ኢትዮጵያ ወዴት? በየታሪካዊ መጋጠሚያው አዲስ መልስ የሚሻ የተደጋገመ ጥያቄ
ዩሱፍ ያሲን
በየታሪክ መጋጠሚያው የሚወጥር ጥያቄ
በተለያዩ የሀገራችን ወሳኝ የታሪክ ምዕራፎች ኢትዮጵያ ለመፃኢ እድሏ ዕጣ ፈንታ ወሳኝ በሆነ መስቀለኛ የታሪክ መጋጣሚያ ላይ ትገኛለች ሲባል ደጋግመን ሰምተናል። በርካታ ጊዜያት መንታ መንገድ ላይ ናት ተብሎ ሲነገር እንሰማለን።
በተወሰነ የታሪክ መጋጠሚያ ላይ ሀገሪቷ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ተገኛለች መባሉ በተራው የወደፊት የጉዞ አቅጣጫዋ ወዴት ነው? የሚለው ጥያቄም ያስነሳል። በለውጥ ማዕበል ዋዜማ ላይ መገኘቷን ሁሉም ቢስማማም የጉዞዋ አቅጣጫ ወዴት እንደሆነ ግን አነጋጋሪ ይሆናል። በዲሞክራሲ ለውጥ አቅጣጫ ትከንፋለች ወይስ ፈርሳ፤ ትበታተናለች? ምኞትና ሟርት፣ ተስፋና ስጋት ይደበላለቃልና የሀገራችን መፃኢ ዕጣ ፈንታ ብዙ ዜጎቿን ያስቆዝማል፤ ያሳስባልም።
አልፎ ተርፎ ኃላፊነት የሚሰማቸው ግለሰቦች የሀገሪቷ መፃኢ ዕድል ያሳሰባቸው በርካታ ጎምቱ ጎመቱ ኢትዮጵያውያን ሃሳብ አፍላቂዎችም በእዚህ ርዕስ ሥር የተሰማቸውንና ያሳሳባቸውን በጽሑፍ መልክ ለማስፈር ሞካክረዋል። አንዳንዶቹ እንዲያውም መጻሕፍት ጽፈዋል። በ1974 ዋዜማ ላይ አቶ አዲስ ዓለማየሁ "ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር" ያስፈልጋታል የሚል ግልገል መጽሐፍ ጽፈው ለሕትመት አብቅተዋል። በ1989 ፕሮፈሠር መስፍን ወልደማርያምም እንዲሁ "ኢትዮጵያ ወዴት" የተሰኘ አነስተኛ መጽሐፍ አበርክተዋል። ሁሉም ሀገሪቷ ከምትገኝበት ወደ አልታወቀ እና ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ እንዳትጓዝ፣ የት መሄድ እንዳለባት በውል ባይጠቁሙም ወዴት አቅጣጫ መጓዝ እንደሌለባት ለመጠቋቆም ሞካክረዋል።
መልካም ዕድሎች የማስመለጥ አባዜ
በሀገሪቷ ዕጣ ፈንታ ወሳኝ ናቸው በተባሉት የታሪክ ማጋጣሚያ ላይ ስጋታቸው ብቻ ሳይሆን በመጋጠሚያ ላይ ቆም ብለን ወርቃማውን ዕድል ሳንጠቀም እንዳያልፍብን የማሳሳቢያ ደወል ነበር ያሳሙት፣ እነዚያ ሃሳብ አፍላቂዎቹ። በእኛ እድሜ እንኳን ያሁኑ ሦስተኛው ጊዜ ነው መልካም ዕድሉን ሳንጠቀምበት ሊያመልጠን ተብሎ ማሳሳቢያው ከየአቅጣጫው በመሰማት ላይ ነው።
በ1974 (ስድሳ-ስድስት) በመስቀለኛ በመንታ መንገድ ላይ ናትም ተባለ። እንደ ገና በ1992 (ሰማኒያ ሦስት) አሁንም በ2012 መጨረሻ ላይ። በሦስቱም ጊዜያት ሀገሪቷ በታሪክ መጋጣሚያ ላይ ትገኛለች ብቻ ሳይሆን በሦስቱም የታሪክ መጋጠሚያዎች ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለት መባሉ ሲደጋገም ሰምነተናል፣ ተመልክተናልም።
