አደራጅተው ገደሉን፤ ተደራጅተን ብንገድልስ?
አብርሃም ዘታዬ
በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ ከደረሰብን ኀዘን ሳናገግም በሜዲትራንያን ባህር የሰጠሙ ወገኖቻችንን መርዶ ተረዳን። በአገር ቤት ከድሮም ጀምሮ በተናጥልም በጅምላም መጨፍጨፋችን አላቆመም። ባለቅኔው "ሞትና የላሊበላ ህንጻ ሁልጊዜ አዲስ ነው" ብሎ እንደተቀኘው ስለአዲሱ አሟሟታችን እንጉርጉሮ እናውጣለት ከተባለ በሰፈር ተደራጅተን እየሞትን ነው።
በሊቢያ ሰማዕትነት ከተሰዉት ውስጥ አምስቱ አብሮ አደጎች በመደዳ ቤታቸው የሚገኘው ቂርቆስ ሰፈር አዲስ አበባ ነው። ይሄው ሜድትራኒያን ባሕር ውስጥ ሰጥመው ከሞቱት ደግሞ አስሩ ከአንድ ሰፈር፣ በተለምዶ መርካቶ "አባኮራን" ከሚባለው የተሰደዱ ናቸው። ልጆቻቸው ተደራጅተው እንደሞቱ ወላጆቻቸውም ተደራጅተው ለቅሶ ተቀምጠዋል።
በስደት አገር በጅምላ መሞታችን አዲስ ነገር ቢመስልም ገዳዮቻችን በኃይማኖት ወይ በሰፈር ዒላማቸው (ታርጌት) አድርገው የገደሉን ቢመስልም ከጥንት ጀምሮ ያለን የዕድር ባህል አሰባስቦናል። ኢትዮጵያዊ የኀዘን ስሜት አንድ አድርጎናል። ለተረኞቹ አባኮራን ኀዘንተኞች ቂርቆሶች እዝን ይዘው መጥተዋል። ከወለጋ ሄዶ ወይ ከትግራይ ሄዶ የሞተውን ቤት ሆነ የሌሎቹንም ቤታቸውን እየፈለጉ ከምስራቅም ከደቡብም የአገሪቱ ክፍሎች እየተጓዙ ሳይቀር መላ ኢትዮጵያውያን ለቅሶ ደርሰዋል። ያልቻሉ ሻማ አብርተዋል። ቁጭታቸውን ገልጸዋል። በእርግጥ ሁላችንም ኀዘን ላይ ነን። የነሱ ለቅሶ ብለን ጣታችንን የምንቀስር ወይም ከንፈራችንን መጥጠን የምናልፍ አይደለንም። አንገታችን የተቀላ ሜዲትራንያን ባህር የሰመጥን እኛም ነን። አሳዳጆቻችን የኑሮ ድህነትና የወያኔ ደህንነት እስካልተወገዱ ድረስ ለቅሶ ሊደርሱን የሚገባ ሁላችንም ቤት ነው።
ግን ራሳችን ለመጽናናት ካልተነሳን የትኛው አገር መጥቶ ያበረታታናል? ቱባ የዕድር ባህላችን ለለቅሶ ብቻ ሳይሆን ለዘላቂ ነጻነት ትግል እናውለው እንጂ። ለማልቀስ እንደተሰባሰብን ወያኔን ለማስለቀስ እንሰባሰብ። በዘር መደራጀትን ሸሽተን ወደሚያሰምጠው ባህር፣ ወደ እሚባላው በረሃ፣ ወደ ተሳለብን የአይሲስ ሰይፍ ለመታረድ ከምንነዳ ነጻነት ያሳጣንን አረመኔ ዘረኛ ሥርዓት እዛው በአገራችን ሜዳ ተናንቀን ብንጥለው የስደት እና የውርደት ምንጭ የሆነውን ከምንጩ እናደርቀዋለን።
በዘር በሰፈር በኃይማኖት የከፋፈለን ወያኔማ ኀዘንንም እየነጠለ ይገኛል። በስንት ዘገምተኛነት የቂርቆስን አንድ ቤት የዜና ሽፋን ሰጥቶ ከአስር በላይ ሜዲትራንያን ባህር ሰጥመው ሬሳቸው አባኮራን ሰፈር አዲስ አበባ የገባውን ዝም ብሎታል። በሊቢያ የሞቱት ዜግነታቸው ይጣራ ያለው ዘረኛ ወያኔ፣ የኛን ያህል ያልተቃጠሉት የዚምባቡዌ፣ የማላዊ፣ የአንጎላ፣ የናይጄሪያ ዜጎች መንግሥታት በደቡብ አፍሪካ ለደረሰባቸው ጥፋት ካሣ እንዲከፈላቸው ሲጠይቁ፤ የቀለደብን መሰሪው ወያኔ፤ በዐረብ አገራት ዜጎች ሲበደሉ ሲገደሉ እንደመንግሥት ያልታደገው አምባገነን ወያኔ ዛሬ ምርጫ ሲደርስ በአዞ እምባው ሊያባብለን ያምረዋል። በሳውዲ ዐረቢያ የተጨፈጨፉ ኢትዮጵያውያን ኀዘን ለመግለጽ ሳውዲ ዐረቢያ ኤምባሲ ፊት ስንሰለፍ እሷን አትንኩብኝ ብሎ ሁሌ ከበዳይ ጎን የሚቆመው ወያኔ፤ ዛሬ የግንቦት ምርጫ ስለደረሰ ኀዘን መግለጫ አደባባይ መውጣት ትችላላችሁ ለቅሶ ማሰማት ግን አትችሉም ይለናል። ለጨፍጫፊው መለስ ዜናዊ አስከሬን የአስራ አምስት ቀን ክብር ሰጥቶ ከሰላሳ በላይ ላለቁት ነፍሳት የአንዲት ቀን ብቻ ለዛውም የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ ዲስኩር አደረገው። በዚህችም ቀን የመንግሥት ካድሬዎች ባንድ ተደራጅተው ተሰለፉ ስለሞቱት ሳይሆን "ስለልማት" ለፈለፉ። መፈክር ያሰሙትን አሳፈሱ።
አብዛኛው ኀዘንተኛ ተደራጅተን ኀዘናችንን ወያኔ ላይ መግለጽ አቅቶን አብዮቱን ቀበርነው። ለትምህርት ይሆነን ዘንድ ግን አንድ ፌደራል ፖሊስን አስር ወጣቶች ከበውት ሲመክቱ አይተናል። እንዲህ አይነት አንድ ፖሊስን ለአስር የማገት አደረጃጀት በመላው ኢትዮጵያ መለመድ አለበት። ሲቀጥል አስር ሆነን ተቀናጅተን ትናንሽ ፖሊስ ጣቢያዎችንም መማረክ እንችላለን። የዋሁ ገበሬ ሳይቀር በወያኔ አንድ ለአምስት ተጠርንፎ አንዱ ሌላውን የሚሰልልበትን መዋቅር እኛ ለበጎ ብናውለውስ። በዕድር፣ በዕቁብ፣ በማኅበር ላይ ያለንን የመደራጀት ልምድ ለነጻነት ትግል በምስጢር ማዋል አያቅተንም።
የሰሜን አፍሪካ ሀገራት አምባገነን ገዢዎች በሕዝባዊ አብዮት የተወገዱት በቱኒዚያ የኑሮ ውድነትን ተቃውሞ ራሱን ባቃጠለ አንድ ሰው ሞት ምክንያትን ተከትሎ ነው። ያሳደደ እና በአይሲስ ወያኔ ያስገደላቸው፤ በአገር ቤት በየቀኑ የሚገደሉ ወገኖቻችን ብዛት ቁጭት ከነሱ አብዮት መብለጥ አለበት። ባለፈው ዓመት የምዕራብ አፍሪካዋን ቡርኪናፋሶ አምባገነን ገዥ ብሌስ ኮምፓወሬን ከሥልጣን ያስወገደው የሁለት ቀን ተቃውሞንም አይተናል። በዚህ በያዝነው ዓመት ደግሞ ሕዝባዊ ማዕበሉ ወደ ምስራቅ አፍሪካዋ ቡሩንዲ አምርቷል። በቀጣይነት ከቡርኪናፋሶ የበለጠ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር የሚል ማንቂያ አባባልና ችሎታ ያለን እኛ ነን። እንኳን ሶሻል ሚዲያዎች ለመገናኛ በዚህ ዘመን ተፈብርከውልን ጥንት አባቶቻችን የውስጥና የውጭ አርበኛ ሆነው በመደራጀት ወራሪ ጣልያንን አባረው ነጻነት አጎናጽፈውናል። ተጠራርተን የሊቢያን በረሃ ለማቋረጥ እንደተነሳን፣ለጉዞው ያሟጠጥነውን ጥሪት በረሃና ባህር ከሚበላብን ያሳደደንን እና ያሳረደንን ወያኔ ማስወገጃ ማኅበር ብናቋቁምበት ወይም ነጻ አውጪ ድርጅትን ብንረዳበት ዘላቂ መፍትሄ ነበር፤ አሁንም ይሆናል።
እነሱ ተደራጅተው እንደሚደበድቡን፣ እንደሚያሰድዱን እኛም ተደራጅተን እናሰድዳቸው።
በአገር ውስጥም በውጭ አገርም እኛው የአንድ ቀዬ ልጆች እየሞትን ነው ስለዚህ እኛው ተደራጅተን ገዳዮቻችንን እንከላከል።
አብርሃም ዘታዬ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



