ቸሩ ላቀው
ለሀገር መሪነት የሚመረጥ ሰው በሁለ መልኩና ዘርፉ ሀገርን ሊመራና ሊያስተዳድር ይችላል ተብሎ እምነት የተጣለበት፣ ሀገር ወዳድ፣ ሕዝብ አክባሪና ተከባሪ የሆነ፣ ለሀገሩ ሟችና ተቆርቋሪ የሆነ፣ የሀገሩን ዳር ድንበር የሚያስከብርና ኅሊናውን ለንዋይ ያልሸጠ፣ ለኃያላን መንግሥታት አጎብዳጅና ተላላኪ ያልሆነ እንጂ እንዲያው ካጠገባችን ዞር ይበልልን፣ ሔዶ ይጠቀምልን፣ በልቶ ያብላን፣ ሰርቆ ያሰርቀን፣ ወዘተ ተብሎ መምረጥ ቀርቶ ለምርጫውም መቅረብ የሌለበት ጭንጋፍ ሰው ነው።

 

 

እንኳን ዘጠና ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ መምራት ቀርቶ ቤተሰብ መምራትም እንደ ቀላል ተግባር የሚታይ አይደለም። ቤተሰቡን ማስተዳደር ያልቻለ ሀገር መምራት ስለማይችል ማስተዳደር መቻልም ከቤት ይጀምራል። ይኸንን በመሰለውና በሌሎችም መስፈርቶች ከላይ እስከ ታች ያሉ የወያኔ መሪዎችና ባለሥልጣናት ባለፉት ሃያ አንድ የስቃይና የግፍ አገዛዝ ዓመታት ባሳዩት ተግባሮቻቸው የሀገር አለኝታ ሆነው መመረጥ ቀርቶ በማንኛውም ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ አይደሉም።

 

ከውጭ መንግሥታትና ብድር ሰጪ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ገንዘብ ተበድረው የፈለጉትን ያህል ዘርፈውና አስዘርፈው በተረፈው ገንዘብ መንገድ ተሰርቶላችኋል ይሉናል። መንገዶቹ የሚሰሩት በኢትዮጵያ ሕዝብ የልጅ ልጅ ዕዳ ነው። የሚሰሩትም መንገዶች በወያኔ ድርጅቶችና በሚያቀርቡትም የግንባታ ቁሳቁሶች ነው። ሠሪዎቹም የወያኔ ድርጅቶችና የካድሬዎቻቸው ድርጅቶች ናቸው። በመሆኑም በራሳችን ገንዘብ በራሳችን ላይ የባሪያ አሳዳሪ ጌቶቻችንን እያበለፀግን መሆኑ ነው። መንገዶቹ ቢሠሩም የሚሸረከሩባቸው እነርሱ ናቸው። እኛማ ስለአደኸዩንና ስለአስራቡን አንጀታችን ከወገባችን ጋር ተጣብቆ እንኳን መኪና ገዝተን ልናሽከረክርባቸው ቀርቶ በአውቶቡሶችና ታክሲዎችም ልንሔድባቸው አቅማችን አልፈቀደም፣ አልቻልንም። ወደ ኋላ ወደ ጥንቱ ተመልሰን በረባሶ ጫማዎቻችንን እየሰፋን ነው በእግራችን የምንጓዘው። የበይ ተመልካች ሆነናል። ሸቀጥ አምላኪዎች ሆነናል።

 

አዲስ አበባን ሕንፃ በሕንፃ አደረግንላችሁ ይሉናል። አዎ ካድሬዎቻቸውና ወታደራዊ መኮንኖቻቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ገንዘብ ዘርፈው ሰማይ-ጠቀስ ፎቆች ያሏቸው ቤቶች ገንብተዋል፣ እየገነቡም ናቸው። እኛ ግን ጎጆ መቀለሻ ቦታና ገንዘብ የለንም። የነበሩንን ጎጆዎቻችንን አፍርሰውና ቦታውን ቀምተውን ወደ ሜዳ ጥለውናል። ለሰው ልጅ ኑሮ ከሆኑት መሠረታዊ ነገሮች አንዱ መጠለያ ነው። በወያኔ አገዛዝ ይኸንን ስለተነፈግን ከሰውነት ደረጃ ወርደን እንደ ጥንቱ የሰው ልጅ ኑሮ አውላላ ሜዳ ላይ ለመኖር ተገደናል።

 

የወያኔ መሪና አባላቱ ለራሳቸውና ለካድሬዎቻቸው ብቻ የቆሙ ስለሆኑ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለድህነት ዳርገዋል። እነርሱ ፖለቲካውንም፣ ኢኮኖሚውንም፣ ማኅበራዊ ዘርፉንም ስለያዙና አጠቃለውም በነርሱ ቁጥጥር ሥር ለማድረግ ሌት ተቀን እየለፉና እየሠሩ ስለሆነ እንድናጣ፣ እንድንደኸይና በነርሱ በጎ ፈቃድ ነዋሪዎች እንድንሆን አድርገውናል። ታዲያ ያጣን ድሆች ሆነን በተረሳንበት፣ በተገለልንበትና እየተራብን ባለንበት ሁኔታ ኢኮኖሚው አድጓል እየተባልን፣ እየተራብን መንገድ እናሠራችኋለን እየተባልን፣ ሳንጣላ እነርሱ በሥልጣን ላይ ከሌሉ ይጨርሱአችኋል እየተባልን፣ እምነታችንን ተቀምተን በማናውቀውና በማንፈልገው አምልኩ እየተባልን፣ የሃይማኖት መሪዎቻችንን እንምረጥ ስንል እኛ መርጠን በምንሾምላችሁ መተዳደር አለባችሁ እየተባልን፣ ወዘተ ስለሆነ በሚነግሩን ብቻ ተማምነን ድምፃችንን ከመስጠት እንቆጠብ። ማየት ማመን ስለሆነ ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ማንነታቸውን በግላጭ አይተናልና ደጋግመን መታለል የለብንም።

