በሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ሰፍኗል- ወያኔ ህወሓት
ይኸነው አንተሁነኝ
ለአንዲት ሀገር ሕዝብ መሰረታዊ ሕይወት መስተካከልና በተረጋጋ ሁኔታ መቀጠል፤ የሰላም መኖር አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም። ያሰቡትን ከውኖ እፎይ ለማለት፣ በሙያ በችሎታ ሰርቶ የልፋትን ዋጋ ያለ ምንም ችግር አግኝቶ የማታ ማታ ያለስጋት ወደ ቤት ለመመለስ፣ በጥቅሉ ወጥቶ ሰርቶ በሰላም የስራን ዋጋ ለማግኘት ሰላም ወሳኝ ነገር ነው።
ነጋዴው የንግድ ስራውን ለማከናወን ሕጋዊ በሆነ መንገድ የሚልከውን ልኮ የሚፈልገውን ለማስገባት ሰላም ያስፈልገዋል። ገበሬው ትነስም ትብዛ የያዛትን ማሳ አርሶና አለስልሶ፤ ዘርቶና አዝምሮ፤ ምርቱን ከጎተራው ለመክተት ሰላምን በእጅጉ ይፈልጋል። ሌላውም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭው፣ የቢሮ ሰራተኛው፣ የእለት ተእለት የጉልበት አገልግሎት ሰጭው፣ መምህሩ፣ የሕክምና ሰራተኛው በሙሉ ስራቸውን ባግባቡ ለመከወን ሰላም ያስፈልጋቸዋል። ተማሪውና ተመራማሪው ጠበቃውና ዳኛው መልካም እይታ እንዲኖራቸውና ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት ሰላም ዋና ግብአታቸው ሊሆን ይገባል።
ስለሆነም መልካም ነገር ለማግኘት ሰላም አስፈላጊ ስለመሆኑ በየትኛውም ወገን ክርክር ያለ አይመስለኝም። ነገር ግን ህወሓት እንደሚያወራው የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ለመኖሩ ማረጋገጫው ምንድን ነው? የመንገዶች መሰራትና የህንጻዎች መገንባት ሕዝባችን በሰላም ስለመነሩ ማረጋገጫዎች ሊሆኑ ይቸላሉን?
ዳኞች በፍርድ ወንበራቸው ስለተቀመጡ፣ መምህራን በትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ማስተማሪያ መሳሪያቸውን ይዘው ስለታዩ፣ እንዲሁም ከስደት የተረፉት የህክምና ባለሙያዎች በየሆስፒታሎች መገኘታቸው በእርግጥ ሰላም ስለመኖሩና በሰላም እየሰሩ ስለመሆኑ ምስክር ሊሆኑ ይችሉ ይሆን?
ይህ የወያኔ "በሀገራችን የተረጋጋ ሰላም ሰፍኗል" ፕሮፓጋንዳ አንድ ነገር አስታወሰኝ፤ ባንድ ወቅት የሀገራችንና የውጭ የስነምድር ተመራመሪዎች ባንድ ላይ ኤርተሌ እየተባለ የሚተራውንና በአፋር ክልል የሚገኘውን የሚፈላ ቅልጥ አለትና አካባቢውን አይተው ከተመለሱ በኋላ የተናገሩት ነው - ነገሩ።
ተመራማሪዎቹ በጥቅሉ ሲናገሩ "አካባቢው ከፍተኛ ሙቀት አለው። በዚህ አካባቢ ያለው የምድር ውስጥ እንቅስቃሴ የቆመ ወይም የሞተ አይደለም። አልፎ አልፎ ተመራማሪዎችና ጎብኝዎች በከፍተኛ ጥንቃቄና ጥበቃ አካባቢውን ሊጎበኙት ቢችሉም በቋሚነት ሕይወትን ባካባቢው ለመመስረት ግን አይቻልም። ምክንያቱም ለጊዜው ሰላም ያለው ቢመስልም በማንኛውም ሰዓት የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ሊከሰትና አካባቢውን እንዳልነበረ ሊያደርገው ይችላልና" ብለው ነበር።
