ሰሎሞን ተሰማ ጂ.

"... ዛሬም ከ55 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን አባቶች፣ የዛሬ ሃያ ዓመት የፈፀሙትን ስህተት ለማረም ወኔ ማጣታቸው ያስደንቃል። ታሪክ ጠቅሰን፣ የዛሬ 55 ዓመት የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን መሪዎች እንዴት በዜግነት ባዕድ ለሆኑት፤ ነገር ግን በኃይማኖት መሪነታቸው ለሚያከብሯቸው ለብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብ እንደተከራከሩና ታሪክም እንደሰሩ እናስታውሳችሁ። ..."

 

 

ባለቅኔው ክፍሌ ዮሃንስ ከዘመናት በፊት፣ “ወከመ ለሰማይ ኢንርአይ ሥነ ግዘፉ፤ ትንንያ ካልአን በክንፉ!” እንዳለው ነው። እውነትነት አለው። ስለ”እውነትም” ነው የተቀኘው። (ትርጓሜውም እንዲህ ነው፤ እውነትን እንኳንና ከምድር በላይ ሊያስርዋት፣ ከምድር ከርስም ውስጥ ቢቀብሯት፣ በድንጋይ መዝጊያ ተዘግቶባት፣ በጠንካራ የብረት መዝጊያም ጭምር እንደገንዘብ ቢከዝኗትና በትጉኋን ዘበኞችም ቢያስጠብቋት፣ “እውነት” መቼውንም የሚሰማ ድምጽ አላት። ከትልቁ የተራራ ሕንፃና ዋሻ ውስጥ ቢያሽጉባትም ሆነ፣ ከጥልቁ ውቅያኖስ ውስጥ ቢቀብሯት፣ በድንጋይ መዝጊያም ቢከረችሟት፣ ከድቅድቁ ዋሻ ውስጥም አዕላፍ ሀሰተኞች ቀርበው ሊይዟት ስለማይችሉ፣ በሦስተኛው ቀንም ተነስታ ሁሉንም ከንቱ አድርጋ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ በእውነትነቷ እየፎከረችና እየሸለለች፣ “አዋቂዎች ነን!” ባዮችን፣ “ዋሾዎች ሆይ!” እያለች ስታሳፍራቸው ትኖራለች። ልክ በማቴዎስ ወንጌል 27፣ 57-66 እና በ1ኛ ቆሮ 1፣ 18-22 እንደተመሰከረው ነው።)

 

የመንፈሳዊ ሥልጣንም ሆነ የፖለቲካ ሥልጣኑ ያላቸውን ሰዎች እንዴት የትንኝ ክንፍ የምታክል ሀሰት፣ ተራራ የሚያክለውን እውነት ልትከልላቸው/ልትጋርድባቸው እንደምትችል ለማወቅ ብንጥርም መረዳት አልቻልንም። በተለይም ብፁዐን አባቶቻችን እንዴት የቤተ-ክርስቲያንን ቀኖና ሊጥሱት እንደደፈሩ ለማመንም ተቸግረናል። ምናልባትም፣ በኃይማኖት ካባ ሥር - ጸያፍ ፖለቲካን የሚያቀነቅኑ “አማካሪ” ተብዬዎች ገፋፍተዋቸው ይሆናል የሚል ቀና ጥርጣሬ ያድርብናል እንጂ፣ በፍፁም ብፁዐን አባቶቻችንን፣ እኛ ከትንኟም ክንፍ የምናንሰው ምዕመናን ከመውቀስ ተቆጥበን ቆይተናል። መቼም፣ ውኃና ተግጻጽ ቁልቁል ሲተም እንጂ፣ ሽቅብ ሲጋልብ አላየንምና፣ ሃሳባችንንም በኢትዮጵያዊ ይሉኝታና ትሕትና አፍነን ይዘነው ቆይተን ነበር። ሆኖም፣ በኅዳር 30/2005 ዓ.ም. ይደረጋል የተባለውን የፓትሪያርክ ምርጫ ዝግጅት ስንሰማ፣ ድምፃችንን ልናሰማ ወደድን። ሃሳባችንንም፣ የትንኝ ክንፍ የምታክል ሕጸጽ እንዳትጋርድብን፣ አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔርም ይረዳን ዘንድ፣ እውነቱንና እውነቱንም ብቻ እንዲያናግረን ከመንበሩ ሥር ተደፍተን እንማፀነዋለን። ... ለዘላለሙ አሜን!!!

