አብርሃ ደስታ Abreha Destaአብርሃ ደስታ ከመቐለ

የህወሓት ደጋፊዎች የአቶ አርከበ ሚና መቀነስ በአቶ አባይ ምክንያት እንደሆነ ያስባሉ። እንደኔ ግን አርከበ የተገለለው በአባይ ወልዱ ሳይሆን በመለስ ነው። መለስ ሥልጣን በጣም ከመውደዱ የተነሳ ሥልጣኑን የሚፎካከሩና አደጋ የሚደቅኑ አቅም ያላቸው የህወሓት ሰዎች ሲያርቅና ሲያጠፋ ነበር።

 

መለስ አቅም ያለው ሰው አይወድም፤ ለሥልጣኑ ስለሚያሰጋ። ለዚህም ነው አቶ አርከበ ተስፋ ቆርጦ ከፖለቲካ እንዲርቅ የተለያየ ተፅዕኖ ሲያረግበት የነበረው። መለስ አርከበን በህዝብ እንዲጠላ ያደርግ ነበር። አርከበ ለምን ስጋት ሆነ?

አርከበ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሳለ በሠራው ነገር የህዝብ ተቀባይነት እያገኘ ነበር። በሌላ በኩል አንድ ወቅት በህወሓት ጉባዔ ስብሰባ በነበረው ምርጫ አርከበ ሙሉ ድምፅ ሲያገኝ፣ መለስ በአንድ ድምፅ በአርከበ ተበልጦ ሁለተኛ ሆነ። በህወሓት ፖለቲካዊ ባህል መሰረት የፓርቲው ሊቀመንበር የሚሆነው (by default) ከፍተኛ የጉባዔተኞች ድምፅ ያገኘ ነው (የሚመረጠው ግን በማዕከላዊ ኮሚቴ ነው)።

እውነታው ይህ ኹኖ ሳለ፤ መለስ ራሱ ሊቀመንበር ኹኖ እንዲመረጥ አደረገ። አርከበን ምክትሉ እንኳን አላደረገውም። አርከበን የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ከማድረግ ይልቅ ስድስተኛ ደረጃ ይዞ የነበረው አቶ ስዩም መስፍንን መረጠ። ለምን ቢባል ስዩም ለሥልጣን አስጊ አይደለማ። ታዛዥ አገልጋይ ነው።

መለስ የሚፎካከረው ሰው አይወድም። በዚህ መልክ የህወሓት ጠንካራ ሰዎች ተስፋ እንዲቆርጡና ከፖለቲካ ራሳቸውን እንዲያገሉ ምክንያት ሆኗል። በዚህ ሂደት ህወሓት ተዳከመ። የህወሓት መዳከም የመለስ ሥራ ነው። የነ አባይ ወልዱ ብቻ አይደለም።

እርግጥ ነው፣ እነ አባይ ወልዱም 'የመለስ ራዕይ ለማስቀጠል' ቆርጠው ስለተነሱ መለስ ያድረገውን በማድረጋቸው እነ አርከበ ቅር መሰኘታቸው አልቀረም።

በ1993 የህወሓት ክፍፍል መለስን የተቃወሙ፣ የመለስን ሃሳብ ያልተቀበሉ፣ መለስ እንደፈለገ እንዲዘውራቸው ያልፈቀዱ ባለሥልጣናት የመለስን ሃሳብ ከመቀበልና ከመተግበር ፓርቲውን ለቀው መውጣት የመረጡ ፖለቲከኞች 'አንጃ' የሚል ስያሜ ተሰጣቸው። 'አንጃ' ማለት 'የማይታኘክ ስጋ' (ዘይሕየኽ ስጋ ... ጅማት) ማለት ነው አሉ።

ይህን 'አንጃ' የሚለው አገላለፅ ተመችቶኛል። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ለመለስ የሚታኘኩ አልሆኑም (ብቀሊሉ ዝሕየኹ አይኮኑን)። መለስ የሚፈልገው ግን በቀላሉ የሚታኘክ ለስለስ ያለ ስጋ ነው፣ እንደፈለገ እንዲያደርገው፣ አኝኮ እንዲውጠው እንደ አንዳንዶቹ። ተገንጣዮቹ ለመለስ አንጃ በመሆናቸው ምክንያት ከፓርቲው ወጡ። ብቻውን ቀረ። ህወሓት ተዳከመ። አሁን ለማቅናት ተቸገሩ።

የተገነጠሉት ሰዎች ግን እንኳን 'አንጃ' ሆኑ እላለሁ። ለምን የሌላ ሰው ምግብ ትሆናለህ? ለምን የሰው ባሪያ ትሆናለህ? ለምን ነፃነትህን አሳልፈህ ትሰጣለህ? ለሥልጣንና ቁሳዊ ጥቅም ነፃነትህን መሸጥ የለብህም። ምክንያቱም ነፃነት ውድ ነው። የነፃነት ዋጋ ነፃነት ብቻ ነው። ነፃነት በቁስ አካል ወይ በሥልጣን ሊገዛ አይችልም። ስለዚህ 'አንጃ' መሆን አለብህ።

እኔ አንጃ ነኝ። ማንም እንዲያኝከኝ አልጋብዝም፣ አልፈቅድም።

ዓረና ትግራይ ፓርቲ 'የአንጃዎቹ ነው' አሉን። ትክክል መሆንም አለበት። የጠንካራዎች ፓርቲ መሆን አለበት። በቀላሉ የሚታኘክ ሰው ደካማ መሆን አለበት። ስለዚህ 'አንጃ መሆን' የጠንካራነት ምልክት አድርጌ እወስዳለሁ።

አንድ ነገር ግን እላለሁ። እነዚህ 'አንጃዎቹ' በአንድ ወቅት የህወሓት አባላት ስለነበሩ አሁን በዓረና ወይ በሌላ በመረጡት የፖለቲካ ድርጅት አባል የመሆን መብታቸውን ከተዳፈርን፤ በህወሓት አባላት ላይ እየቀለድን መሆናችንን ማወቅ አለብን። ምክንያቱም ዛሬ የህወሓት አባላት የሆናቹ ነገ ሰዎች ናችሁና ሃሳባችሁን ልትቀይሩ ትችላላችሁና።

ህወሓት ሲሞት'ኮ እናንተም አብራቹ አትሞቱም። ሌላ አማራጭ አለ፤ ሌላ ዕድል አለ። ደግሞ መብታችሁ ነው። ስለ 'አንጃዎቹ' ስታወሩ ስለ ራሳችሁ እያወራችሁ ነው።

ግን ...

ሃሳባችሁን ስትቀይሩ የፈለጋችሁትን ፓርቲ አባል የመሆን መብታችሁ ሊከበርላችሁ ይገባል። ካልሆነ ግን እንዴት የራሳችሁን መፃኢ የፖለቲካ ሕይወት ታጠባላችሁ? የማንኛውም ፓርቲ አባል የመሆን መብት'ኮ አላችሁ።

እንደዚህ ነው!


አብርሃ ደስታ ከመቐለ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