በሦስቱም ጊዜ ቆም ተብሎ ማሰብ ስለተሳነን ዕድሉን ሳንጠቀምበት ወይም መጠቀም ባለመቻላችን አምልጦናል ባዮች በርካቶች ናቸው - በመካከላችን። በ1974 (ስድሳ ስድስት) ላይ ተብሏል። በ1992 (ሰማኒያ-ሦስት) ላይ እንደገና ተብሏል። በ2005 (97ቱ ምርጫ) ወቅትም እንዲሁ ተብሏል። አሁንም በመጨረሻ የዛሬ 14 ወር የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ ዜናዊን ሕልፈት አስመልክቶ ቆም ብለን ስናስብ፤ ተመሳሳይ ጥሪው ላለፈው አንድ ዓመት ከየአቅጣጫው እየተስተጋባ ነው። ሰሚ ጆሮ አላገኝም እንጂ ልበል?! ከእነዚህ ሦስቱ የታሪክ መጋጠሚያዎት ትንሽ ወደ ኋላ ሄደት ብለንም የ1953ቱ "የታህሳስ ግርግር"፣ በባድሜ የወያኔና የሻዕቢያ ግጭት ጊዜም እንዲሁ ያልተጠቀምንበት መልካም ዕድል አምልጦናል ባዮች ከመካከላችን አሉ። አመለጡን የሚንላቸው ታላላቅ መልካም ዕድሎች አምስት አደረስናቸው። ያውም ባንድ ጎልማሳ ዕድሜ።
እንዲያም በያንዱንዱ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆም ብለን መቆዘም ስንጀምር ያሁኑ መስቀለኛ የታሪክ መጋጠሚያ ካለፈው ይበልጥኑ አሳሳቢ ነው መባሉም አልቀረም። በእዚህ ምክንያትም ለሀገሪቷ ዕጣ ፈንታ ይብልጥኑ ወሳኝ ብቻ ሳይሆኑ በዚያው ምክንያትም የባሰ አስፈሪ ናቸው መባሉም የተለመደ ነው። የሚገረመው እያንዳንዱ መስቀለኛ መንገድ ለሀገሪቷ ሕልውና ከደቀነው ስጋት አንፃር ማጋጣጠሚያው አሳሳቢነቱ፤ አስቸጋርነቱ፤ አደገኛነቱ አፅንዖት ሲሰጠው መስካሪዎች ነን።
በሦስቱም የታሪክ መጋጠሚያ ላይ ማምለጥ ያልነበረብት ወርቃማው ዕድል አምልጦናል ባዮች ብቻ ሳይሆን፤ በያንዱንዱ ታሪክ መጋጠሚያ ላይ ቆመን ያሁኗ ዕድል ማምለጥ አልነበረበት እንላለን። በቁጭት እንብሰከሰካለን። ይህን ወራቃማ ዕድል "ያስመልጠከን አንተ ነህ፣ አንተ ነህ" እየተባባልን እርስ በርሳችን እንካሰሳለን፤ ጣቶቻችንም እንቀሳሰራለን። በአመዛኙ በኤሊቶች መሃል። አሁንም ያለፈው መከራ መክሮን በታሪካዊው መጋጠሚያ ላይና መንታ መንገዱ ላይ ተመሳሳይ ታሪክ ስንደግም እንጂ ካለፈው ትምህርት ቀስመን ልብ ገዝተንና በተመክሮ በልጽገን በመልካም ዕድሉ ስንጠቀም ግን አልታየንም። "ወርቃማው ዕድል በማስመለጥ ማኛውም ዕድል አናስመልጥም ብለን ከራሳችን ጋር ቃል የገባን ይመስል እንደጋግመዋለን" ብሎ ወገኖቹ በሆኑት ዓረብ ኤሊቶች ላይ በምፀት የቀለደው ማሕበራዊ ተቺ ስሙን ለጊዜው ዘነጋሁት። በተተረተባቸው ያልታደሉ ኤሌቶች ተራ ውስጥ እኛም አለንበት። አንድ ሌላ አስገረሚው ትዝብት አለ። በሌላ በኩል ተደጋግሞ የታየው በነዚህ አጋጣሚዎች በሥልጣን ማማ ላይ ለመቆናጠጥ አመቺ ሁኔታ የተፈጠራላቸው ኤሊቶች ደግሞ እነሱ ለሥልጣን የበቁበት መልካም አጋጣሚ እንጂ ከእጅ ያፈተለከ መልካም ዕድል አድርገው አይመለከቱትም። በተቃራኒው ላንዱ ከእጅ ያመለጠ ወርቃማ ዕድል፣ ለሌላው የእሱ ቡድን ወይም ስብስብ ሀገሪቷን ከገደል አፋፍና መበታተን አደጋ እሱ ያዳነበት መልካም አጋጣሚ አድርጎ ይመለከተዋል እንጂ።
የሚደጋገም ጥያቄ፣ አዳዲስ ኹነቶች
ጥያቄው አዲስ አይደለም። ነገር ግን የሚነሱት ተመሳሳይ ሁኔታዎች መሠረት አድርገው አይደለም። ጥያቄው አንድ ቢሆንም ቅሉ በያንዳንዱ መስቀለኛ መጋጠሚያው የነበረው ሁኔታ ተመሳሳይ አልነበረም። እያንዳንዱ መጋጣሚያው በባሕርዩ፣ በተዳፋቱ፣ በአቅጣጫው ይለያል። አዳዲስ ተግዳሮች፣ ተጨባጩ ሁኔታዎቹ ካለፈው ልዩ ያደርጉታል። ደርግ ከሥልጣን የተወገደበት መንገድ የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ከተወገደበት አኳኋን ከስር መሠረቱ የተለየ ነበር። በሥልጣን ያለው መንግሥትም አወዳደቁ ከሁለቱም ውግደቶች እንደሚለይ አጠያያቂ ልሆን አይችልም መቼም። አሁን በሥልጣን ያለው መንግሥት የሚወገድበት ሁኔታ ከየአፄውም ከደርግ ከተወገደበት ሁኔታ መለየቱ ከቶ አያነጋግርም።
አንድ የግብፅ ቀልድ ልንገራችሁ፣ ትንሽ ለማብራራት። የግብፅ ቀልድ (ጆክ) እንዲህ ይሄዳል። ፕሬዝዳንት ሙባራክ ሞቶ በዚያኛው ዓለም ሁለት ከእሱ ቀደሞ የግብፅ ፕሬዝዳንቶች ማለት ጃማል ዓብዱል ናስር እና አንዋር አል-ሳዳት ያገኛል። ቀድመው መንግሥተ ሰማያት (ጀነት) የነበሩት ሟዋቾቹ ሮጠው ወደ እሱ ይመጡና፤ ናስር "በመርዝ ነው የገደሉህ?" ብሎ ይጠይቀዋል። ሙባራክም "አይደለም" ብሎ ይመልስለታል። የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሳዳትም ቀጠል አድርጎ "በሰገነቱ አመፀኛ ወታደሮች ተኩስ አርከፍክፎብህ ነው የገደሉህ?" ብሎ ይጠይቀዋል። አሁንም "አይደለም" ይለዋል ሙባራክ። ሁለቱ ባንድ ላይ "ታዲያ በምንድነው ለሞት ያበቁህ?" ብለው ያፋጥጡታል። ሙባራክም "ፌይስ-ቡክ" ብሎ ባንድ ቃል መለሰላቸው ይላል ጆኩ።
በስልሣ-ስድስትም ሆነ በሰማኒያ-ሦስት ፌይስ-ቡክ የሚባል ነገር አልነበረም። ትዊተርም አልተፈጠርም። የኤሌክቶሮኒክስ መገናኛ ብዙኀን በሀገራችንም ሆነ በዓለም አልነበሩም፣ በዚያን ዘመን ያልነበሩ በርካታ ኹነቶች አሉ። ብዙ ብዙ አዳዲስ የሕዝብ መቀስቀሻ መሣሪያዎች ብቻ ሳይሆኑ በዚያን ዘመን ያልነበረው በርካታ ኹነቶችና አዳዲስ ክስተቶች አሉ ዛሬ። በየካቲት 1966 ሕዝባዊ መነሳሳትና