የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ክፍል 2 - ምላሽ ለዶ/ር ብርሃኑ ነጋ
አማኑኤል ዘሰላም
መግቢያ
አንባቢያን ሰፊ ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ፣ የሙስሊም አክራሪነት እንዴትና ከየት እንደተጀመረ፣ በአሁኑ ወቅትም በአለማችን ምን አይነት ችግር እያስከተለ እንዳለ ለማሳየት ሞክሪያለሁ። በተለይም ሳውዲ አረቢያ፣ ካላት የነዳጅ ክምችት የተነሳ በምታገኘው ፔትሮ ዶላር፣ ምን ያህል፣ ለሰብዓዊነት ክብር የሌለውን አክራሪነት ለማስፋፋት የምትጫወተው አሉታዊና ሰይጣናዊ ሚና፣ የማያሻሙ መረጃዎች በማስቀመጥ ግንዛቤ እንዲኖር ለማድረግ ሞክሪያለሁ። በክፍል ሁለት ትኩረቴን በውጭ አገራት ካሉ የአክራሪነት እንቅስቃሴዎች አንስቼ በአገራችን እየታዩት ወዳሉት የሙስሊም እንቅስቃሴዎች እዞራለሁ።
ኦፌሴላዊ በሆነው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሰረት ሙስሊም ማህበረሰብ ወደ 36 ሚሊዮን ይጠጋል። በአኗር መስኪድ፣ በአዋሊያ ኮሌጅ እንዲሁም በተወሰኑ ሌሎች ቦታዎች የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ሙስሊሙን በሙሉ ይወክላሉ ብሎ መናገር ትንሽ ያስቸግራል። በመሆኑም የሙስሊሞች ተቃውሞ ስል፣ የተወሰኑ ሙስሊሞችን ተቃውሞ ማለቴ እንጂ፣ ጠቅላላ የሙስሊሙ ማህበረሰብን ተቃውሞ ማለቴ እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ።
ኢሕአዴግና ሙስሊሞች
”ኢሕአዴግ መስኪዶችን ዘግቶ የዜጎችን የእምነት ነጻነት እየተጋፋ ነው” የሚል ክስ የሚያቀርቡ አሉ። በአገራችን ኢትዮጵያ ከነበሩት መንግስታት በላይ፣ የሙስሊሙ ማህበረሰብ መብት በስፋት እንዲከበር ያደረገ፣ እንደ ኢሕአዴግ መንግስት ያለ ይኖራል ብዬ አላስብም። ከተገነቡት አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ሲነጻጸሩ፣ የተሰሩ አዳዲስ መስኪዶች ቁጥር እጅግ በጣም ይበልጣል። በተለያዩ የእስልምና አመት በዓሎች ወቅትም፣ ሙስሊሙ፣ በታላቁ ስታዲየምና በመሳሰሉ ሰፋፊ ቦታዎች በነጻናትና ያለ ገደብ፣ ተሰባስቦ አምልኮውን እያደረገ ነው። በመስኪዶች ጸሎት እንዳያደርግ የተከለከለበትም ሁኔታ እንዳለ በመረጃ የሚያሳዩ ዘገባዎች አላነበብንም። (መስኪዶች ተቃውሞ የሚሰማባቸውም ቢሆኑም አልተዘጉም)
መረጃዎች እንደሚያሳዩት አሁን ያለው ችግር፣ ኢሕአዴግ የሃይማኖትን መብት በመርገጡ የመጣ ችግር ሳይሆን፣ በሙስሊሞች መካከል የተፈጠረ አለመስማማት፣ ያመጣው ችግር እንደሆነ ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜ በሙስሊሙ መካከል ችግር እንዳለ የተሰማው የአዋሊያ ኮሌጅ ተማሪዎች ተቃውሞ ባሰሙበት ወቅት ነበር። መጅሊሱ (ከፍተኛ የእስልምና ጉባኤ ምክር ቤት - በኦርቶዶክ ሲኖዶስ እንደሚባለው) ”ከሳውዲ የመጣ የዋሃቢዝም አክራሪነት መንፈስ እየበዛ ነው” በሚል በምርጫና በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ለዘብተኛና ሰላማዊ የሆኑ የእስልምና አስተምህሮዎች በአዋሊያ እንዲሰጡ ወሰነ።
