ግርማ ካሳ

አዲሱ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፣ ለገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ የሰላምና የእርቅ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። "ኢሕአዴግ እኛን እንደ ጠላት እና ሽብርተኛ ማየቱን ማቆም አለበት። እኛም ደግሞ ኢሕአዴግን እንደ አውሬ ማየት ማቆም አለብን። ከጥላቻ ፖለቲካ በመውጣት ችግሮቻችንን በሰላም መፍታት መማር አለብን" ሲሉ ነበር፣ ለአገር በሚጠቅሙ በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢሕአዴግ ጋር ለመስራት፣ ያሉትን ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት አንድነት ፍላጎት እንዳለው የገለጹት።

ይህ የአንድነት ዘመናዊ፣ የሰለጠነ፣ የፍቅርና የመግባባት ፖለቲካ፣ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ሞደሬቶችን ሳይቀር፣ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ያስደሰተ ቢሆንም፣ ስልጣኑን በያዙ በኢሕአዴግ አክራሪዎች ዘንድ ግን የተገኘው የአጸፋ ምላሽ የሚያስደስት አይደለም። ገዥዊ ፓርቲ ኢሕአዴግ ፣ አሁንም የአንድነት ፓርቲን እንደ ጠላት በማየት ፣ አንድነትን ለማዳከም አሳዛኝና አሳፋሪ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው። ወደ መሃል መጥተው፣ ለውይይት ይዘጋጃሉ ብለን ስንጠብቅ፣ ጭራሹኑ እያከረሩ ነው። የታሰሩ የሕሊና እስረኞቹን ይፈታሉ ብለን ስንጠብቅ፣ ጭራሽ የጊዜ ገደባቸው የጨረሱ እንደ አቶ በቀለ ገርባ ያሉ እስረኞችን አንፈታም እያሉ ነው። ጭራሽ ሌሎች ሰላማዊ የፖለቲካ ታጋዮችን በተለይም ከአንድነት ፓርቲ እያሰሩና ለማሰርም እየተዘጋጁ ነው።

ለረዥም ጊዜ የአንድነት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ሆነው ያገለገሉትና፣ አሁን ደግሞ የብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት፣ አቶ አስራት ጣሴ በአሁኑ ጊዜ ታስረዋል። የታሰሩት በአንድ ጋዜጣ ላይ፣ "በፍርድ ቤቶች ፍርድ ማግኘት አይቻልም" በማለታቸው ነው። እውነትን በመናገራቸው።

የአንድነት ልሳን ፍኖት ጋዜጣም፣ በፍትህ ሚኒስቴር ውስጥ ያሉትን ምንጮች በመጥቀስ፣ በኢሕአዴግ ጽ/ቤት ትእዛዝ፣ አቶ ዳንኤል ተፈራ እንዲሁም ሌሎች የአንድነት አመራር አባላትን ለማሰር የክስ ሰነድ እንደተዘጋጀም ዘግቧል።

ይህ የአንድነት አመራር አባላትን ለማሰርና ለማዋከብ የሚደረገው ጥረት፣ ምክንያቱ አንድና አንድ ነው። ኢሕአዴግ፣ የአንድነት ፓርቲ አሰላለፍ በጣም ስላሰጋው፣ መሪዎችን በማሰርና የፓርቲውን አባላትና ደጋፊዎች በማስፈራራት፣ ፓርቲውን ከወዲሁ ለማዳከም ነው።

የአንድነት ፓርቲ በአሁኑ ወቅት፡

1) ከሰማያዊና ከኤዴፓ በስተቀር፣ ከበርካታ ደርጅቶች ጋር ለመዋሃድ ትልቅ ሥራ እየሰራ ነው። በተለይም ከመኢአድ እና ከአራና ጋር ውይይቱ ሥር የሰደደ ይመስላል።

