ግርማ ሠይፉ ማሩ
ሰሞኑን ከፀረ-አሸባሪነት ሕግ በማስቀጠል የአዲስ አበባን ከተማ ነዋሪን በተለይ ሲያምስ ከርሞ አሁንም በማመስ ላይ ያለው የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ነው። በአዲስ አባባ የመኖሪያ ቤት ችግር እንዳለ አሌ የሚባል አይደለም። ይህ ችግር እዚህ እንዲደርስ ደግሞ ዋናው ተዋናይ መንግሥት እንደሆነ መዘንጋት የለበትም። ምክንያቱም ለቤት መስሪያ የሚሆነውን ቦታ በቁጥጥሩ ስር አድርጎ ለዜጎች እንዳይደርስ በማድረጉ ነው።

አንደኛው በቁጥ-ቁጥ ቦታ በሊዝ ጨረታ እያወጣ በውድ ዋጋ እየሸጠ የመሬትን ዋጋ በማስወደድ እና የመኖሪያ ቤት ውድ እንዲሆን በማድረግ ነው። ሌላው ደግሞ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል የብድር አገልግሎት የተለየ አቅርቦት ባለማዘጋጀቱ ሲሆን፣ የመንግሥት ሹሞች ደግሞ በተለየ ሁኔታ የተመረጠ ቦታ እያገኙ በሽያጭ እንዲከብሩ፤ በተቃራኒው ዜጎች ከከተማ ወጣ ባሉ ቦታዎች በሕገ-ወጥ መንገድ እንዲሰፍሩ በማድረግ ነው።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ልዩ ወዳጅነት የመሰረቱ ይመስላል። ባንኩ በተለይ መመሪያ የሚቀበለው በቀጥታ ከብሔራዊ ባንክ መሆኑ ቀርቶ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እስኪመስል ድረስ ግራ አጋቢ ሆኖብናል። በእኔ እምነት በቅርቡ መንግሥት ዜጎች ቤት እንዲኖራቸው ለቤቶች ግንባታ በሚል 10/90፣ 20/80፣ 40/60፣ እና ሌሎችም በቁጠባ ላይ መሰረት ያደረጉ ዜጎችን የማመስ ሥራ እየሰራ ይገኛል። ይህን ጉዳይ ዛሬ ላይ ሆኜ የምፅፈው ከዓመት እና ሁለት ዓመት በኋላ ለውይይት ይጠቅማል በሚል ነው። አቋሜን ግልፅ ለማድረግ የኢህአዴግ መንግሥት በምንም ዓይነት መለኪያ ለኢትዮጵያ ህዝብ የመኖሪያ ቤት ሠርቶ የመስጠት አቅምም ሆነ ፍላጎት የለውም። ስለዚህ የፕሮግራሙ ዓላማ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ ማየት ተገቢ ነው።

የኢህአዴግ መንግሥት በዓለም ላይ ካሉ መንግሥታት በተለየ ሁኔታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቤቶችን እንደኮንትራክተር ለመገንባት ሙከራ እያደረገ ያለ መንግሥት ነው። መንግሥት እንደ መንግሥት ሊሰራቸው የሚችለው ብዙ ተግባራት ወደ ጎን በመተው ዜጎች እንደፍላጎታቸው እና አቅማቸው ቤታቸውን መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሲገባው፤ መንግሥት በፈለገው እና በተወሰኑ የቤት ዓይነቶች ውስጥ ታጥሮ እንዲኖር ለማድረግ እየሞከረ ነው። ወደ መጨረሻ ላይ ይህን መንግሥት ለምን እንደሚያደርግ የግል ምልከታዬን አስቀምጣለሁ።

