ግርማ ካሳ

አቶ ብርሃነመስቀል አበበ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ መብት ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ጽሁፎችን ይጽፋሉ። ቢቢሲ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ስርጭት እንዲኖረው ፔቲሽኖችን በማስፍረም አንድ ዘመቻ እንደነበረ የምናስታወሰው ነው። ይሄንን ዘመቻ ይመሩ ከነበሩት መካከል አቶ ብርሃነመስቀል አንዱ ነበሩ። እኔም ሆንኩም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ፔቲሽኑ ላይ ፊርማችንን በማስፈር፣ ፔቲሽኑ ያልፈረሙ እንዲፈረሙ በማበረታታት እንደነ አቶ ብርሃነመስቀል ባይሆንም፣ የድርሻችንን አበርክተናል።

ላለፉት ሶስት ወራት በኦሮሚያ በተነሳው ተቃውሞ ዙሪያ፣ አቶ ብርሃነመስቀል “የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች ናቸው” ያሉትን ስድስት ጥያቄዎች አስቀምጠዋል።

“የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች ለልመናም ሆነ ለድርድር የሚቀርቡ አይደሉም። ጀግናው እና ደጉ የኦሮሞ ሕዝብም የልመና ባህልም ሆነ የለማኝ ተወካይ የለውም፣ ኖሮትም አያውቅም። መብቱንም ያስከብራከል እንጂ አይለምንም።” ሲሉ በጥያቄዎቹ ዙሪያ ድርድር እንደሌለ በአድን በኩል ይጽፉና ወረድ ብለው፣ አቶ ብርሃነመስቀል ድርድር እንደሚያስፈለግ ይገልጻሉ። እርስ በርስ የሚቃረኑ አባባሎች።

አንደኛ “የልመና ባህል የለውም፣ አይለምንም …” የሚሉት አይነነት አባባሎች መንፈሳቸው ጤናማ አይደለም። አቶ ብርሃንመስቀል ይሄን አይነት፣ “እኛ ያልነው ካልሆነ “ የሚመስል አባባል በመጠቀም ሌላውን ለማስፈራራት መሞከሩ ጠቃሚ አይመስለኝም። ሁለተኛ አቶ ብርሃነመቀል የኦሮሞ መሬት የሚሉት የኦሮሞዎች ብቻ እንዳልሆነ የዘነጉትም ይመስላል። የኦሮሞ መሬት የሚሉት የሁሉም ኢትዮጵይያዊ ነው። ሌላውም መሬት የኦሮሞዎች እንደሆነው። ሶስተኛ የኦሮሞ ሕዝብ አይለምንም እንዳሉትም፣ የሶማሌ ሕዝብ፣ የጉራጌ ሕዝብ፣ የሲዳማ ሕዝብ፣ የአዲስ አበባ ህዝብ ..ሌላውም አይለምንም።

”የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ጋር በጋራ የመኖር ጠቀሜታና አስፈላጊነትን በሚገባ ስለሚገነዘብ በእኩልነትና በጋራ ጥቅም ላይ በተመሠረተ የሰጥቶ መቀበል የድርድር ሕግ ያምናል” ያሉት አባባል ግሩም አባባል ነው። እዚያ ላይ በማተኮር ላሉ ችግሮች፣ ሁሉም አሸናፊ የሆነበት መፍትሄ መፈለጉ ላይ የበለጠ ቢሰሩበት ጥሩ ይሆናል ብዬ አማናለው። አቶ ብርሃኑ መስቀል ባቀረቧቸው ሐሳቦ ላይ ግን መቀበል እንጅ መስጠትን አላየሁበትም። በአንድ ወግን ያለውን ፍላጎት ብቻ ያንጸባረቀ እንጅ በሌላው ወግን የሚነሱትን ጥያቄዎች ከግምት ያስገባ አይመስለኝም። እንግዲህ ሰጥቶ የመቀበል መርህ ማለት መቀብል እንዳለበትም ሁሉ መስጠት አለበት።

አቶ ብርሃነመስቀል የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች ናቸው ብለው ሲጽፉ፣ አንደኛ በምን መስፈርትና ሚዛን እነዚህ ጥያቄዎች የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄውም ስለሞሆናቸው የገለጹልን ነገር የለም። እንዴት አወቁ የኦሮሞ ሕዝብ ያሉት ጥያቄዎቹ እነዚህ እንደሆኑ? ሁለተኛ የኦሮሞ ሕዝብ የሚሉት የትኛውን ሕዝብ ማለት እንደሆነ የጠራ መመዘኛ ያቀረቡ አይመስለኝም።የኦሮሞ ሕዝብ የሚባልው በኦሮሚያ የሚኖረው ወይንም የክልሉ ነዋሪዎች ማለቱ ነው? ወይስ አፋን ኦሮሞ አንደኛ ቋንቋው የሆነው ማህበረሰብ ማለታችቸው ነው? ወይስ ራሳቸውን ኦሮሞ ነን ብለው የሚጠሩ ወገኖች ስብስብን ነው የኦሮሞ ሕዝብ የሚሉት?

