በቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ

እውነት ቤት ስትሠራ ... ውሸት ላግዝ ካለች
ሚስማር ካቀበለች ... ጭቃ ካራገጠች
ቤቱም አልተሠራ ... እውነትም አልኖረች።

... እንደዚያ ነው በባቢሎን ዘመን። የአንዱ ቋንቋ ከአንደኛው ይዘበራረቃል ... መግባባትና መረዳዳት ብርቅ ይሆናል። በጠራ አማርኛ የተጣፈውን በጉግማንጉግኛ በመተርጐም ከውስጡ የሚፈልጉትን ብቻ አለፍ አለፍ እያሉ ያነቡታል። እናም የራሳቸውን ትርጉም ይሰጡታል። ፍየል ወድያ ... ቅዝምዝምም ወዲህ ይሆናል።

ከቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት መካከል ጥቂት አዛውንቶች ታሪክን ደልዘው በወያኔኛ አዲስ ታሪክ ስለ አየር ኃይሉ እንዲጽፉ በህወሓት እየተጠየቁ ነው። እነዚህ ባለ ብዙ አኩሪ ታሪክ ባለቤት አዛውንቶች መንታ መንገድ ላይ ቆመዋል። በዓለም ዙርያ ተበትነው ያሉት የቀድሞው አየር ኃይል አባላት ሃሳባቸውን እንዲደግፉና የእርዳታ እጃቸውንም እንዲዘረጉ ለማግባባት እየሞከሩ ነው። እኛም የቀድሞው የአየር ኃይል አባላት እንዲህ አልን ...

"የአየር ኃይልን ታሪክ ለትውልድ ለማስቀረት የምታደርጉት ጥረት በጐና የሚደገፍ ምግባር ነው በርቱ፤ ነገር ግን የገዢው ፓርቲ ሞግዚትነት አያስፈልጋችሁም። በተጨማሪም በተፅዕኖ ስር ሆናችሁ ሚዛናዊነት የሚጐድለውና የተደለዘ ታሪክ ለትውልድ እንዳታቆዩ ሥጋት ቢጤ አለችን። (ያም ቢሆን መጽሐፉን ካነበብን በኋላ የምንታዘበው ይሆናል ... አያጣላም።)

የአየር ኃይል ቬተራን አሶሴሽንን እናቋቁማለን የምትሉትን በተመለከተ ግን ወራጅ አለ። እጅግ ከስጋት በላይ የሆኑ ጥያቄዎች አሉን። "የቀድሞው አየር ኃይል ቬተራን አሶሴሽን" እያላችሁን ከሆነ ግን እንግባባለን።

የሚለውን ጥቅል ሃሳብ በመልዕክታችን ብንሰድላቸው በጉግማንጉግኛ በመተርጐም እኛ ፖለቲካ አንነካካም ... ፖለቲካንና ኰረንቲን በሩቁ ነው ብለናል ይሉናል ከአዲስ አበባ ደብዳቤ እየፃፉ። እነሱ ለካ የአሁኑን የህወሓትን መንደርተኛ አየር ኃይል ነው ቬተራን እያሉ የሚያንቆለጳጵሱት። በህወሓት ሰማይ ስር ጉድ ሳይሰማ አያድርም አይደል!

እኛ ድፍን የአየር ኃይል ተቋም ላይ ስለተፈፀመ ክህደት ስናወራ ... እነሱ አንድ ግለሰብ ሀገርንና ህዝብን ለከዳ ሥርዓት ስለሚመሰርተው ዕድርና የተዝካር ግርግር ሊያስረዱን ይሞክራሉ።
እኛ'ኮ የቆማችሁበት አፈር ሥር ነፍሱ ያልወጣች የምታጣጥር የገዛ ጓደኛችሁ ነፍስ አለች ነው የምንላቸው። መጀመሪያ ባለንጀራችሁን ነፃ አውጡት፤ እናንተም በጐን በሾርኔ ሳይሆን በአደባባይ በሕግ ነፃ ውጡ፤ ምክንያቱም እንደ ዶሮዋ ገመዳችሁ ረዘመላችሁ እንጂ ፈፅሞ አልተለቀቃችሁም እያልን ነው። ህወሓት እንደሆነ በሰው ተጠቅሞና አዋርዶ እንደሚያባርር የአደባባይ ምስጢር ነው። ደግሞም ይህ ይጠፋችኋል ብለን አንሞግትም፤ ... የመሰንበት ጉጉት ህሊናን ፈፅሞ ካልተቆጣጠረ በቀር።

