ይድረስ ለወላጆች እና ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት

ኃ/ገብርኤል መላኩ (የአሳይ ት/ቤት መምህር)

ይህ ነጻ አስተያየት ነው። እውነቱን ማወቅ የፈለገ ማነኛውም መገናኛ ብዙኃንም ሆነ የመንግስት አካላት ጉዳይን በምስጢር በመከታተል እና በማጣራት እውነቱን መድረስ ይችላሉ።

 

 

አሳይ ት/ቤት አዲስ አበባ-ቦሌ ክ/ከ ከጌቱ ኮመርሻል ሴንተር ፊት ለፊት ይገኛል። አሳይ የሕዝብ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ጉዳይ እጅግ አወዛጋቢ እየሆነ ነው። አሳይ ት/ቤት በአዲስ አበባ ካሉ የሕዝብ ት/ቤቶች ቁጥር አንድ እና ጥሩ የሚባል ት/ቤት ነው። ከየትኛውም የመንግስት ት/ቤቶችም እጅግ የላቀ ነው። የትምህርት ግባቶችም በደንብ የተሟሉለት ከመሆኑም በተጨማሪ ጥሩ መምህራን ያሉበትና ጥሩ ትምህርት የሚሰጥበት ት/ቤት ነው። ነገር ግን አሁን አሁን ፈር እየለቀቀ ነው። የተከበራችሁ የአሳይ ት/ቤት ወላጆች ሆይ ት/ቤቱ ወደባሰ ችግር ውስጥ ሳይገባ ተባብራችሁ መልሱት። ልጆቻችሁ እየተጎዱ ነው። የመንግስት አካላትም ግዴታችሁን ተወጡ። የሚከተሉት ችግሮች አሳይ ት/ቤትን እንደ ት/ቤት እንዳይቀጥል ያደረጉት ዋና ዋና ችግሮች ናቸው።

 

1. የመንግስት ጣልቃ ገብነት

የሕዝብ ት/ቤቶችን በተመለከተ መንግስት ያወጣው አዋጅ ለምንድን ነው አሳይ ት/ቤት ላይ የማይሰራው? የሕዝብ ት/ቤቶች በወላጆች ውሳኔ መሰረት፣ ራሳችንን ማስተዳደር እንችላለን የሚሉ ከሆነ የሕዝብ ሆነው ይቀጥላሉ ወይም ራሳችን ማስተዳደር አንችልም የመንግስት እንሁን ካሉ ወደ መንግስቱ ይዞራሉ ነው የሚለው አዋጁ። ነገር ግን አሳይ ት/ቤት ራሱን የሚችል ት/ቤት መሆንን እነ አቶ ዴላሞ ሳይቀሩ ሚኒሊክ ት/ቤት ውስጥ በተደረገው ስብሰባ ላይ መስክረው፣ የቦሌ ወረዳ ሁለት የትምህርት አመራሮችና ካቢኔዎች እንዲህውም የወላጅ ተወካይ ተበየዎች እና ርዕሰ መምህሩ ጭምር የመግስት እንዲሆን ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። እሁድ ቀን ነበር ወላጅ ስለ ት/ቤቱ እጣ ፈንታ ሊወስን ተስብስቧል። መድረክ ላይ ያሉት ሰዎች ወደ መንግስት እንዲሆን ጉትጎታ ያደርጋሉ። ወላጅ ደግሞ ለምን ተብሎ በእኛ ውሳኔ ነው መሆን ያለበት ይላል። ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ በቃ በድምጽ ብልጫ ይሁን ተባለ። በዚህ ሰዓት ግን ወላጅ ያልሆኑ ብዙ ሴቶች ወደ ት/ቤቱ ግቢ ዘለቁ። እንደሚባለው ከሆነ እነዚህ ሴቶች የመጡት ቀጥታ ከቀበሌ ስብሰባ ነው። ሌሎች ደግሞ በቀጥታ ጥሪ የመጡ ናቸው። በዚህ ጊዜ የተሰበሰቡት ወላጆች የት/ቤታችን እጣ ፈንታ የምንወስን እኛ ነን። ሰለዚህ ሌላ አካል አያስፈልግም አሉ። ነገር ግን የሚሰማቸው ጠፋ። ከመድረክም ተሰብሳቢ ወላጆችን የማናደድ ስራ ይሰራ ነበር። በዚህ ምክንያትም ወደ 80% የሚሆኑት ወላጆች መድረኩን ረግጠው ወጡ። ሲወጡም ከፖሊስ ጋር ሳይቀር ተጣሉ። ግማሹም አለቀሱ። ሌሎቹም አዘኑ። ከውጭ ሆነው ውሳኔውን ይጠባበቁ የነበሩ ተማሪዎችም ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል። በዚህ ምክንያትም በትንሽ ድምጽ ብልጫ የመንግስት ይሁን ተብሎ ተወሰነ። ነገር ግን ውሳኔው በማን ኃይል እንደሆነ አላውቅም ተቀለበሰ። ከሁለት ወር በኋላ አሳይ ት/ቤት የህዝብ እንደሆነ ይቀጥላል ተብሎ በመገናኛ ብዙኃን ተነገረ። በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ጋዜጣና እና አዲስ ጉዳይ መጽሄት ዘግበዋል።

