“ሰውዬው ጉዴን አፈላው አይደል?” - በፈቃዱ ሞረዳ
ከበፈቃዱ ሞረዳ
“የጋዜጠኛው ማስታወሻ” በሚል ስያሜ አንድ መጽሐፍ አዘጋጅቶ (ጽፎ) በተለይም የ“ዲያስፖራው” ቡና ማጣጫና ወግ መሰልቀጫ ሆኖ የሰነበተው ተስፋዬ ገብረአብ በአንድ ድረ ገጽ ላይ ቃል ተውሶ፣ ስሜን ጠቅሶ ውንጀላ ቃጥቶ ነበር።
ጽሑፉን ካነበብኩ በኋላ ሁለት ለምንታዎች በዓይነ ኅሊናዬ ላይ “ሽ-ር” አሉ።
አንደኛው ለምንታ፣ “በሌላ ሰው ስም የተፃፈን ነገር (ፀሐፊው ያያ አባቦር ይባላል) ለምን በእኔ ላይ ማላከክ ተፈለገ?” ባይ ነው።
ሌላኛው ለምንታ፣ “ስለግንቦት ሰባትና ስለብአዴን ለመተረት ተፈልጎ እኔን የጣት ማሟሟቂያ (ማፍታቻ) ማድረግ ለምን ሲባል ነው?” ይላል።
ተስፋዬን ያበሳጨው ጽሑፍ መጀመሪያ ታትሞ የወጣው “ናፍቆት ኢትዮጵያ” በሚባለውና ቺካጎ በሚታተም መጽሔት ላይ ነው። የመጽሔቱ አሳታሚና ዋና አዘጋጅ ባለን ቅርበት መሠረት አንዳንድ ጽሑፎችን ኢሜይል ያደርግልኛል። ተስፋዬን የተመለከተውን ጽሑፍም በፒ.ዲ.ኤፍ. አስሮ የላከልኝ እርሱ ነው።
ጽሑፉን ለራሴ ካነበብኩኝ በኋላ በመጽሔቱ አዘጋጅ ፈቃድ፣ እንዲሁም በፀሐፊው ይሁንታ ለቅርብ ወዳጆቼ አስተላለፍኩ። ለኢትዮ-ሚዲያ ድረ ገጽም፣ በኋላም ለተስፋዬ ገብረአብ።
ኢትዮ ሚዲያ በፒ.ዲ.ኤፍ. የተላከለት ነገር ባይመቸው ነው መሰል በወርድ ፎርማት እንደገና እንዲላክለት በኢሜይል ጠየቀኝ። መላክ መፈለግ አለመፈለጌን በቸልታዬ እገልፀው ዘንድ አሳስቦኝ ስለነበር ቸል አልኩት። የተግባባንም መሰለኝ።
ከዚያ በኋላ የያያ አባቦር ጽሑፍ በኢትዮ ሚዲያ ድረ ገጽ መውጣቱን እኔም ሆንኩ ፀሐፊው ያያ አባቦር ያወቅነው ተስፋዬ ገብረአብ “የግንቦት ማስታወሻ” ብሎ ያዘጋጀውን ጽሑፍ በአንድ ድረ ገጽ ላይ ካስወጣ በኋላ ነው።
ኢትዮ ሚዲያ የያያ አባቦርን ጽሑፍ ለምን ያለ ፀሐፊው ፈቃድ በድረ ገጹ ላይ እንዳወጣ፣ ለምንስ ቶሎ ነቅሎ እንደወረወረው የሎስ ይወቅበት።
የእኔ ክርክር ለያያ አባቦር አቡካቶ በመሆን አይደለም። እስከማውቀው ድረስ እርሱ ራሱን የሚችልና እምነቱንም በብቃት የመከላከል አቅም ያለው ሰው ነውና የገዛ ኳሱን ራሱ ይጫወተው ዘንድ እንተውለታለን።
ተስፋዬ ገብረአብ የ“ሩቅ ወዳጄ” ይበለኝ እንጂ እኔ የቅርብም የሩቅም ወዳጁ ሆኜ እማውቅ አይመስለኝም ነበር። እርሱ ካለው ዘንዳ ግን፤ የ“ሩቅም፣ ቅርብም” የሚለውን ተቀጥላ ገድፌ “ወዳጄ” እያልኩ መዝለቄ ነው።
ተስፋዬን ያስቆጣውና የያያ አባቦርን ባርኔጣ ከአናቴ ይደፋው ዘንድ የግድ ያለው “ግንቦት ሰባት” በሚባለው የፖለቲካ ድርጅት አባልነት መታማቱ ነው። እንደ እርሱ አባባል ያማሁት ደግሞ እኔ ነኝ። ያያ አባቦርን ሆኜ።
ደግሞ እርሱ ራሱ መልሶ፣ “በግንቦት ሰባት አባልነት መታማት የሚያኮራ ነው” ይለናል። ታዲያ ቢታማስ ምን ከፋው? እኔ “ወዳጁ”ስ በግንቦት ሰባት አምቼው ኩራት በኩራት አደረግሁት እንጂ ምን አጎደልኩበት?
