በ“የለውጥ ሐዋርያ” የተወጠረ ሲቪል ሰርቪስ
ነፃነት ዘለቀ
የታያቸውን አላውቅም ከምን ጊዜውም በላይ ወያኔዎች ሰሞኑን ክፉኛ ተጨንቀዋል። እነሱና እኔ ከጥንት ጀምሮ የተለዬ “ዝምድና” ያለን በመሆናችን ነገረ ሥራቸውን በደንብ አውቀዋለሁ። ሲጨነቁና ሲጠበቡ እንዴት እንደሚሆኑና ምን እንደሚያደርጉ በረሃ ሳሉ ጀምሮ በሚገባ እንተዋወቃለን። ከዱሮው ለማጣቀስ ያህል አንዳች አደጋ አንጃቦባቸው ሲጨነቁ ትላልቅ ባለሥልጣኖቻቸውን በቃለ-መጠይቅ መልክ እያቀረቡ ምንም እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል ጀሌያቸውን ያጽናናሉ፤ ያበረታታሉ።
በእስካሁኑ ሁኔታ ያ ዓይነቱ ነገር አልተሳካላቸውም አልልም - ከአሁን ወዲያ ስላለው ግን በእውነቱ እምብዛም አላውቅም። እንደኔ ምኞትና ፍላጎት ከሆነ ግና ፀሐያቸው በጣሙን ጠቋቁራ ትታያለችና ደንቃራና ትብታባቸው ሊሽር ዳር ዳር እያለ ይመስለኛል። እውነቱን ደግሞ አንድዬ ይበልጥ ያውቀዋል - ሊያውም ከነሰከንድና ደቂቃዋ ጭምር።
እንደወያኔዎች ሁሉ ብዙ እንስሳት ከሌሎች መሰሎቻቸው ተለይተው የሚታወቁባቸው ባሕርያት አሏቸው። ለአብነት የሩቅ ምስራቋ ፓንዳ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊከሰት ሲል አስቀድማ የምታውቅበት ተፈጥሯዊ ችሎታ እንዳላት ቻይናውያኑ ይናገራሉ። ሁላችን በደንብ የምናውቃት አህያ እንኳን ባቅሟ ከባድ ዝናብ ወደሚጥልበት አቅጣጫ ሲነዷት ጆሮዎቿን ቀስራ ትቆማለች እንጂ አትንቀሳቀስም። የአጤ ኃ/ሥላሴን የደብረ ዘይት ጉብኝት ያስታውሷል።
ብዙዎቹ የሌሊት እንስሳት (nocturnal animals) ብዙ የሚደንቁ ወያኔያዊ ጠባዮች እንዳላቸውም እናውቃለን። ጅብና የሌሊት ወፍ አንድን ነገር በርቀት ከማየት አኳያ የሚስተካከላቸው የለም። ሰሞኑን በሰማሁት መረጃ ገብረ ጉንዳን ለጥቂት በለጠው እንጂ ውሻን በማሽተት ተፈጥሯዊ ችሎታው አንድም የሚደርስበት ፍጡር እንዳልነበር ይነገር ነበር። በባሕርዩ ከወያኔ በእጅጉ የሚመሳሰለው አያ ጅቦም እንዲሁ ከሩቅ በማሽተት አይታማም። በሆዳምነቱ ከወያኔ የማይተናነሰው አሳማም በእምብርት የለሽነቱ ይታወቃል። …
ወያኔ ምንም እንኳን እብሪተኛና ጥጋበኛ ቢሆንና አንዳችም የሚጨነቅበት ነገር ያለው ባይመስለንም (ለብዙዎቻችን) እውነቱ ግን ከዚህ ተቃራኒ መሆኑን፤ በተለይ በሰሞነኛ ድርጊቶቹ በሚገባ መረዳት ይቻላል። እንደተጠቃቀሱት እንስሳት ወያኔም ስለጭንቀት ጥበቱ የምናውቅበት ዘዴ አላጣንም። እናም አሁን ክፉኛ ወያኔዎች ተጨንቀዋል። አለመግቢያ ነገር አይጣፍጥም።
ደርግ የውይይት ክበብ የሚባል በየ15 ቀን በመንግሥት ሠራተኞች የሚካሄድ የንቃተ ኅሊና ማሳደጊያ ስብሰባ ነበር። ያን ስብሰባ መካፈል የሁሉም ግዴታ ነበረ፤ ወደድክ አልወደድክ ያንተ ጣጣ ነው። አለመካፈል ደግሞ በፀረ ሽብርተኝነት ማለቴ በፀረ አብዮተኝነት እያስፈረጀ ለአሣር ይዳርጋል። የሚገርመው ደግሞ ከጽዳትና ዘበኛ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ዶክተርና ፕሮፌሠር አንድ ቦታ ላይ እንደእህል ተከማችቶ በአንድ አብዮታዊ ጉዳይ ላይ መወያየት ነበር ዋናው የስብሰባው ተግባር። የመናገር ሱስ ያለበት ደመ ሞቃት ሰው ቀኑን ሙሉ ሲደሰኩር ሌላውና አብዛኛው ግን እያፋሸገ በድብቅ እንቅልፉን ይደቃል። ውይይቶቹ ባብዛኛው ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ዓይነት ነበሩ። ይታያችሁ - በዕውቀትና በንቃተ ኅሊና የተለያዩ ሰዎች እንዴት በአንድ መድረክ ሊያውም በአንድ ደደብ ካድሬ አመራር ሥር እንዲወያዩ ይደረጋል? ደርግ ደንቆሮ፣ ወያኔ ደግሞ የባሰበት ደደብና ደንቆሮ። የመንግሥት ሠራተኛ በተለይ የደንቆሮዎች መሞላፈጫ ሆኖ መቅረቱ ያሳዝናል። ሁሌም ቅል ድንጋን እየሰበረ የሚኖርባት - ኢትዮጵያ።
ያ የደርግ የማይምነት ሥራ ተረት ተረት ሆነ ብለን ደስታችንን ከማጣጣማችን ምንም ሳንቆይ በኩረጃ ከዓለም አንደኛ የሆነው ወያኔ ያችን ውይይት መልሶ ሥራ ላይ አዋላትና አሁን ወገኖቻችን በመሰቃየት ላይ ናቸው። የመንግሥት ሠራተኞች በእውነቱ እቶን ላይ ተጥደዋል። እኔስ እግዜር መርቆኝ ተገላግያለሁ። አሁን እንዲህ እየሆነ ነው፡-
ወያኔ የለውጥ ሐዋርያ (የውይይት ክበብ የሚለውን የደርግን ስያሜ ላለመጠቀም ፈልገው ይመስላል) በሚል የስብሰባ የክተት ዘመቻ ሁሉንም የመንግሥት ሠራተኞች በየመሥሪያ ቤታቸው በየ15 ቀን አንዴ እንዲወያዩ ትዕዛዝ ካወረደ ቆይቷል። ያ በ15 ቀን አንዴ ይካሄድ የነበረው ውኃ ወቀጣ ሰልችቷቸው ይጨነቁ በነበረበት ሁኔታ ላይ እንዳሉ 15 ቀኑ ረዘመ ተብሎ በሣምንት አንዴ ውይይቱ እንዲካሄድ ሌላ ትዕዛዝ ይወርዳል። በዚያ እየተንገሸገሹ ሳለ - “የበላችው ያስገሳታል፣ በላይ በላዩ ያጎርሳታል” እንዲሉ - በዚህ ሣምንት ውስጥ ደግሞ ይሄው የለውጥ ሐዋርያ ተብዬው ዜጎችን ማደንቆሪያ የሠራተኞች ስብሰባ በየቀኑ እንዲካሄድ ከበላይ ተወስኖ መመሪያው ወርዷል - ይቺ “መውረድ” የምትል የወያኔ ቃል ስትጥም! መዓት ይውረድባቸውና እንዴት ነው የሚወርደው? የንቀታቸውን ገደብ የለሽነት ከምናይባቸው በርካታ የቃላት አጠቃቀሞቹ አንዱ ይህ “ወረደ” የሚሉት ቃል ነው። ደንቆሮ ሆነው እንጂ ከአንድ ጠባብ የጅቦች ቡድን ወደ ትልቅ ህዝብ አሻቅቦ ሊወርድ የሚገባ ምንም ነገር ሊኖር ባልተገባ ነበር። ሊወርድላቸው የሚገባው ለነሱ ነበር። ግን ቀን የሰጠው ቅል ሆነና ነገሩ ተቸገርን። በቋንቋም ሳይቀር እየተራቀቁብን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው ሁኔታው - እንደሁኔታና እንዳካሄድ።
እናላችሁ ምድረ ምሁር ተጨንቋል እላችኋለሁ - አሁን። በአንድ የመንግሥት ከፍተኛ ተቋም የሚሠራ ጓደኛየ ትናንት ምሽት ይህን መረጃ እንደዋዛ ሲነግረኝ የታየኝ ነገር ወያኔ እጅግ የተጨነቀ መሆኑ ነው። ይሄው ወዳጄ እንደነገረኝ ከሆነ ትዕዛዙ ከላይ እንደወረደና (ለነብዩ መሐመድ ከሰማይ ወረደ እንደተባለው የቅዱስ ቁርዓን ኪታብ መሆኑ ነው)፤ ማንኛውም የመንግሥት ተቋም ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ጥብቅ መመሪያ “ወርዷል” ማለቴ ተላልፏል። የጓደኛዬ መሥሪያ ቤት (የተቋሙ ፕሬዝዳንት) ለመምህራንና ሠራተኞቹ ባስተላለፈው ቀጭን ትዕዛዝ “የለውጥ ሐዋርያ ስብሰባው በየቀኑ መካሄድ እንዳለበት መመሪያ ወርዷል። መነጋገሪያ አጀንዳ ከሌላችሁ እኔ ራሴ እሰጣችኋለሁ” እንዳላቸውም አልደበቀኝም። “ወይ መዓልቲ” አለ ትግሬ!