የመጅሊሱን ውሳኔ ጥቂት ተማሪዎች ተቃወሙ። በሙስሊሞች መካከል ችግር እንዳለ ያኔ በይፋ አወቅን። የተነሳውን የተማሪዎች ረብሻ ለማረጋጋት ፖሊስ ጣልቃ ገባ። ጥቂት ሳምንታት እንዳለፉ ”ብዙ ሙስሊሞችን እወክላለሁ፣ የብዙ ሙስሊሞች ፊርማ አለኝ” የሚል ኮሚቴ ተቋቋመ። ኮሚቴው ጥያቄዎች ይዞ ወደ መንግስት ሄደ፡
በኮሚቴው የቀረቡ ጥያቄዎች የሚከተሉት ነበሩ፡
1. ሕዝበ ሙስሊሙ የመረጣቸው መሪዎች በመጅሊሱ እንዲቀመጡ
2. የአሕባሽ አስተምህሮ ”ከእስልምና መሰረታዊ አስተምህሮ የወጣ ነው” በማለት በእስልምና ተቋማት አስተምህሮ እንዳይሰጥ
3. የአዋሊያ ኮሌጅ በቦርድ እንጂ በመጅሊሱ እንዳይመራ
እንግዲህ አንድ ነገር ልብ ልንል ያስፈልጋል። ከጅምሩ አለመስማማቱ፣ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ በሙስሊሞች በራሳቸው መካከል የተፈጠረ እንጂ፣ በመንግስትና በሙስሊሙ መካከል እንዳልነበረ ነው። የሙስሊሙን ተቃዋሞ እመራለሁ የሚለውም ኮሚቴ ጥያቄዎቹን ይዞ የሄደውም፣ ወደ መንግስት ነበር።
”መጅሊሱ ብቃት የለውም፣ እንደገና የመጅሊስ ምርጫ መደረግ አለበት” ለሚለው የመጀመሪያው የኮሚቴው ጥያቄ መጅሊሱ ተስማማ። ”የአህበሽ አስተምሮ በማናቸውም የእስልማና ተቋማት መሰጠት የለበትም” የሚለው የኮሚቴው ሁለተኛ ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ። ሙስሊሙ በግዴታ እንዲማር እስካልተደረገ ድረስ ”መማር የሚፈልግ፣ የመማር መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል” የሚል ውስኔ ተሰጠ። የአዋሊያ ኮሌጅን በተመለከተ፣ መጅሊሲ የበላይ ጠባቂ ሆኖ በቦርድ እንዲተዳደር ስምምነት ተደረሰ።
ኮሚቴውና የሚደግፏቸው ሙስሊሞች በዚህ አልተደሰቱም። ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑ ጥሩ ሆኖ ሳለ፣ ምርጫው የት መደረግ አለበት በሚለው ላይ አለመስማማት ተፈጠረ። የአህበሽ አስተምህሮ፣ በፍላጎትም እንኳ መሰጠት የለበትም የሚል አቋም ተያዘ። በጠረቤዛ ዙሪያ ማግኘት ያልተቻለውን፣ በሰላማዊ ተቃውሞ ለማግኘት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መሰማት ጀመሩ። ከዚያም ጋር በተገናኘ የኮሚቴው አንዳንድ አባላት ታሰሩ። ለውይይትና ለምክክር ጊዜ ሰጥቶ፣ ሁሉም አሸናፊ የሆኑበትን ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ፣ ብዙዎች ተቃውሞ እያሰሙም፣ የመጅሊሱ ምርጫ ቀጠለ።
የአህበሽ አስተምሮን በተመለከተ
በአህበሽ አስተምሮ ዙሪያ ቅር የተሰኙ የሙስሊም ተቃዋሚዎች ”የአህበሽ አስተምህሮ በግድ እንድንማር እየተደረግን ነው” በሚል መጅሊሱን ብቻ ሳይሆን ኢሕዴግን ከሰሱ። አህበሽን የሚያወግዙ የተለያዩ ጽሁፎች በየድህረ ገጹ ተለቀቁ። አህበሽ ጸረ-እስልምና፣ ከውጭ የመጣ መጤ ትምህርት እንደሆነም በስፋት መነገር ጀመረ።
