ግርማ ካሳ

በዳያስፖራ ቀንደኛ የኢሕአዴግ ደጋፊና የኢሕአዴግ ደጋፊዎች አስተባባሪ የሚባሉት፣ የሲቪሊቲ ፓልቶክ ክፍል ዋና አድሚን፣ አቶ ብርሃኑ ዳምጤ (አባ መላ) ከአውራምባ ታይምሱ ዳዊት ከበደ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አደመጥኩ። አባ መላ ጠንካራ ትችት በኢሕአዴግ ላይ ሰንዝረዋል። ይሄም ብዙዎችን ሳያስገርም አልቀረም። "አባ መላ፣ አራዳ ነው፤ ወያኔ ሊወድቅ ሲል ፍሬቻ አብሮቶ ታጠፈ" ያሉም አሉ። ፡) ፡) እኔ ግን ብዙ አላስገረመኝም።


አባ መላን ጨምሮ በርካታ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ገዢውን ፓርቲ የሚደግፉት በሚደረጉ የልማት እንቅስቃሴዎች እንጂ፣ በዴሞክራሲና በሰብአዊ መብት መከበር ረገድ ብዙ ቅሬታዎች እንደነበሯቸው ስለማወቅ።


አባ መላን ጨምሮ በርካታ የሲቪሊቲ ክፍል አድሚኖች፣ ገዢውን ፓርቲ ይደግፉ እንጂ፣ ገዢው ፓርቲ በሚያደርጋቸው የተሳሳቱ ተግባራት ላይ ተቃውሟቸውን ያሰሙበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። ኢሕአዴግ በልማቱ ረገድ የሚያደርገውን እየደገፉ፣ በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብት ረገድ የሚደረጉትን ስህተቶች ግን ብዙ ጊዜ ሲቃወሙ ሰምቻቸዋለሁ። ፓርቲው እንዲያሻሻል፣ አንዳንድ ጎጂ ፖሊሲዎቹንም እንዲቀይር፣ ውስጥ ውስጡን ግፊት ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው።


አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። ከአራት አመታት በፊት ሰኔ ወር 2001 ዓ.ም ላይ ነው። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በግፍ የታሰረችበት ወቅት። አቶ ስብሐት ነጋ በሲቪሊቲ ፓልቶክ ክፍል እንግዳ ሆነው ይቀርባሉ። በወ/ት ብርቱካን መታሰር ደስተኛ ያለሆኑትና ለመፈታቷ አጥብቀው ውስጥ ለውስጥ ሲታገሉ የነበሩት አባመላ፣ በገዢው ፓርቲ ላይ ያለቸውን ተቃውሞ በይፋ ገለጹ። ብዙ ታዳሚ ባለበት፣ አቶ ስብሃት ነጋን የሚከተለውን ጠየቁ፡-


"አንዳንድ ጊዜ ከኢሕአዴግ በኩል፣ በዳያስፖራው የኢሕአዴግን ደጋፊዎች ሁሉ ሳይቀሩ፣ criticise የሚያደርጉት popular ያልሆኑ ነገሮችን ትወስዳላቹህ። አላስፈላጊ የሆነ። ለምሳሌ በቅርቡ በብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደው እርምጃ ምንም እንኳን ጥፋት አጥፍታለች ቢባልም ቴክኒካሊ፣ አስፈላጊ ያልሆነ confrontation ነው። ብዙ የምንሰራው፣ እንደ አገር የምንሰራው ብዙ ነገር አለ። በሕግ አንጻር ሁሉን ነገር እንደ ሌጦ መተርጎም የለብንም። ሌሎች moral values የሕዝብ አስተያየት የመሳሰሉ ነገሮችን ግምት ውስጥ አስገብቶ ማየት ይገባል። የአንድ ጠንካራ መንግስት መለኪያው እርሱ ነው ብለን እናምናለን። ምን አልባት እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች፣ implication ያላቸውን ጉዳዮች avoid ለማድረግ በኢሕአዴግ በኩል አንዳንድ ድክመት አለ። በሕዝብ ታዋቂ የሆኑ፣ በጥሩም ሆነ በመጥፎ ተወዳጅነት ያላቸው የሙዚቃ ሰው ሊሆን ይችላል። ስፖርተኛ ሊሆን ይችላል። ወይም የፖለቲካ ሰው። በተለይ የብርቱካን ጉዳይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እርስዎም እንደሚያወቁት፣ የሴቶች ታጋዮች ሚና በጣም በጣም ትንሽ ነው። በተቃዋሚም እንኳን ብትሆን "በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ" ብላ የገባች እስከሆነች ድረስ፣ በአምጽ የሚታገሉትን ተቃውመን፣ ጠመንጃ ከሻቢያ ጋር አንስተው ግለሰቦችን ለመግደል፣ ተቋሞችን ለማፍረስ፣ የሚንቀሳቀሱትንም እያወገዝን፣ በሰላም "አገሬ ውስጥ ሕግና ሕገ መንግስት አለ። መንግስትን ፊት ለፊት እታገላለሁ" ብሎ የገባውንም ኃይል እኩል treat ማድረግ የለብንም። በተለይ ሴት በመሆኗ፣ የልጅ እናትም በመሆኗ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶችን ሚና ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ እምነት አለው ብዬ ስለማምን፣ ኢሕአዴግ በእንደዚህ አይነት ሰዎች ላይ የምትወስዱት እርምጃ በምንም መልክ defend ልናደርግ፣ justify ልናደርግ እያቃተን ነው። ከእንደዚህ አይነት unpopular ድርጊት መቼ ነው ኢሕአዴግ የሚገደበው? ይሄን ጉዳይ በቅርቡ ለመፍታት የታሰበ ነገር አለ ወይ?"