እርሱ ግን ዕጣ ክፍሉ ምን ቢሆን ነው የግንቦት ፍቅር እንዲህ የተጣባው? ግንቦት 16፣ ግንቦት ሃያ፣ አሁን ደግሞ ግንቦት ሰባት። የፈረደበት ግንቦት፤ የፈረደብንም እኛ።
በሁለንተናዊ ይዘቱ ላይ ሊኖር የሚችለው የተዓማኒነት ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ተስፋዬ መጽሐፉን ተነባቢ ያደረገለትን ሥነ ጽሑፋዊ ውበት ለመጠበቅ ብዙ ሽቶ እንደነሰነሰበት አምናለሁ። በእውን የተፈፀሙ ክስተቶችንና የፈጠራ ሥራዎችን እንደምን አሰናኝቶ ሕይወት ያለው መጽሐፍ ማድረግ እንደሚቻልም ከተስፋዬ መማሬን መሸሸግ የለብኝም።
“ወዳጄ” ተስፋዬ እርሱን “ፈሪ” ብዬው ራሴን ግን እንደአጀገንኩ አድርጎም ከስሶኛል። በመሠረቱ ተስፋዬ የሚጠቅሰው ጽሑፍ የእኔ ባይሆንም ፀሐፊው ያያ አባቦርም ቢሆን ስለራሱ ጀግንነት የፎከረበት ቦታ አልታየኝም። የነፃውን ፕሬስ አባላት ከተስፋዬ ፉከራ ጋር እያነፃፀረ የግንባር ሥጋ ሆነው ከእነ ተስፋዬ የፖለቲካ ኩባንያ ጋር ይፋለሙ እንደነበር ነው ያያ አባቦር የፃፈው። ይህ ደግሞ ፀሐይ የሞቀው፣ ዓለም ያወቀው እውነት እንጂ ከቶ ማን ተራ ጉራ አደረገውና?
ተስፋዬ እንደሚለኝ እኔ አዲስ አበባ ውስጥ እሠራ የነበርኩ ጦርነትን “የማላውቃት” የኢሠፓ ጋዜጠኛና ካድሬ ነበርኩ። እዚህ ላይ ሁለት ቁም ነገሮችን ላንሳ።
አንደኛው፣ አለቆቹ ካጎረሱት የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች የማንነት (የበስተኋላ) መረጃዎች ውስጥ የእኔን አጓድለውበት ይሁን፣ እርሱ ራሱ አዝረክርኮት ይሁን አላውቅም እንጂ፤ እርሱ አባራሪ (በጊዜው)፣ እኔ ተባራሬ ሆኜ ኋላና ፊት ፊንፊኔ መግባታችንን ሳያውቀው ቀርቶ ነው?
ትልቁ ቁምነገር ይሄ አይደለም። ስለየትኛውስ ጦርነት ነው በማወቃችን (በመካፈላችን) የምንኮራው? ባለማወቃችንም የምናፍርበት? እርስ በርሳችን ለተታኮስንበት? ለተቋሰልንበት? ለተጋደልንበት? ለዚያች ሀገር ህዝብ የዘመናት ሰቀቀን ስላተረፍንበት ጦርነት!? እርሱማ ቁናሳሙ ታሪካችን ነው።
እኔም፣ ተስፋዬም በየተሰለፍንበት ጎራ በታሪክ ፊት አንገት መድፋት በሚኖርብን ጉዳይ ላይ በ“ኩራት” ድርሻ ሽሚያ ጊዜና ጉልበት ባናባክን ነው የሚሻለን። “ወዳጄ”ም እርግጠኛ በማይሆንባቸው ጉዳዮች ብዕር እያነሳ ትዝብት ባያተርፍ ይበጀው ይመስለኛል። ለገበያ ጉዳይ ከሆነ ሌላ የሽቀላ መስክ በሽ ነው።
ተስፋዬ በግንቦት ሰባት በመታማቱ እኔንም በኦነግነት አማኝ። የዛሬ አስራ አምስት ዓመት ያሰረልኝን ቃጭል ዘንድሮ ለምን ማቃጨል እንደፈለገ አላውቅም። የአራዳ ልጆች “የመልስ ምት” የሚሉት ጨዋታ ዓይነት ከሆነ ግን፣ አሪፍ መቂያ ቂያል ነው።
የኦነግ አባል መሆን ያለመቻሌ ዓይነተኛው ምክንያት ደፋር አለመሆኔ ብቻ ነው። እኔ እንደሚመስለኝ፣ ኦነግ በራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ (የተስፋዬ “እፎይታ” ጋዜጣና መጽሔት ቢሮ እዚያ ነበር) ማኪያቶ መጠጪያ ቤቶች ወይንም የውቤ በረሃ ቢራ መቅመሻ ግሮሰሪዎች ዓይነት ማንም ‘ዘው’ ብሎ የሚገባበት አለመሆኑንም ተስፋዬ ከእኔም በላይ ያውቀዋል። ወደደም ጠላም።
