በትረ ሙሴ  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

“ከዘፀዐት በፊት” በሚለው ጽሑፌ ላይ ወደ ሀገራችን መመለስ አለብን፤ ነገር ግን ከዛ በፊት መንፈሣዊ ዝግጅት ያስፈልገናል ብዬ ነበር። ለዚህም አንዳንድ ጠቃሚ ነጥቦችን በዚች አጭር ጽሑፍ አቅርቤአለሁ። ርዕሱን “ኢትዮጵያዊ ቁልፎች” ያልኩበት ምክንያት በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሱት ቀላል፤ ነገር ግን መሠረታዊ ነጥቦች እንደ እኔ ግምት ለችግራችን እንደ መክፈቻ ቁልፍ ናቸው ብዬ ፅኑ እምነት ስላደረብኝ ነው። አንብበናቸው የሚጠቅሙ ናቸው ያልናቸውን ልንጠቀምባቸው ግድ ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቻለው ሁሉ አስተዋጽዖ ያድርግ እየተባለ ነው፤ እኔም በአቅሜ እነሆ ይጠቅማሉ ያልኳቸውን ነጥቦች ታነቡልኝ ዘንድ በፍቅር እጠይቃለሁ።

 

ነጥብ ፩

 

ለአንድ ቤት ጠንካራ መሠረት ያስፈልገዋል፤ በጠንካራ መሠረት የተገነባ ቤት ለብዙ ዘመን ያለምንም ችግር ይቆያል። ለእናት ኢትዮጵያና ልጆቿም እንደ ሀገር የመቆያ ዋናው መሠረታቸው ፍቅርና አንድነት ናቸው። ፍቅር ያስፈልገናል፤ አንድነታችን የሚረጋገጠው ስንፋቀር ብቻ ነው። ብዙ ጠላቶች አሉብን፤ ዋናው ሥራቸው ደግሞ ይህንን መሠረታችንን ማበላሸት ነው። መሠረቱ ሲበላሽ እናት ኢትዮጵያ እንደማትኖር ያውቁታል፤ እናም እየተሳካላቸው ይመስላሉ።

 

ዘፋኙ አለ "እኛ ስንዋደድ ይሰማናል ጌታ"!!!

 

ነጥብ ፪

 

የበደለ አጥፍቷል፤ ይቅርታ ሊጠይቅ ግድ ነው። የተበደለው ግን “ብድሬን እመልሳለሁ” ብሎ ወደ በቀል ከገባ፤ ያው የለመድነው አዙሪት ውስጥ ነው የምንገባው። ይቅር ማለትን መማር አለብን። እንደ እኔ ግምት እንደ ማንዴላ የተበደለ ሰው የለም፤ ነገር ግን ልቡ ለይቅርታ ሰፊ ነበር። እናም ውጤቱ አስተማማኝ ሆነ። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ፤ ፈሪ ሰው ሁልጊዜ ኃይልና በቀል ያበዛል፤ ልበ ሙሉና ደፋር ግን በራሱ እና በአምላኩ ስለሚተማመን ጊዜውን በበቀል አያጠፋም።

 

ኢትዮጵያ እርቀ ሠላም ያስፈልጋታል!!!

 

ነጥብ ፫

 

ማንነትን መተው እና መናቅ የቅኝ ተገዢ ለመሆን መናፈቅ ነው። የቀድሞው ቅኝ ግዛት በኃይል ስለነበር አባቶቻችን በፈጣሪ እርዳታ ባደረጉት የአርበኝነት ተጋድሎ አዳኑን። ያሁኑ ግን ጠንካራ ነው፤ ይኸውም ጭንቅላትህን በመቀየር የሚከናወን ስለሆነ ነው። ብታምኑም ባታምኑም በጭንቅላት እንደተበለጥን እየታየ ነው። ለእኔ ብቁ ምሁር የምለው፤ የራሱን ለሌሎች የሚያሳውቀውን እንጂ፤ እነሱን ለመሆን የሚሮጠውን አይደለም። “ባለቤት ያቀለለውን …” ይላሉ አበው ሲተርቱ። እራሳችንን እና ማንነታችንን ልናከብርና ልናስከብር ያስፈልጋል፤ ማንነታችን የእኛነታችን ማህተም ነውና።

 

ወደ ቀድሞ ነገር እንመለስ!!!

