ይገረም አለሙ

Blue party. ሰማያዊ ፓርቲ

የፖለቲከ ስህተትና የሳንባ ነቀርሳ ጠንቆች የተመሳሳይነት ባህርይ አላቸው። ሁለቱም ችግሮች በለጋነታቸው ወቅት ከተነቃባቸው ችግሮቹን የማስወገድ ዕድል ከፍተኛ ነው። ችግሮቹ ሥር ከሰደዱ በኋላ የሚደረገው መሯሯጥ ግን ፈውስ የማስገኘቱ ሁኔታ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን የማይቻልም ሊሆን ይችላል። (ማርጋሪት ታቸር የእንግሊዝ ጠ/ሚ የነበሩ)

ፓርቲ የምርጫ ቦርድ የምዝገባ ምስክር ወረቀት መያዝ አይደለም፤ ዓርማና ማሕተም ቀርጾ ቢሮ መክፈትም አይደለም፤ አልፎ አልፎ ብቅ እያሉ መግለጫ መስጠትም አይደለም፤ ወዘተ። በዚህ ለሚስማማ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ፓርቲ የለም። ስለሆነም በሌለ ነገር ላይ ምንም አይባልም ተብሎ ዝም ሲባል የዝምታን ግድብ የሚያፈርሱ ጉዳዮች ያጋጥማሉ።

ሰሞኑን የሰማያዊ ሰዎች (ልብ በሉ ፓርቲ አላልኩም) ጉዳይ ከሀገር ቤት ጋዜጦችና ማንም እንደፈለገው ከሚፈነጭበት ማኅበራዊ ድረ ገጽ አልፎ፤ ብዙ አድማጭ ያላቸው የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ራዲዮኖች ዜና ለመሆን መብቃቱ ነው የእኔን ዝምታ አስጥሶ ይህችን እንድጽፍ ግድ ያለኝ።

ከሰማያዊ ሰፈር የምንሰማው ባለፉት ሃያ ዓመታት ስንሰማ ከኖርነው በቃላትም በድርጊትም አንዳችም ልዩነት የሌለው ነው። ፖለቲከኞቹ በሽታቸውን አያውቁም፤ ቢያውቁም አምነው ትክክለኛውን መድኃኒት ለመውሰድ አይደፍሩም። በመሆኑም ሥራቸው ሁሉ መካሰስ፣ መወነጃጀል፣ መፈራረጅ፣ ማገድ፣ ማባረር፣ … ወዘተ ብቻ ይሆናል። ይህ ደግሞ በሽታውን ይበልጥ ያብሰውና ስብስቡ ፓርቲ የሚል ስም ይዞ ግን ፓርቲ ደረጃ ሳይደርስ ይሞታል፤ አልያም የአልጋ ቁራኛ ይሆናል።

ሰሞነኛው የሰማያዊ ሰፈር ዜናም ታገዱ፣ ተባረሩ፣ ውሳኔውን ተቃወሙ፣ ኦዲት ኮሚሽን ውሳኔውን አገደ፣ … ወዘተ የሚል ነው። ይህ በምንም መልኩ ስብስቡን ከበሽታው ሊያድነውና ከሞት ሊታደገው አይችልም። አበው “ውኃን ከጥሩ ነገርን ከስሩ” እንደሚሉት፤ ዘለቅ ብሎ ወደ ውስጥ ጠልቆ የበሽታውን ምንነትና እንዴትነት መመርመር ደፈር ብሎም መድኃኒቱን ለመውሰድ መዘጋጀት ከሌለ፤ ዋይታውን አቁሞ ለቀብሩ መዘጋጀት ነው።

