ኢሳት ገለልተኛ ይሆን ዘንድ እንደገና ይዋቀር
አማኑኤል ዘሰላም
"ስልክ ጠላፊው ሰላይ 'ጋዜጠኛ'" የሚል አንድ ጽሁፍ አነበብኩ። ሲያትል የሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ ናቸው የጻፉት። የአውራምባ ታይምስ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደን አጠንክረው ይተቻሉ። በቅርቡ በድረ ገጾችና ፌስቡክ የተለቀቀው፣ አቶ አበበ ገላው የተናገሩትን አንዳንድ አባባሎችን የያዘ ኦዲዮ ነው። ይህ ኦዲዮ አቶ አበበ፣ ሳያውቁት የተቀዳ ነው። ይህ አይነቱም ንግግርን በሚስጠር የመቅዳት የፓፓራዚ ተግባር በጣም አሳዛኝ ከመሆኑም በተጨማሪ ነውርም ነው።
የሲያትሉ ጸሃፊ፣ ይሄን ነዋራ ተግባር የፈጸሙት፣ አቶ ዳዊት ከበደ ወይንም ፊኒክስ አሪዞና የሚኖሩ የአቶ ዳዊት ከበደ ወንድም እንደሆኑ ሊነግሩን ይሞክራሉ። በኦዲዮ የአቶ ዳዊት ድምጽ ስለመኖሩ የሚያመለክት ምንም መረጃ በሌለበት፣ ጸሃፊው በመላምት፣ ከአቶ ዳዊት ጋር ችግር ስላላቸው፣ አቶ ዳዊትን መክሰሳቸው፣ ሌላው ነዋራ ተግባር ነው።
ይሄንን ኦዲዮ በሚስጠር የቀዳው ማን ሊሆን እንደሚችል ከማንም በላይ ሊያውቁ የሚችሉት አቶ አበበ ገላው ናቸው። ለምን ቢባል፣ በኢዲዮ ያለውን በሚናገሩበት ጊዜ፣ አብረዋቸው የነበሩትን ሊያስታውሱ የሚችሉት እርሳቸው በመሆናቸው። ስለዚህ ከርሳቸው እስክንሰማ ድረስ ብዙም በመላምት ላይ ጊዜ ባናጠፋ መልካም ነው።
ይልቅስ አንዴ ይፋ ከሆነ ዘንዳ፣ አቶ አበበ በተናገሯችው ቁም ነገሮች ዙሪያ አንዳንድ ሃሳቦች ልስጥ። እርሱም የኢሳት እና የግንቦት ሰባትን ግንኙነት በተመለከተ ነው። አቶ አበበ ገላው ኢሳት የአንድነት ድርጅት ጥገኛ እንደሆነ በመግለጽ ራሱን ሪፎርም ማድረግ እንዳለበት ነው የተናገሩት። አቶ አበበ የኢሳት ባልደረባ የነበሩ እንደመሆናቸው የርሳቸው ምሥክርነት፣ ኢሳት የግንቦት ሰባት ጥገኛ እንደሆነ አንዱ ትልቁ መረጃ ነው። አንድ በሉ።
ኢሳት በስፋት የግንቦት ሰባት የሜዲያ ዊንግ እንደሆነ የሚከሱ ጥቂቶች አይደሉም። አቶ መለስ ዜናዊ በኢቲቪ ሁሌ ይታዩ እንደነበረ፣ የግንቦት ሰባት አመራር አባላትም በየጊዜው በስፋት በኢሳት ይቀርቡ እንደነበረ ሁላችንም የምናወቀው ነው። አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ሲያደርጉ አንዳች የማይዘግብ የነበረው ኢሳት፣ ግንቦት ሰባትና ኦነግ በየከተማው የሚያደርጋቸውን ስብሰባዎች በስፋት ያስተላልፉ እንደነበረ የሚረሳ አይደለም። ሚዛናዊነት በጎደለው መልኩ፣ ግንቦት ሰባትን ለማራገብ ይቀርቡ የነበሩ ዘገባዎች በራሳቸው፣ ኢሳት የግንቦት ስባት ጥገኛ እንደሆነ የሚያመላክቱ መረጃዎች ናቸው። ሁለት በሉ።
የግንቦት ሰባትና የኦነግ ዳንኪራ እንደበረዶ ከቀዘቀዘ በኋላ፣ ይመጣል የተባለው የነጻነት ባቡር ሃዲድ ስቶ ተገለበጠ መሰለኝ ሳይመጣ ሲቀር፣ ኢሳት ምናልባትም የሚዘግቡትን ሲያጡ፣ በተለይም የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ ከጠራ በኋላ እና የአንድነት ፓርቲ የሚሊየም ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴን ሲጀርም፣ ያኔ አገር ቤት ለሚደረገው እንቅስቃሴ የአየር ጊዜ መስጠት ጀመሩ። ይሄንን "ጥሩ አዝማሚያ ነው" በሚል በደስታ ተቀበልነው። ለኢሳቶች በዚሁ እንዲቀጥሉ ማበረታቻ መስጠት ጀመርን።