 

ነጥብ ፬

 

“እግዚአብሔር ሰውን በአምሳሉ ፈጠረው” ማለት፤ ሁሉም ሰው ከተጠቀመበት ከፍተኛ የአዕምሮ ብቃት ተሰጥቶታል ማለት ነው። ፈረንጆቹ የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ቀላል ነው፤ እርሱም በተሰጠን ጭንቅላት ማመን ስንጀምር እድገቱና ውጤታማነቱ ይገኛልና። እንዴ! እኛ ሁልጊዜ ተቀባይ መሆን ብቻ የለብንም፤ የኛንም ማሳየትና ማስፋፋት አለብን። አባቶቻችን ለዚህ ዓለም ድንቅ ነገሮችን ጥለው አለፉ፤ እኛ ግን አንድ የዓባይን ውሃ እንኳ ገድቦ መጠቀም አቅቶን ስንዘፍንለት እንኖራለን። ከተጠቀምንበት የራሳችን ብዙ ጥበብና እውቀት አለን፤ ነገር ግን በመጀመሪያ ይሄ ብቃት እንዳለን በብርቱ ልናምን ይገባናል።

 

ለሚያምን ሁሉ ይቻለዋል!!!

 

ነጥብ ፭

 

ባለ ራዕይና እራሱን የሚያከብር ትውልድ መሆን ያስፈልገናል። አሁንማ እራሳችንን በራሳችን እየሰደብን እንገኛለን። ሐበሻ ምቀኛ ነው፣ ወሬኛ ነው፣ ሐበሻ እንዲህ ነው፣ … እንዲያ ነው … እያልን በራሳችን እያላገጥን ነው። ከዛሬ ጀምሮ አንድ ነገር እንጀምር፤ “ምቀኛ” እንዳንባል ጥሩ ለሚሠሩና ላደረጉ ሰዎች ድጋፋችንን እንስጣቸው። አብረናቸውም እንሰለፍ። ወገናቸውን የሚበድሉትን፣ የሚያዋርዱትንና የሚጨቁኑትን እንገስፃቸው፤ ከዚያም አልፎ በመጥፎ ሥራቸው ተባባሪያቸው ሆነን አንገኝ። እንዴ!! ወገኔ ምን ነካህ? ለውጥ እኮ የሚመጣው መጀመሪያ አንተ ስትለወጥ ነው። የራስህን ጉድፍ ሳታወጣ የሌላው እንዴት ልታፀዳ ይዳዳሃል? እራስህን ለማስተካከል ደፋ ቀና በል።

 

የጭንቅላት ተኀድሶ ያስፈልገናል!!!

 

ነጥብ ፮

 

ዘረኝነትና ጎሠኝነት እጅግ የተጠላ ነገር እንደሆነ አታውቅም? ከዘረኝነት በላይ የተዋረደ፣ የድንቁርና እና የኋላ ቀርነት መገለጫ የለም። ወገኔ ኧረ! ለመሆኑ አንተ ስትወለድ ፈጣሪህን አማክረህ ነው እንዴ ወደዚህ ምድር የመጣኸው? አንተ ፈልገህ ነው እንዴ ጎንደር የተወለድከው? ወይስ ወለጋ? ወይም መቀሌ? ወይም ወልቂጤ? ኧረ አስተውል! ዓለም ሲፈጠር አንድ አዳምና ሔዋን ተፈጠሩ፤ በቃ! ነጥቡ ይኼ ነው። ሰው በሰውነቱ እንጂ በተራራና በወንዝ እንዲሁም በመንደር ማመን ከጀመረ የውድቀት ጣራው ላይ ደርሷል ማለት ነው። በመከፋፈል እና በጎጠኝነት የምታመጣው አንዳች ለውጥ አይኖርም። የዘረኝነት ትርፉ ጥላቻ ብቻ ነው፤ ጥላቻ ደግሞ የአዕምሮ ውድቀት ነው።

 

ከሣጥኑ ውጪ ልናስብ ግድ ነው!!!