አየር ኃይል ለሀገር አንድነት የተፋለመ ጀግና እንጂ ጨፍጫፊ ያለመሆኑን በአደባባይ ስትመሰክሩና በሕግ ስታስነግሩ ... የአየር ኃይል ተቋም እንደ ተቋም ነፃ ሲወጣ ... እርቅ ሲወርድ፣ ሀገርን ከጠላት በመከላከላቸው ብቻ የሞትና የዕድሜ ልክ ፍርደኞች በአደባባይ ነፃ ሲወጡ ... ያን ጊዜ ሁላችንም በአንድነት ነፃ እንወጣለን። ያለበለዚያ ግን ትውልድም ሀገርም ላይ ይቅር የማይባል ክህደት ትፈፅማላችሁ እያልን ነው ያለነው፤ በጠራ ሀገርኛ ቋንቋ።

የቬተራን አሶሴሽንን በመወከል ያገባኛል ብለው ከአዲስ አበባ መልዕክት የሰደዱልን ሰው በፍፁም ሃሳባችንና ሥጋታችንን በትክክል የተገነዘቡ አይመስሉም፤ ወይንም ዛሬ ኢትዮጵያ በምትባለው ሀገር ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚከታተሉም መሆናቸውን እንድንጠራጠር እያደረገን ነው። ድንገት ዘንድሮ ጆሮዋቸውም ዓይናቸውም የተከፈተላቸው ይመስል በቃል ያጠኑትንና ስለ አየር ኃይሉ የሚገምቱትን በጐ ፍላጐት ለመተግበር የተነሱ ይመስላል።

የህወሓት አስተዳደር አዛውንት የአየር ኃይሉን አባላት በማምሻ ዕድሜያቸው ታሪክን ደልዘው የእራሱን የተንጋደደና የተንሸዋረረ ታሪክ እንዲጽፉለት እየተጠቀመባቸውና ከጠራ ታሪካቸው አንስቶ ከራሱ ቆሻሻና ስውር ፍላጐት ሥር እያንደባለላቸው ያለ ይመስላል።

አየር ኃይሉ በአዋጅ ሙሉ ለሙሉ ከሥራ ውጪ በተደረገበት ዘመን ላይ፤ ጨፍጫፊ ተብሎም ቅፅል ስም ወጥቶለት ወደ ከርቸሌ መጋዙንና በመንደርተኛ ፓይለቶች እየተተካ መሆኑን ትንፍሽ እንዳይሉ በዚሁ በምሽት ዕድሜያቸው እየተደለሉ ናቸው። እንዲያውም ሙዝየም እስከ መክፈት የዘለቀ ህልምም እንዳላቸው እየጠቀሱ ነው። ሀገር ቢኖረንማ ኖሮ ለትውልድ የሚቀር፣ ታሪክን የሚዘክር ሙዝየም ማቆም እንዴት የተባረከ ህልም ነበር? ነገር ግን ሀገርም ዜግነትም በተዋረዱበትና ዕድሜያቸውን ሙሉ ለሀገር አገልግሎት ያበረከቱ አንጋፎች እንደ አሮጌ ቁና በውርደት እንዲኖሩ በአደባባይና በአዋጅ ባይበየን ኖሮ፣ ትውልድም በበጐ መሰረት ላይ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ... ሁሉም ዓላማ በጐና ለሀገርም ሆነ ለትውልድ የሚጠቅሙ ይሆኑ ነበር።

