ተገፊዎች የባህሪ ለውጥ አምጡ እንጂ!
ገለታው ዘለቀ
ልትታተም ካሰበች አንዲት ልቦለድ ጽሁፍ ላይ አንድ የምናብ ሰው ከተገረመበት ነገር ተነስተን አጭር መልእክት ለማቀበል እንሞክራለን። ይህ የምናብ ሰው ወደ አንድ ሃገር ይሄድና በዚያ በአንድ ሆቴል ውስጥ ተቀምጦ ናሽናል ጂኦግራፊ የተሰኘውን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ያያል። በወቅቱ ይተላለፍ የነበረው ፕሮግራም የዱር እንስሶች ኑሮ ነው።
ይህ የምናብ ሰው ከአልጋው ጫፍ ላይ ቁጢጥ ብሎ ረጃጅም ጢሙን ቁልቁል እየላገ ይህን ፕሮግራም ያያል። የሚያማምሩ የሜዳ አህያዎች መንጋ ረጋ ብሎ ሳሩን ይግጣል። ጥቂት ሳይቆይ ከረጃጅሙ ሳር ውስጥ ሲሹለከለኩ የነበሩ ሶስት ጅቦች መጡ። አንዱን ጅብ ቀድሞ ያየው የሜዳ አህያ ሩጫውን ሲቀጥል ሌላው ነገሩ ያልገባው ሁሉ ተከትሎ ይሰግር ጀመር።
የሜዳ አህያዎቹም ተፋፍገው ሲሮጡ አንድ ወደ ሁዋላ ቀረት ያለ የሜዳ አህያ ነበርና አንዱ ጅብ ከሆዱ ቆዳውን ሊዘነጥል ይጥራል። ይህ የሜዳ አህያ እግሮቹን እያወራጨ ለማምለጥ ይጥራል። ትግሉ ከሚሮጡት ጋር ሩጫውን ለመቀጠል እንጂ የሚነክሰውን ጅብ ለመጉዳት አይደለም።
ሌሎቹም ጅቦች ተጋገዙና ምን ዋጋ አለው ይህን የሜዳ አህያ ሆዱን ዘረገፉት።
ያ የምናብ ሰው ተገረመ። አየ ኑሮ ...
ወደ ሌላ አንዲት ወንዝ ስር ጥሙን ሊያረካ ውሃ ከሚጠጣ ሌላ ያማረ የሜዳ አህያ ጋር ካሜራው ወሰደው። ይህ የሜዳ አህያ ሁለት የፊት እግሮቹን ፈርከክ አርጎ እንዴው እግዜር የሰጠውን ውሃውን በፍቅር ይስባል። ጥቂት ሳይቆይ አንድ ሌላ ጅብ ከሁዋላው ዘሎ ከሆዱ ቆዳውን ሊዘነጥል ትግል ጀመረ። ይህ የሜዳ አህያ ከወራጁ ወንዝ ጫፍ ላይ ተክሎት የነበረውን አፉን ነቀል አረገና ወደ ሁዋላ በቅጽበት ዞረ። የሚታገለውን ጅብ እንደሌሎቹ የሜዳ አህያዎች በርግጫ ብሎ ለማምለጥ አይጥርም። አንገቱን ጠምዝዞ አንድ ሁለቴ ዞረና ወደ ሆዱ ገብቶ ቆዳውን ሊዘነጥለው የሚታገለውን ጅብ ጉሮሮ አስግጎ አገኘውና በዚያ ላይና ታች ክችም ባለ ጥርሱ የጅቡን ጉሮሮ ቀርጥፎ ይዞ ትግል ተጀመረ። አሁን ጅብ ማጥቃቱን ትቶ ራሱን ለማዳን እየታገለ ነው። ነገር ግን አልሆነም። ይህ የሜዳ አህያ የዋዛ አልነበረም። ጥቂት ደቂቃዎች ከታገሉ በሁዋላ ጅቡ መታገሉን ሲያቆም የሜዳው አህያ ሙሉ በሙሉ ከሜዳው ላይ አንጋለለውና ያየው ጀመር። ጥቂት አሸተተውና ጥሎት ለመሄድ ርምጃ ሲጀምር አንድ ሌላ ጅብም መጣ። ያ የሜዳ አህያ በሃይል ወደ ጅቡ መሮጥ ሲጀምር ጅቡም ቂጡን ጥሎ ሮጠ።
የምናቡ ሰው ይህን ነገር እያየ ተገረመ። ለካ ይሄ የሜዳ አህያ ብቻውን በዚህ ጠራራ ጸሃይ በዚህ ወንዝ ሥር የሚያንቀባርረው የባህሪ ለውጥ አምጥቶ ነው። እየተራገጡ መሮጥን አቁሞ መናከስ ጀምሩዋል። ይህ የባህሪ ለውጡም ከተጠቂነት ወደ አጥቂነት አሸጋግሮታል እያለ ይደነቃል ...