አንድ የሕወሃት ታጋይ የነበረ ወዳጅ አለኝ። በእስረኞች መታሰር ዙሪያ ያለኝን ምሬት አደመጠና እንዲህ አለኝ "ወንድሜ ግርማ፣ አንተ በምትለው እስማማለሁ። ኢሕአዴግ ውስጥ ብዙ ችግር አለ። እኔ ጦርነት ላይ ጓደኞቼ ሲሞቱ አይቻለሁ። በርሃ ገብተን የታገልነው ግፍን በመቃወም ነው። አሁን ግፍ በሕዝብ ላይ እንዲሰራ አንፈልግም። ኢሕአዴግ ለውጥ ማድረግ አለበት። ኢሕአዴግ ማሻሻያ እንዲያደርግ ሁላችንም እንጣር። አንዳንች አንዳችንን እንደጠላት በማየት ሳይሆን ለአገራችን የጋራ ጥቅም አብረን እንስራ" ነበር ያለኝ። እኔም ተስማማሁ።


እንግዲህ እነዚህ የሚያሳዩት ብስለት ከማጣት የተነሳ፣ የኢሕአዴግ ደጋፊዎችን ሁሉ በአንድ ጨፍልቆ ማየት ትክክል እንዳልሆነ ነው። በጣም ብዙ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች፣ ኢሕአዴግ የሚያደርጋቸውን የልማት እንቅስቃሴች እየደገፉ በዴሞክራሲና በሰብአዊ መብት መከበር ዙሪያ ለውጦች እንዲደረጉ፣ ውስጥ ውስጡን ግፊት የሚያደርጉ አሉ። በባለስልጣናቱ "እናሻሽላለን፣ ድክመታችን እናርማለን ..." እየተባሉ፣ ከዛሬ ነገ መሻሻሎች ይመጣሉ በሚል ሲጠባበቁ የነበሩ ናቸው። ለዚህም ነው አብዛኞቻችን "በኢሕአዴግ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ ከኢሕአዴግና ከደጋፊዎቹ ጋር መሰዳደብ ሳይሆን በጨዋነት መነጋገር አለብን። በኢሕአዴግ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የሚሰሩ ኢሕአዴጎችን ማበረታታ አለብን" ስንል የነበረው። ይሄ ጥረታችንም ነው "ወያኔ" ሲያስብለን የነበረው።


በነአባመላ እንዳየነው፣ የብዙ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ትእግስት እየተሟጠጠ የመጣ ይመስለኛል። በተለይም በሰብአዊ መብት መከበርና በዴሞክራሲ ዙሪያ፣ እንኳን መሻሻል ሊኖር፣ እየበሳስበት መምጣቱን፣ በፓርቲው ያሉ የበሰሉ ሰዎች ወደ ጎን እየተገፉ በአንጻሩም የጫካ አስተሳሰብ ያላቸው፣ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝንም አላሰራም ያሉ፣ የአስተሳሰብ እንጭጮች አይለው መውጣታቸውን እና ኢሕአዴግ በራሱ ሰዎች ከሕዝብ ጋር በየጊዜው እየተጋጨ፣ በውስጡ እየተሸረሸረ አደገኛ ሁኔታ ላይ መሆኑን የታዘቡ ይመስላል። የታቀዱ የልማት እንቅስቃሴዎች ከግቡ እንዲደርሱ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ.፣ የታሰሩ የሕሊና እስረኞች እንዲለቀቁ፣ ከሙስሊሞች ጋር ያለው ችግር በሰላም እንዲፈታና በአገራችን እርቀ ሰላም እንዲወርድ ለማድረግ፣ ኢሕአደግ ውስጥ ያሉ እንክርዳዶች መወገድ እንዳለባቸው የተረዱ ይመስላል።


