አሃዳዊም ፌዴራላዊም ያልሆነው የወያኔ ሥርዓት
ይገረም አለሙ
ስለ አሃዳዊና ፌዴረላዊ ሥርዓት ምንነትና እንዴትነት በአጭሩና በጥቅሉ የመጀመሪያው ሥልጣን የተማከለበት ሁለተኛው ሥልጣን የተከፋፈለበት ብሎ መግለጽ ይቻላል። ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው ግን ሁለቱንም ያልሆነ ሥርዓት ነው። በወያኔ የትግል ብስራት ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የተጎናጸፉበትን ፌዴራላዊ ሥርዓት ለማግኘት በቅተዋል ተብሎ ቢነገረንም መሬት ላይ የሚታየው እውነታ ግን ይህን አያሳያም።
በሕገ መንግሥቱ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ሥርዓት ፌዴራላዊ መሆኑ ተጽፏል፤ የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ሥልጣንና ተግባር ተዘርዝሮ ተመስርተዋል፤ የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ ብሔር ጠቅላይ ምኒስትሩ የክልል መንግሥታት ርዕሰ ብሔሮች ደግሞ የክልሎቹ ፕሬዝዳንቶች መሆናቸው ተገልጹዋል። ነገር ግን ለሀያ አምስት ዓመታት በተግባር የታየውና አሁንም እየሆነ ያለው ህወሓት ከማዕከል እስከ ቀበሌ በተዘረጋ የዕዝ ሰንሰለት ሀገሪቱን እየገዛ መሆኑ ነው። በዚህ ብቻ አያበቃም ቁልፍ የሆኑ መስሪያ ቤቶች፣ መከላከያ ፖሊስና ደህንነት ወዘተ የሚመሩት በህወሓት ነው። ሌሎች ኢትዮጵውያን በኃላፊነት የተሸሙባቸው መስሪያ ቤቶችም ቢሆኑ የሚመሩት በስም ከእነርሱ በታች፣ በሥልጣን ግን ከእነርሱ በላይ በሆኑ የህወሓት ሰዎች መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ይም በመሆኑ ሥርዓቱ ፌዴራላዊ ሊባል አይችልም።
አሃዳዊ ነው እንዳይባል ደግሞ። አንድ ወጥ የሆነ የተማከለ ማዕከላዊ መንግሥት አይደለም ያለው። ትግራይ ላይ የነገሰው ህወሓት በማዕከላዊው መንግሥት ዕዝ ስር አይደለም፣ እንደውም በተቃራኒው ማዕከላዊ መንግሥቱን የሚያዝና የሚቆጣጠረው የትግራዩ መንግሥት ነው። ይህም ብቻ አይደለም ሁሉንም ክልሎች በሚታየውም በማይታየውም እጁ የሚቆጣጣረው እሱ ነው። የክልል ባለሥልጣኖች ስሙ እንጂ ሥልጣኑ የላቸውም። ሌላው ቀርቶ የክልል ባለሥልጣናት የሚሾሙ የሚሻሩት በትግራዩ መንግሥት ፍላጎትና ቀጥተኛ ትዕዛዝ መሆኑ የሚያከራክር አይመስለኝም። ስለሆነም ሥርዓቱን አሃዳዊ ነው ማለትም አይቻልም።
ይህን ደግሞ ብዙ ወደ ኋላ መሄድ ሳያስፈልግ በቅርብ ግዜያት ከተፈጸሙ ድርጊቶች ጥቂት ግን የማያወላዱ ማስረጃዎችን በማቅረብ ማሳየት ይቻላል።
1. የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣንና ተግባር የሚገልጸው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51 ን.አ 14 “ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድሩ ጥያቄ ሲቀርብለት መከላከያ ኃይል ያሰማራል” ቢልም በተግባር የሚታየው ግን ይህን የሚያሟላ አይደለም። በቅርቡ በኦሮምያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማፈን ተሰማርቶ ዜጎችን የገደለው የደበደበውና ያሰረው ከዚህም አልፎ የሲቪል አስተዳደሩን አግልሎ ወታደራዊ አገዛዝ የመሰረተው ሠራዊት ወደ ክልሉ ያገባው በክልሉ መንግሥት ጥያቄና በፌዴራል መንግሥቱ ውሳኔ ሳይሆን በጥቂት የህወሓት ሰዎች ትዕዛዝ ብቻ መሆኑን ለማረጋገጥ መሪ ተዋናይዮቹ እነማን እንደነበሩ መለስ ብሎ ማስታወስ በቂ ነው።