አብዮቱ ዋዜማ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ ፓርቲም አልነበረም። አንድ በኅቡዕ ከተደራጀ በስተቀር ማለቱ ሊኖርብኝ ነው መሰለኝ። በአለፉት ሁለቱ የለውጥ ዋዜማ ላይ ያልነበሩና ዛሬ ወሳኝ ሚና ካላቸው ጥቂቶችን ብቻ ለመጠቃቀስ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ፓልቶክ ግንቦት 20 ቀን 1983 አልነበሩም። ወያኔው አዲስ አበባ በተቆጣጠረ ዕለት።
በ66 ላይ 2 ሚልዮን የሚጠጉ መኖሪያቸውን በውጭ ሀገራት በአራቱ የዓለም ማዕዘናት ያደረጉ ዲያስፖራ የሚባል ጫና አሳዳሪ ስብስብ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምኅዳር ውስጥ ከቶ አልነበረም። ኢትዮጵያ በግንቦት 1983 የደርግ መንግሥት ለውጥ ዋዜማ ላይ ደበብ ሱዳንና ኤርትራ የሚባሉ ሉዓላዊ ጎረቤት ሀገራት አልነበራት። በ66 የካቲቱ መነሳሳት ላይ ጅቡቲ የምትባል ነፃ ሀገር አልነበረችም። ዛሬ ሀገሪቷ ሦስት አዳዲስ ጎሮቤት ሀገራት አፍርታለች። ኢትዮጵያም ባህር በር መውጫ አልባ ሀገር ናት። ዛሬ ከ90 በላይ ፓርቲዎች አሉ። አብዛኞቹ የብሔረሰብ አደረጃጀትን መሠረት ያደረጉ ናቸው። ደጋግመን እንደምንለው የራሱን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም በብሔረሰብ አደራጅቶ የሚያናክሳቸውና ባንድ አውራ ፓርቲ ፊታውራሪነት እንዳሻው የሚዘውራቸው ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በኃይማኖት አደራጅቶ የሚያተረማምስ መንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረበት ሀገር ሆናለች ኢትዮጵያችን።
እነዚህ ሁላ አዳዲስ እድገቶች ደግሞ ጫና አሳዳሪ ክስተቶች ናቸው። አዳዲስ አንደርዳሪ ግፊቶችን (ዳይናሚክስ) ፈጥረዋል። በየካቲት 66 ኢትዮጵያን ሙስሊሙ ሕብረተሰብ ከሁለተኛው ዜግነት ያልተላቀቀ እዚህ ግባ የማይባል የፖለቲካ ተሳትፎም ሆነ ጫና የማሳደር አቅም የሌለው ኃይል ነበር። ይህ ምንም ማጋነን የለበትም። 1966 ከዚህ ለመላቀቅ ከክርስቲያን ወገኖች ልክ እንደ ሌሎች ብሶት ያነሳሳቸው ክፍሎች ለእኩልነት መብት ድል እና ደመቅ ያለ ትዕይነተ-ሕዝብ ካደረጉት የሕብረተሰብ ክፍሎቹ አንዱ ነበር። ያለ ጥርጥር፣ ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከሥር መሠረቱ ተለውጧል። የዛሬዪቷ ኢትዮጵያ የየካቲት 66 ዓ.ም.፣ የግንቦት 83 አይደለችም። ለክፉም ለደጉም።