የመንግሥት ቤቶች ግንባታ ዋና ዓላማ መንግሥት በ2006 በጀት መግለጫ ላይ እንዳስቀመጠው የሀገር ውስጥ ቁጠባን ለማሳደግ ከተያዙት ዕቅዶች አንዱ ነው። ይህ የሀገር ውስጥ ቁጠባን ማሳደግ የተቀደሰ ሃሳብ ነው። ይህን ቁጠባን በፈቃደኝነት ማሳደግ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አይመስለም። ለዚህ ብዙ ምክንያት ስለአለው ዝርዝር ውስጥ አልገባም። መንግሥት ግን ለዚህ እንደመፍትሔ አድርጎ ያስቀመጠው ዜጎች ቤት ይሰራልናል በሚል በተስፋ ላይ መሰረት ያደረገ ገንዘብ ተቀማጭ እንዲያደርጉ ማድረግ ነው። እግረ መንገዱንም መንግሥት ለተለያየ ሥራ የሚፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት እንዲችል ዕድል መፍጠር ነው። ይህ በቁጠባ የተሰበሰበ ገንዘብ በግል ባንኮች ቢቀመጥ፣ የግል ባንኮች ለግል ባለሀብቶች በብድር መልክ ሊሰጡት ስለሚችሉ መንግሥት የሚፈልገውን ገንዘብ ላያገኝ ስለሚችል፤ ይህ ገንዘብ ተጠቃሎ ወደ ንግድ ባንክ እንዲገባ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ሆኖ ተገኝቶዋል። በዚህ ፖሊሲው መንግሥት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ተቋማትን እና ዜጎችን በአንድ ዓይን እንደማይመለከት ግልፅ ማሳያ ነው።

ብዙ ሰዎች የመንግሥት ዋና ዓላማ የገባቸው አይመስሉም። ይልቁንም መንግሥት ቤት መሥራት ለማይችሉ ሰዎች ቤት ቢሠራ ምን ችግር አለው? የሚሉ አሉ። መንግሥት እንደሚያወራው ቤት መሥራት ያልቻሉ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ቤት ለመሥራት እንዳልሆነ የሚያሳብቀው ግን፤ በተነፃፃሪ የተሻለ አቅም ያላቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ቢሆኑ በዚሁ ፕሮግራም እንዲሳተፉ ዕድሉ ክፍት ነው ይባላል። ይህ ዕድል ግን ክፍት የተደረገው በውጭ ምንዛሪ መቆጠብ ሲችሉ ነው። ገባችሁ አይደለም የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመቅረፍ የተያዘ ዕቅድ ነው - ትክክለኛውም ዕቅድ ይህ ነው። ተስፋን እየመገቡ ዶላር መሰብሰብ። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሀገራችን ላለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት መፍትሔ መስጠት መቻል ተገቢ ነው። ነገር ግን የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ዜጎች ለጋራ ልማታችን የሚያውሉት እንጂ መንግሥት ብቻ ለሚያቅደው ዕቅድ መዋል አለበት የሚል እና የግል ባለሀብት ከጨዋታ የሚያስወጣ ዕቅድ ለመተግበር መሆን የለበትም።

ሌላው የመንግሥት ዕቅድን ፊት ለፊት ከሚያወራው በተቃራኒው መሆኑን የሚያሳብቀው በአርባ በስልሣ ሙሉ ክፍያ የከፈለ ቅድሚያ ያገኛል የሚለው መመሪያ ነው። ቅድሚያ መክፈል የሚችል ማለት አርባ በስልሳ (አርባ ቆጥቦ ስልሳ በብድር የነበረ ፕሮግራም) ሳይሆን መቶ ዜሮ (መቶ ቆጥቦ ዜሮ ብድር ሆኖዋል) ፕሮግራሙ መባል ያለበት። በእርግጥ መንግሥት ቤት በተመጣጣኝ ዋጋ የመሥራት ዕቅድ አለው ብለን እንድናምን የሚያደርግ ነገር አለወይ? ነው የእኔ ጥያቄ። መልሱ በፍፁም መንግሥት ይህ ዕቅድ የለውም። ዕቅዱ በጭፍን አለው ብለን ብንወሰድም አቅሙ የለውም።