የዚህ ጽሁፍ ዓላማ አውቀውት፤ ግን ድፍረት በማጣት አልያም ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ሆኖባቸው ያላወቁትን በሽታቸውን ከነምክንያቱና ምልክቱ በማሳየት፤ በርግጥ ችግሩ የየግል ጉዳይ ሳይሆን ስብስቡን መታደግና በሂደትም ወደ ፓርቲ ደረጃ ማሸጋገር ከሆነ፤ ደፍረው በበሽታቸው ላይ እንዲነጋገሩ መድኃኒቱንም ሁሉም እንደ ሕመማቸው መጠን እንዲወስዱ ለማበረታታት ነው። ነገር ግን ለዚህ ፈቃደኝነቱም ዝግጁነቱም ድፍረቱም ያላቸው ምን ያህል ሰዎች ይኖሩ ይሆን የሚለው ስጋቴ ነው። ቢሆንም ቀብሩ ላይ ከማልቀስ ከበሽታው እንዲፈወስ የሚቻለውን ማድረጉ ይሻላልና የእኔን ልወጣ። ይህች ጽሁፍ በበቂ ማስረጃ ላይ የተመሰረተች እንድትሆን ስለ ሰማያዊ ካለኝ እውቀት በተጨማሪ ወደ ኋላ ተመልሼ ጽሁፎችን ለማየትና ከአባላቱና ከአመራሮችም ጥቂቶችን ለማነጋገር ሞክሬአለሁ፤

ሰማያዊ የታመመው ወፌ ቆመች ሳይባል ነው። ለዚህ ያበቁት ምክንያቶች ደግሞ፤

1. የግንቦት 2004 ሰላማዊ ሰልፍ፤

ሰማያዊ የፓርቲነት ምስክር ወረቀት አግኝቶ ሁለት ዓመት ሳይሞላው የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ውጤታማ ሆነ። ይህ ሰልፍ ከምርጫ 97 በኋላ የመጀመሪያ በመሆኑም ለሰባት ዓመታት የተዘጋውን የሰላማዊ ሰልፍ በር ያስከፈተ የሚል ቅጽል ተሰጥቶት የመገናኛ ብዙኀን አብይ ትኩረት ሆነ። የስብስቡ አባላት በተለይም በመሪነት ቦታ የነበሩት ሰልፉን ውጤታማ ያደረገው ከእነርሱ ሥራ በላይ የወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት (የሙስሊሞች ተቃውሞ) መሆኑን እያወቁ፤ ቢያውቁም የእነርሱ ሥራ፣ የፓርቲያቸው ጥንካሬ፣ የመሪዎቹ ብቃት እንደሆነ አድርገው ተኮፈሱ ተኩራሩ። በዚህም ገና ወፌ ቆመች ሳይባሉ ፓርቲ ለመሆን የሚያበቃቸውን ድርጅታዊ ሥራ ሳይከውኑ በሽታው ጀመራቸው።

2. የሊቀመንበሩ የአሜረካ ጉዞ፤

ሊቀመንበሩ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከአሜሪካ የተመለሱት ለ“ፓርቲያቸው” ገንዘብና ቁሳቁስ ለራሳቸው ደግሞ ማን አህሎኝነት ይዘው ነው። ከዲያስፖራው የተለገሳቸው አክብሮት አድናቆት ሙገሳና ጭብጨባ ከሚችሉት በላይ ሆነና ራሳቸውን የሰማያዊ ብቸኛ ሰው አድርገው እንዲያዩ አበቃቸው።

3. ሊቀመንበሩ በተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች መጋበዝ፤

አስቀድሞ የግብዣው ዓላማ ምንድን ነው፤ ከእኛ የሚፈልጉት ምን ይሆን፤ እኛስ ከዚህ የምናተርፈው ነገር አለ ወይ ብሎ፤ ከግንኙነቱም በኋላ ከዴፕሎማቶቹ ምን ተረዳን፤ ከእኛ ምን አገኙ፤ እኛስ ምን አገኘን፤ ወደ ፊት ከእኛ ስለሚፈልጉት ነገርስ ምን ተረዳን፤ … ወዘተ ብሎ ሂደቱን ገምግሞ ለበለጠ ሥራ ከመዘጋጀት ይልቅ ሰማያዊ ተለይቶ የተጋበዘው ጠንካራና አማራጭ ሊሆን እንደሚችል በመገንዘባቸው ነው የሚል እብጠት ተፈጠረና ሥራ ቀርቶ ወሬው ሁሉ ይሄ ሆነ።

