የሄነከን ቢራ ዘረፋ ምስጢር በኢትዮጵያ ሲጋለጥ
ክንፉ አሰፋ
የሆላንድ ዜምብላ[1] ጋዜጠኞች የኦሮሞ ፀሐፊው የሆነውን ያሶ ካባባን ይዘው ወደ ጊንጪ ያመራሉ። እግረመንገድ ላይ የሚያገኟቸው ገበሬዎችም ሲጠይቋቸው በምስሉ ይታያል። እነዚያ በቀያቸው ማረፍያ እንኳን የሌላቸው ገበሬዎች የጋዜጠኞቹን መኪና ከብበው እንዲህ ሲሉ ይደመጣሉ። "መሬታችንን ቀምተው ለነጮች ሰጡብን። እኛንም በታተኑን ..."
በገዛ ቀያቸው ስደተኛ የሆኑ እነዚህ ወገኖቻቸን ሰቆቃቸው የከፋ ነበር። በመጨረሻ ተሰባሰቡና መከሩ። ሰባት ሺህ የሚሆኑ የጊንጪ ተወላጆች ሆ! ብለው ወጥተው ይህንን የሁለት ሚሊዮን ዩሮ (ሃምሳ ሚልዮን ብር) ንብረት በሰኮንዶች ውስጥ አወደሙት። ምስላቸውን ለካሜራ ሳይደብቁ፣ ስሜታቸውን እና የወደፊት እቅዳቸውን ይናገራሉ። "ከአንባገነን መንግሥት ጋር አብሮ ከመሥራት ይልቅ የአካባቢው ነዋሪዎች ሊጠቀሙ በሚችሉበት መንገድ መሥራት እንደሚችሉም።" ለፈረንጆቹ ይመክራሉ። "ይህ ካልሆነ ግን ማውደሙን እንቀጥልበታለን!" ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ይህ ማስጠንቀቅያ ግዙፉ ዓለም አቀፍ ኩባንያ የሆነው ሄነከን ቢራንም ይመለከታል።
ባለፈው ሣምንት በሆላንድ ብሔራዊ ቴለቭዥን የተላለፈው ዜምብላ ፕሮግራም የሚሊዮኖችን ቀልብ ስቧል። ለዚህም ምክንያቶች አሉት። አንደኛው ምክንያት፤ የዜምብላ ፕሮግራም በምርመራ ጋዜጠኞች የሚሰራ በመሆኑ እጅግ የሚፈራ እና በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ በኢትዮጵያ እየወደመ ያለው ይህ ንብረት የተቋቋመው በሆላንድ መንግሥት ድጎማ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ የእያንዳንዱ ሆላንዳዊ ግብር ከፋይ ገንዘብ በመሆኑ ነው።
የሆላንድ የልማትና ትብብር ሚንስትር ለድሃ ሀገሮች እርዳታ ከመለገስ ይልቅ ወደ ንግድ ድጎማ ፊቱን ባዞረ ግዜ፣ 130 አትራፊ የንግድ ድርጅቶች ድጎማ እየተቀበሉ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። ከነዚህ ውስጥ ትልቁን የድጎማ ድርሻ የወሰደው ሄነከን ቢራ ነው። ሄነከን ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የሆላንድ መንግሥት አንድ ቢሊየን ዩሮ ድጎማ አድርጓል። እንደ ሆላንድ መንግሥት እሳቤ፣ ይህንን የልማት ትብብር ገንዘብ በእርዳታ መልክ ከመስጠት ይልቅ ይህንን አትራፊ ተቋም አበራትቶ ሥራ በመፍጠር እና በንግድና በሥራ ታክስ ሀገሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ ነበር። የሆነው ግን በተቃራኒ ነው።
የዜምብላ ቴሌቭዥን ዘገባ ያጋለጠው ጉዳይ በእጅጉ ያስደምማል። እንዲህ ነው የሆነው። እ.ኤ.አ. በ2011 ሄነከን ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ የቢራ ሥራ አዋጭ መሆኑን ስለተገነዘበ ስመ ጥሮቹን በደሌ እና ሐረር ቢራን ገዛቸው። ሥራውንም በእጅጉ አስፋፋ። በአኢትዮጵያ የቢራ ተጠቃሚዎች ቁጥር በእጥፍ እንዳደገም ዘገባው አስምሮበታል። ትርፉም እንደዚያው አደገ።
በደሌ ቢራ ከመሸጡ በፊት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ዩሮ ግብር ይከፍል ነበር። ሄነከን ከገዛው በኋላ ግን የከፈለው ዘጠኝ መቶ ሺህ ዩሮ ብቻ ነው። አንድ ሚሊየን ዩሮ ግብር ይከፍል የነበረው ሐረር ቢራም አሁን ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ዩሮ ብቻ ነው ያስገባው። ትርፉ ከእጥፍ በላይ እያደገ፣ ግብሩ ከእጥፍ በላይ የመቀነሱ ምስጢር ምን ይሆን?