በመሆኑም በኢሕአዴግን ውስጥ ያሉ ስልጣን የጨበጡ አክራሪዎችን ለመታገል፣ ከወሬ ያለፈ፣ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ጀምረዋል። ከፍተኛ ገንዘብ የማሸሽ እንቅስቅሴ እየተደረገ እንዳለ የጠቆሙት፣ የሲቪሊቲ አድሚኖች በዴንቨርና በዲሲ፣ 1 ዶላር በ27 ብር እንደሚመነዘር፣ አገር ቤት ያሉ አንዳንድ ግለሰቦችም እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር ወደ ውጭ ለማሸሽ፣ በአገር ቤት 27 ሚሊዮን ብር ለመክፈል እየሞከሩ እንደሆነ ይናገራሉ።


በአሜሪካና በካናዳ እንዲሁም በለንደን ፣ በዚያ መኖር ከጀመሩ አንድ አመት ባልሞላቸው ሰዎች የተገዙ ከ300 ሺህ ዶላር በላይ የሚያወጡ በርካታ ቤቶች ፣ (ሃብታሞች በሚኖሩባት በኦሬንጅ ካውንቲ ካሊፎርኒያ ብቻ የታወቁ፣ ወደ አራት የሚሆኑ ቪላ ቤቶች) እንዲሁም የተከፈቱ በርካታ ቢዝነሶች እንዳሉ ያስረዱት የሲቪሊቶ ክፍል አድሚኖች፣ እነዚህን ከሕዝብ በተዘረፈ ገንዘብ፣ የተገዙ ቤቶችንና ቢዝነሶችን በተመለከተ ያሰባሰቧቸው፣ በፎቶ ግራፍ ላይ የተመረኮዘ መረጃዎች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይፋ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል። (በነገራችን ላይ የሕወሃት ነባር ታግይ ያልኩት ከላይ የጠቀስኩት ወዳጄ የሚኖረው፣ እየሰራ፣ እንደማንኛውም ሌላው ኢትዮጵያዊ መለስተኛ በሆነ አፓርተማ ውስጥ ነው። የ300 ሺህ ዶላር ቤት አልገዛም። ስለዚህ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ደጋፊ ሁሉ ገንዘብ በልቷል፣ ሰላይ ነው ወዘተረፈ የሚል የተሳሳተ አስተያየት አይኑረን። ስንከስ በስሜት ሳይሆን በመረጃ ይሁን። እንሰልጠን።)
ይህ የተዘረፈውን የሕዝብ ገንዘብ ለማስመለስ በ"ኢሕአዴግ ደጋፊዎች" የሚደረገውን ጥረት፣ አገሩን በሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊደገፍ ይገባዋል ባይ ነኝ። ይህ መልካም እንቅስቃሴ፣ ትምህርት ሆኖን፣ ዜጎችን "ወያኔ፣ ሆዳም" እያሉ የመስደብ አመላችንን አቁመን፣ "በምንስማማባቸው ነጥቦች ከኢሕአዴግ ደጋፊዎች ጋር አብረን መስራት መልመድ" አለብን እላለሁ።


በርካታ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች፣ እኛ እንዲኖር የምንፈልገውን መልካም ለውጥ፣ በኢሕአደግ ውስጥ ይፈልጋሉ። የሕሊና እሥረኞች በሙሉ እንዲፈቱ ይፈልጋሉ። የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ ይፈልጋሉ። እርቀ ሰላም እንዲወርድ ይፈልጋሉ። አሁን በአገዛዙ እየተደረገ ያለው የልማት እንቅስቃሴ እንዲቀጥልም ይፈልጋሉ።


እንግዲህ ለመልካም ለውጥ፣ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ ለእርቅ ፣ ለሰላም፣ ለልማት አብረናቸው የማንሰራበት ምክንያት የለም። የሚያሳዝነው አሁን ስልጣን ከበስተጀርባ የጨበጡትና በኢሕአዴግ ውስጥም ችግር የፈጠሩት ጥቂት ጨካኝ፣ ዘረኛና ክፉ ባለስልጣናት መሆናቸው ነው። "EPRDF is controlled by hateful elements" በሚል በቅርብ ጊዜ ይሄንኑ እውነታ ለማንጸባርቅ ሞክሪያለሁ።