እናም ወያኔዎች “ተጨንቀዋል” ነው የምላችሁ ባጭሩ። ምንና ከየትኛው አቅጣጫ ሲመጣባቸው እየታያቸው እንደሆነ አላውቅም - ፓንዳን መሆን ያስፈልጋል ያን ለማወቅ። እያስበረገጋቸው ያለ አንዳች ነገር መኖሩ ግን በግልጽ ይታያል። ሲጨነቁ ደግሞ ምንም ነገር ከማድረግ አይመለሱም። ባህር ላይ እየሰመጠ ያለ ሰው የሚያድነው እየመሰለው ዐረፋውንም የሚንሣፈፈውን ገለባና የፊላ ቅጠሉንም ይጨብጣል። ግን የቀን ጉዳይ ነውና አይድንም። ቀንን የሚያልፍ የለም። እስከ ቀኒቷ ድረስ ማንም ያሻውን ያደርጋል።
እንደኔ ግና ያሻውን ባያደርግ ይሻለው ነበር። ምክንያቱም ቀኒቷን ያከፋበታል እንጂ በጭራሽ አይጠቀምም። ብልኅ ሰው ቀን የሰጠችውን መልካም ዕድል በአግባቡ ይጠቀማል። መፃኢ ዕድሉም ለራሱና ለተተኪ ትውልዶቹ ያማረ ይሆናል። ወያኔዎች ግን ግብዞችና ልበ ሥውራን ሆኑና በታሪክ ረዥም ዘመን ውስጥ ከስንት አንዴ የምትገኝን ጠባብ ዕድል አጓጉል አድርገው አበለሻሽዋት። ለዚህ ነው ሟቹ ዐማራ አጎቴ “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ፣ አሁን ምን ያደርጋል ወጪት ጥዶ ማልቀስ” ይል የነበረው። ትግሬዋ አክስቴም ለተረት ቀላል አልነበረችም - “ዝአኽለን ጥህነን በዓል ማርያም ትብላ” ትል ነበር። “የሚበቃትን ያህል ከፈጨች በኋላ “ውይ ለካንስ ዛሬ ማርያም ናት” እንደማለት ነው።
ወያኔዎች ላለፉት 17 ሲደመር 25 ዓመታት ሰይጣናዊ ፈረሳቸው ያዘዛቸውን ሁሉ በመከወን እንደፈለጉ ሲፈነጩብን ከሰነበቱ በኋላ አሁን ከረፈደ ተነስተው በለውጥ ሐዋርያም ይሁን በሌላ መንገድ ሊያባብሉንና ሊሰብኩን ቢቃጡ የድፍረታቸውን መጠን መጨመራቸውን ከመረዳት ውጪ የሚራራላቸው አንድም ኢትዮጵያዊ ይኖራል ተብሎ አይገመትም። ሁሉም ተንገሽግሸዋል። የኛ ነው የሚሉት ሳይቀር የነሱ አይደለም። አንድም የመንግሥት ሠራተኛ ከነሱ ጋር እንደሌለ እንኳን እኛ እነሱም አሣምረው ያውቃሉ። አማራጭ በማጣት እንጂ “በመጪው ዘመን ብዙ የምጠየቅበት ነገር አለኝ” ብሎ ከአሁኑ የሚፈራው ሌባና ሙሰኛ ዜጋም ሣይቀር ልቡ ሸፍቷል - ይህን በደንብ እናውቃለን።
ብቻ በተቃውሞው ጎራ መሠራት ያለበት ሥራ ይሠራ። የበቀልና የጥላቻ አዙሪት ተወግዶ ሁሉም በፍትህ የሚዳኝበት የሽግግር ዘመን ይመቻች። መርከቧ ክፉኛ እየተናጠች ነው። ወያኔዎች በክፋታቸው ብዛት ወደጭራቅነት በመለወጣቸው የሚደፍር ጠፍቶ እንጂ ሀገሪቱ ባዶ ናት - አስተዳዳሪ የላትም። ማንም እንደፈለገ የሚፈነጭባት ሆናለች። እነሱ ደግሞ ሥልጣን እንኩላችሁ ብለው ለማንም አያስረክቡም - ልረከብ ብሎ የሚደፍር እንኳን ቢኖር ማለቴ ነው። ወኔያችንን ሰልበውታል። ደርግ ያመቻቸላቸውን የወኔ ድርቀት በመጠቀም ወያኔዎች ድራሻችንን አጠፉን። ግን ቀን ቀንን እንደሚወልድ፣ ጀግናም ከፈሪ ማሕጸን እንደሚጸነስ፤ ሁሉ ነገር ባለበት አይቆይምና ወላድ በድባብ ትሂድ በቅርቡ ተዓምር ሲኸለቅ እናያለን - እኔ እየታየኝ መጽናናት ይዣለሁ።
