አንዱዓለም ግንቦት ሰባት ከተባለ፤ እኔም ግንቦት ሰባት ነኝ
ግርማ ካሳ
"በሕገመንግሥቱ የመደራጀት መብታቸው የተጠበቀላቸው ፓርቲዎችን አልከሰስንም። ፓርቲዎችን ግን ሽፋን አድርገው ሥርዓቱን ወይንም ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ እንንቀሳቀሳለን የሚሉ ኃይሎችን ግን ዛሬም፣ ነገም፣ ሕጉን የማስከበር ግዴታና ኃላፊነት ስላለብን ከመከሰስ አያመልጡም ማለት ነው።"
ኢቲቪ በ"ሽብርተኝነት" ላይ፣ በቅርቡ ባቀረበው አሳዛኝ ዶኩሜንተሪ ላይ፣ የፌደራል መንግሥት አቃቤ ሕግ፣ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ የተናገሩት ነበር።
እኝህ የሕግ ባለሞያ እየደጋገሙ ሕግን ስለማክበርና ስለሕገመንግሥቱ ነግረውናል። ስለሕገመንግሥት ካነሳን አይቀር አንድ ነገር ጣል ላድርግ። የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 4 "በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይንም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኀን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል" የሚል ድንጋጌ ያካትታል። ኢቲቪ በሕዝብ ገንዘብ የሚተዳደር እንደመሆኑ ይህ የሕገመንግሥት አንቀጽ ይመለከተዋል። ነገር ግን ኢቲቪ በቀጥታ፣ ሕገመንግሥቱን ሲንድ፣ ገለልተኛነት በጎደለው መልኩ የአንድ ድርጅት የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያ ሲሆን ነው እያየን ያለነው። እነ አንዱዓለም አራጌ ላይ፣ ኢቲቪ የአንድ ወገንን አቋም የያዘ፣ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲያዥጎደጉድ፣ ቢያንስ ቢያንስ ጥቂት ሰኮንዶች፣ የአንዱዓለምን ጠበቃዎች፣ ወይንም ቤተሰብ፣ አሊያም የትግል አጋሮቹ የሆኑት የአንድነት አመራር አባላትን ለማነጋገር አልተሞከረም። እንግዲህ ከዚህ የምንረዳው፣ ሕግን በማክበር አኳያ፣ ህወሓት/ኢሕአዴጎችና ኢቲቪ፣ አንድ ጣታቸውን ወደሌሎች ሲጠቁሙ፣ አራቱ ጣቶቻቸው ወደ እነርሱ መዞራቸውን፣ ሕገመንግሥቱን እየጣሱ ያሉ እነርሱ መሆናቸውን ነው።
"አንዱዓለም አራጌን በተመለከተ፣ የግንቦት ሰባትን ተልዕኮ ለማስፈጸም ሀገር ውስጥ በህቡዕ (ስውር) ይንቀሳቀሳል፤ በሰላማዊ ትግል እንታገላለን የሚሉ የፓርቲዎችን ሽፋን አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረ በመሆኑ በቂ ማስረጃ አቅርበናል" ሲሉ ነበር የፌደራል አቃቤ ሕጉ ለኢቲቪ አክለው የገለጹት። ምን አይነት መረጃ እንዳቀረቡ ግን አልነገሩንም። ለምን ቢባል ምንም ስለሌለ።
አንዱዓለም ያደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ሲያደርግ የነበረው በግልጽና በገሃድ ነው። ለተለያዩ ፓልቶክ ክፍሎች፣ ሀገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙ ሜዲያዎች በርካታ ቃለ መጠይቆችን ሰጥቷል። በሀገር ቤት፣ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ሆነ በተለያዩ ቦታዎች በተደረጉ ውይይቶችና ስብሰባዎች ያቀረባቸው ንግግሮች በሙሉ የተደበቁ አይደሉም። ውጭ ካሉ ኢትዮጵያዊያን ጋር (አንዱም እኔው ነበርኩ)፣ ብዙ ጊዜ በስልክ ሃሳቦችን ተለዋውጧል። በስልክ ያደረጋቸው