 

ሌላው ጉዳይ ደግሞ በወጣው አዋጅ መሰረት የህዝብ ት/ቤቶች የህዝብ ሆነው ከቀጠሉ መንግስት እጁን አይዘረጋም። ምንም እርዳታም አልሰጥም ብሎ ነበር። የመንግስት ተቀጣሪ የሆኑም እንደሚነሱ ነበር የተነገረው። አሳይ ት/ቤት ውስጥ ግን ይሄ ጉዳይ አይሰራም። ርዕሰ መምህሩ፣ ሁለቱ ምክትል ርዕሳነ መምህራን እና ዩኒት ሊደሮች መንግስት የቀጠራቸው ናቸው። እነዚህ ሰዎች ሁሉም የመንግስት ካድሬዎች ናቸው። ማንም ወላጅና የት/ቤቱ ማህበረሰብ እነዚህን ሰዎች አይፈልጓቸውም። ነገር ግን መንግስት እንዳይነኩ የብረት አጥር ሰርቶላቸዋል። እያንዳንዱን የመምህር እንቅስቃሴም ይከታተላሉ።

 

2. ሙስና

የሙስና ጉዳይ በት/ቤታችን ትልቁ ጉዳይ ነው። የት/ቤቱ ማህበረሰብ በሹክሹክታ ዘወትር የሚያወራው ነው። አሳይ ት/ቤት በአመት እስከ 6 ሚሊዮን ብር ገቢና ወጭ ያደርጋል። ነገር ግን አንድ ቀን በትክክል ኦዲት ተደርጎ የማያውቅ ት/ቤት ነው። ይህ ችግር አቶ ታደሰ አርዓያ ወደ ርዕሰ መምህርነት ከመጡ በኋላ ብቻ የተጀመረ እንዳይመስላችሁ። የበፊቱ ርዕሰ መምህር በነበሩት አቶ ክፍሌ ሞገስም የነበረ ችግር ነው። አቶ ክፍሌ ከወንበራቸው ሲነሱ በሙስና ይጠረጠሩና ኦዲት ይደረግ ይባላል። በዚህ ምክንያትም የ25 ዓመት ሰነድ ኦዲት እንዲደረግ ጨረታ አወጡ። ጨረታውም በሸገር ሬዲዮ ጭምር ተነገረ። እናም ኦዲት አድራጊዎች ስራ ጀመሩ። በነገራችን ላይ ኦዲት አድራጊዎች ብዙ ነበሩ። ፖሊስም ጉዳይን አብሮ ይከታተል ነበር። ነገር ግን የኦዲቱ መጨረሻ ሳይገለጽ ቀረ። ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ አይደለም።