እንግዲያውስ እነዚህ በህወሓት እየተደለሉ ያሉት የአየር ኃይሉ ነባር አዛውንቶች እርማቸውን ያውጡ። ህወሓት ሀገሪቷን ከተቆጣጠረ ወዲህ ያለውን አየር ኃይል ተብዬ እንጂ የቀድሞውን ታሪክ ምናምኒት አሻራ እንኳ አያገኙም። አጠቃላይ ሰፈሩና ቢሮዎቹም ጭምር በአይጥ መንጋ እንደተመታ ባድማ ዶክመንቶች ተፈርፍረው ድምጥማጣቸው መጥፋቱን አይጠራጠሩ። የአየር ኃይሉን የታሪክ አሻራ ሊያስረዱ የሚችሉ የተለያዩ አውሮፕላኖችን ምናምኒት ሳያስቀር አቧራቸውን እያራገፈ የህወሓቱ አበበ ተ/ኃይማኖት (ጆቤ) እዚህ ግባ በማይባል ዋጋ መቸብቸቡን እንዴት ሳይነግራቸው እንደቀረ ይገርመናል? ይህ ቀበኛ ሽፍታ ለጌጥና ለታሪክ በአየር ኃይሉ ጠ/መምሪያ ፊት ለፊት እንኳ ተቀምጣ የነበረችውን ገብሬ ቦላሌን ሳይቀር አንጠፍጥፎ መሸጡን ለምን ደበቃቸው? ታሪክ በመሥራት ሀገራችንን ያስከበረችውን ኤፍ-5 አውሮፕላንንስ አንዲት ሳያስቀር መቸብቸቡንስ? በትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር የሚመራውን የአሁኑን ሥርዓት አያውቁትም እንበል፤ ወይስ የክፋትና የብቀላ ምግባሩን ሁሉ ትተው በጐ ተክለ ሰውነት ሊገነቡለት እየሞከሩ ይሆን? ታዲያ ይህንን እየሠሩ እንዴት ፖለቲካ አንነካካንም ይሉናል?

በእነርሱው አመራር ስር የተገነባው የአየር ኃይል ሠራዊት እኮ በጅምላ ጨፍጫፊና ወንጀለኛ ተብሎ ዕድሜውን ሙሉ ከአቀናው መስሪያ ቤት በውርደት ተባሮ፤ ቤተሰቡ ተበትኖ በረሃብና በችጋር እንዲያልቅ ተፈርዶበታል!

እውነተኛዎቹ የአየር ኃይሉ አርበኞች ድፍን 22 ዓመታት ሙሉ ተሸማቀውና አንገታቸውን ደፍተው መሃል ደብረዘይት ውስጥ (በቀለ ሞላ ሆቴል ፊት ለፊት) በጠጠርና በቆርኪ ዳማና ቼዝ ሲጫወቱ የአዛውንቶቻችን መንግሥት የት ነበር? ለዚህ ሁሉ ግፍና በደል ተጠያቂው ማነው? እነዚህንና ሌሎች በደሎችን እንዴት ነው የሚያስታርቁት? በምንስ መመዘኛ ቀበኛ ሽፍታ የመሰረት ድንጋይ እንዲያነጥፍላቸው ያደርጋሉ?! ከረገጡት ምድር ስር የባልንጀሮቻቸው የምትቃትት ነፍስ ምን ትላቸው ይሆን?

ፖለቲካ ... ፖለቲካ ... ለምን እንደሚሉን አልገባንም። ፖለቲካ ምንድነው?

ለዘመነኖቹ የመንግሥት ባለሥልጣናት ማደር? ለስብሰባ ሲጠሩ ፈጥኖ ሸገር ላይ መከሰት? ወይስ ሲመሩት የነበረውን ሠራዊት አስማርኰና ክዶ ለትግራዩ የነፃነት (ተገንጣይ) ግንባር በፈቃደኝነት መገበር?

