ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ጤና ይስጥልኝ ክቡራትና ክቡራን አንባቢያን፤

በዚያኛው ሰሞን ስለብዙዎቹ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከእግዚአብሔር መንገድ መራቅና ስለሕዝበ ክርስቲያን የመንፈስና የልብ መሸፈት አንዳንድ ነጥቦችን ተናግሬ ነበር። አንድ ሦስት ያህል የነጻው ሚዲያ ድረገጾች አስተናግደውታል። እግዚአብሔር ይባርክልኝ፤ መንግሥተ ሰማይንም ያውርስልኝ። ሙከራየ ጥቂቶችን ከገቡበት አረንቋ እንዲወጡ - እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ - ለማሳሰብ እንጂ ኃይማኖተኝነትን ለመክሰስ ወይ ለመውቀስ አይደለም።

ኃይማኖት የሌለው ሰው ልጓም እንደሌለው የጋማ ከብት ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ እንደመኖሩ በዚያው መጠን ኃይማኖት አለኝ የሚልም ሰው ከለየለት ኃይማኖት የለሹ ሰው ባላነሰ ምናልባትም በከፋ ደረጃ አጥፊ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ይስተዋላልና ያን መረዳትና ሲቻልም ማስቀረት እንዲቻለን በዚህ ረገድ የሚታዩብንን ማኅበረሰብኣዊ ህፀፆች በግልጽ መመልከቱ እንደጥፋት ሊወሰድ አይገባም። በግልጽ የሚታይንና ጥፋት የሚመስልን ነገር የማጋለጥ መብት ደግሞ ከማንም በችሮታ ሊሰጥ ወይ ሊከለከል የማይችል ሰው በመሆን ብቻ ሊገኝ የሚችል ሥልጣን ነው። በዚህ አጋጣሚ የእረኛ ማጋጣ በጎችን ቀበሮ እንደሚያስበላ መጠቆምም ዋናው ዓላማየ ነው። ጋጣውና በረቱ በየትኛውም የኃይማኖት ክፍል (You may call it sect or denomination,) ይመራ ዋናው ጉዳይ ግን የራሱን ቀኖና በትክክል መከተሉ ላይ ነው። ወያኔን ብዙዎች የምንወቅሰውና የምንከሰው ሌላው ሁሉ ይቅርና ራሱ የሚያወጣቸውን ሕጎችና ካለሕዝብ ቀጥተኛ ተሣትፎ በሚመስሉት አፈንጋጮች ብቻ ተደግፎ የደነገገውን ሕገ መንግሥት እንኳን ማክበር ባለመቻሉ ነው። ራሱ ያቆመውን ሕግ ማክበር የማይችል ደግሞ ዕብድ ወይ ሕጻን ልጅ እንጂ ዐዋቂ ሊባል አይችልም። ‹ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ› የሚባለውም ለዚህ ዓይነቱ አፄ በጉልበቱ ነው።

ለማስተናገድ ድፍረት ያጡት አንድም ያልኩት ሊገባቸው አልፈለጉም አለበለዚያም የሀገራችን ችግር የዴሞክራሲ እንጂ የኃይማኖት አይደለም ብለው ተዘናግተው ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ እውነትን በጥሬው መናገር ለሺዎች ዘመናት በሕዝብ ጫንቃ ላይ ተጎብሮ በእግዚአብሔር ስም ሲያነሆልለን የባጀው ከማይምነትና ከባህላዊ ልማዶች ጋር የተዛነቀው ኃይማኖታዊ ይትበሃላችን በነሱም ላይ የፍርሀት ድሩን አድርቶ ላለመዳፈርና ጥርስ ውስጥም ላለመግባት ፈልገው ይሆናል - ግን ግን እኔ እላለሁ - መጠንቀቅስ ኅሊናን ከሚያስጨንቅ የእውነት ፍላጻ ነው፤ መጽሐፉም ‹ሥጋን የሚገድሉትን … ሣይሆን ነፍስን የሚገድለውን… ፍሩ› ይላልና። በየትኛውም መንገድ ይሁን ያን “ወርቅ ጽሑፍ” አለማስተናገዳቸው በዚህ ወይ በዚያ የሚያሳማቸው ነገር መኖሩን የሚያመላክት ብቻ ሳይሆን በሀገራችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ባህል ገና (እ)ያልዳበረ እንደሆነና ዕዳ ጉዳችን ተዝቆ የማያልቅ መሆኑን ጭምር የሚጠቁም ነው። እግዚአብሔር ይሁነን ከማለት ውጪ ምን ይባላል?

በዚያ ጽሐፍ በራሴ አጎት ላይ የደረሰ አሳዛኝ ታሪክ ወደፊት እገልጣለሁ ብዬ ነበር። ነገር ግን ቆይቼ ሳስበው ከዚያ በላይ መሄዱ ጥሩ እንዳልሆነ ስለተረዳሁ ያ የጠቀስኩት የአጎቴ የነፍስ አባት የትላልቅ ሴቶችና ወንዶች ልጆች እናት የነበረችውን አሮጊት ባለቤቱን ጣጥሎ የአጎቴ ዐርባ በቅጡ ሳይወጣ ጓዙን ጠቅልሎ መግባቱን ብቻ መጠቆሙ ከበቂ በላይ ነው። ይህ እንግዲህ የዛሬ 50 ዓመት ገደማና በገጠር ውስጥ ነው። በተለይ በዚህ ዘመነ መንሱት ውስጥ በከተማ እየተሠራ ያለውማ ከዚህ በስንት እጥፍ ይብስ? ይህን መሰል ጨዋታ ከጓደኞች ጋር አንስቼ በቀደም ዕለት ስናወራ አንዷ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሩቅ ሴት ጓደኛችን ያጫወተችን ገጠመኝ በእጅጉ አስደመመኝ - በእውነቱ የሚዘገንኑና እጅግ የሚያስጨንቁ ብዙ ነገሮችን እንሰማለን። እናም እሷን ብቻ ተንፍሼ ወደጀመርኩት ሃሳብ እገባለሁ። ይቅርታችሁንና ትዕግስታችሁን ወዳጆቼ፤ የችግሮቻችንን ዙሪያ ገባ መረዳት ለመፍትሔው ሁለንተናዊ ፍለጋ ያመቻልና ነው በዚህ አቅጣጫ ትግስታችሁን መሻቴ። እንጂ የቄሣርን ለቄሣር በሚለው ነባር ብሂል የኃይማተኞችን ጉዳይ ለነርሱው ሰጥቶ ሥጋዊውን መንገድ ብቻ መንጎድ በተቻለ። ግና ያ ብቻውን አይበቃም። ሥጋና ነፍስ የተቆላለፉ ናቸው። የአንዱ መጎሳቆል ለሌላኛው መጎሳቆል ቀጥተኛ ተጠያቂ ነው። በተለይ ፍቅርንና ሰላምን የተጠማች ነፍስ ቂም በቀልንና ዐመፅን ካረገዘች ሥጋ ጋር ስትዋሃድ ምን ሊከሰት እንደሚችል ኢሕአዲጋውያንን የሚያውቅ ያውቃል። ስለዚህ የኃይማኖት በቅጡ መኖርና አለመኖር በአንድ ማኅበረሰብ ገጽታ ላይ ያለው ተፅዕኖ ቀላል ባለመሆኑ እነዚህን መሰል ማኅበራዊ ጉዳዮች አንዳንዴ መዳሰሱ ጉዳት የለውም ባይ ነኝ።