 

ይህ ችግር አሁንም እንዳለ ነው። የት/ቤቱ አካውንታት አቶ ወንድሙ ኮልቤ በጣም አስቸጋሪ ሰው ነው። ደሞዝ በቀኑ ለሰራተኛች አይከፍልም። ኦዲትም አድርጎ አያውቅም። አንድ ቀን ኦዲት አድርግ ተብሎ ተያዘ። እናም ጨነቀው። ያደረገው ምን መሰላችሁ፣ ኮምፒተር ላይ ያለውን ፋይል ቫይረስ አጠፋብኝ አለ። በዚህ ምክንያትም ኦዲት ማድረግ እንደማይችል ተናገረ። እንዴት ብሎ የተናገረው አንድም ሰው ግን የለም፣ ታለፈ። አቶ ታደሰ (ርዕሰ መምህሩ) ለምን አይናገረውም ካለችሁ፤ የግቢው ማህበረሰብ እንዲህ ብሎ ይመልስላችኋል። የሙስናውን ሞሰብ አብረው ጎርሰው እንዴት ይናገረዋል ይሏችኋል። ይህ ብቻ አይደለም የት/ቤቱ ንብረት የሆነች አንድ አባ ዱላ መኪና አለች። ድሮ ግቢ ውስጥ ነበር የምትውለው። አሁን ሙሉ በሙሉ አቶ ታደሰ እጅ ውስጥ ወድቃለች። የራሱን መኪና አስቀምጦ ይዟት የሚመላለስ እሱ ብቻ ነው። ሌላ ጊዜ ደግሞ መኪናዋን አንድ ሳምንትና ከዚያ በላይ ከግቢ ውስጥ አታዩአትም። እናም ብዙ ሰዎች ተከራይታ ይሆናል ብለው ይጠረጥራሉ። ሌላው ደግሞ ለዚህች መኪና እድሳትና ምርመራ እየተባለ የሚወጣው ወጪ በጣም አነጋጋሪና አስጠርጣሪ ነው።

 

3. የት/ቤቱ አስተዳደር ክፍሎች ሥራቸውን ባግባቡ አለመስራት

ስለዚህ ጉደይ ማንም ገለልተኛ የሆነ ሰው መጥቶ ሊታዘብ ይችላል። የአንድ ት/ቤት አድራጊ ፈጣሪ ነው ብዬ የማስበው ርዕሰ መምህሩ ነው። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ምክትል ርዕሳነ መምህራን ናቸው። ነገር ግን አሳይ ት/ቤት ውስጥ ርዕሰ መምህር መኖሩን እጠራጠራለሁ። እንዲህውም ምክትል ርዕሳነ መምህራን። ዩኒት ሊደሮችም እንዲሁ የሞቱ ናቸው። ሥራውን በትክክል እና በብቃት የሚሰራ የአንደኛ ደረጃ ምክትል ርዕሰ መምህር የሆነው ዘመድኩን ብቻ ነው። ርዕሰ መምህሩ ግቢ ውስጥ የሥራ ሰዓት አክብሮ አይገኝም። ቢመጣም ግቢ ውስጥ ላይቆይ ይችላል። በት/ቤቱ ግቢ ውስጥም ያለው ሚና እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ተማሪዎችን በመቆጣጠር እና ጠንክሮ በመስራት ለመምህራን ተምሳሌት መሆን አልቻለም።

 