 

ነጥብ ፯

 

ሀገራችን እውነቱን ለመናገር እጅግ በጣም ሀብታም ምድር ነች። ብዙ ገና ምንም ያልተነካ የመሬት ውስጥ ሀብት አላት። ዋናው ቁም ነገር ይኽንን ነገር ለህዝባችን ጥቅም፣ እድገትና ብልጽግና እንዲሁም የደስታ ምንጭ ማዋሉ ላይ ነው። በውጭ ተበትነን ያለነው ወገኖች ጠቅላላ ፊታችንን ወደ ሀገራችን ማዞር አለብን፤ እናም ወገናችንን ባለን እውቀት እና ብርታት ማገልገል አለብን። ፈረንጆቹ አባቶቻችንን በኃይል ስላልቻሉ አሁን እኛን ልጆቻቸውን በእርዳታ እያሽመደመዱን ነው። በጀታችንን በእነርሱ እርዳታ ላይ አርገናል፤ እንዲሁም ከህዝባችን አብዛኛው ያው አንደኛቸውን እነርሱ ይግዙን ማለት ጀምሯል። አይበለውና ትርምስ ቢፈጠር እናረጋጋ ብለው ይገቡና ሲያልሙት የቆዩት የዘመናት ቁጭት ከልብ ይደርሳል። ሀገራችንና ህዝባችንን ከልመና ማውጣት አለብን።

 

መጽሐፉም ብሏል "ከመለመን ሞት ይሻላል"!!!

 

ነጥብ ፰

 

ቀናውን መንፈሥ በህዝባችንና በወገናችን ላይ ማስረጽ መጀመር አለብን። ክፉም ሆነ ጥሩ ስሜት የመዛመት ባሕሪይ አለው፤ ስለዚህ ጥሩ ጥሩውን ስሜት ማዛመት መቻል አለብን። ሀገራችንን መለወጥ እንደሚቻል፣ ያለውን የክፋት መንፈሥ ማስወገድ እንደሚያስፈልግ፣ የተፈጥሮ ሀብቱን አውጥተን መጠቀም እንደምንችል፣ ብቃት የሚፈጠረው ጠንክሮ ከመሥራት እንደሆነ፣ … ወዘተ አንዱ ለሌላው ማሳወቅ እና ማስታወስ ያስፈልጋል። ከምንም በላይ በተመረዘ እና በጥፋት ላይ ያለውን የሀገር አመራር ቡድን እና የታወሩ ደጋፊዎቹን በቅዱሱ መንፈሥ ከዚህ ካሉበት የክፋት አስተሳሰብ ነፃ ማውጣት አለብን። የነፃነት ትግሉ እኛን ሳይሆን እነሱን ነው ኣርነት የሚያወጣቸው። እናም እኛ ሠላሙንና ፍቅሩን በመሣሪያና በጦርነት ሳይሆን በፍቅርና በመግባባት መንፈሥ ማምጣት አለብን። ፍቅር ሁሉን ያሸንፋል፤ በኃይል የሰውን ልብ መግለጥ አይቻልም፤ በፍቅር የታነፀ ግን እንኳን ሰውን አምላኩንም ያሸንፋል።

 

ጠላትህን እወቅ! ጠላትህ ክፉ መንፈሥ፣ ምቀኝነት፣ ስግብግብነት፣ ውሸት፣ ፍቅር ማጣት፣ ጎሠኝነት፣ መነካከስ፣ ስንፍና፣ ጥበብ ማጣት፣ ጥል እና የመሳሰሉት ናቸው። ስንፍናን በእውቀት ታጠፋዋለህ፤ እውቀት ደግሞ ከጥበብ ነው፤ ጥበብ ደግሞ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር ደግሞ ፍቅር ነው።

 

በሰይፍ የሚኖሩ በሰይፍ ይወድቃሉ!!!

 

ነጥብ ፱

 

ሀገር በአንድ ቀን አትገነባም፤ ነገር ግን ባለ ራዕይ እና ከቂም በቀል ነፃ የሆነ ትውልድ ሲነሳ ሣር ቅጠሉ ሳይቀር እልል ይላል፤ ልጆቿም ጠግበው ማደር ይጀምራሉ። አካሄዳችን ፈጣሪያችንን ደስ ካሰኘው ሠላሙን ያወርድልናል። መሪ ለህዝቡ እንደ አባት ሊሆን ግድ ነው፤ አባት ደግሞ ከልጅ ልጅ አያዳላም፤ መምራት ያልቻለ ደግሞ “አቅቶኛል! አበላሽቻለሁ! ይበቃኛል!!!” ማለት አለበት። ትልቅ አዋቂ የሚባለው መሪ ራሱን ዝቅ ማድረግ የሚችል መሪ ነው፤ ከራሱም ይልቅ ወገኑን ሊወድ ግድ ነው፤ትውልድ መሞከሪያ ሊሆን አይገባምና።

 