 

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በ1968 ዓ.ም.፣ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ በ1984 ዓ.ም. ከፓትሪያርክነታቸው የተሰናበቱበትና የብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብ ከግብፅ ቤተ-ክርስቲያን መንበራቸው በ1947 ዓ.ም. የተሰናበቱበት ሁናቴ በብዙ መልኩ ተመሳሳይ ነው። ሦስቱም ፓትሪያርኮች፣ በኢትዮጵያና በግብፅ የነበሩትን መንግሥታት በኃይል ተገርስሰው፣ ከነርሱ ለጥቀው የመጡት የደርግና የኢሕአዴግ-በኢትዮጵያ በኮሎኔል ጋማል አብደል ናስር ይመራ የነበረው ወታደራዊ ቡድንን በግብፅ ጡጫ አቅምሷቸዋል። ሁለቱ ፓትሪያርኮች መንበራቸውን ለቀው ወደገዳም ሕይወታቸው ገብተው ነበር። ብፁዕ አቡነ መርቆሪዎስ፣ በጥር 1984 ዓ.ም. ማለቂያ ላይ ነው ሲሰናበቱ ወደምስካዬ ህዙናን ገዳም ላጭር ጊዜ ገብተው ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታም፣ ብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብም ከካይሮ ወጣ ብላ ወደምትገኘው ቁስቋም ገዳም ገብተው ለአንድ ዓመት ያህል ቆይተዋል። በአንጻሩ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ወታደራዊው ደርግ ገዳም እንዲገቡ ሳይፈልግ ቀርቶ፣ ለእስርና ለግፍ ግድያ ተዳረጉ።

 

በሕገ ወጥ ሁናቴም በሰኔ 30/1968 ዓ.ም. አባ መላኩ የተባሉትን የገዳም መነኩሴ ከሁለት ጳጳሳትና ከሁለት መነኮሳት ጋር አወዳድሮ ሾማቸው። እኚህ አባትም ብፁዕ አቡነ ተክለ ኃይማኖት ከተባሉም በኋላ፣ እንደምንኩስናቸው ዘመን በባዶ እግራቸው ነበር የሚሄዱት። ደርግ በኃይማኖት ካባ ሥር በሠራው ጸያፍ ፖለቲካም፣ ሁለተኛው ፓትሪያርክ ከዚህ አለም በሞት እስኪለዩም አላስችል ብሎት፣ የቤተ-ክርስቲያኗን የፓትሪያርክ ምርጫ ደንብ እንደሚፈልገው አሻሽሎ፣ ለምዕመናኑ “ይኼውላችሁ የመረጥኩላችሁ ፓትሪያርክ!” አለ። ከፍ ብሎ የተሰማ የተቃውሞ ድምጽ ስለመኖሩ መዛግብት አያሳዩም። በመሆኑም፣ የደርግ ፀረ-ቀኖናና ፀረ-ሕገ ቤተክርስቲያን አጀንዳ ተተገበረ። በሐምሌ 7/1971 ዓ.ም.ህረትም አቡነ ቴዎፍሎስን አንቆ ገድሎ የአቡነ ተክለ ኃይማኖትን ሹመት እንዳያከራክር አድርጎ ከረቸመው።

 

