ከዘፀዐት በፊት (በትረ ሙሴ)
በትረ ሙሴ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
የተወደዳችሁ ወገኖቼ!
ተደጋጋሚ ውድቀት፣ ውርደት፣ ስደት፣ መከራ፣ ችግር እና የመሳሰለት ነገሮች ለገጠመው አንድ ህዝብ በነገሮች ላይ እምነት ቢያጣ አይፈረድበትም። እኛ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ሰዓት የገጠመን ድክመት ይኼ ነው። እምነት የለንም። ስለዚህ ሁለ ነገር ጭልምልም ብሎ ይታየናል፤ ከዚያ ሁሉ ነገር ይበላሻል። ለማንኛውም ነገር ትዕግስት አስፈላጊ መሣሪያ ነው።
እኔ ትዕግስትን ከመንፈሣዊ እሴቱ በላቀ መልኩ እንደ መሣሪያ እመለከተዋለሁ። ትዕግስት ያለው ሰው የጊዝን ትርጉም በደንብ ሊገነዘብ ይችላል። አሁንም ደግሜ ልለው የምችለው ነገር ቢኖር ትዕግስት ያለው ሰው ሁለንም በጊዝው ያገኘዋል። መሆን ከሚፈልገው ነገር የሚያዳግተው ምንም ነገር የለም። እንደ ህዝብም፤ የአሸናፊ ህዝብ ትልቁ መገለጫው ትዕግስታዊ ፅናቱ ነው። ስለዚህ ለአንድ ህዝብ እምነት እና ትዕግስት ወሳኝ ከድል ማድረሻ መሣሪያዎች ናቸው።
እምነት ሲኖርህ ነው በትዕግስት የምትጠብቀው፤ እንዲሁም ትዕግስት ሲኖርህ ነው የእምነትህን ውጤት የምታየው። ከዚህ በኋላ ነው ታዲያ ወደ አምላክህ የምትጠጋው። እነዚህን ነገሮች ይዘህ አምላክህን ተስፋ ካደረግከው በእርግጠኝነት ከተነሳህለት ዓላማ ትደርሳለህ።
እኛ ኢትዮጵያዊያን በአሁኑ ሰዓት እንዲህ እያልን ነው፤ ”አቤቱ! የሆነብንን አስብ፣ ተመልከት ስድባችንንም እይ። ርስታችን ለእንግዶች፣ ቤቶቻችን ለሌሎች ሆኑ። ድሃ አደጎችና አባት (መልካም መሪ) የሌለን ሆነናል። እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆነዋል። ውሃችንን በብር ጠጣን፣ እንጨታችን በዋጋ ገዛን። አሳዳጆቻችን በአንገታችን ላይ ናቸው፤ እኛ ደክመናል፣ እረፍትም የለንም። ለሌሎች እንግዳ ህዝቦች (ዐረቦች፣ አውሮፓውያን፣ ... የመሳሰለት) እንጀራ እንጠግብ ዘንድ እጅ ሰጠን። አባቶቻችን ኋጢአትን ሠሩ፤ ዛሬም የሉም፤ እኛም በደላቸውን ተሸከምን። ባሪያዎች ሠልጥነውብናል፤ ከእጃቸው የሚታደገን የለም። ከምድረ በዳ ሰይፍ የተነሣ በሕይወታችን እንጀራችንን እናመጣለን። ከሚቃጠል ከራብ ትኩሳት የተነሣ ቁርበታችን እንደ ምድጃ ጠቆረ። በጽዮን ሴቶችን በኢትዮጵያም ከተሞች ደናግልን አጎሰቆሉ። አለቆች በእጃቸው ተሰቀሉ፤ የሽማግሌዎች ፊት አልታፈረም። ...