ያቺ ጥሩ ክርስቲያን እንደሆነች የገመትኳት የሥራ ባልደረባችን እንዲህ አለችን፡- “የእህቴ ነፍስ አባት ጸሎት አድርገው ቤቷን ጠበል ረጭተው ሊሄዱ ሲሉ አንድ መቶ ብር ከቦርሣዋ አውጥታ ልትሰጣቸው ስትል ‹አይይ…! ይችማ ምን አላት! ዛሬ መቶ ብር አንድ ብር ሆና ምን ትገዛለች ብለሽ ነው የኔ ልጅ?› ብለው ገንዘብ እንድትጨምርላቸው የሌሎች ነፍስ ልጆቻቸውን ትሩፋት እየጠቀሱ በቃላትና በዐይነ ውኃቸው ቢማጸኗትም ‹እንዴ አባ! እኛ እኮ ድሆች ነን፤ አቅማችን የቻለውን እንሰጣለን እንጂ ከሀብታሞቹ ጋር ለምን ያወዳድሩናል? ብላ ሸኘቻቸው።” ይህን ስትነግረን የጠላታችሁ ዐመድ ቡን ይበል ሁላችን ዐመዳችን ቡን አለ። እስከዚህ ወርደናል። ኃይማኖታችንን ሸቀጥና ውራጅ ልብስ አድርገውብናል፤ ክርስቶስ ይሄኔ ነበር ‹የአባቴን ቤት መሻቀጫ አደረጋችሁት!› ብሎ ድንብርብራቸውን ማውጣት የነበረበት - ታሪክ ተደገመ።

መስቀል ከተሳለምክ በኋላ እጅ እጅህን የሚያየው ቄስ ብዙ ነው፤ ከነአካቴው ሀፍረቱን ሸጦም ‹ለመስቀሉ አምስት ብር ወዲህ በል!› የሚልህ ዐይኑን በጨው ያጠበ ደፋርም ያጋጥምሃል - በቅዳሤ ሰዓት ልብሰ ተክህኖውን ግጥም አድርጎ ለብሶ ንዋየ ቅድሣትን ይዞ በቡድንና በተናጠል በታቦት ስም የሚለምንህ ሞልቷል - እንደምክንያት ለታቦት ማሠሪያና ለዕድሳት ይበሉህ እንጂ በአብዛኛው ለግላቸው ነው - ማኅተምና ካርኒ እንደሆነ ዕድሜ ለጥቅም ሼሪኮችና ፎርጀሪ ችግር የለም - የትም ይገኛል። በዚህ ‹የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ግንባታ› በሚሰኝ የዘመኑ ታላቅ ኢንቬስትመንት የልመና ቢዝነስ ምክንያት ያለፈላቸው ካህናትና ምዕመናን በጣም ብዙ ናቸው ይባላል። በሥራ ከሚገኝ ገቢ ይህኛው ስንጥቅ ነው አሉ ልጄ። በገበያ ጥናት የኢኮኖሚክስ ሕግ መሠረት አንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሰው ወደሌላ ሥፍራ እንዳይሄድ ብዙ ጽላት በመደራረብ የሚሸቅጡ ቄሶች አሉ - ‹እመብርሃን እዚሁ ካለችልኝ ለምን ወደሌላ ቦታ በመሄድ እለፋለሁ?› እንድትልና በዚያው ሁሉንም እንድታገኝ። በጠበል ሽያጭ የሚከብሩ አሉ - ደግነቱ በገንዘብ የሚገኝ ጠበል የፈዋሽነት ኃይሉ በፈጣሪ ይሰረዛል እንጂ። የደብር አለቃንና ቀዳሽ ወይ አወዳሽ ካህንን ደህና ገቢ ያለው ቦታ በጥሩ ደሞዝ ለመመደብ በሺዎች የሚገመት ጉቦ አስከፍለው በቀላሉ የሚከብሩ አለቆችና ሊቃነ ጳጳሣትን ጨምሮ ከፍተኛ የቤተ ክህነት ባለሥልጣናት ሞልተዋል።

ጉቦ ካልከፈልክ - ለምሳሌ - የቅ. ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን አለቃ ሆነህ መሾም አትችልም ይሉሃል። በኪነ ጥበቡ ይታረቀን እንጂ በቁማችን ጠፍተናል። እረኛው የጠፋበት በግ እና መሪ የሌለው ሕዝብ ደግሞ ምን ሊገጥማቸው እንደሚችል በሀገራችን በግልጽ እየታዬ ነው። እነኚህን በክተው እያበከቱ ያሉ ሰው መሳይ በሸንጎዎችን መንካት ኃጢያት ከሆነ አሁኑኑ ልኮነን። ግን እንዳይመስለን - በዚህ የሚኮንን አምላክ የለም - እነሱው ናቸው እንዳናያቸው ያሳወሩን። ሀገርንና ሕዝብን ከመንግሥት ባልተናነሰ እንዲያውም በበለጠ ሁኔታ እንዴት አድርገው አሽመድምደዋት እንዳሉ ብዙ ነገር መናገር ይቻላል። አፄ ቴዎድሮስን የመሰለ ይላክባቸው!!