እኛ ፖለቲከኞች እያሉን የሚያበሻቅጡን ከሀገር በግፍ ተገፍታሪ ስደተኞች በሰላም ተከባብረንና ተዛዝነን ድፍን 20 ዓመታትን እንዳሳለፍን በአለፈው የበጋ ወቅት በዋሽንግተን ከተማ ተገኝተው መታዘባቸውን እናውቃለን። አየር ኃይል ማለት ለኛ መታወቂያችን፣ ማንነታችንና ዜግነታችንም ጭምር ነው። በሕብረት ተደጋግፈን እንኖራለን፤ የተቸገረን እንረዳለን፣ የታመመን እናስታምማለን ... እንጠይቃለን፣ እስከወዲያኛው የሚሰናበተንንም በኀዘን እንሸኛለን።

ጀግኖቻችንን ከተጣሉበት እያስታወስንና እያነሳን እናከብራቹኋለን እንላለን። በየዓመቱም የአየር ኃይል ቀን በማለት በሕብረት ዩኒፎርማችንን ለብሰን ባንዲራችንን ከፍ አድርገን እያውለበለብን ኢትዮጵያ ሀገሬን እንዘምራለን ...።

ይህንን ባንዲራና ዝማሬ የአሁኑ መንግሥት አይወደውም። በዘር ከፋፍሎ እኛ እና እነርሱ፣ የቀድሞውና የአሁኑ፣ ጨፍጫፊና ዲሞክራቲክ በማለት እየለያየ አጥፍቶናል። አሁን ደግሞ እዚሁ ያለንበት ሀገር ድረስ ክንዱን እያረዘመ መካከላችን ሊገባ እየተቅበዘበዘ እንደሆነ ይገባናል። እባካችሁን አዛውንቶቻችን ለዚህ መንደርተኛ ሥርዓት ክርንና ጅማት እየሆናችሁ ህወሓት ጣቱን እቤታችን ድረስ እንዲያረዝም እየረዳችሁ፤ መካከላችን እንዲገባ አታድርጉ፤ በማኅበራችንም በኩል አትምጡ።

በግል እኮ መጽሐፍ አይደለም ኤግዚቢሽንም መክፈት ትችላላችሁ። አሁን እየመጣችሁበት ያለው መንገድ ግን የሁሉንም ምክር፣ የብዙኀንን ይሁንታ ይጠይቃል። እናንተ ደግሞ እዚያው ሀገር ቤት ያሉትን እውነተኞቹን አርበኞች አንድ በአንድ ሲያልቁ ጠብቃችሁ፣ በሕይወት የተረፉትንም ንቃችሁና ገፍትራችሁ ቀበኛ የሀገር ጠላት የሆኑትን ቱባ የህወሓት ባለሥልጣናትን በጀርባችሁ አዝላችሁ አትላንቲክን በማቆራረጥ ልታነታርኩን ትሞክራላችሁ።

ለምን ድምፃችሁን አጥፍታችሁ ታሪክ መፃፍም ሆነ ዕድር ማቋቋም አልመረጣችሁም? በማኅበራችን በኩል ለመምጣት ለምን መረጣችሁ? በብዙኀን ስደተኛና በውርደት ተባራሪ ስም በየሸራተኑ ከበሮ መደለቁንስ ምን አመጣው?

እንግዲያውስ ለሁለተኛ ጊዜ ምክር እንለግስ ...

ሰው ባለቀ ዕድሜው ላይ ለኑዛዜ ይመቻቻል ... እውነትን ተናግሬ ካልሞትኩ ብሎ ከህሊናው ጋር ትንቅንቅና እልክ ይጋባል ... እውነቱን አፍርጦ በመሸበት ያድራል ...፤ እንጂ ለዳግም ምርኰ እራሱን አሳልፎ አይሰጥም።

በዚህ ዕድሜ እኮ ግጥም ብሎ ከሞላ የውስኪ ባንኰኒ ላይ የምንጭ ውሃ ካልሆነ ንክች አላደርግም፤ ከተትረፈረፈ ጮማና ቁርጥ መሃል ቲማቲምና ቅጠላ ቅጠል ካልሆነ ምናምኒት አልቀምስም፤ እየተባለ የሚኖርበት ዕድሜ ነው፤ ብዙ የሚያጓጓ ሕይወት የለም። ታዲያ ምንድነው በዚህ በኪኒኒ ተደግፎ በሚኬድበት የምሽት ዕድሜ ላይ ሆኖ ውሃና ዘይትን ለመቀላቀል መሞከር? በዚህ ምግባር ትውልድ አይደለም ከአብራክህ የወጣ ልጅ ይጠየፍሃል።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ታዛቢዎች በሕብረት
ከቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በያሉበት

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