Hugo Chavezታምሩ ገዳ
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዜና እረፍታቸው ለህዝባቸው እና ለመላው ዓለም ይፋ የተደረገው የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ሁጎ ቻቬዝ በብዙዎች ዘንድ አስገራሚ እና አወዛጋቢ ባህሪ የተላበሱ መሪ ነበሩ። ያቺ በላቲን አሜሪካ ውስጥ በተፈጥሮ ጋዝ ሃብቷ ቀዳሚ ስፍራ ያላት ቬንቩዌላን ላለፉት 14 አመታት በሶሻሊስታዊ ርእዮት ዓለም አካሄድ የመሯት ቻቬዝ ላለፉት ሁለት አመታት ከካንሰር ህመም ጋር ውጊያ ቢያደርጉም በተወለዱ በ58 አመታቸው የሚወዱት ህዝባቸውን እና ከብዙዎች አዕምሮ የማይጠፉ አሰገራሚ ትዝታዎቻቸውን ጥለው ወደ ማይቀረው ዓለም ሄደዋል።

 

 

ቻቬዝ በህይወት ዘመናቸው ኑሯቸውን የቀየሩላቸው በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቬንዙዊላዊያን ባለፈው አርብ ዕለት በተካሄደው የአስክሬን ስንብት ሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘት ለታላቁ መሪያቸው ያላቸውን ዘለዓለማዊ ክብር እና ፍቅር ለመገለጽ አብዛኞቹ ከ26 ሰዓታት በላይ ተሰልፈው ተራቸው እስኪደርስ መጠባበቅ ነበረባቸው። እነዚያ የአገሪቱ ቤጫ፣ ሰማያዊ እና ቀይ ቀለማትን ያካተተው ብሄራዊ ሰንደቃ ዓላማን በመልበስ እና በማውለብለብ ወይም የሟቹ ቻቬዝ ምስሎችን በአንገታችው ላይ በማንጠልጠል በዋና መዲናይቱ ካርካካስ ጎዳናዎች ላይ የተሰለፉ የቻቬዝ ደጋፊዎች መሪር ሃዘናቸውን እና እንባቸውን ማፍሰሳቸው አልቀረም።

 

የታላቁ መሪያቸው (የቻቬዝን) አሰክሬን መሰናበት ለአብዛኛው ደጋፊዎቻቸው (ቻቬስታስ) ከመስዋዕቶች ሁሉ እጅግ ትንሿ መስዋዕት ነበረች ማለት ይቻላል። ከዚያ በላይ ማድረግ ቢቻል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት እነዚህ የቻቬዝ ደጋፊዎች ሁሉንም ነገር በፍቃደኝነት ባደረጉት ነበር። አብዛኞቹ የቻቬዝ ደጋፊዎች ለምን ወደ አደባባይ እንደ ወጡ ሲጠየቁ "ወደዚህ ቦታ ማልደን የመጣነው በፍቅር ነው። ይህ ታላቁ መሪያችንን የመሰናበት እድል ጨርሶ ሊያመልጠን አይገባም።" ሲሉ ተደምጠዋል።

 

ቬንዙዌላዊያን የመሪያችውን መሞት እንደሰሙ ሲላቀሱ
(ቬንዙዌላዊያን የመሪያችውን መሞት እንደሰሙ ሲላቀሱ) 

 

ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚቆጠሩ ቬንዙዌላዊያን ርዝማኔው ከአንድ ኬሎ ሜትር በላይ በሚሆነው የዋና መዲናይቱ ጎዳና ላይ ጸሃይ፣ ብርድ፣ ረሃብ፣ የውሃ ጥም ሳይሉ በጽሞና ሲጠባበቁ በቴሌቭዥን መስኮት ለተመለከተ "ተወዳጅ መሪ ማለት እንደ ቻቬዝ ነው" ሳያሰኝ አልቀረም። ጁአና ኡካቲጋ ትባላላች የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር ስትሆን አፍቃሪ ቻቬዝ ከሚባሉት ወገኖች መካከል አንዷ ነች። ጁአና የታላቁ መሪዋን አስክሬንን ለመሰናበት ከተሰላፊው ህዝብ ብዛት የተነሳ ከ15 ሰዓት በላይ ወረፋ መጠበቅ ነበረባት። መቼም መድረሱ አይቀር ተራዋ ሲደርስ ምን እንደተሰማት ለዜና ሰዎች ስትናገር "ወደአስክሬናቸው ስጠጋ መሪር ሃዘን ተሰምቶኝ ነበር፤ ይሁንና ከአስክሬናቸው አጠገብ ስደርስ ያ ዘወትር የሚያጠልቁት ቀዩ የወታደራዊ ኮፍያችውን፣ የደምብ ልብሳቸውን ለብሰው የክብር ሜዳሊያቸውን አጥልቀው ስምለከታቸው ከፍተኛ ደስታ ተስምቶኛል። ቀረብ ብዬ ስመለከታቸው ቻቬዝ እጅግ ውብ ነበሩ" ብላለች።