4. የሥራ አስፈጻሚ አባላቱ የግልም የጋራም ኃላፊነታቸውን አለመወጣት፤

ሥራ አስፈጻሚው በመተዳደሪያ ደንብ ላይ የሚገለጹ ኃላፊነቶቹን እንዲወጣ የእያንዳንዱ የሥራ አስፈጻሚ አባላቱ ብቃት፣ ትጋትና ራስን ለትግሉ መስጠት ወሳኝ ነው። በአንጻሩ እያንዳንዱ የሥራ አስፈጻሚ አባል የተመደበበትን የየግል ኃላፊነት እንዲወጣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴውና የሊቀመንበሩ ድርሻ ወሳኝ ነው። ነገር ግን በአመራር ላይ የነበሩ ሳይቀሩ ይህ እንዳልነበረ ነው የሚናገሩት። በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን የሚታዩትና የሚሰሙት ሊቀመንበሩ ብቻ መሆናቸውም የሥራ አስፈጻሚ አባላቱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ እንዳልነበረ የሚያረጋግጡ ናቸው። ይህም ስብስቡ መተዳደሪያ ደንቡን አክብሮ በመመሪያ እየተመራ የሚሠራ ሳይሆን በፍላጎትና ስሜት ብቻ የሚጓዝ እንደነበረ ያሳያል። ዛሬ ሰበብ ሆኖ የሚነገረው የገንዘብ ጉዳይ ከመነሻው የገንዘብ አጠቃቀም መመሪያ ቢኖር እዚህ ደረጃ ባልተደረሰ ነበር።

ሌሎች ብዙ ምክንያቶች መጥቀስ ቢቻልም፤ በዚህ ይብቃኝና የበሽታውን ምልክቶች በመጠኑ ላሳይ፤

1. ከሰማያዊ በቀር ሌላ ፓርቲ የለም፤

ፓርቲ ለመባል የሚያበቃ ደረጃ ላይ ያልደረሰው ሰማያዊ፤ ሌሎቹን በሙሉ ፓርቲ አይደላችሁም በማለት ገና ወፌ ቆመች ሳይባል ግጭት ውስጥ መግባቱ።

2. ፍረጃና ውንጀላ፤

የሚነሱ ሃሳቦችንና ጥያቄዎችን በውይይት መፍታት የሚባል ነገር ጠፍቶ፤ ወገን ለይቶ ቡድን መፍጠር መወነጃጀልና መፈራረጅ፤ ከዚህም አልፎ ለአንድ ዓላማ በአንድ ፓርቲ የተሰባሰቡ ሰዎች እንደ ደመኛ ጠላት መተያየት።

3. በጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ መለያየት፤

የአንድ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ መቼ፣ እንዴት፣ በማንና ለምን እንደሚጠራ መተዳደያ ደንቡ ስለሚወስን ልዩነት ሊፈጥር አይችልም። የሰማያዊ አባላት በ2006/07 ጠቅላላ ጉባዔ ይጠራ፤ አይጠራም በማለት የከረረ ቅራኔ ውስጥ መግባታቸው የበሽታቸው አንዱ ምልክት ነበር። በወቅቱ እንደሰማነው የአይጠራም ባዮቹ መከራከሪያ የሰማያዊ ዕድሜ የሚቆጠረው መስራች ጉባዔው ከተካሄደበት ሳይሆን ምርጫ ቦርድ ሰርተፍኬት ከሰጠበት ግዜ ነው የሚል መሆኑ በሽታቸው ስር እየሰደደ ለመሄዱ የሚያሳይ ነበር።