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከአንድ አገር (ግብጽ ወይንም ኤርትራ ሳይሆኑ እንደማይቀር ነው) 500 ሺህ ዶላሮች እንደተቀበሉ፣ ከዚያም 200 ሺህ ዶላር ለኢሳት እንደተመደበ የሚገልጽ፣ የማይካድ መረጃ ይፋ ሆነ። በአንድ በሲያትል ስብሰባ 50 ሺህ ዶላር ለኢሳት እንደተሰበሰበ አስታውሳለሁ። በአራት የሲያትል አይነት ስብሰባዎች 200 ሺህ ዶላሩን መሸፈን በቀላሉ ይቻል ነበር። ኢሳት ከሻዕቢያ ወይንም ግብጽ በግንቦት ሰባት በኩል የተሰጠውን ገንዘብ መመለስ፣ በይፋም ራሱን ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ማግለል ነበረበት። ግን ያ አልሆነም። ይሄም በርግጥ ኢሳት በግንቦት ሰባት ጥገኝነት ሥር መሆኑን የሚያሳይ አንድ ሌላ መረጀ ነው። ሶስት በሉ።
የኢሳት ሥራ አስኪያጅ ይሁን ኃላፊ የሆኑት በዲሲ የሚኖሩት የተከበሩ አቶ ነኣመን ዘለቀ ይባላሉ። በአካል አላውቃቸውም ግን ጎበዝና ጠንካራ የዲሞክራሲ አክቲቪስት ናቸው። አቶ ነኣመን በብዙ ሰዎች ዘንድ ይታወቃሉ። አቶ ነኣመን የጥምረት ዋና ፀሐፊ ናቸው። ጥምረት ደግሞ የግንቦት ሰባት፣ የአንድ የአፋር ድርጅትና አንድ አሁን የረሳሁት ደርጅት በጋራ የመሰረቱት ግንባር ነው። በሌላ አባባል አቶ ነኣመን ከግንቦት ሰባት ጋር የሚሰሩ ሰው ናቸው። ይሄን በራሱ ኢሳት የግንቦት ሰባት ጥገኛ እንደሆነ የሚያሳት ሌላ መረጃ ነው። አራት በሉ።
ሌሎችን መረጃዎች መዘርዘር እችላለሁ። ግን ነጥቤን ለማሳየት የቀረቡት መረጃዎች የሚበቁ ይመስለኛል። ወደ መፍትሄ ሃሳቦቼ ልምጣ።
ሜዲያ አስፈላጊ ነው። ኢሳት ለትግሉ በጣም ያስፈልጋል። ኢሳት የበለጠ እንዲጠናከር መደረግ ያለበት ይመስለኛል። ለዚህም በዋናነት ከግንቦት ሰባት ጥገኝነት መውጣት ይኖርበታል። መሰረታዊ የመዋቅር ለውጥ መደረግ አለበት። ለዚህም እንዲረዳ አንዳንድ ሃሳቦችን ላቅርብ፦
1. ኢሳት ግልጽነትና ተጠያቂነት ሊኖረው ይገባል። የሚንቀሳቀስበት ባጀት፣ ወጪ በግልጽ መታወቅ አለበት። ኢሳት የሕዝብ ነው ካልን፣ ሕዝብ ሊደግፈውና ሊንከባከበው እንደሚገባ ካመንን፣ በሚስጢርና ሕዝብ ሳያውቅ የሚደረግ ነገር መኖር የለበትም።
2. አቶ ነኣመን እስከአሁን ላበረከቱት አስተዋጾ ምስጋናዬን እያቀረብኩ፣ በፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው ላይ ትኩረት ቢሰጡና፣ ከኢሳት ኃላፊነታቸው ቢነሱ ጥሩ ይሆናል። አዲስ፣ ገለልተኛ፣ የሥራ ብቃቱና ተመክሮ ያለው ሥራ አስኪያጅ ሊኖር ይገባል። በዚህ ረገድ ሊሰሩ የሚችሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አሉ። እንደ አቶ ብርሃነ መዋ፣ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ፣ አቶ አበበ በለው፣ አቶ ክንፉ አሰፋ የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።
3. የኢሳት ቦርድ አባላት እነማን እንደሆኑ አይታወቅም። ቦርድ አባላቱ መታወቅ ይኖርባቸዋል። የቦርድ አባላቱም፣ ኢሳት በኤዲቶሪያል ፖሊሲው መሰረት እንደሚንቀሳቀስ በየጊዜ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።
ከላይ እንዳስቀመጥኩት፣ ኢሳት አስፈላጊ ነው። ኢሳት በትክክል መረጃ እንዲያቀርብልን እንፈልጋለን። ኢሳት ለዲሞክራሲ፣ ለሰላም፣ ለነጻነት የሚደረገውን ትግል በመደገፍ አንጻር ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለን እናምናለን። ዳግማዊ ኢቲቪን አንፈልግም። ኢሳት በቶሎ ሪፎርመድ ይሁን!



