አጭር ማስታወሻ የሰማያዊ ፖርቲ የተቃውሞ ሠልፍ
ይድነቃቸው ከበደ (የሰማያዊ ፓርቲ የሕግ ጉዳይ ኃላፊ)
ነኀሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሰማያዊ ፓርቲ ታላቅ የተቃውሞ ሠልፍ መጥራቱ የሚታወቅ ነው፤ ይሁን እንጂ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እንደሰፈር ጉልበታኛ ድንኳን ሰባሪ ዘው ብሎ በኃይማኖት ሰበብ ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ቀንና ሰዓት እንዲሁም ቦታ በሕግ አግባብ ሣይሆን በጉልበት ሠልፍ መሰል ሠልፍ ማካሄዱ የሚታወቅ ነው።
ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም. የተቃውሞ ሠልፍ በማድረግ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የተቃውሞ ሠልፈኞች እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጪ የመገናኛ ብዙኀን በተገኙበት መንግሥት ሊመልሳቸው የሚገቡ ጥያቄዎችን የጠየቀ ሲሆን፤ ለጥያቄዎቹም ምላሽ የሰጠው የጊዜ ገደብ ሦስት ወር መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ይሁን እንጂ መንግሥት በተሰጠው ጊዜ የተጠየቀውን ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ፓርቲውን በመወንጀል እና ስም የማጥፋት ዘመቻውን አጠናክሮ ቀጥሏል። ሰማያዊ ፓርቲ መንግሥት ላሣየው ቸልተኝነት እርማታ እንዲያደርግ በመግላጫ የጠየቀ ሲሆን፤ ይህንንም ተከትሎ ከአንድ ወር በፊት በፓርቲው ጽ/ቤት በተሰጠ መግለጫ ነኀሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. ፓርቲው ቀድሞ ለጠየቃቸው ጥያቄዎች ምላሽ ባለማግኘቱ በድጋሚ በተጠናከረ መልኩ የተቃውሞ ሠልፍ መጥራቱን ለመንግሥትም ለህዝብም ገልጿል።
ሰማያዊ ፓርቲ በሠላማዊና በሕጋዊ መንገድ የሚታጋል እንደመሆኑ መጠን የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንቀፅ 30፣ ንዑሰ አንቀፅ 1'ን መሰረት በማድረግ ነኀሴ 13 ቀን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት የሰላማዊ ሰልፍ ስብሰባ ማሳወቂ ቢሮ ነኀሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. የተቃውሞ ሠልፍ እንደሚያካሂ ያሳወቀ ሲሆን፤ የከንቲባ ጽ/ቤት የሰላማዊ ሰልፍ ስብሰባ ማሳወቂ ቢሮ ነኀሴ 15 ቀን ለፓርቲው በላከው በአስቸኳይ የደብዳቤ መልዕክት ሦስት ጥያቄዎችን ለፓርቲው ሲጠይቅ፤ ሰማያዊ ፓርቲ ነኀሴ 17 ቀን የተጠየቁትን ጥያቄዎች በመመለስ የማሳወቂያ ደብዳቤ አስገብቷል።
ይሁን እንጂ የከንቲባ ጽ/ቤት የሰላማዊ ሰልፍ ስብሰባ ማሳወቂ ቢሮ ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጠም፤ ይህ ደግሞ የማሳወቂያ ደብዳቤ ከገባ በ48 ሰዓት ውስጥ ምንም ዓይነት ምላሽ ካልተሰጠ የተጠራው የተቃውሞ ሠልፍ እውቅና እንዳለው ይቆጠራል ተብሎ በአዋጅ ተደንግጎ ይገኛል። በዚህም መሰረት ሰማያዊ ፓርቲ በ48 ሰዓት ውስጥ ምንም ዓይነት ምላሽ ስላልደረሰው የሕጉን ሥርዓት ጠብቆ ለተቃውሞ ሠልፉ ዝግጅቱን አጠናክሮ በመቀጠል ላይ እንዳለ፤ ነኀሴ 20 ቀን የኃይማኖት ጉባዔ የተባለ በመንግሥት ድጋፍ የሚንቀሳቀስ አካል ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ቀንና ሰዓት እንዲሁም ቦታ ሠልፍ መጥራቱ ታወቀ።
