ግርማ ካሳ
በፌስቡክ የሚጽፋቸውን እየሰበሰቡ አንዳንድ ድረ ገጾች ያስነብቡናል። በመቀሌ ነው የሚኖረው። ወጣት ነው። አብርሃ ደስታ ይባላል። የሚያምንበትን ከመናገርና ከመጻፍ ወደኋላ አይልም። በቅርቡ ከጻፋቸው አስተያየቶች አንዱ፣ ልቤን ማረከው። እኔም በዚያ ላይ ጨመር ለማድረግ ፈለኩ።

 

"ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩል ናቸው ብለን ከተነሳን ሁሉንም ብሔራቸውን ግምት ውስጥ ሳናስገባ (ምክንያቱም ሁሉም እኩል ናቸው ብለናልና) በኢትዮጵያዊነታቸው እንመዝናቸው። ለማንኛውም ጉዳይ (ለሥራ፣ ለሥልጣን ...) በትምህርት ደረጃቸው ወይ ብቃታቸው ወይ ሌላ፣ ለሁሉም በእኩል ሊያገለግል በሚችል መስፈርት እንመዝናቸው። ሁላችን እኩል ከሆንን፣ አንድ ሰው ለመመዘን ጉራጌነቱን፣ ኦሮሞነቱን፣ ትግሬነቱን፣ አማራነቱን፣ ዓፋርነቱን፣ ሶማሌነቱን፣ ጋምቤላነቱን ... ማስታወስ አያስፈልገንም። ማንነቱ የራሱ ነው። በኢትዮጵያዊነቱ መመዘን መቻል በቂ ነው።" ነበር ያለው ወጣቱ።

"አቶ መለስ ታመዋል፣ ሞተዋል" እየተባለ በሚወራበት ወቅት፣ ማን ሊተካቸው እንደሚችል፣ ከህወሓት/ኢሕአዴጎች ጋር ቅርበት ካለው አንድ ወዳጄ ጋር የተነጋገርኩትን ላካፍላችሁ። "ላለፉት ሃያ ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ትግሬ ስለነበረ አሁን ከሌላ ብሔር ብሔረሰብ መሆን አለበት" አለኝ። "ይሄማ አይሆንም። መስፈርቱ መሆን ያለበት፣ ዘር ሳይሆን ብቃት ነው" አልኩኝ። ትግሬም ቢሆኑ፣ አቶ አርከበ እቁባይ፣ መለስን ቢተኩ መልካም ሊሆን እንደሚችል ገለጽኩ። "ለምን?" ቢባል፣ አዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩ ጊዜ መልካም የሠሩ ተወዳጅ ስለነበሩ። መቼም አቶ አርከበ እቁባይን፣ በሌሎች ነገሮች ሊወቀሱ ቢችሉም፣ አዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩ ጊዜ "ጥሩ አልሰሠም ነበር" የሚሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብዙ ይኖራሉ ብዬ አላስብም። ታዲያ በተግባር መልካም ያደረገ ሰው፣ ከአንድ ዘር ስለሆነ ሀገር እንዳይመራ ለምን ይከለከላል? ሰው መመዘን ያለበት በዘሩ ሳይሆን በሥራው መሆን የለበትም ወይ?

እርግጥ ነው ህወሓት/ኢሕአዴጎች ዘረኛ በመሆናቸው፣ ጠዋትና ማታ የሚለፍፉት የዘር ፖለቲካን በመሆኑ፣ እኛንም በመጠኑም ቢሆን በክለውናል። እኛም እንደነርሱ "ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ ..." መባባል እየለመድን ነው። "ለሃያ ዓመት ትግሬ ገዝቶ፣ እንዴት ከአሁን በኋላ ትግሬ ይገዛል?" የምንልም አለን። መልካም ከሠራ፣ ሕዝብን ካከበረ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ፣ ሳይሰርቅ፣ ሳያጭበረብር በሕዝብ ከተመረጠ፣ ኢትዮጵያዊ እስከሆነ ድረስ ማንም ለምን መቶ ዓመት አይገዛም?! ዘሩ ምን እንደሆነ በማይታወቀው በመንግሥቱ ኃይለማርያም ዘመንና በትግሬው/ኤርትራዊው መለስ ዜናዊ ዘመን፣ የሕዝቡ ጥያቄ ዳቦና መብት ነበር። በወላይታው ኃይለማርያምም ዘመን አሁንም ጥያቄው ዳቦና መብት ነው። የገዚዎች ዘር ቢለዋወጥም፣ የሕዝቡ ጥያቄ አልተለወጠም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ "ማን ነው ሥልጣን ላይ ያለው?" የሚል ሳይሆን "ሥልጣን ላይ ያለው ምን እየሠራ ነው?" የሚል ነው።