1948/9 ዓ.ም.፣ የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን ተወካዮች 115ኛው ፓትሪያርክ አቡነ ዮሳብ ወደመንበራቸው እንደሚመለሱ ክፍተኛ ጥረት አድርገው ነበር። ሁለተኛው ፓትሪያርክ አቡነ ቴዎፍሎስና አራተኛው ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስ ወደመንበራቸው እንዲመለሱ የተደረገ እዚህ ግባ የሚባል ጥረት ግን አልነበረም። “ቄሱም ዝም፣ መጽሐፉም ዝም!” የሆነ መሰለ። ይህም የብፁዐን አባቶች ተግባር፣ በ35 ዓመታት ውስጥ (ከ1948-1984 ዓ.ም.) ምን ያህል ቁልቁል እንደሄድን አመላካች ነው። ብፁዐን አባቶችና የቤተ ክርስቲያኗም ለመርህ የመቆም አቅም ሙልጭ ብሎ ጠፍቶ ወደአዘቅት ለመውረዱ ዋናው ማሳያ ነው። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስና አቡነ መርቆሪዎስ ያለአጥጋቢ ምክንያት ከመንበራቸው ሲነሱ አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያኗ ሊቃነ ጳጳሳት የአቋም መግለጫ እንኳን ሳያወጡ መቅረታቸው በሰፊው አጠያይቋል። ዝምታው ፍርሀት የወለደው ነበር። “ፍርሃቱ ከዬት መጣ?” ካሉ ደግሞ፣ በኃይማኖት ካባ ስር ስውር የዘር ፖለቲካ የሚከተሉ አባቶች ስለነበሩ ነው። ለራሳቸው ፈርተው፣ ሌሎችንም አስፈራሩ!

 

ይህ ባይሆን ኖሮ፣ ከ35 ዓመታት በፊት የግብፅ ቤተ-ክርስቲያን ብፁዐን አባቶች ያደረጉት ሕግና ሥርዓትን የማክበር ተግባር እነርሱም ይፈፅሙት ነበር። የእስክንድርያ ፓትሪያርክ ብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብ በኅዳር 4 ቀን 1949 ዓ.ም. ካረፉ በኋላ ነበር ቀጣዩ ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ስድስተኛ፣ በግንቦት 2 ቀን 1951 ዓ.ም. (ልክ የዳግም ትንሳኤ ዕለት) የተቀቡት። አቡነ ቄርሎስም በቁጥር 116ኛው ፓትሪያርክ ሆኑና ሥራቸውን ጀመሩ። በአንፃሩ ደግሞ በኢትዮጵያ የፓትሪያርክነት መንበር ሲቀመጡ ሁለተኛና አራተኛ የሆኑት ብፁዐን፣ ከዚህ ዓለም በሞት እስኪለዩ ድረስ ሳይጠበቁ፣ በሰኔ 30/1968 እና በሐምሌ 5 ቀን 1984 ዓ.ም.፣ ተተኪዎቹ ፓትሪያርኮች በአናት ተቀቡ። ብፁዕ አቡነ ትክለ ኃይማኖት ከገዳም መጥተው የተሾሙ የመጀመሪያው ፓትሪያርክ ሲሆኑ፣ ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ደግሞ ከስደት መልስ የተሾሙም የመጀመሪያው ፓትሪያርክ ሆኑ።

 