እስልምና አንድ ሆኖ፣ በአምልኮ ስርዓት እንዲሁም በቁራን ውስጥ ባሉ አንዳንድ ሱራዎችም(ምእራፎች) አተረጓጎም ዙሪያ የሚለያዩ የተለያዩ አስተምህሮዎች አሉ።
ለምሳሌ የዋሃቢዝም አስተምህሮን ካየን፣ በመጀመሪያው ክፍል ጽሁፌ በስፋት ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ በአገራችን የተለመደው የመውሊድ ባእል እንዳይከበር ይከለክላል። ሴቶች በሕይወት እያሉ እንዲገነዙ ያስገድዳል። እስላማዊ የሻሪያ መንግስት መቋቋም አለበት ይላል።
ወደ አህበሽ አስተምህሮ ስንሄድ መውሊድን ማክበር አይከለክልም፤ ሴቶች ሙሉ ለሙሉ በሕይወት እንዲገነዙ አያዝም፣ ሙስሊሙ ከሌሎች አምነቶች ጋር ተከባብሮ መኖር አለበት ይላል፤ የእስላማዊ ሻሪያ መንግስትም እንዲቋቋም አላማው አያደርግም።
የአህበሽ አስተምሮን የጀመሩት የሐረር ተወላጅ የሆኑት ኢትዮጵያዊው አብዱላ አል ሃሪሪ ናቸው። ስለዚህ አህበሽ ስሙ እንደሚገልጸው ከሃበሻ (ኢትዮጵያ) የተነሳ አስተምህሮ ነው። በአገራችን ያሉ ሙስሊሞች ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በሰላም ተከባብረው የኖሩ እንደመሆናቸው፣ ያንን የመቻቻልና የመከባበርን መንፈስ ያንጸባረቀ እንደ ሊባኖስ ባሉ፣ በርካታ እምነቶች ባሉበት አገር፣ በስፋት ተቀባይነት ያለው፣ በተለይም ከዋሃቢዝም በተቃራኒው የቆመ አስተምህሮ ነው።
ከሳውዲ ለመጣው አክራሪ የዋሃቢዝም አስተምህሮ፣ ተቃውሞ ከሚያሰሙ የሙስሊም ወገኖች አካባቢ፣ ብዙ ተቃውሞ አንሰማም። ነገር ግን መሰረቱ ከኢትዮጵያ የሆነውን (ወይንም በኢትዮጵያዊ የተጀመረ) የአህበሽን አስተምሮ ላይ ይሄን ያህል ጠንካራ ተቃውሞ ለምን ሊኖራቸው እንደቻለ ግን በራሱ የሚያነጋግር ነው።
እንደዚያም ሆነ፣ የአህበሽን አስተምህሮ አለመቀበል የማንም ሙስሊም ሙሉ መብት እንደሆነ አምናለሁ። ዜጎች እንኳን የአንድ እስልምና አስተምህሮ አለመቀበል ቀርቶ፣ ከእስልማና ወደ ክርስትና፣ ወይንም ወደ ሌላ እምነት የመሄድ ሙሉ መብት አላቸው። ስለዚህ ኮሚቴው ”የአህበሽ አስተምህሮን አንፈልግም” ማለቱ ሊያስወቅሰውና ሊያስኮንነው፣ ሽብርተኛም ሊያስብለው አይገባም።
ነገር ግን ኮሚቴው ”እኛ የማንፈልገው ትምህርት ስለሆነ፣ ሌሎች ቢፈልጉም መማር የለባቸውም ” በማለት ማክረሩ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም።
ዋሃቢዝም የሰዎችን ምርጫ አያከብረም። አንድ ሙስሊም ክርስቲያን ከሆነ መገደል አለበት ነው የሚለው። ከዋሃቢዝም ውጭ ሌላ የእስልምና አስተምህሮ በምንም አይነት መሰጠት የለበትም ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ሌላ አስተምህሮ የሚቀበሉትን ጸረ-አላህ እና ጸረ-እስልምና አድርገው በመቁጠር እንዲጠፉ ያስተምራል። ታዲያ በአህበሽ ላይ ይሄን አይነት ጠንካራ አቋም መያዝ፣ በዋሃቢዝም የአክራሪነት መንፈስ መያዝ ተደርጎ በአንዳንዶች ቢወስድ ስሀትት ነው ሊባል ይችላልን?