ሌላው አስተዳደሩ በተማሪዎች ላይ ምንም እርምጃ አይወስድም። በጣም ግድየለሾች ሁነዋል። የሰረቀ ተማሪ፣ ሞባይል፣ ጩቤ እና ሃሺሽ ይዘው የሚመጡትን ተማሪዎች፣ መምህር የተደባደበ እና የተሳደበ ተማሪ፣ ተማሪ የተማታ እና የተሳደበ፣ የት/ቤቱን እቃ የሚያጠፋ እና የሚሰብር ተማሪ ላይ ምንም እርምጃ አይወሰድም። በተቃራኒ ግን መምህር ተማሪ ቢሳደብ ወይም በጥፊ ነካ ካደረገ ከት/ቤቱ አልፎ እስከ ፍርድ ቤት ይከሰሳል። ርዕሰ መምህሩ አቶ ታደሰ ሰብስቦን “ተማሪ የተሳደበ ወይም የተማታ ሴት የደፈረ ማለት ነው” ካለ በኋላ “ይሄንን ያደረገ መምህር እዚህ ግቢ ተመልሶ እንዳይመጣ” ብሎ አስጥንቅቆናል። በዚህ ምክንያትም መምህራን ምን አገባን እያሉ ነው። መምህር ምን አገባኝ ካለ ደግሞ ት/ቤቱ ሞተ ማለት ነው። አንድ መምህር ተማሪ መማታት እንደሌለበት ማንም መምህር ጠንቅቆ ያውቃል። ነገር ግን ት/ቤቱ ውስጥ ያለው አካሄድ ቅጥአምባሩ የጠፋባቸው ይመስላሉ። አመራሩንም ፈጽሞ አልቻሉበትም። ባጠቃላይ አስተዳደሮቹ ት/ቤቱን ለማቅናት ሳይሆን ለማፍረስ የሚሰሩ ነው የሚመስሉት።

  

4. የመምህራን ፍልሰት

ብቃት እና ልምድ ያላቸው መምህራን በየጊዜው እየለቀቁ ነው። በዚህ አራት ወር ወስጥ ብቻ ከ 20 መምህራን በላይ ት/ቤቱን ለቀዋል። ዋናው ምክንያት በት/ቤቱ ግቢ ውስጥ ጥሩ የሚባል የስራ አትሞስፌር ስለሌለ ነው። የመጡት አዳዲስ መምህራንም ግማሾቹ ወዲያው ለቀው ይሄዳሉ። ሌሎቹ ደግሞ አዲስ መምህራን በመሆናቸው ምክንያት ክፍል ሲገቡ ተማሪዎች ባንድ ላይ፣ በአድማ መልክ ሙድ እየያዙ ለማስተማር የተቸገሩበት ሁኔታ ነው ያለው። በዚህ የተነሳ ት/ቤቱ በየጊዜው የሥራ ማስታወቂያ ማውጣቱን እንደተያያዘው ነው። በዚህ መካካልም ብዙ ክፍለ ጊዜያት እየባከነ ነው።

 

5. በትምህርት ቤቱ ውስጥ በሶስት የተከፈለ ቡድን መኖሩ

በዚህ ት/ቤት ውስጥ ሶስት ቡድን አለ። አንደኛው የቀድሞው ርዕሰ መምህር ክፍሌ ሞገስ ቡድን፣ ሁለተኛው የአሁኑ ርዕስ መምህር የአቶ ታደሰ አርዓያ ቡድን ሲሆኑ፣ ሶስተኛው ቡድን ደግሞ አዲስ የገቡት ሲሆኑ- ግማሹ ሚናውን ያልለየ፣ ግማሹ ድግሞ ብቸኝነትን የመረጠ ነው። ይህ ቡድን በተለይ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ወደ እነ አቶ ክፍሌ ቡድን ከተጠጋ አለቀለት ማለት። በየስብሰባው ወሬ አመላላሽ ተብሎ በአሽሙር ይዘለፋል። ሌላው በጣም የሚገርመው አቶ ታደሰ ሲሰበስበን ሁሌ ማስፈራራት ነው የሚቀናው። አንዴ ሐምሌ ወር ላይ አጠቃላይ የመምህራን ስብሰባ በነበረበት ገዜ፣ አሳይ ለብቻው ሂስና ግለ ሂስ ሲያደርግ “እኔን እደበድበዋለሁ እያላችሁ የምታወሩና የምትፎክሩ አላችሁ! እኔ ያደግሁት ደብረ ዘይት ኤር ፎርስ ሃይል ውስጥ ነው፤ ለድብደባው አሳምሬ ነው የማውቀው።” እያለ እንደጎረምሳ እየነጠረ ነበር የሚናገረው። ድርጊቱ ብዙ መምህራን ያሸማቀቀና ያሳፈረ ጉዳይ ነበር። ምክንያቱም ካንድ የት/ቤት ድሬክተር የማይጠበቅ ነውና።