ይህ ያቡነ ተክለ ኃይማኖትም ሆነ የአቡነ ጳውሎስ ሹመት፣ ከፍተኛ የሆነ የቀኖና፣ የሕገ ቤተ ክርስቲያን ጥሰቶች የተስተዋሉበት ነው። የዚህ ጽሑፍም መነሻ ነጥብም በዋናነት ስለሦስተኛውና ስለአምስተኛው የኢትዮጵያ ብፁዕ ወቅዱሳን ፓትሪያርኮች ጉዳይ ይመለከታል። በእርግጥ ሁለተኛውና አራተኛው የተሻሩበት አግባብና ሦስተኛውና አምስተኛው ፓትሪያርኮች የተሾሙበት ሥርዓት በኒቅያው ቀኖና አንቀጽ 50፣ እንዲሁም በዚሁ በኒቂያው ቀኖና ስለፓትሪያርክ በሚናገረው፣ በ4ኛው አንቀጽ በ5ኛው ክፍል የተደነገጉትን ሕጎች የሚተላለፍ ከመሆኑም በላይ፤ “ስለኢትዮጵያ ፓትሪያርክ አመራረጥ የወጣውን የ1963 ዓ/ም የምርጫ ደንብና የ1968ቱን የምርጫ ማሻሻያ ደንብ” ሥነ ሥርዓቶች መሠረት ባለመካሄዱ ትክክለኛ አልነበረም።

 

ይህንን ትክክለኛ ያልሆነ የቤተ-ክርስቲያን ቀኖናና ደንብ ጥሰት ለማለባበስ ከሰሞኑ የሚታዩትም ሩጫዎች የሚስተዛዝቡ ሆነዋል። የማኅበረ-ቅዱሳን ሁለቱ ልሳኖች፣ ማለትም “ስምዓ ጽድቅ” ጋዜጣና “ሐመር” መጽሔት፣ ችግሩ የእርቅና የምሕረት እንደሆነ አድርገው በኅዳር ወር እትማቸው “ከፓትሪያርክ ምርጫ በፊት እርቀ ሰላም ይቅደም” የሚል አጀንዳ ያራግባሉ። በርግጥ ቤተ-ክርስቲያን የዕርቅና የምሕረት አደባባይ መሆኗ ባይካድም፣ የተያዘው አቋም ግን ትክክል አይደለም። በሌላም በኩል፣ ባለፈው ጥቅምት ወር ተሰብስቦ የነበረው የሲኖዶስ ጉባኤ አንድ አስገራሚና ከብፁዓን አባቶች የማይጠበቅ ውሳኔ ማስተላለፉ ተገልጧል። “እንዴት አምስተኛው ፓትሪያርክ ስንል ሃያ አመታት ያህል ኖረን፣ እንደገና ወደ አራተኛው ፓትሪያርክ እንመለሳለን? ሰውስ ምን ይለናል?” የሚል ስጋት እንዳላቸውም ተሰምቷል። ይህም ቢሆን ዓለምን ንቀው፣ በእግዚአብሔር መንገድ ለሚመላለሱ ብፁዐን አባቶች ያልተገባ አቋም ነው። ከበቁ የኃይማኖት መሪዎችና አባቶች አእምሮ እንዲህ ያለ የይሉኝታና የፖለቲከኛነት አስተያየት እንሰማለን ብለንም ለማንጠብቀው ለኛ ለምዕመናኑም ቢሆን አሸማቃቂ ነው።

 

ዛሬም ከ55 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን አባቶች፣ የዛሬ ሃያ ዓመት የፈፀሙትን ስህተት ለማረም ወኔ ማጣታቸው ያስደንቃል። ታሪክ ጠቅሰን፣ የዛሬ 55 ዓመት የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን መሪዎች እንዴት በዜግነት ባዕድ ለሆኑት፤ ነገር ግን በኃይማኖት መሪነታቸው ለሚያከብሯቸው ለብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብ እንደተከራከሩና ታሪክም እንደሰሩ እናስታውሳችሁ። (እርግጥ ነው፣ ነገራችን ሁሉ “ለቀባሪው አረዱት” ዓይነት ነው።) የመግለጫው መግቢያ ቃል እንዲህ ይነበባል። “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን፤ የእስክንድሪያ ፓትሪያርክ ብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብ ከሥልጣናቸው መወገዳቸውን እንደሰማች፤ ይህ ከሲኖዶስ የወጣ አደራረግ፤ አንደኛ) ከአባቶቻችን ከሐዋርያት ሲያያዝ የመጣውን መንፈሳዊ ሥርዓት የሚቃወም በመሆኑ፤ ሁለተኛ) ኢትዮጵያ ከ1600 ዘመን ጀምሮ ከመንበረ-ማርቆስ ጋር ባላት መንፈሳዊ ግንኙነት መሠረት፣ የእስክንድሪያን ፓትሪያርክ መንፈሳዊ መብት የሚነካ ነገር በተነሣ ጊዜ ሁሉ ጉዳዩ በቀጥታ የሚያገባት መሆኑን በማመልከት ለግብፅ መንግሥትና ለመጅሊስ ሚሊ አባሎችም” መልዕክት ተልኳል።

