባሳደር ግርማ ብሩ እንዳሉት የመተማመን፣ የመቻቻልና የመከባበርን መንፈስ እንዲሰፍን ማድረግ ነው። ኢሕአዴግ የሚደግፉትን ብቻ ይዞ መሄድ ሳይሆን፣ አገርን በጋራ አንድ እርምጃ ለማስኬድ ሲባል፣ የማይደግፉትንና የሚቃወሙትን ማቅረብ መቻል ያለበት ይመስለኛል።

 

ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር የፓርቲዎች የምክር ቤት አባል ከሆኑ (የምርጫ ስነ ምግባር ኮዱን ከፈረሙ) የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙርያ እንደሚነጋገሩ ግልጽ አድርጓዋል። የምርጫ ስነ ምግባር ኮዱን ያልፈረሙ እንደ መድረክ ያሉ፣ የድርጅቶች ስብሰብ ከሆኑ ጋር ግን ለመነጋገር የኢሕአዴግ ፍቃደኛት እንደሌለ አስረድተዋል። ይህ ትልቅ ስህተት መሰለኝ። ኢሕአዴግ መንግስት ነው። መንግስት ደግሞ ያኮረፉትን፣ ያመጹትን ወደ ሰላም የማምጣት ትልቅ ሃላፊነት አለበት። ኢሕአዴግ ጠንካራ ከሚባሉ ተቃዋሚዎች ጋር አልነጋገርም ካለ፣ የመከባበሩንና የመቀራረቡን መንፈስ አደፈረሰው ማለት ነው።

 

ሌላው ብዙዎቻችን እንደምናወቀው ሽብርተኞች ተብለው የታሰሩ በርካታ ወገኖቻችን አሉ። ጋዜጠኛ እስክንደር ነጋ፣ አቶ አንድዋለም አራጌ፣ አቶ በቀለ ገርባ ፣ እህት ርዮት አለሙ የመሳሰሉ ዜጎች በቃሊቲ እሥር ቤት ይገኛሉ።

ከአቶ እስክንደርና ከአቶ አንዱዋለም ጋር ጥሩ ቀረቤታ አለኝ። ብዙ ጊዜ በስልክና በኢሜል እንገናኝ ነበር። እግዚአብሄርን የሚፈሩ፣ በምንም መልኩ ፣ በማንም ላይ ጉዳት እንዲደርስ የማይፈልጉ፣ ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የሕዝብን ጥቅም ያስቀደሙ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው። ግንቦት ሰባት አባል ናችሁ ተብለው ተከሰዋል። ግንቦት ሰባት የተሰኘውን ድርጅት እንኳን ሊደግፉ፣ በውጭ ባሉ ሜዲያዎች የግንቦት ሰባት «የሰላማዊ ትግል አይሰራም» ፖለቲካን በይፋ የተቃወሙ ናቸው። እነዚህን ወገኖችን ሽብርተኞች ናቸው ብሎ መፈረጅ በጣም አሳዛኝ ከመሆኑ የተነሳ ማንም የማይቀበለው ነው። እነርሱን ባሰሯቸው ባለስልጣናትም ላይ ጤናማ ያልሆነ አመለካከት እንዲኖረን ያደረገና የሚያደርግ ነው።ጎጂ ነው።

 

በቅርቡ ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ፣ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ እነ እስክንደር ነጋን «ሁለት ባርኔጣ እያደረጉ የሽብር ሥራ ላይ የተሰማሩ» ሲሉ እንደከሰሷቸው አንብቢያለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን አይነት መረጃ ይዘው ይሄን ሊሉ እንደቻሉ ሊገባኝ አልቻለም። አቃቢ ሕግ ያቀረባቸው የቪዲዮ መረጃዎች ሁሉ ሳይቀሩ፣ የነ እስክንድርን ሰላማዊነት ነው ያረጋገጡት። ውጭ አገር ላሉ ሜዲያዎች በሰጡት ቃለ ምልልሶች፣ ከሰላማዊ ትግል ውጭ ሌላ ነገር እንደማያዋጣና እንደማይደግፉ ነው እነእስክንድር በግልጽ ያሰቀመጡት። የጻፏቸውን ጽሁፎች፣ አገር ቤት በሚታተሙ ጋዜጦችና በይፋ በሚነበቡ ድህረ ገጾች አወጡ እንጂ፣ በሚስጠር ያቀባበሉትና የበተኑት አመጽ የተሞላበት ጽሁፎች የሉም።

