የኦሮሞ ሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ የመብት ጥያቄዎች ለድርድር እና ለልመና የሚቀርቡ አይደሉም
ብርሃነመስቀል አበበ
አንዳንድ ወዳጆቼ የኢትዮጵያ መንግሥት የኦሮሞ ሕዝብ እየጠየቀ ላለው፣
1ኛ፣ በጉልበት እና ሕግን ሽፋን በማድርግ የተዘረፈው የኦሮሞ ሕዝብ መሬት እንድመለስ፣ የወረራው መሠረት የሆኑት ሕጎች እንዲሻሩና የዘረፋ ተቐማቶቹ እንዲፈርሱ፣
2ኛ፣ ኦሮምኛ ከአማርኛ ጎን ለጎን የኢትዮጽያ ፌድራል መንግሥት የሥራ ቐንቐ እንዲሆን፣
3ኛ፣ አድስ አበባ እንደ ሌሎቹ ትላልቅ የኦሮሚያ ዞኖች የዞን ደረጃ ተሰጥቷት፣ አማርኛ እና ኦሮምኛ የሥራ ቐንቐ ሆነው በኦሮሚያ ሥር እንድትተዳደር፣
4ኛ፣ በግፉ ለተገደሉና ለታሰሩ የኦሮሞ ልጆች ካሳ ተከፉሎ ገዳዮችና አሳርዎች ለፉርድ እንድቀርቡ፣
5ኛ፣ የኦሮሞ ሕዝብን ለ140 ዓመታት ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የለየው ሥረዓት ተሽሮ ፣ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲ እንድወጣ፣
6ኛ፣ የኦሮሞ ሕዝብ በክልል ደረጃ ከፌዴራል ተላላኪዎች እጅ ወጥቶ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድርና በፌዴራል ደረጃ ኢትዮጵያን በድርሻው ልክ ተወክሎ እንድያስተዳድር፣
በማለት ላለፉት ሶስት ወራት እያካሄደ ባለው ሰላማዊ ሠልፎች እያቀረበ ላላቸው የመብት ጥያቄዎች የኢትዮጵያ መንግሥት እስከ አሁን ድረሰ መልስ ያልሰጠው ከOPDO ጋር እየተደራደረ ስለሆነ ነው ይላሉ።
የኦሮሞ ሕዝብም በርካታ ውድ ልጆቹን ለግድያና ለእስራት ቢገብርም ለነዚህ የመብት ጥያቄዎቼ መልስ ካላገኘሁ የልጆቻችን ደም በከንቱ ፈሷል ማለት ነው በማለት በሰላማዊ ትግሉ ቀጥሏል። ሰላማዊ ትግሉን ከመቀጠል ውጭ ሌላ ምርጫም የለውም።
እነዚህ ህገ መንግሥታዊ መብቶቹ ካልተከበሩለት የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ሕዝብ የመቀጠል ህልውናም የለውም።
ስለዚህ አሁን ጥያቄው OPDO እነኝህን የሞትና የሽረት ህገ መንግሥታዊ የኦሮሞ ሕዝብ የመብት ጥያቄዎችን ይዞ ምን እያደረገ ነው ያለው ነው?
የኢትዮጵያስ መንግሥት የት ገባ? ምነው የኢትዮጵያ መንግሥትን የበላ ጅብ አልጮህ አለ? ወይስ ስለኦሮሞ ሕዝብ አያገባውም?
የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች ለልመናም ሆና ለድርድር የሚቀርቡ አይደሉም። OPDO ም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ምክንያት በሌባና ፖሊስ ድብብቆሽ ከተጠመዱ ተሳስተዋል።
OPDO እየለመነ ከሆነ ለማኝ የሰጡትን መቀበል ወይም ባዶ እጅን ዘርግቶ መቀመጥና ቀኑ ሰደርስ መሞት ነው።
ተለማኙ የኢትዮጵያ መንግሥትም ለለማኝ የመስጠት ግዴታ የለበትም። ስጀመርም መብት በልመና አይገኝም። አይሰጥምም።
ጀግናው እና ደጉ የኦሮሞ ሕዝብም የልመና ባህልም ሆነ የለማኝ ተወካይ የለውም፣ ኖሮትም አያውቅም። መብቱንም ያስከብራከል እንጂ አይለምንም።
ድርድር ግን ለጋራ ጥቅም ስባል ሠጥቶ መቀበል ነው። አስፈላጊ ካልሆነ የመከልከል መብት ወይ ከፉተኛ ዎጋ አስከፉሎ መስጠትን ይጨምራል።
የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ጋር በጋራ የመኖር ጠቀሜታና አስፈላጊነትን በሚገባ ስለሚገነዘብ በእኩልነትና በጋራ ጥቅም ላይ በተመሠረተ የሰጥቶ መቀበል የድርድር ሕግ ያምናል።
ነገር ግን ከላይ የተዘረዘሩት የኦሮሞ ሕዝብ ህገ መንግሥታዊ የመብት ጥያቄዎች እስከ አሁን የነበሩትና ያሉት ጨቐኝ ሥረዓቶች የኦሮሞን ሕዝብ ሥልጣን በመግፈፉ፣ መሬቱን እና የተፈጥሮ ሃብቱን በመቀማት የኦሮሞ ሕዝብን የበታች እና ዳሃ አድርጎ ለመግዛት በተሸረቡ ሤራዎች የተነጠቃቸው መብቶች ስለሆኑ በፉፁም ለድርድር የሚቀርቡ አይደሉም። አሁን ደግሞ በልጆቹ ደም የተገዙ ፣ በምንም የማይለወጡ መብቶች ናቸው።
ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦችም በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተፈፀሙት ግድያዎች፣ የግፉ እስራቶች፣ በማን አለብኝነት የተፈፀሙት የሃብት እና የመሬት ዘረፋዎች ቆመው፣ የኦሮሞ ሕዝብ የአገሩና የሀብቱ ባለቤት ለመሆን የምያደርገውን ሰላማዊ ትግል ይደግፋሉ። የነዚህ መሠረታዊ መብቶች ያለመከበር በኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል ላይ ያለውን ከፉተኛ አደጋም ይገነዘባሉ።
OPDO ም ሆነ ሌላ የኦሮሞ ድርጅት እነዚህን መብቶ መሉ በሙሉ ሰይሸራረፉ የማሰከበር እንጂ በነዚህ መብቶች ላይ የመደራደር ወይም ለማኝ ሆኖ የኦሮሞን ሕዝብ የማሰደብ ውክልና የላቸውም። ቢያደርጉትም ልመናቸውና ድርድራቸው ሙሉ በሙሉ ተቀበይነት የለውም።
ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት የኦሮሞ ሕዝብ መሠረታዊና ህገ መንግሥታዊ ጥያቄዎችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መሉ በሙሉ በመመለስ፣ ሕዝባችን ትግሉን ብቸኛ ጠላቱ ወደ ሆነው ድህነት እንዲያዞር የሁሉም ኢትዮጵያዊያን አስቸኳይ ጥሪና ጥያቄ ነው።
ምንጭ፡- ፌስቡክ



