“ግብር ለሚገባው ግብር ገብሩ”
ፕሮፌሠር ጌታቸው ኃይሌ
የክርስቲያኖቹ መጽሐፍ “ግብር ለሚገባው (ሹም) ግብር ገብሩ” ይላል። ግብር ለማይገባው እንደወያኔ ላለ ገዢ ግን ግብር ስለማይገባው አንዲት ቀይ ቤሳ አታቅምሱት ማለቱ ነው። ጊዜ ስለሰጠው ቀምቶ ይወስዳል። ግን ብዕሬ ስቦኝ ነው እንጂ ለማለት የፈለግሁት እንኳን “አድናቆት ለሚገባቸው የኦሮምኛ ተናጋሪ የጎሣ ፖለቲከኞች አድናቆት ስጧቸው” ለማለት ነበር።
ታሪኩ እንዲህ ነው፤ ኢጣልያ ሰሜን ኢትዮጵያን ቆርሳ ወስዳ በቁራሹ ውስጥ ያሉትን የተለያየ ስም ያላቸውን ወረዳና አውራጃዎች ሰብስባ አንድ ራሷን የቻለች ሀገር ለማድረግ “ኤርትራ” የሚል ስም አወጣችለት። ከ1890 ዓ.ም. ጀምሮ ብዙዎቹ ክፍለ ሀገሮች አንድ ሀገር ሆኑ። ከኢትዮጵያ የመገንጠል ሐሳብ በውስጣቸው የሠረፀባቸው የዚያ አካባቢ ልጆች በአንድ ስም ለመጠራት አመቻቸው። ኢጣልያ ያንን አካባቢ ወስዳ አንድ ሀገር እስክታደርገው ድረስ ነዋሪዎቹን ከኢትዮጵያዊነት በቀር “ማን” የሚያደርጋቸው ሌላ ነገር ወይም ምክንያት አልነበራቸውም። በሀገር ደረጃ ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ በጎሣ ደረጃ በየራሳቸው ስም የሚጠሩና ወደብዙ ጎሣ የሚዘረዘሩ ዘጠኝ ጎሣዎች ናቸው። አሁንም በዚያው ደረጃ አሉ። የኢጣልያ አገዛዝ ስማቸው ኢትዮጵያዊ ከመባል ኤርትራዊ ወደመባል ለወጠው እንጂ የውስጥ የጎሣ መታወቂያቸው እንዳለ ነው። ከኢጣልያ ግዛት ሲወጣና ከኢትዮጵያ ጋር ሲደባለቅ እልል ያለው ህዝብ ስሙንም ሆነ መገንጠሉን መውደዱን ለማመን ያስቸግራል። ተደባብሶ ከዚህ ደረሰ እንበል።
አሁን ተራው የቱለማና የበረይቱማ ልጆች ነው። አንደኛ፣ የታሪኩ እውነተኛነት በማንም የታሪክ ሊቅ ሳይረጋገጥ፣ የበረይቱማና የቦረን ልጆች ኦሮሞ የሚባል አንድ ህዝብ ሳይሆኑ፣ “ኦሮሞ የሚባል አንድ ህዝብ ነን” ብለው ዓለምን አሳመኑ። ሊደነቁ ይገባቸዋል። ሁለተኛ ኢጣልያ ከኢትዮጵያ ላይ መሬት ቈርሳ ኤርትራ የምትባል ሀገር እንደፈጠረች፣ የበረይቱማና የቦረን ልጆችም፣ ማንም ልብ ሳይለው በወያኔዎች አዋላጅነት ኦሮሚያ የሚባል ሀገር ፈጠሩ። ተደባብሶ ከዚህ ደረሰ እንበል። እንግሊዞች ያልሆነላቸው ለነሱ ሆነላቸው። ሊደነቁ ይገባቸዋል። ዛሬ ስለ ኦሮሞ ህዝብና ስለኦሮሚያ ሀገር አፉን ሞልቶ የማይናገር፣ ጆሮውን ከፍቶ የማይሰማ በቍጥር ነው። “የቱ ነው የኦሮሞ ህዝብ?” ብሎ ለሚጠይቅ (የሚጠይቅ ካለ) የሚያሳዩት በኦሮሞ ህዝብነት ምን ጊዜም ያልመከቱትን ኦሮምኛ ተናጋሪዎችን (የበረይቱማንና የቦረንን ጎሣዎችን) አንድ ህዝብ አድርገው ነው። ታሪካቸውን እንደምናውቀው ከሆነ፣ ጎሣዎቹ ከባህል ያለፈ አንድነት የነበራቸው ጊዜ አልነበረም። የህዝብ አንድነት ምልክቱ፣ ለአንድ ጉዳይ (በተለይ ለአንድ ችግር) በአንድነት መመከቱ፣ አጸፋውን መስጠቱ ነው። አንድ ህዝብ አንድነቱን የሚያሳየው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳደረገው በአንድነት ሲዘምት፣ በአንድነት ሲመክት፣ በአንድነት አጸፋ ሲሰጥ ነው። አፄ ሠርጸ ድንግል ቱርኮችን ከምድረ ባሕር (ዛሬ ኤርትራ ከምትባለው ሀገር) ያስወጣቸው አንድነት ያለውን የኢትዮጵያ ህዝብ (በተለይ የበረይቱማ ጎሣዎችን) አስሰልፎ ነበር። አድዋንና ማይጨውንም መጥቀስ ይቻላል። የበረይቱማና የቦረን ጎሣዎች እንዲህ ዓይነት ታሪክ የላቸውም። የጋራ ችግር ገጥሟቸው በጋራ አልመከቱም፤ በጋራ አጸፋ አልሰጡም። የቱለማና የበረይቱማ ጎሣዎች ከደቡብ ተነሥተው ማህል ኢትዮጵያን የወረሩት ለከብታቸው ግጦሽ ፍለጋ ስለነበረ፣ ወረራቸው እንደ አንድ ህዝብ ሳይሆን እንደ ባላንጣ እርስ በርሳቸው እየተዋጉ ነበረ።
እርግጥ፣ የባህል አንድነት በመሠረቱ የህዝብን አንድነት ያመለክታል። የበረይቱማና የቦረን ልጆች ቋንቋቸውና ሌላው ባህላቸው ተመሳሳይ ነው። አንድ ጊዜ አንድ ህዝብ ቢሆኑ ነው። አንድ ያልሆነ ህዝብ ከመነሻው በአንድ ቋንቋ አይናገርም። ግን ያ የጥንቱ አንድነት በጥንትነት ቀርቷል። የአዳም ልጆች በአንድ ቋንቋ ይናገሩ ነበር እንደማለት ነው። በልጂጎችና ፈንሳዮች፣ አልናኖችና ነምሳዎች፣ (ጀርመኖችና አውስርቲያዎች) በአንድ ቋንቋ እንደሚናገሩ እንደማለት ነው። የአሁኖቹ የበረይቱማና የቦረን ጎሣዎች ሁኔታቸው የሱማሌዎችን ሁኔታ አይቶ ማየት ነው። ከቀረው ከጥንቱ አንድነታቸው ወዲህ አንድነት ነበራቸው ከተባለ በኢትዮጵያዊነትና በኬንያዊነት ነው። ኤኮኖሚያቸው ከላይ እንደጠቀስኩት፣ ከብት ማርባት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ፣ የነዚህ እንደ አሸን የሞሉት ጎሣዎቻቸው ታሪክ የአንድ ህዝብነት ሳይሆን፣ በግጦሽ መጣላት ነበር። ለምሳሌ፣ ወረንሻ መጀመሪያ ከወርድያ ጋር ተስማምቶ ነበር፤ ወርድያን ከድቶ፣ ህዝቡን ፈጅቶ ከአክቹ ጋር ሆነ፤ አክቹን ከድቶ ህዝቡን ፈጅቶ ወደ ሊበን ሄደ፤ ሊበንን ከድቶ ህዝቡን ፈጅቶ ወደ ወሎ ተጠጋ፤ ወሎን ከድቶ፣ ከሊበን ጋር ታረቀ።