በነገራችን ላይ ትችቴ በኦርቶዶክስ ላይ ጠንከር ያለ እንደሚመስል አላጣሁትም። ይህ የሆነው የአነሳሴ ሚዛን ነው። እንጂ የተለያዩ ጥፋቶች በሌሎች እምነት ተከታዮችም እንደሚስተዋሉ ጠፍቶኝ አይምሰላችሁ። አብነቶችን ግን ሳልጠቁም ማለፍ አልፈልግም - ከወቅታዊው ልጀምር።

ሀገራችን የጉድ መፍለቂያ ከሆነች ዋል አደር ማለቷ አይዘነጋም። ‹በሕይወትህ ምን የሚያሳዝንህ ነገር ይታወስሃል?› ተብሎ የተጠየቀ 85 ሚሊዮን ሕዝብ ‹የሚመራ› ሰው ‹በብዙ ነገሮች ደስተኛ ነኝ፤ ነገር ግን በእናቴ አለመዳን ሁልጊዜ አዝናለሁ› ብሎ መናሩን ስሰማ እኔም በዚህን መሰል ሰው ‹በመመራቴ› ክፉኛ ማዘኔን የምገልጽላችሁ ፈጣሪ ከዚህን መሰሉ ሞኝነት እንዲመልሰው በመማጸን ነው። በእውነቱ ትልቅ ስህተት ነው፤ የሆዱን በሆዱ ይዞ ቢያንስ በአደባባይ እንዲህ ባይናገር ይመረጥ ነበር። የሰውዬው ሴክት በትልቅ ግምት 10 ሚሊዮን ተከታይ አለው ቢባል ቀሪው 75 ሚሊዮን ሕዝብ የሌላ እምነት ተከታይ ነው ማለት ነው - ‹የጠፋ›። ስለዚህ ይህ ሰው ‹የጠፋ› ወይም በርሱው አገላለጽ ‹ያልዳነ› 75 ሚሊዮን ሕዝብ ‹እየመራ› ነው ማለት ነው። ከዚህ በላይ ድንቁርና የለም። የኔን መዳንና አለመዳን እንኳን ሌላ ሰው እኔ ራሴም አላውቅም። ማን ነውና እሱ ስለኔ መዳን አለመዳን በአደባባይ አፉን ከፍቶ የሚናገር? ከዚህ ዓይነቱ አስነዋሪ ንግግር መታቀብ ያስፈልጋል፤ በዚህ የረቀቀ መለኮታዊ ሥራ አላግባብ እገቡ ብዙዎች ሲጃጃሉ አስተውላለሁ። እውነትን መናገር ካስፈለገ የጠፋውስ በኃይማኖቱ ምክንያት ሳይሆን በደም ባሕር ከሚዋኝና በሙስና ከተጨማለቀ ፓርቲ ውስጥ የሚገኘው ርሱ ራሱ ነው። በመስትዋት ቤት ውስጥ የሚኖር ሰው ድንጋይ ለመወርወር የመጀመሪያው መሆን የለበትም መባሉ ይህን ዓይነቱን ዐላዋቂነት ለማለዘብ ነው። የእርሱ እናት ይዳኑ አይዳኑ የሚያውቀው አንድ አምላክ ሆኖ በዚህ ንግግሩ ግን መላውን የሌላ እምነት ተከታይ ሕዝብ አስቀይሟልና ንስሃ ይግባ።

ማንኛችንም ይህን ነባራዊ እውነት በቅጡ ብንረዳ ለማኅበራዊ ተራክቦኣችን ስኬታማነት ይበልጥ ይጠቅመናል። ‹ከአንተ ኃይማኖት ይልቅ የኔ ትክክለኛው ነው› የሚሉት ፈሊጥ የከንቱዎች እንጂ የአስተዋዮች ሊሆን አይችልም። የሚያዋጣውን የሚያውቅ ባለቤቱ እንጂ ጎረቤቱ ሊሆን አይገባም፤ አይችልምም። ዕድሜው ለአካለ መጠን የደረሰን ሰው ይህን ተከተል ያን አትከተል ብሎ የሐኪም ማዘዣ ዓይነት ኃይማኖታዊ ትዕዛዝ ማውጣት የጤናማነት ምልክት አይደለም። ከዚህ አንጻር ብዙ ስህተቶችን ከየእምነት ተቋሙ እናያለን - በተለይ ተከታይን በማፍራት ረገድ። አስታውሳለሁ - አንድ ወቅት በአንድ ሴክት አንድ ፊልም ተሠርቶ ለዓለም ተሠራጭቶ ነበር። በጣም ነው ያስገረመኝ። ሆሊውድ እንኳን እንደዚያ ያለ አስደናቂ ፊልም ሊሠራ አይችልም። የፊልሙ ይዘት አንድ የኃይማኖት አባት ከአንድ ሴክት ወደሌላ ሴክት እንደኮበለሉ የሚያሳይ የቁጩና ፍጹም ያልተሳካ ሙከራ ነበር - ያን ጉድ የሸፋፈንኩት ሆን ብዬ ነው - እንኪያውስ ብዙ ስንክሳር ባጻፈኝ። ያሣፍራል፤ ነገርን ከሥሩ የሚመረምር ሰው ጠፍቶ እንጂ በዚያ መጥፎ ሥራቸው ምክንያት ሴክታቸው ምዕመናንን አጥቶ ባዶ በቀረ ነበር። ልብ አድርጉ! ሰውን ማታለል ቀላል ሊሆን ይችላል - አንዴም ሁለቴም ምናልባትም ከዚያም በላይ፤ ፈጣሪን ማታለል ግን በጭራሽ አይቻልም። ለተወሰነ ጊዜ ማታለል ቢፈቀድልን እስከዘላለሙ ማታለል እንችላለን ማለት አይደለም።

እናም የየትኛውም እምነት ተከታይ መጠንቀቅ የሚኖርበት ነገር አለ፤ ይሄውም በአንዱ ኪሣራ ሌላው ለማትረፍ የሚደረገው ሩጫ በፍጹም የማያዋጣ መሆኑን ተገንዝቦ ወደኅሊና መመለስና ፈጣሪን በትክክል መታዘዝ እንደሚገባ መረዳት ይገባል፣ ‹እንዳገርህ ቀድስ፣ እንዳገሬ እቀድሳለሁ› ይባላል። ጥሩ ብሂል ነው - ‹ሰው በወደደው ይቆርባል›ም እንላለን፤ እናም ኃይማኖትን ተመርኩዞ የሚፈጸምን በጉልኅ የሚታይ ህፀፅና ነውር ከመንቀስና ከማሳየት ባሻገር የሰውን የእምነት ነጻነት ባንጋፋ መልካም ነው። ይህ ሲባል ደግሞ ለእውነትና ስለእውነት ብለን በእውነት መንገድ እንመላለስ እንጂ ያለንበት ሴክት በግድ ከሌሎች የበለጠ ወይም ያነሰ ነው ለማለት እንዳልሆነ መገንዘብም ያሻል። ጣፋጭ ፍሬ ከዛፉ ላይ ያስታውቃል፤ መልካም ሥራና ጥሩ አረማመድም ከመንገዱ በበለጠ ወደጽድቅ ቦታ ያደርሳሉ። እናም ‹የኔ ካንተ ይበልጣል› የሚለውን የደናቁርት ዜማ እንተወው።