”... ሽማግሌዎች ከአደባባይ ጎልማሶችም ከበገናቸው ተሻሩ። የልባችን ደስታ ቀርቶአል፤ ዘፈናችን ወደ ልቅሶ ተለውጦአል። አክሊል ከራሳችን ወድቋል።ኋጢአት ሰርተናልና ወዮልን! ስለዚህ ልባችን ታሟል፤ ስለዚህም ነገር ዓይናችን ፈዝዝአል፤ ስለ ጽዮን ተራራ (ቤተክርስቲያን) ባድማ ሆናለችና ቀበሮዎችም ተመላልሰውባታልና። አቤቱ! አንተ ለዘላለም ትኖራለህ፤ ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው። ስለምን ትረሳናለህ? ስለምንስ ለረጅም ዘመን ትተወናለህ? አቤቱ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን። ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ። ነገር ግን ፈጽመህ ጥለኸናል፤ እጅግ ተቆጥተኸናል።” (ሰቆቃወ ኤርምያስ 5)
ከላይ የተጠቀሰው በርግጠኝነት እኛ ላለንበት ሁኔታ ትክክል ማሳያ ነው። የእኔም ትልቁ የጽሑፌ መነሻም ለዚህ ሁለ ነገር መፍትሔው ወደ ሀገራችን ዘጸአት አድርገን ወደ ቀድሞ ማንነታችን መመለስ አለብን የሚለው ነው። ለዚህም ዘጸአት የምናደርግበትን መንገድ መጠቆም ከዚያም አልፎ አብሮ መፍትሔ መፈለግ ነው።
ከምናደርገው ዘጸአት በፊት ጠንካራ መንፈሣዊ ዝግጅት ያስፈልገናል። በመንፈሥ የታጀበ ነገር ሁሌም ውጤቱ አስተማማኝ ነው። ጌታችንና መድኋኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ እንዲህ ብሎቸው ነበር፤ ”እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ሄጄ የሚያግዛችሁን፣ የሚያጽናናችሁንና እስከ ዓለም ዳርቻ በስሜ ብዙ ታምራትን እንድታደርጉ የሚመራችሁን ቅደሱን የእውነት መንፈሥ እስክልክላችሁ ድረስ በእየሩሳሌም ቆዩ”። እኔም እንደ እኔ በስደት ለሚኖሩ ወንድሞቼና እህቶቼን የምላቸው ነገር ቢኖር በስደት ከአሁን በኋላ የምንቆየው ቢበዛ ለአንድ ዓመት ብቻ መሆን አለበት። ይህም ጊዜ እራሳችንን ከታላቁ ዘጸአት በፊት በመንፈሣዊ እሴት የምንዘጋጅበት ጊዜ ሊሆን ይገባዋል።
ከሁለም በላይ ከማንኛውም የፖለቲካ አመለካከት የራቀና በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን የተዋቀረ አንድ አስቸኳይ ግብረ ኃይል በኮሚቴ መልክ መዋቀር አለበት። እናም ይኼ ስብስብ በመጀመሪያ በውጪ በመላው ዓለም ተበትነው የሚገኙትን በስደት፣ በመከራ እና አንገትን በመድፋት ያለውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በመቀስቀስ ወደ ብሔራዊ መግባባት፣ መፈቃቀርና መረዳዳት ማምጣት አለበት። በአሁኑ ሰዓት የፖለቲካ፣ የጎሣ፣ የእምነት መለያየት የሚባለውን ነገር ሁለም እርግፍ አድርጎ ትቶ ወደ መግባባት እና አንድ ወጥ ፍቅር መምጣት አለበት። ፍቅር ለሁለም ነገር አስተማማኝ መሠረት ነውና። በፍቅር፣ በእምነትና በተስፋ መሰረቶች የተገነባ አንድነት በምንም መልኩ አይደረመስም።
ከዚህ በኋላ በሚዋቀረው ኮሚቴ አማካኝነት ይሄ የምንፈልገው ብሔራዊ እርቅና መግባባት በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ወደ አንድ ምዕራፍ ከተሸጋገረ የሚቀጥለው እርምጃ በተለያዩ ንዑስ ኮሚቴዎች ይዋቀራሉ። እነዚህም ንዑስ ኮሚቴዎች በስደት የሚገኘው ወገናችን ወደ ሀገሩ ከገባ በኋላ በምን በምን መልኩ መሠማራት እና ሀገራዊ ግዳታውን መወጣት እንደሚኖርበት የሚያገናኝና የሚያመቻች ክፍል ይሆናል። ይህም ማለት ለምሳሌ የኢኮኖሚ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የመሰረተ ልማት፣ የኃይል፣ የእርሻ ልማት፣ የመኖሪያ ቤቶች እና የመሳሰሉትን ዘርፎች ባለሙያዎችን በማገናኘት የምክክር እና የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲያስቀምጡ የሚያደርግ ይሆናል። ከዚያም የእነዚህ ሰዎች መገናኘት ሀገራችን እስክ ዛሬ በደሃ አቅሟ ብዙ ወጪ በማውጣት ያስተማረቻቸው ልጆቿ ሀገራዊ ግዳታቸውን ለመወጣት ምቹ መንገድ ይፈጥርላቸዋል ማለት ነው።
ውድ ወገኖቼ! ከላይ እርግጥ ሀርገን መተው አለብን ላልኳቸው ነጥቦች ምክንያት አለኝ። ይኸውም ብዙ ሰዎች ያለምንም የፖለቲካ፣ የጎሣ፣ የእምነት ጣልቃ ገብነት ሀገራቸውን ማገልገል የሚፈልጉ አሉ። ስለዚህ በዚህ በሚፈጠረው እርቅና መግባባት በተለያት አመለካከቶች ተራርቀው የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖችን በማቀራረብ ለሀገራቸው አስተዋጽዖ ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ እንዲፈልጉ ከሁለም ተጽዕኖ ነፃ የሆነ እና ሀገርንና ወገንን ለማገልገል ብቻ የተዘረጋ መንገድ ሊሆን ይገባል።
እዚህ ላይ ልጨምር የምፈልገው ነጥብ ደግሞ፤ አንዳንድ ግለሰቦች ሀገራቸውንና ወገናቸውን ለመርዳትና ለማገልገል በሚጠሩበት ጊዜ አንድም ብዙ ልመና፣ ሙገሳና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው፤ አሊያም ከነጭራሹ የሀገር እና የወገን ፍቅር የጠፋባቸው እና በራሳቸው የሚቀልዱ እና ሌሎችን (ፈረንጁን) ለመምሰል በሩጫ ላይ ያሉትስ ለእነርሱ የምናጠፋው ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ የለንም። ሁለም ወገን እዚህ ጋር ማስተዋል ያለበት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዲህ ይነበባል፤ ...
”ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዲይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቧልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ህዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቶአልና። የንጉሡን ቁጣ ሳይፈራ የግብጽን ሀገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና።” (ዕብራውያን ም. 11 ቁ. 24-27)።
ስለዚህ ችግርም ቢኖር፣ ውጣ ውረድ ቢበዛ የወገኑን ችግር እንደራሱ ሳያይ አንገቱን ለሚያዞር ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠየቅበት ነገር እንዳለ ሆኖ፤ እኛ ግን ከሀገር ከሃዲ ባንዳ ምንም ለይተን አናየውም፤ ለእርሱም ለወደፊቱ ቦታ የለንም።
ወገኖቼ! የምወዳችሁ የሀገሬ ሰዎች ሁሉ!
የማይቻል ምንም ነገር የለም፤ ዓላማውን አስተካክሎ በእምነት ለተነሳ ሰው እግዚአብሔርም አብሮት ይሰለፋል። በሀገር ደረጃም ቢሆን የራሳቸውን ጥቅም በሚያስጠብቁ ሀገሮች፣ መሪዎች ከምንተማመን አንድ እግዚአብሔር አይሻለንም? ሚሊዮን ግዜ እሱ ይሻለናል።
ወገን፣ መላው የኢትዮጵያ ልጅ ሆይ!
ተነስ! በእምነት እና በተስፋ ታጠቅ! ተዘጋጅ! በወገኖችህ ፍቅር ተቃጠል! የሀገርህን ጥፋት እንዲያሳይህ እጅህን ወደ ፈጣሪ ልብህን ወደ ሀገርህ መልስ። ተንቀሳቀስ፣ እልፍ እልፍ በል፤ አንተ ስለወገኖችህ ፍቅር ስትነሳ ሌሎች ሲሳለቁብህ አትገረም፤ ሰይጣን በቻለው ነገር ሁሉ ይዋጋሃል። አስታውስ አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤ የምንሞት ስንመስል ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘውትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። ስለዚህ በእምነት ካልተነሱ ሰዎች ጋር በማያመች አካሄድ አትጠመድ፤ ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለውን?
ይሄ የእግዚአብሔር ጥሪ ነው፤ እኔ ከሁላችሁ በትምህርትም በዕድሜም የማንስ ልሆን እችላለሁ፤ እንደ እናንተም ነገር አሳምሮ ማቅረብ አልችል ይሆናል፤ ነገር ግን ስለሀገሬ፣ ስለለምለሚቱ ምድር ስለቅኖቹ ሀገር፣ ስለየጥቁር ህዝብ አለኝታ፣ ስለቅድስቲቱ ሀገር ዘወትር አለቅሳለሁ። አሁንም ቢሆን ለሚያምን ሁለ ይቻለዋል፣ ሁሉም ይከናወንለታል፣ ከእኛ የሚጠበቀው ማመን ብቻ ነው። እውሩስ የበራለት በማመኑ አይደል? ሴትየዋስ ደሟ የቆመው በእምነቷ አይደለምን? ብዘዎችስ ታላላቅ ነገሮችን የፈጸሙት አምነው ስለተነሱም አይደል?
የቴዲ አፍሮን ”ወደ ሀገር ቤት” እና ”ያስተሰርያል” የሚሉትን ዘፈኖች ለሁሉ ወገኖቼ እንደ መድኃኒት እንክብል ይሁኑና ሁሉ ይስማቸው አሁንም!!
እግዚአብሔር ሀገራችንና ወገናችንን ይጠብቅልን! እጅግ በጣም እወዳችኋለሁ! ቸሩ ፈጣሪያችን ፍቅርና አንድነት ይስጠን! - አሜን!!!
ክብር ለእግዚአብሔር! አሁንም ለዘላለምም ይሁን!
ወንድማችሁ በትረ ሙሴ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