የግብር ማጭበርበር ጥቆማ የደረሳቸው እነዚህ ጋዜጠኞች ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ንግድ ሚንስትር ሄዱ። ምኒስትሩ በዚህ የማጣራት ጉዳይ ላይ ሊተባባራቸው ፈቃደኛ አልነበረም። ከዚያም ወደ ጉምሩክ እና ቀረጥ ቢሮ አመሩ። እዚያም ምንም መረጃ እንሰጥም ይሏቸዋል። ምስጢሩን ለማውጣት የጓጉት እነዚህ ጋዜጠኖች ተስፋ አልቆረጡም። በመጨረሻ ወደ ንግድ ምክር ቤት አመሩ። የዚያ ባለሥልጣን የሰጧቸው ምላሽ የሚያስቅ ነው። "የንግድና ትርፍ ዘገባ አይደርሰንም።" አሉ። ታዲያ ንግድ ምክር ቤት ይህንን ካልመዘገበ ምን ይሆን የሚሰራው?
የንግድና የሥራ ግብር መቀነሱ ብቻ አይደለም። ቀድሞ በሐረር እና በበደሌ ቢራ ቋሚ ሰራተኛ የነበሩ 699 (44%) ሰራተኞችም ከሄነከን ቢራ ተቀንሰዋል። የሆላንድ መንግሥት ሥራ ፍጠሩ ብሎ ድጎማ ሲያደርግ፣ ይልቁንም ነባሩን ሰራተኛ ከሥራው አፈናቀሉት።
በኢትዮጵያ የሄነከን ተወካይ ሆላንዳዊ ነው። የዜምብላ ጋዜጠኖች የዚህን እንቆቅልሽ ለመፍታት እሱን ማፋጠጥ ይችላሉ። ስለዚህም ወደሱ አመሩ። የገቢና ወጪ ዘገባውን እንዲሰጣቸው ጠየቁት። እንቢ እንዳይል ቸገረው። ምክንያቱም በዚያ ዘገባ የሆላንድ መንግሥት የድጎማ ገንዘብ ሰላለበት። እሺ ብሎ ይፋ እንዳያደርገው ደግሞ ምስጢሩ ለህዝብ ሊወጣ ነው። እሱም አለ። "የፋይናንስ ሪፖርቱን እሰጣችኋለሁ። እናንተ ግን ለህዝብ ይፋ እንደማታደርጉት ቃል ግቡልኝ።"
ዘገባውን በእጃቸው ያስገቡት እነዚህ ጋዜጠኖች፣ ዶክመንቱን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቁዋም አማካሪዎች ጋ ይዘውት ሄዱ። የአይ.ኤም.ኤፍ. ባለሙያው ወረቀቱን እንዳየ ምስጢሩን ለማወቅ ሰከንዶች አልፈጁበትም። የኢትዮጵያ ህዝብ በታክስ ተዘርፏል። ሰራተኛውም ወገን ከሥራው እንዲፈናቀል ተደርጓል።
የመንግሥት ባለሥልጣን ሀገር ሲዘረፍ እና ወገን ከሥራ ሲፈናቀል፣ ጉዳዩን ማፈን መርጠዋል። ምክንያት ቢኖራቸው እንጂ ይህን መረጃ መስጠት ሀገርን የሚጠቅም ነበር። በእርግጥ ይህ የግብር ማጭበርበር ተግባር እነሱ ሳያውቁት ሊሆን አይችልም። "የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ!" ነው ነገሩ። እንዲህ እየተዘረፈ ኢኮኖሚው እንዴት ነው በ11 በመቶ የሚያድገው?
እንግዲህ ይህ በኢትዮጵያ ከዘመቱት 130 የሆላድ የንግድ ድርጅቶች አንዱ ታሪክ ነው። ገቢውና ወጭው በግልጽ የሚታይ፣ ግዙፍ እና ዓለም አቀፍ ድርጅት። ሄነከን ከገዥው ፓርቲ ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር ይህንን ያህል ከዘረፈ የሌሎቹ - የማይታወቁት ምን ያህ ይሆን?
የቀድሞው የሆላንድ ልማትና ትብብር ሚንስቴር የነበሩት ጃን ፕሮንክ፣ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከልማት እና እደገት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ለሌላቸው የንግድ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግን ክፉኛ ይወቅሳሉ። በተለይ መንግሥታቸው በልማትና ትብብር ስም፣ በብሄራው ጥቅም ስም የስብአዊ መብት ረገጣን ችላ ማለቱን ያወግዛሉ።
በልማት ስም በሚሊዮኖች እየፈሰሰ ያለው የሆላንድ ግብር ከፋዮች ገንዘብ በኢትዮጵያ ሥራ አልፈጠረም። እንደውም ሰራተኞችን አፈናቀለ። ሀገሪቱን በበለጠ የሥራና የንግድ ግብር ተጠቃሚ ያደርጋል ይባል እንጂ ግብሩ በ 70 እጅ ያነሰ ሆኗል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የገበሬው መሬት እየተነጠቀ ለነዚህ ዘራፊዎች መሰጠቱ የህዝብ ቁጣን አስነስቷል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ አመጽ የገዥው ፓርቲ ችግር ብቻ ሳይሆን የሆላንድም ችግር መሆኑን በመግለጽ ዜምብላ ዘገባውን ይደመድማል።
[1] http://zembla.vara.nl/seizoenen/2016/afleveringen/23-03-2016