የደርጉ ሊቀ መንበር ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አንድ ወቅት “በርግጥ አሁን ደርግ አለ?” ማለታቸው ይታወሳል። በርግጥም ያኔ ደርግ አልነበረም፤ ምክንያቱም መለዮውን አውልቆ ባለሱፍና ባለ ክራቫት የጠብደል ወርሃዊ ደሞወዝ ባለቤት ባለሥልጣን ሆኖ ነበርና። ያኔ የደናቁርቱ የደርግ መሪ መንግሥቱም ሌሎች ከየጎሣውና ከየብሔሩ - እንደሚመስለኝ - ታስቦበት ሳይሆን በአጋጣሚ የተውጣጡ የደርግ አባላትም ስማቸው ተቀየረ እንጂ በሕይወት ነበሩ። (‹ደርግ›ን ደብድብ፣ ርገጥ፣ ግዛ እንለው ነበር በምህጻረ ቃልነት)

ዛሬስ ኢሕአዴግ አለ?

እንተማመን ኢሕአዴግ የለም። ሰዎች ግን ያለ እየመሰላቸው ሲደነብሩ ይታያሉ - (ክፉ አውሬ ለምሳሌ እባብ ሞቶም ያስደነግጣል - አንበሣ ያላልኳቸው አክብሬው ነው - ለምን፣ አንበሣ ጀግና ነው - ጀግና ደግሞ መሐሪ ነው ፤ ማሸነፉን ሲያውቅ እንደወያኔ ቀብር ድረስ ገብቶ ‹እከሌን ገዳይ!› ብሎ አይፎክርም - ፈሪ ነው ማሸነፉን የማውቅና ዕድሜ ልኩን በጠላትነት የፈረጀውን አካል እንዳላሸነፈ እየተጠራጠረ ሬሣ የሚደበድብ - ለነገሩ ሞቶ የተቀበረስ ሲኖር አይደል - ወደፊት እናያለን)። ኢሕአዴግ አቶ መለስ ዜናዊ ሲሞት አብሮ ሞቷል። ነገር ግን አንዳንዴ እንደዚህ ያለ ነገር ያጋጥማል - ሞቶ ያለመሞት ወይም ያሉ መስሎ መሞት። ከታሪክ ለማስታወስ ያህል ደርግ የሞተው ግንቦት 8 ቀን 1983ዓ.ም መሆኑን ያጤኗል። ኮ/ል መንግሥቱ እነኚያን ሀገሪቱ በድህነት አቅሟ ለብዙ ዓመታት በሀገር ውስጥና በውጪ ያሠለጠነቻቸውን ‹ጥቂት/ጢኖ› የጦር መኮንኖች ብዙ የደከሙላትን ሀገራቸውን ለአፍታም ቢሆን ማሰብ አቅቷቸው ለአንዲት የሥልጣን ወንበራቸው ሲሉ ከረሸኗቸው ማግሥት ጀምሮ ሀገሪቱ ውቃቢ ራቃት። ‹በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም› ያሉ ሌሎች የጦር አመራሮችና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ኮሎኔሉን ጅባት ብሎ በመጥላትና በመክዳት ብቻቸውን አስቀራቸው። እሳቸውም የሠሩትን መጥፎ ነገር ሁሉ እንደታላቅ ድል በመቁጠር በግትርነታቸው ገፉበት - ራሳቸውን ለመመርመር የአምባገነንነት ባሕርይ አልፈቀደላቸውም - በዚያ ላይ ሆድ አምላኪው አጨብጫቢና አንፋሽ አከንፋሹም በዙሪያቸው አለ፤ አምባገነኖች ደግሞ ሞተውም እንዳልሞቱ የሚቆጥሩ ጅላጅሎች ናቸው። ሕዝቡና ጦሩ ሌላ አማራጮች ቢዘጋጉበት በወቅቱ በለስ እየቀናቸው ለመጡት ለወያኔና ሻዕቢያ ያን ክፉ መሪ አጋልጦ ሰጣቸው።

እሾህን በእሾህ ያስነቀሉት የመሰላቸው ጦሩና ሕዝቡ ግን ከአንዱ የመከራ አዙሪት ሲወጡ ወደባሰበት የመከራ አዙሪት ገቡና መለስ ዜናዊ የተባለ በቂም በቀል ተረግዞ ለጥፋትና ዕልቂት የተወለደ የባንዳ ልጅ ቁም ስቅላቸውን ያሳያቸው ጀመር። መራገም የሚያውቅበት የኢትዮጵያ ሕዝብ - ተሓት፣ ተሓሕት፣ ማገብት፣ ሕወሓት፣ ማሌሊት፣ኢማሌኃ፣ ኢሕአዴግ፣… በሚሉ የክትና የሠርክ ስሞች የራሱን ድርጅት አባላትና ኤሊቶች ሳይቀር እያታለለና በሥልት እየጨፈጨፈ፣ እያሰደደና እያሳደደ የመጣውን ለገሠ ዜናዊን ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት አለቀሰበት - ይሄውና በውስጥ ዐዋቂዎች እንደተገለጸው ባለፈው ሐምሌ 7 ቀን 2004ዓ.ም ከሰንኮፉ ወልቆ ተገነደሰ። እሱም ብቻ አይደለም፡- ከገሚስ የሚያልፈውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በኃይማኖቱ ገብተው እንዲያኮላሹለት ኃይማኖቱንም እንዲበርዙና እንዲከልሱ ከውጪ ሀገር አስመጥቶ ከሕግ አግባብ ውጪ ያስቀመጣቸውም አረማዊ ፓትርያርክ አብረው ተገነደሱ - ‹ሃሌ ሉያ› ይባላል እንጂ አይለቀስም፤ አይታዘንምም - ምክንያቱም እንደመጽሐፉ ‹ብንኖርም ለርሱ ባንኖርም ለርሱው› ነውና! የሕዝብ ጸሎት ሥምረት ከዚህ በላይ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አይታወቅም - የነዚህን ግለሰቦች የዐዋጅ ሞት ተከትሎ የተስተዋለውን የዕብደት መሰል ቲያትር ግን ለጊዜው በዝምታ ማለፉ ይመረጣል። ይህን መሰል ቲያትር ይነስም ይብዛም ዱሮም ነበር ፤ አሁንም አለ፤ ወደፊትም ይኖራል። እውነት ግን ምን ጊዜም እውነት ናትና ብትሰለስል እንጂ አትበጠስም። ለሞተ ማዘን ተገቢ ቢሆንም ያን ያህል የተነረተው ድራማ ግን ለትዝብትና ለሥላቅ ከመዳረግ በስተቀር ማንንም አይጠቅምም። ‹ሲነጋ ለማፈር!› እንዲሉ ነው። ነገ ያፍሩበታል።