አገር የጋራ ሃይማኖት የግል ነው። ሌላውን እስካልነካ ድረስ፣ ማንም የፈለገውን መማር፣ የፈለገውን መቀበል፣ የፈለገውን መምረጥ ይችላል። አህበሽ መማር የፈለገ እንዳይማር ማንም ሊከለክለው አይገባም። መማር የማይፈልግ ደግሞ በግድ እንዲማር መገደድ የለበትም።
ያሉት መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ማንም ሙስሊም በግዴታ አህበሽን ሆነ ሌላ አስተምሮ የተማረበት ሁኔታ ያለ አይመስለኝም። በኢሕአዴግ ሸምጋይነት በመጅሊሱና በኪሚቴው መካከል በተደረገው ውይይት ወቅትም ግልጽ የተደረገው፣ የአህበሽ አስተምህሮ በፍቃደኝነት እንዲሰጥ ነው። ስለዚህም ”በግድ መጤ ኃይማኖት እንድንማር እየተደረግን ነው” የሚባለው ክስ ትንሽ ውሃ የሚቋጥር አይመስለኝም።
መጅሊሱ እንዴት ይመረጥ?
ሌላው የአለመስማማት ምክንያት የሆነው የመጅሊሱ ምርጫ ነው። ”ምርጫው እንዴት ይካሄድ ?” የሚለው ትልቅ ውዝግብን አስነሳ። በየቀበሌውና በየወረዳው ሙስሊሞች ተወካዮቻቸውን እንዲመርጡ፣ መጅሊሱ ሲወስን፣ የሙስሊም ተቃዋሚዎችን የሚመራው ኮሚቴ ”ምርጫው መደረግ ያለበት በመስኪዶቹ ውስጥ ነው” የሚል አቋም ያዘ። ”ምርጫችን በመስጊዳችን” የሚል መፈክርም መስማት የጀመርነው በዚህ ምክንያት ነው።
ምርጫው በመስኪዶች ከተደረገ፣ በዋና ዋና መስኪዶች በብዛት ይገኛሉ የሚባሉት ዋሃቢስቶች መጅሊሱን የመቆጣጠር አቅም ይኖራቸዋል። በየወረዳው ከተደረገ ደግሞ፣ በአብዛኛው ሱፊ የሆነው ለዘብተኛው ሙስሊም መጅሊሱን ሊቆጣጠር ነው። ፍጥጫው እንግዲህ እዚህ ላይ ነው።
መጅሊሱ በየወረዳው ምርጫ ይደረግ ብሎ ሲወስን ”ከመስኪድ በጣም ርቀው ወይንም መስኪዶች የሌሉባቸው ቦታዎች የሚኖሩ፣ በተለያዩ ምክንያቶች መስኪድ መምጣት የማይችሉ (ወራቸው የደረሰ ሴቶች ….) ሙስሊሞች በምርጫው እንዲሳተፉ ያደርጋል” በማለት ነበር።
ሙስሊም ተቃዋሚዎች ግን ”በየወረዳው ከሆነ የምርጫ ማጭበርበር ይኖራል። በመስኪዶች ግን፣ ምርጫውን በቅርበት ለመከታተል ይቀላል። ስለዚህም ምርጫው በመስኪድ መሆን አለበት” በሚለው አቋማቸው ጸኑ። በአዋሊያ ኮሌጅ፣ በአኗር መስኪድ አካባቢ ሰላማዊ ተቃውሞዎቻቸውንም ማሰማት ጀመሩ። ከመስኪድ በመውጣት፣ በመርካቶ አካባቢ ጩኸታቸውን ለማሰማት በሞከሩበት ጊዜ፣ የፌደራል ፖሊስ ጣልቃ ገባ። የኮሚቴ መሪዎችም በብዛት ተይዘው ታሰሩ።
ኢሕአዴግ በመጅሊሱ የርሱ ሰዎች እንዲመረጡ ሊያደርግ አይችልም የሚል አስተያየት የለኝም። እንደተባለው ምርጫው ሊጭበረበርም ይችላል። ነገር ግን በመስኪድ መደረጉ ደግሞ፣ የባሰ ጸረ-ዴሞክራሲያዊና የአብዛኛውን ሙስሊም ፍላጎት ያላንጸባረቀ ምርጫ የሚሆንበትን ሁኔታ ይፈጥራል። በመስኪድ አካባቢ ያሉ ጥቂቶች፣ አብዛኛው ሙስሊም ሳይመርጣቸው፣ መጅሊሲን በአቋራጭ ሊቆጣጠሩ ይችላሉ። በተለይም ደግሞ ዋሃቢስቶች መጅሊሱን ከተቆጣጠሩ፣ በሳውዲ አረቢያ እንደምናየው፣ በእስላማዊ ተቋማት በሙሉ፣ እንደ ሳውዲ አረቢያ ባሉ አገራት በስፋት የሚሰጠው አይነት የአክራሪነት ትምህርት ሊስፋፋ ይችላል። ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሰላማዊ የሆኑ፣ በመቻቻልና በመከባበር ላይ ያተኮሩ የእስልምና አስተምህርዎች እንዳያገኝ፣ እርስ በርሱ የበለጠ እንዲከፋፈል፣ ከሌሎች እምነቶች ተከታይች ጋር ፊት ለፊት እንዲላተም ያደርጋል። ይህ ደግሞ የአገራችንን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው።
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እንዳሉት፣ አሁን ያለው ችግር የጥቂት ሙስሊሞች ተቃውሞ የመብት ጥያቄ ሳይሆን የሌላውን መብት የመርገጥ ጥያቄ ነው። አህበሽ በግድ ተማሩ አልተባሉም። ነገር ግን መማር የሚፈልግ ሌላ ሙስሊም ”አህበሽን መማር የለበትም ነው” እያትባለ ያለው። በወረዳቸው መመረጥ መምረጥ ይቻላሉ። ያንን መብታቸውን ማንም አልነፈጋቸውም። ምርጫው እንዳይጭበረበር ከተፈለገ ደግሞ፣ ምርጫው ትክለኛ የሚሆንበትን ሃሳቦች በማቅረብ በጋራ መስራት ሲኖርባቸው፣ ምርጫው በመስኪድ ካልሆነ በሚል፣ በተለያዩ ምክንያቶች መስኪድ መምጣት የማይችለው ሙስሊም እንዳይመርጥ እያከላከሉት ነው። ይህ ደግሞ ለማንም የሚበጅ አይደለም።
የመፍትሄ ሃሳቦች
እንግዲህ ያለውን ችግር ባሉኝ ግንዛቤዎች በዚህ ሁኔታ ለማሳየት ከሞከርኩ፣ ከዚህ ቀጥሎ እንዴት መቀጠል ያስፈልጋል በሚለው ጥያቄ ዙሪያ አንዳንድ ሃሳቦችን ላቅርብ።
እንደሚታወቀው በርካታ ሙስሊሞች እየታሰሩ ነው። ችግሮች እየለዘቡ ሳይሆን እየከረሩ ነው የመጡት። የሚያሳዝነው ደግሞ ይሄን ችግር ለማስፋት የሚሞክሩ ውጭ አገር የሚቀመጡብ አንዳንድ የፖለቲካ ደርጅቶችና ሜዲያዎች መኖራቸው ነው።
ሙስሊሙ ማህበረሰብ መረዳት የሚኖርበት፣ እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ያሉ የፖለቲካ መሪዎች፣ የሙስሊሙን ጉዳይ እያነሱ፣ እየለጠጡ የሚያወሩት፣ የሙስሊሙን እንቅስቃሴ ለፖለቲካ ፍጆታ ሊጠቀሙበት ስለፈለጉ እንጂ፣ ሙስሊሙን ለመጥቀም አስበው እንዳልሆነ ነው። ትግሉን ወደፊት የሚወስድ፣ የሚያንጽ፣ የሚገነባ፣ ሰላምና እርቅን የሚያመጣ፣ የሰለጠነ፣ በእውነት ላይ የተመሰረተ፣ ተስፋ የሚሰጥ ፖለቲካ ሲያራምዱ አናያቸውም። ለችግሮች መፍትሄ ሲያስቀመጡ አናያቸውም። ፖለቲካቸው ጨለምተኝነት የሞላባትና መካረርን የሚያመጣ ነው።
ሙስሊሙን ለመጥቀም የሚፈልግ አካል፣ በዋናነት ይዞ የሚንቀሳቀሰው አጀንዳ፣ ”በሙስሊሙ አካባቢ ያለው ችግር፣ በሙስሊሙ ማህበረሰብ እራሱ በሰላም ይፈታ” በሚለው የሰላም አጀንዳ ላይ ነው።
