አማኑኤል ዘሰላም

መግቢያ

ከእስልምና ጉባዔ ምርጫ ዙሪያ፣ በወሎ ክፍለ ሃገር ፣ ሀገራ ከተማ በተነሳው ግጭት ሶስት ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸው እንዳለፈ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል። ምርጫው ከተደረገ ከበርካታ ቀናት በኋላ፣ በምርጫ በተሳተፉትና በምርጫ ባልተሳተፉት መካከል የተነሳውን ግጭት ለማብረድ ፖሊስ ጣልቃ እንደገባ የዘገበው ሪፖርተር፣ ከሞቱት ሰዎች መካከል አንዱ የፖሊስ አባል እንደሆነም ጠቅሷል።

ወደ ዝርዝር ሃተታዬ ከመሄዴ በፊት በተፈጠረው ግጭት የዜጎች ሕይወት በመጥፋቱ የተሰማኝን ሃዘኔታ እየገለጽኩ፣ ለሟች ቤተሰቦች «እግዚአብሄር ማጽናናቱን ይስጣቸው» እላለሁ። በቦታው የተፈጠረውን የሚያጣራ፣ ለደም መፋሰሱም ምክንያት የሆኑ ግለሰቦች ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያደርግ ገለልተኛ ኮሚሽን እንዲቋቋም ጥሪ አቀርባለሁ።

ኢካዴፍ የተሰኘው የፓልቶክ ክፍል ተገደሉ ያላቸውን የሁለት ሰዎች አስክሬን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ድህረ ገጹ ላይ ያሳፈረ ሲሆን፣ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ እንዲሁም በጀነራል ገልቺ የሚመራውና አስመራ የሚገኘው ኦነግ በሙስሊሞች ላይ ተፈጸመ ያሉትን ግድያዎች አውግዘዋል። «ገዢው ፓርቲ የዜጎችን የሃይማኖት ነጻነት እየረገጠ ነው» ሲሉም ሕዝቡ(ክርስቲያኑንም ጨምሮ) አገዛዙን እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል።

የግንቦት ሰባቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከኢሳት ጋር በዚሁ በእስልምና ጉዳዮች ዙሪያ ወደ አንድ ሰዓት የሚሆን ቃለ መጠይቅ አድርገዋል። የጉዳዩን ሴንሲቲቭነት፣ እኝህም የኢኮኖሚክስ ምሁር በበርካታ በውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያያውያን ዘንድ ያላቸውን ታዋቂነት በመረዳት፣ ቃለ መጠይቃቸውን አደመጥኩ።

ቃለ መጠይቃቸውን «የሙስሊሞች ጥያቄ የመብትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው። ወያኔ የዜጎችን የሃይማኖት ነጻነት እየረገጠ ነው። ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ደግፈው ወያኔን መታገል አለባቸው» በሚሉት አረፍተ ነገሮች ማጠቃለል ይቻላል።

አንድን ነገር ስንቃወም ምክንያት ሊኖረን ይገባል ባይ ነኝ። ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ይህን ያህል ሰፊ ሃተታ ሲሰጡን በሙስሊሞች አካባቢ ያለውን ችግር በሁሉም ማእዘናት ምን ያህል እንዳዩትና እንዳጠኑት አላውቅም።

በአገራችን ያለውን ችግር በሁለተኛው ክፍል ጽሁፌ የምመለስበት ይሆናል። በዚህ ክፍል ግን ጠቅላላ ሃሳቦችና ግንዛቤዎች እንዲኖረን፣ ከኢትዮጵያ ውጭ በሙስሊም ማህበረሰቡ አካባቢ ስላሉት አንዳንድ ሁኔታዎች ትንሽ ልበል።

ዋሃቢዝም/ሳላፊዝም

እስልምና አንድ ሆኖ፣ ሙስሊሞች ግን በአምልኮ ስርዓታቸው ላይ የተለያዩ አመለካከት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። እንደ አካባቢውና እንደ ባህሉም የተለያዩ ትምህርቶች አሉ። በኢራን፣ በባህሬን በኢራቅ፣ በሊባኖስ በካታር በመሳሰሉ አገሮች የሺሃ እስልምና ተከታዮች አሉ። ከሺሃዎች ውጭ ያሉት ሱኒዎች ይባላሉ። በአገራችን ኢትዮጵያ፣ በቱርክ፣ በግብጽ፣ በዮርዳኖች፣ በሳውዲ አረቢያ ፣ በሱዳን …ያሉት ሙስሊሞች ደግሞ በብዛት ሱኒዎች ናችው። በሱኒዎችም መካከል የአህበሽን አስተምሮ የሚከተሉ፣ ሱፊዎች፣ ሳላፊስቶች(ሌላ መጠሪያቸው ዋሃቢስቶች) …በመባልም አንዳንድ ልዩነቶች አሉ።

