ፎቶ ከኢዜአ Photo from ENAታደሰ ብሩ
በቅድሚያ የሚከተለውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን (ኢዜአ) ዜና አጣጥሙልኝ።
በባሌ ዞን በንብ ማነብ ፓኬጅ የተሳተፉ አርሶ አደሮች ከ53 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚበልጥ ገቢ አገኙ
ጎባ ጥር 10/2006፦ በባሌ ዞን ከእርሻ ስራ በተጓዳኝ በንብ ማነብ ፓኬጅ የተሳተፉ አርሶ አደሮች ከ53 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘታቸውን የዞኑ የእንስሳት ሀብት ልማትና ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

 

በጽህፈት ቤቱ የእቅድና ግምገማ በለሙያ አቶ ታዬ ኣጋ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት የማር ምርቱን ለአካባቢው ገበያ ያቀረቡት ከ89ሺ 200 የሚበልጡ አርሶ አደሮች ናቸው።

የማር ምርቱን ለአካባቢያቸውና ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ከሆኑት አርሶ አደሮች መካከል ከ21 ሺህ 699 የሚበልጡት ሴቶች መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በዞኑ ዘጠኝ ደጋማ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች የማር ምርቱን የሰበሰቡት ከ100 ሺ ከሚበልጡ ባህላዊ፣ የሽግግርና ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች በመጠቀም እንደሆነ አብራርተዋል።

በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት ለገበያ የቀረበው የማር ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ1 ሺህ ኪሎ ግራም ብልጫ ያለው እንደሆነም አስታውቀዋል።

ጽህፈት ቤቱም የዞኑን አርሶ አደሮች የማር ምርትና ምርታማነት በሁለት እጥፍ ለማሳደግ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሮቹ በማሰራጨት ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል። (ይህንን ዜና ከምንጩ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)

* * * * *

ዜናውን በጥንቃቄ ያላነበበ ሰው የተለመደ ልማታዊ ዜና በመሆኑ ምንም የሚያስደንቅ ነገር አያገኝበትም። ሆኖም ትንሽ ስሌት ብጤ እንጨምርበት።

ሀ. ከሽያጭ የተገኘው ገንዘብ 53.7 ሚሊዮን: ብር 53, 700, 000
ለ. የአምራቾቹ ብዛት: 89, 200 ገበሬዎች
ሐ. የፈጀባቸው ጊዜ: 6 ወር

ከዚህ በመነሳት የሚከተለውን ማስላት ይቻላል።

የአንድ አምራች አማካይ የሽያጭ ገቢ: 53, 700, 000 ÷ 89, 200 = ብር 602.02
የአንድ አምራች አማካይ ወርሃዊ የሽያጭ ገቢ: 602.02/ 6 = ብር 100.34

በዚህ "ድንቅ ስኬታማ ፓኬጅ" አንድ ገበሬ በወር በአማካይ የሚያገኘው የሽያጭ ገቢ ብር 100.34 ነው። በአማካይ ማለት ደግሞ ከዚህም በታች የሚያገኙ ብዙ አሉ ማለት ነው። በተለይ አንድ ብርቱ "ልማታዊ" ገበሬ ካለ የሌሎቹ ሰብስቦ ነው የሚወስደው። ለማንኛውም ግን የገበሬዎች ምርታነት እኩል ነው ብለን እናስብና ስሌታችንን በአማካይ እንቀጥል።

አንባቢ እንደሚያውቀው የሽያጭ ገቢ የተጣራ ገቢ (ወይም ትርፍ) አይደለም። ገበሬዎች ከዚህ ፓኬጅ ምን ያህል እንደተጠቀሙ ለማስላት ወጪያቸው መሰላት አለበት። ከዜናው በመነሳት በአዕምሯችን የሚመጡ ወጪዎች የሚከተሉት ናቸው።

1. እያንዳንዱ ገበሬ በአማካይ በወር ምን ያህል ሰዓታት በዚህ ሥራ ላይ አዋለ?
2. "ከ100 ሺ ከሚበልጡ ባህላዊ፣ የሽግግርና ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች" በሥራ ላይ ውለዋል። የእነዚህ ቀፎዎች የእልቀት ዋጋ (depreciation) በወር ምን ያህል ነው?

(በነገራችን ላይ ይኼ ራሱ ሌላ ዜና የሚወጣው ነገር ነው። በሀገሪቱ ትልቁ የዜና አገልግሎት በትላልቅ ፎንት ዜና የሠራለት "ፓኬጅ" ለአንድ ገበሬ በአማካይ ሁለት ቀፎ እንኳን ሳያቀርብ ነው። ለ89,200 ሰው 100, 000 ማለትም በአማካይ ለአንድ ገበሬ 1.12 ቀፎ ነው!)

3. ማሩ በምን ታሸገ? (ስልቻም ከሆነ የስልቻው ዋጋ)
4. ማሩ በምን ተጓጉዞ ገበያ ደረሰ?

የገበሬን ድካም ለሚያውቅ ወጪዎቹ እነዚህ ብቻ እንደማይሆኑ ይረዳል፤ ግን ይብቃኝ።

ይህንን ሁሉ ስናስብ ነው ዜናው እጅግ አስገራሚ የሚሆነው። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዜና አቀራረብ ጋዜጠኞችን ብቻ ሳይሆን አንባቢን ያሳፍራል። ይህንን ዜና ሳነብ የተሰማኝ ስሜት እፍረት ነው። ይህ ነው የኢዜአ ልማታዊ ጋዜጠኝነት!!!

የኢዜአ ስኬትን የማጋነን ፍላጎት፤ ማለትም የተገኘው ገንዘብ እና በፓኬጁ የተሳተፉ ገበሬዎችን ብዙ አድርጎ የማቅረብ ፍላጎት፣ ብዙ ሲካፈል ብዙ ትንሽ የሚሆን መሆኑ ያስረሳው ይመስለኛል።

ታደሰ ብሩ

ጥር 11 ቀን 2006 ዓ.ም.

ፀሐፊውን ለማግኘት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