አንድነት ፓርቲን በተመለከተ መልስ ለኢሳቱ ፋሲል የኔዓለም
ግርማ ካሳ
የኢሳት ባልደረባ አቶ ፋሲል የኔዓለም "የአንድነት ፓርቲ የመጪው ጊዜ ፈተና" በሚል ርዕስ የጻፉትን ዘ-ሐበሻ ድረገጽ ላይ አነበብኩ። አቶ ፋሲል ጽሑፉን ያቀረቡት እንደ ግል አስተያየት እንደመሆኑ፣ ኢሳትን በዚህ ውስጥ ጣልቃ አላስገባም። የአንድነት ፓርቲ አዲሱ ሊቀመንበር፣ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፣ ሀገር ውስጥ ለሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ከሰጡት ቃለ ምልልስ፣ የሚከተለውን በመጥቀስ ነበር አቶ ፋሲል ጽሑፋቸውን የጀመሩት፤
"ከኢሕአዴግ ጋር ገንቢ ግንኙነት እንዲኖረን እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ የጥላቻ ፖለቲካ ማብቃት አለበት። ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችን የሚያያቸው እንደ ጠላት ከዚያም አልፎ እንደሽብርተኛ ነው። በእኛም በኩል ኢሕአዴግን የምናየው እንደ አውሬ ነው። ምናልባትም የሠራውን ሥራ ሁሉ ዋጋ ያለመስጠት አለ። አንዳንድ ጊዜ ፖለቲካችን ኢሕአዴግን መቃወም ብቻ ሆኗል። ያ መቆም አለበት። ትልቁ ኳስ ያለው ኢሕአዴግ ዘንድ ነው። እኔ በበኩሌ ወደፊት በማደርገው እንቅስቃሴ ገንቢ ግንኙነት አድርገን ያለውን የፖለቲካ ምኅዳር ለሁላችንም እኩል መሆን አለበት" በማለት ነበር።
"ይህ መንገድ (ኢንጂነር ግዛቸው በሪፖርተር የታናገሩት)፣ ካልተሳሳትኩ ሦስተኛ መንገድ የሚባለውና አቶ ልደቱ አያሌው የ1997 ምርጫ አጣብቂኝ በገባበት ወቅት አምጥተው የደነጎሩት፣ በሌላ አነጋገር መሃል ላይ መቆም የሚባለው የፖለቲካ አካሄድ ነው" ሲሉ የጻፉት አቶ ፋሲል፤ ከአገዛዙ ጋር እርቅና ሰላም ለመፍጠር ፍቃደኝነት መኖሩ፣ በአንዱዓለም አራጌና በናትናኤል መኮንን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳደር እንደሚችል፣ የአንድነት ፓርቲንም አደጋ ላይ እንደሚጥል የሚያመላክቱ ሃሳቦችን ለማሳየት የሞከሩ ይመስላል። የአንድነት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔም፣ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራውን ሊቀመንበር አድርጎ በመምረጡ፣ ትክክል እንዳልሠራም አቶ ፋሲል ጠቆም ሳያደርጉንም አላለፉም።
እዚህ ጽሑፍ ላይ ስለ ኢንጂነር ግዛቸው ብዙ መጻፍ አልፈልግም። ኢንጂነሩን ከማንም በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃቸዋል። አብዛኞቹ ወጣቶች በሆኑበት፣ ከክልሎች ሁሉ በተወጣጡ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት የተመረጡም ናቸው። በዲሞክራሲ የማምን እንደመሆኔም፣ ሀገር ቤት ፊት ለፊት አፈናን እየተጋፈጡ ያሉ፣ የአንድነት ፓርቲ አባላት "እነዚህ ናቸው የሚመሩን!" ብለው የመረጡትን እደግፋለሁ። እቀበላለሁም።
አሁን ግን ኢንጂነሩ ለሪፖርተር ሰጡ በተባሉት ሃሳቦች ላይ፣ አንዳንድ አስተያየቶችን እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ። አንድነት ፓርቲ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ፤ የአንድነት ፓርቲ ከገዢው ፓርቲ ጋር፣ ችግሮችን በሰላምና በውይይት ለመፍታት ሁልጊዜ ፍላጎት እንደነበረው፤ የአንድነትን እንቅስቃሴ በቅርበት የሚከታተሉትና በሚገባ የሚያውቁት ነው። ገዢው ፓርቲ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን እያስቀመጠ፣ ለውይይት ፍቃደኛ አልሆነም እንጂ፤ አንድነት ሁልጊዜ ለውይይት በሩን የከፈተ ሰላማዊ ድርጅት ነው። ኢንጂነር ግዛቸው፣ የተናገሩት አዲስ አባባል አይደለም። አቶ ፋሲልንም ለምን እንዳስቆጣ አልገባኝም። የቀድሞ ሊቀመናብርት፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጠይቆ መረዳትም ይቻላል። (በነገራችን ላይ ኢንጂነር ግዛቸውን ከልደቱ አያሌው፣ አንድነትን ከኢዴፓ ጋር የማገናኘቱ ነገር ትንሽ አስቆኛል። አቶ ልደቱ በቅርቡ በአዲስ አድማስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ዙሪያና ስለ ኤዴፓ ሦስተኛ መንገድ ወደፊት በሰፊው እመለስበታለሁ)
አቶ አንዱዓለምን በተመለከተ አንድ ነገር ላንሳ። ይህ ወጣት የዴሞክራሲ ታጋይ፣ የሰላም ሰው ነው። ብሔራዊ እርቅ በሀገራችን እንዲመጣ የሚፈልግና የሚመኝ ነው። ኢንጂነር ግዛቸው የተናገሩትን እርሱም ቢሆን ይናገረው ነበር። አንዱዓለም ለዓላማው የፀና ሰው እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን። ነገር ግን ለዓላማ መጽናት ማለት በጥላቻ መሞላት ማለት አይደለም። የገዢውን ፓርቲ ተግባራት እንጂ አንዱዓለም የሚጠላው፣ አሳሪዎቹን እንደ ጠላት የሚያይ አይደለም። ልብ ገዝተው ወደ ቀናው መንገድ ከመጡ ከምንም በላይ የሚያስደስተው ያ ነው። ለዚህም ነው ቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩ እንደ አቶ ስዬ ያሉ ወገኖች፣ ወደ አንድነት እንዲመጡ ትልቅ አስተዋጾ ካደረጉ ወገኖች መካከል አንዱ የነበረው። አንዱዓለም፣ ሰላምና እርቅ እንደማይፈልግና ግትር እንደሆነ ተደረጎ መቅረቡ ትልቅ ስህተት ከመሆኑም ባሻገር፣ ዜጎች አንዱዓለም አራጌ ያልሆነው እንደሆነ አድርጎ እንዲያስቡ የሚያደርግ ጎጂ አቀራረብ ነው።
የአንድነት መሪዎች ከአንዱዓለም ጋር በቅርበት ይገናኛሉ። በአንድነት ውስጥ ያለውን ሁኔታም አንዱዓለም ያውቃል። እሥር ቤት ባሉ፣ በነአንዱዓለም እና በውጭ ባሉት አንድነቶች መካከል ልዩነት የለም። አቶ ፋሲል የሚያስታወሱ ከሆነ፤ በአዲስ አበባ፣ በቀበና አንድነት በጠራው በመቶ ሺሆች በተገኙበት ሰልፍ ላይ፣ ከእሥር ቤት የመጡ የነአንዱዓለም ደብዳቤዎች ተነበው ነበር። የመንፈሰና የዓላማ አንድነት በአንድነቶች ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነው። ለዚህ ነው አቶ ፋሲል አንዱን የአንድነት አባል በአንድ ወገን፣ ሌላውን በሌላ ወገን ማቅረባቸው ብዙ ያላስደሰተኝ።
ለሰላምና ለእርቅ በር መክፈት፣ ገዢውን ፓርቲ ለማነጋገር መፈለግ፣ ፍርሃት አይደለም፤ የሠለጠነ የፍቅር ፖለቲካ እንጂ። ስለፍርሃት ማወቅ ከተፈለገ፣ ያገር ቤቱን ትግል ሸሽተው፣ በውጭ "ዘራፍ" የሚሉ፣ በእነ አቶ ፋሲልም ይደገፋሉ የሚባሉ፣ የአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችን ማነጋገሩ መልካም ሊሆን ይችላል። ኢንጂነር ግዛቸው እዚያው አገዛዙ አፍንጫ ሥር ሆነው እየታገሉ ያሉ ናቸው። ውጭ ሆነን እርሳቸውን "ፈሪ" ማለት፣ ትንሽ የሚያስተዛዝብ መሰለኝ።