ይህ ደግሞ ተገቢ አለመሆኑ ምን አልባትም ከመረጃ እጥረት ከሆነ ወይም ሌላ ምክንያትም ቢኖርም ሰማያዊ ፓርቲ የሕግ አግባብ ተከትሎ ቀድሞ የያዘው ፕሮግራም መሆኑ እና ለተፈጠረው የፕሮግራም መደራረብ መንግሥት በአስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግ፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለሚፈጠሩ ማናቸውም ችግሮች መንግሥት ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ሰማያዊ ፓርቲ በሰጠው መግለጫ አሳስቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነኀሴ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ፖሊሲ ኮሚሺን ሦስት የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችን የእንወያይ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችም ጥሪውን በማክበር በቦታው ተገኝተዋል። "የአ/አ አስተዳደር ፓርቲያችሁ ለጠራው የተቃውሞ ሠልፍ እውቅና አልሰጠም፤ በዚህም መሰረት ሰልፉን ማካሄድ አትችሉም" በማለት ፖሊስ ማስጠንቀቂያ የሰጠ ቢሆንም፤ የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች "ፖሊስ ይህን የማለት መብት የለውም፤ የአ/አ አስተዳደር ፓርቲያችን ላስገባው ደብዳቤ በ48 ሰዓት ውስጥ የሰጠው ምንም ዓይነት ምላሽ የለም፤ ይህ ደግሞ የጠራነው የተቃውሞ ሠልፍ የሕግ አግባብነት ያለው ነው፤ በመሆኑም ምንም ዓይነት የሕግ ስህተት ባለመፈጸማችን ሰልፉን እናካሂዳልን፤ በዕለቱም ፖሊሲ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አለበት" በማለት ሃሳባቸውን ገልፀዋል።
በመሆኑም ሰማያዊ ፓርቲ ዝግጅቱን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ ነኀሴ 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ የፓርቲው አመራሮችና አባላቶች እንዲሁም ደጋፊዎች በፓርቲው ጽ/ቤት ቅጥር ግቢ በማግስቱ እሁድ ለሚደረገው የተቃውሞ ሠልፍ እጅና ጓንት በመሆን ከምንም በላይ በሚያስቀና ጓዳዊ ስሜት ሲንቀሳቀሱ ማየት ብርታትም ፍቅርም የሚሰጥ ነው። ይሁን እንጂ በመንግሥት ሚድያ በዕለቱ ማለትም ቅዳሜ ከ7 ሰዓት ጀምሮ በማከታተል ሰማያዊ ፓርቲ የጠራው የተቃውሞ ሠልፍ ሕገ-ወጥ መሆኑና ሠልፉ ቢካሄድ ፓርቲው ኃላፊነቱን እንደሚወስድ በፖሊስ ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎ በአባላቶች መካከል ሠልፉ ይካሄዳል ወይስ ምን ይሆን በማለት የእርስ በእርስ ንግግር ሲያደርጉ ሞቅ ሞቅ ያለው እንቅስቃሴ ከዝናቡ ጋር ተዳምሮ በግቢ ውስጥ ቀዝቃዛ ስሜትን ፈጠረ።