ሙስሊም አይደለሁም። የክርስትና እምነት ተከታይ ነኝ። ክርስቲያኖች የሙስሊሙን እንቅስቃሴ እንዲደግፉ የሚጠይቅ ጥሪ ስለቀረበ ነው አስተያየቴን ለመስጠት ችየተነሳሁት። እኔ በሙስሊሞች ቦታ ብሆን፣ የምፈልገውና የምመኘው፣ ነገሮች እንዲከሩ ሳይሆን እንዲለዝቡ፣ ችግሮችም በሰላምና በውይይት እንዲፈቱ ነው። በመሆኑም ሊጠቅሙ ይችላሉ የምላቸውን አንዳንድ ምክሮች እንደሚከተሉት በትህትና አቀርባለሁ፡
1. በየአርቡ፣ የጸሎት ቦታ በሆኑ መስጊዶች፣ ተቃውሞዎች ማሰማቱ፣ የዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብታቸው ቢሆንም፣ ምን ጥቅም ሊያመጣ እንደሚችል ግን አላውቅም። ይልቅስ ቢጫ ወረቀት ሳይሆን ነጭ ወረቀት በማውለብለብ፣ በእርጋታና በቅንነት ከመጅሊሱ ጋር መነጋገሩ አይበጅምን? በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ቤተ ክርስቲያን፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ለመጠበቅ፣ አባቶች በቅንነት ላይ ያተኮረ ውይይት አያደረጉ ነው። ይህ አይነቱ ቅንነት ያለበት ምክክርና ውይይት ነው ሙስሊሞች ማድረግ ያለባቸው የሚመስለኝ። ”እኛ ያልነው ካልሆነ” የሚል ያከረረ አቋም ብዙም ሊያስኬድ አይችልም። በሳውዲ አረቢያ ሊሰራ ይችላል። በኢትዮጵያ ግን አይሰራም።
2. መስኪዶች የጸሎት ቦታዎች ናቸው። ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ከጸሎት ቤትነት ወደ ተቃውሞ ማድረጊያ ቦታነት እየተቀየሩ ነው። ይህ ከቀጠለ፣ ወደፊት የሰፋ ችግር ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም ለመስኪዶች ሊሰጥ የሚገባው ክብርና ጥንቃቄ ሊሰጥ ይገባል ባይ ነኝ።
3. ከሳውዲ አረቢያ ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ በብዙ ገንዘብ እየተደገፉ፣ የዋሃቢስት አክራሪነት ትምህርቶችን ለማስፋፋት የሚሰሩ ብዙዎች አሉ። እነዚህ አክራሪነትን ሲያስፋፉ የነበሩ ወገኖች፣ ከሞላ ጎደል፣ ላለፉት ሃያ አመታት፣ የኢሕአዴግን መንግስት ቡራኬ አግኘተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው። የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባሌበትን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በመሆኑም ለአክራሪነት መስፋፋት ኢሕአዴግ በተወሰነ ደረጃ ሃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል እላለሁ።