በ1991 (ሰማኒያ ሦስት) ላይ ከሰሜን በኩል የተረዳዱና በአጎራባች ሀገራት ድጋፍ የሕዝብን ድጋፍ ያጣውን የደርግ መንግሥት በቀላሉ ለማሸነፍና እነሱ የፈቀዱትን ወገኖች ብቻ ለሽግግሩ ሂደት የጋበዙበት ሁኔታ ነበረ። ያልፈቀዱትንም ከሽግግሩ ሂደት ያገለሉበት ሁኔታ ነው፣ የተመለከትነው። 1966 በግብታዊነት የፈነዳውን ሕዝባዊ አመፅ ማን መራው? የሚል ጉንጭ-አልፋ ክርክር በሰማኒያ ሦስት ላይ አልነበረም። መሪውና አሸናፊው "ብሶት የወለደው" በህወሓት የሚመራው ኢህአዴግ ነበር ጠርናፊው። ብዙ፣ ብዙ በዚያን ዘመን ያልነበሩ፣ አሁን ያሉ አዳዲስ ኹነቶች በሰፊው መጠቃቀስ ይቻላል። አጼ ኃይለ ሥላሴን ከሥልጣን ለማውረድ ከአካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ አስገዳጅነት የትግል ሥልት አማራጮችንና፣ የሽግግር ንድፎችን የሚያወጣና የሚያወርድ ኃይል በትግል ሜዳም አልነበረም። በከተማም አልነበረም። በሀገር ቤትም በውጭ ሀገራትም አልተደራጀም። ዛሬ እንደምናደርገው በትግል ሥልት አማራጮች ዙሪያ የሃሳብ መንሸራሸሮች አልተደረጉም። በአፄው ሥርዓትም ሆነ በወታደራዊ የደርግ ውድቀት ዋዜማ ላይ በሰላማዊና የትጥቅ ትግል አማራጮች ላይ በተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች መካከል ውይይት ሲደረግ አልተመለከትንም። ማስገደድ ወይስ ማስወገድ በሚባሉት አማራጮች ዙሪያም የሃሳብ ልውውጥ አላነታረከም። ሁለቱም መንግሥታዊ ሥርዓቶች የተወገዱበትን ስልት አካባቢያውና ዓለማቀፋዊ ሁኔታ የሚያሳርፉት ጫናም እንደምታ እንደ ራሱን የቻለ ታሳቢ ሲተነተኑ አላየንም።
በተደጋጋሚ መልካም ዕድሎች አመለጡን ብለን ብንቆጭም ቅሉ፤ ካለፉት የታሪክ መጋጠሚያዎች ከኢትዮጵያውን የፖለቲካ አክቲቪስቶች ከእነጭራሹ ምንም ትምህርት አልተማርንም ማለት አይቻልም። እነዚህ የተመለከትናቸው አዳዲስ ኹነቶች፣ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች በግምት ለማስገባት እየተሞከረ ነው፣ እንዳቅሚቲ። አዳዲስ አንደርዳሪ ግፊቶችም የራሳቸውን አሻራዎች እያሳደሩ ናቸው።
በተለያዩ ተለዋዋጭ ተጨባጭ ሁኔታዎች አስገዳጅነት፣ አዳዲስ የትግል ስልቶች መንደፍ የግድ ሆኖዋል። የትግል ስልት ክርክርም አንዱና ዋነኛው መወያያ ርዕስ ነው፤ ልክ እንደ ዛሬው። በሥልጣን ያለው መንግሥት ወደ ክብ ጠረጴዛ እንዲደራደር እናስገድደው ወይስ ከናካቴው እናስወግደው ሙግትና እሰጣ-አገባ በእዚሁ ምክንያት ይጧጧፋሉ። ሁሉገብ የትግል ስትራተጂ ከተመረጠ በኋላም ሁለቱን የትግል አማራጮች የመቀየጡ ጉዳይ ማነታረኩ አልቀረም። የአስወጋጅና አስገዳጅ አማራጮቹም ሆኑ ሰላማዊ እና የትጥቅ ትግል ምርጫ ዙሪያም አወሳሳቢ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ናቸው። ሁሉገብ ትግል የሁለቱ ቅልቅል ስለተባለ ብቻ ከየትኛው በምን ያህሉ ምጥጥን፣ ቅመማ ራሱን የቻለ ጥበብም ሳይንስም እየሆነ የማዳቀሉ ተግባር ቀላል ሆኖ አልተገኘም።