 

የሰላሳ ዓመቷ ኬምብሬይ ጋርሼያ ሌላኛዋ የቻቬዝ ደጋፊ ስትሆን፤ በቆራጡ መሪዋ መሞት የተሰማትን ሃዘን የገለጸችው "ቻቬዝ ጸሃያችን ናቸው። ቻቬዝ ሰማያችን ናቸው። እርሶን ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል። እንዲያው በደፈናው ዛሬ አገር እንዲኖረን ስላደረጉን እናመሰግንወታለን።" በማለት አፍቃሪ ቻቬዝነቷን ስሜቷን መቆጣጠር እስኪሳናት ድረስ በማልቀስ ገልጻለች።

 

ሁጎ ቻቬዝ በተለያዩ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ባንኮች ውስጥ የሚገኙ ዋጋቸው በብዙ ቢሊዮኖች የአሜሪካ ዶላር የሚገመቱ የቬንዙዌላ ተቀማጭ ወርቆች ከባንኮቹ ወጥተው ወደ አገሪቱ ብሄራዊ ባንክ እንዲቀመጡ ውሳኔ በማስተላለፍ የብሄርተኛነት (ናሽናሊስት) ስሜት በማንጸባረቃቸው፣ በአገሪቱ የሚገኙ የነዳጅ ማምረቻዎች ለደሃው የአገሬው ህዝብ መሰረታዊ ፍጆታዎች ማሙያዎች እንዲያበረክቱ በማድረግ፣ ደሃው ዜጋ ተመጣጣኝ እና አንስተኛ ዋጋ የሚጠይቁ መኖሪያ ቤቶች እንዲኖራቸው በማድረግ፣ የአብዛኛው ደሃው ማህብረሰብ አባት ተብለው ሲጠሩ፤ በምትኩ ቱጃር ቬንዙላዊያኖች ከተስፋ ምኞት ውጪ ለሃብታሞች ያልጠቀሙ የአገሪቱን አንጡራ ሃብት ለፖለቲካ ፍጆታቸው ያደረጉ፣ ኤኮኖሚውን ወደ ተሳሳተ መንገድ እንዲሄድ ያደረጉ፣ ተቃዋሚዎችን የሚደፈጥጡ (አምባገንን) መሪ ናቸው ሲሉ ይወነጅሏቸዋል።

 

እኝህ በህይወት ዘመናቸው ብዙ ወዳጆች (ከዝቅተኛው ማህበረሰብ) እና መጠነኛ ተቃዋሚዎችን ያፈሩት ሁጎ ቻቬዝ የቀድሞው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽን "ሰይጣን" በማለት በአደባባይ በመጥራት ለኃያሏ አገር አሜሪካ ያላቸውን ንቀት ያስመሰከሩ ሶሻሊስታዊ መሪ ነበሩ። በተቃራኒው ቻቬዝ የቀድሞው የኩባ ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮን "መምህሬ እና አባቴ" በማለት ለዚያች ትንሽ አገር የነበራቸውን ልዩ ፍቅር እና ቀረቤታ ከማሳየታቸው በተጨማሪ፤ ኩባ በቀላሉ ከማይነጥፈው የቬንዙዌላ የተፈጥሮ ጋዝ በርካሽ ዋጋ እንዲፈስላት አድርገዋል።

 

Hugo Chavez

ሁጎ ቻቬዝ ለአገራችው፣ ለህዝባቸው እና

ለሰንደቅ ዓላማዋ "ልዩ ፍቅር" ነበራቸው 

ሌሎቹ ጎረቤት አገሮች ኔኳራጓ እና ቦሊቪያ ተመሳሳይ የቻቬዝ ምጽዋተኞች አድርገው የሚቆጥሯቸው ተቃዋሚዎቻቸው የቦሊቪያው ፕሬዝዳንት ኤቮ ሞዳሌ ካለፈው ረቡዕ አንስቶ ከቻቬዝ እስክሬን አጠገብ ባለመለየት የማልቀሳቸው ነገር "እንደ ጨቅላ ህጻን ልጅ ገንዘብ ተከፍሏቸው ያለቀሱ ፕሬዝዳንት" የሚል ስላቅ ተሰልቆባቸዋል። በርካታ አገሮች በቻቬዝ መሞት የተሰማቸውን ሃዝን ለመግለጽ ሲሉ በአገራቸው ብሄራዊ የሃዘን ቀን እስከ ማወጅ ደርሰዋል።

 