 

እስከሚገባኝ ድረስ፣ በፍርድ ቤት አቃቢ ሕግ ባቀረባቸው መረጃዎች ሁሉ በግልጽ የተረጋገጠው፣ እነ እስክንድር አንድ ባርኔጣ ብቻ እንዳደረጉ ነው። እርሱም ነጭ የሰላም ባርኔጣ። አቶ ኃይለማርያም በዚህ ጉዳይ ላይ፣ ከእውነት የራቀ ጠቃሚ ያልሆኑ አባባሎችን በመሰንዘር ከኢትዮጵያውያን ጋር ብዙ ባይቀያየሙ ይሻላል።

 

እንግዲህ በነ እስክንድር ላይ እየተደረገ ያለው አሳዛኝ ክስተት ነው ሌላው በዋናነት የመቀራረብንና የመግባባትን መንፈስ እያደፈረሰ ያለው።

እርግጥ ነው ምንም ነገር ይምጣ በኢሕአዴግ ላይ በጭራሽ ቀና አመለካከት የሌላቸው፣ ኢሕአዴግ እንዲጠፋ የሚፈልጉ ጥቂት ወገኖች ይኖራሉ። አንዳንዶች ጭራቅ ከሚባለውና ከመረብ በስተሰሜን ያሉ ወገኖቻችን ደም ከሚጠጣው ከሻእቢያ ጋር በመተቃቀፍ፣ ለሰላምና ለእርቅ የሚደረጉ ጥረቶች ላይ ውሃ ለመከልበስ የሚሞክሩ አሉ። እነዚህ ኃይሎች «ኢሕአዴግ አይለወጥም። ኢሕአዴግ እነ እስክንድርን አይፈታም፣ በሕዝቡ ላይ የፍርሃት ቀንበር ጭኖ በኃይል መግዛት ነው የሚፈልገው። በኃይል ኢሕአዴግን አስገድዶ ማንበርከክ፣ አሊያም ከናካቴው ማስወገድ ነው የሚያስፈልገው» ይላሉ።

 

ይህ አይነት አመለካከት ያላቸው ወገኖች እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው። በዳያስፖራ ተቀባይነት የሌላቸው ከመሆናቸውም በተጨማሪ ፣ የፖለቲካ ክስረት እንደደረሰባቸው አለም የሚያውቀው ነው። እነዚህን በመፍራትና እንዲሁ በመደናበር ኢሕአዴግ ዱላውን ሰላማዊ ዜጎች ላይ ማሳረፍ የለበትም። አብዛኛው በዳያስፖራ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ፣ በልማቱ እንቅስቃሴ ኢሕአዴግን መደገፍ የሚፈልግ፣ ነገር ግን ኢሕአዴግ በሚወስዳቸው አላስፈላጊ፣ መቀራረብን በሚያደፈርሱ የፖለቲካ ውሳኔዎች ያዘነ፣ ያኮረፈና የተቆጣ ነው።

 

እንግዲህ ኢሕአዴግ ከእልህና ከግትርነት ፖለቲካ ወጥቶ ለአገር የሚበጀውን ነገር ማድረግ ይጠበቅበታል። አገራችን ኢትዮጵያ ትላልቅ ፈተናዎች ከፊቷ ተደቅነዋል። የተጀመሩ በርካታ የልማት እንቅስቃሴዎች መቀጠል አለባቸው። እንደ ግብጽ ያሉ አገራት መቼም ስላማይተኙልን የአገራችን አንድነት ከመቼውም በበለጠ መጠናከር አለበት። በኤርትራ በኩል ያለውን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት ያስፈልጋል። «no Peace, no war» የተባለው ፖሊሲ ሰውነታችን ላይ መግል ይዘን እንድንኖር ያደረገ ፣ መቀየር ያለበት ፖሊሲ ነው። በመሆኑም የግዴታ ኢትዮጵያውያን መቻቻል መቀራረብና መያያዝ አለብን። ይሄም እንዲሆን በዋናነት ኢሕአዴግ ነው ትልቅ ሚና ሊጫወት የሚችለው። ኳሱ ኢሕአዴግ ሜዳ ላይ ነው።

 