በአንድ ሃገር የሚኖሩ ህዝቦች አንዳንዴ ጅብ በሆነ ስርዓት ይጠቃሉ። ጥቂት ቡድኖች ያለውን የሃገሪቱን ሃብት ተቆጣጥረው አብዛኛውን ሰው ጦሙን ያሳድሩታል። የኢኮኖሚው ሰፊ ልዩነት ሌሎች የህይወት ዘርፉን ሁሉ ያጠቁትና ያልተመጣጠነው እድገት በፍትህ ፊት፣ በባህልላዊ ቡድን፣ በአጠቃላይ በኑሮ ዘየ ሁሉ ከባድ የእኩልነት እጦትን ይስብበታል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ቢሊየነር ሁሉ ያላት አገር ናት። በሌላ ጥግ ደሞ የ ዓለምን የመጨረሻ ድህነት የሚኖሩ ብዙ ህዝቦችም አሉባት፣ ይህ ሰፊ ያልተመጣጠነ እድገት በተወሰነ ደረጃ ቢሳለጥ አሁን ያለው የድህነት ገጽታ መልኩን ይቀይር ነበር። የገቢ አለመመጣጠን ስንል ሁሉ እኩል ይካፈል ማለታችን አይደለም። ሁላችን እኩል በመካፈላችንም ፍትህ አይሰራም። ግን ደሞ ለሃብታሙ ህንጻ የሚሰራው ወዛደር ቢያንስ ቤት አከራይቶ የቀን ኑሮውን የሚገፋበትን ሊከፍለው ይገባል። ቀን ቀን አሸዋና ሲሚንቶ ሲያቦካ ውሎ ለምን ጎዳና ላይ ይወድቃል? መንግስትስ እንዲህ ያለውን አስከፊ ስርዓት ለምን በተወሰነ ደረጃ አያጠብም? ለምን ፖሊሲ አያወጣም?። የካፒታሊዝም ጽንሰ ሃሳብ እኮ እንደዚህ አይደለም። ካፒታሊዝም ፍትህ አለው። ዜጎች ባላቸው የሥራ አቅም እየሰሩ የተለያየ የገቢ መጠን መኖሩ ትክክል ነው። ይሁን እንጂ ድሃውን ያለልክ ጎድቶ ሃብታሙን ያለልክ ማበልጸግ የካፒታሊዝም ስርዓት ልብ አይደለም።
የሚገርመው ስርዓቱ ፍትሃዊ ባይሆንም እነዚህ ዜጎች አይናከሱምና ኑሮአቸው ሁሉ የሚያሳዝን ይሆናል።
ደሞ መንግስት ሥራ ጠፋ ሲሉት ሥራ ንቃችሁ ነው አይነት ይናገራል። ተናቀ የተባለው ስራ ምንድን ነው? ብላችሁ ብትጠይቁ ያው የወዛደርነት ሥራ ነው። የመጀመሪያው ጥያቄ ታዲያ አሁን ይህ ሚሊዮን ሥራ አጥ በቃ ሥራ አንንቅም እሺ ወዛደርነቱን እንሥራ ብሎ ቢወጣ ይህንን የሚያስተናግድ ኢንዱስትሪ ወይም የኮንስትራክሽን ስራስ የታለና ነው? የትኛው የፋብሪካ ስራ ወይም የኮንስታራክሽን ስራ በወዛደር እጦት ስራ አቆመ?