ስለዚህ ዜጎች ተደራጁ - ማለትም እንደራጅ። እንደእስካሁኑ ዘምቦለል ሆነን አንቅር። ለማስመሰል እንኳን ብዙ አስርት ዓመታትን በሚወስደው የወያኔ ቁጭ በሉ ዴሞክራሲ ለውጥ እንደማይመጣ ግልጽ ነው። በወያኔዎች እንቶ ፈንቶ የዴሞክራሲ ልግጫ የኢትዮጵያ ኅልውና አይረጋገጥም። ለውጥ የሚመጣው በጉልበት ነው። በጣም በትንሽ ግን ጥበብ በተሞላበት ጉልበት። ወያኔዎች ለነሱም እጅግ በሚገርም ሁኔታ ካሰቡት በላይ ለብዙ ጊዜ ሥልጣን ላይ ቆይተዋል። የመቆያ ጥበባቸው እርግጥ ነው ወደር የለሽ ጭካኔያቸው ነው። እንፈራለን። ፈሪ አድርገውናል። እባብን ያዬ በልጥ እንደሚበረይ ሁሉ፤ እኛም የአራት ኪሎን ቤተ መንግሥት እንደቄራ እናየዋለን - እውነታችንንም ነው። ስንቶች የተቀሉበትን ቤተ መንግሥት፣ ስንቶች አንገታቸው እንዲሠየፍ ትዕዛዝ የተላለፈበትን የአጋንንት ምሽግ የሆነውን ቤተ መንግሥት ብንፈራና በወሬ ብቻ የተስፋ ዳቦ እየገመጥን ብንኖር አይፈረድብንም - እርግጥ ነው የመፍራታችን ውጤት የሆነውን የባርነት ሕይወትም ተቀብለን እየኖርን ነው። በወደዱት ይቆርቧል። የነፃነታችንን ምጥ እኛም በያቅማችን እናግዝና ትወለድ። ከሰው ብቻ አንጠብቅ። “እኔስ ምን አደረግሁ?” ብለንም ራሳችንን እንጠይቅ።
አታሞ በሰው እጅ ታምራለች። የነፃነት ትግል ሲይዟት ታደናግራለች። ስለሆነም ከኅሊናችን እንሁንና በሂደቱ እንግባበት። ከፖለቲካው ዐውድ መሸሻችን ለከፋ የኅሊና፣ የመንፈስና የአካል መራቆት ዳረገን እንጂ አልጠቀመንም። በዚህ ከቀጠልን ደግሞ ከዚህም የባሰ ይመጣብናል። ከወያኔ የከፉ ጭራቆች ለወደፊቱ እንዳይመጡብን ዋስትናው የሁላችንም ያልተቆጠበ ተሣትፎ ነው። በዚያ ላይ ማንበብ፣ ማንበብ፣ ማንበብና በቀናነት ተነጋግሮ በውይይት መግባባት ወሳኝ መሆኑን እንወቅ። ዘርና ኃይማኖትን እንርሳቸው። በዘርና በኃይማኖት መቧደን የጠፋ እንጂ የለማ ሀገር የለም - ሊኖርም አይችልም። … ወደመዘምዘሚያየ እያመራሁ ነው።
… የገንዘብ ነገር ግና እየገረመኝ ነው። ዱሮ አንድ ሺህ ብር ሲባል ያስደነግጥ ነበር። አሁን ቢሊዮን ሲባልም ማስደንገጡ እየቀረ ነው።
በትናንት ማታ አንድ ስብሰባ ላይ መንግሥት ተብዬው የወያኔ ጭፍራ በአዲስ አበባ ለመንግሥት ሠራተኞች መጓጓዥያ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ 120 ሚሊዮን ብር ማውጣቱን ድሪባ የተባለ የህወሓት ጭምብል በአንድ በብሶት የተሞላ ስብሰባ ላይ ሲናገር ሰማሁ። ይሄ ሚሊዮን የሚሉት ከሰው ስም ውጪ ሲሰሙት የሚያስደነግጥ ነገር ገረመኝ። መኪኖቹን ለመግዛት ነው ወይንስ ለማጓጓዝ ብቻ ይህ ሁሉ ገንዘብ የወጣው?