ከደቡብ ኢትዮጵያ እየወጡ ማህል ኢትዮጵያን ሲወሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የነበራቸው ጥል፣ የአርሶ አደሩን ሰብል ኍልቍ ወመሳፍርት ለሌለው መንጋችሁ መኖ አድርጋችሁ ሰላማዊውን ህዝብ አታስርቡት፤ ቅዱሳት መካናትንም የከብት በረት አታድርጓቸው ስለሚባሉ ነበር። የከብታቸው ብዛት እንደ አንበጣ ሰብሉን ላስ ያደርገው ነበር። ነገሥታቱ ቢቸግራቸው አንዳንዶቹን ባዶ ቦታ እየፈለጉ ያሰፍሯቸው ነበር። አልሆነም፣ ከአንዱ ጋር ሰላም ሲፈጠር ሌላው ይከዳል። ከላይ የጠቀስኩት ወረንሻ ሊበንን ከድቶ ከንጉሥ ሱስንዮስ ጋር ተስማምቶ ወለቃ ላይ ቢያሰፍረው የወለቃን ሰዎች ፈጃቸው።
የጎሣዎቹ ቍጥር በልክና በትክክል አይታወቅም። አለቃ ታየ ባደረጉት ጥናት እነዚህን መዝግበዋል፤
የጎሣ አባቶች፤ ከረዩ፣ መረዋ፣ ኢቱ፣ አክቹ፣ ወረነሻ፣ ሁምበና።
ልጆች ጎሣዎች፤ ሊበን፣ ሜጫ፣ ቱለማ፣ ወሎ፣ ጅሌ፣ አቦ፣ ሉባ፣ በላእ፣ ወርድያ፣ አሩሲ፣ ኢቱ፣ ኡር፣ አበጢ፣ ጅሌ፣ ጅንጉር፣ ጨፋ፣ ሰዩ፣ አቡ፣ ጫቡ፣ ይሉ፣ ጉድሩ፣ ኩታይ፣ አሞሩ፣ ሆሮ፣ ራያ፣ አዘቦ፣ አሸንጌ፣ ዳጨ፣ ኮኖ፣ ቦች፣ አካኮ፣ ወቦ፣ ጭሌ፣ ሊበን፣ ሆኮ፣ ሌቃ፣ ጨለባ፣ ወለጋ፣ ጉማ፣ ሊሙ፣ ጅማ፣ ጌራ፣ አብቹ፣ ግምብቹ፣ ወበሪ፣ ገላን፣ ሉሜ፣ ሜታ፣ ዋዩ፣ ጉለሌ፣ ሰላሌ፣ አበቲ፣ ደራ፣ ቦረና።
ወያኔዎች የትግራይን ህዝብ “አማራ በድሎሃል” እያሉ በማሳመንና በማስፈራራት ኢትዮጵያ የትግራይ ጠላት መሆኗን ያመኑ፣ ለመግደልም ለመሞትም የቈረጡ ብዙ ልጆች መለመሉ። ህዝቡንም ፕሮፓጋንዳውን ማመን አለማመኑ ሳይታወቅ፣ ያመነና ሀገሩን የከዳ አደረጉት። የነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው ጎሣዎች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። የፖለቲከኞቹ ጥረት ጎሣዎቹ ከራሳቸው ጎሣና ከኢትዮጵያዊነታቸው በቀር አንድ የኦሮሞ ህዝብ መሆናቸውን ሳያውቁት እንዲቀበሉት ለማድረግ ነው። እየቀናቸው ነው። የበረይቱማና የቦረን ዘር የሆነ ሁሉ የጎሣ ፖለቲከኞች የጠነሰሱለትን መጐንጨት ጀምሯል። አንዲት ሴትሙስሊማ ከሆነች “ፊትሽን በሂጃብ መጀቦን አለብሽ” እንደምትባል ማለት ነው። ማስገደጃው በኃይል ማስጨነቅና በፕሮፓጋንዳ ወጥሮ መያዝ ነው። ተበድላችኋል ተብለዋል፤ የሰፈሩበትን መሬት ሰፍረውበትና እየተጠቀሙበት ሳለ፣ “አልሰፈራችሁበትም፣ አልተጠቀማችሁበትም፣ አማራ ወስዶባችሁ መሬት አልባ ሆናችኋል” ተባሉ። በዓይን ማየት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ፖለቲካ እውነትን ለማመን አልጠቀመምና የተባለውን የሚቀበሉት ቍጥራቸው እየጨመረ የሄደ ይመስላል።
ከላይ እንደገለጽኩት፣ መቸም “ኦሮሞ” የሚለው ስም ለሌለ ህዝብ አልወጣም። በጎሣ ከመበታተናቸው በፊት እንደ ቋንቋው ከጥንት የተወረሰ ሆኖ የጥንት ሀገራቸውን ሳይለቁ የተጠሩበት ስም ሊሆን ይችላል። ማህል ኢትዮጵያን ከወረሱ በኋላ ግን የሚታወቁት በየጎሣቸው ነው። “ጃዊ የአዘዞን ህዝብ ሰለበ”፤ “በወርድያ ጦር ምክንያት አገሪቷ ተሸበረች”፤ “በዚህ ዓመት መጠኑ አርባ ሺ የሚሆን ለበቻ ወደ ትግሬ መጣ”፤ ወዘተ. የሚል እንጂ አንድም ቦታ “ኦሮሞዎች እንዲህ አደረጉ” የሚል ሰነድ የለንም። በአንድ ህዝብነት ስማቸው ታውቆ ቢሆን ኖሮ ሊቃውንቱ ዛሬ በተጠላው ስም ከመጥራት ይልቅ በታወቀው ስም ይጠሯቸው ነበር። ጎሣዎቹም ኦሮሞ ነን አላሉም፤ ጸሐፊዎቹም ኦሮሞ አላሏቸውም። ግን “ኤርትራ” ከሚለው የቅኝ ገዢዎች ካወጡት ስም ይሻላል፤ አገር በቀል ነው።
የታሪክን ሂደት ስናይ፣ ሀገር የሚገነባውም፣ የሚፈርሰውም በኃይል ስለሆነ፣ ኦሮሚያን ለመፍጠር የሚካሄደው ድርጊት አዲስ ሊሆንብን አይገባም። ግን ያለንበት ዘመን የህዝብ ድምፅ የሚከበርበት ስለሆነ፣ አባቶቻቸው በጋራ የገነቧት ሀገር (ኢትዮጵያ) የወደፊት ዕጣዋ ሲጣል፣ እነሱም ኢትዮጵያዊነታቸው ሲገፈፍ፣ ፈቃዳቸው መጠየቅ ነበረበት። የማይጠየቁት መልሱ ስለማይጥም መሆኑን በየምርጫ አጋጣሚ አይተነዋል። ጎሰኝነትን “ዓይንህን ለዐፈር ይዳርገው” ብለውት ነበር። ግን የህዝብ ፈቃድ መጠየቅ በዲክታተሮች ዘመን የማይታሰብ ነው። ዲክታተሮች “የሥልጣን ምንጩህዝብ ነውና ህዝብ ልቀቁ ብሏችኋል” ሲባሉ፣ “ዛሬ ማታ ሕይወታችሁ ታልፋለች” የተባሉ ይመስል፣ ሕይወታቸው እስክታልፍ በእምቢተኝነቱ ይጸናሉ።