እውነቱን ለመናገር አንዳንድ ሰው ወደ ወዛደርነት ስራ የማይሳበው ገቢው ስላነሰ ወይም ስለማያኖረው ነው። በሃገራችን ውስጥ የሲቪል ኤንጂኔር ስራ ስለምን ተከባሪ ሆነ? ባህላዊው ሲቪል ኤንጂነር (አናጺው) የተከበረ ነበር ወይ? ብለን ብንጠይቅ አልነበረም። "አናጢ መናጢ" ነበር የሚባለው። ምንም የሌለው ድሃ ማለት ነው መናጢ ማለት። ሁዋላ ላይ ታሪክ ተቀየረና ዘመናዊ ትምህርት ተምረው የመጡ አናጺዎች (civil engineers) ገቢያቸው ዳጎስ ያለ በመሆኑና የነሱን ኑሮ ብቻ ሳይሆን የቤተሰባቸውን ህይወት የሚቀይር ገቢ ስላላቸው ተወደዱ።
በድሮ ጊዜ፣
"የኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ
ወሰደሽ አስተማሪ ..." ይባል ነበር አሉ።
በኔ ጊዜ አስተማሪ ለትዳር የማይመረጥበት ጊዜ ስለምን ሆነ? ያው ከኑሮው ጋር ከገቢው አቅም ጋር ተያይዞ ነው።
ያ የሜዳ አህያ ዘይዱዋል። የባህሪ ለውጥ በማምጣቱ ተከብሮ ከተባራሪነት ወደ አባራሪነት ተሸጋግሩዋል። የተባረከ ነውና የጅቡን ስጋ ግን አይበላም። እነዚህ እንስሳት እንደዚህ የሜዳ አህያ የባህሪ ለውጥ ቢያመጡ ያ ጅቡም ቅጠላቅጠል መብላት ይጀምርና የነዚህ እንስሶች መንደር ሰላም ይወርድበታል። መከባበር፣ መተሳሰብ ይመጣና አብረው ይኖራሉ። ጅብና የሜዳ አህያ ሳይጠራጠሩ ተቃቅፈው ያድራሉ።
ድሆች በኢትዮጵያ ውስጥ የባህሪ ለውጥ ሊያመጡ ይገባል። እነዚህ በሙስና የከበሩ ሚሊየነሮችና ቢሊየነር ኢትዮጵያ ውስጥ ስንት ፊላንትሮፒክ ወይም ሰባዊ የሆነ ድርጀት እንዳላቸው ወይም እንደሚረዱ አላውቅም። ርሃብ ሲመጣ አለማቀፍ ድርጅቶች ናቸው ስንዴና ዘይት ለማቅረብ ሲሮጡ የሚታዩት።
ዛሬ ሃገራችን ባልተመጣጠነ እድገት ጎዳና ላይ እየነጎደች ነው። ያለው እየጨመረ፣ የሌለው የሚበላው እያጣ ወጣቱ ጢሙን አንዠርግጎ የጡረታ አባቱን ቤት ሳይለቅ እየኖረ ነው። ካልተናከሰ እንዲሁ ይኖራል። መናከስ ከጀመረ የባህሪ ለውጥ ካመጣ ግን ተከብሮ፣ መብቱ ተጠብቆ ይኖራል።
አንድ ጊዜ ትዝ ይላችሁ እንደሆነ የ ኢትዮጵያ ጦር ላይቤሪያ ዘምቶ ነበር። በዚያ ቆይታው ዩናይትድ ኔሽን (UN) ዳጎስ ያለ አበል ያስብለት ነበርና ይህንን አበሉን የኢትዮጵያ መንግስት እኔ አከፋፍላለሁ ብሎ ነው መሰለኝ ይቀበላል። ተቀብሎ ለወታደሮቹ ማካፈል ነበረበት። ይሁን እንጂ ይሄ የጅብ ባህሪ ያለው አሰራራቸው ባህሪ ሆኖባቸዋልና ያንን ገንዘብ ቆይ ዛሬ ቆይ ነገ እያሉ ያቆዩባቸዋል። መንግስትን የሚያህል ትልቅ ነገር የነዚያ የድሃ ወታደሮች አበል አጓጉታው አልሰጥም ብሎ ቆየ። ከተዘራፊዎቹ አንዱ መንግስት ዘረፈኝ ብሎ አስቆናል። እንግዲህ ይታያችሁ ዩናይትድ ኔሽን ለሰጠው መንግስት ቀንቶ እነዚያን ድሆች ቀማ። ሁዋላ ላይ ግን እነዚህ ወታደሮች አምጸው እንደነበር ዜና ሰምተናል። መንግስትም ደንግጦ እሰጣለሁ ብሎ ነበር መሰለኝ። መናከስ በመጀመራቸው እንጂ መንግስት የልፋት ዋጋቸውን ነጥቆ አፍንጫችሁን ላሱ ብሎ ነበር። በጠራራ ጸሃይ መንግስት እንዲህ አድርጎ ድሆችን የሚቀማባት አገር ናት ኢትዮጵያ።
ቸሩን ያሰማን ጃል!
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.