  1. ኢሕአዴግ የታሰሩ የፖለቲካ እሥረኞችን በሙሉ መፍታት አለበት። የነ እስክንድር ጉዳይ በይግባኝ የተያዘ ነው። እነ እስክንድርን የከሰሰው ፌደራል መንግስቱ እንደመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስተሩ ካቤኔ አባል የሆኑት፣ የፍትህ ሚኒስትሩ፣ ክሱ እንዲነሳ ማድረግ ይችላሉ። ይግባኙን የሚያየው ፍርድ ቤት ከአቃቤ ሕግ ተቃውሞ እስካልሰማ ድረስ የመከላከያ ጠበቃዎችን መከራከሪያ አድምጦ በቀላሉ እስረኞችን ሊፈታ ይችላል። አራት ነጥብ። «በፍርድ ቤት ጉዳይ ውስጥ መግባት አንፈልግም» የሚል ምክንያት ሊሰጥ አይችልም። እነ እስክንደርን የከሰሰው የሥራ አስፈጻሚው አካል ነው።የሥራ አስፈጻሚው አካልም አዲስ መረጃ በማግኘት ይሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ክሱን በማናቸውም ጊዜ ሊያነሳ ይችላል።
  2. መድረኩ የስነ-ምግባር ኮዱን ቢፈርም መልካም ነበር። የአመራር አባላቱ በሰከነ መልኩ ትኩረት ሰጥተውበት ለሰላምና ለእርቅ የደርሻቸውን ያደርጋሉ ብዬ አስባለሁ። በኢሕአዴግ ዘንድ ግን መድረኩ ፈረመም አልፈረመም ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጥ የለበትም። ለኦብነግ ያሳየውን ለመድረኩ የማያሳይበት ምንም ምክንያት የለም። በመሆኑም ኢሕአዴግ ከመድረክ ጋር የገባውን እልህ አቁሞ፣ ለአገርና ለሕዝብ ሲል ለመቀራረብና ለእርቅ ቦታ መስጠት አለበት። አብረው በጋራ የአገርን ችግር በመፍታቱ ዙሪያ ከሌሎች እንደ ኤደፓ ካሉ ድርጅቶች ጋር ሆነው መነጋገር አለባቸው።
  3. የመልካም አስተዳደር፣ የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ኢሕአዴግ ቁርጠኝነቱን ማሳየት ይኖርበታል። ከምርጫ ዘጣና ሰባት በፊት የታየ መልካም ጅማሮ ነበር። ወደዚያ መመለስ ያስፈልጋል። ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኋላ የተፈጠሩ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ደግሞ ከላይ እንደገለጽኩት፣ አሉ ከሚባሉ በአንጻራዊነት ጠንካራ ከሚባሉ እንደ መድረክ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅንነት እንደ ወንድማማቾች መነጋገር ያስፈልጋል።
  4. የኢሕአዴግ ባለስልጣናት በሚሰጧችው ቃለ መጠይቆችና ንግግሮች መጠንቀቅ ያለባቸው ይመስለኛል። በአገራችን ብዙ ቁስል ያለባቸው በርካታ ወገኖች አሉ። አንዱ የሌላውን ስሜት መጠበቅ መቻል አለብን። በተለይም በአመራር ላይ ያለን ሰዎች፣ የምንናገራቸው በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንደሚሰሙት ተረድተን፣ በተቻለ መጠን የሚያንጽ፣ የሚያቀራረብ፣ የሚያበረታታ ቃላት እንጂ የሚያፈርስ፣ የሚያቃቅርና ሌላውን የሚያዋርድ ቃላቶች ከአንደበቶቻችን ባይወጡ መልካም ነው።

በርግጥም አቶ ኃይለማርያም እንዳሉት ብዙ ነገሮች እንደ አንድ ሕዝብ ማከናወን እንችላለን። የታቀዱትን ብቻ ሳይሆን ከታቀዱት ውጭ የማድረግ አቅምና ጉልበት ኢትዮጵያውያን አለን። ከማንም ሕዝብ አናንሰም። የጎደለንና ያጣነው ፍቅር ነው። እንግዲህ የፍቅር አምላካ እግዚአብሄር ልባችንን ለፍቅር፣ አይሞሮዋችን ለጥበቡ ይከፍትልን።


አማኑዔል ዘሰላም

 

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!