ወያኔ ያልፋል፣ ጠንቁ ለትውልድ ይተርፋል
ይገረም አለሙ
ዘለዓለማዊ የሚሆን ምድራዊ ኃይል የለም። የግዜ እንጂ የሰው ጀግናም የለም። በመሆኑም አንድ ቀን በወያኔ ላይ ፀሐይ ልትጠልቅበትና ከመኖር ወደ አለመኖር ሊሸጋገር፤ አለያም እንደ ዛሬው ከፊሉን በሆድ ገዝቶ፣ ከፊሉን ሥነ-ልቦናውን ሰልቦ፣ ወዘተ በአሽከርነት ያሰለፈበትን፤ ብዙኃኑን ደግሞ በጠመንጃ አፍኖ ለመግዛት የበቃበትን አቅም አጥቶ የእጁን የሚያገኝበት ግዜ የዘገይ እንደሁ እንጂ መምጣቱ አይቀሬ ነው። ዘላለማዊነት የለምና።
ከጫካ ጀምሮ በኢትዮጵያውያን እንደማይወደድ ያወቀው ወያኔ ትግረኛ ተናጋሪውን ኢትዮጵያዊ መጠጊያ መከታ ለማድረግ ራሱን የትግራይ ነጻ አውጪ ብሎ ከመሰየም አልፎ፤ ይህ የሕብረተሰብ ክፍል በሌላው ኢትዮጵያዊ በጥላቻ እንዲታይና እርሱም ሌሎቹን እንዲጠላና ከርሱ ጋር እንዲጣበቅ ለማድረግ ብዙ ብዙ ሠርቷል። ከሌላው የሀገሪቱ ክፍል እየዘረፉ ወደ ትግራይ ማጋዙ፤ ከክልል አቅም በላይ የሆኑ ግንባታዎች መካሄዳቸው ወዘተ በሌለው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ትግሬ የሥርዓቱ ተጠቃሚ ነው የሚል አስተሳሰብ እንዲጎለብትና ጥላቻ እንዲያድርበት የማድረግ እኩይ ዓላማ ውጤቶች ናቸው።
በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጸመው ግድያ፣ እስራት፣ ከቤት ንብረት ማፈናቀል፣ ለሰላማዊ ተቃውሞአቸው የጥይት ምላሽ መስጠት፤ በተለይ ደግሞ በዘር ላይ የተመሰረተ ግፍ መፈጸምም እንዲሁ ሌላው ኢትዮጵያዊ በትግራይ ወገኖቹ ላይ ጥላቻ እንዲያድርበት ለማድረግ የሚሠራ እኩይ ተግባር ነው። ዋናው ዓላማ በሌሎች ሲጠሉ እነርሱም ሁሉንም እንዲጠሉና ከወያኔ ጋር እንዲጣበቁ ማድረግ ነው።
ያለምንም ወንጀል የታሰሩ ዜጎች አማራነታችን እየተነገረን በትግረኛ ተናጋሪ መርማሪዎች ተፈጸመብን በማለት የሚናገሩት ሊሰሙት እንኳን የሚዘገንን አረመኔያዊ ድርጊት በአማራና ትግሬ መካከል ስር የሰደደ ጠላትነት እንዲፈጠር ለማድረግ ከመፈለግ ውጪ ሌላ ምክንያት ሊሰጠው የሚችል አይደለም። ይህ ከትግረኛ ተናጋሪ ውጪ ባሉት ኢትዮጵውያን ላይ ሁሉ በተለያየ ስልትና መንገድ የሚፈጸመው ኢ-ሰብዓዊና ሕገ-ወጥ ተግባር ከትግረኛ ተናጋሪው ወገን ተቃውሞ የማይገጥመው መሆኑ ደግሞ ትግሬና ወያኔ አንድ ናቸው የሚለው አስተሳብ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝና ጥላቻውን ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር እንዳያደርገው ያሰጋል።
በመሆኑም ወያኔ በእነርሱ ስም ተደራጅቶ እነርሱን ጋሻና መከታ አድርጎ በሌሎች ወገኖቻቸው ላይ የሚፈጽመውን አረመኔያዊ ተግባር ሁሉም ትግረኛ ተናጋሪ በአንድ አብሮና ተባብሮ መቃወም እንደማይችል ቢታወቅም፤ የትግራይ ሽማግሌዎችና ምሁራን ደም አታቃቡን ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦንብ ለልጆቻችን አትቅበሩብን በማለት ወያኔዎችን ሊመክሩ፣ ከጥፋት ጉዞአቸውም ሊገቱዋቸው ይገባል።