በምን ምጥጥን፣ ተቀይጦ ሲቀመም ነው ትክክለኛነቱና የፈዋሽነቱ ፍቱንነት ዋስትና ማረጋገጫው አስቸጋሪ ጥዳንጥድ ነው። በከሜስትሪው ላብራቶሪ የማይጣድ ነገር። እንኳን የትግል ቅመማ ምጥጥንና ዶዜጅ ይቅርና የቤት እመቤቶች ያንዱ ምግብ አሰራር በግምት እንጂ በትክክል ስንት የሻሂ ማንኪያ ጨው፣ ስንት ሚሊግራም ዱቄት ባንድ ላይ እንደሚቀላቀልና እንደሚቀመም እምብዛም በማይታወቅበት ባህል ላደግን ሰዎች። የሀገረ-ሰብ መድኃኒቶቻች ቅመማም ወደ ፈዋሽ እንክብሎች እንዳይቀየሩ ጋት አላነቃንቅ ያለውም ይሄው ትክክለኛው ምጥጥን ቅመመ ጉዳይ ነው ቢባል ማጋነን አለበትም። ሁሉም ድስት ጥዶ በነሲብ ይጨምራል። ያማረላት ሽር ጉድ ትላለች። ያረረባት "ድስት ጥዳ ታለቅሳለች" ከእነ ተረቱ።
በተለይም በሰላማዊ ትግሉ አቶ ግርማ ሞገስ በቅርቡ "ይሁን እንጂ የአልበርት አነስታይን ሰላማዊ ትግል ምርምር ተቋም ባልደረቦች እነጅን ሻርፕ የመሳሰሉት የዘመናዊ ሰላማዊ ትግል የፖለቲካ ሳይንስ ጠበብቶች እነዚህን 200 ሰላማዊ ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች ጥናት እንዲቻል ለማድረግ በሦስት አብይ ክፍሎች ከፍለዋቸዋል" በማለት ብዛቱን እንዳስገነዘቡት። እነዚህ ከ200 በላይ ዓይነቶቹን መቀየጡም እጅግ አስቸጋሪ ነው። በሰላማዊ የተጀመረው ትግል ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ደም-አፋሳሽ መተላለቅ እንዳይሸጋገር ስጋትም እንዳለም ሳንዘነጋ። ዛሬ ሦስት ዓመቱን ለማስቆጠር የተቃረበው የሶሪያ ደም-አፋሳሹ ትርምስ የተቀየረው ለሰባት ወራት ሰላማዊና ሕዝባዊ አልገዛባይነት አመፅ ሆኖ ከዘለቀ በኋላ መሆኑን ማስታወስ ብቻ በቂ ነው። ዓለም አቀፍ ጂሃዳዊ ኃይሎች፣ የአካባቢያዊና ዓለም አቀፍ መንግሥታት እጆቻቸውን በሶሪያ የውስጥ ጉዳይ ከዶሉ በኋላ ነው። መፈትፈት ከጀመሩ ወዲህ ነው። እነዚህ ሁላ ተጨማሪ አወሳሳቢ ኹነቶችና ናቸው።
1983 ላይ የተመለከትነው መሸነጋገል ወይም በ2005 (1997) ከምርጫ በኋላ የተመለከትነው አንዱ የሌለኛውን ጥረት መና ማድረጉና የማምከኑ ጥረቶች በብሔረሰብ ኤሊቶች መካካል ያለውን ያለመተማመን መገለጫዎች ናቸው። ዛሬም ባንድ ሀገር ልጅነት ላይ የተመሠረት የሀገር የጋራ ባለቤትነትን ያሰናከሉ ጥርጣሬዎች እንዳሉ ናቸው።