የኃይማኖቱ መሪ መድረኩ ላይ ወጥቶ የሚሰብከውን ትምህርት እራሱ በተግባር ማሳየት አለበት። እምነት በሥራ ይገለፃል፤ ስለዚህም ስለመንፈሥ ልጆቹ ሊዋደቅ ይገባዋል። መሪ መሆን ቀላል ነገር አይደለም፤ ጥበብና ትዕግስት፤ ማስተዋልም ይጠይቃል። አባት የቤተሰቡ መሪ ነው፤ ስለዚህም ብቁ እና ንፁኅ ዜጋ ለመፍጠር ልጆቹን በፍቅርና በቤተሰባዊ መተሳሰብ ማሳደግ አለበት፤ ልጆቻችን የእኛ ነፀብራቅ ናቸውና። ልጅህ ፊት ስለጎሣ፣ ስለበቀል፣ … ወዘተ ስትናገር ነገ እርሱም በአደባባይ ያንኑ ነው የሚገልፀው። ለልጅህ መልካም ስብዕና አውርሰው፤ ከዛ ሀገርህ ሠላም በከበበው ትውልድ ትሞላለች።

 

አዋቂና ጥበበኛ ትውልድ ሲነሳ ሀገር ትቀናለች!!!

 

ነጥብ ፲

 

እግዚአብሔር ሀገርን ካልጠበቀ ጠባቂዎች በከንቱ ይለፋሉ፤ በምንለፋበት እንዲሁም ደፋ ቀና በምንልበት ሁሉ ፈጣሪያችን አብሮን ካልወጣ ከንቱ ድካም ነው። ሥራችንን ከላይ ሆኖ በበላይነት የሚመራው እርሱ ቸሩ ፈጣሪያችን ነው፤ ሥራችንን እንዲያቀናልን እኛ ደግሞ እርሱ በሚሳተፍበት ማዕቀፍ ውስጥ መሆናችንን ማረጋገጥ አለብን። በምቀኝነት፣ በጎሠኝነት፣ በመወነጃጀል፣ በጥል፣ በክርክር፣ በፍቅር ማጣት፣ በስንፍና እና በመሳሰሉት ውስጥ ሆነን አምላካችን እንዲረዳን መጠበቅ የለብንም። የእኛ ዋናው ሥራ ከልብ መዋደድ ነው፤ ይኼኔ አምላካችን ክብሩን ይገልፃል። ደም መፋሰስ በሀገራችን የሚቆመው ሁሉም ሰው ጦሩንና ሰይፉን ወደ ማረሻ መሣሪያ ሲለውጠው ነው። ከኃያላኑ ሀገር በመሣሪያ ብቻ ብዙ ዕዳ አለብን፤ ስለዚህ አሁን ወደ አዕምሮአችን የመመለሻው ጊዜ ነው። የለመድነው ዑደት ውስጥ ተመልሰን እንዳንገባ ይኽንን አፍዝ አደንግዝ አሽቀንጥረን መጣል አለብን።

 

በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፤ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል!!!

 

ማጠቃለያ

 

ሀገራችን ሰፊ ናት ለሁሉም ትበቃለች፤ ስለዚህ ወደ ሀገራችን መመለስና ማቅናት አለብን። በስደት ያለነው ወገኖች ሁሉ ምንም ጊዜ ሳንሰጥ ብሔራዊ እርቁንና መግባባቱን ልንጀምር ግድ ነው። ከዚያ ሳናስበው ይኼ ነገር ሀገር ቤትም ደርሶ እናየዋለን፤ የምንፈልገው ለውጥም ይመጣል። ልንከባበር ያስፈልጋል፤ ማንም ታላቅ ታናሹን አይናቀው፤ ታናሹም ታላቁን ያክብር፤ መከባበር የእውቀት መገለጫው ነው። በነገራችን ላይ ዓለም አሁን በሁሉ መልኩ ጥሩ አይደለም፤ በተለይ የምግብና የውሃ እጥረት ብዙዎችን ሀገሮች አሳስቧል፤ ስለዚህም ብዙ ሀገሮች የሰውን ሀገር መሬት በገንዘብ እየወረሩ ነው። እኛ እዚህ ቁጭ ብለን የሀገራችን ለም መሬት የሌላ የባዕዳን ህዝቦች የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ሲሆን እያየን ነው። ወደ ምድራችን ተመልሰን ብንበረታ ከራሳችን አልፈን ለአህጉራችንም እንተረፋለን።

 