የብዙነት ኃይሎች የአንድነት ኃይሎችን መብት ነጥቀው ትጥቃቸውን አስፈትተው ይገዟቸዋል፤ ፍላጎታቸው ተጨቁኗል። ሀገራቸውንም የጠላት ንብረት አድርገዋታል። “የአንድነት ኃይሎች” ስንል “ነፍጠኞች አማሮች” የምንል ያስመስሉታል። “ነፍጠኞች” ቢሉ እውነታቸውን ነው። “ነፍጥ” ማለት ጠመንጃ ማለት ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት አገር ያቀናው፣ ዳር ድምበር ያስከበረው፣ በነፍጥ እንጂ በአርጩሜና በአለንጋ አይደለም። ቅጽሉ “ለአማሮች” መሆኑ ግን ስሕተት ነው፤ የኢትዮጵያን የጦር ሠራዊት ታሪክ ማንበብ ከስሕተት ያድናል–ከስሕተት ለመዳን ለሚፈልግ ማለት ነው።
ብዙዎች አውራጃዎችን ማጠቃለል የሚወደደውም ሆነ የሚጠላው በዓላማው ነው። ለአስተዳደርና የሀገሪቱን ኢኮኖሚው ለማዳበር እንዲመች ከሆነ ይደገፋል፤ ያውም ቢሆን በህዝብ ፈቃድ ሲፈጸም ነው። በቋንቋ ማጠቃለል ግን ተንኮልና በደል አለበት፤ ይጠላል። ተንኮልና በደልን አጥብቀን መቃወም አለብን፤ የሠለጠነ ህዝብ ግዴታና ምልክት ነው። ተንኮሉ፣ “አንድ ህዝብ አይደለንም” ብሎ ለመለያየትና ኢትዮጵያዊነትን ለማስቀረት ማመቻቸት ነው። ለዚያ ክፉ ቀን እንዲያመች “ኦሮሚያ” እና “ትግሪያ” ነፍጣቸው በጋለበ ሰፋፊ መሬት ይዘዋል። በደሉ፣ ቋንቋው ሌላ የሆነ ኢትዮጵያዊ ሰብአዊ መብቱ ይወሰድበታል፤ ወይ ይባረራል፣ ወይ ማንነቱን እንዲለውጥ ይገደዳል። “ኦሮሚያ” ውስጥ ያለቁትና በሺ የሚቈጠሩ ተፈናቃዮች በማስተጃነት እንውሰዳቸው። “ጥፋቱ የኛ አይደለም፤ የነእገሌ ነው” ለሚሉት ጥፋትን ካንዱ ወደሌላው ማንቀዋለል ዋጋ አንሰጥም። የጥፋቱ ምንጭ አንድን ህዝብ በቋንቋ መከፋፈል ነው። ዘዴው አለማግባቢያ መሆኑ የሰናኦርን ግምብ በገነቡ ሰዎች ላይ አይተነዋል።
ማንነትን በተመለከተ በወልቃይ ጸገዴ ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን ሥቃይ እንመልከት።
ለኦሮሞ ታሪክ ጸሐፊዎች በተለይ፤ የኦሮሞዎች ታሪክ የተፈጸመው በኢትዮጵያ ምድር ላይ ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው። የቦረንና የበረይቱማ ልጆች ማህል ኢትዮጵያን እንዴት እንደያዙ ሊቃውንቱ ብዙ ጽፈዋል። ታሪካችን ስለሆነ እንቀበለዋለን። የደናቁርቱን ጫጫታ ንቃችሁ የሊቃውንቱን መዛግብት በገለልተኝነት መርምሩና ታሪካችንን አስተምሩን። ትልቅ ህዝብ ታሪክ አንብቦ የሚቆጨው፣ “ምነው በዚያን ጊዜ እንዲህ በሆነ ነበር” ብሎ ነው እንጂ፣ “በዚያን ጊዜ እንዲህ ከሆነ ዛሬ መበቀል አለብን” ብሎ በቀል ለማንሣት አይደለም። በደል ያልደረሰበት የለም። በደል ያላደረሰ አባት ያለው የለም።
ለአማርኛ ተናጋሪዎች፤ ጀግና “ተበደልኩ” እያለ እሮሮ አያሰማም።