 

ብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብን ወደመንበራቸው ለመመለስ በነበረው ክርክር ዋና ዋናዎቹ የመከራከሪያ ነጥቦች የሚከተሉት ነበሩ። አንደኛ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን በነሐሴ 30/1947 ዓ.ም. የፓትሪያርኩን ከመንፈሳዊ ሥልጣናቸው መነሣት ተቃውማ፣ በመስከረም 16/1948 ዓ.ም. “ቀኖና ተጥሷል” ብላ በሊቀ ጳጳሷ በኩል ቴሌግራም ማስተላለፏን ያወሳል። ሁለተኛም) ኢትዮጵያ በትልቁ የዓለም ፓትሪያርኮች ጉባኤ ላይ በስምንተኛው መንበር ላይ የምትቀመጥ ሀገርና ተሰሚነቷም ቢሆን ከፍተኛ እንደሆነና ይህም በኒቂያው ቀኖና በ42ኛው አንቀጽ መሠረት የፀና መሆኑን ይገልፃል። ሦስተኛ) በዚሁ በኒቂያው ቀኖና በአንቀጽ 50 መሠረት፣ አንድ ፓትሪያርክ ላይ ክስ ሲቀርብ ነገሩን ለመስማት በሚደረገው ጉባኤ፣ በኃይማኖት መካከል ቢያንስ አንድ ፓትሪያርክ፣ ቢበዛ ደግሞ ሁለትና ከዚያም በላይ ፓትሪያርኮች መገኘት የሚገባቸው ሲሆን፣ “በፓትሪያርኩ ብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብ ላይ ውሳኔ ሲደረግ በስብሰባው ላይ አንድም ፓትሪያርክ ያልተገኘበት በመሆኑ ስብሰባውም ሆነ ውሳኔው ሕጋዊ አይደለም፤” ይላል። አራተኛ) በኒቂያው ቀኖና ስለፓትሪያርክ በሚናገረው 4ተኛው አንቀጽ፣ በ5ተኛው ክፍል እንደሚደነግገው ከሆነና፣ በቤተ-ክርስቲያንም ቀኖና መሠረት፤ “አንድ ፓትሪያርክ ከመንፈሳዊ ሥልጣኑ የሚነሳው አእምሮው ከተናወጸ ብቻ ነው፤” ይላል። ስለዚህም ውሳኔው ሕግን የተመረኮዘ አለመሆኑን በስፋት የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ፣ ዓርብ ጥር 4/1948 ዓ.ም.፣ ገጽ-1 ላይ ይገልፃል።

 

እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ሁለት የመከራከሪያ ጭብጦች መሠረት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ፣ ከፓትሪያርክነታቸው የተሰናበቱበት አግባብ ሕጋዊ አልነበረም። በመጀመሪያ፣ አንድም የተገኘ ፓትሪያርክ ሳይኖር በመሰናበታቸውና፤ ምንም የጤንነት ችግር ሳይኖርባቸው ከመንበራቸው በመነሳቸው ነው። የጤናቸውን ጉዳይ ላለፉት 21 ዓመታት በሙሉሰውነት መኖራቸው ያረጋግጣል። በስደትም ላይ ሆነው ቤተ-ክርስቲያንን እየመሩ ናቸው። በተጨማሪም፣ ፓትሪያርኩ የተሰናበቱት በሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ትዕዛዝ ለመሆኑ የwikileaksም ማረጋገጫ ከአዲስ አበባው የአሜሪካን ኤምባሲ ተገኝቷል። ይኼ ሕገ-ወጥ አካሄድ፣ እ.አ.አ በ1929 በዓለም አብያተ-ክርስቲያናት ጉባኤ የተወሰነውንና ኢትዮጵያም ያፀደቀችውን የጳጳሳት ምልዐተ-ጉባኤ ደንብ ያላከበረ ነው። ስምምነቱ እንደሚለው ከሆነ፣ የሲኖዶስ ውሳኔዎች ሲወሰኑ ቢያንስ ሁለት-ሦስተኛው የጳጳሳት ምልዐተ-ጉባኤ መሟላት ነበረበት። በ1984 ዓ.ም. ግን ይህ አልሆነም። አቶ ታምራት ላይኔ፣ በልዩ ትዕዛዝ ፓትሪያርኩን አሰናብቶ ሲያበቃ፣ በሐምሌ 5/1984 ዓ.ም. በተወካዩ በአቶ መረባ አለማየሁ አማካይነት እንዲህ አለ፤ “ያለፉት የጭለማ ዓመታት አልፈው ሰላም፣ ዲሞክራሲ የሕግ የበላይነት እየተስፋፉ ነው” (አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ሐምሌ 7/1984 ዓ.ም.፣ ገጽ-1)። (እውነት ነው፤ ሰላም ተስፋፍቷል። ነገር ግን፣ የዲሞክራሲውንና የሕግ የበላይነቱን መስፋፋት አቶ ታምራት አንዴ ይደግሙልን ይሆን? እንጃ! አይመስለንም።)

*****************************************************************

ይህንን ጽሑፍ ከማጠናቀቃችን በፊት ለሰፊው የዚህ መጣጥፍ አንባቢዎች አንዳንድ ታሪካዊ ማስታወሻዎችን ልናካፍላቸው እንወዳለን። በተለይም እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ፣ አራተኛው ፓትሪያርክ ይመለሱ ይሆን ወይስ ስድስተኛውን ፓትሪያርክ ይመርጡና በኢ-መርሕ፣ በኢ-ቀኖናና በ1963 ዓ.ም. የፀደቀውን፣ “ስለኢትዮጵያ ፓትሪያርክ አመራረጥ የወጣውን የምርጫ ደንብና”፤ በ1968 ዓ.ም. የወጣውን ማሻሻያ ወደጎን ትተው ይቀጥሉበት ይሆን?” ለምንለው ምዕመናን በቂ መልስ ይሰጠናል። ከላይ እንደገለጽነው አራተኛውን ፓትሪያርክ መልሶ በመንበራቸው ማስቀመጥ ከፍተኛ የሆነ ክርስቲያናዊ ተግባርና ለቀኖናም ተገዢነት ነው። “የለም፣ አምስተኛው ስንል ኖረን እንዴት ወደአራተኛው ፓትሪያርክ እንመለሳለን!” ማለቱ ደግሞ ቤተ-ክርስቲያኗን ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል እናምናለን። (መቼስ፣ “ኃይማኖት ማለት ማመን ነውና፣ “እንዴት ልታምኑ ቻላችሁ?” ብላችሁ እንደማትጠይቁን፣ አሁንም እናምናለን!!!)