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች አስቸኳይ ስበሰባ በማድረግ ፖሊስ በሰጠው ማስጠንቀቂያ ዙሪያ ሰፊ ውይይት በማድረግ ላይ እያሉ አባላቶች ከስብሰባው ምን አይነት ውሳኔ ይተላለፍ ይሆን በማለት በጉጉት ይጠብቁ ነበር። የፓርቲው አመራሮች ስብሰባ እንደጨረሱ ከአባላት ጋር በመሰብሰብ አመራሩ የደረሰበትን ውሳኔ የተቃውሞ ሠልፉ እንደሚካሄድ መንግሥት እየተከተለ ያለው የሕግ ጥሰት አግባብ እንዳልሆነ እና ይህን አስመልክቶ የተቃውሞ ሠልፉ አብይ መፈክር "የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ዘመቻ" እንደተባለና አባላቶች አጠናክረው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ላይ መደረሱን ሲገልፁ፤ በስብሰባው ላይ የተገኙ አባላቶች ጭብጨባና ደስታ እንዲሁም ያሳዩት የነበረው ቁርጠኝነት አመራሩ ያስተላለፈው ውሳኔ ትክክለኝነትን አጉልቶ የሚያሳይ ነበር።
ዘመቻ ለሕግ የበላይነት ከ10፡30 ጀምሮ በግቢ ውስጥ እንደ ፍም እሳት ይፋጅ ጀመረ፤ ሀገራዊ ሙዚቃዎች ድምፃቸው ከፍ ብሎ ሲሰማ ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው እንደሚባለው ወጣትና አንጋፋ የፓርቲው አባላቶች የፓርቲውን ዓርማ በመያዝ ያሳዩት የነበረው እንቅስቃሴ እና ለሀገራቸው ያላቸው ተቆርቋሪነት እንዴት ያለ የሀገር ፍቅር ልክፍት ነው? ያስብላል። ወጪ ወራጁ መንገደኛ ሲጀምር የአግርሞትና አድናቆት ዕይታ ሲብስበት ተቀላቅሎ የድርጊቱ አንድ አካል ለመሆን ያሳዩቱ የነበረው እንቅስቃሴ ሌላው አስደሳች ክስተት ነበር።
ዘመቻ ለሕግ የበላይነት በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ማምሻውን በድምቀት እየተካሄደ እንዳል በ4 የተለያዩ መኪናዎች ተጭነው የመጡ ሙሉ የጦር መሣሪያ ትጥቅ የታጠቁ የፌዴራል ፖሊሶች የፓርቲው መውጫና መግቢያ መንገዶችን በ50 ሜትር ዙሪያ በቅድሚያ ከበባ አካሄዱ፤ ቀጥሎም ቁጥራቸው ወደ 30 የሚጠጉ ሌሎች የፌዴራል ፖሊሶች የፓርቲው ግቢ ጥሰው በመግባት መስኮትና በር በኃይል በመስበር ወደ ቢሮ በመግባት አባላትን በማገት በቢሮ ውስጥ የሚገኙ ንብረቶችን በማውደም፣ የተቀሩትን በመኪና በመጫን ካሸሹ በኋላ የፓርቲው አመራርና አባላትን በመኪና ይዘው ሳይሆን ጭነው ወደ ጃንሜዳ ፖሊስ ጣቢያ ይዘዋቸው ሄዱ።
ወጣትና አንጋፋ የፓርቲው አባላቶች በጃንሜዳ የጠበቃቸው ነገር፤ መጀመሪያ ሁሉም የሞባይል ስልካቸውን እንዲያጠፉና እንዲያስረክቡ፤ ቀጥሎም ጫማቸውን እንዲያወልቁና እንዲንበረከኩ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ የሆነው ነገር ስሜትን የሚነካና የሚያስቆጭ ነው። በፖሊስ ጣቢያ ግቢ ውስጥ በሚገኝ የሽንት መውረጃ ቆሻሻ ቦታ ላይ በጀርባ በማስተኛት በብረትና በዱላ ፍፁም ሰብዓዊነት በጎደለው ሁኔታ አህያ እንኳን የማይችለውን ዱላ በሰው ገላ ላይ ፖሊስ ድብደባ ፈጸመ። በዚህም ምክንያት በአባላቶች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሷል።
ይህ አይነቱ ኢሰብዓዊ ድርጊት ከምሽቱ 3፡30 ፍፃሜ አገኘ። ወጣትና አንጋፋ የፓርቲው አባላቶች አብዛኞቹ ቆመው ለመሄድ በጣም ይቸገሩ ነበር፤ መኖሪያ ቤታቸው ቅርብ የሆኑ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ፣ ራቅ የሚሉት ደግሞ በግሩፕ በመሆን ሰብሰብ በማለት በተለያዩ የፓርቲ አባላት መኖሪያ ቤት ለማደር ችለዋል።
ወጣትና አንጋፋ የሰማያዊ ፓርቲ አባላቶች ይህን ሁሉ የዱላ ውርጂብኝ በመቋቋም በድጋሚ እንዲህ ሲሉ ዘመሩ፤
የትግል ጉዞው ታሪካዊ
ዓላመው ፍፁም ህዝባዊ
ራዕይችንም ኢትዮጵያዊ
ሰማያዊ ሰማያዊ
ፓርቲያችን ነው ሰላማዊ
ይድነቃቸው ከበደ
የሰማያዊ ፓርቲ የሕግ ጉዳይ ኃላፊ