በርካታ የሱኒ እስልማና ምሁራን በእስልምና እምነት መሰረት፣ እራስን ለመከላከል ካልሆነ በቀር የሌላውን ሰው ሕይወት ማጥፋት እንደሚከለክል ያስተምራሉ። ከክርስቲያኖችና ሌሎች እምነቶች ጋር ተከባብረውን ተቻችለው የሚኖሩ ናቸው።

ነገር ግን በቁራን ሱራ(ምእራፍ) 59 ላይ ያሉ ሶስት ጥቅሶችን በጥሬው ለጥጦ በመተርጎም መሰረታዊ ከሆነው ሰላማዊ የእስልምና ትምህርት የወጣ አክራሪነት የሞላበት አስተምህሮ መስፋፋት ጀመረ። የዚህ አስተምርሆ ጠንሳሽ፣ በሳውዲ አረቢያ ይኖሩ የነበሩ፣ መሃመድ ኢብን አልዋህድ ዋሃብ የሚባሉ ሼክ ነበሩ።

በወቅቱ፣ አሁን ሳውዲ አረቢያ በምትባለው ሰፊ ግዛት፣ የተለያዩ መሳፍንቶች ፣ የተለያዩ የእስልምና አስተምህሮ ያላችው እንደ ሺያ ያሉ ሙስሊሞችም ነበሩ። ጸሎት ወደ አላህ ሳይሆን ወደ ቅዱሳን በተዘዋዋሪ መንገድ መደረጉ፣ በቅዱሳን ስም ሃውልቶች መሰረታቸውን፣ በሞቱ ሰዎች መቃብር ላይ መስኪዶች ቆመው በዚያ ሙስሊሙ መሰባሰቡን፣ የነብዩ መሃምድ ልደት መውሊድ መከበሩን … የመሳሰሉ፣ በሙስሊሞች ዘንድ ይታዩ የነበሩ፣ የተሳሳተና የተበረዘ የሚሏቸውን የአምልኮ ስርዓቶችን «ማጥራት ያስፈልጋል» በሚል ነበር ሼክ መሐመድ ኢብን አብደል ዋሃብ የተነሱት። (ዋህብ ከሚለው ስም ነው ዋሃቢዝም የሚለው ቃል የመጣው)

በ1744 ዓ.ም በሳውዲ የነበሩ መሐመድ ቢን ሳውድ የሚባሉ መሳፍንት፣ ከመሐመድ ኢብን አብደል ዋሂድ ጋር ትብብር በመመስረት፣ የመጀመሪያው የሳውዲ ንጉሳዊ አገዛዝን መሰረቱ። በአካባቢው የነበሩ፣ «ያልጠራ» እስልምና የነበራቸውን ወደ ትክክለኛ እስልምና ወደሚሉት ( ዋሃቢዝም) እንዲመጡ ተደረገ። ፈቃደኛ ያልሆኑት ተገደሉ።

በዋሃቢዝም መሰረት፣ ከላይ እንዳልኩት ሱራ 59 ያሉ ጥቅሶችን በጥሬውና በተሳሳተ መንገድ በመለጠጥ ፣ በምድር ላይ የሚኖር ማንኛው ሰው፣ የጠራ ሙስሊም መሆን አለበት። ክርስቲያን፣ አይሁድ፣ ወይንም ሙስሊም ሆኖ በትክክል የማያመልክ ሙስሊም (እንደ ሺሃ፣ ሱፊ፣ አህበሽ … የመሳሰሉ ) ቃሪፎች (መለወጥ ወይንም መጥፋት) እንዳለባቸው ተደርጎ መወሰድ ፣ «ሰው ሁሉ በሸሪያ እስላማዊ ሕግ መተዳደር አለበት። ሌላ አማራጭ የለም» የሚል አቋም መያዝ ጀመረ።

በአማርኛ የተጻፈ ቁራን፣ ለጊዜው ባለማግኘቴና ወደ አማርኛ ስተረጎም የጥቅሱን ትርጉም እንዳላላላ ካለኝ ፍላጎት የተነሳ፣ ከቁራን ሱራ 59 ከቁጥር 3 እስከ 5 ያለውን አንባቢያን በትንሹ ይረዱ ዘንድ እንደሚከተለው በእንግሊዘኛ አስፍሬዋለሁ፡

"59.3": And had it not been that Allah had decreed for them the exile, He would certainly have punished them in this world, and in the hereafter they shall have chastisement of the fire.