‹ኢትዮጵያን አደራ፤ ጀግና አይሞትም፤ ባለራዕዩ መሪያችን፣ ….› ያልተባለ ነገር የለም። በጸሎት ብዛትና በኅሊና ጸሎት መዝጎድጎድ፣ በቢልቦርድና በአርቲፊሻል የሀዘን ጥብቀት ሰው ቢድን ኖሮ መለስን ቀድሞ የሚድን ባልነበረ። ግን ቂልነት ነው። ሳያምን የሞተን ለማጽደቅ የተደረገው ነገር ሁሉ ቤተ ክርስቲያንንም ሰዎቿም ለትዝብት ከመዳረግ ውጪ አንዳችም አይፈይድም። ያ ሁሉ ልፋት በጠቀመ እግዚአብሔርም እግዚአብሔርን ባልሆነ! ዜጎችም ዕንባቸውን በከንቱ እንዲያባክኑ ተገደዱ - ላይመልሰው ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲባል ብቻ ብዙ ነገር ታዘብን። ልድግመው - ‹ሲነጋ ለማፈር!›

በወፍ በረር ቅኝት ታሪካዊ ዳራውን በመጠኑ ከዳሰስን ኢሕአዴግ እንዴት ነው የሌለው ለምንስ ነው ኢሕአዲጋዉያን አሁን በሚገኙበት የተዘበራረቀ ሁኔታ ውስጥ ሊገኙ የቻሉት የሚሉትን ባጭሩ መመልከት ተገቢ ነው። ለዚህም ዓለማቀፋዊ መነሻ ታሪክ አናጣም።

ሌኒን የዛሩን መንግሥት ለመጣል ሲታገል ‹ምን ነካህ? አብደሃል? ከዚህ እንደብረት ከጠነከረ ግድግዳ ጋር ታግለህ እንዴት ታሸንፋለህ?› የሚሉት ወገኖች ነበሩ። መልሱም ‹ግድግዳው የበሰበሰና ያረጀ ስለሆነ በትንሽ ኃይል ሲገፋ የሚወድቅ ነው› የሚል ነበር። እውነት ነው። ለድል ለመብቃት መስዋዕትነት መክፈል ያለ በመሆኑ ቦልሼቪኮች ትግሉ የጠየቀውን ከፍለው ለድል በቅተዋል።

ወያኔም በሕዝብ መክዳትና በጦር የውጊያ ሞራል ማሽቆልቆል እንዲሁም በምዕራባውያን ሁለንተናዊ ድጋፍ በዚያም ላይ ለገንዘብ ባደሩ የጦር መኮንኖች ሻጥር ተደጋግፎ ካራ ምሽግን በማለፍ የሸዋ እምብርት ሸገር ላይ ጉብ አለ - በህልም ብቻም ሳይሆን በቅዠትም ዐይቶት የማያውቅ ድል በድንገት በእጆቹ መዳፍ ገባለት - በለስ ሲቀና እንዲያ ነው። በቁሙ በስብሶ የነበረው የደርግ ሥርዓት የሚገፋው አጥቶ ለሁለት ዓመታት ያህል በሰመመን እንቅልፍ በአለሁ የለሁም እየተንጠራወዘ ከቆዬ በኋላ የምናውቀውና በያመቱ እየዘገነነንም ቢሆን በጆሯችን ‹የሚንቆረቆረው› ‹ጀግናው የኢሕአዴግ ሠራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረው ሬዲዮ ጣቢያ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል…› የሚል አዲስ ቅንቅን ሊዘመርበት በቃ። ነገሩ የሎሚ ተራ ተራ ጉዳይ ነው። ያ መዝሙር ታድሶ ወደፊትና በቅርቡ በሌላ ቃናና ቅላጼ እንደሚዘመርበት በጣም ግልጽ ነው። ግን ለመልካም ይሁን ብሎ መጸለይ ወቅታዊ ምኞታችን ሊሆን የሚገባው ይመስለኛል።

ኢሕአዴግ አልሞትኩም ብሎ ሌት ከቀን እንዲዋሽ የተገደደበት ምክንያት የመሞቱ ምሥጢር ፋታ ስላሳጣው ነው እንጂ ከሞተ ቆይቷል። በመሠረቱ ኢሕአዴግ የሞተው ዛሬ ሳይሆን ከሰባት ዓመታት በፊት በተደረገው የ97ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ነው። ይሁንና ዕድሜ ለመርዝ አቀባዮቹ ምዕራባውንና የሩቅ ምሥራቅ ሼሪኮቹ ሬሣውን በግብጽ የዘምዘም ውኃ አባብሰው(mummification)፣ በአይ ኤም ኤፍና በዓለም ባንክ ብድር እስትንፋሱን አጠናክረው በነጻ እንዲጋልበን ፈረስን ያለልጓም ሰጡትና በሜዳ በምንመሰለው ጭቁን ኢትዮጵያውያን ላይ ለቀቁብን - ያበደ ውሻን ጃዝ ብለው የመልቀቅ ያህል፤ የሥራቸውን ይስጣቸው። እኛም የሞተውን እንዳልሞተ ቆጥረን ተጋለብንለት - አሁን ድረስ። ቁጥጥሩን አጠበቀ፤ ሥቃዩን ጨመረ፤ በኑሮ ውድነቱ ሰንጎ ያዘን፤ እንኳንስ ለመንግሥት ተቃውሞ ለሽንት ማውጫም የሚሆን የወንድነት መግለጫ ሥነ ሕይወታዊ የሰውነት ክፍል አጣን። ግን ይህም የሚያልፍና ለበጎም ነው። እኛ ብቻ አይደለንም በዚህን ዐይነቱ ሸምቀቆ ውስጥ እያለፍን ያለነው - ብዙዎች ነበሩ - አሉም። ሂደት ነውና ወደፊትም ይኖራሉ። የኛን ግን አደራውን በቃችሁ ይበለን።