ይሄን ስል ግን ጥያቄዎቹ መነሳት የለባቸው ማለቴ አየደለም። ግን አቶ ብርሃነመስቀል የ”ኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች ናቸው” ብለው ከሚያቀርቧቸው “ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መመለስ አለባቸው የምላቸውም ወይንም የኦሮሞ ጥያቄዎች ናቸው ብዬ የማስባቸው ጥያቄዎች ናቸው” ብለው ቢያቀርቡት መልካም ይሆን ነበር። እኔም ጥያቄዎች እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች ሳይሆን በአቶ ብርሃነመስቀል የተነሱ ጥያቄዎች አድርጌ ሐሳብ እሰጥባቸዋለሁ፡

1. “በጉልበት እና ሕግን ሽፋን በማድርግ የተዘረፈው የኦሮሞ ሕዝብ መሬት እንዲመለስ፣ የወረራው መሠረት የሆኑት ሕጎች እንዲሻሩና የዘረፋ ተቋማቶቹ እንዲፈርሱ፣” ይላሉ አቶ ብርሃኑ መስቀል።

ትክክል ብለዋል። ሆኖም የኦሮሞ ሕዝብ መሬት የሚለው አባባል አይመቸኝም። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፣ ይህ አባባል የተወሰኑ ቦታዎች የኦሮሞ መሬት፣ ሌላው ደግሞ የሌሎች መሬት እንደሆነ የሚያመላክት አባባል ይመስለኛል። ሁሉም የኢትዮጵያ መሬት የኦሮሞዎች መሬት ነው። ሁሉም የትግሬዎች መሬት ነው። በመሆኑም በምትኩ “በጉልበትና ሕግን ሽፋን በማድረግ ከመሬታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችን መሬታቸው እንዲመለስ” የሚል አባባል ቢጠቀሙ ጥሩ ይሆን ነበር።

“የመሬት ነጠቃው መሰረት የሆኑ ሕጎች እንዲሻሩም” ሲሉ ጽፈዋል። ይሄንን ሲጽፉ፣ በሕገ መንግስቱ የተቀመጠውን “መሬት መሸጥና መለወጥ አይቻልም፣ መሬት የመንግስት ነው” የሚለውን አባባል ለምን እንዳልጠቀሱ አልገባኝም። አንዱና ትልቁ ችግር መሬት የአራሹ አለመሆኑ ነው። ገበሬው የመሬቱ ባለቤት መሆኑ በህግ እስካልተቀመጠ ድረስ ገበሬውን እና ድሃ ከተሜዎች እንዳይፈናቀሉ ሊያስቆም የሚችል የሕግ መሰረት አይኖርም። ብዙ የኦሮሞ ብሄረተኞች ገበሬው የመሬቱ ባለቤት እንዲሆን አይፈለጉም። መሬቱ የመገርሳ፣ የቶላ፣ የቀልቤሳ፣ የቱሉ ..ከሆነ መሬቱ የነዋሪዎቹ እንጂ የኦሮሞ ብሔረሰብ መሆኑ ይቀራል። በኦሮሚያ ውስጥም እነ ጎይቶም፣ እነ ሸምሹ፣ እነ አበጋዝ፣ እነቤርሳሞም የመሬት ባለቤት ይሆናሉ። ያንን የኦሮሞ ብሄረተኞች አይፈልጉም። እንደ ኦፌኮ ያሉ ደርጅቶች በዚህ ምክንያት ነው መሬት ለአራሹን የማይደገፉት።

2. “ኦሮምኛ ከአማርኛ ጎን ለጎን የኢትዮጽያ ፌድራል መንግስት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን” ሲሉ በሁለተኛነት አቶ ብርሃነመስቀል ያስቀምጣሉ።

ይሄም የሚደገፍ ሐሳብ ነው። አፋን ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ሶማሌኛና ትግሪኛም ቢጨመሩ ጥቅም ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። በተለይም ሶማሌኛ ተናጋሪ ከሆኑት ከሶማሊያ፣ ከሶማሌላንድና ጅቡቲ ጋር እንዲሁም ትግሪኛ ተናገሪ ከሆንችው ኤርትራ ጋር መቀራረቡን የበለጠ ለማጠናከር ይረዳል።

ቋንቋ በመሰረቱ ጠቃሚ ነገር ነው። ብዙ ቋንቋዎችን ማወቅ ጸጋ ነው። ብዙዎች የተለያዩ ቋንቋዎች ቢችሉ ጥቅም አለው እንጂ ጉዳት የለውም። ቋንቋ የመለያየት ምክንያት ሊሆን አይችልም፣ አይገባምም። በቅንነት ነገሩን ካየነው ከአማርኛ ቀጥሎ ሌሎች ቋንቋዎችም ፌዴራል ቋንቋ መሆናቸው ተቃውሞ ሊያስነሳ አይገባም።

ሆኖም በኦሮሚያ ክልል፣ ከአፋን ኦሮሞ ጎን አማርኛም የሥራ ቋንቋ የመሆኑ አስፈላጊነት ሊሰመርበት ይገባል። አቶ ብርሃነመስቀል በዚህ ረገድ ጥቂት ቢሉ ጥሩ ነበር። በአዳማ ከ75% በላይ የሚሆነው ነዋሪ አማርኛ ተናጋሪ ሆኖ፣ የክልል መንግስት አገልግሎት በአማርኛ መነፈጉ፣ አፋን ኦሮሞ ባለመቻሉ የኦሮሚያ ክልል መንግስት መስሪያ ቤቶች ተቀጥሮ የመስራት፣ የመመረጥ መብቱ መረገጡ ተገቢ ነው ይላሉን? አዳማን እንደ ምሳሌ ጠቀስኩ እንጂ በቡራዩ ከ45% በላይ፣ በሻሸመኔ፣ ቢሾፍቱ፣ ጂማ ባሉ ከተሞች ከ60% አፋን ኦሮሞ የማይችሉ ኢትዮጵያውውያን ይኖራሉ። አዲስ አበባን ጨመሮ በአራቱም የኦሮሚያ የሸዋ ዞኖች ከ44% በላይ ሕዝብ አፋን ኦሮሞ አይናገረም። ታዱያ ይሄን ያህል እጅግ በጣም ትልቅ ማይኖሪቲ “አፋን ኦሮሞ ብቻ” በሚል ፖሊሲ መገፋት አለበትን?

3. “አድስ አበባ እንደ ሌሎቹ ትላልቅ የኦሮሚያ ዞኖች የዞን ደረጃ ተሰጥቷት፣ አማርኛ እና ኦሮምኛ የሥራ ቋንቋ ሆነው በኦሮሚያ ሥር እንድትተዳደር፣” ሲሉ በአዲስ አበባ ዙሪያ ከዚህ በፊት ያልሰማሁት ሐሳብ አቅርበዋል። ከዚህ በፊት በሰጠሁት አስተያየት አዲስ አበባ በዙሪያዋ ያሉትን አካባቢዎች ያካተተ፣ አፋን ኦሮሞና አማርኛ የሥራ ቋንቋ የሆነበት፣ 10ኛ ክልል ቢኖር ጥሩ የሚል ሐሳብ አቅርቤ ነበር። እኔ ያቀርብኩት ሐሳብ አቶ ብርሃነመስቀል ካቀረቡት ሐሳብ ጋር ይመሳሰላል። ልዩነቱ እርሳቸው አዲስ አበባ ብቻ ሲሆን ያሉት እኔ ደግሞ አዲስ አበባ እና አካባቢዋንም እጨምራለሁ። እርሳቸው ኦሮሚያ ውስጥ ተኩኖ በዞን ደረጃ ይሁን ሲሉ እኔ ደግሞ ራሱን የቻለ ክልል ይሁን እላለሁ።

ሆኖም አቶ ብርሃኔ መስቀል ያቀረቡት ሐሳብ በጊዜያዊነት ተግባራዊ ቢሆን ችግር ይኖራል ብዬ አላስብም። እደግማለሁ እጊዜያዊነት። ይሀእን ስል ግን ሁለት ነጥቦችን በማስቀመጥ ነው። አንደኛ አዲስ አበባን ለብቻ ዞን ከማድረግ፣ የቡራዩ ልዩ ዞንና የሰሜን ሸዋ ዞንን ከአዲስ አበባ ጋር በማዋሃድ፣ አንድ ትልቅ ዞን በመፍጠር የዞኖኑ ቆዳ ስፋት ማስፋት ጥቅም አለው። ይህም ዞን በፌዴራል መንግስት ሥር የሚሆንን ሳይሆን፣ ተጠሪነቱ ለኦሮሚያ ክልል መንግስት ይሆናል። ሁለተኛ በሂደት ሕዝቡ ከፈለገ ዞኖችን ማዋሃድ፣ ወይንም ዞኖች የራሳቸው ክልል የመሆን መብት እንደሚኖራቸው ስምምነት መደረሰ አለበት። አሁን ያለችው ኦሮሚያ የምትባለው ክልል በሕዝብ ፍላጎት የተመሰረተች ክልል አይደለችም። “ኦሮሚያ ወይም ሞት” የሚለው የአንዳንድ ኦሮሞ ብሄረተኞች አባባል ተቀባይነት የሚኖረው አባባል አይደለም። ሕዝቡ በፈለገ ጊዜ እንዴት መተዳደር እንዳለበት የመወሰን ሙሉ መብት አለው። ኦሮሚያን መቀየር አይደለም፤ ሕዝቡ ከፈለገ ፌዴራሊዝምን አልፈለግም ማለት ይችላል።

