የፓልቶክ ኋይል ሚዛን ተናጋ ፤ የጥገናዊ ለውጥ ተስፋ አንሰራራ
ያሬድ አይቼህ
የፓልቶክ ክፍሎች የኋይል ሚዛን በዚህ ወር (ሜይ) ድብልቅልቁ ወቷል። ላለፉት 7 ዓመታት የበላይ ሆኖ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች መወያያ መድረክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ጠንዝቷል። የቃሌ ክፍል ግን ከሰኞ እስከ አርብ ሞልቶ መግቢያ አጥቼ ከክፍሉ ደጅ ቆሜ ስንቆራጠጥ ሰንብቻለሁ። የሚያስደንቀው ግን የሲቪሊቲ ምጥቀት ነው።
ሲቪሊቲ ባለፈው አርብ ሲከፈት ቦታ ለመያዝ ቶሎ ዘው ብዬ ገባሁ። 45 ደቂቃ ሳይሞላ ክፍሉ 250 ሰው ሆነ። ሁለት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ክፍሉ 500 ሰዎቸ ሞላ። ድንቅ ነው!
የአባ-መላ የቀድሞ አፍቃሪዎች (ያሁኑ አኩራፊዎች) ክፍሉን ትተው ገዝኣ-ተጋሩን ሊሞሉት ትንሽ ቀርቷቸዋል። ሆኖም ግን ሲቪሊቲ ያለህወሓቶች ድጋፍ ሞልቶ መፍሰሱ የህወሓት ደጋፊዎችን ግር ሳያሰኛቸው አልቀረም። ለነሱ እንኳ "የሰኞ ክፍል" (የስዊዝ ክፍል) አለላቸው። አያርገውና፤ ሲቪሊቲ ሰኞ ጭምር ቢከፈት፣ የስዊዝ ክፍል በአንድ ሰኞ ሊዘረር ይችላል።
ይህ ሁሉ የፓልቶክ ኋይል ሚዛን መናጋት የአገራችንን የፖለቲካ ትኩሳት ለመለካት ይጠቅም ይሆን? ወይስ የዲያስፓራውን የፖለቲካ አዝማሚያ ጥቂት ግለሰቦች በአንድ ወር ሊቆጣጠሩት የሚችሉት ስር ያልሰደደ የፖለቲካ ቱሪስቶች ስብስብ ነውን?
ቁምነገሩ ይህ ነው፦ የአገራችን የፖለቲካ ውጥረት፤ በጠላትነት ሳይሆን በተፎካካሪነት፤ በጥላቻ ሳይሆን በሰቶ-መቀበል መፈታት ለምንመኝ ወገኖች፤ የሰሞኑ ግርግር ህብረተሰባችን የጥገናዊ ለውጥ ጭላንጭል ያዬ ሲመለስለው ምን ያህል መንፈሱ በፍጥነት እንደሚታደስ በማየቴ እጅግ ደስ ብሎኛል።
በተለይ በጥገናዊ ለውጥ አማራጭነት ላይ ደብዝዞ የነበረውን ተስፋዬን ሰሞኑን በፓልቶክ የሰማኋቸው የጥገናዊ ለውጥ ሃሳቦች መንፈሴን አድሰውታል። አንድ ታሪክ ላጫውታችሁ፤
አንዲት አሜሪካዊት ጎረቤቷ "ፈጣሪ የለም!" እያለ ያበሽቃት ነበር። እሷ ደሞ "ኧረ ፈጣሪ አለ" ትለዋለች። አንድ ቀን ያ የማያምነው ሰው ከዛች ጎረቤቱ በር ላይ አንድ ስጦታ አስቀምጦ ማንነቱን ሳይገልጽ ሮጦ ቤቱ ገብቶ በመስኮት ያያል። ያቺ ሴት በሯን ስትከፍት ያገኘችው ስጦታ አስደስቷት "ተመስገን አምላኬ!" ስትል የሰማው ጎረቤቷ "አሃ! አየሽ እኔ ሰጥቼሽ፤ ፈጣሪ ሰጠኝ ትያለሽ!" ብሎ ሲያፋጥጣት "ወይ አምላኬ! ሰይጣንን ተጠቅመህ ስጦታ ሰጠኸኝ" ብላ አምላኳን አመሰገነች ይባላል።
የሰሞኑ የፓልቶክ የሚዛን ለውጥ ማንም ያምጣው ማን፤ ለአገራችን ጥገናዊ ለውጥ እንዲሆን ለምንመኝ ሰዎች በጎ ሰሞን ነበር። የቃሌ ክፍል ከሰኞ እስከ አርብ፤ ሲቪሊቲ ከአርብ እስከ እሁድ የፓልቶክን የፖለቲካ አዙሪት አጡዘውታል። ይጡዝ! ይጧጧዝ።
አብዮት ልጆቿን ትበላለችና፤ ጥገናዊ ለውጥ ለአገራችን ይሁን! አሜን በሉ እንጂ?
ያሬድ አይቼህ
ሜይ 28 ቀን 2013 እ.ኤ.አ.
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.