ንግግሮችም፣ 24 ሰዓት የሰላማዊ ተቃዋሚ መሪዎችን ስልክ በሚጠልፈው ቴሌ ዘንድ የተሰሙ ናቸው። ቤቱና ቢሮው ከላይ እስከ ታች ተበርብረው፣ የሚስጥራዊ የኮሚኒኬሽን መሣሪያዎች፣ ቦምቦች፣ ፈንጂዎች፣ ሚስጥራዊ ሰነዶች አልተገኙም። ኢሜሎቹ በሙሉ ተነበዋል። አንዱዓለምን ከግንቦት ሰባት ጋር የሚያገናኝ፣ በህቡዕ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ የሚያመለክት አንዳች መረጃ አቃቤ ሕግ አላቀረበም። መረጃዎች ቢኖሩ ኖሮ፣ "እንኳን ዘንቦብሽ ድሮም ጤዛ ነሽ" እንደተባለ፣ ዜጎችን በማዋረድና በማሳነስ የሚታወቀው ኢቲቪ፣ ይሄን ጊዜ በስፋት ያወራልን ነበር።
ኢቲቪ ግን አንዱዓለምን ለመክሰስ ያቀረበው፣ አንድ የአንድነት አባል የነበሩ፣ ተስፋሁን አናጋው የተባሉ ሰው የተናገሩትን ነው። አንዱዓለም ከታሰረ በኋላ አቃቤ ሕጎች መረጃ ማቅረብ ባለመቻላቸው፣ የውሸት መረጃዎች ማሰባሰቡ የግድ ሆነባቸው። የታሰሩ ሌሎች የአንድነት አባላትን ማግባባት ጀመሩ። "በአንዱዓለም ላይ እኛ ተናገሩ የምንላችሁን ከተናጋራችሁ እንፈታችኋለን" ብለው እጆቻቸውን ጠመዘዙ። ብዙዎች በአንዱዓለም ላይ የውሸት መረጃ ማቅረቡ ሕሊናቸውን ስለከበደው ፍቃደኛ አልሆኑም። ነገር ግን እንደ ተስፋሁን አናጋው፣ የሚባሉ ደካማ ሰዎች ተገኙና የውሸት ምስክርነት ቀረበ። እንግዲህ በአገዛዙ ካድሬዎች ተቀናብረው ከቀረቡ የውሸት ምስክርነቶች ውጭ፣ ቅንጣት የምታክል፣ አንዱዓለምን ሽብርተኛ ወይንም ከግንቦት ስባት ጋር የሚሠራ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ አልቀረበም።
"ግንቦት ሰባት፣ ግንቦት ሰባት ..." እንባላለን። ከጅምሩ በግንቦት ሰባት ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ያለኝ ሰው ነኝ። የግንቦት ሰባት ፖለቲካ አይመቸኝም፣ ለሀገርም ይጠቅማል ብዬ አላስብም። ግንቦት ሰባቶች ከያዙት የተሳሳተ መንገድ እንዲመለሱ፣ በሻዕቢያ ድጋፍ ሳይሆን፣ በሕዝብ ጉልበት በመተማመን ወደ ሰላሙ መንገድ እንዲመጡ መክሬአለሁ። በተለያዩ ጊዜያት ለአንባቢያን ያቀረብኳቸውን ጽሑፎቼን መመልከት ይቻላል።
ከቅንጅት ጊዜ ጀምሮ በሀገር ውስጥ በሰላም ለውጥ ለማምጣት የሚሠሩ ድርጅቶችን ደግፌያለሁ። በተለይም የአንድነት ፓርቲ በጣም የሚመቸኝ ፓርቲ እንደመሆኑ፣ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ፣ ከፓርቲው አመራር አባላት ጋር ሃሳብ የተለዋወጥኩባቸው በርካታ ጊዜያት ነበሩ። አንዱዓለም አራጌ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ የልጆች አባት፣ የሰላማዊ ትግል አርበኛ ነው። አንዱዓለም ስለ ትጥቅ ትግል ያለውን አመለካከት አውቃለሁ። በየትኛውም መድረክና ፍርድ ቤት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እጄን ጭኜ የምመሰክረው ነው። አንዱዓለም አራጌ የግንቦት ስባት አባል ወይንም ሽብርተኛ ነው የሚለውን፣ በምን መስፈርትና መልኩ ልቀበለው አልችልም። በርግጥ አንዱዓለም የግንቦት ሰባት አባል ከተባለ፣ እኔም የግንቦት ሰባት አባል ነኝ እንደ ማለት ነው።
በጣም ያሳዝናል። እንደ አንዱዓለም አራጌ አይነት ሀገር ወዳድ ዜጎች፣ ሀገራቸውን በመውደዳቸው፣ የሕዝብ መብት ይከበር በማለታቸው፣ "ሽብርተኞች" በሚል አሳዛኝ ክስ ሲታሰሩ ማየት፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዜጎች ቀና ብለው የሚራመዱባት ሳይሆን፣ አሳፋሪ ድራማ የሚካሄድባት፣ ሕግ መቀለጃ የሆነባት ሀገር መሆኗ፣ በርግጥ ልብን የሚያደማ ነው።