የሥንግ የተያዘ ሕዝብ ደግሞ አይፈረድበትም። ጊዜ ጀግናን ይፈጥራል። ጊዜ ፈሪን ይፈጥራል። ጊዜ ጀግናን ፈሪ ያደርጋል። ጊዜ ፈሪንም ጀግና ያደርጋል። ‹የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም› መባሉም ለዚህ ነው። ጀግንነት ደግሞ ከአመራርም ይወለዳል። ቁጥር ብቻውን ደግሞ የትም አያደርስም። አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን የሚገመተው የቻይና ሕዝብ ሌላ አማራጭ እንዳይኖረው ተደርጎ በአንድ የኮሚኒስት ፓርቲ ብቻ የሚቀጠቀጠው ፈሪ ሆኖ አይደለም። 90 ሚሊዮኑ የግብጽ ሕዝብ ለ30 ዓመታት በሙባረክ የተቀጠቀጠው ፈሪ ሆኖ አይደለም፤ 6.5 ሚሊዮኑ የሊቢያ ሕዝብ ለ41ዓመታት በጋዳፊ የማሰነው፣ 23 ሚሊዮኑ የየመን ሕዝብ በአብደላ ሳለህ ለ33 ዓመታት የተቀጠቀጠው፣ ሃያ ሚሊዮኑ የሦርያ ሕዝብ ከ42 ዓመታት በላይ በአባትና ልጅ በዙር የሚቀጠቀጠው ፈሪ ሆነው አይደለም፤ 142 ሚሊዮን የሚሆነው የራሽያ ሕዝብ ለፑቲን የተመሳሳይ ጉልቻ መለዋወጥ የተንበረከከው ፈሪ ሆኖ አይደለም፤ 304 ሚሊዮን የሚደርሰው የሰሜን አሜሪካ ሕዝብ በዴሞክራሲ ስም የሚቀለድበትና ከራሱ ብዙዎቹ ሳያልፍላቸው የሀብታም ተመራጭ መሪዎቹና የጠብ ያለሽ በዳቦ መንግሥቱ ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲባል አምባገነን መንግሥታትን ሲረዳና በሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ሲያግዝ፣ በድንበር ዘለል ጣልቃ ገብነትም ጠላቶችን ሲያፈራና የገዛ ጥያራቸውን ወደነዲዳዊ ፍላፃነት ለውጠው በአሸባሪነት ንጹሓን ዜጎችን እንዲጨርሱ ሜዳና ፈረሱ ሲበጃጅላቸው በዝምታ የሚያልፈው ፈሪ ሆኖ አይደለም ፣ … ብዙ ነገሮችን መናገር ይቻላል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ጉልበቱ ጸሎቱ፣ ተበቃዩም ፈጣሪው ነውና ከሰባት ዓመት በፊት የሞተውን የሀገሩን ጠላት በድጋሚ ገደለለት፤ሰው ሲሞት ጠላትም ቢሆን እልል ተብሎ አይቀበርምና በምርም ሆነ በለበጣ ተለቀሰለት። በሕይወት እየኖረ የጥፋት ዘመቻውን ከሚያካሂድ ሞቶልን አልቅሰን መቅበራችን በጣም የሚያንስበት ውለታው ነው። ዱርዬና የቤት ዕቃን ሸጦ የጨረሰ መጥፎ ልጅ ሲሞትስ ለደንቡ ያህል ተለቅሶ ይቀበር የለምን? እናም አንቅናበት። ተመልሶ ባለመምጣቱ ግን እርግጠኛ እንሁና ቢያንስ በዚያ እንደሰት። እንዳይመጣ ታዲያ ከወሬና ከአሉቧልታ ባለፈ ብዙ ነገር መሥራት ይጠበቅብናል። አመራር - አመራር - አመራር፤ ወሳኝ የወቅቱ ጥያቄ!!

ይህ ሁሉ ወያኔዊ ትርምስ ሞታቸውን ለመደበቅ ነው። ሞት ደግሞ አይደበቅም። ሬዲዮው ቲቪው ሁሉ መሞታቸውን በገሃድ እያሳበቀ ነው። እንደልማድ ሆኖ ብዙዎቻችን የወያኔን ሚዲያ የምንቀበለው ከሚናረው በተቃራኒው ነው። ወያኔ ደግሞ በተፈጥሮው እውነት እርሙ ነው። እውነትን መናገር አይችሉም ብቻ ሳይሆን ሥነ ተፈጥሯቸው አይፈቅድላቸውም። ስለዚህ ለምሳሌ በነሱ ጣቢያ ብዙ ተመረተ ከተባለ ምንም ምርት የለም ማለታቸው መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ያዝን ካሉ ለቀዋል፤ ተሸሎታል ካሉ ሞቷል፤ ተፈርዶልናል ካሉ ተፈርዶባቸዋል፤ ወጣ ካሉ ወርዷል፤ … በዚህ ሥሌት 11 በመቶ የሚሉት ተረት ተረቱ የሀገሪቱ ዕድገት -11(ኔጌቲቭ 11) በመቶ መሆኑን በግምት መገንዘብ ይቻላል። ዱሮውንስ የ30 ብር ጤፍ ሁለት ሺ ብር ሊገባ ዳር ዳር እያለ፤ የሃምሣ ሣንቲሙ አንድ ሊትር የምግብ ዘይት 60 ብር ገብቶ… የምን 11 በመቶ ዕድገት ነው? ለማንቻውም እንደዚህ ናቸው ወያኔዎች እንግዲህ። የውሸትና የክህደት አምባሳደሮች።