የአንድነት ፓርቲ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራቶች በሦስት መስክ፣ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ዝግጅት ላይ እንዳለ በአንድነት ራዲዮ ኢንጂነር ግዛቸው ለማስረዳት ሞከረዋል። የመጀመሪያው የተበታተኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን አሰባስቦ ጠንካራ ተቃዋሚ መመስረት ነው። የሕዝቡ ጥያቄ "ተባበሩ ወይንም ተሰባባበሩ" የሚል ነው። የህዝብን ጥያቄም አክብሮ፤ በዚህም ረገድ ንግግሮች ከዓረና ትግራይና እና ከመኢአድ ጋር እየተደረጉ ናቸው። ውይይቱ ተሳክቶ መልካም ዜና እንሰማለት የሚል ተስፋ አለኝ።
ሁለተኛው ወደ ሕዝቡ ወርዶ የፖለቲካ ሥራ መሥራት ነው። ከሰኔ 2005 እስከ መስከረም 2006 ዓ.ም. ተደረጎ በነበረው የሚሊየሞች ድምፅ ለነፃነት እንቅስቃሴ ወቅት፤ በደሴ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በመቀሌ፣ በአዲስ አበባ፣ በአዳም፣ በፍቼ፣ በባሌ/ሮቢ፣ በወላይታ ሶዳ፣ በአርባ ምንጭ፣ በጂንካ፣ ... ሰላማዊ ሰልፎች ተደርገዋል። ሕዝቡ ድረስ ተኺዶ፣ በየበሩ እየተንኳኳ፣ ወረቀቶች እየታደሉ ሕዝቡ ለመብቱና ለነፃነቱ እንዲነሳ የመቀስቀስ ሥራ ተሠርቷል። ያኔ የተደረገው አይነት እንቅስቃሴ፣ በስፋት፣ በተጠናከረ መልኩ፣ የሚሊየኖች ድምፅ ለነፃነት ክፍል ሁለት፣ ሦስት በሚል ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ፤ አገዛዙ ፍቃደኛ ከሆነ፤ ያሉትን የፖለቲካ ችግሮች በሰላምና በውይይት መፍታት ነው። ኢንጂነር ግዛቸው "ኢሕአዴግ ፍቃደኛ ካልሆነ፣ እጆቻችንን አጣምረን እንቀመጣለን" አላሉም። የአንድነት ፓርቲም ከአገዛዙ መመሪያ የሚቀበል ድርጅት አይደለም። የትም ቦታ ቢኬድ፣ ችግሮችን በሰላም መፍታት ከተቻለ፣ ጭንቅላት ያለው ሰው ሁሉ፣ የሚመርጠው መንገድ ያ ነው። ኢንጂነሩ ግልጽ አድርገውታል። "ኳሷ ኢሕአዴግ ሜዳ ላይ ናት" ነው ያሉት። ኢሕአዴግ በሩን ከዘጋ፣ ለውይይት ፍቃደኛ ካልሆነ፣ የታሰሩ የሕሊና እሥረኞችን ካልፈታ፣ ትግሉ አይቋረጥም። ነፃነቱን እና መብቱን ሕዝቡ በልመና የሚያገኘው አይደለም። ታግሎ እንጂ።
አቶ ፋሲል ስለ ምርጫ ስነ-ምግባር ኮድም አንስተዋል። የምርጫ ስነምግባር ኮዱን ካልፈረሙ ኢሕአዴግ ሊያነጋግራቸው እንደማይፈልግ የገለጹት አቶ ፋሲል፤ ኮዱን አንድነት መፈረም እንደሚኖርበትም ይናገራሉ። እዚህ ላይ ትክክል ናቸው። ገዢው ፓርቲ ከነአብነግ ጋር ያለምንም ችግር ሲደራደር፤ ከነአንድነቶች ጋር ግን የምርጫ ሥነ ምግባር ኮዱን ፈርሙ የሚል ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ በሩን መዝጋቱን እናውቃለን። የምርጫ ሥነ ምግባር ኮዱን አንድነት ከፈረመ ደግሞ፣ እንደ ፈሪና ደካም ተቆጥሮ፣ የአንድነት ተቀባይነቱ እንደሚያሽቆለቁል አቶ ፋሲል ለመግለጽ ሞክረዋል። በዚህ ከርሳቸው ጋር ልዩነት አለኝ።