እንግዲህ፣ ሁሌ እንደማደርገው፣ ጥሪ ለኢሕአዴጎች አስተላልፋለሁ። ኢሕአዴግ ውስጥ፣ ለሀገርና ለሕዝብ የሚያስቡ ካሉ፣ በድርጅታቸው ውስጥ እየተደረገ ያለውን አፈናና ግፍ በቃ የማለት አቅምና ጉልበት ሊኖራቸው ይገባል ባይ ነኝ። ድርጅታቸው ውስጥ ያሉ ጥቂቶች ድርጅታቸውን ይዘው ገደል እንዲወስዱ ሊፈቀዱላቸው አይገባም። እነ አንዱዓለምን በማሰር ኢሕአዴግ ምንም የሚጠቀመው ነገር የለም። እነ አንዱዓለምን በውሸት ክስ ከሶ፣ በቴሌቭዥኝ ደግሞ ስማቸውን ማጉደፍ፣ ነውር ነው። ኢሕአዴግ የበለጠ እንዲጠላ የሚያደርግ ነው። የዓረና ትግራይ አመራር አባል አብርሃ ደስታ አንዴ ሲጽፍ፣ የህወሓት እምብርት በነበረችው የትግራይ ክልል፣ አንዱዓለም አራጌ በጣም ተወዳጅ ፖለቲከኛ እንደሆነ ገልጾ ነበር። አንዱዓለም አራጌ፣ በክልሎች ሁሉ ሕዝብ የሚያውቀው ጀግና መሪ ነው። በርሱ ላይ እየተደረገ ያለው ዘመቻ፣ የበለጠ አንዱዓለምን ከፍ የሚያደርግ፣ ኢሕአዴግን ደግሞ የሚያሳንስ ነው። አንዱዓለምን እና ሌሎች የሕሊና እስረኞች፣ አለመፍታት በቀጥታ ከሕዝቡ ጋር እንደመላተም ነው። አይጠቅምም። ጉዳት አለው።
ለኢሕአዴጎች ጥሪ ባቀርብም፣ የነአንዱዓለም ጉዳይ፣ የኢሕአዴጎች ጉዳይ ብቻ ግን አይደለም። ኢሕአዴጎች ወደ ሕሊናቸው ተመልሰው መልካም ነገር ያደርጉ ዘንድ እነርሱን ማነጋገርና ለማሳመን መሞከር፣ ማበረታታት ተገቢ ነው የሚል እምነት ቢኖረኝም፣ ሁሉንም ነገር ከነርሱ ጠብቆ ቁጭ ማለቱ ግን፣ እጅግ በጣም ትልቅ ስህተት ነው። እነርሱ ቢሰሙ መልካም ነው፤ ካልሆነ ግን እያንዳንዳችን መብታችንን የማስከበር ኃላፊነት ያለብን ይመስለኛል። ዛሬ እነ አንዱዓለም ናቸው። ነገ እያንዳንዳችን ቤት ይንኳኳል። ዛሬ ሊመቸን ይችላል። ነገር ግን ለሕይወታችን ምንም ዋስትና አይኖረንም።
አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ፊታችንን አይቶ ከጠላን፣ በቀላሉ ወደ ወህኒ ሊወረወረን የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ማወቅ አለብን። አለን የምንለውን ቢዝነስ አንዱ ከፈለገው፣ "ያለ የሌለውን እያመጡ፣ ይሄን ያህል ግብር ክፈል" ተብለን ከጨዋታ ውጭ በቀላሉ ልንሆን የምንችልባት ሀገር ነው ያለችን። አቤት የምንልበት የሕግ ሥርዓት የለም። አብዛኞቹ ዳኞች በመመሪያ የሚፈርዱ ካድሬዎች ናቸው። በመሆኑም፣ ኢትዮጵያ፣ ሕግ የበላይ የሆነባት፣ ለሁሉም ዜጎቸ እኩል የሆነች፣ ኢትዮጵያዊያን ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ ሃሳባቸውን በነፃነት መግለጽ የሚችሉባት፣ መቀባበል፣ ይቅርታ፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ ፍትህና ወንድማማችነት የሰፈነባት፣ የበለፀገች ሀገር እንድትሆን፣ እያንዳንዳችን የድርሻችንን መወጣት አለብን። ዳር ሆኖ ተቀምጦ ማውራት ይብቃ። ሌሎች ለምን እንዲህ አላደረጉም ብሎ መክሰስ ይብቃ። ሌሎች ሞተው በነርሱ አስክሬን ላይ ተረማምደን ለመሻሻል መሞከር ይብቃ። ሀገራችን የእስክንደር፣ ወይንም የአንዱዓለም፣ ወይንም የበቀለ ገርባ፣ ወይንም የርዕዮት ዓለሙ ብቻ ሳትሆን የሁላችንም ናት፤ ሁላችንም ተስፋ ሳንቆርጥ፣ ሌሎች ነፃ እንዲያወጡን ሳንጠብቅ፣ የድርሻችንን እንወጣ።