4. “በግፉ ለተገደሉና ለታሰሩ የኦሮሞ ልጆች ካሳ ተከፉሎ ገዳዮችና አሳርዎች ለፉርድ እንድቀርቡ” በማለት ተጠያቂነትን እና ፍትህ መኖር እንዳለበት አቶ ብርሃነመስቀል ይጽፋሉ። 200% እስማማለሁ። በትክክል መሆን ያለበት ነገር ነው።

5. “ የኦሮሞ ሕዝብን ለ140 ዓመታት ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የለየው ሥረዓት ተሽሮ፣ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲ እንዲወጣ” ሲሉ አቶ ብርሃነመስቀል በጻፉት ላይ ትንሽ ያልተመቸኝ ነገር አለ። ለ140 አመታት ያሉት ምን ለማለት እንደፈለጉ ቢዘረዝሩት በስፋት ሐሳብ ለመስጠት ይረዳ ነበር። ይመስለኛል፤ በአይምሯቸው አጼ ሚኒሊክን እያሰቡ መሰለኝ። አንደኛ እርሳቸው ምናልባት ወደሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች ሄደው የሕዝቡን ሁኔታ ቢመለከቱ ጥሩ ሊሆን ይችል ነበር። በይፋት፣ በመንዝ፣ በቆቦ፣. በኣጽቢ፣ በአሳይታ ምን ያህል ሌላው ማህበረሰብ በድህነት የማቀቀ እንደሆኑ ይረዱ ነበር። ኦሮሞው ብቻ የኢኮኖሞ ተጠቃሚ እንዳልሆነ አድርገውም አያቀርቡም ነበር። ሁለተኛ ታሪክን እያነሳን እንነጋገር ከተባለ ከመቶ አመት በፊት ሆነ የተባለውን ብቻ ሳይሆን ከሁለት፣ ሶስት፣ አራት መቶ አመታት በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረገውን ልናነሳ እንችላለን። ይልቅ ተጣሞ የቀረበን ታሪክ እያነበበን ከመወነጃጀል፣ የወደፊቱን ላይ ብናተኩር የሚበጅ ይመስለኛል። ሂሳብ መተሳሰብ ከተጀመረ፣ ሌሎችም ሊመነዝሩት የሚችሉት ብዙ ነገር በእጃቸው እንዳለ እነ አቶ ብርሃነመስቀል መረዳት ያለባቸው ይመስለኛል።

6. “የኦሮሞ ሕዝብ በክልል ደረጃ ከፌዴራል ተላላኪዎ እጅ ወጥቶ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድርና በፌዴራል ደረጃ ኢትዮጵያን በድርሻው ልክ ተወክሎ እንዲያስተዳድር” ሲሉ አቶ ብርሃነመስቀል ስድስተኛ ነጥባቸውን ያስቀምጣሉ።

የፌዴራል ስርዓት እስከሆነ ድረስ ያለው በአገሪቷ የፌዴራል ስርዐት የተቀመጡ ሕጎች መከበር አለባቸው። ሕግ የበላይ ካልሆነ የፌዴራል ስርዓት ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። አምባገነናዊ ስርዓት ብለበት ሁኔት ፌዴርሊዝም አይሰራም።በመሆኑም እውነተኛ ፌዴራሊዝም እንዲኖር ሕግ የበላይ የሆነበት ስርዓት መኖር አለበት። የፌዴራል መንግስት ከሕግ ውጭ በክልል ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም። ክልሎችም በዞን እና በወረዳ አስተዳደሮች ሕጉ ከሚፈቅድላቸው ውጭ ጣልቃ መግባት የለባቸው። ላችንንም ሕግ ከገዛን ነገሮች ይስተካከላሉ።

የአቶ ብርሃነመስቀል አበበን ጽሑፍ (“የኦሮሞ ሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ የመብት ጥያቄዎች ለድርድር እና ለልመና የሚቀርቡ አይደሉም”) ለማንበብ ከሁለት አንዱን አስፈንጣሪዎች ይጫኑ!

1፣ ፌስቡክ 

2፣ ኢትዮጵያ ዛሬ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