"59.4": That is because they acted in opposition to Allah and His Apostle, and whoever acts in opposition to Allah, then surely Allah is severe in retributing (evil).

"59.5": Whatever palm-tree you cut down or leave standing upon its roots, It is by Allah's command, and that He may abase the transgressors.

የሳውዲ አረቢያ አክራሪነትን የማስፋፋት እንቅስቃሴዎች

ሳውዲ አረቢያ ሁለት ግንዶች ነው ያሏት። አንደኛው ፖለቲካውን የሚቆጣጠሩት የሳውድ ቤተሰቦች ሲሆኑ ፣ ሁለተኛው ደግሞ የአብዱል ዋሃብን ግንድ ይዘው የመጡ፣ አል አሽ ሼክ የሚባሉት የሳኡዲ አረቢያን ኡላማ የሚቆጣጠሩት ናቸው። ኡላማ እንደ ከፍተኛ የእስልማና ፍርድ ቤት የሚታይና በእስልምና ጉዳዮች የበላይ አካል ነው። (በኦርቶዶክስ ቤተ ከርስቲያን ሲኖዶስ እንደሚባለው)

ዋሃቢስቶች፣ ላለፉት ሶስት መቶ አመታት፣ በሳውዲ አረቢያ የነበሩ ቢሆንም በስፋትና በብዛት በተለያዩ አገሮች መንቀሳቀስ የጀመሩት ግን ላለፉት አምሳ አመታት ነው። በተለይም በሳውዲ የሚገኘው ፔትሮ ዶላር በአብዛኛው፣ በቀጥታና ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጥቅም ላይ የሚውለው ዋሃቢዝምን ለማስፋፋት ነው።

በሳውዲ አረቢያ ባሉ 35% ትምህርት ቤቶች፣ የእስልምና እምነት ትምህርት በግዴታ ይሰጣል። ለዚህ ትምህርት እንዲጠቅም በሳውዲ መንግስት የትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጁ መጽሃፎች አሉ። ፍሮንት ላይን (Frontline) የተሰኘው የፕቢኤስ (PBS) ፕሮግራም፣ በነዚህ መጽሃፎች ዙሪያ ሰፊ ዝግጅት አቅርቦ ነበር። በሚከተለው ድህረ ገጽ መመልከት ትችላላችሁhttp://www.pbs.org/wgbh/pages/frontline/shows/saudi/etc/textbooks.html

ቤተ ክርስቲያናት በሙሉ ከአካባቢያችን መቃጠል አለበት ያሉት ሙፍቲመጽሃፍቶቹ የዋሃቢዝምን ትምህርት ያንጸባረቁ ናቸው። ዋሃቢስቶች ሰዎችን ለሁለት ይከፍሏቸዋል። አንደኛው «ትክክለኛ የእስልምና አምልኮ ያላቸው፣ የተመረጡ፣ ያሸነፉ» የሚሏቸው ሲሆኑ ሁለተኞቹ ደግሞ «ቃሪፎችና ሙሽራኮች» የሚሏቸው እንደ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶች እና ዋሃቢስቶች የማይደገፉንት እንደ መውሊድን ማክበር የመሳሰሉ ስርዓቶች የሚከተሉ ሌሎች ሙስሊሞችን ያካተተ ነው። የሌሎችን እምነት አክብሮ፣ ተስማምቶ የመኖር ነገር በነርሱ ዘንድ በፍጹም የማይታሰብ ነው።

ብዙዎች ይሄንን ላናውቅ እንችላለን። በሳውዲ አረቢያ፣ አንድ እንኳን ተገንብቶ የቆመ ቤተ ክርስቲያን የለም። ክርስቲያን ካለ መስለም አለበት። ሙስሊም የነበረ ክርስቲያ ከሆነ መገደል አለበት። (በቅርቡ በሳውዲ አረቢያ ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ሴቶች በቤታቸው ሲጸልዩ ተይዘው የደረሰባቸውን ችግር ሁላችንም የምናውቀው ነው)