 

ማየት፣ መስማት፣ ማሽተት፣ መዳሰስና መቅመስ የተባሉ የስሜት ሕዋሳቶች ስለአሉን ባለፉት ሃያ አንድ የአፓርታይድ ማለትም በዘር ለያይቶ የመግዛት ፖሊሲአቸው የወያኔን ማንነት ጠለቅ አድርገን በጆሮአችን ከመስማትም አልፎ በገሃድ አይተናል። የእሬሣ ክምር ሽታ አሽትተናል። ችግርን ቀምሰናል፣ እየቀመስንም ነው። የችግሮች ሁሉ ቤተ ሙከራ አድርገውን ቀምሰናል፣ እየቀመስንም ነው። የመከራና የችግሮቹም ብዛት አልዋጥ እያሉ እያንገሸገሹንና እየተናነቁን ናቸው።

 

ከመምረጥ ሂደት ጋር ባለፉት ተደጋጋሚ ዓመታት በርካታ ትዝብቶችን ያየንና ችግሮቹንም እኛው ተመልሰን የተሸከምናቸው እንደሆኑ ሳንገነዘብ የቀረን አይመስለኝም። አንዳንድ ሁኔታዎቹ ግራ ያጋቡአቸው የቤት እመቤቶች ወደ ምርጫው ሲሔዱ "እነርሱ እንዳቦኩ ራሳቸው ይጋግሩ እንጂ ሌሎቹ ምን በወጣቸው አነርሱ በፈጠሩት ችግር ውስጥ ገብተው መግቢያና መውጫ በሌለው ችግር ይዳክሩ" እያሉ ድምፅ የሚሰጡ ነበሩ። ግን ስህተት ነበር። መምረጥ ካልፈለጉ ምንም ወያኔ ቁጥሩን አባዝቶ በዚህ ያህል ድምፅ አሸነፍኩ እንደሚል ቢታወቅም ለኅሊና እርካታ አለመምረጡ ይመረጣል። ድምፃችንን በምርጫ ካርድ በምንሰጥበት ጊዜ ማንን እንደመረጥን የምናውቀው እኛው ራሳችን ብቻ ስለሆን የወያኔ አምላክ ያየናል ብለን ለዚያች ለሰጡን ጉቦ አንፍራ። ይሉኝታ አይያዘን። የወያኔ አምላክ ሰይጣን ነው። ሰይጣንን አንፍራ። ለመምረጥና ላለመምረጥ መብታችን ስለሆነ በመብታችን ጠላት አንግዛ። ጠላትን ማስወገድ እንጂ ማቅረብ ተገቢ አይደለም። ካላስወገድነው እኛኑ ነው መልሶ የሚጎዳን። ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ምን ያህል እንደተጎዳን አይተናል፣ ቀምሰናል። ስለሆነም ሁልጊዜ መታለል ይቅርብን።

 

ባለፉት ሃያ አንድ የወያኔ የመከራና የጭቆና አገዛዝ ዘመን ብዙ ምርጫዎች ተካሂደው አጎብዳዶቻቸው ተመረጡ እየተባሉ በየቢሮአቸው ተቀምጠው ወንበሮቻቸውን ያሞቃሉ። በመሆኑም የመረጡአቸውን ወገኖቻቸውን ወክለው የማይቆሙና ችግሮቻቸውን ከሚመለከታቸው ጋር ተወያይተው የማይፈቱላቸው ከሆነ፣ በሕዝቡ ስም ቢሮ ተቀምጠው ከሕዝቡ ከሚሰበሰበው ግብር ዳጎስ ያለ ደመወዝ እየተከፈላቸው የወያኔን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም የሚጠብቁትና የሚያስጠብቁት ከሆነ፣ ከወያኔ ጋር አብረው ተቀምጠው የወከሉአቸውን ወገኖቻቸውን መልሰው የሚያስሩ፣ የሚገርፉ፣ የሚያሰቃዩና የሚገድሉ ከሆኑ፣ በሕዝቡ ስም እዚያ ተጎልተው ሀገር የሚያስማሙና የሚሸጡ ከሆኑ የኛ መምረጥ ከወንጀለኞች ጋር መተባበር ስለሚሆን ደግመን ደጋግመን ማሰብ ይኖርብናል። የግፍ አገዛዝ ዘመን በቃ እንበል። የጭቆና አገዛዝ ዘመን በቃ እንበል። ሀገራችንን የሚሸጡትን በቃችሁ እንበላቸው። መከራው ከምንሸከመው በላይ ስለሆነ መሸከሙ በቃ እንበል። ነፃነታችንን አስከብረን በነፃ እንኑር እንበላቸው። እነዚህን ሁሉ ለመግለጽ የምንችለው በመብታችን ተጠቅመን አንመርጣችሁም ስንላቸው ነው።

 

ለመምረጥም ሆነ ላለመምረጥም መብታችን የተጠበቀ ስለሆነ ጠላቶቻችንን በኛው ላይ መርጠን አናስቀምጥ!
ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለሀገሩ ዘብ ይቁም!
ቸሩ ነኝ በቸር ይግጠመን!


ቸሩ ላቀው
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