ዐይን ያልገለጡ ቡችሎች እናታቸው ብትሞት እንዴት ሊያድጉ ይችላሉ? እንደምናውቀው መለስ ዜናዊ የወያኔዎች ሁለነገራቸው ነበር። እርግጥ ነው እርሱ ዐዋቂና አንባቢ ነበር። ይህን ማንም አይክድም። መለስ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ግሩም የዲፕሎማሲ ሰዎች፣ እጅግ ሊጠቅሙ ይችሉ ከነበሩ ብልሆች ዜጎች መካከል አንዱ ሊሆን በተቻለው ነበር - ፍጥረቱ ግራኝ ሆኖ አጥፍቶን ጠፋ እንጂ(በውነት እኮ - ሚስቱን ጎርፍ የወሰደበት ባል እንብላ ሲላት እንተኛ እያለች ስታውከው ኖራ ‹ሚስቴን ከወንዙ ወደታች ሳይሆን ከወንዙ ወደ ላይ ነው የምትፈልጓት› ብሎ ነገረኝነቷን ባደባባይ እንደመሰከረባት ጠማማ ሴት ሆኖ ነው መለስ የሞተው - ‹ሢሠራው ለዚህ› አሉ?)። ለዚህም ነው እኮ ሌሎችን ረግጦ እንደተናጋሪ እንስሳት በመቁጠር እርሱ ብቻ ሊገን የቻለው። በመለስ ዐዋቂነትና ነገር ጎንጓኝነት ማንም ሊከራከር አይገባም። ነገር ግን ዋናው ጥያቄ ማንን ጠቀመበት? የሚለው ነው። ሰይጣንም እኮ እጅግ ዐዋቂና በመልክም - የመለስን እንተወውና - ከመላዕክት ሁሉ የሚበልጥ አብረቅራቂ ነበር ይባላል። እምብዝም ስለት የገዛ አፎትን መቅደዱ የነበረ ሆነና ይሄውና የመለስ አንጎል ሰይጣናዊ ቀለም በዝቶበት ሀገሩን እንጦርጦስ አውርዶ ድርጅቱንም ትንሣኤ ለሌለው ሞት አጋልጦ ሞተ። አሁን ምንም ተባለ ምን መለስን የሚተካ ሰው ከወያኔው መንደር በፍጹም ሊኖር አይችልም። ይህም የሆነው በፈጣሪ ጣልቃ ገብነት ይመስለኛል - ካለሱ ባዶ ነበሩ - እሱም ተላላፊ ነው፤ እናም ከሞት ወደሞት ተላለፈ። በቁሙም አልኖረም። ሞቶም አይኖርም። የተሠራው የኛን ዕዳ ሊያስከፍል በመሆኑ እየገፈገፍን እንገናለን። አሁን ግን እንመለስ። የዕዳ ደብዳቤያችን እንዲቀደድ በርትተን እንጸልይ!

መንጫጫት ያለ ነው። እናታቸው የሞቱባቸው ጫጩቶችም ሆኑ የውሻ ቡችሎች መንጫጫታቸው ሲያንሳቸው ነው። ከቻሉና ዕድሉን ካገኙም አጠገባቸው የሚገኝን ምግብ አይለቁም፤ እስኪሞቱ ይበላሉ። የነጋበት ጅብም እንደዚሁ ነው። ያገኘውን እየጠራረገ ከቻለ ወደጎሬው ይዞ ይገባና ለማታ ግዳዩ ይሰማራል፤ ካልቻለም የያዘውን ይዞ ይጠፋል - ይሞታል። ስለዚህ በቀሪዎቹ ወያኔዎች ልቅ ንግግርም ሆነ ዕኩይ ድርጊት ብዙም ሳንጯጯህና ሳንደነጋገር መሥራት ያለብንን ነገር በብልሃት እንሥራ። በየሚናገሩት ጠያፍና ለዳፋ ንግግር ሁሉ ጊዜ ስናጠፋ ደስ ይላቸዋል። መናኛና ባለጌ ሰው ሰውን በመሳደብ ይረካል፤ መለስም እንዲሁ ነበር - ሰው ከቢሮው ገብቶ ሲወጣ እንደባለጌ ሕጻን ምላሱን የሚያወጣበት እስኪመስለኝ ድረስ በምናቤ እስለዋለሁ - መለስን። ከባለጌ ከዚህ በላይ እንጂ በታች አይጠበቅምና በነዘርፍጤ ‹አቦይ› ስብሃትና በመሀመድ የኑስ ብዙ አንናደድ፤ መናደዳችን ለተግባራዊ እንቅስቃሴያችን እንደማቀጣጠያ ሆኖ የሚያነሳሳን ከሆነ እሰዬው ይሁን ፣ ጥሩ ነው። ነገር ግን እነዚህ ጀምበራቸው የገባች ዋልጌዎች የአብሮነት ሕይወታችንን ሊያጠይሙና ከወንድሞቻችንም ጋር ሊያቀያይሙን አይገባምና ሰውነታቸውን ከደረጃ በታች አስቀምጠን ወቅቱ የሚጠብቅብንን የነጻነት ትግል በየፊናችንና በየምንችለው እናድርግ። ከእንግዲህ ወዲያ የዘረኝነት አባዜ ከፈጣሪ ተቆርጦ የወደቀ ይመስለኛልና በዚያ ረገድ ባንሞክረው ይሻለናል። …