በደበበ ሰይፉ “የብርሃን ፍቅር” ቅጽ ሁለት (ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ) የግጥም መድብል ውስጥ “የአክሱም ጫፍ አቁማዳ” የተሰኘውን ነፍስ የሆነ ግጥም ተስፋዬ አንብቦታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ቢያነበውም ባያነበውም እኔ ማለት ግን እርሱ ግጥም ነኝ። የእኔ የፖለቲካ ኃይማኖትም፣ ፍልስፍናም፣ ዲሲፒሊንም፣ ፓርቲም፣ … ደስታዬና ኀዘኔም እርሱ አቁማዳ ውስጥ ነው።
ሌላ ነጥብ ላንሳ። የዛሬ ሃያ ዓመት ገደማ “ጀጎል” በሚል ርዕስ አንዲት አጭር መወደስ በሐረር ከተማ ውስጥ ለሚገኘው ታሪካዊ የጀጎል መንደር ጽፌ ነበር። ነገርዬውን በረሳሁት በስንት ዓመቱ ግጥሙን እንድልክለት “ወዳጄ” ተስፋዬ ጠየቀኝ። ለጥያቄው የሰጠሁትን ጨዋ ምላሽ አንዳች ስርቻ ስር ወሽቆት የፈጠራ እንቶ ፈንቶ አዘጋጅቶ ለወዳጆቹ የድረ ገጽ ጀግኖች መላኩ አስደምሞኛል።
የተፃፃፍነው የእኔም የእርሱም እናት ቋንቋ ባልሆነው እንግሊዘኛ ነው። ምናልባት ቋንቋው ሳያግባባን ቀርቶ ይሆናል። አለማወቅ ጢቢ ጢቢ ቢጫወትብን በእኔና በእርሱ አልተጀመረምና እርሱስ ዕዳው ገብስ ነው። ለማንኛውም የፃፍኩለት እንዲህ የሚል (እንዲል የተፈለገ) ነው።
“ጀጎልን ማስታወስህ ይገርመኛል። እርሱ ግጥም አሁን በእጄ የለም። የት እንዳለም እንጃ። ስለሌሎች ግጥሞቼ ግን አድራሻህን ላክልኝና ልልክልህ እችላለሁ። መጽሐፍህን አስመልክቶ አንዳንድ ቆንጣጭ አስተያየቶች እየተፃፉ ነው። የቀድሞው የጋዜጣችን አምደኛ ‘ናፍቆት ኢትዮጵያ’ በተሰኘ መጽሔት ላይ የፃፈውን አግኝቼ ልኬልሃለሁ። እኔም የፃፍኩት ስለአለ እልክልሃለሁ” ብዬ የናፍቆት መጽሔት አዘጋጅ በፒ.ዲ.ኤፍ. አስሮ የላከልኝን አስተላለፍኩለት በኢሜይል።
ሌላው በአንድ የራዲዮ ስርጭት ላይ ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት፣ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በመጽሐፉ ላይ የሰጡት አስተያየት እንዳላስደሰተው ወይም ትክክል አለመሆኑን በስልጡን ሥነ ምግባር ማስረዳት ሲኖርበት፤ “ነጋሶ ምን ያውቃል? እርሱ የታሪክም የምንም ምሁር አይደለም። እንዲያውም እኔ ከእርሱ የተሻልኩ ኦሮሞ ነኝ” ብሎ ሲያቅራራ ሰምቼው ነበር። እንዲህ ዓይነቱ በ“ለምን ተተቸሁ?” ስሜት የሰዎችን ስብዕና ጥቀርሻ መቀባት ጥሩ ስላልሆነ ለወደፊቱ ቢጠነቀቅ እንደሚሻለው ጠቅሼ ፃፍኩለት። በመጽሐፉም ውስጥ አንዳንድ ቦታ ላይ የስብዕና ዝርጠጣውን አልወደድኩለትምና ነው ‘ወዳጃዊ’ ምክር ለመስጠት መቃጣቴ።
እውነቱ ይኼና ይኼን የሚመስል ሆኖ ሳለ፤ “ጋዜጠኛና ደራሲ” ተስፋዬ ገብረአብ የያያ አባቦርን ጥሩር ለብሼ፤ በብዕር ስም ውስጥ ተለሽልሼ በባዙቃ እንደ ደበደብኩት ብቻ አጉልቶ ማውጣት ፈለገ።
ተስፋዬ “አደረጋቸው፣ አላቸው” ያልኩዋቸውን ነጥቦች መጠቃቀሴ የቃሎች ኳኳታ ለማብዛት አይደለም።