በሀገራችንም ወያኔ ህወሓት ልክ በሕዝባችን መካከል አመጽ የሚያፈነዳ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ (እንደ አፋሩ ኤርታሌ አንጻራዊ ፀጥታ እስካለ ድረስ) አደጋ የለም፣ ሕዝባችንም በሰላም እየወጣ እየገባ ነው ባይ ነው። የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበረሰባዊ ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ፤ በሀገራችን አስተማማኝና የተረጋጋ ሰላም ሰፍኗል ለማለት የሚያስደፍሩ ነገሮች አይታዩም። እንደውም እየታዩ ያሉ ምልክቶችና እየተደረጉ ያሉ ድርጊቶችን ስናስተውል ተቃራኒውን እንድናስብ እንገደዳለን። ለምሳሌ ያህልም፦
ሀገራችን እጅግ በጣም ሰፊ የሆነ ለእርሻ የሚሆን መሬት እንዳላት ቢታወቅም የሀገራችን ሰፊው አፈር ገፊ ገበሬ ግን በቂ የእርሻ መሬት እንዲያገኝ አልተፈቀደለትም። ይባስ ብሎ ለሱ የሚገባው መሬት ለዐረብና ለሕንድ ነጋዴዎች እየተሰጠበት አዝኖ ነው ያለው። ስለሆነም አብዛኛው የሀገራችን ገበሬ ዛሬ መሬት የለውም፤ በሬ የለውም፤ መኖሪያ እንኳ የሌለው ብዙ ነው። የበሬ ግንባር የምታክል ሽራፊ መሬት ያለው እንኳ ቢኖር እሷኑ ለማረስና አለስልሶ ለመዝራት ጊዜ አላገኘም፤ ልክ በፊውዳሉ ሥርዓት እንደነበረው የሚበዛውን ጊዜውን የካድሬ መሬት ለማረስ ነውና የሚያጠፋው። "ይህ እንዴት ይሆናል? ለራሳችን መሬት ጊዜ ይኑረን!" ብለው የጠየቁ አርሶ አደሮች በካድሬዎች ከይዞታቸው ተገፍተው በየከተማው ሎተሪ አዟሪና ለማኝ ሆነዋል። ይህን የሚያውቀው ህወሓት ግን ያለው ችግር አመጽ ወልዶ ትርምስ እስካልተፈጠረ ድረስ በወያኔያዊ ቋንቋ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ነው እያለን ነው።
የንግዱን ማኅበረሰብ ስንመለከትም፤ ካርሶ አደሩ የማይተናነስ ችግር ተሸክሞ በሀዘንና በቁጭት ነው እየኖረ ያለው። የስራ ግብር እንደማይከፍሉ ከሚነገርላቸውና የተለያዩ የውጭ ምርቶችን ያለቀረጥ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚያስገቡት የወያኔ ድርጅቶች ጋር እንዲወዳደሩ ተፈርዶባቸው በመከራና በስቃይ ላይ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ስራን ለማስፈጸም ከተለያዩ የህወሓት ባለስልጣናት የሚጠየቁት እጅ መንሻና ያልተቋረጠው የወያኔ መዋጮ ወገባቸውን ሰብሮታል። ስራቸውን ለመቀጠልም ለማቆምም ተቸግረው ነው ያሉት። ቢሆንም ግን ሙሉ በሙሉ የንግድ ፈቃዳቸውን መልሰው ስራ እስካላቆሙና ችግራቸው አመጽ እስካልወለደ ድረስ በወያኔያዊ ቋንቋ ለንግዱ ማኅበረሰብ የሚሆን የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ሰፍኗል።