ገዢዎቻችን ሁሉንም ነገር የሚያሰሉትና የሚያስቡት በዘር ሂሳብ ስለሆነ፣ በብቃት ሳይሆን በዘር ላይ ተመስርተው የሥልጣን ድልድል አደረጉ። አቶ ኃይለማርያምን ጠ/ሚኒስትር፣ ሌሎች ዘሮችን ለማስደሰት ደግሞ፣ ከሕገመንግሥቱ ውጭ፣ በርካታ ጠቅላይ ሚኒስትሮች መደቡ። አንዱን ለአማራ፣ አንዱን ለትግሬ፣ አንዱን ለኦሮሞ ሰጡ። የካቢኔ ድልድልም ሲደረግ፣ ክርክሩ "የኔ ዘር ብዙ አላገኘም ... ወዘተረፈ" የሚል ነበር። ብቃት ሳይኖራቸው ከአንድ ዘር በመሆናቸው ብቻ ኃላፊነት እየተሰጣቸው፣ ሕዝብን በሥራቸው የሚበድሉ በዙ።

ዜጎች በመታወቂያቸው ላይ፣ ወደዱም ጠሉም ዘራቸውን መጻፍ አለባቸው። ኦሮሞ ወይ ትግሬ ወይ አማራ ካላሉ መታወቂያ አያገኙም። ኢትዮጵያ ኤምባሲ ባሉ ፎርሞች ላይ ዘር መጠቀስ አለበት። እኔ በዘሬ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነቴ ነው መታወቅ ነው የምፈልገው፤ ዘሬ ኢትዮጵያዊነት ነው" የሚል ካለ አንዳች የዜግነት መብት አይሰጠውም። እንደ የውጭ ሀገር ሰው ነው የሚቆጠረው። ከዘር ውጭ አሁን ምን አለ ከዚህ ኋላቀር ጎጣዊ አመለካከት ነፃ ብንወጣ? ምን አለ አብርሃ ደስታ እንዳለው፣ በሥራችን ብንመዘን?

በነገራችን ላይ አብርሃ ደስታ፣ በቅርቡ ከአንድነት ጋር ለመዋሃድ ጥያቄ ያቀረበው የአረና ትግራይ አመራር አባል ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ደግሞ፣ የቀድሞ የአረና ሊቀመንበር፣ የተከበሩ አቶ ገብሩ አስራት የተናገሩት ግሩም አባባልም ነበር። ከአምስት ሺኽ በላይ በተሰበሰቡበት የመቀሌ ስብሰባ፣ አንድ ጥያቄ በአንድ የህወሓት ካድሬ ተጠየቁ። "እንዴት ከትግራይ ጠላቶች ጋር ትሠራላችሁ?" የሚል። አሳፋሪ፣ ዘረኛ ጥያቄ!!!! የአቶ ገብሩ መልስ ቀጥተኛና ግልጽ ነበር። "ማንም ኢትዮጵያዊ ለማንም ጠላት አይደለም። ትግራይ የትግሬዎች ብቻ ሳይሆን የአማራው፣ የኦሮሞው የሁሉም ናት። ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ብቻ ሳትሆን የትግሬው፣ የጉራጌው የሁሉም ናት። ማንም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የሀገሪቷ ግዛት የመኖር መብት አለው" የሚል የሚያረካ መልስ ነበር የመለሱት።

ከቀድሞ የአረና አመራር አቶ ገብሩ፣ ከአሁኑ ደግሞ አቶ አብርሃ ደስታ አባባሎች የምንማረው፣ የሠለጠነ የኢትዮጵያዊነትን ፖለቲካ ነው። ህወሓት/ኢሕአዴግ የሚያራምደው የዘር ፖለቲካ ምን ያህል የከሰረ መሆኑን በግልጽ ያጋለጠ ነው። አረናዎች፣ በትግራይ እንደነበሩት ጀግኖቻችን (ራስ አሉላ፣ አጼ ዮሐንስ) የኢትዮጵያዊነት አርበኞች፣ በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ቀዳሚ ሆነው የተሰለፉ መሆናቸውን እያስመሰከሩ ነው።