4. ውይይትን አሻፈረኝ ማለት፤

2006 ላይ በወቅቱ ለነበረው የቁጥጥር ኮሚሽን ክሶች ቀረቡ። ኮሚሽኑ ክሱን ካጣራ በኋላ የርሱ ውሳኔ ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጣ በመረዳት፤ የፖለቲካ ችግር መፍትሔ የሚያገኘው በውይይት ነውና የውይይት መድረክ ይዘጋጅ የሚል ሃሳብ ሲያቀርብ፤ አንወያይም ውኔህን አሳውቀን የሚል ምላሽ ነው ያገኘው። በዚህም ኮሚሽኑ የገንዘብ ቅጣትን ጨምሮ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎችና የተቀጡትን ሰዎች ገለጸ። ነገሩን ይበልጥ አከረረው፤ መጠላላቱን አከፋው እንጂ መፍትሔ አልሆነም።

5. ምርጫ 2007፤

ሰማያዊ ለምርጫ 2007 ዝግጅት እንዳልነበረው ያቀረባቸው እጩዎች አብዛኛዎቹ ከአንድነት የገቡ መሆናቸው ብቻውን በቂ ማረጋገጫ ነው። ለምን አልተዘጋጀም፣ ሳይዘጋጅስ ለምን ምርጫ ገባ፤ በደል ደረሰበኝ እያለ እስከ መጨረሻው በምርጫው ለምን ቀጠለ፤ ከምርጫው ምን አተረፈ፤ … ወዘተ ለሚሉ ጥያቄዎች አመራሮቹ ሳይቀሩ በቂ ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም። ይህ ለህዝብ ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ ለአባላቱና ለአመራሩ ጭምር ግልጽ ካልሆነ የበሽታ እንጂ የሌላ ምልክት ሊሆን አይችልም።

6. ጠቅላላ ጉባዔ፤

እነዚህና ሌሎች የበሽታ ምልክቶች በግልጽ እየታዩ ባለበት ወቅት የተጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ተሰብስቦ ተበተነ ከማለት ያለፈ ተግባር ሊያከናውን አለመቻሉ፤ የሰማያዊ በሽታ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ቢሆንም፤ በተለይ አመራሩ በሽታውን ለማግኘትና መድኃኒት ለመፈለግ ፍላጎትም ዝግጅትም እንደሌለው ያሳየ ነበር።

የሥነ ሥርዓት ኮሚቴም ሆነ የቁጥጥር ኮሜቴ ውሳኔ የበሽታውን ምንነትን የደረሰበትን ደረጃ ለማወቅ አያስችልም። በዚህ ሁኔታ ጠቅላላ ጉባዔ ቢጠራም መድኃኒት አይሆንም። እኔ ግን እላቸዋለሁ ደፈር በሉና ቀናነቱም ይኑራችሁና ከላይ ያነሳሁዋቸውንና ከዚህም የሚልቁትንና እናንተ የምታውቁዋቸውን ለበሽታ የዳረጉዋችሁን ምክንያቶች በቅጡ መርምሩ፤ ተነጋገሩ። ከዛም መድኃኒት ፈልጉ። ደረጃው ይለያይ እንደሆነ እንጂ በበሽታው ያልተለከፈ አይኖርምና፤ ሁላችሁም እንክብሉን ለመውሰድ ተዘጋጁ። በውስጥም በውጪም ያላችሁ አባላትም ሆናችሁ ደጋፊዎች፤ ጎራ ለይታቹሁ በሽተኞቹን ወደ መቃብር የሚገፋ ሆይ ሆይታችሁን አቁሙና በሽታቸውን እንዲያውቁ መድኃኒቱንም እየመረራቸውም ቢሆን እንዲውጡ ለማበረታታትም፤ ከቻላችሁ ለማስገደድም ትጉ። ይህ ካልሆነ የቻላችሁ በአካል፤ ያልቻላችሁ በማኅበራዊ ድረ-ገጽ ለቀብሩ ትገናኛላችሁ። እኔ ግን ፈጣሪ መልካሙን ለመስማት ያበቃን ዘንድ እመኛለሁ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