4. በመስኪዶች ሰላማዊ ተቃውሞ ማሰማት፣ የመጅሊስ አመራሮች እንዲለወጡ መጠየቅ ”ሽብርተኛ” ሊያሰኝ አይገባም። በመሆኑም ከሳውዲ አረቢያ ጋር ግንኙነት የሌላቸው፣ የዋሃቢዝም አክራሪነትን ማስፋፋታቸውን የሚያሳይ መረጃ ያልተገኘባቸው፣ በአዋሊያና በመስኪዶች ሕገ መንግስቱ የሚፈቅድላቸውን ተቃውሞ በማሰማታቸው ብቻ የታሰሩ፣ ሰላማዊ ሙስሊም ወገኖቻችን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ መፈታት አለባቸው። እነርሱን በማሰር የሚገኝ አንዳች ጥቅም የለም። ዜጎች ተቃውሞ ስላሰሙ የሚታሰሩበት አሰራር መቆም አለበት። ኢሕአዴግ በዚህ አንጻር ከኃይል እርምጃዎች ተቆጥቦ፣ ማስተዋል ያለበት እርምጃ እንዲወስድ እመክራለሁ።
5. የኢሕአዴግ መንግስት ለአመታት በሳውዲ አረቢያ የተደገፈ አክራሪነት ሲያስፋፋ ዝም ማለቱ ስህተት እንደነበረ ተረድቶ፣ ከዚህ በኋላ በተለያዩ ስሞች፣ ከሳውዲ አረቢያ የሚመጡ ገንዘቦችና እርዳታዎች ላይ የጠበቀ ክትትል ሊያደርግ ይገባዋል። ሳውዲዎች፣ ግብጾች የመሳሰሉ አገራት፣ ኢትዮጵያውያን ተከባብረን፣ ተዋደን፣ ተቻችለን በሰላምና በፍቅር እንድንኖት አይፈልጉም። ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው። በመሆኑም ውስጥ ውስጡን ኢትዮጵያን እንዲያደሙ ሊፈቀድላቸው አይገባም።
6. ኢሕአዴግ፣ መጀመሪያውኑ ሕግና ስርዓትን ከማስጠበቅ ውጭ፣ በመጅሊሱና በሙስሊም ተቃውሚዎች መካከል፣ ለማስታረቅም ቢሆን፣ መግባት አልነበረበትም። እነርሱ እራሳቸው ከተሰማሙ መልካም፣ ካልሆነ ግን ”ፍርድ ቤት ሄዳችሁ በዚያ ችግራችሁን ፍቱ” ብሎ፣ አርፎ መቀመጥ ነበረበት። ስለሆነም መንግስት ከሙስሊሞች ጉዳይ እራሱን ሙሉ ለሙሉ ማውጣት አለበት።
7. እርግጠኛ ነኝ የተከበሩ፣ በሁሉም ተሰሚነት ያላቸው፣ ሙስሊም አባቶች ይኖራሉ። ከነዚህ አባቶች የተወጣጣ አንድ የሙስሊም አስታራቂ ኮሚቴ ይቋቋም። በመጅሊሱና በሙስሊም ተቃዋሚውች መካከል ያሉት ችግሮች፣ ሁሉም አሸናፊ በሆኑበት፣ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት መንገድ ለመፍታት ይንቀሳቀሱ።
8. ክርስቲያኑ ማህበረሰብ በሙስሊሙች ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት መሞከር የለበትም። ሙስሊሞች የራሳቸውን ችግር እራሳቸው ነው የሚያውቁት። እኛ ከዳር ሆነን ብዙ በማናውቀውና በማንረዳው ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብተን፣ አንዱ ቡድን ደግፈን ሌላውን የምንቃወምበት ምንም ምክንያት የለም። በመሆኑም እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ያሉ ጥቂቶች፣ ክርስቲያኑ እንዲነሳ ያቀረቡት ጥሪ፣ ”ቦታ ሊሰጠው አይገባም። ጎጂም ነው” እላለሁ።
አማኑኤል ዘሰላም
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