የወያኔዎችን ታሪክ በቅርብ የሚያውቁ እንደተናገሩትና እንደጻፉት፤ ወያኔዎች በትግራይ ስም የተደራጁ ሰዎችን ሳይቀር በገፍና በግፍ እየገደሉ፣ ከራሳቸውም ድርጅት በሃሳብ የተለዩትን በተለያየ ስልትና መንገድ እያስወገዱ ነው ለሥልጣን የበቁት። በሥልጣን ቆይታቸው ደግሞ አንድም ወንበራቸውን ላለማስነካት፣ ሁለትም የሀገሪቱን ሀብት ያለምንም ከልካይ ለመዝረፍ ሲሉ፤ ተቀዋሚያቸውንም፣ የአባልና አጋር ድርጅቶች አባላትንም፣ የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸውን ዜጎችንም ወዘተ አጥፍተዋል። በመሆኑም ስለ እርቅ ሲጠየቁ፣ እንነጋገር ሲባሉ፣ በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው የፈጸሙት ወንጀል ሁሉ እየታሰባቸው ከሥልጣናቸው ሲወርዱና ፍትህ አደባባይ ሲቆሙ እየታያቸው፤ ውይይትን ሳይሆን ጉልበትን፣ ሕግን ሳይሆን ጠመንጃን ምርጫቸው አድርገው በጥፋት ላይ ጥፋት እየፈጸሙ፤ ነገሩን ሁሉ ከሮ ወደሚበጠስበት ደረጃ እየገፉት ነው። ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ እንዳይበጠስ መጣሩ ነው የሚበጀው።
የትግራይ ሽማግሌዎችና ምሁራን ሀገር ቤት ያሉት ባይችሉ፤ በውጪ የሚገኙት ተዉ ይህ አድራጎታችሁ አይበጅም ለእናንተም ልጆቻችሁና ለልጆቻችንም አይጠቅምም በማለት ድምጻቸውን ማሰማት ባለመቻላቸው የደደቢት ወያኔዎች ሁሉ ትግሬ ቢሆኑም ትግሬ ሁሉ ወያኔ አይደለም በማለት ሽንጣችንን ገትረን ለዓመታት ያካሄድነውን ትግል ወደ ሽንፈት እየወሰደው ነው።
ኢትዮጵያውያን ለሚያሰሙት ተቃውሞም ሆነ ለሚለግሱት ምክር ከወያኔ የሚሰጠው ምላሽ የጸረ ሰላም ኃይሎች፣ የጠባቦች፣ የትምክህተኞች፣ የኤርትራ ተላላኪዎች ወዘተ የሚል በመሆኑ የወያኔ እኩይ ድርጊት ለትውልድ የሚተላለፍ ነቅርሳ ተክሎ እንዳያልፍም ሆነ ትግሬና ወያኔ አንድ አይደሉም የሚለው አስተሳሰብ ተቀባይነት እንዲያገኝ የማድረጉ አቅም እየተሟጠጠ ነው።
የቀረው አንድና የመጨረሻ ዕድል በትግራይ ተወላጆች እጅ ነው ያለው። ደም አታቃቡን ቂም አታውርሱን ማለትና ልጆቻቸውን ከቻሉ ከጥፋቱ መንገድ መመለስ፤ ካልቻሉ አውግዘው ድጋፋቸውን መንሳትና እኛም የእናንተ አይደለንም፤ እናንተም የእኛ አይደላችሁም በማለት፤ ዛሬ በወያኔ አገዛዝ ውስጥም ሆነ ነገ ከወያኔ ሥርዓተ መንግሥት ህልፈት በኋላ ልጆቻቸውና ልጆቻችን በሰላምና በፍቅር የሚኖሩበትን ሁኔታ ከወዲሁ ለመፍጠር መጣር ይኖርባቸዋል። ምንግዜም ቢሆን ያልዘሩትን ማጨድ አይቻልምና፤ የትግራይ ወገኖቻችን ቢዘገይም ጨርሶ ሳይጨልም ለነገ ለልጆቻችን የሚበጀውን መልካሙን ዘር ለመዝራት ነገ ሳይሆን ዛሬ ተነሱ!