ጋዜጠኛ ፋሲል ምን ያህል ስለ ምርጫ ሥነ-ምግባር ኮዱ እውቀት እንዳላቸው፣ ምን ያህልም እንዳነበቡት አላውቅም። ኮዱ የሀገሪቷ ሕግ ሆኖ የወጣ፣ አንድነትም ሆነ ሀገር ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ሁሉ የሚቀበሉት ነው። በኮዱ ያሉ አንቀጾች ከአንድነት መርሆዎችና እሴቶች ጋር የሚቃረኑ አይደሉም። በመርህ ደረጃ፣ በኮዱ በተካተቱት፣ ያኔም የአንድነት ፓርቲ ችግር አልነበረውም። በኮዱ ዙሪያ የተነሱ ውዝግቦች፣ የሥነ ምግባር ኮዱ መጥፎ ሆኖ ሳይሆን፣ በሌሎች ተጨማሪ ሁለት ሰነዶች ላይ ለምን ንግግር አልተደረገም በሚል ነበር። ሕግ ሆኖ የወጣው የሥነ ምግባር ኮዱ፣ የምርጫ ተወዳዳሪዎች ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የሚተነትን ነው። የምርጫ አስፈጻሚውን (ምርጫ ቦርድ) እንዲሁም የምርጫ ታዛቢዎች ሊያደርጉት ስለሚገባው የሚተነትኑ ሌሎች ሁለት ሰነዶች ነበሩ። በነርሱ ላይም ስምምነት ለምን አልተደረገም የሚል ነበር ክርክሩ።
አንድነት ያኔ በመድረክ ውስጥ ሆኖ ነበር የሚደራደረው። መድረኩ፣ "ሦስቱንም ሰነዶች ተወያይተን በሦስቱም ላይ መፈረም ነው ያለብን" የሚል አቋም ያዘ። ከዚህም የተነሳ እራሱን ከድርድር አወጣ። ያ ውሳኔ በኔ ግምት ስህተት ነበር። አንድነት የያኔውን የመድረክ ስህተት መድገም ያለበትም አይመስለኝም። አንዱን ሰነድ ፈርሞ፤ በሌሎቹ ሁለት ላይ በሂደት መነጋገር ይቻል ነበር'ኮ። የአንድነት ፓርቲ በሕግ የወጣውን እና የሚቀበለውን የምርጫ ሥነ-ምግባር ኮድ ቢፈርም፤ ከዚያም የተነሳ ከአገዛዙ ጋር የውይይትን በር ማስከፈት ቢችል፤ ትልቅ ሥራ ነበር የሚሠራው። አንዳንዴ በትንሹም በትልቁም ማክረር ጥሩ አይመስለኝም። ከዋናዎቹና አበይት ከሆኑ ፕሮግራሞቻችን ጋር እስካልተጋጨ ድረስ፣ በሌሎች ማናቸውም ጉዳዮች ዘንድ ፈረንጆች እንደሚሉት ፍሌክሲቢሊቲ ሊኖረን ይገባል።
በመጨረሻ ይሄን ብዬ ላጠቃል
የአንድነት ፓርቲ ይኸው ከተመሰረተ ጀምሮ ሦስት ጠቅላላ ጉባዔዎችን አድርጓል። በሦስቱ የተለያዩ ሊቀመናብርት ነው የተመረጡት። የግድ ሌላ ጠቅላላ ጉባዔ መደረግ የለበትም፤ በማናቸውም ጊዜ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ኢንጂነር ግዛቸውን ከኃላፊነታቸው ሊያነሳ ይችላል። ፓርቲውን በትክክል የማይመሩ ከሆነ፣ አብዛኛው የአንድነት አባል ሳይደግፍ፣ ድርጅቱን በአንድ አቅጣጫ ሊወስዱት አይችሉም። ተጠያቂ ናቸውና። በመሆኑም "ከአሁን ለአሁን እንዲህ ይሆናል" የሚል መሰረት የሌለው ውዥንብሩ ውስጥ ባንገባ ጥሩ ነው። አንድ ሰው ገና ሥራ ሳይጀምር ወደ ትችት መሮጡ አግባብነት ያለውም አይመስለኝም። የአንድነት ፓርቲ ላይ ከወዲሁ ከማሟረት፣ ከዳር ሆኖ ጠጠር ከመወርወር፣ ፓርቲው ሀገር ቤት የሚያደርጋቸውን እንቅስቅሴዎች መደገፍ፣ ፓርቲው ሥራውን የማይሠራ ከሆነ ደግም፣ እንደደገፍነውም ያኔ መተቸት የአባት ነው።
እንግዲህ እነዚህ ጥያቄዎች ለአቶ ፋሲልም ሆነ ለተቀረው ኢትዮጵያዊም መጠየቅ እፈልጋለሁ። በኢትዮጵያ ሕዝብ ጉልበት እና አቅም እንተማመናለን ወይ? የኢትዮጵያን ሕዝብ ከላይ እስከ ታች ማደራጀቱ ዋና የፖለቲካ ተግባር ነው እንላለን ወይ? በአዲስ አበባ እና ክልሎች ሰላማዊ ሰልፎች፣ ህዝባዊ ስብሰባዎች በስፋት እንዲደረጉ፣ ህዝቡ በራሱ እንዲተማመን የማድረግ ሥራ እንዲሠራ፣ በ547 ወረዳዎች ጊዜና ጉልበታቸውን ሰጥተው፣ ለመታሰር፣ ለመገደል ዝግጁ የሆኑ፣ ሕዝቡን የሚያደራጁ ታጋዮች በስፋት እንዲሰማሩ፣ ሕዝቡ ያነባቸው ዘንድ ጋዜጦች፣ የቅሰቀሳ ወረቀቶች በስፋት እንዲሰራጩ እንፈልጋለን ወይ? መልሳችን አዎን ከሆነ፣ ታዲያ የዚህ ጥረት አካል መሆን አይጠበቅብንም?