 

ስድስተኛው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ መጡም-አልመጡም፣ ከአንደኛው እስከ አምስተኛው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሆነው ሲመረጡ ምን ዓይነት የቤተ-ክርስቲያን አገልግሎት አበርክተው እንደሆነ ተራ በተራ እናወሳለን። በመጀመሪያም ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ እንጀምራለን። በ1884 ዓ.ም. በሚዳ አውራጃ፣ በአሞደል ጊዮርጊስ ተወለዱ። ሥመ-ጥምቀታቸውም ገብረ ጊዮርጊስ ነበር። በ1905 ዓ.ም.ህረትም አመክሯቸውን ጨርሰው በደብረ ሊባኖስ መነኮሱ። በ1911 ዓ.ም. ጀምሮም የመናገሻ ማርያም መምህር ሆነው ተሾሙ። ብፁዕ አቡነ ማቴዎስም የቁምስና ማዕረግ ጨመሩላቸው። ከ13 ዓመታትም በኋላ፣ በ1924 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብኤል (ግቢ ገብርኤል) አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ። በ1925 ዓ.ም. ደግሞ፣ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ራይስ (ጠቅላይ አስተዳዳሪ) ሆነው ለሁለት ዓመታት ሠሩ። በ1927 ዓ.ም. ከኢየሩሳሌም ተጠርተው መጥተው የደብረ ሊባኖስ 59ኛው እጨጌ ሆነው ተሾሙ። በ1940 ዓ.ም. በእጨጌነቱ ላይ የጵጵስና ማእረግ ተሰጣቸው። እስከ1951 ዓ.ም.ህረትም አርባ ሁለት አብያተ-ክርስቲያነትን አሠርተዋል። አስራ ሁለት ትምህርት ቤቶችንም አልምተዋል። በተለይም፣ በደብረ ጽጌ ያለውን የእብነት ትምህርት ቤት በግል ገንዘባቸው ነበር የሚያስተዳድሩት (አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 3/1963 ዓ.ም.)።

 

ጥር 6/1943 ዓ.ም.፣ “ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ” ተብለው እስከ 1951 ዓ.ም. ድረስ ቆዩ። በሰኔ 21 ቀን 1951 ዓ.ም.፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ የራሷን “ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትሪያርክ” ስታገኝ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የኢትዮጵያ ፓትሪያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ካይሮ በሚገኘው የቅዱስ ማርቆስ ቤተ-ክርስቲያን፣ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ሳድሳዊ እጅ ተሾሙ። በተወለዱ በ79ዓመታቸው ጥቅምት 2/1963 ዓ.ም.፣ ከቀኑ በአስር ሰዓት ዐረፉ። ጥቅምት 4/1963 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ።

 

ሁለተኛው ፓትሪያርክም በዓለ ሲመት መጋቢት 29 ቀን 1963 ዓ.ም. በመንበረ ፓትሪያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተከናወነ። “ሕዝባዊ መንግሥት እንጂ፣ ወታደራዊ ጁንታ አያዋጣንም!” ስላሉ፣ ወታደራዊ ደርግ የካቲት 9/1968 ዓ.ም. ከመኖሪያ ቤታቸው ወስዶ፣ መጀመሪያ በእዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት፣ ከዚያም በልዑል ራስ አስራተ ካሣ ቤት አስሮ ካቆያቸው በኋላ፣ በሐምሌ 7/1971 ዓ.ም. በዚያው በታሰሩበት ቤት በገመድ ታንቀው እንዲገደሉ ተደረጉና እዚያው እንዲቀበሩ መደረጋቸውን፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሐምሌ 3/1984 ዓ.ም. ዕትሙ ይገልፃል። ከልዑል ራስ አስራተ ካሣ ግቢም አፅማቸው ወጥቶ፣ በሐምሌ 4/1984 ዓ.ም.፣ በቅድስተ ቅዱሳን ሥላሴ ካቴድራል ተቀበሩ። ፓትሪያርክ ከመሆናቸውም በፊት የሐረርጌ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ከ1943 ዓ.ም. ጀምሮ ከሠላሳ ሁለት አብያተ-ክርስቲያናትን አሠርተዋል። አቡነ ጳውሎስን ጨምሮ፣ በርካታም ጳጳሳትን ሾመዋል።

 