በቅርቡ የሳውዲ አረቢያ ታላቁ ሙፍቲ (መንፈሳዊ መሪ) ሼክ አብዱል ሃዚዝ አል ሃሼክ፣ «በአካባቢያችን ያሉ ቤተ ክርስቲያናትን ማፍረስ ያስፈልጋል» ሲሉ በይፋ የዋሃቢስቶችንና የሳውዲን መንግስት አላማን በግልጽ አስቀምጠዋል። http://www.christianpost.com/news/saudis-top-religious-official-calls-for-destruction-of-all-churches-71506/

እንግዲህ ሳውዲዎች፣ ከሙፍቲው ንግግር በግልጽ እንደምንረዳው፣ አላማቸው አንድና አንድ ነው። ሁሉም ሰው ሙስሊም ዋሃቢስት ሆኖ እንዲጠራ፣ ሙስሊም ያልሆነ ደግሞ ሙስሊም እንዲሆን፣ ከዚያ ውጭ ያሉ እንዲጠፉ!

ዳር ፊትና፣ ዳር ሃርባ እና ዳር ሰላም

በምድር ላይ ያሉትን ቦታዎች በሙሉ ዋሃቢስቶች በሶስት ነው የሚከፍሏቸው። ዳር ፊትኒ፣ ዳር ሃርባ እና ዳር ሰላም ይሏቸዋል። ዳር ማለት ምድር ማለት ነው። ፊትኒ ማለት ፈተና ማለት ሲሆን፤ ሃርባ ማለት ጦርነት ማለት ነው።

ሙሉ ለሙሉ የጠሩ ሙስሊሞች (ዋሃቢስቶች) የሚኖሩባት አካባቢ ዳር ሰላም ይሉታል። ዋሃቢስቶች ማይኖሪቱ የሆኑባቸው፣ ለምሳሌ እንደ አውሮፓ፣ አሜሪካ ፣ በአገራችንም ክርስቲያኖች በብዛት የሚኖሩባቸው እንደ አንደ አዲስ አበባ ያሉ አካባቢዎችን ፣ የፈታና ምድሮች (ዳር ፊትኒ) ይሏቸዋል። በነዚህ ቦታዎች በፈተናና ውስጥ ተኩኖ፣ ዋሃቢዝምን ለማስፋፋት፣ ብዙ በመውለድም ማጆሪቲ ለመሆን መሞከር ትልቁ አላማቸው ነው። ማጆሪቲ እስኪሆኑ ድረስ በሰላም እንታገላለን ይላሉ። ነገር ግን ዋና አላማቸውና ታርጌታቸው ቀስ በቀስ የበላይነትን መጨበጥ ነው። ማጆሪቲ እንደሆኑና አቅም እንዳገኙ ጦር መመዘዙ አይቀሬ ነው።

ዋሃቢስቶቹ ማጆሪቲ የሆኑበትን ቦታዎች ፣ የጦርነት ምድር ወይንም ዳር ሃርባ ይሏቸዋል። ማጆሪቲ ስለሆኑ በዚያ ያሉ ማይኖሪቲዎችን (ሺያዎች፣ ሱፊዎች፣ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶች …) በሃይልና በጉልበት እውነትኛ ሙስሊም እንዲሆኑ አሊያም እንዲጠፉ ማድረግ፣ ቤተ ክርስቲያናትን ፣ ሙክራቦች፣ የሺሃና የሱፊዎች መስኪዶችን ማቃጠል፣ በአጭሩ ከሌላው ጋር ተቻችሎ ሳይሆን በሌሎች ላይ ጦርነት መግጠም ዋና ተግባራቸው ነው። በነዚህ ቢታዎች ያለምንም ማንገራገር እስላማዊ የሻሪያ ሕግ መዘርጋት አለበት።

ለምሳሌ በአገራችን አሸንዳቦ የሆነውን እንመልከት። በአብዛኛው ሙስሊም የሚኖርባት መንደር ናት። በዚያች መንደር ቤተ ክርስቲያናት ይመሰረታሉ። ዋሃቢስቶች «ዳር ሃርብ» በሚለው መርኃቸው መሰረት ቤተ ከርስቲያኑን በእሳት አቃጣሉ። ለምን እነርሱ በብዛት ያሉበት አገር እንዴት ተደረጎ ቤተ ከርስቲያን ይኖራል?