ተሰነጣጣቂ የኤሊቶች አንጃነት (Factionalized Elite) ለጨንጋፍ ወይም ውሉ ለተፈታ መንግሥትነትና ላላባሩ መናቆሮች ብቻ ሳይሆን ለሀገር ሕልውና ጭምር ጠንቅ ነው ይላል ከ2005 ጀምሮ የተጨነገፉ ሀገራት ሊስት በየዓመቱ የሚያወጣው ፎሪን ፖሊሲ (Foreign Policy) የተባለው በአሜሪካ የሚታተመው ጆርናል። የሚገረመው ለኢትዮጵያ የመጨረሻው ጠንቅ ተደረጎ የተወሰደውም እሱ ነው። እንደ አንድ ምክንያት በስሌት መግባቱ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ስፍራ ተቆናጥጦዋል። በዘንድሮው ሊስት ኢትዮጵያ በ20ኛ ስፍራ ላይ ትገኛለች። ለብዙ ዓመታት ሶማሊያ በአንደኝነት ሊስቱን ትመራለች።
ማጠቃለያ
በኤሊቶች መካከል መግባባት የሚያስፈልገው በሥልጣን ያለውን መንግሥት ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን በረጅሙ አብዛሕነታችንን ለማስተናገድ የሚያስችል ለነገ የማይባል ቀዳሚ ተግባር ነው። በእዚያኑ መጠን የሽግግሩ ጊዜ በስኬታማ አኳኋን እንዲጠናቀቅ የአብዛኛዎቹ ኃይሎች ይሁንታ የታከለበት መግባባት ወሳኝ ነው። ተቃዋሚዎች ገዢውን ፓርቲ ከሥልጣን ለማስወገድ የሚያደርጉት ግብግብ ላይ ብቻ ከማተኮር ጎን ለጎን በቦታው መመሥረት ስላለበት ሥርዓት ላይም በቅድሚያ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ይኖርባቸዋል። እስከተቻለ ድረስ የብዙዎቹ ይሁንታ የታከለበት ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ መግባቢያ ጉባዔ ተጠርቶ የአብዛኛው ሕዝብ ፍላጎትና ምኞት፤ ህዝባዊና ሀገራዊ መግባባት የሚገለጽበትና የአብዛኛዎቹ የፖለቲካ ኃይሎችና ቡድኖች ተሳትፎ የታከለበት የሽሽግሩ ቃል ኪዳን ላይ ስምምነት መደረሱ ሽግግሩን ይበልጥ አስተማማኝና ሳንካ-አልባ ያደርገዋል ተብሎ ይታመናል።
በመሸነጋገሉና አንዱ ለሌላው ወኪልና ወካይ ብሔረሰብ ድርጀት በመጠፍጠፉ ምትክ በመጨራሻው የዛሬ አንድ ዓመት ሁሉን በእጁ ቀፍድዶ ከያዘው ጠቅላይ ሚንስትር ከመድረኩ የሚሰናበትበትን ጊዜ ያባተው መልካም አዲስ ዕድል አለማስመለጥ ብቻ መልካም ዕድሎችን የማባከንም ሆነ ካመለወጡ በኋላ በቁጭት ከመብሰክሰኩ ይልቅ የዕጣ-ፈንታችን ወሳኞች እኛው ራሳቸን እንሆናለን። ያኔ ኢትዮጵያ ወዴት የሚለው ወጣሪ ጥያቄ እንቅልፍ አይነሳንም። ያን ጊዜ አቅጣጫችንን ጠቋሚ ካርታ በጋራ የመንደፉ ቀዳሚ ተግባር በምር ተያይዘናል ማለት ነው። ወዴት እንደምትመራ በውል እናውቀዋለን፤ ምክንያቱም ያን ጊዜ የጀልባ እርፉ በእጃችን ይሆናልና።
አመሰግናለሁ!
ዩሱፍ ያሲን
(በሦስተኛው የኢሳት ባዓል ላይ በሙኒክ (21. 09. 2013) የተዘጋጀ ንግግር)