የኢትዮጵያ አቀማመጥ በመልክዐ ምድርም ሆነ በምጣኔ ሀብት ስትራቴጂክ ነው። በአቀማመጥ ከሳህራ በታች ያለውን ክፍል ከእስያና አውሮፓ በገበያ ለማገናኘት ምቹ ቦታ ነው። በምጣኔ ሀብታዊ ረገድ እኔ እራሴ የማውቀው ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት አለ (ለዚህ ማስረጃ ደግሞ የአሜሪካንን የነዳጅ ጥናት ውጤቶች ማንበብ ይቻላል)፤ እንደውም ስለዚህ ጉዳይ ከአንዳንድ ባለሙያዎች ጋር ስነጋገር ሳውዲ ዐረቢያ በድፍድፉ ውስጥ ያለውን ሰልፈር የተባለ ንጥረ ነገር ለማጣራት ብዙ ውጪ እንደምታወጣ ነገር ግን የእኛ መጠኑ አነስተኛ ስለሆነ የምርት ወጪያችንን እንደሚቀንስልንና ተመራጭነት እንዳለው አስረድተውኛል። እንደሚባለው በኦጋዴን ብቻ አይደለም የነዳጅ ክምችት ያለው፤ በጋምቤላ እንዲሁም አሁን ሸፍጠኛው አገዛዝ ለሱዳን በተሰጠው የጎንደር ክፍል ከፍተኛ አስገራሚ ክምችት ይገኛል።

 

በሀገራችን ብዙ ወንዞች አሉ፤ እንዚህን ለግብርናና ለመጠጥ ለማዋል እውቀቱ ከእኛ ነው የሚጠበቀው። በሀገራችን ፀሐይ ዓመቱን ሙሉ አለ፤ እንዲሁም የድንጋይ ከሰል በብዙ ቦታዎች እንዳለ በማስረጃ አውቃለሁ፤ ስለዚህም ለኃይል አቅርቦታችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። እንደዚሁም ዩራኒየም የተባለውን ንጥረ ነገር ያገኘው ሰው ከነ ምስክር ወረቀቱ አሳይቶኛል፤ ስለሆነም አንድ ቀን እንደ አደጉት ሀገሮች የኒውክሊየር ኃይልን ልንጠቀም እንችላለን ማለት ነው። በማዕድን ሀብቶች ብዙ ነገር እንዳለን እንደውም ከእኔ በላይ የሚያውቁ ብዙ የሀገራችን ምሁራን በውጭ ሀገር ይገኛሉ።

 

አሁን በሀገራችን በአመራር ያለው የክፋት ቡድን ዘረፈ የሚባለውን ገንዘብ በቅጡ ባላውቀውም፤ እንደ እኔ ግምት ግን ከምንም አልቆጥረውም። ለምን ቢባል ለውጥ ሲፈጠር በእኩልነት እንሳተፍ ቢባል መዝረፍ የለመደ ጭንቅላት አዕምሮውን እና ትጋቱን ተጠቅሞ ከሚሰራው ጋር ሊውዳደር ቀርቶ የጨዋታው ሜዳ እንኳን አይገባውም። በጥረት ማምጣት እና በማጭበርበር ማግኘት ሊወዳደሩ አይችሉምና፤ ስለዚህም እነሱ ስለዘረፉት ገንዘብ እያወራን የምናጠፋው ጊዜ የለንም።

 

የአንድ ሀገር ዜጋ ከመሆን ጋር ኃላፊነትም አብሮ ይመጣል፤ ሁላችንም ለሀገራችንና ለወገናችን ግዴታ አለብን። ሀብቱ እንዳለን ሁሉም ያውቀዋል፤ ነገር ግን እኛ ስናድግ የሚሰጉ የጠላት ሀገሮች ስላሉ እኛን ለማናከስ ቀን ከሌት ይለፋሉ ስለዚህ የመጀመሪያው ዓበይት ነገር መዋደድና መፋቀር ነው።

 

ሁሌም አባቶቻችንና እናቶቻችን ሲፀልዩ እንዲህ ይላሉ፤ "አምላካችን ሆይ! ኢትዮጵያ ሀገራችንን እምነትን በማያስለውጥ አንድነትንና ፍቅርን በማያናውጥ መልኩ የሥልጣኔን በር ክፈትላት" ይላሉ።

 

አዎ! ፈጣሪ ከሁሉም በላይ የፍቅርን በር ይክፈትልን!

 

ቸሩ ፈጣሪያችን ሀገራችንና ህዝባችንን ሁሉ ይባርክልን።

 

እኛ ታላቅ ነን! ልባችንም!


 

በትረ ሙሴ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