2) በአድዋ ከተማና በአዲስ አበባ፣ የአድዋን ድል በአል ለማክበር፣ እንዲሁም፣ በአማራው ክልል የሚኖረውን ሕዝብ የተሳደቡ የብአዴን አመራር አባል ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚጠይቅ፣ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በባህር ዳር ለማድረግ አቅዷል።

3) የሚሊየነም ድምጽ ለነጻነት ክፍል ሁለት ዘመቻ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይፋ ለማድረግ በዝግጅት እንዳለ ይነገራል።

እነዚህና የመሳሰሉት የአንድነት እንቅስቃሴዎች፣ የፖለቲካውን አስተላለፍ በእጅጉ የሚቀየሩ እንደመሆናቸው፣ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያሉ ፖሊሲ አውጭዎችን ማሳሰቡ አያስገርምም። አንድነት፣ የኢሕአዴግ ስርዓት ለመቀየር ና ለውጥ ለማምጣት ሰላማዊና ሕግን በተከተለ መንገድ ስራውን ሲሰራ፣ ኢሕአዴጎችም በስልጣናቸው ለመቆየት የራሳቸውን ሥራ መስራት የሚጠበቅ ነው። የሚያወቁትና የለመደባቸው ደግሞ ዜጎችን ማሰርና ማዋረድ ስለሆነ ይኸው እያሰሩ ነው።

ይህ በኢሕአዴግ፣ አመራር አባላቱን በማሰር አንድነቶች ለማስፈራራት የሚደረገው እንቅስቃሴ የሚሰራ ግን አይመስለኝም። የአንድነት ፓርቲ መሪዎች፣ ትግሉን ሲቀላቀሉ፣ እንደሚታሰሩ፣ ሊገደሉ እንደሚችሉ በማወቅ ነው። በብርቱካን ሚደቅሳ፣ በአንዱዋለም፣ በእስክንደር ነጋ ...የሆነውን ያውቃሉ። ነገር ግን ከምቾታቸውና ከጥቅማቸው ይልቅ አገራቸውን ያስቀደሙ በመሆናቸው ፣ ለእስራቱም ሆነ ሊመጣ ለሚችለው መከራ የተዘጋጁ ይመስላል።

እንግዲህ መልእክቴ ይሄ ነው። ኢሕአዴግ በአንድነት ፓርቲ ላይ በአንድ በኩል የያዘውን ጠመንጃ ተጠቅሞ ጫና ሲያሳደር፣ አገር ቤት ያሉ ታጋዮች ሕይወታቸውን መስመር ላይ አድርገው ዋጋ ለመክፈል ሲዘጋጁ፣ እኛ ደግሞ የአንድነት ፓርቲን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በመርዳትና በመደገፍ ማጠናከር አለብን። የአራት ኪሎ ባለስልጣናት በያዙት ዱላ ይተማመናሉ። አንድነት፣ በኔ እና በ እናንት፣ በኛ ፣ አገር ቤት ባለነውም ሆነ በውጭ በምንኖር ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ጉልበት ይተመመናል።

እንግዲህ ጨዋታው ተጀምሯል። ፊሽካው ተነፍቷል። ተስፋ ቆርጠን፣ "አይቻልም" ብለን ሜዳውን ለቀን ከወጣን በፎርፌ ዜሮ ገባን ማለት ነው። ነገር ግን ዝምታ፣ ተስፋ መቁረጥ አይሁን። ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ።

ለኢሕአዴጎች ይህንን እላለሁ። "ጸሃይ ሳትጠልቅ ቀናውን ነገር ማድረግ ተማሩ። ትንሽ እንኳ የሰላም ነገር ልባችሁ ይግባ። ይህ በሌሎች ላይ የመዘዛችሁት ሰይፍ መልሶ እናንተኑ ነው ስለሚበላችሁ ሰይፋችሁን ወደ ሰገባው መለሱና ለሰላም እጆቻችሁን ዘርጉ"

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