 

6. የተማሪዎች ሥነ ምግባር ከመጠን በላይ እየተበላሸ መሄድ

የተማሪዎች ሥነ ምግባር አቶ ክፍሌ ሞገስ ርዕሰ መምህር በነበረበት ሰዓት እጅግ ጥሩ ነበር። አሁን ግን በመልካም ሥነ ምግባር ይታወቅ የነበረው ት/ቤት ተቀየረና ሥነ ምግባር የጎዳላቸው ተማሪዎች መናኸሪያ እየሆነ ነው። ተማሪዎች የደንብ ልብሳቸውን እንዲለብሱ አይገደዱም፣ ጸጉራቸውን እንደፈለጉ ነው የሚያሳድጉት፣ በት/ቤቱ ውስጥ ስርቆት በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቷል፣ የተማሪዎች ምግብ በየጊዜው ይሰረቃል። ተማሪዎች በቡድን ሆነው ጩቤ እስከመማዘዝ ደርሰዋል። ብዙ ተማሪዎች ጩቤ ይዘው ይመጣሉ። አንዳንዶችም ተማሪዎችን እያስፈራሩ (በተለይ ሕጻናትን) መጽሐፍ ሰርቀው እንዲወስዱላቸው ያደርጋሉ። ይህንን መረጃ እራሱ አቶ ታደሰ (ርዕሰ መምህራን ስብሰባ ላይ በግልጽ ነግረውናል)። ከዚህ በተጨማሪም ት/ቤት ውስጥ ሃሺሽ ይዘው በመምጣት የሚነፉ ተማሪዎች እጅግ እየበዛ ነው። ስለዚህ ጉዳይ የጽዳት ሰራተኞቸ ብዙ ምስጢሮችን ያውቃሉ። ክፍል ዘግተው (በ 28/03/2005) ሃሺሽ ሲያጨሱ የተያዙ ተማሪዎች በጽዳት ሰራተኞች ጥቆማ እንደተያዙም መረጃ ደርሶኛል። መምህራን በተማሪዎች እየተሰደቡ ነው፣ መምህራንን የተደባደቡና ለመደባደብ የተገለገሉም ተማሪዎች ብዙ ናቸው፤ ነገር ግን ት/ቤቱ ምንም እርምጃ አይወስድም። ተማሪዎች በተደጋጋሚ አርፍደው ነው የሚመጡት፣ ተማሪዎች አንድ ሰሜስተር ሙሉ ቢቀሩ እንኳ በአስተዳደሩ ተፈቅዶላቸው ፈተና ይፈተናሉ። ተማሪዎች በግድ እንዲያልፉ ይደረጋል-በተለይ የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች። የተማሪዎች ሥነ ምግባር በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ብቻ ሳይወሰን ወደ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች እየተሸጋገረ ነው። ይህ ችግር የመማር ማስተማሩን ሁኔታ እንዴት እንደሚያውክ ለማንም ግልጽ ነው።

ይህን ችግር ወላጅና መንግስት ተባብሮ ካልቀረፈው ት/ቤቱ የዋልጌዎች መዋያ ብቻ ሳይሆን የወንጀልና የእጽ አዘዋዋሪዎች መናኸሪያ ይሆናል። ስለዚህ በአፋጣኝ ምላሽ ያገኝ ዘንድ እኛ የአሳይ መምህራን በጋራ እንጠይቃለን።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