ወያኔዎች በ200 ሚሊዮን ብር ታሪካቸውን ለማጻፍ የዘረፋ እንቅስቀሴ መጀመራቸውን ከአቶ አስገደ ጽሑፍ ተረድተናል። ይህ ሁሉ ገንዘብ በርግጥ አስፈልጎ ነው ወይንስ ውሻ በቀደደው ጅብ እንደሚገባ በሰበቡ ወያኔዎቹ እንደለመዱትና በሚገባ እንደተካኑበት ገንዘብ ሊያጋብሱ ነው? እነዚህ ሰዎች እምብርት የሚባል ነገር እንደሌላቸው አውቃለሁ፤ በ25 ዓመታት ውስጥ የማይሶብር የረሃብ ስሜት በስንት ዓመት ይረካ ይሆን ግን? ምን ዓይነት ተፈጥሮ ነው? ገድለው የማይረኩ ወያኔዎች ብቻ ናቸው። አስረውና አሰቃይተው የማይረኩ ወያኔዎች ብቻ ናቸው። በልተውና ጠጥተው የማይረኩ ወያኔዎች ብቻ ናቸው። ዘርፈውና መዝብረው የማይረኩ ወያኔዎች ብቻ ናቸው። ደድበውና ጀዝበው የማያበቁ ወያኔዎች ብቻ ናቸው። ምን ይሻላቸው ይሆን? እኛስ ምን ይሻለን? አሻ!
አንድ ሚሊዮን የሚፈጅ አነስተኛ የመንገድ ፕሮጀክት በ20 ሚሊዮን ይወራረዳል፤ ሁለት ሚሊዮን የሚፈጅ የጤና ጣቢያ ግንባታ በ25 ሚሊዮን ይወራረዳል፤ ሦስት ሚሊዮን የማይፈጅ ትምህርት ቤት በ30 ሚሊዮን ይወራረዳል፤ አራት ሚሊዮን የሚፈጅ የጦርነት መገልገያ መሣሪያ በ35 ሚሊዮን ይወራረዳል፤ አምስት ሚሊዮን የሚፈጅ … በ40 ሚሊዮን ይወራረዳል - ለዚያውም ጥራትን በከፍተኛ ደረጃ ተደራድረውበት አፈር ድሜ አብልተውት። ሀገርና ህዝብ ተሟጠው ከወጡበት አዕምሮ ከዚህ ሌላ ምን ደግ ነገር ይጠበቃል? ለእኔ እንጂ ለእኛ የሚል የጋራ ስሜት ከነጠፈባት ምድር ምን መልካም ነገር ይገኛል? ...
እግዚአብሔር ሆይ! - ስማን! ፊትህን ወደኢትዮጵያ መልስ! ጨርሰን ከመጥፋታችን በፊት እነዚህን መዥገሮችና ነቀዞች ከላያችን ላይ አንስተህ በፍቅርና በአንድነት መንፈስ የሚያስተዳድሩንን ያንተን ልጆች ስጠን! እንደነዚህ ያሉ የሚያቃቅሩና የሚያጨራርሱ የሰይጣን ሽንቶችን በአፋጣኝ አስወግደህ ርህራሄና ሰብዓዊነትን የተላበሱ መልካም እረኞችን ላክልን - የሚሳንህ ነገር የለምና። የጠፉብንን ደጋግ ኃይማኖታዊ እሴቶችንና ኃይማኖታዊ አባቶችን መልስን። የኃይማኖት መስመራቸውን ስተው፤ ከሰይጣናት ጋር ያበሩ የዲያብሎስ አገልጋይ የሆኑ ጳጳሳትንና ሼኮችን አንስተህ በምትካቸው አንተን የሚፈሩ፣ ህዝባቸውን የሚያከብሩና የሚያፈቅሩ መልካም እረኞችን አንተው ሹምልን። እስካሁን የሆንነውና የደረሰብን ይብቃን! አሁንስ ጌታ ሆይ ማረን! - አሜን!!!
ነፃነት ዘለቀ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.