“የጋዜጠኛው ማስታወሻ” በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ የትኞቹ የፈጠራ (ምናባዊ)፤ የትኞቹ እውነተኛ ክስተቶች እንደሆኑ እኔም፣ ተስፋዬም ሌሎችም ከነገሮቹ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ያለን ስሜት አለ። የምናውቀውም ሐቅ ጭምር።
ሁለት ገጽ እንኳን በቅጡ በማይሞላ የኢንተርኔት ድረ ገጽ ጽሑፍ ሦስትና አራት የፈጠራ ነገሮችን በእኔ ላይ ለመደረት የቆፈጠነው ተስፋዬ፣ በባለ 412 ገጽ መጽሐፉ ምን ያህሉን የፈጠራ ታሪክ (ልብወለድ) እንደወታተፈበት ጊዜው ሲደርስ ማሳየት ይቻላል።
እኔ ኢሜይል ያደረግሁለትን ጽሑፍ አንብቦ እንደጨረሰ ፕሪቶሪያ ደቡብ ወደሚገኘው ተራራ (ኮረብታ) እየነዳ መብረሩን ጽፎልናል። በዚህም አዝናኝ ለበጣ ላይ አንድ ሁለት ቁም ነገር መወርወር የሚቻል ይመስለኛል።
“እነተስፋዬ” ትንሽ በተበሳጩ ቁጥር ለምን ወደ ተራራ መሮጥ እንደሚወዱ የፈጠራቸው ብቻ ነው የሚያውቀው። ያን ያህል አሳሳቢ ሆኖ ወደ ተራራ የሚያስሮጥ ነገርም ተጽፏል ብዬ አላስብም። ከመሰለው ግን ምን ይደረጋል? ይሩጥ እስከተቻለው ድረስ።
በእርግጥ፣ እርሱ ከእኔ እንደሚበልጥ ለማወጅ ያስችለው ዘንድ የሊዎ ቶልስቶይና የአንቷን ቼኮቭን ተረብ ለማስታወስ ወደተራራ መሮጥ ባላስፈለገው። በደጉም፣ በደርጉም ዘመን በብዛት ወደ አማርኛ የተተረጎሙትን የሩሲያ ፀሐፊዎች ሥራ እንደአነበባቸው አውቃለሁ። እርሱ ይመራው በነበረው ፕሬስ መምሪያ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ሞልተዋልና። ባያነባቸውም እንኳ ለሩሲያ ሥነ ጽሑፍ ቅርበትና ፍቅር ያላቸውን ሰዎች በግድም በውድም ይቀርባቸው ስለነበር እርሱ ያላነበባቸውን እነርሱ እየተረኩለት ሲያዝናኑት እንደነበርም ይታወቃል። አሽቃባጮቹ።
ተስፋዬ እኔን እንደሚበልጠኝ የተረት ሐረግ መዘዛ ባይሄድም፣ ዝርው ሊቀኝብኝ ባይባጅም እኔ ራሴ መመስከር እችል አልነበር? “ወዳጄ” በእርግጥም ይበልጠኛል። ጮሌ የአራዳ ልጅነት፣ የተገለባባጭነት (የአክሮባት) ብልህነት መች ቀላል እውቀት ሆነና እኔ ከእርሱ እወዳደራለሁ?
ከኢትዮጵያ ዛሬ፦ ከዚህ ቀደም ያያ አባቦር ”’የአደአው ጥቁር አፈር’ ጋዜጠኛ ወይስ የፓርቲ ካድሬ?” በሚል ርዕስ ቺካጎ በሚታተመው “ናፍቆት ኢትዮጵያ” መጽሔት ላይ የጻፉትን ተከትሎ፤ በሰሜን አሜሪካ በስደት የሚገኘው የ”ጦማር” ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ በፈቃዱ ሞረዳ ”እኔም ማስታወሻ አለኝ” በሚል ርዕስ በዛው መጽሔት ላይ የጻፈውን፤ በመጨረሻም ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ደግሞ ”የግንቦት ማስታወሻ” በሚል ርዕስ ኢትዮ-ፎረም ድረ ገጽ ላይ የሰጠውን ምላሽ ማስነበባችን ይታወሳል። በፍቃዱ ሞረደ የተስፋዬ ገብረአብን “የግንቦት ማስታወሻ”ን ተንተርሶ ይህንን ምላሽ የሰጠው በ”ናፍቆት ኢትዮጵያ” መጽሔት ላይ ነው።