ለምሳሌ ጋዜጣኛ ተመስገን ዳሳለኝ እንደዘገበው፣ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንዲሁም አቶ ደመቀ ብርሃኑ፣ እነ እስክንድር ነጋ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ይፈልጋሉ። ዶር ቴዎድሮስ አዳኖም እና ከሃላፊነታቸው የተሰናበቱት፣ በአዲስ አበባ ከተማ በሰሩት ሥራ የማከበራቸው፣ አቶ አርከበ እቁባይ ተመሳሳይ አመለካከት እንዳላቸው ፣ ካሉኝ አንዳንድ መረጃዎችም ፍንጭ ለማግኘት ችያለሁ። ፕሬዘዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የአጼ ኃይለስላላሴ ሃውልት በአፍሪካ ሕብረት ከጋናው ንክሩማ ጎን እንዲቆም ደብዳቤ ጽፈዋል።


ነገር ግን ለእስረኞች መፈታትም ሆነ ለአጼ ኃይለስላሴ ሃውልት መሰራት፣ መሰናክል የሆኑት፣ እነ እስክንድርን "መለስ ዜናዊ አደገኛ ብሎ አስሯቸዋል። እዚያው ቃሊቲ ይበስብሱ" የሚሉ ፣ እነ ደምቀ ብርሃኑን አላሰራም ያሉ፣ ሚሊተሪውንና ደህንነቱን የሚቆጣጠሩ፣ እፍኝ የማይሞሉ ጥቂት ግለሰቦች ናቸው። እርግጠኛ ነኝ አብዛኛው የኢሕአዴግ ደጋፊ፣ እነ አባመላ እንዳደረኩት፣ ከተነሳ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እነዚህ እፍኝ የማይሞሉ እፉኞች ታሪክ ይሆናሉ።


ምንም እንኳን በነአባ መላ እያየን ያለነው አስደሳች ዜና ቢሆንም፣ የተቀረው የተቃዋሚ ኃይል ግን የበለጠ እራሱን ማደራጀት ይጠበቅበታል። ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በኢሕአዴግ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ መጠበቁ፣ ለዚያም መስራቱ ተገቢ ቢሆንም፣ ያንን ብቻ ጠበቆ ግን ቁጭ ብሎ መቀመጥ ትልቅ ስህተት ነው። የተቃዋሚው ኃይል እራሱን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ፣ በቲቪና በስብሰባዎች ቀርቦ ከማውራትና፣ መግለጫዎች ከማውጣት ያለፈ፣ በተጨበጡ ስራዎች ዙሪያ እራሱን የማሰማራት እንቅስቃሴ ይጠበቅበታል። ለዚህም ነው እንደ አንድነት ፓርቲና መኢአድ ያሉ፣ አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች ሆነ፣ ከአገር ውጭ የሚገኙ፣ እንደ ሽግግር መንግስት ምክር ቤትና አዲሱ የኦሮሞ ዴሞክራሲያ ግንባር ያሉ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ አገር ቤት ያለው የሰማያዊ ፓርቲ፣ ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ፊት ለፊት በጠራው የሰላማዊ ሰልፍና ከግንቦት 15 እስከ ግንቦት 17፣ ጥቁር አልባሳት በመልበስ፣ ለሚደረገው የሰላማዊ ተቃውሞ ወቅታዊ ጥሪ፣ ሕዝባዊ ምላሽ መስጠት ያለባቸው። ማንም ይጠራው ማንም፣ መልካም እስከሆነ ድረስ መደገፍ አለበት። የምንፈልገው በአገራችን ለውጥ እንዲመጣ እንጂ ድርጅት አምላኪዎች አይደለንም። (በዚህ ረገድ እንደ ቃሌ ፓልቶክ ክፍል፣ ኢትዮጵያ ሪቪው፣ ዘሃበሻ፣ ኢኤም.ኤፍ የመሳሰሉ ድህረ ገጾች፣ እንዲሁም ኢሳት፣ ይሄንን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማገዝ እያደረጉ ያሉትን ጥረት ለማበረታት እወዳለሁ። በዚህ ጉዳይ በሰፊው የምመለስበት ይሆናል። እስከዚያም በቸር እንሰብት።


ግርማ ካሳ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ግንቦት 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