በወያኔ የማኅበራዊ ተቋማት ተቀጥሮ የሚሰራውና የከተማ ኗሪው ባጠቃላይ በሀገራችን እየሆነ ያለው አላስደሰተውም። የኑሮ ውድነቱ ካቅሙ በላይ ሆኗል። በብሔር ብሔረሰቦችና በግለሰቦች መካከል የሚደረገው መድሎ ተስፋ አስቆርጦታል። ከዛሬ ነገ የተሻለ ነገር ይመጣል ብሎ ቢጠብቅም ምንም ማየት አልቻለም። የተወሰኑ የህወሓት ባለስልጣናት ተቀያይረው ቢያይም ማሰቢያቸው ግን እንዳልተለወጠ ማስተዋል ችሏል፤ ምንም የታየ ለውጥ የለምና። ስለሆነም በሲቪል ሰራተኛውም ሆነ በከተሜው ላይ በችግር ላይ ችግር በምሬት ላይ ምሬት በስቃይ ላይ ስቃይ ጨመረ እንጅ፤ ላፋታ እንኳ አላባራም። ይህም ቢሆን ግን አንድ ቦታ ላይ ፈንድቶ ላገዛዙ አስቸጋሪ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ ለወያኔ ህወሓት የአስተማማኝና የተረጋጋ ሰላም ምልክት ነው።
በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በየትኛውም ቦታና የስራ መስክ በሚባል መልኩ ችግሩ ብሶቱ ከቋፍ ደርሶ ውጥረቱ አይሏል። የውጥረቱ መጠን ልክ በቤንዚን ባህር ላይ አንዲት ክብሪት ተጭራ ብትጨመር ሊፈጠር እንደሚችለው አደጋ አይነት ነው። ግን ይህ ውጥረት አልፈነዳም፤ ልክ እንደ ኤርታሌ ውስጥ ለውስጥ ይታመሳል፣ ይብላላል፤ ጊዜና ወቅት በመጠበቅ። ይሁን እንጅ ውጥረቱ ከትላንት ዛሬ ጨመረ እንጅ አልቀነሰም። ወያኔ ህወሓት ግን ጭራችሁ ለኩሳችሁ ወይም አመጽ አስነስታችሁ፤ አፈንድታችሁ እስካላየሁ ድረስ አስተማማኝና የተረጋጋ ሰላም አለ እያለን ይገኛል።
በእርግጥ ወያኔ ሕዝብ እያስተዳደርኩ ነው ብሎ የሚያስብ ቢሆን ኖሮ ችግሮች ከጫፍ ደርሰው ፈንድተው እስኪወጡ ባልጠበቀም ነበር። ምክንያቱም ፍንዳታ አካባቢ አይመርጥም፣ እሳት ወገን አይለይም፣ ገሞራ ዘመድ አይመርጥም ብሔርና ኃይማኖት አይለይም፣ ቋንቋና ጾታ አይልም፤ ሁሉንም እንዳመጣጡ ያጠፋል። ያገኘውን ነገር ሁሉ ባለው አቅም ያወድማል።
የሕዝብ እምቢተኛነት በቃኝ አልገዛም ባይነት፤ በዚሁ የተነሳ የሚፈጠር የህዝብ አመጽም ልክ እንደ ገሞራ ነው፤ ለጥፋቱ ቀመር የለውም። ለጉልበቱ የሚስተካከል ነገር አይገኝለትም። ባንድ ጊዜ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ሊከሰት የሚችል ከመሆኑ አንጻር ለመቆጣጠርም ካቅም በላይ ነው። ሊያደርስ የሚችለው ጥፋትም ከግምት በላይ ነው የሚሆነው። ለጊዜው ሕዝባችንን አብሮ መኖር፣ መቻቻል፣ መተሳሳብ ዝም ቢያደርገውም ምሬቱና ለወያኔ ያለው ጥላቻ ጠፋ ማለት አይደለም። ስለዚህም ወያኔ ህወሓት በፈጠረው ችግር የተወለደው የምሬት ክብሪት የሕዝብን አልገዛም ባይነትና አመጽ ጭሮ ከመውለዱ በፊት ማን አለብኝ ብሎ እየገዛ ያለው ወያኔ ከውሸት እንቅልፉ መንቃት አለበት እላለሁ።
ይኸነው አንተሁነኝ
ግንቦት 29 ቀን 2013 እ.ኤ.አ.