የመለስ ልቅሶ እስካሁን ድረስ እንዲሀ መግነኑም የሚደንቅ አይደለም። በመሠረቱ እንደእውነቱ ከሆነ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ‹ተመርጦ› ሥልጣን ከያዘ በኋላ የሞተው ባለሥልጣን ስም በካህናትና በቤተሰብ ይጠራ እንደሆነ እንጂ እስከዚህን የዓለም መሣቂያና መሣለቂያ እስኪሆኑ ድረስ በስሙ ሊዘባበቱበት ባልተገባ ነበር - በውነት እርሱም እንዳያርፍ አለመላው ወደው ላይወዱት ነፍሱን እያስጨነቋት ነውና ወዳጅ ካላቸው ይምከራቸው፤ ይረፍበት። ሚዲያውም የኢትዮጵያ እንጂ የአንድ ሰው ሊያውም የሞተ ሰው አይደለምና አይጫወቱበት - ለ30 ሴከንድ ማስታወቂያ ኅያውና ሀገር ጠቃሚ ዜጎችን ስንትና ስንት እያስከፈሉ ለአንድ በሞት ለተሰናበተ ሰው እንዲህ ሃያ አራት ሰዓት መብከንከን የጤና አይደለምና እባካችሁን ወደ አቅላችሁ ተመለሱ በሏቸው። ያ ተመረጠ የተባለው አዲስ ‹ጠ/ሚኒስትር›ም ለሥልጣኑ ቀናኢ ባለመሆኑና የሞተን ሰው እንደወከለ ስለሚቆጥር እንጂ - በራስ መተማመን ብሎ ነገር ስለሌለው - እኔ እሱን ብሆን ከተሾምኩ በኋላ የዱሮውን ቢያነሱብኝ ማቄን ጨርቄን ሳልል ‹ከቆረባችሁበት ከዱሮ ሰውዬኣችሁ ጋር ገደል ልትገቡ ትችላላችሁ!› ብየ ውልቅ እል ነበር፤ የአሁኑ ሰውዬ ግን ይህን ሊያደርግ አይችልም - ወኔና ድፍረት የማጣት ጉዳይ ብቻም አይደለም - ከበፊቱኑ ‹ይህ ሥልጣን ለኔ የሚገባ ሳይሆን ጌቶቼ ሰው እስኪያፈላልጉ ድረስ በታዛዥነት ለማገልገል የገባሁበት ስለሆነ እንዲህ ዓይነት ቅብጠት ለኔ አይገባም› ብሎ የሚያምን ይመስለኛል - የምን ይመስለኛል ነው - ነው እንጂ! ሚስትህ ሞታ ሌላ ሚስት አግብተህ በአዲሲቷ ሚስትህ ፊት ነጋ ጠባ በዕንባ ብትታጠብ ምን ሊሰማት እንደሚችል አስበው። ባልሽ ሞቶ ተቀብሮ ሌላ ባል አግብተሸ ባገባሽው ባል ደረት ላይ ተለጥፈሽ የዱሮውን ባልሽን ስምና ዝና እያነሳሽ በዕንባ ብትታጠቢ ጥፊና እርግጫው በዘመናዊ አስተሳሰብ ቅኝት ተዋዝቶ ከድምር ሒሳቡ ቢቀነስልሽ የፍቺው ጥያቄ ግን ጎሕ ሳይቀድ እንደሚቀርብልሽ አትጠራጠሪ - ደግሞም በኢትዮጵያ መሬት። ስለዚህ እነዚህ ወያኔዎች ከሰው ሠራሽ ሕግም ከተፈጥሮ ሕግም ከፈጣሪ ሕግም ከሞራልም ከልምድና ተሞክሮም ብቻ ምን አለፋን ከሁሉም የዚህች ምድር ሕግጋትና ሥርዓቶች በእጅጉ ያፈነገጡ ለምንም ነገር ደንታ የሌላቸው አረማውያን ወይም አሕዛብ ናቸው ማለት እንችላለን። ለነዚህ ሰዎች ስም ማውጣትም አይቻልም። ደግነቱ ሁሉም አንድ በመሆናቸው የአንዳቸው ግማት ለሌላኛቸው አይሰማቸውም። ሙትቻዎች! 85 ሚሊዮኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ሰው ይተኩት? እነሱ በቁማቸው ቢሞቱ ሌላውም የሞተ መሰላቸው? ወይ ጊዜ!!

ይህን የሞተ ሥርዓት አለ እያሉና ያልተገባ ክብደት እየሰጡ የበሬውን ቆለጥ ስትከተል እንደዋለችው ሞኝ ቀበሮ መሆን ለበለጠ ጥፋት ይዳርጋል። ወያዎች ከሞቱ በኋላ የሚልሱት ነገር እንዳላቸውም መረዳት ተገቢ ነው። እባብ ከሞተ በኋላ ይነሳል ይባላል - በመርዝ አቀባዮቹ አማካይነት። አሁን ግን የወያኔ ሞት እውነት ስለሆነ ሁሉም ዜጋ መተባበርና መነሳት ያስፈልጋል። እርግጥ ነው - ፈጣሪ የዚህችን ሀገር የመንግሥት ዛብ የሚሰጠው ለተመሳሳይ ዘረኛና የኃይማኖት አክራሪ እንደማይሆን በፍጹም ልባችን እናምናለን። የዚህችን ሀገር የመንግሥት አመራር የሚረከቡት ከዘውገኝነትና ከኃይማኖታዊ ጽንፈኝነት የተላቀቁ፣ የሁሉንም እንደሁሉም ሆነው የሚያከብሩ፣ በኢትዮጵያዊነት የአንድነት ጥላ ሥር ብቻ የሚንቀሰቀሱና ጥላቻን በፍቅር ግለኝነትን በወል የተኩ ወገኖች እንደሚሆኑ እንጠብቃለን፤ እምነታችንም ነው። አለበለዚያ ብድር ሲመላለሱ ማደር ሰልችቶናልና በተመሳሳይ ቅኝት የሚመጣ በአድልዖ የተመረዘ አስተዳደር በአፍንጫችን ይውጣ።

እስካሁን እንደምንታዘበው የሕዝቡን ፍላጎት ለማጤን የሚተጉ ተቃዋሚዎች ከስንት አንድ ናቸው። ለዚህም ይመስላል በለስ እንዳይቀናቸውና በለመድነው የበሰበሰ ሥርዓት እንድንቆይ ፈጣሪ ምርጫው ሆኖ ያለው። ቆሻሻ ቆሻሻን ሊያጸዳ እንደማይችል መታወቅ አለበት - መጽሐፉም ‹ብዔል ዘቡል ብዔል ዘቡልን አያወጣም ይላል›። ሐጎስ ሄዶ ስንሻው ቢመጣና የሐጎስን መመሪያ ቀባብቶ ቢከተል ወይም ጎይቶም ቢሄድና ቶሎሣና ዘበርጋ ተተክተው በቀደመው ጠባብ መንገድ እየተጓዙ ተመሳሳይ ትርምስ እንፍጠር ቢሉ ሕዝቡ ቀርቶ ምድሪቱ አትቀበላቸውም፤ ይህ ዓይነቱ ነገር በእጅጉ ሰልችቶናል - ጋዝ ጋዝ ብሎናል። በቴዎድሮስ ካሳሁን የቅርብ ጊዜው የሙዚቃ ኮንሰርት ከሕዝቡ የተንጸባረቀውን ፍላጎት ማጠየን ይገባል። ፈጣሪ ደግሞ ልብንና ኩላሊትን ያያል፤ ይመረምራልም። በተመሳሳይ ቅኝት ለመዝፈን የአራት ኪሎን ቤተ መንግሥት የሚቀላውጥ ካለ ቁርጡን ይወቅ፤ ያ ዓይነቱ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ጎሣን ከጎሣ፣ ቋንቋ ከቋንቋ፣ ኃይማኖትን ከኃይማኖት እያናካሱና አንዱን ከሌላው እያባሉ በሥልጣን ላይ መቆየት ከእንግዲህ ሊታሰብ አይገባውም። ይህ የሚሆነው ግን ትክክለኛው የፈጣሪ ሰው ወደ መንበሩ መምጣት ከቻለ ነው። ያ እንዲሆን ደግሞ ከኛም ብዙ ይጠበቃል፤ ‹እግዚአብሔር ይመስገን›ና ‹አልሃምዱሊላሂ ረቢንአለሚን›ም ትልቅ ጦር ናቸው - ካወቅንበት!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፤ ሕዝቧንም ከአረመኔዎች ግርፋት ያድን። አሜን!!!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