እዚህ ላይ አንድ ነገር አንርሳ። ይህ አሁን በህወሓት/ኢሕአዴግ አማካኝነት በሀገራችን ላይ የተዘረጋው፣ በዘር ላይ የተመሰረተው፣ ኋላቀር ፖለቲካ፣ ይህ አሁን ዜጎችን ትግሬ፣ አማራ ብሎ የመለየትና የመከፋፈል አባዜ፣ መሰረቱ ትግራይ አይደለም። በአንድ በኩል ከሞስኮ፣ ከማርክሲስቶች፣ ከነስታሊን ኮርጀው፤ እነዋለልኝ መኮንን ያመጡት፣ አንድ ወቅት ኢሕአፓዎችም ሲያራግቡት የነበረው፣ አጉልና እንግዳ ፍልስፍና ሲሆን፤ በሌላ በኩል አንዳንድ ክርስቲያን ተብዬ፣ ፀረ-ወንጌልና ፀረ-ፍቅር የሆኑ ሚሲዮናውያን (በተለይም በምዕራብ ኢትዮጵያ) የላካቸው መንግሥት ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት እንዲመቸው ሆን ብለው፣ ሕዝቡን ለመከፋፈል የረጡት መርዝ ነው። እነመለስ እና ስብሃት ነጋም ከዚያ ወስደው ነው፣ በትግራይና በተቀረው ኢትዮጵያዊ ላይ መርዘኛና ዘረኛ ሥርዓትን የጫኑት። እንጂ መሰረቱ ከትግራይ የሆነው ኢትዮጵያዊነት ነው!!!!!

ቃሊቲ እሥር ቤት የነበሩ ጊዜ፣ ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም ስለትግሬዎች የጻፉት አንድ ጽሑፍ ነበር። አንድ የቀድሞ ተማሪያቸው፣ ደርግ እንደወደቀ ትግራይ ሄዶ የታዘበውንና ያካፈላቸውን ነበር የጻፉት። ህወሓት በአደባባይ፣ የህወሓት እንጂ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ እንዳይውለበለብ አግዶ ነበር። "ኢትዮጵያዊነት" እንደ ሐጢያት ይቆጠር ነበር። ኢትዮጵያዊነት ወደዚያ ተጥሎ፣ ዋናውን ስፍራ የያዘው "ትግሬነት፣ ኦሮሞነት፣ ጉራጌነት ..." ነበር። ነገር ግን ሕዝቡ በአደባባይ ቢከለከልም፣ በቤቱ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይሰቅል ነበር። "ምንም እንኳን ህወሓት ቢያስፈራራንም ኢትዮጵያን ከልባችን የሚወስዳት የለም። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ልባችን ውስጥ ናት። ቤታችን ውስጥ ናት" እያሉ፣ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ከማንም በበለጠ እንጂ ባልተናነሰ መልኩ ያንፀባርቁ ነበር። በርግጥ ትግራይ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ፣ የነበረው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጠፍቶ ወይንም መንምኖ አያውቅም፤ እንደውም የበለጠ ጠነከረ እንጂ።

ለማጠቃለል አንድ ነጥብ ልጨመር። ሀገራችን ውስጥ ያሉ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ የተለያዩ ባህሎች ኢትዮጵያዊነት ናቸው። የኢትዮጵያ የተለያዩ ጅማቶች ናቸው። አፋን ኦሮሞ፣ ትግሪኛ፣ ጉራጌኛ እንዲስፋፋ ማድረግ ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከር ነው። እናቴ ጅጅጋ ተወልዳ ሐረር ያደገች ናት። ሶማሌኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ እኩል ትናገራለች። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ አማርኛ ያስተማሩኝ አንድ መምህር ነበሩ። ጉራጌኛ፣ ትግሪኛ፣ አፋን ኦሮሞ እና አማርኛ አቀላጥፈው ይናገሩ ነበር። ሲዳማዎች በብዛት በሚኖሩባት ይርጋለም ከተማ፣ ከወላይታ ቤተሰቦች ነው የተወለደችው። በደርግ ጊዜ አስመራ መካነ ሕይወት ሆስፒታል ለብዙ ዓመታት ሠርታለች። ሲዳምኛ፣ ወላይትኛ፣ አማርኛና ትግሪኛ ትናገራለች። አያስደስትም?! ቋንቋ ጠቃሚ ነው። ቋንቋ መግባቢያ ነው። ብዙ ቋንቋ ባወቅን ቁጥር እንጠቀማለን እንጂ አንጎዳም። ቋንቋ የልዩነት ምክንያት ሊሆን አይችልም።

ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ስል "የብሔረሰቦች ቋንቋ ይደጉ፣ የብሔረሰቦች ባህል ይስፋፋና ይዳብር" ማለቴ ነው። "አፋን ኦሮሞ፣ ትግሪኛ፣ ጉራጌኛ ... የኦሮሞዎች፣ ትግሬዎች፣ ጉራጌዎች ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች፤ የኢትዮጵያ ሀብቶች ናቸው" ማለቴ ነው። እንደ አንድ ሕዝብ ተያይዘን፣ የተለያዩ ቋንቋዎቻችንና፣ ባህሎቻችን እናዳብራለን። የኢትዮጵያ ውበቷ ብሔረሰቦቿ ናቸውና!!!!!!!
ግርማ ካሳ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