የመንግሥት አቅም እንዴት እንለካው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ሁሉም እንደሚያውቀው ኢህአዴግ በ1997 የአዲስ አበባ ህዝብ ያለበትን ችግር ለመቅረፍ ቅድሚያ የሚሰጠው የመኖሪያ ቤት ነው በሚል ከአራት መቶ ሃምሳ ሺ በላይ ቤቶችን በአምስት ዓመት ለመገንባት ብሎ ምዝገባ አድርጎ ነበር። ዛሬ ላይ ቆመን ውጤቱን ስንመለከተው በስምንት ዓመት ውስጥ በጅምር ላይ ያሉትን ጨምሮ አንድ መቶ ሺ ቤቶችን ነው መገንባት የተቻለው። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳሉት መቶ ሺ ቤቶች የገነባ ሌላ መንግሥት የለም። ምክንያቱም የሌላ ሀገር መንግሥታት በማያገባቸው አይገቡም። ስለዚህ ይህን ያህል ቤት አይገነቡም። እስራኤል አወዛጋቢ በሆኑ ቦታዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ስትገነባ እንኳን ለግል ኮንትራክተሮች ነው የምትሰጠው። መንግሥታት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ያውቃሉ፤ እርሱን በቅጡ ይተገብራሉ። የእኛ መንግሥት ለአምስት ዓመት ከያዘው ዕቅድ ውስጥ በስምንት ዓመት ውስጥ ከሃያ በመቶ በታች ብቻ በማከናወን ሌላ ሦስት ዕጥፍ የሚሆን ሌላ ዕቅድ ይዘው ብቅ ብለዋል። ይህ ዕቅድ ዝርክርክ እንደሆነ ለማወቅ በምዝገባ ወቅት ብቻ የሚለዋወጠውን መመሪያ ማየት በቂ ነው። ለድሃ ነው የምንሠራው ብለው፣ መሉ በሙሉ ለከፈለ ቅድሚያ ይሰጣል ይሉናል። በዚህም ተባለ በዚያ መንግሥት የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት የሚያስችል መላው ዜጋውን እና በተለይም የግሉን ዘርፍ የሚያበረታታ ዕቅድ ማውጣት ግድ ይለዋል። 

ሌላው በጥቂቱም ቢሆን የተሠሩት ቤቶች ዓላማ ምንድነው ካላችሁ በልማት ስም የተነሱ የቀበሌ ቤቶችን በመተካት ዜጎችን ለቁጥጥር በሚመች መልኩ ማስፈር ነው። ለዚህ ዋነኛው ማሳያ የኮንዶሚኒየም ቤቶች በሕጋዊ መንገድ በሽያጭ ማዛወር አይቻለም። ዜጎች ይህን የመንግሥት ቁጥጥር መስመር ለማለፍ የተለያዩ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን፤ ይህን ለማድረግም የተለያዩ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን ይፈፅማሉ። ይህ ብቻም አይደለም፣ የመንግሥት የቁጥጥሩ አባዜ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም የሚቀር አይደለም። ገንዘባቸውን ገቢ ካደረጉ በኋላ መንግሥትን በሚቃወም ተግባር ቢሳተፉ በቁጠባ ያስቀመጡት ገንዘብ አደጋ ላይ ስለሚወድቅ ጭጭ ማለት ይጠበቅባቸዋል። ነፃነታችንን ከፍለን ሽጠናል የምለው ለዚህ ነው። በሀገራችን ቤት እናገኛለን ብለው ነፃነታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። በቅርቡ ሁሉም እንደሚታዘበው ኢትዮጵያዊያን ለሁለት ተከፍለናል ግማሹ ለነፃነት፣ ቀሪው ለኮንዶሚኒየም እየተሰለፈ ነው። 

ኢህአዴግ የቀበሌ ቤቶችን በመንግሥት ቁጥጥር ስር እንዲቆይ ያደረገው በምንም ዓይነት በቀበሌ ቤት ለሚኖሩት ሰዎች አዝኖ አይደለም። ዋና ዓላማው በገጠር ገበሬውን በመሬት ጭሰኝነት እንደያዘው ሁሉ፤ በከተማ ደግሞ በቀበሌ ወይም በኪራይ ቤት እንድንኖር ታቅዶ እየተተገበረ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። የቀበሌ ቤቶች በዕድሜ ምክንያት ከጫወታ ሲወጡ፤ ይህ ተግባር በኮንዶሚኒየም በኩል ነብስ እንዲዘራ ዕቅድ አለ። ይህ ዕቅድ የለም የሚሉ ከሆነ ለዜጎች በነፃነት ቤታቸውን ሽጠው እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ ትክክል አይደለም።

 


ግርማ ሠይፉ ማሩ (ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባል)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