በአሸንዳቦ በአክራሪዎች የተቃጠለ ቤተ ክርስቲያን ግንባሯ በጥይት የተመታው ማላላበአሸንዳቦ በአክራሪዎች የተቃጠለ ቤተ ክርስቲያን ግንባሯ በጥይት የተመታው ማላላበርካታ ሙስሊሞች በሚኖሩበት የናይጄሪያ አካባቢ፣ ክርስቲያኖች የገና በዓል በሚያከብሩበት ጊዜ ዋሃቢስት አክራሪዎች ክርስቲያኑን ሕዝብ በቦምብ አጋዩት። በኢራቅ በቅርብ ጊዜ ውስጥ አንድ ዋሃቢስት በሺያ መስኪድ ውስጥ ገብቶ ራሱን አጥፍቶ፣ ብዙ ቺሃ ሙስሊሞች ገደለ። በፔሻዋር ፓኪስታን የ14 አመት ወጣት፣ ሴቶች መማር እንዳለባቸው በመናገሯ፣ እስልምናን አረከሽ ተብላ ግንባሯ ላይ በጥይት ተመታች። ይች ወጣት እግዚአብሄር ሕይወቷን አትርፎ፣ በአሁኑ ሰዓት በለንደን ሕክምና እየተከታተለች ነው። ዩሳፍዛይ ማላላ ትባላለች። በሳውዲ አረቢያ አንዲት ሴት ወደ ክርስትና በመቀየሯ፣ አክራሪ ዋሃቢስት አቧቷ ምላሷን በመቁረጥ ጀምሮ፣ በጭካኔ አረዳት። በግብጽ ቤተ ክርስቲያናት እየፈረሱ መስጊዶች እንዲሰሩ ማንም ማድረግ ሲችል፣ የግብጽ ኦርቶዶክ ቤተ ክርስቲያን ግን የፈረሱ ቤተ ክርስቲያናታቸውን እንኳን ለማደስ ፍቃድ መጠየቅ አለባቸው።

ይሄ ሁሉ የሚያሳየን ዋሃቢዝም፣ በ«ዳር ሃጋር» መርህ መሰረት ፣ ባለ በሌለ አቅም ሌሎች እምነቶችን የማጥፋት፣ ብቸና የጠራ የሚሉትን የእስልምና አክራሪነትን የማስፋፋት እንቅስቃሴ መሆኑን ነው።

ቴሌግራፍ ኢንዲያ የተሰኘ የሕንድ ሜዲያ ከሁለት አመታት በፊት አንድ ዜና በድህረ ገጹ ላይ አውጥቶ ነበር። በሕንድ፣ በሰሜን ቦምቤ በምትገኝ ካንዲቫሊ በምትባል ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩባት መንደር ወደ 1500 ሙስሊሞች ኢድ ባክሪ (አብርሃም ልጁን ይሳእቅን ለመሰዋት የተዘጋጀበትን ቀን ) ለማክበር ወደ መስኪድ ይመጣሉ። ፓንታዋዲ ከምትባል ሌላ ጎሮቤት ከተማ ወደ ሰባት መቶ የሚሆኑ በተለይም ወጣት አክራሪ ዋሃቢስቶች ቀድመው በቦታው በመድረስ፣ በጉልበትና በኃይል መስኪዱን ተቆጣጥረው የአካባቢ ሙስሊም እንዳይገቡ ያግዳሉ። ሙስሊሙ ማህበረሰብ በውጭ ሰግዶ ወደ ቤቱ ይመለሳል። በዚህ ሁኔታ ሰላማዊው ሙስሊም አፉን ይዞ፣ ፈርቶ በየቤቱ እንዲቀመጥ ሲደረግ፣ አክራሪዎቹ ግን ጥቂቶች ሆነው፣ ሙስሊሙን እንደሚወክሉ ተደርጎ መታየት ጀመሩ።

በኢትዮጵያ የተወሰኑ ሙስሊሞች የሚያነሱት ጥያቄ

«የሕዝበ ሙስሊሙን ወቅታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለማፈላለግ የተወከልኩ ኮሚቴ ነኝ፤ በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ሙስሊሞች በተፈረመ ፒቲሺን ውክልና አለኝ» የሚል ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ መሐመድ በሚባሉ ግለሰብ የሚመራ አንድ ኮሚቴ አለ። ይህ ኮሚቴ ማእከሉ አደርጎ የነበረው የአዋሊያን ኮሌጅ ነበር። ይህ ኮሚቴ ነው አሁን አለ የሚባለውን የሙስሊሞች እንቅስቃሴ የሚመራው። ሶስት ጥያቄዎችን ይዞ ነበር ይህ ኮሚቴ የተነሳው። (የኮሚቴው አባላት በአሁኑ ጊዜ እሥር ቤት ናቸው) ። የቀረቡት ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው፡