በሌላ በኩል ከቻቬዝ ጋር ምንም አይነት የጥቅም ግንኙነት ሳይኖራችው የዓላማ ቁርኝት ብቻ ያላቸው በርካታ የዓለም መሪዎች እና ታዋቂ ሰዎች የቻቬዝ አስክሬንን ለመሰናበት ባለፈው አርብ ዕለት ቬንዚዌላ ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ ከቻቬዝ ጋር የተለየ ቅርርቦሽ የነበራቸው የኢራኑ ፕሬዝዳንት አህመዲን ናጃት የቻቬዝን መሞት ገና እንደሰሙ በግል ድረ ገጻቸው ላይ "ቻቬዝ እንደ እየሱስ ክርስቶስ እና እንደ ሼያቱ ሙስሊም ኤማሙ መሃዲን ሞትን ድል አደርገው በመነሳት ስለ ሰላም እና ፍትህ መስፈን ይሰብካሉ" ማለታቸው በአገር ቤት (ኢራን) ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ቁጣ ያስነሳባችው ቢሆንም "ጽረ- ኤምፔሪያሌስቱ" አህመድ ነጃት በቬንዙዊላ ቆይታቻው የቻቬዝ አስክሬን በእጃቸው በመዳሰስ እና የራሳቸው የቀኝ እጅ ወደ ላይ ከፍ በማድረግ እርሳቸው ሆኑ አገራቸው ኤራን ቻቬዝን ለዘላለም የማትረሳ መሆኗን ለታዳሚው ለማሳይት ሞክረዋል። የኤራኑ መሪ አቀራረብ ምንም እንኳን የፕሮቶኮል ሂደቱን የጣሰ ቢሆንም በርካታ እንግዶች ድጋፋቸውን ለአህመድ ነጃት ከመስጠት አለተቆጠቡም።

 

የቻቬዝን ወንበር በጊዜያዊነት በቃለ መሃላ የተረከቡት ምክትላቸው ኔኮላስ ማደሮ በበኩላቸው ሲቃ እየተናነቃቸው "ጓድ ቻቬዝ ዛሬ አልተሸነፉም። ለዘለዓለም ይኖራሉ!" ሲሉ ተናግረዋል። ሀዘንተኛውም በበኩሉ "ቻቬዝ ለዘላለም ይኑሩ! ትግሉም ይቀጥላል!" በማለት ጠንካራ ሶሻሊስታዊ አቋሙን ገልጿል። በነገራችን ላይ የኤራኑ መሪ እና ከፍተኛ የቬንዙዌላ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በርካታ አፍቃሪ ቻቬዞች በቆራጥ እና ብሄርተኝነት አቋሟቸው ከምዕራባዊያኖች አካባቢ ጠላት እንዳተረፉ የሚነገርላቸው ቻቬዝ ለሞታቸው መንስኤው የተፈጥሮ ህመም ብቻ ሳይሆን የአሜሪካኑ የስልላ ድርጅት የሆነው (ሴ.አይ.ኤ) እና የእስራኤሉ አቻው (ሞሳድ) እጆች ሳይኖርበት አይቀርም ከሚል ጥርጣሬ ላይ የደረሱ ሲሆን፣ ለዚህ አባባላቸው እንደማስረጃ የሚያቀርቡት የቀድሞው የኩባ ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮን ለመግደል ተሞክረው የከሸፉትን በርካታ የግድያ ሙከራዎችን ይጠቅሳሉ። ሁኔታውም እንዲጣራ ቬንዙዌላ ውስጥ ምርምር ተጀምሯል።

 

የቬንዙዌላ መንግስት የቻቬዝ አስክሬንን እንደ ቀድሞው የራሺያው ቭላዲሜር ሌኒን እና ጆሴፍ ስታሊን እንዲሁም፣ እንደ ቻይናው ኮሚኒስት መሪ ማኦ ዘእይቱንግ ሳይፈራርስ በመስታወት ውስጥ በማድረግ ህዝቡ እና ቱሪስቶች እየመጡ በክብር እንዲጎበኙት ውሳኔ አስተላልፏል። የላቲን አሜሪካ ፖለቲካን በብዙ መልኩ የቀየሩት ሁጎ ቻቬዝ አገራቸው ድህረ ቻቬዝ ምን አይነት የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ፖሊሲን ትከተል ይሆን የሚለው ጥያቄ ዛሬም ነገም በጥያቄነቱ የሚዘልቅ ይመስላል። ቬንዙዌላ አዲስ ፕሬዝዳንት ለመምርጥ በመጪው ወር ሜያዚያ 14 ቀን 2013 እ.ኤ.አ. የቀን ቀጠሮ ይዘዋል። ምርጫው ምን ሆነ ምን አንድ ነገርን በቅድሚያ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። እርሱም ቻቬዝን የሚተካ ደፋር፣ ከግል ጥቅሙ ስለህዝቡ ኑሮ መሻሻል የሚጨነቅ እና በፈገግታው እና በአነጋገሩ የብዙሃኑን ቀልብ የሚስብ መሪ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው።


ታምሩ ገዳ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