ሦስተኛው ፓትሪያርክም ሆነው የተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ኃይማኖት ናቸው። ፓትሪያርክ ከመሆናቸውም በፊት በወላይታ አውራጃ፣ በደብረ መንክራት ተክለ ኃይማኖት ገዳም መነኩሴ ነበሩ። ሆኖም፣ በሰኔ 30/1968 ዓ.ም. ከ619 ድምጽ ውስጥ 317ቱን አግኝተው ፓትሪያርክ ሆኑ። በነበሩበትም በወላይታ አውራጃ ከሦስት መቶ ሺህ በላይ ምእመናንን ከማጥመቃቸውና የቤተ ክርስቲያኗም ተከታዮች ከማድረጋቸው በላይ፣ 35 አብያተ-ክርስቲያናትን አሠርተዋል። አስራ ስድስት የሕፃናት ማሳደጊያዎችን አቋቁመው፣ ከሃያ ሺህ በላይ ችግረኛ ሕፃናትን አሳድገዋል።.... ግንቦት 28/1980 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩና ስርዓተ-ቀብራቸውም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰኔ 1 ቀን 1980 ዓ.ም. ተፈፀመ።

 

አራተኛው ፓትሪያርክም ሆነው የተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ናቸው። ከላይ በመግቢያችን በሰፊው ስለርሳቸው ያተትን በመሆኑ አንደግመውም። ነሐሴ 22/1980 ዓ.ም. ፓትሪያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሆነው እስኪመረጡ ድረስ፣ የጎንደር ክፍለ-ሀገር ሊቀ ጳጳስ ነበሩ። በክፍለ-ሀገሩም ሠላሳ አብያተ ክርስቲያናትን ከማሠራታቸውም ባሻገር፣ የተለያዩ የአረጋዊያን መጦሪያ ተቋማትን፤ ከሃያ በላይ ወፍጮ ቤቶችን፣ 32 ዳቦ ቤቶችንና የተለያዩ የልማት ተቋማትን አሠርተው እንደነበር፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በነሐሴ 24/1980 ዓ.ም. ዕትሙ ገልጧል። እኚህ ፓትሪያርክ ከሀገር ከወጡም በኋላ የዴንቨር የቅዱስ ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን ብዙ ጳጳሳትን ሾመው ሲኖዶሳቸውን አጠናክረዋል።

 

ወደማጠቃለያችን እየሄድን ነው። አምስተኛው ፓትሪያርክም ሆነው የተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ናቸው። በሐምሌ 5/1984 ዓ.ም. ፓትሪያርክ ከመሆናቸው በፊት፣ በደርግ መንግሥት ለሰባት ዓመታት ያህል ታስረዋል። ከዚያም በስደት ግብፅ-አሌክሳንደሪያና አሜሪካን ኖረዋል። በስደት ላይም ሳሉ፣ በሥነ-መለኮት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። በ1983 ዓ.ም. ማብቂያም ላይ በወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው፣ አምስተኛው ፓትሪያርክ ለመሆን በቅተዋል። እስከሚሾሙም ድረስ ያሠሯቸውን አብያተ-ክርስቲያናት ቁጥር አዲስ ዘመን ጋዜጣ አልገለፀም። በታኅሣሥ 1968 ዓ.ም. ጵጵስና የሾሟቸውን የሁለተኛውን ፓትሪያርክ የብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስን አጽም ከበዐለ ሢመታቸው አንድ ቀን ቀደም ብለው፣ በሐምሌ 4/1984 ዓ.ም. በክብር እንዲያርፍ በዋናነት የተጉት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ናቸው። በነሐሴ 11/2005 ዓ.ም.ህረትም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው፣ በነሐሴ 18/2005 ዓ.ም. በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተቀብረዋል። (ቸር እንሰንብት!)

ሰሎሞን ተሰማ ጂ. (www.semnaworeq.blogspot.com)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