1. ሕዝበ ሙስሊሙ የመረጣቸው መሪዎች በመጅሊሱ እንዲቀመጡ

2. የአሕባሽ አስተምህሮ «ከእስልምና መሰረታዊ አስተምህሮ የወጣ ነው» በማለት በእስልምና ተቋማት አስተምህሮ እንዳይሰጥ

3. የአዋሊያ ኮሌጅ በቦርድ እንጂ በመጅሊሱ እንዳይመራ

ኮሚቴው ከመጅሊሱ ጋር ያለውን ችግር ይዞ የሄደው ወደ ፌደራል መንግስት የሃይማኖት ጉዳዮችን ወደ ሚመለከት መሥሪያ ቤት ነበር። የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴውንና ሕጋዊ የሙስሊሞች ምክር ቤት ልዩነቶችን ለማጥበብ በኢሕአዴግ ሸምጋይነት ውይይት ጀመሩ። ስለዚህን የችግሩ መጀመሪያ በኢሕአዴግና በሙስሊሙ መካከል ሳይሆን በሙስሊሞች መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ነው።

ኢሕአዴግ ላይ ያለኝ ችግር አለ። ኢሕአዴግ ብጥብጥና ረብሻ ከተፈጠረ ሕግና ስርአትን የማስጠበቅ ግዴታ አለበት። ነገር ግን በሃይማኖቶች ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ለመገላገል መሞከር አልነበረበትም። ሙስሊሞች ችግራቸውን እራሳቸው እንዲፈቱ፣ መፍታት ካልቻሉ ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት እንዲሄዱ መደረግ ነበረበት።

ከላይ በዘረዘርኳቸው የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሜቴ ባሰነሳቸው ጥያቄ፣ ከዚያም በኋላ በተፈጠሩ ክስተቶችና አህበሽ በተባለው አስተምህሮ ዙሪያ ፣ በስፋት በሚቀጥለው በክፍል ሁለት ጽሁፌ እመለስበታለሁ። እስከዚያው ግን አንባቢያን እራሳቸውን እንዲጠይቁ የምፈልጋቸው ቁልፍ ጥያቄዎች አሉ።

በአገራችን የተነሳው የሙስሊሙ እንቅስቃሴ የሳውዲ አረቢያ ሼኮች በቀጥታም ሆነ ከበስተጀርባ የሚመሩትና የሚደግፉት ነው ወይ? ከሆነ አገራችን ለትልቅ አደጋና አለመረጋጋት ውስጥ ሊከታት አይችልም ወይ? (ሳውዲዎች ከወዳጆቻቸው ግብጾች ጋራ ለኢትዮጵያ ጥሩ እንደማይስቡ መቼም መዘንጋት የለብንም) እንቅስቃሴው በሕንድ ካንዲቫሊ እንዳየነው፣ የአብዛኛው ሙስሊምን ፍቃድ ረግጦ፣ መስኪዶችን በኃይል በመቆጣጠር ሙስሊሙ ተሳሳተ ከሚባለው፣ በኢትዮጵያ መቻቻልን ከሚያስተምረው፣ ከተለመደው የእስልማና ትምህርት ሙስሊሞችን በኃይል የማጥራት፣ በሳውዲ አረቢያ ያለውን አይነት የአክራሪነት መንፈስ የማሰራጨት እንቅስቃሴ ቢሆንሽ? መሰረቱ ሃረር ውስጥ የሆነ፣ ግን በስፋት በሊባኖስና በሌሎች በርካታ የሙስሊም አገሮች የተስፋፋ ፣ የአህባሽ የእስልምና አስተምር በፍቃደኝነት ሙስሊሙ ቢማረው ምን ችግር አለ? ዋሃቢዝምስ የመጣው ከሳውዲ አክራሪዎች አይደለምን? ኢሕአዴግ እንደ እንድ መንግስት በሌሎች አገሮች ያሉ የአክራሪነት ችግሮች እንዳይከሰቱ፣ ሰላምና መረጋገት እንዲኖር የማድረግ ሃላፊነትስ የለበትምን?

በሚቀጥለው ጽሁፍ እስክንገናኝ ለሁላችንም ቸር ይግጠመን !

አማኑኤል ዘሰላም

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