2. ወልቃይት መተዳደር ያለበት በአማራ ክልል እንጂ በትግራይ አይደለም በማለት በጉልበት የተነጠቁትን ማንነት በሕግ አናስመልሳለን ብለው፣ መንግሥት አለ ብለው፣ ፍትህ እናገኛለን ብለው፣ አቤቱታ ለማቅረብ ወደ ፌዴራል መንግሥት የተንሳቀሱ ሰዎች ኦሮምያ ክልል ውስጥ መታገታቸው የቅርብ ግዜ ዜና ነበር። የኦሮምያ ክልል መንግሥት ይህን እኩይ ሕገ ወጥ ተግባር ለመፈጸም የሚያበቃው ሕጋዊ ምክንያትም ሆነ የማንአለብኝነት ሰበብ የለውም። የፌዴራል መንግሥቱም ቢሆን እንዲሁ ይህን እንዲያደርግ የሚያበቃው ምክንያት የለም። በመሆኑም የድርጊቱ ፈጻሚ በጉልበት የወሰድክብንን በሕግ እናስመልሳለን የሚል ሙግት የገጠመው የትግራዩ መንግሥት ለመሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። ይህም የሚያሳየው ትግራይ ላይ የነገሰው ህወሓት ከክልሉ አልፎ የፌዴራሉን መንግሥትም ሆነ የኦሮምያ ክልልን ማዘዝ መቻሉ ነው። ማዘዝም ብቻ አይደለም ከልካይ የሌለው ገዢ መሆኑንም ያረጋገጠ ነው።
3. ሰሞኑን በጎንደር ለፈነዳውና የሕይወትና የንብረት ጉዳት ላደረሰው አስከፊ ድርጊት ምክንያት የሆነው የትግራዩ መንግሥት በሕጋዊ መንገድ እየሞገቱት ያሉትን ሰዎች ለማፈን ያደረገው ሙከራ ነው። ይህ የትግራዩ መንግሥት ርምጃ የአማራ ክልል መንግሥትን ሉዓላዊነት የተዳፈረ፤ ራሱን ከፌዴራል መንግሥትም በላይ መሆኑን ያሳየ ነው። ድምጽ ሳያሰማ ሞጋቾቹን የኮሚቴ አባላት አፍኖ ወደ ትግራይ ለመውሰድ ያደረገው ሙከራ ሲከሽፍና ሴራው ሲጋለጥ በአማራ ክልልና በፌዴራል መንግሥት ስም የተሰጡት መግለጫዎች የትግራዩን መንግሥት የሁሉም የበላይነት ያረጋገጡ ናቸው።
የአማራ ክልል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረው ነጻነትና ሥልጣን ያለውና የሀገሪቱም ሥርዓት ፌዴራላዊ ቢሆን ከእርሱ እውቅና ውጪ በክልሉ ውስጥ ስለተፈጸመው ሕገ ወጥ ድርጊት ተቃውሞ ሊያሰማ የትግራዩን መንግሥት ያሰማራቸውን አፋኝ ኃይሎችም በቁጥጥር ስር አውሎ ጉዳዩን ማጣራት መቻል ነበረበት። ነገር ግን የክልል መንግሥትነት ስሙ እንጂ ሥልጣኑ ስለሌለው ሉዓላዊነቱን ለጣሰውና በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ግድያና አፈና ለፈጸመው ኃይል ደጋፊና ተከራካሪ ሆነ።
የፌዴራል መንግሥት ተብየውም የአፈናው ፈጻሚዎች የፌዴራል ፖሊሶች እንደሆኑና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አውጥተው እንደሆነ በመግለጽ ሕገ ወጡን ድርጊት በሌላ ሕገ ወጥ ድጊት ለመሸፈን መሞከሩ በትግራዩ መንግሥት ስር ያለ ለመሆኑ አስረጂ ነው። በፌዴራል መንግሥት ስም በተሰጠው መግለጫ እንደተባለው በሕገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎች በአማራ ክልል መኖራቸው ከተረጋገጠ እነዚህን ሰዎች በሕግ ቁጥጥር ስር የማዋል ኃላፊነትም ሆነ ሥልጣን የክልሉ መንግሥት ነው። በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሰረት ፌዴራል መንግሥቱ በአማራ ክልል ኃይል ማሰማራት የሚችለው የሚገባውም የክልሉ መንግሥት አልቻልኩም አቃተኝ ብሎ ርዳታ ሲጠይቅ ነው። የትግራዩ መንግሥት በፌዴራል መንግሥት ካባው ባወጣው መግለጫ ግን የአማራ ክልል ጥያቄ ስለማቅረቡ አልገለጸም። የአማራ ክልል መንግሥትም ይህን አላሳወቀም።
እነዚህን መሰል ብዙ ማስረጃዎች ማቅረብ ቢቻልም መቀሌ ቤተ መንግሥት ያለው የክልል ትግራይ መንግሥትን የበላይነትን ለማሳየትና የሀገሪቱ ሥርዓት አሃዳዊም ፌዴራላዊም ሊሰኝ እንደማይችል ለማሳየት የቀረበው ማስረጃ በቂ ነው። ይህ ሁኔታ የትግራዩ መንግሥት መላዋን ኢትዮጵያ በመግዛት የደደቢት ህልሙን ተግባራዊ እያደረገ በሥልጣኑ እንዲቆይ አስችሎታልና ወደ ፊትም እንደሚቀጥልበት አያጠራጥርም። ካልተነቃበት በስውር የሚፈልገውን ሁሉ ያደርጋል። ሲነቃበት ደግሞ ድርጊቱን ወደ ክልሎች ወይንም ወደ ፌዴራል መንግሥቱ በማዞር ሲሻው ሰዎችን የጭዳ ዶሮ እያደረገ ሲሻው ጠቅላይ ምኒስትሩን ይቅርታ እያስጠየቀ ራሱን ነጻ አድርጎ ሴራውን ይሰራል።
የክልል መንግሥትነት ስም ይዘው ለትግራዩ መንግሥት አገልጋይ በመሆን ወገናቸውን እያፈጁ ያሉት እነ ብአዴን ኦህዴድ እስከ መቼ ነው በዚህ ሁኔታ የሚቀጥሉት። መቼ ነው እንደ ሰው ማሰብ የሚጀምሩት። ምን ቢሁኑ ምን ቢደረጉ ነው አሽከርነት በቃን የሚሉት። ትግሉ በእነርሱ ላይ ማተኮር ያለበት ይመስለኛል። ከገዳዩ አስገዳዩ ይከፋል፤
ሌላው ዜጋስ አሃዳዊ ይሁን ፌዴራላዊ በውል ያልታወቀ ሥርዓት ፈጥረው ጥቂት የደደቢት ሴረኞች በዙሪያቸው ያለውን በአሽከርነት አሰልፈው በየተራ የሚፈጽሙበትን ግድያ አስር እንግልትና መፈናቀል ወዘተ ችሎ የሚኖረው። አልፎ አልፎ ያውም በህዝቡ ፍላጎትና ዝግጅት ሳይሆን በወያኔ ተንኳሽነት የሚካሄዱት እንቅስቃሴዎች ያልተቀናጁና የአንድ ሰሞን መሆንም ወያኔን በደንብ አላወቅነውም የሚያሰኝ ነው። ይህ ደግሞ ውጤት አልባ መስዋዕትነት እየከፈለ ነው። በየግዜው በውጤት አልባ ትግል መስዋዕት የሆኑ ዜጎች ቁጥር የትየለሌ ነው። በቅርቡ አንኳን በኦሮምያ ብቻ ከአራት መቶ በላይ ወገኖቻችን መገደላቸውን ሰምተናል። በዚህ ሣምንት በጎንደር የሞቱት ገና በውል አልታወቁም።
ወያኔ በሕገ መንግሥት ላይ ፌዴራላዊ የሚል ስም ሰጥቶ በተግባር ግን አሃዳዊም ፌዴራላዊም ሊባል የማይችል ሥርዓት የፈጠረው መላ ኢትዮጵያን እየገዛ የደደቢት ህልሙን ከግብ ለማድረስ እንዲያስችለው ነው። እውነተኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት መላ ኢትዮጵያን ለመግዛት አያስችለውም። አሃዳዊ ሥርዓት ደግሞ በዓለም ዘንድ ተቀባይነት የለውምና በኢትዮጵያ ስም የሚያግበሰብሰውን ርዳታና ብድር አያስገኝለትም፣ እናም በተግባር ከሁለቱም ያልሆነ ሥርዓት እያራመደ እያጭበረበረና የሚሞኘውን እያሞኘ ቀጥሏል። እኛም በተራ በተራ ግፍና መከራውን እየተቀበልን ቀጥለናል። ግፍ አንገፍግፎን ጥቃት መሮን በአንድነት የማንነሳ ጉዶች።



